በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

“ይሖዋ አልረሳኝም”

“ይሖዋ አልረሳኝም”

የምኖረው በደቡብ አሜሪካ፣ ጋያና ውስጥ በሚገኝ ኦሪያላ የተባለ መንደር ውስጥ ነው፤ የመንደሩ ነዋሪዎች 2,000 ገደማ ቢሆኑ ነው። መንደሩ የሚገኘው በጣም ገለልተኛ በሆነ አካባቢ ስለሆነ ወደዚያ መሄድ የሚቻለው በትንሽ አውሮፕላን ወይም በጀልባ ብቻ ነው።

የተወለድኩት በ1983 ነው። ትንሽ እያለሁ ጤናማ ልጅ ነበርኩ፤ አሥር ዓመት ሲሆነኝ ግን መላ ሰውነቴን በጣም ያመኝ ጀመር። ከሁለት ዓመት ገደማ በኋላ አንድ ቀን ጠዋት ስነቃ መንቀሳቀስ አቃተኝ። እግሬን ለማንቀሳቀስ ብታገልም አልቻልኩም። ከዚያ ቀን ወዲህ ሽባ ሆንኩ። የያዘኝ ሕመም ሰውነቴ ማደግ እንዲያቆምም አድርጎ ነበር። ስለዚህ አሁንም እንኳ ሰውነቴ ሲታይ የትንሽ ልጅ ይመስላል።

በሕመሜ የተነሳ ቤት መዋል ከጀመርኩ ከጥቂት ወራት በኋላ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ። እንግዶች ሲመጡ ብዙ ጊዜ እደበቅ ነበር፤ የዚያን ቀን ግን የመጡትን ሴቶች አነጋገርኳቸው። በገነት ስለሚኖረው ሕይወት ሲነግሩኝ፣ የአምስት ዓመት ልጅ እያለሁ የሰማሁት ነገር ትዝ አለኝ። በዚያ ወቅት ጄትሮ የሚባል በሱሪናም የሚኖር አንድ ሚስዮናዊ በየወሩ ወደ መንደራችን መጥቶ አባቴን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናው ነበር። ጄትሮ በደግነት ይይዘኝ ስለነበር በጣም እወደው ነበር። በተጨማሪም አያቶቼ የይሖዋ ምሥክሮች በመንደራችን በሚያካሂዷቸው ስብሰባዎች ላይ ሲገኙ አንዳንድ ጊዜ ይዘውኝ ይሄዱ ነበር። በመሆኑም ያን ዕለት መጥተው ካነጋገሩኝ የይሖዋ ምሥክሮች አንዷ የሆነችው ፍሎረንስ፣ መጽሐፍ ቅዱስን መማር እፈልግ እንደሆነ ስትጠይቀኝ ተስማማሁ።

ፍሎረንስ ከባለቤቷ ከጀስተስ ጋር ተመልሳ መጣች። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠኑኝ ጀመር። ማንበብ እንደማልችል ሲያውቁ ፊደል አስቆጠሩኝ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ማንበብ ቻልኩ። አንድ ቀን እነዚህ ባልና ሚስት በሱሪናም እንዲያገለግሉ መመደባቸውን ነገሩኝ። የሚያሳዝነው፣ ኦሪያላ ውስጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴን ሊያስቀጥለኝ የሚችል ሰው አልነበረም። ደስ የሚለው ግን ይሖዋ አልረሳኝም።

ብዙም ሳይቆይ፣ ፍሎይድ የተባለ አቅኚ ወደ ኦሪያላ መጣ። ፍሎይድ ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግል አገኘኝ። መጽሐፍ ቅዱስን እንዳጠና ሲጋብዘኝ ሳቅ አልኩ። ፍሎይድ “ምንድን ነው ያሳቀህ?” ብሎ ጠየቀኝ። አምላክ ከእኛ የሚፈልገው ምንድን ነው? የተባለውን ብሮሹር አጥንቼ እንደጨረስኩና ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት * የተባለውን መጽሐፍ ማጥናት ጀምሬ እንደነበር ነገርኩት። ጥናቴ ለምን እንደተቋረጠም ገለጽኩለት። ከፍሎይድ ጋር እውቀት መጽሐፍን አጥንተን ጨረስን፤ በኋላ ላይ ግን እሱም ሌላ ቦታ እንዲያገለግል ተመደበ። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ እንደገና ተቋረጠ።

ሆኖም በ2004 ግራንቪል እና ጆሹዋ የተባሉ ሁለት ልዩ አቅኚዎች በኦሪያላ እንዲያገለግሉ ተመደቡ። እነሱም ከቤት ወደ ቤት ሲያገለግሉ አገኙኝ። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እፈልግ እንደሆነ ሲጠይቁኝ ፈገግ አልኩ። እውቀት መጽሐፍን ከመጀመሪያው አንስቶ እንዲያስጠኑኝ ጠየቅኋቸው። የሚያስተምሩኝ ነገር የበፊቶቹ አስጠኚዎቼ ካስተማሩኝ ነገር ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ማረጋገጥ ፈልጌ ነበር። ግራንቪል በመንደራችን ውስጥ ስብሰባ እንደሚያደርጉ ነገረኝ። ከቤት ከወጣሁ አሥር ዓመት ገደማ ቢሆነኝም ስብሰባው ላይ መገኘት ፈለግሁ። ስለዚህ ግራንቪል ቤቴ መጣና ተሽከርካሪ ወንበር ላይ አስቀመጠኝ፤ ከዚያም እየገፋ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ወሰደኝ።

ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግራንቪል በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ ክፍል እንዳቀርብ አበረታታኝ። እንዲህ አለኝ፦ “የአካል ጉዳተኛ ብትሆንም መናገር ትችላለህ። አንድ ቀን የሕዝብ ንግግር ታቀርባለህ። ይህ እንደሚሆን አትጠራጠር።” ማበረታቻው አደፋፈረኝ።

ከግራንቪል ጋር ሆኜ አገልግሎት መውጣት ጀመርኩ። ይሁንና በመንደራችን የነበሩት ብዙዎቹ መንገዶች ወጣ ገባ ስለነበሩ ለተሽከርካሪ ወንበር አይመቹም። ስለዚህ ግራንቪልን የዕቃ ጋሪ ላይ አስቀምጦ እየገፋ እንዲወስደኝ ጠየቅሁት። ይህ ዘዴ ተስማምቶን ነበር። ሚያዝያ 2005 ተጠመቅሁ። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ ወንድሞች ስብሰባ አዳራሹ ውስጥ በጽሑፍ ክፍልና በድምፅ ክፍል እንድሠራ አሠለጠኑኝ።

የሚያሳዝነው በ2007 አባቴ ጀልባ ላይ ሳለ በገጠመው አደጋ ሕይወቱ አለፈ። ቤተሰባችን በከፍተኛ ሐዘን ተውጦ ነበር። ግራንቪል አብሮን የጸለየ ከመሆኑም ሌላ ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን አካፈለን። ከሁለት ዓመት በኋላ ደግሞ ሌላ ሐዘን ገጠመን፤ ግራንቪልም ጀልባ ላይ ሳለ በገጠመው አደጋ ሕይወቱን አጣ።

በሐዘን የተደቆሰው ትንሹ ጉባኤያችን የነበረውን አንድ ሽማግሌ አጣ፤ ጉባኤው የቀረው አንድ አገልጋይ ብቻ ነበር። ግራንቪል የምወደው ጓደኛዬ ስለነበር የእሱ ሞት በጣም ጎዳኝ። በመንፈሳዊም ሆነ በሌሎች መንገዶች ብዙ ይረዳኝ ነበር። እሱ ከሞተ በኋላ ባደረግነው ስብሰባ ላይ መጠበቂያ ግንብ እንዳነብ ተመድቤ ነበር። የመጀመሪያዎቹን ሁለት አንቀጾች እንደምንም ብዬ አነበብኩ፤ ከዚያ በኋላ ግን ማልቀስ ጀመርኩ፤ እንባዬን መቆጣጠር አልቻልኩም። ከመድረክ ከመውረድ ሌላ አማራጭ አልነበረኝም።

ወንድሞች ከሌላ ጉባኤ ወደ ኦሪያላ መጥተው ሲረዱን ቀስ በቀስ ተጽናናሁ። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ኮጆ የተባለ ልዩ አቅኚ መደበልን። እናቴና ታናሽ ወንድሜ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምሩና በኋላም ሲጠመቁ በጣም ተደሰትኩ። ከዚያም መጋቢት 2015 የጉባኤ አገልጋይ ሆኜ ተሾምኩ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ የመጀመሪያ የሕዝብ ንግግሬን አቀረብኩ። ያን ዕለት ግራንቪል ከዓመታት በፊት “አንድ ቀን የሕዝብ ንግግር ታቀርባለህ። ይህ እንደሚሆን አትጠራጠር” ያለኝን አስታወስኩና ሳቅ አልኩ፤ ዓይኔም እንባ አቀረረ።

በJW ብሮድካስቲንግ ላይ በሚተላለፉት ፕሮግራሞች አማካኝነት፣ እንደ እኔ ዓይነት ሁኔታ ያላቸውን የእምነት ባልንጀሮቼን የማየት አጋጣሚ አግኝቻለሁ። እነዚህ ክርስቲያኖች የአካል ጉዳተኛ ቢሆኑም ደስተኛና ውጤታማ ናቸው። እኔም ብሆን ማድረግ የምችላቸው ነገሮች አሉ። አቅሜ በፈቀደው መጠን ይሖዋን ለማገልገል ያለኝ ፍላጎት የዘወትር አቅኚ እንድሆን አነሳሳኝ። መስከረም 2019 ደግሞ ያልጠበቅሁት ዜና ሰማሁ! በዚያ ወር፣ 40 አስፋፊዎችን ባቀፈው ጉባኤያችን ውስጥ ሽማግሌ ሆኜ እንዳገለግል መሾሜን አወቅሁ።

መጽሐፍ ቅዱስን ላስጠኑኝና አገልግሎቴን ሳከናውን ላገዙኝ ውድ ወንድሞችና እህቶች አመስጋኝ ነኝ። ከሁሉ በላይ ግን ይሖዋን ስላልረሳኝ በጣም አመሰግነዋለሁ!

^ አን.8 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ፤ አሁን መታተም አቁሟል።