በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 48

የወደፊቱን ጊዜ “በትኩረት ተመልከት”

የወደፊቱን ጊዜ “በትኩረት ተመልከት”

“ዓይኖችህ በቀጥታ ይዩ፤ አዎ፣ ፊት ለፊት በትኩረት ተመልከት።”—ምሳሌ 4:25

መዝሙር 77 በጨለማ ዓለም ውስጥ ብርሃን ማብራት

ማስተዋወቂያ *

1-2. በምሳሌ 4:25 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

እስቲ ስለሚከተሉት ሁኔታዎች አስብ። አንዲት አረጋዊት እህት ያሳለፉትን አስደሳች ሕይወት በትዝታ ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት ሕይወት ከባድ ቢሆንባቸውም ይሖዋን ለማገልገል የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። (1 ቆሮ. 15:58) ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ በየቀኑ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸዋል። አንዲት ሌላ እህት በአንድ የእምነት ባልንጀራዋ የተጎዳችበትን ወቅት ጨርሶ ባትረሳውም ቂም ላለመያዝ መርጣለች። (ቆላ. 3:13) አንድ ወንድም ደግሞ ቀደም ሲል የፈጸማቸውን ስህተቶች ባይረሳቸውም ከዚህ በኋላ ባለው ሕይወቱ ታማኝ ለመሆን ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ያተኩራል።—መዝ. 51:10

2 እነዚህን ሦስት ክርስቲያኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ሦስቱም ቀደም ሲል የገጠማቸውን ነገር አልረሱትም፤ ሆኖም ስለዚያ ነገር እያሰቡ አይብሰለሰሉም። ከዚህ ይልቅ የወደፊቱን ጊዜ ‘በትኩረት ይመለከታሉ።’ምሳሌ 4:25ን አንብብ።

3. የወደፊቱን ጊዜ ‘በትኩረት መመልከት’ ያለብን ለምንድን ነው?

3 የወደፊቱን ጊዜ ‘በትኩረት መመልከታችን’ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው አሥር ጊዜ ወደ ኋላ እየተመለከተ ወደ ፊት ቀጥ ብሎ መራመድ አይችልም፤ እኛም በተመሳሳይ ስላሳለፍነው ሕይወት ነጋ ጠባ የምናስብ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት ወደ ፊት መግፋት አንችልም።—ሉቃስ 9:62

4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

4 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ስላለፈው ጊዜ ከልክ በላይ እንድናስብ የሚያደርጉ ሦስት ወጥመዶችን እንመለከታለን። እነሱም (1) በትዝታ መኖር፣ (2) ቂም፣ (3) ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ናቸው። ከእያንዳንዱ ወጥመድ ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ‘ከኋላችን ባሉት ነገሮች’ ላይ ከማውጠንጠን ይልቅ ‘ከፊታችን ወዳሉት ነገሮች እንድንንጠራራ’ የሚረዱን እንዴት እንደሆነ እንመረምራለን።—ፊልጵ. 3:13

በትዝታ መኖር ወጥመድ አይሁንብህ

የወደፊቱን ጊዜ በትኩረት እንዳንመለከት የሚያደርገን ምን ሊሆን ይችላል? (አንቀጽ 5, 9, 13⁠ን ተመልከት) *

5. መክብብ 7:10 ከየትኛው ወጥመድ እንድንርቅ ያሳስበናል?

5 መክብብ 7:10ን አንብብ። ይህ ጥቅስ “የቀድሞው ዘመን ለምን ጥሩ ሆነ?” ማለት ስህተት ነው እንደማይል ልብ በል። ጥሩ ትዝታ የይሖዋ ስጦታ ነው። ጥቅሱ የሚለው “‘የቀድሞው ዘመን ከአሁኑ ዘመን ለምን ተሻለ?’ አትበል” ነው። ስለዚህ ወጥመድ የሚሆነው፣ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከቀድሞው ሕይወታችን ጋር በማነጻጸር አሁን ሁሉ ነገር እንደተበላሸ ማሰባችን ነው።

እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ በኋላ ምን ስህተት ሠርተዋል? (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት)

6. የቀድሞው ሕይወታችን የተሻለ እንደሆነ እያሰብን መብሰልሰል ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

6 የቀድሞው ሕይወታችን የተሻለ እንደሆነ እያሰብን መብሰልሰል ሞኝነት የሆነው ለምንድን ነው? በትዝታ የምንኖር ከሆነ የምናስታውሰው በቀድሞው ሕይወታችን የገጠሙንን ጥሩ ነገሮች ብቻ ይሆናል። በዚያን ጊዜ የገጠሙንን ችግሮች ልንረሳ እንችላለን። የጥንቶቹን እስራኤላውያን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ከግብፅ ከወጡ በኋላ፣ በዚያ ያሳለፉት ሕይወት ምን ያህል በመከራ የተሞላ እንደነበረ ወዲያውኑ ረሱ። እስራኤላውያኑ ያስታወሱት በዚያ ሳሉ ይበሉት የነበረውን ጥሩ ምግብ ነበር። እንዲህ ብለው ነበር፦ “በግብፅ እያለን በነፃ እንበላው የነበረው ዓሣ እንዲሁም ኪያሩ፣ ሐብሐቡ፣ ባሮ ሽንኩርቱ፣ ቀይ ሽንኩርቱና ነጭ ሽንኩርቱ በዓይናችን ላይ ዞሯል!” (ዘኁ. 11:5) እውነት ይህን ምግብ ያገኙት “በነፃ” ነበር? አልነበረም። እንዲያውም እስራኤላውያን ባሮች ነበሩ፤ ግብፃውያን ከባድ ጭቆና ያደርሱባቸው ነበር። (ዘፀ. 1:13, 14፤ 3:6-9) በኋላ ላይ ግን ያን የመከራ ዘመን ረስተው የቀድሞውን ጊዜ መናፈቅ ጀመሩ። ይሖዋ ባደረገላቸው መልካም ነገሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ የቀድሞውን ዘመን እያሰቡ “. . . ድሮ ቀረ” ማለት ጀመሩ። ይሖዋ እንዲህ ያለ ዝንባሌ በማሳየታቸው አልተደሰተም።—ዘኁ. 11:10

7. አንዲትን እህት በትዝታ መኖር ወጥመድ እንዳይሆንባት የረዳት ምንድን ነው?

7 በትዝታ መኖር ወጥመድ እንዳይሆንብን ምን ማድረግ እንችላለን? በ1945 በብሩክሊን ቤቴል ማገልገል የጀመረችን የአንዲት እህት ምሳሌ እንመልከት። ይህች እህት ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ አንድ ቤቴላዊ ያገባች ሲሆን አብረው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ይሁንና በ1970ዎቹ ዓመታት አጋማሽ ባለቤቷ ታመመ። እህት እንደተረከችው፣ ባለቤቷ የሚሞትበት ጊዜ ሲቃረብ ብቸኝነቷን ለመቋቋም የሚረዱ አንዳንድ ጥሩ ምክሮች ሰጣት። “ብዙ ሰዎች የሌላቸው አስደሳች ትዳር ነበረን” ብሏት ነበር። አክሎ ግን እንዲህ የሚል ምክር ሰጣት፦ “ምንም እንኳ ትዝታዎቹ ከአእምሮሽ ባይጠፉም ያለፈውን ሕይወትሽን በማስታወስ አትብሰልሰይ። ጊዜ እያለፈ ሲሄድ ትጽናኛለሽ። ባጋጠመሽ ሁኔታ ከሚገባው በላይ በማዘን ምሬት እንዲያድርብሽ አትፍቀጂ። እንደዚህ ያለ አስደሳች ጊዜ በማሳለፍሽና ባገኘሻቸው በረከቶች ደስ ይበልሽ። . . . ያሳለፍነውን ጊዜ የማስታወስ ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው።” ይህ እንዴት ያለ ጥሩ ምክር ነው!

8. እህታችን በትዝታ እንዳትኖር የተሰጣትን ምክር ተግባራዊ ማድረጓ ምን ጥቅም አስገኝቶላታል?

8 እህታችን ምክሩን ተግባራዊ አድርጋለች። በ92 ዓመቷ በሞት እስካንቀላፋችበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግላለች። ከመሞቷ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት እንዲህ ብላ ነበር፦ “ይሖዋን በሙሉ ጊዜ በማገልገል ያሳለፍኳቸውን ከ63 የሚበልጡ ዓመታት መለስ ብዬ ሳስብ ሕይወቴ አርኪ ነበር ብዬ መናገር እችላለሁ።” ለምን? እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ከምንም ነገር በላይ በሕይወት ውስጥ እርካታ የሚያስገኘው . . . ድንቅ የሆነው የወንድማማች ማኅበራችን እና ብቻውን እውነተኛ አምላክ የሆነውን ታላቁን ፈጣሪያችንን ይሖዋን ለዘላለም እያገለገልን ከወንድሞችና ከእህቶቻችን ጋር ገነት በሆነች ምድር ላይ የመኖር ተስፋችን ነው።” * በእርግጥም ይህች እህት የወደፊቱን ጊዜ በትኩረት በመመልከት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትሆነናለች!

ቂም ወጥመድ አይሁንብህ

9. በዘሌዋውያን 19:18 ላይ እንደተገለጸው ይቅር ማለት ይበልጥ ከባድ የሚሆንብን መቼ ሊሆን ይችላል?

9 ዘሌዋውያን 19:18ን አንብብ። አንድ የእምነት ባልንጀራችን፣ የቅርብ ወዳጃችን ወይም የቤተሰባችን አባል ሲበድለን ይቅር ማለት ይበልጥ ከባድ ይሆንብናል። የአንዲትን እህት ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ አንዲት ክርስቲያን ይህችን እህት ‘ገንዘብ ሰርቀሽኛል’ በማለት ወንጅላት ነበር። ክሱን የሰነዘረችው እህት ከጊዜ በኋላ ይቅርታ ጠየቀች፤ በሐሰት የተወነጀለችው እህት ግን ስለተፈጠረው ነገር ማሰቧን ማቆም አልቻለችም። አንተስ እንዲህ ተሰምቶህ ያውቃል? አብዛኞቻችን እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞን ባያውቅም እንኳ የበደለንን ሰው ይቅር ልንለው እንደማንችል የተሰማን ጊዜ ይኖራል።

10. ቅያሜያችንን መተው ሲከብደን ምን ሊረዳን ይችላል?

10 ቅያሜያችንን መተው ሲከብደን ምን ሊረዳን ይችላል? አንደኛ፣ ይሖዋ ሁሉን ነገር እንደሚያይ እናስታውስ። የደረሰብንን በደል ጨምሮ በሕይወታችን ውስጥ የሚገጥመንን ነገር በሙሉ ያውቃል። (ዕብ. 4:13) ስሜታችን ሲጎዳ ያዝንልናል። (ኢሳ. 63:9) ደግሞም የደረሰብን በደል ያስከተለብንን ማንኛውም ጉዳት ወደፊት እንደሚያስወግድ ቃል ገብቷል።—ራእይ 21:3, 4

11. ቂም አለመያዝ ራሳችንን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

11 በተጨማሪም ቂም አለመያዝ የሚጠቅመው ራሳችንን እንደሆነ እናስታውስ። በሐሰት የተወነጀለችው እህት ከጊዜ በኋላ ይህን ተገንዝባለች። ውሎ አድሮ ቅሬታዋን መተው ቻለች። ሌሎችን ይቅር ስንል ይሖዋም ይቅር እንደሚለን ተገነዘበች። (ማቴ. 6:14) እህታችን፣ ይቅር ብላለች ሲባል የእምነት ባልንጀራዋ ያደረገችው ነገር ጥፋት እንዳልሆነ ተሰምቷታል ወይም በደሉን አቅልላ ተመልክታዋለች ማለት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ቅያሜዋን ለመተው መርጣለች ማለት ነው። ይህም እህታችን ይበልጥ ደስተኛ እንድትሆንና በይሖዋ አገልግሎት ላይ ማተኮር እንድትችል ረድቷታል።

ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ አይሁንብህ

12. አንደኛ ዮሐንስ 3:19, 20 የትኛውን እውነታ ግልጽ ያደርጋል?

12 አንደኛ ዮሐንስ 3:19, 20ን አንብብ። ሁላችንም አልፎ አልፎ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች እውነትን ከመስማታቸው በፊት ባደረጓቸው ነገሮች የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ የሚሰማቸው ከተጠመቁ በኋላ በፈጸሟቸው ስህተቶች የተነሳ ነው። እንዲህ ያለው ስሜት የተለመደ ነው። (ሮም 3:23) ማናችንም ብንሆን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።” (ያዕ. 3:2፤ ሮም 7:21-23) የጥፋተኝነት ስሜት ደስ የሚል ነገር ባይሆንም ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የጥፋተኝነት ስሜት አካሄዳችንን እንድናስተካክልና ስህተታችንን ላለመድገም እንድንጥር ስለሚያነሳሳን ነው።—ዕብ. 12:12, 13

13. ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብን ልንጠነቀቅ የሚገባው ለምንድን ነው?

13 በሌላ በኩል ግን ንስሐ ከገባንና ይሖዋ ይቅር እንዳለን ካሳየን በኋላም እንኳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማን ይሆናል፤ ይህ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ነው። እንዲህ ያለው የጥፋተኝነት ስሜት ጎጂ ነው። (መዝ. 31:10፤ 38:3, 4) ለምን? ቀደም ሲል በፈጸመችው ኃጢአት የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት ትሠቃይ የነበረችን አንዲት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች እህት “ምሕረት እንደማላገኝ ስለተሰማኝ በይሖዋ አገልግሎት በትጋት ለመካፈል ጥረት ማድረጌ ምንም ዋጋ እንደሌለው አሰብኩ” ብላለች። ብዙዎቻችን የእህትን ስሜት መረዳት አይከብደንም። እንግዲያው ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። ደግሞም ይሖዋ በእኛ ተስፋ ሳይቆርጥ እኛ በራሳችን ተስፋ ቆርጠን እሱን ማገልገላችንን ብናቆም ሰይጣን ምን ያህል እንደሚደሰት አስበው!—ከ2 ቆሮንቶስ 2:5-7, 11 ጋር አወዳድር።

14. ይሖዋ ተስፋ እንዳልቆረጠብን የምናውቀው እንዴት ነው?

14 ያም ቢሆን ‘ይሖዋ በእኔ ተስፋ እንዳልቆረጠ እንዴት አውቃለሁ?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይህን ጥያቄ ማንሳታችን በራሱ የይሖዋን ይቅርታ ልናገኝ እንደምንችል ያሳያል። ከበርካታ ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “በቀድሞ ሕይወትህ የነበረህ አንድ መጥፎ ልማድ፣ ካሰብከው የበለጠ ሥር ከመስደዱ የተነሳ በተደጋጋሚ እያገረሸ ያስቸግርህ [ይሆናል]። . . . ከሆነ ተስፋ አትቁረጥ። ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደፈጸምክ አታስብ። እንዲህ ብለህ እንድታስብ የሚፈልገው ሰይጣን ነው። በጥፋትህ መጸጸትህና ማዘንህ በራሱ ብዙ እንዳልራቅህ የሚጠቁም ነው። በትሕትና እና ከልብ በመነጨ ስሜት የአምላክን እርዳታ መጠየቅህን አታቋርጥ፤ ይቅር እንዲልህ፣ እንዲያነጻህ እና እንዲረዳህ አምላክን ለምነው። ችግር በገጠመው ቁጥር ሮጦ ወደ አባቱ እንደሚሄድ ልጅ ሁን፤ ይሖዋን ስለ ድክመትህ የለመንከው ምንም ያህል ጊዜ ቢሆን፣ በጸጋው የሚያስፈልግህን እርዳታ በደስታ ይሰጥሃል።።” *

15-16. አንዳንዶች ይሖዋ ተስፋ እንዳልቆረጠባቸው ሲገነዘቡ ምን ተሰምቷቸዋል?

15 ብዙ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋ ተስፋ እንዳልቆረጠባቸው መገንዘባቸው አጽናንቷቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከተወሰኑ ዓመታት በፊት አንድ ወንድም “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው ዓምድ ሥር በወጣ አንድ ተሞክሮ ልቡ ተነክቶ ነበር። በተሞክሮው ላይ አንዲት እህት፣ በቀድሞ ሕይወቷ ባጋጠሟት ነገሮች የተነሳ ይሖዋ እንደሚወዳት ማመን ከብዷት እንደነበር ተናግራለች። ከተጠመቀች ከዓመታት በኋላም እንኳ ይህ ስሜት አልጠፋም። ሆኖም በቤዛው ላይ ስታሰላስል አመለካከቷ መቀየር ጀመረ። *

16 ታዲያ ይህ ተሞክሮ ወንድምን ያበረታታው እንዴት ነው? እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ወጣት ሳለሁ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን የማየት ሱስ ስለነበረብኝ ይህን ልማድ ለማሸነፍ እታገል ነበር። በቅርቡ ይህ ልማድ አገረሸብኝ። ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲረዱኝ የጠየቅሁ ሲሆን ችግሬን በማሸነፍ ረገድ መሻሻል እያሳየሁ ነው። ሽማግሌዎቹም አምላክ እንደሚወደኝና ምሕረት እንደሚያደርግልኝ አረጋገጡልኝ። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ፣ ይሖዋ ሊወደኝ እንደማይችል ስለማስብ የዋጋ ቢስነት ስሜት ያድርብኛል። [የዚህችን እህት] ተሞክሮ ማንበቤ በጣም ረድቶኛል። አምላክ ይቅር ሊለኝ እንደማይችል ማሰብ የልጁ መሥዋዕት የእኔን ኃጢአት ለመሸፈን በቂ አይደለም የማለት ያህል እንደሆነ ተገንዝቤያለሁ። ስለዚህ በዋጋ ቢስነት ስሜት በምዋጥበት ጊዜ ሁሉ ይህን ተሞክሮ እያነበብኩ ማሰላሰል እንድችል ገጹን ቆርጬ በማውጣት በቅርብ አስቀምጬዋለሁ።”

17. ሐዋርያው ጳውሎስ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንበት ምን አድርጓል?

17 እንዲህ ያሉት ተሞክሮዎች ሐዋርያው ጳውሎስን ያስታውሱናል። ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ከባድ ኃጢአቶች ሠርቷል። ጳውሎስ የፈጸማቸውን ስህተቶች አልረሳቸውም፤ ነጋ ጠባ ስለ እነሱ ያስብ ነበር ማለት ግን አይደለም። (1 ጢሞ. 1:12-15) ቤዛውን ለእሱ በግሉ እንደተሰጠው ስጦታ አድርጎ ቆጥሮታል። (ገላ. 2:20) በመሆኑም ጳውሎስ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዲሆንበት አልፈቀደም። ትኩረት ያደረገው፣ ከዚያ በኋላ ለይሖዋ መስጠት በሚችለው ነገር ላይ ነው።

በወደፊቱ ጊዜ ላይ ትኩረት አድርግ!

ለወደፊቱ ተስፋ የምንበቃ ሰዎች ለመሆን የቻልነውን ሁሉ እናድርግ (ከአንቀጽ 18-19⁠ን ተመልከት) *

18. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን ትምህርት አግኝተናል?

18 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ልንጠነቀቅባቸው ስለሚገቡ ወጥመዶች ካደረግነው ውይይት ምን ትምህርት አግኝተናል? (1) ጥሩ ትዝታ የይሖዋ ስጦታ ነው፤ ሆኖም ያሳለፍነው ሕይወት ምንም ያህል አስደሳች ቢሆን ወደፊት በአዲሱ ዓለም የምናገኘው ሕይወት እጅግ የላቀ ነው። (2) ሌሎች ይበድሉን ይሆናል፤ ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት ወደ ፊት መግፋት የምንችለው ይቅር ለማለት ስንመርጥ ነው። (3) ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ይሖዋን በደስታ እንዳናገለግለው እንቅፋት ይሆንብናል። ስለዚህ እንደ ጳውሎስ፣ ይሖዋ ይቅር እንዳለን ማመን ያስፈልገናል።

19. በአዲሱ ዓለም ውስጥ፣ ስላለፈው ሕይወታችን እያሰብን በጸጸት እንደማንብሰለሰል በምን እናውቃለን?

19 ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶልናል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ ያለፈውን ሕይወታችንን እያሰብን በጸጸት አንብሰለሰልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚያ ጊዜ ሲናገር “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም” ይላል። (ኢሳ. 65:17) እስቲ አስበው፦ ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ያገለገልን አንዳንዶቻችን ዕድሜያችን ገፍቷል፤ በአዲሱ ዓለም ግን እንደገና ወጣት እንሆናለን። (ኢዮብ 33:25) እንግዲያው ስላለፈው ጊዜ ከልክ በላይ ላለማሰብ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በወደፊቱ ተስፋ ላይ ትኩረት በማድረግ ለዚያ የምንበቃ ሰዎች ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ!

መዝሙር 142 ተስፋችንን አጥብቀን እንያዝ

^ አን.5 ስላለፈው ጊዜ ማሰብ ምንም ስህተት የለውም። ሆኖም ስላለፈው ጊዜ እያሰቡ መብሰልሰል አሁን ያለንን አጋጣሚ እንዳንጠቀምበት ወይም የወደፊቱን ተስፋችንን እንድንረሳ ሊያደርገን ይችላል። በዚህ ርዕስ ላይ ስላለፈው ጊዜ ከልክ በላይ እንድናስብ የሚያደርጉ ሦስት ወጥመዶችን እንመለከታለን። ከእነዚህ ወጥመዶች እንድንርቅ የሚረዱንን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ዘመናዊ ምሳሌዎችም እናያለን።

^ አን.14 የየካቲት 15, 1954 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ገጽ 123⁠ን ተመልከት።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ በትዝታ መኖር፣ ቂም መያዝና ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ከባድ ሸክም እየጎተቱ ወደ ፊት ለመጓዝ እንደ መሞከር ሊቆጠሩ ይችላሉ፤ እነዚህ ነገሮች ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ ወደ ፊት መጓዝ ከባድ እንዲሆንብን ያደርጋሉ።

^ አን.65 የሥዕሉ መግለጫ፦ እነዚህን ሸክሞች ስናስወግድ እፎይታና ደስታ እናገኛለን፤ እንዲሁም ኃይላችን ይታደሳል። የወደፊቱን ጊዜ አሻግረን መመልከትም እንችላለን።