በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሁልዳ ግቧ ላይ ደረሰች

ሁልዳ ግቧ ላይ ደረሰች

ኢንዶኔዥያ ውስጥ ሳንጊር ቤሳር በምትባል ትንሽ ደሴት ላይ ሦስት እህቶቻችን ይኖራሉ። ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በባሕሩ ዳርቻ ላይ አብረው ይሠሩ ነበር። በደሴቲቱ ላይ የሚታወቁት በአገልግሎታቸው ማለትም ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ በማስተማራቸው ነው። በዚያ ወቅት ግን ለየት ያለ ሥራ እየሠሩ ነበር።

በሰሜናዊ ኢንዶኔዥያ የሚገኘው የሳንጊር ቤሳር ደሴት

በመጀመሪያ ወደ ባሕሩ በመግባት ድንጋዮችን ይሰበስባሉ። አንዳንዶቹ ድንጋዮች እግር ኳስ ያክላሉ። ከዚያም ሴቶቹ በእንጨት ዱካ ላይ ተቀምጠው ድንጋዮቹን በመዶሻ ይፈረካክሷቸዋል። ቀጥሎም ጠጠሩን በፕላስቲክ ባልዲ ውስጥ ጨምረው ብዙ ደረጃ በመውጣት ወደሚኖሩበት አካባቢ ይወስዱታል። ከዚያም ጠጠሩን በትልቅ ከረጢት ውስጥ ከትተው መኪና ላይ ይጭኑታል፤ በመጨረሻም ጠጠሩ ለመንገድ ሥራ ይውላል።

ሁልዳ የባሕሩ ዳርቻ ላይ ድንጋይ ስትሰበስብ

ከእነዚህ እህቶች አንዷ ሁልዳ ትባላለች። ያለችበት ሁኔታ ከሌሎቹ እህቶች ይበልጥ በዚህ ሥራ ረዘም ያለ ሰዓት እንድታሳልፍ ይፈቅድላታል። የምታገኘውን ገንዘብ የምትጠቀምበት ቤተሰቧን ለማስተዳደር ነው። በዚህ ወቅት የምትሠራው ግን ተጨማሪ ግብ በአእምሮዋ ይዛ ነበር። JW Library አፕሊኬሽንን ለመጠቀም ታብሌት መግዛት ፈልጋ ነበር። ሁልዳ አፕሊኬሽኑ ላይ የሚገኙት ቪዲዮዎችና ሌሎች ጽሑፎች ለአገልግሎት እንደሚጠቅሟትና መጽሐፍ ቅዱስን በተሻለ መንገድ ለመረዳት እንደሚያግዟት ተሰምቷት ነበር።

ሁልዳ ለአንድ ወር ተኩል ያህል በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ለሁለት ሰዓት ይህን ሥራ ታከናውን ነበር፤ በዚህ መንገድ አንድ አነስተኛ የጭነት መኪና የሚሞላ ድንጋይ መከስከስ ቻለች። በስተ መጨረሻ ታብሌት ለመግዛት የሚበቃ ገንዘብ አገኘች።

ሁልዳ ታብሌቷን ይዛ

ሁልዳ እንዲህ ብላለች፦ “ለረጅም ሰዓት ድንጋይ በመከስከሴ ሰውነቴ ደክሞና ዝሎ ነበር፤ ሆኖም አዲሱ ታብሌት በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆንና ለስብሰባዎች በቀላሉ ለመዘጋጀት እንዳስቻለኝ ሳይ ሕመሜንና ድካሜን ወዲያውኑ ረሳሁት።” በተጨማሪም ወረርሽኙ በጀመረበት ወቅት ሁሉም የጉባኤ እንቅስቃሴዎች የሚካሄዱት በቪዲዮ ኮንፈረንስ ስለነበር ታብሌቷ በእጅጉ እንደጠቀማት ተናግራለች። ሁልዳ ግቧ ላይ በመድረሷ በጣም ተደስተናል።