በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

በይሖዋ በመታመኔ ተረጋግቼ መኖር ችያለሁ

በይሖዋ በመታመኔ ተረጋግቼ መኖር ችያለሁ

ሰዎች ስለ ሕይወቴ ሲጠይቁኝ ብዙውን ጊዜ “እኔ በይሖዋ እጅ ያለሁ ሻንጣ ነኝ” እላቸዋለሁ። እንዲህ ስል፣ ሻንጣዬን ወደፈለግኩበት ቦታ እንደምወስደው ሁሉ ይሖዋና ድርጅቱ መቼና ወዴት መሄድ እንዳለብኝ እንዲመሩኝ እፈልጋለሁ ማለቴ ነው። ተፈታታኝ፣ አንዳንድ ጊዜም አደገኛ የሆኑ የአገልግሎት ምድቦችን ተቀብያለሁ። ሆኖም ተረጋግቶ ለመኖር ቁልፉ በይሖዋ መታመን እንደሆነ ተምሬያለሁ።

በይሖዋ መታመን የጀመርኩበት መንገድ

በ1948 በደቡብ ምዕራባዊ ናይጄርያ በምትገኝ አንዲት ትንሽ መንደር ውስጥ ተወለድኩ። በዚያ ወቅት የአባቴ ታናሽ ወንድም የሆነው አጎቴ ሙስጠፋ ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ፤ በኋላም ታላቅ ወንድሜ ዋሃቢ ተጠመቀ። የዘጠኝ ዓመት ልጅ ሳለሁ አባቴ ሞተ። በዚህ ጊዜ በሐዘን ተዋጥኩ። ዋሃቢ አባባን በትንሣኤ ዳግመኛ እንደምናገኘው ነገረኝ። ይህ የሚያጽናና ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት እንድጀምር አነሳሳኝ። በ1963 ተጠመቅኩ። ሌሎች ሦስት ወንድሞቼም ተጠመቁ።

በ1965 በሌጎስ ከሚኖረው ከታላቅ ወንድሜ ከዊልሰን ጋር መኖር ጀመርኩ። በዚያም በኢግቦቢ ጉባኤ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች የዘወትር አቅኚዎች ጋር ተቀራረብኩ። ደስታቸውና ቅንዓታቸው ልቤን ነካው። ከዚያም ጥር 1968 እኔም በአቅኚነት ማገልገል ጀመርኩ።

በቤቴል የሚያገለግል አልበርት ኦሉግቤቢ የተባለ ወንድም ከወጣቶች ጋር ልዩ ስብሰባ በማካሄድ በሰሜናዊ ናይጄርያ ልዩ አቅኚዎች እንደሚያስፈልጉ ነገረን። ወንድም ኦሉግቤቢ በግለት ያቀረበልንን ግብዣ እስካሁን አስታውሰዋለሁ። “እናንተ ወጣቶች ናችሁ። ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ለይሖዋ አገልግሎት ማዋል ትችላላችሁ። መስኩ ክፍት ነው” አለን። እንደ ነቢዩ ኢሳይያስ ዓይነት የፈቃደኝነት መንፈስ ለማሳየት ስለጓጓሁ ማመልከቻ አስገባሁ።—ኢሳ. 6:8

ግንቦት 1968 በሰሜናዊ ናይጄርያ በሚገኘው በካኖ ከተማ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። ይህ የሆነው ከ1967 እስከ 1970 በተካሄደው በቢያፍራ ጦርነት ወቅት ነበር። ጦርነቱ በሰሜናዊ ናይጄርያ ዘግናኝ እልቂትና መከራ ካስከተለ በኋላ ወደ ምሥራቃዊ ናይጄርያ ተሻገረ። አንድ ወንድም በአሳቢነት ተነሳስቶ ወደዚያ አካባቢ እንዳልሄድ ሊያሳምነኝ ሞከረ። እኔ ግን “ስለ አሳቢነትህ አመሰግናለሁ። ሆኖም ይሖዋ በዚህ ምድብ እንዳገለግለው ከፈለገ ከጎኔ እንደማይለይ አልጠራጠርም” አልኩት።

በጦርነት በታመሰ አካባቢ ውስጥ በይሖዋ መታመን

በካኖ የነበረው ሁኔታ ልብ የሚሰብር ነበር። የእርስ በርስ ጦርነቱ ይህን ትልቅ ከተማ አውድሞታል። አንዳንድ ጊዜ አገልግሎት ላይ ሳለን በጦርነቱ ምክንያት የተገደሉ ሰዎችን አስከሬን እናይ ነበር። በካኖ በርካታ ጉባኤዎች የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ወንድሞች ሸሽተው ነበር። በዚያ የቀሩት 15 የማይሞሉ አስፋፊዎች ነበሩ፤ እነሱም በፍርሃትና በተስፋ መቁረጥ ተውጠው ነበር። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ስድስት ልዩ አቅኚዎች ሲመደቡላቸው በጣም ተደሰቱ። አስፋፊዎቹ ለሰጠናቸው ማበረታቻ በጎ ምላሽ ሰጡ። በድጋሚ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች አዘውትረው መካፈላቸውን እንዲሁም የመስክ አገልግሎት ሪፖርታቸውንና የጽሑፍ ትእዛዛቸውን ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው መላካቸውን እንዲቀጥሉ ረዳናቸው።

በዚያ የምናገለግለው ልዩ አቅኚዎች የሃውሳ ቋንቋን መማር ጀመርን። ብዙዎቹ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ስንናገር ሲሰሙ በጥሞና ያዳምጡን ነበር። ሆኖም በአካባቢው ሰፊ ተቀባይነት የነበረው ሃይማኖት አባላት ለስብከቱ ሥራችን ጥሩ አመለካከት አልነበራቸውም። ስለዚህ በጣም መጠንቀቅ ነበረብን። በአንድ ወቅት አንድ ሰው እኔንና የአገልግሎት ጓደኛዬን ቢላ ይዞ አሳዶናል። ደግነቱ ሮጠን አመለጥነው። አደገኛ ሁኔታዎች ቢኖሩም ይሖዋ ‘ተረጋግተን እንድንኖር’ አድርጎናል። (መዝ. 4:8) የአስፋፊዎቹ ቁጥርም ማደግ ጀመረ። በአሁኑ ወቅት ካኖ ውስጥ በ11 ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉ ከ500 በላይ አስፋፊዎች አሉ።

በኒጀር ተቃውሞን መጋፈጥ

በኒያሜ፣ ኒጀር ልዩ አቅኚ ሆኜ ሳገለግል

በካኖ ለጥቂት ወራት ካገለገልኩ በኋላ ነሐሴ 1968 ከሁለት ሌሎች ልዩ አቅኚዎች ጋር የኒጀር ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኒያሜ ተላክሁ። በምዕራባዊ አፍሪካ የምትገኘው ኒጀር በምድር ላይ ካሉት እጅግ ሞቃታማ ቦታዎች አንዷ መሆኗን ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብን። ሙቀቱ ካስከተለብን ተፈታታኝ ሁኔታ በተጨማሪ የአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ የሆነውን ፈረንሳይኛን መማር ነበረብን። እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩም በይሖዋ በመታመን በዚያ ካሉት ጥቂት አስፋፊዎች ጋር ሆነን በመዲናዋ መስበክ ጀመርን። በአጭር ጊዜ ውስጥ፣ ኒያሜ ውስጥ ያሉ ማንበብ የሚችሉ ሰዎች በሙሉ ማለት ይቻላል ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራው እውነት የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ማስጠኛ መጽሐፍ ደረሳቸው። እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች መጽሐፉን እንድንሰጣቸው ሲሉ እኛን ፈልገው ይመጡ ነበር።

ብዙም ሳይቆይ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት ለይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ አመለካከት እንደሌላቸው ተገነዘብን። ሐምሌ 1969 በአገሪቱ ውስጥ የመጀመሪያውን የወረዳ ስብሰባ ለማካሄድ ተሰበሰብን። በስብሰባው ላይ 20 ገደማ ሰዎች ተገኝተው ነበር። ሁለት ተጠማቂዎችም ነበሩ። ይሁንና በስብሰባው የመጀመሪያ ቀን ላይ ፖሊሶች መጥተው ስብሰባውን አስቆሙ። ልዩ አቅኚዎቹንና የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷቸው። ምርመራ ካደረጉብን በኋላ በማግስቱ ወደ ጣቢያው እንድንመለስ አዘዙን። ችግር ሊፈጠር እንደሚችል ስለጠረጠርን የጥምቀት ንግግሩ በአንድ ግለሰብ ቤት እንዲቀርብ ካደረግን በኋላ ተጠማቂዎቹን በአንድ ወንዝ ውስጥ በድብቅ አጠመቅናቸው።

ከተወሰኑ ሳምንታት በኋላ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴሩ እኔንና ሌሎች አምስት ልዩ አቅኚዎችን ከአገሪቱ አባረረን። አገሪቱን ለቀን ለመውጣት 48 ሰዓት ሰጡን፤ ደግሞም የራሳችንን መጓጓዣ ማመቻቸት ነበረብን። እኛም ትእዛዛቸውን ተከትለን ከአገሪቱ በመውጣት በቀጥታ በናይጄርያ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ አመራን። በዚያም አዲስ ምድብ ተሰጠን።

በናይጄርያ በምትገኝ ኦሪሱንባሪ የምትባል መንደር እንዳገለግል ተመደብኩ። እዚያ ከሚኖሩት ጥቂት አስፋፊዎች ጋር ፍሬያማ አገልግሎት ማከናወን ችያለሁ። ሆኖም ከስድስት ወር በኋላ ቅርንጫፍ ቢሮው ብቻዬን ወደ ኒጀር እንድመለስ ጠየቀኝ። መጀመሪያ ላይ የደነገጥኩና የፈራሁ ቢሆንም በኒጀር ያሉትን ወንድሞች በድጋሚ ለማግኘት ጓጉቼ ነበር።

ወደ ኒያሜ ተመለስኩ። እዚያ በደረስኩ በማግስቱ አንድ ናይጄርያዊ ነጋዴ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ስላወቀ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥያቄዎችን ይጠይቀኝ ጀመር። ሰውየው ጥናት ጀመረ፤ ከዚያም የሲጋራና የመጠጥ ሱሱን ካሸነፈ በኋላ ተጠመቀ። ከዚያ በኋላ በኒጀር የተለያዩ ክፍሎች መስበክና በአገሪቱ ያሉት አስፋፊዎች ቁጥር ቀስ በቀስ ሲያድግ ማየት ችያለሁ። እዚያ በደረስኩበት ወቅት በአገሪቱ የነበሩት አስፋፊዎች 31 ነበሩ፤ ከአገሪቱ በወጣሁበት ጊዜ ግን 69 ደርሰው ነበር።

“በጊኒ ስለሚከናወነው የመንግሥቱ ሥራ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም”

በ1977 መገባደጃ ላይ ሥልጠና ለመውሰድ ወደ ናይጄርያ ተመለስኩ። በሦስት ሳምንቱ ሥልጠና ማብቂያ ላይ የቅርንጫፍ ኮሚቴው አስተባባሪ የሆነው ወንድም ማልኮም ቪጎ ከሴራ ሊዮን ቅርንጫፍ ቢሮ የተላከ ደብዳቤ አስነበበኝ። ወንድሞች ጊኒ ውስጥ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ የሚያገለግል እንግሊዝኛና ፈረንሳይኛ የሚችል ጤናማ የሆነ ነጠላ አቅኚ እየፈለጉ ነበር። ወንድም ቪጎ ሥልጠና የወሰድኩት ለዚህ ምድብ እንደሆነ ነገረኝ። ምድቡ ቀላል እንደማይሆን አጽንኦት ሰጥቶ አስረዳኝ። “ምድቡን ከመቀበልህ በፊት በደንብ አስብበት” ብሎ መከረኝ። እኔም ወዲያውኑ “የላከኝ ይሖዋ እስከሆነ ድረስ እሄዳለሁ” አልኩት።

በአውሮፕላን ወደ ሴራ ሊዮን ሄጄ በቅርንጫፍ ቢሮው ካሉ ወንድሞች ጋር ተገናኘሁ። አንደኛው የቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል “በጊኒ ስለሚከናወነው የመንግሥቱ ሥራ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም” አለኝ። አጎራባች አገር በሆነችው በጊኒ የሚካሄደውን የመንግሥቱን ሥራ የሚከታተለው የሴራ ሊዮን ቅርንጫፍ ቢሮ ቢሆንም እዚያ ባለው አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ የተነሳ ቅርንጫፍ ቢሮው ከአስፋፊዎቹ ጋር መረጃ መለዋወጥ አልቻለም። በተጨማሪም ቅርንጫፍ ቢሮው ወደ አገሪቱ ተወካይ ለመላክ በተደጋጋሚ ጥረት ቢያደርግም አልተሳካለትም። በመሆኑም የጊኒ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ኮናክሪ ሄጄ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንድሞክር ጠየቁኝ።

“የላከኝ ይሖዋ እስከሆነ ድረስ እሄዳለሁ”

ኮናክሪ ስደርስ ወደ ናይጄርያ ኤምባሲ ሄጄ ከአምባሳደሩ ጋር ተገናኘሁ። ለአምባሳደሩ ጊኒ ውስጥ የመስበክ ፍላጎት እንዳለኝ ነገርኩት። እሱም ልታሰር ወይም የከፋ ነገር ሊደርስብኝ ስለሚችል እዚያ እንዳልቆይ አጥብቆ አሳሰበኝ። “ወደ ናይጄርያ ተመልሰህ እዚያ ስበክ” አለኝ። እኔም “እዚህ ለመቆየት ወስኛለሁ” አልኩት። ስለዚህ የጊኒ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትር አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግልኝ የሚጠይቅ ደብዳቤ ጻፈልኝ፤ ሚኒስትሩም ጥሩ አቀባበል አደረገልኝ።

ብዙም ሳይቆይ በሴራ ሊዮን ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተመልሼ የሚኒስትሩን ውሳኔ ለወንድሞች ነገርኳቸው። ወንድሞች ይሖዋ ጉዞዬን እንዳሳካልኝ ሲሰሙ በደስታ ፈነጠዙ። ጊኒ ውስጥ የመኖሪያ ፈቃድ አገኘሁ።

በሴራ ሊዮን በወረዳ ሥራ ስካፈል

ከ1978 እስከ 1989 ባሉት ዓመታት በጊኒና በሴራ ሊዮን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት፣ በላይቤሪያ ደግሞ በተተኪ የወረዳ የበላይ ተመልካችነት አገልግያለሁ። መጀመሪያ አካባቢ፣ ብዙ ጊዜ እታመም ነበር። አንዳንድ ጊዜም የምታመመው ከከተማ ርቀው በሚገኙ አካባቢዎች ሆኜ ነው። ሆኖም ወንድሞች እኔን ሆስፒታል ለመውሰድ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ያደርጉ ነበር።

በአንድ ወቅት ከባድ የወባ በሽታና የአንጀት ትል ይዞኝ ነበር። ካገገምኩ በኋላ፣ ወንድሞች የት እንቅበረው የሚለውን ሲወያዩ እንደነበረ ሰማሁ። ሕይወቴን አደጋ ላይ የሚጥሉ እንዲህ ያሉ ችግሮች ቢያጋጥሙኝም ምድቤን ስለመተው ጨርሶ አስቤ አላውቅም። አሁንም ቢሆን፣ በዘላቂነት ተረጋግተን መኖር የምንችለው ከሞት ሊያስነሳን በሚችለው አምላክ ከታመንን ብቻ እንደሆነ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።

በትዳር ሕይወት በይሖዋ መታመን

በ1988 በሠርጋችን ዕለት

በ1988 ዶርካስ ከተባለች በጣም ትሑትና መንፈሳዊ የሆነች አቅኚ ጋር ተዋወቅኩ። ከእሷ ጋር ተጋባን፤ ከዚያም በወረዳ ሥራ አብረን መካፈል ጀመርን። ዶርካስ አፍቃሪና የራሷን ጥቅም መሥዋዕት የምታደርግ ሚስት ሆናልኛለች። ከአንዱ ጉባኤ ወደ ቀጣዩ ጉባኤ ስንሄድ ሻንጣችንን ተሸክመን 25 ኪሎ ሜትር ያህል በእግራችን እንጓዝ ነበር። ሩቅ ወደሆኑ ጉባኤዎች ስንሄድ ደግሞ በተቆፋፈሩ የጭቃ መንገዶች ላይ ያገኘነውን መጓጓዣ ተጠቅመን እንጓዝ ነበር።

ዶርካስ በጣም ደፋር ነች። ለምሳሌ አንዳንድ ጊዜ በአዞ የተሞሉ ወንዞችን ማቋረጥ ይጠበቅብን ነበር። በአንድ ወቅት አምስት ቀን የሚፈጅ ጉዞ እያደረግን ሳለን ወንዙን ለመሻገር የሚያገለግለው የእንጨት ድልድይ በመሰበሩ በታንኳ ለመሻገር ተገደድን። ዶርካስ ከታንኳው ለመውረድ ስትቆም ወንዙ ውስጥ ወደቀች። ሁለታችንም መዋኘት አንችልም። ወንዙ ውስጥ ደግሞ አዞዎች ነበሩ። ደግነቱ የተወሰኑ ወጣቶች ወንዙ ውስጥ ዘለው በመግባት ዶርካስን አወጧት። ሁለታችንም ለተወሰነ ጊዜ ያህል ያ ክስተት ሌሊት ያቃዠን ነበር። ሆኖም በምድባችን ማገልገላችንን ቀጠልን።

ልጆቻችን ጃህጊፍት እና ኤሪክ የይሖዋ ስጦታ እንደሆኑ ይሰማናል

በ1992 መጀመሪያ አካባቢ ዶርካስ ማርገዟን ስናውቅ በጣም ደነገጥን። “የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችንን በዚሁ ልናቆም ነው ማለት ነው?” ብለን አሰብን። “ይሖዋ ስጦታ ሰጥቶናል” ብለን ስለደመደምን ለልጃችን ጃህጊፍት የሚል ስም አወጣንላት። ጃህጊፍት ከተወለደች ከአራት ዓመት በኋላ ወንድሟ ኤሪክ ተከተለ። በእርግጥም ሁለቱም ልጆቻችን የይሖዋ ስጦታ እንደሆኑ ይሰማናል። ጃህጊፍት በኮናክሪ በሚገኘው የርቀት የትርጉም ቢሮ ውስጥ ለተወሰነ ጊዜ አገልግላለች፤ ኤሪክ ደግሞ የጉባኤ አገልጋይ ነው።

ዶርካስ ከጊዜ በኋላ በልዩ አቅኚነት ማገልገሏን ብታቆምም ልጆቻችንን በምናሳድግበት ጊዜም የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገሏን ቀጥላለች። እኔ ደግሞ በይሖዋ እርዳታ በልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈሌን ቀጠልኩ። ልጆቻችን ካደጉ በኋላ ዶርካስ በድጋሚ በልዩ አቅኚነት ማገልገል ቻለች። አሁን ሁለታችንም ኮናክሪ ውስጥ የመስክ ሚስዮናውያን ሆነን እያገለገልን ነው።

እውነተኛ መታመኛ

እስካሁን ድረስ ይሖዋ ወደወሰደኝ ሁሉ ስሄድ ቆይቻለሁ። እኔና ባለቤቴ የእሱን ጥበቃና በረከት በተደጋጋሚ ተመልክተናል። በይሖዋ በመታመናችን በቁሳዊ ነገሮች የሚታመኑ ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ብዙ መከራዎች መዳን ችለናል። እኔና ዶርካስ እውነተኛው መታመኛ “አዳኝ አምላካችን” የሆነው ይሖዋ እንደሆነ በሕይወታችን ተመልክተናል። (1 ዜና 16:35) በእሱ የሚታመኑ ሁሉ ሕይወታቸው “በይሖዋ ዘንድ በደንብ በታሰረ የሕይወት ከረጢት ውስጥ” እንደምትቀመጥ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ነኝ።—1 ሳሙ. 25:29