በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ኦኔሲም እና ዤራልዲን

ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች የሚያገኙት የተትረፈረፈ በረከት

ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች የሚያገኙት የተትረፈረፈ በረከት

በማደግ ላይ ካሉ አገሮች ወደ ምዕራቡ ዓለም ተሰደው የነበሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ለይሖዋና ለባልንጀራቸው ያላቸው ፍቅር፣ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው አካባቢዎች ሄደው እንዲያገለግሉ አነሳስቷቸዋል። (ማቴ. 22:37-39) ይህን ለማድረግ ምን መሥዋዕት ከፍለዋል? ምን በረከትስ አጭደዋል? መልሱን ለማወቅ በምዕራባዊ አፍሪካ በምትገኘው በካሜሩን ላይ ትኩረት እናድርግ።

“ብዙ ‘ዓሦች ማጥመድ’ የሚቻልበት ቦታ”

ኦኔሲም የተባለ ወንድም በ1998 ከትውልድ አገሩ ከካሜሩን ወደ ሌላ አገር ሄደ። ለ14 ዓመታት የኖረው ከካሜሩን ውጭ ነው። አንድ ቀን በጉባኤ ስብሰባ ላይ፣ ስለ ስብከቱ ሥራ የሚናገር አንድ ምሳሌ ሰማ። ተናጋሪው እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሁለት ጓደኛሞች በተለያየ ቦታ ሆነው ዓሣ እያጠመዱ ነው እንበል፤ አንደኛው ከሌላኛው የበለጠ ብዙ ዓሣ ያዘ። ታዲያ ትንሽ ዓሣ የያዘው ሰው፣ ብዙ ዓሣ ያጠመደው ጓደኛው ወዳለበት ቦታ አይሄድም?”

ኦኔሲም ይህን ምሳሌ ሲሰማ፣ በመንፈሳዊ ሁኔታ ሲታይ ብዙ ዓሣ ወደሚገኝበት ወደ ካሜሩን ተመልሶ በመሄድ በዚያ የሚገኙትን አስፋፊዎች ለማገዝ አሰበ። ሆኖም ያሳሰቡት ነገሮች ነበሩ። ለበርካታ ዓመታት የኖረው በውጭ አገር ስለሆነ በትውልድ አገሩ ያለውን ሕይወት መልመድ መቻሉ አሳስቦት ነበር። ኦኔሲም ይህን ለመሞከር ሲል ወደ ካሜሩን ሄዶ ለስድስት ወር ቆየ። ከዚያም በ2012 ጠቅልሎ ካሜሩን ገባ።

ኦኔሲም እንዲህ ብሏል፦ “በዚያ ያለውን ሞቃት የአየር ንብረት እንዲሁም ኑሮውን መልመድ ነበረብኝ። በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ደረቅ አግዳሚ ወንበር ላይ መቀመጥን መልመድ አስፈልጎኝ ነበር።” አክሎም “በትምህርቱ ላይ ይበልጥ ትኩረት ማድረግ ስጀምር ግን በውጭ አገር የነበሩትን ምቹ ወንበሮች ረሳኋቸው” በማለት ሳቅ እያለ ተናግሯል።

በ2013 ኦኔሲም፣ ዤራልዲን የተባለች እህት አገባ፤ ዤራልዲን፣ ፈረንሳይ ውስጥ ለዘጠኝ ዓመታት ከኖረች በኋላ ወደ ካሜሩን የተመለሰች እህት ናት። እነዚህ ባልና ሚስት፣ ሕይወታቸው በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረጋቸው ምን በረከት አስገኝቶላቸዋል? ኦኔሲም እንዲህ ብሏል፦ “በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት እንድንካፈል ተጋበዝን፤ ከዚያም በቤቴል ማገልገል ጀመርን። ባለፈው ዓመት፣ በጉባኤያችን ያሉ 20 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ተጠምቀዋል። አሁን፣ ብዙ ‘ዓሦች ማጥመድ’ የሚቻልበት ቦታ ላይ እንዳለሁ ይሰማኛል።” (ማር. 1:17, 18) ዤራልዲን አክላ ስትናገር “ከጠበቅሁት በላይ ብዙ በረከት አግኝቻለሁ” ብላለች።

መንፈሳዊ ልጆች ማፍራት የሚያስገኘው ደስታ

ጁዲት እና ሳም ካስትል

ጁዲት ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዳ በዚያ ትኖር ነበር፤ ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት የምታደርገውን ተሳትፎ ለመጨመር በጣም ትጓጓ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “ቤተሰብ ለመጠየቅ ካሜሩን ደርሼ በተመለስኩ ቁጥር አለቅስ ነበር፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያስጀመርኳቸውን በርካታ ሰዎች ትቼ መምጣት ነበረብኝ።” ያም ቢሆን ጁዲት በቋሚነት ወደ ካሜሩን ለመመለስ አመንትታ ነበር። በዩናይትድ ስቴትስ፣ ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ ነበራት፤ ይህም በካሜሩን ያለው አባቷ ለሕክምና የሚያስፈልገውን ወጪ ለመሸፈን የሚያስችላት ነበር። ያም ቢሆን በይሖዋ በመታመን ወደ ትውልድ አገሯ ለመመለስ ወሰነች። ውጭ አገር ሳለች የነበራት የተመቻቸ ሕይወት አንዳንድ ጊዜ ይናፍቃት እንደነበር ሳትሸሽግ ተናግራለች። ስለዚህ በካሜሩን ያለውን ሕይወት ለመልመድ እንዲረዳት ወደ ይሖዋ ጸለየች። በተጨማሪም አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችና ባለቤቱ የሰጧት ማበረታቻ ጠቅሟታል።

ጁዲት ያለፈውን ጊዜ መለስ ብላ ስታስብ “በሦስት ዓመት ውስጥ አራት መንፈሳዊ ልጆች በማግኘቴ ተደስቻለሁ” ብላለች። በኋላ ላይ ጁዲት ልዩ አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች። በአሁኑ ወቅት ከባለቤቷ ከሳም ካስትል ጋር በወረዳ ሥራ እየተካፈለች ነው። የአባቷ ሁኔታስ እንዴት ሆነ? እሷና ቤተሰቧ ለአባቷ ቀዶ ሕክምና የሚያደርግ ሆስፒታል በሌላ አገር አገኙ፤ የሕክምና ወጪውን የሸፈነውም ሆስፒታሉ ነበር። ደስ የሚለው ቀዶ ሕክምናው ተሳካ።

የይሖዋን እጅ ማየት

ካሮሊን እና ቪክቶር

ቪክቶር የተባለ ወንድም ወደ ካናዳ ሄዶ ይኖር ነበር። መጠበቂያ ግንብ ላይ ስለ ከፍተኛ ትምህርት የሚናገር አንድ ርዕስ ካነበበ በኋላ እሱ ስለሚከታተለው ትምህርት አሰበበት። የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋርጦ አጠር ያለ የሙያ ሥልጠና ወሰደ። እንዲህ ብሏል፦ “ይህም ቶሎ ሥራ እንዳገኝ አስቻለኝ፤ በመሆኑም ለረጅም ጊዜ ስጓጓለት በነበረው በአቅኚነት አገልግሎት መካፈል ቻልኩ።” ከጊዜ በኋላ ቪክቶር፣ ካሮሊን የተባለች እህት ያገባ ሲሆን ለጉብኝት አብረው ወደ ካሜሩን ሄዱ። በካሜሩን የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሮ በጎበኙበት ወቅት ወንድሞች ወደ ካሜሩን መጥተው ስለ ማገልገል እንዲያስቡበት አበረታቷቸው። ቪክቶር “ፈቃደኛ የማንሆንበት ምክንያት አልነበረም፤ ደግሞም አኗኗራችንን ቀላል አድርገን ስለነበር ግብዣውን መቀበል ቻልን” ብሏል። ካሮሊን አንዳንድ የጤና ችግሮች ቢኖሩባትም ወደዚያ ለመዛወር ወሰኑ።

ካሜሩን ውስጥ መስኩ ላይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን የመማር ፍላጎት ያላቸው ብዙ ሰዎች ስለነበሩ ቪክቶርና ካሮሊን የዘወትር አቅኚዎች ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ያጠራቀሙት ገንዘብ ስለነበራቸው ለተወሰነ ጊዜ ያህል መሥራት አላስፈለጋቸውም። በኋላ ላይ ደግሞ ወደ ካናዳ ሄደው ለጥቂት ወራት ከሠሩ በኋላ ያጠራቀሙትን ገንዘብ ይዘው ወደ ካሜሩን በመመለስ በአቅኚነት ማገልገላቸውን ቀጠሉ። ታዲያ ምን በረከቶች አግኝተዋል? በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት መካፈልና ልዩ አቅኚዎች ሆነው ማገልገል ችለዋል፤ አሁን ደግሞ የግንባታ አገልጋዮች ናቸው። ቪክቶር “የነበረንን የተመቻቸ ሕይወት ትተን መምጣታችን የይሖዋን እጅ ለማየት አስችሎናል” ብሏል።

ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ መርዳት የሚያስገኘው ደስታ

ስቴፋኒ እና አላ

በ2002 አላ ጀርመን ውስጥ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እየተከታተለ በነበረበት ወቅት፣ ወጣቶች—በሕይወታችሁ ምን ለማድረግ አስባችኋል? የሚለውን ትራክት አነበበ። በትራክቱ ላይ ያለው ሐሳብ አዳዲስ ግቦች እንዲያወጣ አነሳሳው። በ2006 በአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ከተካፈለ በኋላ በትውልድ አገሩ በካሜሩን እንዲያገለግል ተመደበ።

አላ ካሜሩን ውስጥ ለተወሰነ ሰዓት ብቻ የሚሠራበት ሥራ አገኘ። በኋላ ላይ ደግሞ የተሻለ ደሞዝ የሚያስገኝ ሥራ አግኝቶ መሥራት ጀመረ፤ ሆኖም እንደ ቀድሞው ለአገልግሎቱ ሰፊ ጊዜ አለማግኘቱ አሳስቦት ነበር። ስለዚህ ልዩ አቅኚ ሆኖ እንዲያገለግል ሲጋበዝ ወዲያውኑ ግብዣውን ተቀበለ። አሠሪው ደሞዙን እንደሚጨምርለት ቢነግረውም አላ በውሳኔው ጸና። ከጊዜ በኋላ አላ፣ ለበርካታ ዓመታት ፈረንሳይ የኖረች ስቴፋኒ የምትባል እህት አገባ። ስቴፋኒ ወደ ካሜሩን ከተመለሰች በኋላ ምን ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋት ነበር?

ስቴፋኒ እንዲህ ብላለች፦ “ከባድ ያልሆኑ የጤና እክሎችና የአለርጂ ችግር አጋጥሞኝ ነበር፤ ሆኖም ቋሚ የሕክምና ክትትል በማድረግ ችግሩን መቋቋም ቻልኩ።” ባልና ሚስቱ በመጽናታቸው ተክሰዋል። አላ እንዲህ ብሏል፦ “ካቴ ወደተባለች ራቅ ያለች መንደር ሄደን ስንሰብክ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የሚፈልጉ ሰዎች አገኘን። በኋላ ላይ ከእነዚህ ሰዎች ጋር በስልክ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርን። ከእነዚህ ጥናቶቻችን ሁለቱ የተጠመቁ ሲሆን በአካባቢው አንድ ቡድን ተቋቋመ።” ስቴፋኒ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ሰዎች ራሳቸውን ለይሖዋ እንዲወስኑ ከመርዳት የበለጠ ደስታ የሚያስገኝ ነገር የለም። እዚህ በማገልገላችን ይህን ደስታ ብዙ ጊዜ ማጣጣም ችለናል።” አላ እና ስቴፋኒ በአሁኑ ወቅት በወረዳ ሥራ እየተካፈሉ ነው።

‘ያደረግነው ውሳኔ ትክክል ነበር’

ሊዮንስ እና ዢዜል

ዢዜል የተጠመቀችው ጣሊያን ውስጥ የሕክምና ትምህርቷን እየተከታተለች በነበረበት ወቅት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኗት አቅኚ ባልና ሚስት በነበራቸው ቀላል የሆነ አኗኗር ስለተማረከች በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ተሳትፎ ማድረግ ፈለገች። ስለዚህ ዢዜል ትምህርቷን እየተከታተለች የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች።

ዢዜል ወደ ካሜሩን ተመልሳ ይሖዋን ይበልጥ የማገልገል ፍላጎት ነበራት፤ ሆኖም ያሳሰቧት ነገሮች ነበሩ። እንዲህ ብላለች፦ “ውሳኔው የጣሊያን የመኖሪያ ፈቃዴን ያሳጣኛል፤ እንዲሁም በጣሊያን ከሚኖሩ ወዳጆቼና የቤተሰቤ አባላት መለየት ነበረብኝ።” ያም ቢሆን ግንቦት 2016 ዢዜል ወደ ካሜሩን ተመለሰች። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ ሊዮንስ የተባለ ወንድም አገባች። በካሜሩን የሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ፣ ባልና ሚስቱ አዮስ ወደተባለች የመንግሥቱ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባት ትንሽ ከተማ ሄደው እንዲያገለግሉ ሐሳብ አቀረበላቸው።

ታዲያ በአዮስ የነበራቸው ሕይወት ምን ይመስል ነበር? ዢዜል እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጊዜ ለሳምንታት የኤሌክትሪክ ኃይል ስለማይኖር ሞባይላችንን ቻርጅ ማድረግ አንችልም ነበር። በመሆኑም ሞባይላችን ከሚሠራበት የማይሠራበት ጊዜ ይበልጣል። በእንጨት ማብሰል ተማርኩ፤ ምሽት ላይ ደግሞ ጋሪና የእጅ ባትሪ ይዘን ምንጭ እንወርዳለን፤ በማታ የምንሄደው ሰው በማይበዛበት ሰዓት ውኃ ቀድተን ለመምጣት ነበር።” ባልና ሚስቱ ይህን ሁኔታ ለመቋቋም የረዳቸው ምንድን ነው? ዢዜል እንዲህ ብላለች፦ “የይሖዋን መንፈስ ማግኘታችን፣ እርስ በርስ መደጋገፋችን እንዲሁም ከቤተሰባችን አባላትና ከወዳጆቻችን የምናገኘው ማበረታቻና አልፎ አልፎ የሚሰጡን የገንዘብ እርዳታ ሁኔታውን ለመቋቋም አስችሎናል።”

ዢዜል ወደ ትውልድ አገሯ በመመለሷ ደስተኛ ነች? “አዎ! በጣም ደስተኛ ነኝ” ብላለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በእርግጥ መጀመሪያ ላይ የከበዱንና ተስፋ ያስቆረጡን ሁኔታዎች ነበሩ፤ እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም ስንችል ግን እኔና ባለቤቴ ያደረግነው ውሳኔ ትክክል እንደነበር ተሰምቶናል። በይሖዋ የምንታመን ሲሆን ወደ እሱ ይበልጥ እንደቀረብን ይሰማናል።” ሊዮንስ እና ዢዜል በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት የመካፈል አጋጣሚ አግኝተዋል፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ጊዜያዊ ልዩ አቅኚዎች ሆነው እያገለገሉ ነው።

ብዙ ዓሣ ለማግኘት ሲሉ የተለያዩ ሁኔታዎችን በድፍረት እንደሚወጡ ዓሣ አጥማጆች ሁሉ፣ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱ ክርስቲያኖችም የመንግሥቱን መልእክት የመስማት ፍላጎት ያላቸውን ቅን ሰዎች ለመርዳት ሲሉ በፈቃደኝነት ብዙ መሥዋዕቶች ይከፍላሉ። ይሖዋ እነዚህን ትጉ አስፋፊዎች በመልካም እንደሚያስባቸውና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳ ጥርጥር የለውም። (ነህ. 5:19፤ ዕብ. 6:10) አንተስ የምትኖረው ከአገርህ ውጭ ነው? በትውልድ አገርህ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ የሚያስፈልጉ ከሆነ ወደዚያ መመለስ ትችል ይሆን? እንዲህ ካደረግህ የተትረፈረፉ በረከቶች ታገኛለህ።—ምሳሌ 10:22