ለይሖዋ ታማኞች ሁኑ
“ይሖዋ በእኔና በአንተ፣ በዘሮቼና በዘሮችህ መካከል ለዘላለም ይሁን።”—1 ሳሙ. 20:42
መዝሙሮች፦ 125, 62
1, 2. ዮናታን ከዳዊት ጋር የነበረው ወዳጅነት በታማኝነት ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው?
ወጣቱ ዳዊት ግዙፉን ጎልያድን የተጋፈጠበት መንገድ ዮናታንን በጣም አስገርሞት መሆን አለበት። አሁን ዳዊት “የፍልስጤማዊውን ራስ በእጁ እንደያዘ” የእስራኤል ንጉሥና የዮናታን አባት በሆነው በሳኦል ፊት ቆሟል። (1 ሳሙ. 17:57) ዮናታን ዳዊትን እንዲያደንቅ ያደረገው ድፍረቱ ሳይሆን አይቀርም። አምላክ ከዳዊት ጋር እንደሆነ በግልጽ ማየት ችሏል፤ በመሆኑም “ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ። . . . ዮናታንም ዳዊትን እንደ ራሱ ስለወደደው ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን ተጋቡ።” (1 ሳሙ. 18:1-3) ዮናታን በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ለዳዊት ታማኝ ሆኗል።
2 አምላክ ቀጣዩ የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን የመረጠው ዳዊትን ቢሆንም ዮናታን ከዳዊት ጋር ያለው ወዳጅነት ቀጥሏል። ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ይፈልገው በነበረበት ወቅት ዮናታን ስለ ዳዊት ተጨንቆ ነበር። በመሆኑም በይሁዳ ምድረ በዳ በሚገኘው በሆሬሽ የነበረውን ወዳጁን ዳዊትን ለማበረታታት ወደዚያ ሄደ። ከዚያም “በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር [ዳዊትን] ረዳው።” እንዲህ አለው፦ “አትፍራ፤ አንተ በእስራኤል ላይ ንጉሥ ትሆናለህ፤ እኔ ደግሞ ከአንተ ቀጥዬ ሁለተኛ ሰው እሆናለሁ።”—1 ሳሙ. 23:16, 17
3. ዮናታን ለዳዊት ታማኝ ከመሆን ይበልጥ ቅድሚያ የሰጠው ነገር ምን ነበር? ይህን እንዴት እናውቃለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
3 ታማኝነት ሁሉም ሰው የሚያደንቀው ባሕርይ ነው ማለት ይቻላል። ይሁንና ዮናታን ለአምላክ ያለውን ታማኝነት ከግምት ሳናስገባ ለዳዊት ያሳየውን ታማኝነት ብቻ አድንቀን ብናልፍ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ያመልጠናል። ዮናታን ዳዊትን እንደ ተቀናቃኙ ሳይሆን እንደ ወዳጁ የተመለከተው ለምንድን ነው? በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ዮናታን ሥልጣን ከማግኘት አስበልጦ የሚያየው ነገር አለ። “በይሖዋ ላይ ያለው ትምክህት እንዲጠናከር” ዳዊትን እንደረዳው አስታውስ። ዮናታን ቅድሚያ የሰጠው ነገር ለአምላክ ያለው ታማኝነት እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል። በእርግጥም ዮናታን ለዳዊት ታማኝ እንዲሆን ያነሳሳው ዋናው ነገር ለይሖዋ ታማኝ መሆኑ ነው። ሁለቱም ሰዎች “ይሖዋ በእኔና በአንተ፣ በዘሮቼና በዘሮችህ መካከል ለዘላለም ይሁን” በማለት በመሐላ የገቡትን ቃል ጠብቀው ኖረዋል።—4. (ሀ) እውነተኛ ደስታና እርካታ የሚያስገኝልን ምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ነገሮች እንመለከታለን?
4 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን፣ የሌሎችን ታማኝነት ከማድነቅ ባለፈ እኛ ራሳችን ለቤተሰባችን አባላት፣ ለወዳጆቻችን እንዲሁም ለእምነት አጋሮቻችን ታማኝነት እናሳያለን። (1 ተሰ. 2:10, 11) ይሁንና ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ለማን ያለን ታማኝነት ነው? ከማንም በላይ ታማኝ ልንሆን የሚገባው ሕይወት ለሰጠን አምላክ እንደሆነ ጥርጥር የለውም! (ራእይ 4:11) ምንጊዜም እንዲህ ያለውን ታማኝነት ማሳየታችን እውነተኛ ደስታና እርካታ ያመጣልናል። ሆኖም ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ከፈለግን ተፈታታኝ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙን ጊዜም እንኳ ከእሱ ጋር መጣበቅ አለብን። በዚህ ርዕስ ውስጥ በአራት ተፈታታኝ ሁኔታዎች ሥር ይኸውም (1) ሥልጣን ላይ ያለ አንድ ሰው ክብር ሊሰጠው እንደማይገባ ሲሰማን፣ (2) ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብን ግራ ስንጋባ፣ (3) ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽሙብን እንዲሁም (4) ቃላችንን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ሲሰማን ለይሖዋ ታማኞች ለመሆን የዮናታን ምሳሌ እንዴት እንደሚረዳን እንመለከታለን።
ሥልጣን ላይ ያለ ሰው ክብር ሊሰጠው እንደማይገባ ሲሰማን
5. ሳኦል ንጉሥ በነበረበት ወቅት እስራኤላውያን ለአምላክ ታማኝ መሆን ፈታኝ የሆነባቸው ለምን ነበር?
5 አምላክ የዮናታን አባት የሆነውን ሳኦልን ንጉሥ እንዲሆን የቀባው ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ሳኦል ታዛዥ ሳይሆን በመቅረቱ ይሖዋ ተወው። (1 ሳሙ. 15:17-23) አምላክ ሳኦልን ከሥልጣኑ ወዲያው ስላላወረደው፣ የእሱ መጥፎ ድርጊት ለተገዢዎቹም ሆነ በቅርቡ ለነበሩት ሰዎች ፈተና ሆኖባቸው ነበር። “በይሖዋ ዙፋን ላይ” የተቀመጠው ንጉሥ የተከተለውን መጥፎ አካሄድ እየተመለከቱ ለአምላክ ታማኝ መሆን ተፈታታኝ ነበር።—1 ዜና 29:23
6. ዮናታን ለይሖዋ ምንጊዜም ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
6 ሳኦል የዓመፀኝነት መንፈስ ማሳየት በጀመረበት ወቅት ልጁ ዮናታን ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። (1 ሳሙ. 13:13, 14) ነቢዩ ሳሙኤል “ይሖዋ ስለ ታላቁ ስሙ ሲል ሕዝቡን አይተውም” ብሎ ነበር። (1 ሳሙ. 12:22) ግዙፍ የሆነ የፍልስጤማውያን ሠራዊት 30,000 የጦር ሠረገሎች አሰልፎ በእስራኤል ላይ በዘመተ ጊዜ ዮናታን ነቢዩ ሳሙኤል በተናገረው ሐሳብ ላይ እምነት እንዳለው አሳይቷል። ከሳኦል ጎን የነበሩት ተዋጊዎች 600 ሲሆኑ መሣሪያ የነበራቸው ደግሞ ሳኦልና ዮናታን ብቻ ነበሩ! ያም ሆኖ ዮናታን፣ ጋሻ ጃግሬውን ብቻ አስከትሎ ወደ ፍልስጤማውያን የጦር ሰፈር ገባ። “ይሖዋ በብዙም ሆነ በጥቂት ሰዎች ተጠቅሞ ከማዳን የሚያግደው ነገር” እንደሌለ ዮናታን ተናግሯል። ሁለቱ እስራኤላውያን በጦር ሰፈሩ ውስጥ 20 የሚያህሉ ሰዎችን ገደሉ። ከዚያም “[ምድሪቱ] መንቀጥቀጥ ጀመረች፤ ከአምላክ የመጣ ሽብርም ወረደባቸው።” ግራ የተጋቡት ፍልስጤማውያን እርስ በርሳቸው ተጨፋጨፉ። በመሆኑም ዮናታን በአምላክ ላይ ያለው እምነት ድል አስገኘ።—1 ሳሙ. 13:5, 15, 22፤ 14:1, 2, 6, 14, 15, 20
7. ዮናታን ለአባቱ ምን አመለካከት ነበረው?
7 ሳኦል ከአምላክ ጋር ያለው ግንኙነት እየተበላሸ 1 ሳሙ. 31:1, 2
ቢሄድም እንኳ ዮናታን ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ከአባቱ ጋር ይተባበር ነበር። ለምሳሌ፣ በአምላክ ሕዝብ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ለመከላከል ሲሉ አብረው ተዋግተዋል።—8, 9. ባለሥልጣናትን ማክበራችን ለአምላክ ታማኝ እንደሆንን የሚያሳየው እንዴት ነው?
8 አንዳንድ የበላይ ባለሥልጣናት ክብር ሊሰጣቸው እንደማይገባ ይሰማን ይሆናል፤ ሆኖም አምላክ ባዘዘው መሠረት ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ሁሉ ለእነሱ በመገዛት እንደ ዮናታን ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን ማሳየት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የመንግሥት ባለሥልጣን ምግባረ ብልሹ ሊሆን ይችላል፤ ያም ሆኖ “ለበላይ ባለሥልጣናት” በአንጻራዊ ሁኔታ መገዛት ስላለብን ሥልጣኑን እናከብራለን። (ሮም 13:1, 2ን አንብብ።) ሁላችንም ይሖዋ ሥልጣን ለሰጣቸው ሰዎች አክብሮት በማሳየት ለእሱ ታማኝ መሆን እንችላለን።—1 ቆሮ. 11:3፤ ዕብ. 13:17
9 በደቡብ አሜሪካ የምትኖረው ኦልጋ [1] በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ባሏን በማክበር ለይሖዋ ታማኝ መሆኗን አሳይታለች። ለበርካታ ዓመታት ባለቤቷ፣ ኦልጋ የይሖዋ ምሥክር መሆኗ እንደሚያበሳጨው በተለያየ መንገድ ይገልጽ ነበር። ስሜቷን የሚጎዳ ነገር ያደርግ፣ ይሰድባት፣ ያኮርፋት እንዲሁም ልጆቻቸውን ይዞ ጥሏት እንደሚሄድ በመናገር ያስፈራራት ነበር። ኦልጋ ግን ክፉን በክፉ አልመለሰችም። ለባለቤቷ ምግብ በመሥራትና ልብሶቹን በማጠብ እንዲሁም ልጆቻቸውንም ሆነ የእሱን ቤተሰብ በመንከባከብ ጥሩ ሚስት ለመሆን የተቻላትን ታደርግ ነበር። (ሮም 12:17) ቤተሰቦቹ ወይም የሥራ ባልደረቦቹ ሲጋብዟቸው ሁኔታዋ የሚፈቅድላት ከሆነ አብራው ትሄድ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ለአባቱ ቀብር ወደ ሌላ ከተማ መሄድ በፈለገ ጊዜ ልጆቻቸውን እንዲሁም ለጉዞ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር አዘጋጀች። ከዚያም ሥነ ሥርዓቱ እስኪያበቃ ድረስ የቤተ ክርስቲያኑ ደጃፍ ላይ ሆና ባለቤቷን ጠበቀችው። ኦልጋ ትዕግሥትና አክብሮት ስላሳየች ባለቤቷ ከበርካታ ዓመታት በኋላ አመለካከቱን መለወጥ ጀመረ። አሁን ወደ መንግሥት አዳራሹ ይወስዳታል፤ አልፎ ተርፎም እንድትሄድ ያበረታታታል፤ አንዳንድ ጊዜም ከእሷ ጋር በስብሰባ ላይ ይገኛል።—1 ጴጥ. 3:1
ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብን ግራ ስንጋባ
10. ዮናታን ለማን ታማኝ መሆን እንዳለበት ለመወሰን የረዳው ምንድን ነው?
10 ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ቆርጦ ስለተነሳ ዮናታን ለማን ታማኝ መሆን እንዳለበት ግራ ተጋብቶ ነበር። ዮናታን ከዳዊት ጋር ቃል ኪዳን የተጋባ ቢሆንም ለአባቱም ታዛዥ ነበር። ሆኖም ዮናታን፣ 1 ሳሙኤል 19:1-6ን አንብብ።
አምላክ ከዳዊት እንጂ ከሳኦል ጋር እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ዮናታን ከሳኦል ይበልጥ ለዳዊት ታማኝ ሆኗል። ዳዊትን እንዲደበቅ ካስጠነቀቀው በኋላ ስለ እሱ ለአባቱ መልካም ነገር ተናግሯል።—11, 12. ለአምላክ ያለን ፍቅር ለእሱ ታማኝ እንድንሆን የሚረዳን እንዴት ነው?
11 አሊስ የተባለች አንዲት አውስትራሊያዊት እህት፣ ለሌሎች ለምታሳየው ታማኝነት ምን ያህል ቦታ ልትሰጥ እንደሚገባት ለመወሰን የረዳት ለአምላክ ያላት ታማኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ስትጀምር የተማረቻቸውን መልካም ነገሮች ለቤተሰቧ ታካፍል ነበር። ውሎ አድሮ አሊስ ለቤተሰቦቿ ገናን አብራቸው እንደማታከብር ነገረቻቸው። በዓሉን የማታከብርበትን ምክንያት ለቤተሰቦቿ ስታስረዳቸው መጀመሪያ ላይ አዘኑ፤ ውሎ አድሮም በጣም እየተበሳጩ መጡ። ይህን ያደረጉት ለቤተሰቧ ግድ እንደሌላት ስለተሰማቸው ነው። አሊስ እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ‘ከእንግዲህ የእኔ ልጅ አይደለሽም’ አለችኝ። ቤተሰቦቼን በጣም ስለምወድ ሁኔታው አስደነገጠኝ፤ ስሜቴም በእጅጉ ተጎዳ። ያም ቢሆን በሕይወቴ ውስጥ ቅድሚያውን ለይሖዋና ለልጁ ለመስጠት ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ፤ በመሆኑም በቀጣዩ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተጠመቅኩ።”—ማቴ. 10:37
12 እኛም ካልተጠነቀቅን ለአንድ አገር፣ ትምህርት ቤት ወይም የስፖርት ቡድን ያለን ታማኝነት ቀስ በቀስ ለአምላክ ካለን ታማኝነት ሊበልጥብን ይችላል። ቼዝ መጫወት ይወድ የነበረውን የሄንሪን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ትምህርት ቤቱ በቼዝ ውድድር ሁልጊዜ ያሸንፍ ስለነበር እሱም ለማሸነፍ የተቻለውን ጥረት ማድረግ እንዳለበት ይሰማው ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ለትምህርት ቤቴ የማሳየው ታማኝነት ለአምላክ ከማሳየው ታማኝነት ቀስ በቀስ እየበለጠ ሄደ። ቅዳሜና እሁድ የሚደረጉት የቼዝ ጨዋታዎች ለመንግሥቱ አገልግሎት የማውለውን ጊዜ እየተሻሙብኝ መጡ። በመሆኑም ከቼዝ ቡድኑ ለመውጣት ወሰንኩ።”—ማቴ. 6:33
13. በቤተሰብ ውስጥ ችግር ሲያጋጥመን ለአምላክ ያለን ታማኝነት የሚረዳን እንዴት ነው?
13 አንዳንድ ጊዜ በቤተሰብ ውስጥ ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብን ግራ ልንጋባ እንችላለን። የኬንን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ እንዲህ ብሏል፦ “በዕድሜ የገፋችውን እናቴን ሁልጊዜ መጠየቅና አንዳንድ ጊዜ ደግሞ እኛ ጋር እንድትሰነብት ማድረግ እፈልጋለሁ። ሆኖም እናቴና ባለቤቴ አይግባቡም። አንዳቸውን ለማስደሰት ስጥር ሌላኛውን ማስከፋቴ ስለማይቀር መጀመሪያ ላይ ግራ ተጋብቼ ነበር። በኋላ ግን እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ በቅድሚያ ታማኝ መሆን ያለብኝ ለባለቤቴ እንደሆነ ተገነዘብኩ። በመሆኑም ባለቤቴን የሚያስደስት መፍትሔ ለማግኘት ጥረት አደረግኩ።” ኬን ባለቤቱ እናቱን በደግነት መያዝ፣ እናቱ ደግሞ ባለቤቱን ማክበር ያለባት ለምን እንደሆነ አስረዳቸው፤ ይህን ለማድረግ ድፍረት እንዲያገኝ የረዳው ለአምላክ ያለው ታማኝነትና ለቃሉ ያለው አክብሮት ነው።—ዘፍጥረት 2:24ን እና 1 ቆሮንቶስ 13:4, 5ን አንብብ።
ሌሎች በተሳሳተ መንገድ ሲረዱን ወይም ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽሙብን
14. ሳኦል በዮናታን ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር የፈጸመበት እንዴት ነው?
14 ኃላፊነት ያለው አንድ ሰው ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲፈጽምብን ለአምላክ ያለን ታማኝነት ሊፈተን ይችላል። ዮናታን እንዲህ ያለ ተፈታታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ሊሆን ይችላል። አምላክ የቀባው ንጉሥ ሳኦል፣ ልጁ ከዳዊት ጋር ጓደኝነት እንደመሠረተ ቢገነዘብም ይህን ያደረገው ለምን እንደሆነ አልገባውም ነበር። በመሆኑም ሳኦል ዮናታንን ተቆጥቶ ኃይለ ቃል በመናገር አዋረደው። ያም ሆኖ ዮናታን አጸፋውን አልመለሰም። ለአምላክም ሆነ ከጊዜ በኋላ የእስራኤል ንጉሥ ለሚሆነው ለዳዊት ያለውን ታማኝነት አላጓደለም።—1 ሳሙ. 20:30-41
15. አንድ ወንድም ተገቢ ያልሆነ ነገር ቢፈጽምብን ምን ማድረግ ይኖርብናል?
15 በዛሬው ጊዜ በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ውስጥ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሊፈጸምብን የሚችልበት አጋጣሚ በጣም ጠባብ ነው። ሆኖም በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡን ወንድሞች ፍጹም ባለመሆናቸው፣ የምናደርገውን ነገር በተሳሳተ መንገድ ሊረዱት ይችላሉ። (1 ሳሙ. 1:13-17) ሰዎች ተገቢ ያልሆነ ነገር በሚፈጽሙብን ወይም በተሳሳተ መንገድ በሚረዱን ጊዜም ለይሖዋ ታማኝ መሆናችንን እንቀጥል።
ቃላችንን መጠበቅ ከባድ እንደሆነ ሲሰማን
16. የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለአምላክ ታማኝ መሆንን የሚጠይቁ ሁኔታዎች የትኞቹ ናቸው?
16 ሳኦል፣ በዳዊት ፋንታ ንጉሥ እንዲሆን ዮናታንን ይገፋፋው ነበር። (1 ሳሙ. 20:31) ሆኖም ዮናታን ለአምላክ ያለው ታማኝነት፣ ንግሥናውን የራሱ ለማድረግ ከመሞከር ይልቅ ከዳዊት ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርት አነሳስቶታል። በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው ሰው፣ “ጉዳት ላይ ሊጥለው ቢችልም እንኳ ቃሉን አያጥፍም” የሚለውን ሐሳብ በአእምሯችን መያዛችን ዮናታን ያሳየውን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መንፈስ መኮረጅ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። (መዝ. 15:4) ዮናታን ለዳዊት የገባውን ‘ቃል አላጠፈም።’ እኛም በተመሳሳይ የገባነውን ቃል ማጠፍ አይኖርብንም። ለምሳሌ ያህል፣ አንድን የንግድ ስምምነት መፈጸም ካሰብነው በላይ ከባድ በሚሆንብን ጊዜ ለአምላክ ያለን ታማኝነትና ለመጽሐፍ ቅዱስ ያለን አክብሮት ቃላችንን እንድንጠብቅ ሊያነሳሳን ይገባል። የትዳር ሕይወት ከጠበቅነው በላይ ከባድ ቢሆንብንስ? ለአምላክ ያለን ፍቅር ለትዳር ጓደኛችን ታማኞች እንድንሆን ያደርገናል።—ሚልክያስ 2:13-16ን አንብብ።
17. ከዚህ የጥናት ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?
17 ዮናታን በተወው ምሳሌ ላይ ስናሰላስል ለአምላክ ያሳየውን ታማኝነት ለመኮረጅ አንነሳሳም? የራሳችንን ጥቅም ብቻ የምናሳድድ ሰዎች መሆን የለብንም። ልክ እንደ ዮናታን፣ ለአምላክ ሕዝቦች ሌላው ቀርቶ ቅር ላሰኙን ሰዎች ታማኝ በመሆን ለይሖዋ ታማኝነታችንን እናሳይ። በአስቸጋሪ ጊዜያትም እንኳ ለይሖዋ አምላክ ታማኝ ከሆንን ልቡን ደስ ማሰኘት እንችላለን፤ ይህም ከፍተኛ እርካታ ያስገኝልናል። (ምሳሌ 27:11) ለይሖዋ ታማኞች ሆነን ከቀጠልን፣ እሱ ለሚወዱት ሁሉ ምንጊዜም የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግላቸው በሕይወታችን መመልከት እንችላለን። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ፣ በዳዊት ዘመን የነበሩ ታማኝ የሆኑና ያልሆኑ ሰዎች ካደረጓቸው ነገሮች ምን ትምህርት እንደምናገኝ እንመለከታለን።
^ [1] (አንቀጽ 9) አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።