በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 47

እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

እርስ በርስ ያለንን ፍቅር ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው?

“እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው።”—1 ዮሐ. 4:7

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

ማስተዋወቂያ a

1-2. (ሀ) ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ፍቅር ‘ከሁሉ የሚበልጥ’ ባሕርይ እንደሆነ የተናገረው ለምንድን ነው? (ለ) የትኞቹን ጥያቄዎች እንመልሳለን?

 ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ እምነት፣ ተስፋ እና ፍቅር ከተናገረ በኋላ “ከእነዚህ [ባሕርያት] መካከል የሚበልጠው ግን ፍቅር ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 13:13) ጳውሎስ ይህን ያለው ለምንድን ነው? ወደፊት፣ አምላክ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ በገባው ቃል ላይ እምነት ማሳደር ወይም ቃሉ እንደሚፈጸም ተስፋ ማድረግ አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም ያኔ ተስፋው ተፈጽሟል። ሆኖም ለይሖዋና ለሕዝቡ ምንጊዜም ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል። እንዲያውም ለእነሱ ያለን ፍቅር ለዘላለም እየጨመረ ይሄዳል።

2 ምንጊዜም ፍቅር ማሳየት የሚያስፈልገን ከመሆኑ አንጻር ለሦስት ጥያቄዎች መልስ እንሰጣለን። አንደኛ፣ እርስ በርስ መዋደድ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ሁለተኛ፣ አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ሦስተኛ፣ ፍቅራችን ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

እርስ በርስ መዋደድ የሚኖርብን ለምንድን ነው?

3. እርስ በርስ ለመዋደድ የሚያነሳሱን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

3 እርስ በርስ መዋደዳችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ፍቅር እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን የሚያሳይ መለያ ስለሆነ ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:35) ከዚህም ሌላ፣ እርስ በርስ መዋደዳችን አንድነት እንዲኖረን ያደርጋል። ጳውሎስ “ፍቅር ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ ነው” ብሏል። (ቆላ. 3:14) ሆኖም እርስ በርስ እንድንዋደድ የሚያነሳሳን ሌላም አስፈላጊ ምክንያት አለ። ሐዋርያው ዮሐንስ ለእምነት አጋሮቹ “አምላክን የሚወድ ሁሉ ወንድሙንም መውደድ ይገባዋል” በማለት ጽፎላቸዋል። (1 ዮሐ. 4:21) እርስ በርስ ስንዋደድ አምላክን እንደምንወደው እናሳያለን።

4-5. ለአምላክ ያለን ፍቅር እርስ በርስ ካለን ፍቅር ጋር የሚያያዘው እንዴት እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ።

4 ለአምላክ ያለን ፍቅር ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ካለን ፍቅር ጋር በጥብቅ የሚያያዘው እንዴት ነው? ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ በልባችንና በሌሎቹ የአካላችን ክፍሎች መካከል ያለውን ዝምድና ለማሰብ ሞክር። አንድ ሐኪም ክርናችንን ይዞ የልብ ምታችን ጠንካራ ወይም ደካማ መሆኑን በማየት ስለ ልባችን ጤንነት የተወሰነ መረጃ ማግኘት ይችላል። ይህ ምሳሌ ከፍቅር ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው?

5 አንድ ሐኪም የልብ ምታችንን በማየት ስለ ልባችን ጤንነት የተወሰነ መረጃ ማግኘት እንደሚችለው ሁሉ እኛም ለሌሎች ያለንን ፍቅር በማየት ለአምላክ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ማወቅ እንችላለን። ለእምነት አጋሮቻችን ያለን ፍቅር በተወሰነ መጠን እንደቀነሰ ካስተዋልን ይህ ሁኔታ ለአምላክ ያለን ፍቅርም እንደቀነሰ ሊያሳይ ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ለእምነት አጋሮቻችን አዘውትረን ፍቅር ማሳየታችን ለአምላክ ያለን ፍቅር ጠንካራ እንደሆነ ይጠቁማል።

6. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እየቀነሰ ከሆነ ጉዳዩ ሊያሳስበን የሚገባው ለምንድን ነው? (1 ዮሐንስ 4:7-9, 11)

6 ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እየቀነሰ ከሄደ ጉዳዩ ሊያሳስበን ይገባል። ለምን? ምክንያቱም በመንፈሳዊ አደጋ ላይ ነን ማለት ነው። ሐዋርያው ዮሐንስ “ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም” በማለት አደጋውን በግልጽ ጠቁሞናል። (1 ዮሐ. 4:20) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ የሚደሰትብን ‘እርስ በርሳችን የምንዋደድ’ ከሆነ ብቻ ነው።—1 ዮሐንስ 4:7-9, 11ን አንብብ።

አንዳችን ለሌላው ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

7-8. አንዳችን ለሌላው ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

7 በአምላክ ቃል ውስጥ ብዙ ቦታዎች ላይ ‘እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ’ የሚለውን ትእዛዝ እናገኛለን። (ዮሐ. 15:12, 17፤ ሮም 13:8፤ 1 ተሰ. 4:9፤ 1 ጴጥ. 1:22፤ 1 ዮሐ. 4:11) ሆኖም ፍቅር በልባችን ውስጥ ያለ ስሜት ነው፤ ልባችንን ደግሞ ማንም ሰው ከፍቶ ማየት አይችልም። ታዲያ አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር እንዲታይ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በንግግራችንና በድርጊታችን ነው።

8 ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንዳንድ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት። “እርስ በርሳችሁ እውነትን ተነጋገሩ።” (ዘካ. 8:16) “እርስ [በርሳችሁ] ሰላም ይኑራችሁ።” (ማር. 9:50) “አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።” (ሮም 12:10) “አንዳችሁ ሌላውን ተቀበሉ።” (ሮም 15:7) “እርስ በርስ . . . ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” (ቆላ. 3:13) “አንዳችሁ የሌላውን ከባድ ሸክም ተሸከሙ።” (ገላ. 6:2) “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።” (1 ተሰ. 4:18) “እርስ በርስ ተናነጹ።” (1 ተሰ. 5:11) “አንዳችሁ ለሌላው ጸልዩ።”—ያዕ. 5:16

የተጨነቀ የእምነት አጋራችንን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 7-9⁠ን ተመልከት)

9. ሌሎችን ማጽናናት አስፈላጊ የፍቅር መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው? (ሥዕሉንም ተመልከት።)

9 ባለፈው አንቀጽ ላይ ከተጠቀሱት ፍቅራችንን የምናሳይባቸው መንገዶች አንዱን እስቲ በጥልቀት እንመርምር። ጳውሎስ “ሁልጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ” በማለት በሰጠው ማበረታቻ ላይ እናተኩራለን። ሌሎችን ማጽናናት አስፈላጊ የፍቅር መግለጫ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሣከሪያ እንደገለጸው፣ ጳውሎስ የተጠቀመበት “ማጽናናት” የሚለው ቃል “አንድ ሰው ከባድ ፈተና ሲያጋጥመው ከጎኑ ቆሞ እሱን ማበረታታት” የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ማጽናኛ በመስጠት በጭንቀት የተዋጠ የእምነት አጋራችን ተነስቶ በሕይወት መንገድ ላይ መጓዙን እንዲቀጥል እንረዳዋለን። አንድ ወንድማችንን ወይም እህታችንን ባጽናናን ቁጥር ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን።—2 ቆሮ. 7:6, 7, 13

10. በርኅራኄ እና በማጽናኛ መካከል ምን ተያያዥነት አለ?

10 ርኅራኄ እና ማጽናኛ በጥብቅ የተቆራኙ ነገሮች ናቸው። በምን መንገድ? ሩኅሩኅ ሰው ሌሎችን ለማጽናናትና መከራቸውን ለማቅለል ይነሳሳል። ስለዚህ ርኅራኄ ካለን ሌሎችን ለማጽናናት እንነሳሳለን። ጳውሎስ የይሖዋን ርኅራኄ ከሚሰጠው ማጽናኛ ጋር ያያያዘው እንዴት እንደሆነ ልብ በል። ጳውሎስ፣ ይሖዋ “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” እንደሆነ ገልጿል። (2 ቆሮ. 1:3 ግርጌ) ይሖዋ “ከርኅራኄ የመነጨ ምሕረት አባት” የተባለው የርኅራኄ ምንጭ እሱ ስለሆነ ነው። ይህ ርኅራኄው ደግሞ “በሚደርስብን መከራ ሁሉ” እንዲያጽናናን ያነሳሳዋል። (2 ቆሮ. 1:4) ከምንጭ የሚፈልቅ ንጹሕ ውኃ የተጠሙ ሰዎችን እንደሚያረካ ሁሉ ይሖዋም የተጨነቁ ሰዎችን ያጽናናል። ለሌሎች በመራራትና እነሱን በማጽናናት ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ማጽናኛ ለመስጠት የሚያነሳሱ ባሕርያትን በልባችን ውስጥ በማዳበር ነው። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

11. በቆላስይስ 3:12 እና በ⁠1 ጴጥሮስ 3:8 መሠረት ሌሎችን ለማጽናናት የሚያነሳሳ ፍቅር እንዲኖረን የትኞቹን ባሕርያት ማዳበር ያስፈልገናል?

11 ‘ሁልጊዜ እርስ በርስ ለመጽናናት’ የሚያነሳሳ ፍቅር እንዲኖረን ምን ይረዳናል? የሌላውን ስሜት መረዳት እንዲሁም የወንድማማች መዋደድንና ደግነትን የመሳሰሉ ባሕርያትን ማዳበር ይኖርብናል። (ቆላስይስ 3:12፤ 1 ጴጥሮስ 3:8ን አንብብ።) እነዚህ ባሕርያት የሚረዱን እንዴት ነው? ርኅራኄ እና ተመሳሳይ ባሕርያት የማንነታችን ክፍል ከሆኑ የተጨነቁ ሰዎችን እንድናጽናና ውስጣችን ይገፋፋናል። ኢየሱስ እንዳለው “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና። ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል።” (ማቴ. 12:34, 35) በእርግጥም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማጽናናት ለእነሱ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ወሳኝ መንገድ ነው።

በመካከላችን ያለው ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

12. (ሀ) መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) የትኛውን ጥያቄ እንመልሳለን?

12 ሁላችንም ‘እርስ በርስ መዋደዳችንን መቀጠል’ እንፈልጋለን። (1 ዮሐ. 4:7) ሆኖም ኢየሱስ “የብዙዎች ፍቅር ይቀዘቅዛል” የሚል ማስጠንቀቂያ እንደሰጠ ማስታወስ ይኖርብናል። (ማቴ. 24:12) ኢየሱስ ይህን ሲል የአብዛኞቹ ደቀ መዛሙርቱ ፍቅር እንደሚቀዘቅዝ መናገሩ አልነበረም። ያም ቢሆን፣ በምንኖርበት ዓለም ውስጥ ፍቅር መጥፋቱ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን ልንጠነቀቅ ይገባል። ይህን ሐሳብ በአእምሯችን በመያዝ የሚከተለውን ጥያቄ ለመመለስ እንሞክር፦ ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር ጠንካራ መሆኑን መፈተን የምንችልበት መንገድ አለ?

13. ፍቅራችን በምን ሊፈተን ይችላል?

13 ፍቅራችን ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ መፈተን የምንችልበት አንዱ መንገድ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን አንዳንድ ሁኔታዎች እንዴት እንደምንይዝ መገምገም ነው። (2 ቆሮ. 8:8) ሐዋርያው ጴጥሮስ ከእነዚህ ሁኔታዎች መካከል አንዱን ሲጠቅስ እንዲህ ብሏል፦ “ከሁሉም በላይ አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ፤ ምክንያቱም ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።” (1 ጴጥ. 4:8) በመሆኑም የሌሎች ድክመትና አለፍጽምና ፍቅራችንን ሊፈትነው ይችላል።

14. በ⁠1 ጴጥሮስ 4:8 መሠረት የሚያስፈልገን ምን ዓይነት ፍቅር ነው? አብራራ።

14 እስቲ የጴጥሮስን ቃላት በጥልቀት እንመርምር። ቁጥር 8 መጀመሪያ ላይ፣ ምን ዓይነት ፍቅር ሊኖረን እንደሚገባ ሲገልጽ “የጠለቀ ፍቅር” ይላል። ጴጥሮስ የተጠቀመበት “የጠለቀ” የሚለው ቃል ቀጥተኛ ትርጉሙ “የተለጠጠ” የሚል ነው። የጥቅሱ ሁለተኛ ክፍል ደግሞ የጠለቀ ፍቅር የሚያስገኘውን ውጤት ይገልጻል። የወንድሞቻችንን ኃጢአት ይሸፍናል። ነገሩን በምሳሌ ለማስረዳት፣ ፍቅራችንን በሁለት እጃችን እንደያዝነው የሚለጠጥ ጨርቅ አድርገን ልንቆጥረው እንችላለን። ፍቅራችን አንድ ወይም ሁለት ኃጢአቶችን ብቻ ሳይሆን ‘ብዙ ኃጢአቶችን’ እስኪሸፍን ድረስ እንለጥጠዋለን ማለት ነው። ‘መሸፈን’ የሚለው ቃል ይቅር ማለትን የሚያመለክት ጥሩ ዘይቤያዊ አገላለጽ ነው። አንድ ጨርቅ ቆሻሻን እንደሚሸፍን ሁሉ ፍቅርም የሌሎችን ድክመትና አለፍጽምና ይሸፍናል።

15. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር ጠንካራ ከሆነ ምን ማድረግ እንችላለን? (ቆላስይስ 3:13)

15 በጣም ከባድ በሚሆንበት ጊዜም ጭምር የእምነት አጋሮቻችንን አለፍጽምና ይቅር ለማለት የሚያስችል ጠንካራ ፍቅር ሊኖረን ይገባል። (ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።) ሌሎችን ይቅር ካልን ፍቅራችን ጠንካራ እንደሆነ እንዲሁም ይሖዋን ማስደሰት እንደምንፈልግ እናሳያለን። ወንድሞቻችን ያሏቸውን የሚያበሳጩ ባሕርያትና ስህተቶቻቸውን ችላ ብለን ለማለፍ ሌላስ ምን ሊረዳን ይችላል?

ጥሩ ጥሩዎቹን ፎቶግራፎች አስቀምጠን የቀረውን እንደምናጠፋ ሁሉ ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያለንን መልካም ትዝታ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን፤ መጥፎውን ግን ከአእምሯችን እናጠፋዋለን (ከአንቀጽ 16-17⁠ን ተመልከት)

16-17. የሌሎችን አነስተኛ ስህተቶች ችላ ብለን ለማለፍ የሚረዳን ሌላስ ምን ነገር አለ? በምሳሌ አስረዳ። (ሥዕሉንም ተመልከት።)

16 በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ መጥፎ ጎን ላይ ሳይሆን በመልካም ጎናቸው ላይ አተኩሩ። እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ከተወሰኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር ተሰብስባችሁ እየተጫወታችሁ ነው እንበል። በጣም ጥሩ ጊዜ አሳልፋችሁ ልትለያዩ ስትሉ አንድ ላይ ፎቶ ትነሳላችሁ። ፎቶውን ስታነሱ ለማንኛውም ብላችሁ ሁለት ተጨማሪ ፎቶዎችን አነሳችሁ። በድምሩ ሦስት ፎቶዎች አንስታችኋል ማለት ነው። አንደኛው ፎቶ ላይ አንድ ወንድም እንደተኮሳተረ አስተዋላችሁ። ይህን ፎቶ ምን ታደርጉታላችሁ? ፎቶውን ታጠፉታላችሁ፤ ምክንያቱም በሌሎቹ ሁለት ፎቶዎች ላይ ይህን ወንድም ጨምሮ ሁሉም ሰው ፈገግ ብሏል።

17 የምናስቀምጣቸውን ፎቶግራፎች በአእምሯችን ከምንይዛቸው ትዝታዎች ጋር ልናመሳስላቸው እንችላለን። ብዙውን ጊዜ፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ጊዜ ስናሳልፍ ጥሩ ትዝታ ይኖረናል። ሆኖም በአንድ ወቅት አንድ ወንድማችን ወይም እህታችን ደግነት የጎደለው ነገር ቢያደርጉ ወይም ቢናገሩስ? ይህን ትዝታ ምን ልናደርገው ይገባል? አንደኛውን ፎቶ እንደሰረዝነው ሁሉ ይህን ትዝታ ከአእምሯችን ብናጠፋው የተሻለ አይሆንም? (ምሳሌ 19:11፤ ኤፌ. 4:32) ወንድማችን የሠራውን አነስተኛ ስህተት ከአእምሯችን ልናጠፋው እንችላለን፤ ምክንያቱም ከዚያ ግለሰብ ጋር ብዙ አስደሳች ትዝታዎች አሉን። አእምሯችን ውስጥ መያዝ የምንፈልገው እንዲህ ያሉትን ትዝታዎች ነው።

በተለይ በአሁኑ ጊዜ ፍቅር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18. በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ ፍቅር የትኞቹን ዋና ዋና ነጥቦች ተመልክተናል?

18 አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው? እስካሁን እንደተመለከትነው ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ካሳየን ይሖዋን እንደምንወደው እናሳያለን። ለእምነት አጋሮቻችን ያለንን ፍቅር የምናሳየው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ እነሱን ማጽናናት ነው። ርኅራኄ ካለን ‘ሁልጊዜ እርስ በርሳችን ለመጽናናት’ እንነሳሳለን። አንዳችን ለሌላው ያለን ፍቅር ምንጊዜም ጠንካራ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የሌሎችን ስህተት ይቅር ለማለት የቻልነውን ሁሉ በማድረግ ነው።

19. በተለይ በአሁኑ ጊዜ አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንዳለን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

19 በተለይ በአሁኑ ጊዜ አንዳችን ለሌላው ፍቅር እንዳለን ማሳየታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ጴጥሮስ ምክንያቱን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የሁሉም ነገር መጨረሻ ቀርቧል። ስለዚህ . . . አንዳችሁ ለሌላው የጠለቀ ፍቅር ይኑራችሁ።” (1 ጴጥ. 4:7, 8) የዚህ ክፉ ዓለም መጨረሻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ሲቃረብ ምን እንደሚሆን እንጠብቃለን? ኢየሱስ ስለ ተከታዮቹ ሲናገር “በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ብሏል። (ማቴ. 24:9) እንዲህ ያለውን ጥላቻ ለመቋቋም አንድነታችንን መጠበቅ ይኖርብናል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ “ፍጹም የሆነ የአንድነት ማሰሪያ” የሆነው ፍቅር ስለሚያስተሳስረን ሰይጣን እኛን ለመከፋፈል የሚያደርገው ጥረት ይከሽፋል።—ቆላ. 3:14፤ ፊልጵ. 2:1, 2

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

a ዛሬ፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየታችን አስፈላጊ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ፍቅራችንን ይበልጥ በተሟላ ደረጃ ማሳየት የምንችለውስ እንዴት ነው?