በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአዲሱ ጉባኤህ ጋር መላመድ የምትችለው እንዴት ነው?

ከአዲሱ ጉባኤህ ጋር መላመድ የምትችለው እንዴት ነው?

አለን “ወደዚህ መምጣት አስጨንቆኝ ነበር” ብሏል። * አክሎም “‘ጓደኞች ማፍራት እችል ይሆን? እነሱስ ይቀርቡኝ ይሆን?’ የሚለው ነገር አሳስቦኝ ነበር” ሲል ተናግሯል። አለን፣ ይኖርበት ከነበረው ቦታ ከ1,400 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ከሚገኘው አዲሱ ጉባኤው ጋር ለመላመድ ጥረት እያደረገ ያለ ወንድም ነው።

አንተም ወደ ሌላ ጉባኤ ተዛውረህ ከሆነ በተወሰነ ደረጃ ስጋት አድሮብህ ሊሆን ይችላል። ታዲያ ከጉባኤው ጋር ለመላመድ ምን ሊረዳህ ይችላል? ይህን ማድረጉ ከጠበቅከው በላይ ከባድ ከሆነብህ ምን ማድረግ ትችላለህ? በሌላ በኩል ደግሞ አንተ ወዳለህበት ጉባኤ የሚዛወሩ ክርስቲያኖች ጉባኤውን በቀላሉ እንዲለምዱት መርዳት የምትችለው እንዴት ነው?

ከጉባኤው ጋር መላመድና መዋሃድ የምትችለው እንዴት ነው?

አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ ዛፎች ከአንድ ቦታ ተነቅለው ሌላ ቦታ ላይ ሲተከሉ ለውጡን ለመልመድ ጊዜ ይወስድባቸዋል። ሰዎች አንድን ዛፍ ከነበረበት ቦታ ነቅለው ወደ ሌላ ቦታ ሲወስዱ፣ ለማጓጓዝ እንዲመቻቸው ሲሉ አብዛኞቹን ሥሮቹን ይቆርጧቸዋል። ዛፉ ሌላ ቦታ ላይ ከተተከለ በኋላ ወዲያውኑ አዳዲስ ሥሮችን ማብቀል ያስፈልገዋል። በተመሳሳይ አንተም ወደ ሌላ ጉባኤ መዛወርህ ያስከተለውን ለውጥ መልመድ ከብዶህ ሊሆን ይችላል። እንደ ዛፉ ሁሉ አንተም በቀድሞው ጉባኤህ ውስጥ “ሥር ሰደህ” ነበር፤ በሌላ አባባል የምትወዳቸው ጓደኞች አፍርተህ እንዲሁም በቋሚነት መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን የምታከናውንበት ፕሮግራም አዳብረህ ነበር። አሁን ደግሞ ከአዲሱ ጉባኤህ ጋር በደንብ ለመዋሃድ ልክ እንደ ዛፉ አዳዲስ ሥሮች ያስፈልጉሃል። ታዲያ እንዲህ ለማድረግ ምን ሊረዳህ ይችላል? ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎችን ተግባራዊ አድርግ። እስቲ አንዳንዶቹን እንመልከት።

የአምላክን ቃል አዘውትሮ የሚያነብ ሰው “በጅረቶች ዳር እንደተተከለ፣ ፍሬውን በወቅቱ እንደሚሰጥ፣ ቅጠሉም እንደማይጠወልግ ዛፍ ይሆናል። የሚሠራውም ሁሉ ይሳካለታል።”መዝ. 1:1-3

አንድ ዛፍ በጥሩ ሁኔታ እንዲያድግ ዘወትር ውኃ ማግኘት እንደሚያስፈልገው ሁሉ አንድ ክርስቲያንም በመንፈሳዊ ጤናማ ሆኖ ለመኖር የአምላክን ቃል አዘውትሮ መመገብ አለበት። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ ማንበብህንና ዘወትር በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትህን ቀጥል። በተጨማሪም የቤተሰብ አምልኮና የግል ጥናት ማድረግን የመሳሰሉ ጥሩ መንፈሳዊ ልማዶችን ይዞ መቀጠል አስፈላጊ ነው። ቀደም ሲል ታደርጋቸው የነበሩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችን በሙሉ ወደ አዲሱ አካባቢ ከመጣህ በኋላም ማቋረጥ የለብህም።

“ሌሎችን [የሚያረካ] እሱ ራሱ ይረካል።”ምሳሌ 11:25

በአገልግሎት የተሟላ ተሳትፎ ስታደርግ፣ አንተ ራስህ የምትበረታታ ከመሆኑም በላይ ከጉባኤው ጋር ቶሎ ትላመዳለህ። ኬቨን የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴን በጣም የረዳን ነገር ወደ አዲሱ ጉባኤያችን ከተዛወርን ብዙም ሳይቆይ ረዳት አቅኚዎች መሆናችን ነው። በመሆኑም ከወንድሞችና ከአቅኚዎች ጋር ለመተዋወቅ እንዲሁም ክልሉን ለመልመድ ጊዜ አልፈጀብንም።” ሮጀር የተባለ ወንድም ደግሞ ይኖርበት ከነበረው ቦታ ከ1,600 ኪሎ ሜትር በላይ ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ ተዛውሯል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ከአዲስ ጉባኤ ጋር ለመላመድ ከሁሉ የተሻለው መንገድ በተቻለ መጠን አዘውትሮ በአገልግሎት መካፈል ነው። በተጨማሪም ጉባኤ ውስጥ አስፈላጊ በሆነው ቦታ ሁሉ እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆንህን ለሽማግሌዎች አሳውቃቸው፤ ለምሳሌ አዳራሹን ለማጽዳት፣ ክፍል ማቅረብ ያልቻሉትን ተክተህ ለማቅረብ ወይም በመኪናህ ሌሎችን ወደ ስብሰባ ለማምጣት ፈቃደኛ መሆንህን ግለጽ። ወንድሞችና እህቶች፣ ለጉባኤያቸው አዲስ ብትሆንም የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ እንዳለህ ሲያዩ አንተን መቅረብ አይከብዳቸውም።”

“ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።”2 ቆሮ. 6:13

ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ በመክፈት ለወንድሞቻችሁ ፍቅር አሳዩ። ሜሊሳና ቤተሰቧ ወደ ሌላ ጉባኤ ከሄዱ በኋላ አዳዲስ ወዳጆችን ለማፍራት ልዩ ጥረት ማድረግ ጀመሩ። እንዲህ ብላለች፦ “ከስብሰባ በፊትና በኋላ ወደ ወንድሞች ቀረብ ብለን ለመጨዋወት እንሞክር ነበር። ይህም ሰላምታ ከመለዋወጥ ባለፈ ከእነሱ ጋር ለመተዋወቅ ጊዜ እንድናገኝ አስችሎናል።” ሜሊሳና ቤተሰቧ እንዲህ ማድረጋቸው የጉባኤውን አባላት ስም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማወቅ ረድቷቸዋል። በተጨማሪም እንግዳ ተቀባይ በመሆን ልባቸውን የከፈቱ ሲሆን ይህም ከአዲሶቹ ጓደኞቻቸው ጋር የመሠረቱት ወዳጅነት እንዲጠናከር አድርጓል። ሜሊሳ አክላም “ስልክ ቁጥር መለዋወጣችን ከወንድሞቻችን ጋር ለመገናኘት እንዲሁም በመንፈሳዊና በሌሎች እንቅስቃሴዎች ላይ አብረናቸው ለመካፈል አስችሎናል” ብላለች።

የማታውቃቸውን ሰዎች ቀረብ ብሎ ማዋራት የሚጨንቅህ ከሆነ ብዙም የማይከብዱህን ነገሮች በማድረግ መጀመር ትችላለህ። ለምሳሌ ፈገግ ማለትህ ሌሎች እንዲቀርቡህ ሊያነሳሳቸው ይችላል፤ እርግጥ እንዲህ ማድረግ መጀመሪያ ላይ ይከብድህ ይሆናል። ሆኖም “ብሩህ ገጽታ ልብን ደስ ያሰኛል።” (ምሳሌ 15:30 አ.መ.ት) ካደገችበት ቦታ በጣም ርቆ ወደሚገኝ አካባቢ የተዛወረችው ሪቼል እንዲህ ብላለች፦ “በተፈጥሮዬ በጣም ዓይናፋር ነኝ። አንዳንድ ጊዜ፣ በአዲሱ ጉባኤዬ ውስጥ ካሉት ወንድሞችና እህቶች ጋር የማወራው ራሴን አስገድጄ ነው። በአዳራሹ ውስጥ ብቻውን ዝም ብሎ የተቀመጠ ሰው ይኖር እንደሆነ ለማየት እሞክራለሁ። ያ ግለሰብ እንደ እኔ ዓይናፋር ሊሆን ይችላል።” ከእያንዳንዱ ስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ከአንድ የማታውቀው ክርስቲያን ጋር ለመጨዋወት ለምን ግብ አታወጣም?

በሌላ በኩል ደግሞ በአዲሱ ጉባኤህ ውስጥ ካሉት ሰዎች ጋር መተዋወቅ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ሳምንታት ያስደስትህ ይሆናል። ሆኖም ጊዜ እያለፈ ሲሄድ አዲስ የጉባኤው አባል መሆንህ ስለሚቀር ይህ ስሜት ላይቀጥል ይችላል። አዳዲስ ወዳጆች ለማፍራት የምታደርገውን ጥረት ግን መቀጠል ይኖርብሃል።

ከአንድ ቦታ ተነቅሎ ሌላ ቦታ የተተከለ ዛፍ ለውጡን ለመልመድ ጊዜ ቢወስድበትም አዲሱ ቦታ ላይ ሥሮችን ማብቀል ይጀምራል

መላመድ ጊዜ እንደሚወስድ አስታውስ

አንዳንድ ዛፎች በአዲስ አካባቢ በደንብ ሥር ለመስደድ ከሌሎች ዛፎች ይበልጥ ጊዜ ይወስድባቸዋል። በተመሳሳይም ከአዲስ ጉባኤ ጋር ለመላመድ የሚወስደው ጊዜ ከሰው ወደ ሰው ሊለያይ ይችላል። አንተም ወደ አዲሱ ጉባኤህ ከተዛወርክ የተወሰነ ጊዜ ቢያልፍም እንኳ ለመላመድ ገና እየታገልክ ሊሆን ይችላል፤ ይህ ከሆነ የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በሥራ ላይ ማዋል ሊረዳህ ይችላል፦

“ካልታከትን ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።”ገላ. 6:9

ከጉባኤው ጋር መላመድ መጀመሪያ ላይ ካሰብከው የበለጠ ጊዜ ቢወስድብህ አትገረም። ለምሳሌ ያህል፣ በጊልያድ የሠለጠኑ ብዙ ሚስዮናውያን ቤተሰባቸውን ለማየት ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱት በተመደቡበት አገር የተወሰኑ ዓመታት ከቆዩ በኋላ ነው። እንዲህ ማድረጋቸው ከአካባቢው ወንድሞች ጋር ወዳጅነት ለመመሥረትና በተመደቡበት አገር ካለው ባሕል ጋር ለመላመድ ይረዳቸዋል።

አሌሃንድሮ በተለያዩ ቦታዎች የኖረ ሲሆን ከአዲስ ጉባኤ ጋር መላመድ ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦ “በቅርቡ ወደ አንድ አካባቢ ከተዛወርን በኋላ ባለቤቴ ‘ጓደኞቼ ሁሉ ያሉት የቀድሞው ጉባኤ ውስጥ ነው’ አለች።” አሌሃንድሮ ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ሌላ አካባቢ በተዛወሩበት ጊዜም ተመሳሳይ ነገር ተናግራ እንደነበረ አስታወሳት። ይሁን እንጂ በእነዚያ ሁለት ዓመታት ውስጥ ከሌሎች ጋር ለመቀራረብ ልባዊ ጥረት ስላደረገች ቀደም ሲል የማታውቃቸው ሰዎች የቅርብ ጓደኞቿ ሆነዋል።

“‘የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?’ አትበል፤ እንዲህ ብሎ መጠየቅ ጥበብ አይደለምና።”መክ. 7:10

አዲሱን ጉባኤህን ከቀድሞው ጉባኤ ጋር አታወዳድር። ለምሳሌ በአዲሱ ጉባኤህ ውስጥ ያሉት ወንድሞች በቀድሞው ጉባኤህ ከነበሩት ይልቅ ቁጥብ ሊሆኑ ይችላሉ፤ አሊያም አንተ ከለመድከው በተለየ መልኩ ሐሳባቸውን በግልጽ ይናገሩ ይሆናል። በመልካም ባሕርያቸው ላይ ለማተኮር ሞክር፤ አንተም ብትሆን እንዲህ እንዲያደርጉልህ እንደምትፈልግ አስታውስ። ወደ ሌላ ጉባኤ የተዛወሩ አንዳንዶች ‘በእርግጥ “ለመላው የወንድማማች ማኅበር” ፍቅር አለኝ?’ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው ተገንዝበዋል።—1 ጴጥ. 2:17

“ደጋግማችሁ ለምኑ፣ ይሰጣችኋል።”ሉቃስ 11:9

ይሖዋ እንዲረዳህ መጸለይህን ቀጥል። ዴቪድ የሚባል አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ “ሁኔታውን በራስህ ለመወጣት አትሞክር። ያለ ይሖዋ እርዳታ ማከናወን የማንችላቸው ብዙ ነገሮች አሉ። ስለ ጉዳዩ ወደ እሱ ጸልይ!” ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሪቼል በዚህ ሐሳብ ትስማማለች። እንዲህ ብላለች፦ “እኔና ባለቤቴ ከጉባኤው ጋር እንዳልተዋሃድን ከተሰማን፣ ወደ ይሖዋ እንዲህ ብለን በግልጽ እንጸልያለን፦ ‘ሳናውቀው ሌሎች ወደ እኛ መቅረብ እንዲከብዳቸው እያደረግን ከሆነ ምን ማድረግ እንዳለብን እባክህ አሳውቀን።’ ከዚያም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር የበለጠ ጊዜ ለማሳለፍ እንጥራለን።”

ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ከጉባኤው ጋር መቀላቀል እንዳስቸገራቸው ካስተዋላችሁ ስለ ሁኔታው አብራችሁ ጸልዩ። ከወንድሞች ጋር ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በማመቻቸት አዳዲስ ጓደኞች እንዲያፈሩ እርዷቸው።

አዲሶች እንግድነት እንዳይሰማቸው እርዷቸው

ወደ ጉባኤያችሁ የተዛወሩ ክርስቲያኖችን ለመርዳት ምን ማድረግ ይቻላል? ከመጀመሪያው ጀምሮ እውነተኛ ወዳጅ ለመሆን ጥረት አድርግ። አዲስ የመጣኸው አንተ ብትሆን ኖሮ ምን ቢደረግልህ ደስ እንደሚልህ ለማሰብ ሞክር፤ ከዚያም ይህንኑ ለሌሎች አድርግ። (ማቴ. 7:12) አዲሶቹ ወንድሞችና እህቶች በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ እንዲገኙ አሊያም ወርሃዊውን የJW ብሮድካስቲንግ ፕሮግራም አብረዋችሁ እንዲመለከቱ ማድረግ ትችሉ ይሆን? ከእናንተ ጋር እንዲያገለግሉ ለምን አትጠይቋቸውም? ቀለል ያለ ምግብ አዘጋጅታችሁ ብትጋብዟቸው እንግዳ ተቀባይነታችሁን አይረሱትም። አዲሶች ወደ ጉባኤያችሁ ሲመጡ ሌሎች ምን ነገሮችን ልታደርጉላቸው ትችላላችሁ?

ካርሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ወደ አዲሱ ጉባኤያችን ስንመጣ አንዲት እህት፣ በተመጣጣኝ ዋጋ ሸቀጦችን መግዛት የምንችልባቸውን ሱቆች ነገረችን። ይህም በጣም ጠቅሞናል።” ከእናንተ የተለየ የአየር ንብረት ካለበት አካባቢዎች የሚመጡ ሰዎች በአዲሱ አካባቢ በሙቀት፣ በቅዝቃዜ ወይም በዝናብ ወቅት ምን መልበስ እንዳለባቸው ብትነግሯቸው ደስ ይላቸዋል። በተጨማሪም ስለ ማኅበረሰቡ ባሕልና ታሪክ ወይም ስለ ነዋሪዎቹ ሃይማኖት በመግለጽ በአገልግሎታቸው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆኑ ልትረዷቸው ትችላላችሁ።

ከጉባኤው ጋር ለመላመድ የምታደርገው ጥረት ይክስሃል

በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው አለን ወደ አዲሱ ጉባኤው ከመጣ አንድ ዓመት አልፎታል። ያሳለፈውን ጊዜ መለስ ብሎ በማስታወስ እንዲህ ብሏል፦ “መጀመሪያ ላይ ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ለመቀራረብ ራሴን ማስገደድ ነበረብኝ። አሁን ግን እንደ ቤተሰቤ ሆነዋል፤ በዚህም በጣም ደስተኛ ነኝ።” አለን አሁን ወዳለበት ጉባኤ መዛወሩ የቀድሞ ጓደኞቹን እንዳላሳጣው ተገንዝቧል። ከዚህ ይልቅ ተጨማሪ ጓደኞች ያፈራ ሲሆን ከእነሱም ጋር የዕድሜ ልክ ወዳጅነት መሥርቷል።

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።