ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸውን ምሰሉ
“ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው።”—መዝ. 25:14
መዝሙሮች፦ 106, 118
1-3. (ሀ) የአምላክ ወዳጅ መሆን እንደምንችል እርግጠኞች የምንሆነው ለምንድን ነው? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ እነማን እንመረምራለን?
አብርሃም የይሖዋ ወዳጅ እንደሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሦስት ጊዜ ተጠቅሷል። (2 ዜና 20:7፤ ኢሳ. 41:8፤ ያዕ. 2:23) መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የይሖዋ ወዳጅ ብሎ የጠራው ብቸኛው ሰው ታማኙ አብርሃም ነው። ይህ ሲባል ግን ‘ከሰዎች መካከል የይሖዋ ወዳጅ የሆነው አብርሃም ብቻ ነው’ ብለን መደምደም ይኖርብናል? በፍጹም፤ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት መመሥረት እንደምንችል ይጠቁማል።
2 የአምላክ ቃል ይሖዋን ስለሚፈሩ፣ በእሱ ላይ እምነት ስላላቸውና ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ስለመሠረቱ በርካታ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዟል። (መዝሙር 25:14ን አንብብ።) ሐዋርያው ጳውሎስ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” እንደሆኑ የጠቀሳቸው ሰዎች አሉ። (ዕብ. 12:1) የተለያየ ዓይነት ሕይወት የነበራቸው እነዚህ ሰዎች፣ የአምላክ ወዳጆች እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም።
3 በመንፈስ መሪነት በተጻፈው ዘገባ ላይ ከተጠቀሱት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የነበራቸው ሰዎች መካከል እስቲ ሦስቱን እንመልከት። እነሱም (1) ሞዓባዊት መበለት የሆነችው ታማኟ ሩት፣ (2) ጻድቅ የሆነው የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ እንዲሁም (3) የኢየሱስ እናት የሆነችው ትሑቷ ማርያም ናቸው። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ ከረዳቸው ነገር ምን እንማራለን?
ታማኝ ፍቅር አሳይታለች
4, 5. ሩት ምን ከባድ ውሳኔ ተደቅኖባታል? ውሳኔውን ከባድ የሚያደርገውስ ምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)
4 ሦስት መበለቶች፣ ነፋሱ ልብሳቸውን እያውለበለበው የሞዓብን ሜዳ አቋርጠው ሲጓዙ በዓይነ ሕሊናህ ለመመልከት ሞክር። እነዚህ ሴቶች ናኦሚ እንዲሁም ምራቶቿ የሆኑት ሩትና ዖርፋ ናቸው። ዖርፋ በሞዓብ ወደሚገኘው ቤቷ ለመመለስ ስለወሰነች ከእነሱ ተለይታ ሄደች። ናኦሚ ግን ወደ ትውልድ አገሯ ወደ እስራኤል የጀመረችውን ጉዞ ለመቀጠል ቆርጣለች። ከእሷ ጋር የቀረችው ሩት በሕይወቷ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ውሳኔ ተደቅኖባታል። ወደ አገሯና ወደ ሕዝቧ ከመመለስ አሊያም ከአማቷ ከናኦሚ ጋር ወደ ቤተልሔም ከመጓዝ አንዱን መምረጥ ይኖርባታል።—ሩት 1:1-8, 14
5 ወጣት መበለት የሆነችው ሩት፣ በሞዓብ ቤተሰቦቿ ስላሉ እናቷና ሌሎች ዘመዶቿ ሊያስጠጓት ብሎም ሊንከባከቧት እንደሚችሉ ማሰብ ትችል ነበር። ሞዓብ የትውልድ አገሯ ነው። ባሕሉ፣ ቋንቋውም ሆነ ሕዝቡ ለእሷ አዲስ አይደለም። ሩት በቤተልሔም እነዚህን ነገሮች እንደምታገኝ ናኦሚ ቃል ልትገባላት አትችልም። ናኦሚም ብትሆን ሩትን የመከረቻት በሞዓብ እንድትቀር ነው። ናኦሚ፣ ምራቶቿ ትዳርም ሆነ የራሳቸው ኑሮ እንዲኖራቸው ልትረዳቸው ስለመቻሏ ስጋት አድሮባታል። ታዲያ ሩት ምን ታደርግ ይሆን? “ወደ ወገኖቿና ወደ አማልክቷ” በተመለሰችው በዖርፋና በሩት መካከል ያለውን ልዩነት ልብ በል። (ሩት 1:9-15) ሩት ወገኖቿ ወደሚያመልኳቸው የሐሰት አማልክት ለመመለስ ትወስን ይሆን? በፍጹም እንዲህ አላደረገችም።
6. (ሀ) ሩት ምን ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አድርጋለች? (ለ) ቦዔዝ፣ ሩት በይሖዋ ክንፎች ሥር ለመጠለል እንደፈለገች ሲናገር ምን ማለቱ ነበር?
6 ሩት ስለ ይሖዋ አምላክ የምታውቀው ነገር አለ፤ ይህን ያወቀችው ከቀድሞ ባሏ ወይም ከናኦሚ ሊሆን ይችላል። ይሖዋ ከሞዓብ አማልክት የተለየ ነው። ሩት፣ ይሖዋ ልትወደውና ልታመልከው የሚገባ አምላክ እንደሆነ ተገንዝባ ነበር። እውቀት ብቻውን ግን በቂ አይደለም። ሩት ውሳኔ ማድረግ ይኖርባታል። ይሖዋ፣ አምላኳ እንዲሆን ትመርጥ ይሆን? ይህች ወጣት ጥበብ የተንጸባረቀበት ውሳኔ አድርጋለች። ለናኦሚ “ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል” ብላታለች። (ሩት 1:16) ሩት ለናኦሚ ስለነበራት ፍቅር ስናስብ ልባችን በጥልቅ የሚነካ ቢሆንም ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ለይሖዋ ያላት ፍቅር ነው። ሩት በይሖዋ ክንፎች ሥር ለመጠለል በመፈለጓ ከጊዜ በኋላ ቦዔዝ አድንቋታል። (ሩት 2:12ን አንብብ።) ቦዔዝ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ጥላ ከለላ ለማግኘት በወላጆቿ ክንፎች ሥር የምትሸሸግን ጫጩት እንድናስብ ያደርገን ይሆናል። (መዝ. 36:7፤ 91:1-4) ይሖዋ ለሩት እንደነዚህ ወላጆች ሆኖላታል። ስላሳየችው እምነት ወሮታዋን የከፈላት ሲሆን በውሳኔዋ እንድትቆጭ የሚያደርግ ምንም ነገር አላጋጠማትም።
7. ራሳቸውን ለይሖዋ ለመወሰን የሚያመነቱ ሰዎች የትኞቹን ነጥቦች ማሰባቸው ሊረዳቸው ይችላል?
7 ብዙዎች ስለ ይሖዋ ቢያውቁም እሱን መጠጊያቸው ለማድረግ ያመነታሉ። ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ እሱን ከማገልገል ወደኋላ ይላሉ። ራስህን ለይሖዋ ለመወሰን የምታመነታ ከሆነ ምክንያትህ ምን እንደሆነ ቆም ብለህ አስበህበት ታውቃለህ? ማንኛውም ፍጡር የሚያመልከው አካል መኖሩ አይቀርም። (ኢያሱ 24:15) ታዲያ ሊመለክ የሚገባውን ብቸኛ አምላክ ለምን መጠጊያህ አታደርገውም? ለይሖዋ ራስህን መወሰንህ፣ በእሱ ላይ እምነት እንዳለህ ማሳየት የምትችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ነው። ይሖዋ ከውሳኔህ ጋር ተስማምተህ መኖር እንድትችልና የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትወጣ ይረዳሃል። አምላክ ለሩት እንዲህ አድርጎላታል።
አስተዳደጉ ጥሩ ባይሆንም ‘ከይሖዋ ጋር ተጣብቋል’
8. የሕዝቅያስ የልጅነት ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል አብራራ።
8 ከሩት በተለየ ሁኔታ ወጣቱ ሕዝቅያስ የተወለደው ይሖዋን ለማገልገል በወሰነ ብሔር ውስጥ ነው። ከዚህ ውሳኔ ጋር ተስማምተው የኖሩት ግን ሁሉም እስራኤላውያን አይደሉም። የሕዝቅያስ አባት የሆነውን ንጉሥ አካዝን ለዚህ እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል። ይህ ክፉ ሰው የይሁዳ ሕዝብ በጣዖት አምልኮ እንዲዘፈቅ ከማድረግም አልፎ በኢየሩሳሌም የሚገኘውን የይሖዋን ቤተ መቅደስ አርክሷል። አካዝ፣ ከሕዝቅያስ 2 ነገ. 16:2-4, 10-17፤ 2 ዜና 28:1-3
ወንድሞች አንዳንዶቹን በሕይወት እያሉ በእሳት በማቃጠል ለሐሰት አምላክ መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧቸዋል! በመሆኑም የሕዝቅያስ የልጅነት ሕይወት ምን ያህል ከባድ እንደነበር መገመት አያዳግትም።—9, 10. (ሀ) ሕዝቅያስ በምሬት እንዲሞላ ሊያደርገው የሚችል ምን ሁኔታ አጋጥሞት ነበር? (ለ) አምላክን ማማረር የሌለብን ለምንድን ነው? (ሐ) በሕይወታችን ውስጥ የምንከተለው ጎዳና በአስተዳደጋችን ላይ የተመካ እንደሆነ ማሰብ ተገቢ ያልሆነው ለምንድን ነው?
9 ሕዝቅያስ በምሬትና በቁጣ ሊሞላ ብሎም በአምላክ ላይ ሊያምፅ ይችል ነበር። የዚህን ያህል የከፋ ሁኔታ ያላጋጠማቸው ሰዎች እንኳ ‘በይሖዋ ላይ ለመቆጣት’ ወይም በድርጅቱ ለመማረር የሚያበቃ ምክንያት እንዳላቸው ተሰምቷቸዋል። (ምሳሌ 19:3) አንዳንዶች ደግሞ አስተዳደጋቸው መጥፎ በመሆኑ እነሱም የወላጆቻቸውን ስህተት በመድገም መጥፎ ሕይወት መምራታቸው እንደማይቀር ያስባሉ። (ሕዝ. 18:2, 3) እንዲህ ያሉት አመለካከቶች ትክክል ናቸው?
10 በፍጹም! የሕዝቅያስ ሕይወት ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ይሆናል። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ ሰዎች ለሚደርሱባቸው መጥፎ ነገሮች ተጠያቂው ይሖዋ ስላልሆነ እሱን ለማማረር የሚያበቃ ምንም ዓይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም። (ኢዮብ 34:10) እርግጥ ነው ወላጆች፣ በበጎም ይሁን በመጥፎ በልጆቻቸው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊያሳድሩ ይችላሉ። (ምሳሌ 22:6፤ ቆላ. 3:21) ይህ ሲባል ግን አንድ ሰው በሕይወቱ የሚከተለው ጎዳና በአስተዳደጉ ላይ የተመካ ነው ማለት አይደለም። ይሖዋ ለሁላችንም ውድ ስጦታ ይኸውም የመምረጥ ችሎታ ሰጥቶናል፤ በመሆኑም ምን ዓይነት አካሄድ መከተል ወይም ምን ዓይነት ሰው መሆን እንደምንፈልግ መምረጥ እንችላለን። (ዘዳ. 30:19) ሕዝቅያስ ይህን ስጦታ የተጠቀመበት እንዴት ነው?
11. ሕዝቅያስ በጣም ጥሩ ከነበሩት የይሁዳ ነገሥታት መካከል አንዱ እንዲሆን ያስቻለው ምንድን ነው?
11 ሕዝቅያስ፣ በጣም መጥፎ ከሆኑት የይሁዳ ነገሥታት መካከል የአንዱ ልጅ ቢሆንም በጣም ጥሩ ንጉሥ መሆን ችሏል። (2 ነገሥት 18:5, 6ን አንብብ።) አባቱ መጥፎ ምሳሌ እንደነበረ ባይካድም ሕዝቅያስ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩበትን ሰዎች ምሳሌ ለመከተል መርጧል። በወቅቱ ኢሳይያስ፣ ሚክያስና ሆሴዕ በነቢይነት ያገለግሉ ነበር። ንጉሥ ሕዝቅያስ፣ እነዚህ ታማኝ ነቢያት በመንፈስ መሪነት የሚያውጁትን መልእክት በጥሞና በማዳመጥ የይሖዋ ምክርና እርማት ወደ ልቡ ጠልቆ እንዲገባ ፈቅዶ እንደነበር ማሰብ እንችላለን። በመሆኑም ሕዝቅያስ አባቱ የፈጸማቸውን መጥፎ ነገሮች ለማስተካከል እርምጃ ወስዷል። ይህንንም ያደረገው ቤተ መቅደሱን በማንጻት፣ ለሕዝቡ ኃጢአት ማስተሰረያ በማቅረብ እንዲሁም የአረማውያንን ጣዖታት ለማጥፋት ቅንዓት የተንጸባረቀበት ሰፊ ዘመቻ በማካሄድ ነው። (2 ዜና 29:1-11, 18-24፤ 31:1) ሕዝቅያስ፣ ከባድ ፈተናዎች ባጋጠሙት ጊዜ ለምሳሌ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በኢየሩሳሌም ላይ ጥቃት ለመሰንዘር በሞከረበት ወቅት ታላቅ ድፍረትና እምነት እንዳለው አሳይቷል። አምላክ እንደሚያድነው የተማመነ ከመሆኑም ሌላ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ሕዝቡን አበረታቷል። (2 ዜና 32:7, 8) ከጊዜ በኋላ ሕዝቅያስ ልቡ በመታበዩ እርማት ሲሰጠው ራሱን ዝቅ በማድረግ ንስሐ ገብቷል። (2 ዜና 32:24-26) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሕዝቅያስ፣ ያለፈው ሕይወቱ የአሁኑን ሕይወቱን እንዲያበላሽበት ወይም ጥሩ የወደፊት ሕይወት እንዳይኖረው እንቅፋት እንዲሆንበት አልፈቀደም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ወዳጅ በመሆን እኛም ልንከተለው የሚገባ ጥሩ ምሳሌ ትቷል።
12. እንደ ሕዝቅያስ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎች የይሖዋ ወዳጅ መሆናቸውን ያሳዩት እንዴት ነው?
12 የምንኖረው ፍቅር በጠፋበትና ጭካኔ በሞላበት ዓለም ውስጥ በመሆኑ ብዙ ልጆች የወላጆቻቸውን ፍቅርና ከለላ ሳያገኙ ማደጋቸው የሚያስገርም አይደለም። (2 ጢሞ. 3:1-5) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ብዙ ክርስቲያኖች መጥፎ አስተዳደግ የነበራቸው ቢሆንም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ችለዋል። እንደ ሕዝቅያስ ሁሉ እነሱም አንድ ሰው በሕይወቱ የሚከተለው ጎዳና የተመካው በአስተዳደጉ ላይ እንዳልሆነ አሳይተዋል። አምላክ የመምረጥ ነፃነት በመስጠት አክብሮናል፤ ይህን ስጦታ በመጠቀም ከይሖዋ ጋር የመጣበቅ እንዲሁም ለእሱ ክብርና ግርማ የማምጣት መብት አለን።
“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ!”
13, 14. ማርያም የተሰጣት ኃላፊነት በጣም ከባድ እንዲሆን የሚያደርጉት የትኞቹ ሁኔታዎች ሊሆኑ ይችላሉ? ሆኖም ለገብርኤል ምን ምላሽ ሰጠች?
13 ሕዝቅያስ ከኖረበት ዘመን ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ በናዝሬት የምትኖር አንዲት ትሑት አይሁዳዊት ወጣት ከይሖዋ ጋር ልዩ የሆነ ወዳጅነት መሥርታ ነበር። እሷ ከተሰጣት ጋር የሚወዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ማንም ሰው የለም። ይህች ሴት የአምላክን አንድያ ልጅ እንደምትፀንስ፣ እንደምትወልድና እንደምታሳድግ ተነገራት! ይሖዋ፣ የሄሊ ልጅ ለሆነችው ለማርያም እንዲህ ያለ ታላቅ አደራ የሰጣት ምን ያህል ቢተማመንባት እንደሆነ አስበው! ሆኖም ማርያም የተሰጣትን ተልእኮ በሰማችበት ወቅት ምን ተሰምቷት ይሆን?
14 ማርያም ባገኘችው አስደናቂ መብት ላይ ትኩረት ስናደርግ፣ ሊያስጨንቋት የሚችሉት ነገሮች ወደ አእምሯችን አይመጡ ይሆናል። የአምላክ መልአክ የሆነው ገብርኤል በተአምራዊ ሁኔታ ይኸውም ከወንድ ጋር ግንኙነት ሳትፈጽም እንደምትፀንስ ነገራት። ገብርኤል፣ ማርያም እንዴት እንዳረገዘች ለቤተሰቧ አባላት ወይም ለጎረቤቶቿ እንደሚያስረዳቸው አልነገራትም። ታዲያ ስለ እሷ ምን ያስቡ ይሆን? ማርያም እጮኛዋ ዮሴፍ ምን ሊሰማው እንደሚችል አሳስቧት መሆን አለበት። እርጉዝ ብትሆንም ለእሱ ያላትን ታማኝነት እንዳላጓደለች ልታሳምነው የምትችለው እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ የልዑሉን አምላክ አንድያ ልጅ ተንከባክቦ ማሳደግና ማሠልጠን እንዴት ያለ ከባድ ኃላፊነት ነው! ማርያም፣ ገብርኤል ባናገራት ወቅት አሳስበዋት ሊሆኑ የሚችሉትን ነገሮች ሁሉ ማወቅ አንችልም። ሆኖም ሉቃስ 1:26-38
“እነሆ፣ እኔ የይሖዋ ባሪያ ነኝ! እንደ ቃልህ ይሁንልኝ” ብላ መልስ እንደሰጠች እናውቃለን።—15. ማርያም ያሳየችው እምነት አስደናቂ የሆነው ለምንድን ነው?
15 ማርያም ያሳየችው እምነት አስደናቂ አይደለም? በዚያ ዘመን የነበረች ባሪያ፣ ጌታዋ ያዘዛትን ሁሉ ለመፈጸም ፈቃደኛ ናት። ማርያም ይህን ስትል፣ ጌታዋ የሆነው ይሖዋ እንደሚንከባከባትና ጥበቃ እንደሚያደርግላት መተማመኗን መግለጿ ነበር። እሱ በሚፈልገው በማንኛውም መንገድ ልታገለግለው ፈቃደኛ ነበረች። ማርያም እንዲህ ዓይነት እምነት ሊኖራት የቻለው እንዴት ነው? እምነት ስንወለድ ጀምሮ የሚኖረን ባሕርይ አይደለም። አንድ ሰው እምነት ለማዳበር ከፈለገ፣ ጥረት ማድረግና የአምላክን እገዛ ማግኘት ያስፈልገዋል። (ገላ. 5:22፤ ኤፌ. 2:8) ማርያም እምነቷን ለማጠናከር ጥረት እንዳደረገች የሚጠቁም ነገር አለ? አዎ። ያዳመጠችበትን መንገድና የተናገረችውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት።
16. ማርያም ጥሩ አድማጭ እንደነበረች የሚያሳየው ምንድን ነው?
16 ማርያም ያዳመጠችበት መንገድ። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ለመስማት የፈጠንን እና ለመናገር የዘገየን’ እንድንሆን ይመክረናል። (ያዕ. 1:19) ታዲያ ማርያም ጥሩ አድማጭ ነበረች? እንደዚህ ብለን ለመደምደም የሚያበቃ ምክንያት አለን። ማርያም ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም ያላቸውን ሐሳቦች በትኩረት እንዳዳመጠች፣ ከዚያም የሰማችውን ነገር ጊዜ ወስዳ እንዳሰላሰለችበት የሚገልጹ ሁለት ዘገባዎች በሉቃስ ወንጌል ላይ እናገኛለን። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት እረኞች፣ መላእክት የነገሯቸውን መልእክት ለማርያም ገልጸውላት ነበር። ከ12 ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ ኢየሱስ ገና ልጅ ቢሆንም ትልቅ መንፈሳዊ ትርጉም ያለው ነገር ተናግሮ ነበር። በሁለቱም ጊዜያት ማርያም የተነገራትን ነገር አዳምጣለች፣ አስታውሳለች እንዲሁም በቁም ነገር አስባበታለች።—ሉቃስ 2:16-19, 49, 51ን አንብብ።
17. ማርያም ከተናገረችው ነገር ስለ እሷ ምን ማወቅ እንችላለን?
17 ማርያም የተናገረችው ነገር። ማርያም ከተናገረቻቸው ነገሮች መካከል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙት ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። በሉቃስ 1:46-55 ላይ የሚገኘው ሐሳብ ማርያም ከተናገረቻቸው ሐሳቦች ሁሉ ረጅሙ ነው። የማርያም ንግግር፣ በመንፈስ መሪነት የተጻፉትን ቅዱሳን መጻሕፍት በሚገባ እንደምታውቅ ይጠቁማል። የማርያም ሐሳብ፣ የነቢዩ ሳሙኤል እናት የሆነችው ሐና ከተናገረችው ነገር ጋር በተወሰነ መጠን ይመሳሰላል። (1 ሳሙ. 2:1-10) ማርያም 20 ጊዜ ያህል ከቅዱሳን መጻሕፍት ጠቅሳ እንደተናገረች ይገመታል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ስለ መንፈሳዊ ነገሮች መናገር የምትወድ ሴት ነበረች። ማርያም በልቧ ካስቀመጠችው ውድ ሀብት ይኸውም ከታላቁ ወዳጇ ከይሖዋ አምላክ በተማረቻቸው ውድ እውነቶች ከተሞላው ጎተራ እያወጣች የተናገረች ያህል ነው።
18. ማርያምን በእምነቷ ልንመስላት የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?
18 እንደ ማርያም ሁሉ እኛም አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ የሚሰጠን ኃላፊነት ከባድ ሊመስለን ይችላል። ልክ እንደ እሷ፣ ይሖዋ የሚጠቅመንን ነገር እንደሚያደርግልን በመተማመን የሚሰጠንን ኃላፊነት በትሕትና እንቀበል። ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማዎቹ የምንማረውን ነገር በጥሞና በማዳመጥ፣ በመንፈሳዊ እውነቶች ላይ በማሰላሰል እንዲሁም የተማርናቸውን ነገሮች ለሌሎች በደስታ በማካፈል ማርያምን በእምነቷ መምሰል እንችላለን።—መዝ. 77:11, 12፤ ሉቃስ 8:18፤ ሮም 10:15
19. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ግሩም የእምነት ምሳሌዎች የምንኮርጅ ከሆነ ምን እንደምናገኝ እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን?
19 እንደ አብርሃም ሁሉ ሩት፣ ሕዝቅያስና ማርያምም የይሖዋ ወዳጆች እንደነበሩ ምንም ጥርጥር የለውም። እነዚህም ሆኑ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” የተባሉት የአምላክ አገልጋዮች እንዲሁም በታሪክ ዘመናት ሁሉ የኖሩ ሌሎች በርካታ ታማኝ ሰዎች፣ የአምላክ ወዳጆች የመሆን ግሩም መብት አግኝተዋል። እነዚህን ሰዎች በእምነታቸው መምሰላችንን እንቀጥል። (ዕብ. 6:11, 12) ይህን ስናደርግ ታላቅ ሽልማት እንደምናገኝ ይኸውም ለዘላለም ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንደሚኖረን እርግጠኞች መሆን እንችላለን!