በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ትምህርት ማግኘት

ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ትምህርት ማግኘት

“ይሖዋ ከአንተ የሚፈልገው ምንድን ነው? ፍትሕን እንድታደርግ፣ ታማኝነትን እንድትወድና ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር እንድትሄድ ብቻ ነው!”—ሚክ. 6:8

መዝሙሮች፦ 63, 43

1, 2. ዳዊት ለአምላክ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ዳዊትና አቢሳ፣ በውድቅት ሌሊት ጭልጥ ያለ እንቅልፍ በወሰዳቸው 3,000 ወታደሮች መካከል ኮቴያቸውን አጥፍተው እየተጓዙ ነው። ሁለቱ ሰዎች፣ ንጉሥ ሳኦል በጦር ሰፈሩ መሃል ድብን ያለ እንቅልፍ ወስዶት አገኙት። ሳኦል ዳዊትን አግኝቶ ለመግደል በይሁዳ ምድረ በዳ ሲጓዝ ነበር። አቢሳ “አንድ ጊዜ ብቻ [ሳኦልን] በጦር ወግቼ ከመሬት ጋር ላጣብቀው፤ መድገም አያስፈልገኝም” በማለት በሹክሹክታ ተናገረ። ዳዊት የሰጠው መልስ ግን የሚያስገርም ነበር! እንዲህ አለው፦ “ጉዳት እንዳታደርስበት፤ ለመሆኑ ይሖዋ በቀባው ላይ እጁን አንስቶ ከበደል ነፃ የሚሆን ማን ነው? . . . በእኔ በኩል ይሖዋ በቀባው ላይ እጄን ማንሳት በይሖዋ ዓይን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነው!”—1 ሳሙ. 26:8-12

2 ዳዊት ለአምላክ ታማኝ መሆን ሲባል ምን ነገሮችን እንደሚጨምር ተገንዝቦ ነበር። ሳኦልን የመጉዳት ሐሳብ አልነበረውም። ለምን? ምክንያቱም ሳኦል በአምላክ የተቀባ የእስራኤል ንጉሥ ነበር። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች እሱ ለሾማቸው ሰዎች አክብሮት አላቸው። በእርግጥም ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ሁሉ ‘ታማኝነትን እንዲወዱ’ ይጠብቅባቸዋል።—ሚክያስ 6:8ን አንብብ።

3. አቢሳ ለዳዊት ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

3 አቢሳ ለዳዊት አክብሮት እንዳለው አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር የፈጸመውን ምንዝር ለመሸፋፈን ሲል የቤርሳቤህ ባል የሆነው ኦርዮ በጦርነት ላይ እንዲገደል ሁኔታዎችን እንዲያመቻች ኢዮዓብን አዘዘው። (2 ሳሙ. 11:2-4, 14, 15፤ 1 ዜና 2:16) አቢሳ የኢዮዓብ ወንድም ስለሆነ ስለዚህ ጉዳይ ሳያውቅ አይቀርም፤ ያም ሆኖ በአምላክ ለተሾመው ለንጉሥ ዳዊት አክብሮት ማሳየቱን ቀጥሏል። ከዚህም በተጨማሪ አቢሳ የጦር አዛዥነት ሥልጣኑን በመጠቀም የእስራኤል ንጉሥ ለመሆን አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ዳዊትን ከጠላቶቹና በእሱ ላይ ካሴሩ ሰዎች ታድጎታል።—2 ሳሙ. 10:10፤ 20:6፤ 21:15-17

4. (ሀ) ዳዊት ለአምላክ ታማኝ በመሆን ረገድ ምሳሌ የሚሆነን እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን ተጨማሪ ምሳሌዎች እንመረምራለን?

4 ዳዊት፣ ንጉሥ ሳኦልን ከመጉዳት መታቀቡ ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ መሆኑን የሚያሳይ ነው። ዳዊት ወጣት እያለ ‘ሕያው በሆነው አምላክ ሠራዊት ላይ ሲሳለቅ’ የነበረውን ጎልያድ የተባለ ግዙፍ ፍልስጤማዊ ገድሏል! (1 ሳሙ. 17:23, 26, 48-51) ዳዊት ንጉሥ ከሆነ በኋላ ምንዝር በመፈጸምና ነፍስ በመግደል ከባድ ኃጢአት በፈጸመበት ወቅት፣ ነቢዩ ናታን የሰጠውን ወቀሳ ተቀብሎ ንስሐ ገብቷል። (2 ሳሙ. 12:1-5, 13) ካረጀም በኋላ አምላክን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ለምሳሌ ያህል፣ የይሖዋን ቤተ መቅደስ ግንባታ ለመደገፍ ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። (1 ዜና 29:1-5) እርግጥ ነው፣ ዳዊት ከባድ ኃጢአቶችን ፈጽሟል፤ ሆኖም ለአምላክ ታማኝ ነበር። (መዝ. 51:4, 10፤ 86:2) ስለ ዳዊትና በእሱ ዘመን ስለነበሩት ሰዎች የተጻፉትን ሌሎች ዘገባዎች ስንመረምር ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት ጥረት እናድርግ፦ ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው? ታማኝ ለመሆን የትኞቹን ባሕርያት ማፍራት ያስፈልገናል?

ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብን ለማን ነው?

5. አቢሳ ከሠራው ስህተት ምን ትምህርት እናገኛለን?

5 አቢሳ ወደ ሳኦል የጦር ሰፈር በገባበት ወቅት ታማኝነት ያሳየው ለተገቢው አካል አልነበረም። አቢሳ ለዳዊት ያለው ታማኝነት ንጉሥ ሳኦልን ለመግደል እንዲነሳሳ አድርጎት ነበር፤ ዳዊት ግን “ይሖዋ በቀባው ላይ” እጅ ማንሳት ተገቢ እንዳልሆነ ስለተገነዘበ ይህን እንዳያደርግ አቢሳን ከልክሎታል። (1 ሳሙ. 26:8-11) ከዚህ ዘገባ የምናገኘው አንድ ጠቃሚ ትምህርት አለ፦ ለተለያዩ አካላት ታማኝ መሆናችን ተገቢ ቢሆንም በዋነኝነት ታማኝ መሆን የሚገባን ለማን እንደሆነ ለመወሰን በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይኖርብናል።

6. ለቤተሰባችንና ለወዳጆቻችን ታማኝ መሆናችን ተገቢ ቢሆንም መጠንቀቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

6 ታማኝነት የሚመነጨው ከልብ ነው፤ የሰው ልብ ግን ከዳተኛ ነው። (ኤር. 17:9) በመሆኑም ለአምላክ ታማኝ የሆነ አንድ ሰው፣ የቅርብ ጓደኛው ወይም ዘመዱ መጥፎ ድርጊት እየፈጸመ ቢሆንም ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለበት ሊሰማው ይችላል። ይሁንና እውነትን የተወው በጣም የምንቀርበው ሰው ቢሆንም እንኳ ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብን ለይሖዋ እንደሆነ ማስታወስ ይኖርብናል።ማቴዎስ 22:37ን አንብብ።

7. አንዲት እህት አስቸጋሪ ሁኔታ ቢያጋጥማትም ለአምላክ ታማኝ መሆኗን ያሳየችው እንዴት ነው?

7 የቅርብ ዘመዳችን በሚወገድበት ጊዜ ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብን መወሰን ሊከብደን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አን [1] የተባለች እህት ያጋጠማትን እንመልከት፤ የተወገደች እናቷ ስልክ ደወለችላት። እናቷ ከቤተሰቧ መገለሏ በጣም ስለጎዳት መጥታ ልትጠይቃት እንደምትፈልግ ለአን ነገረቻት። አን የእናቷ ጥያቄ በጣም ስላስጨነቃት መልሷን በደብዳቤ እንደምትገልጽላት ቃል ገባች። ደብዳቤውን ከመጻፏ በፊት ግን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተመለከተች። (1 ቆሮ. 5:11፤ 2 ዮሐ. 9-11) አን በደብዳቤዋ ላይ፣ መጥፎ ድርጊት በመፈጸምና ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆን ራሷን ከቤተሰቡ ያገለለችው እናቷ ራሷ እንደሆነች በደግነት ገለጸች። እንዲሁም “ከዚህ ሥቃይ መገላገል የምትችዪበት ብቸኛው መንገድ ወደ ይሖዋ መመለስ ነው” በማለት ጻፈችላት።—ያዕ. 4:8

8. ለአምላክ ታማኝ ለመሆን የሚረዱን የትኞቹ ባሕርያት ናቸው?

8 በዳዊት ዘመን የኖሩ ሰዎች የነበራቸው ታማኝነት፣ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን የሚረዱንን ሦስት ባሕርያት ጎላ አድርገው ያሳያሉ። እነዚህ ባሕርያት ትሕትና፣ ደግነትና ድፍረት ናቸው። እስቲ እነዚህን ባሕርያት አንድ በአንድ እንመርምር።

ለአምላክ ታማኝ መሆን ትሕትና ይጠይቃል

9. አበኔር፣ ዳዊትን ለመግደል የፈለገው ለምንድን ነው?

9 ዳዊት የጎልያድን ጭንቅላት ይዞ ከንጉሥ ሳኦል ጋር ሲነጋገር ቢያንስ ሁለት ሰዎች ተመልክተውታል። አንደኛው ከዳዊት ጋር የወዳጅነት ቃል ኪዳን የገባው የሳኦል ልጅ ዮናታን ነው። ሌላኛው ደግሞ የሠራዊቱ አለቃ የነበረው አበኔር ነው። (1 ሳሙ. 17:57 እስከ 18:3) ከጊዜ በኋላ አበኔር፣ ሳኦል ዳዊትን ለመግደል ጥረት ሲያደርግ ተባባሪ ሆኗል። ዳዊት “ጨካኝ ሰዎችም ሕይወቴን ይሻሉ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 54:3፤ 1 ሳሙ. 26:1-5) አበኔር ከዳዊት ጋር በተያያዘ ያደረገው ነገር ዮናታን ካደረገው የተለየ የሆነው ለምንድን ነው? ልክ እንደ ዮናታን አበኔርም፣ አምላክ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እንደመረጠው ያውቅ ነበር። ሳኦል ከሞተ በኋላ አበኔር፣ የሳኦልን ልጅ ኢያቡስቴን ሳይሆን ዳዊትን በመደገፍ ትሑትና ለአምላክ ታማኝ መሆኑን ማሳየት ይችል ነበር። ከጊዜ በኋላ ከንጉሥ ሳኦል ቁባት ጋር ግንኙነት የፈጸመ ሲሆን ይህም ንግሥናውን ለራሱ መውሰድ እንደፈለገ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል።—2 ሳሙ. 2:8-10፤ 3:6-11

10. አቢሴሎም ለአምላክ ታማኝ ያልሆነው ለምንድን ነው?

10 የዳዊት ልጅ የነበረው አቢሴሎም፣ ትሕትና ስላልነበረው ለአምላክ ታማኝ ሳይሆን ቀርቷል። እንዲያውም “አቢሴሎም ሠረገላ፣ ፈረሶችና ከፊቱ የሚሮጡ 50 ሰዎች አዘጋጀ”! (2 ሳሙ. 15:1) በተጨማሪም የሕዝቡን ልብ ሰረቀ። ልክ እንደ አበኔር፣ አቢሴሎምም ዳዊትን ለመግደል ተነስቶ ነበር፤ ይህን ያደረገው ይሖዋ ዳዊትን የእስራኤል ንጉሥ እንዲሆን እንደሾመው እያወቀ ነው።—2 ሳሙ. 15:13, 14፤ 17:1-4

11. ስለ አበኔር፣ አቢሴሎምና ባሮክ ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

11 ከአበኔርና ከአቢሴሎም ታሪክ መመልከት እንደሚቻለው የሥልጣን ጥመኝነት፣ አንድ ሰው ለአምላክ ታማኝ እንዳይሆን ሊያደርገው ይችላል። ማንኛውም ታማኝ የሆነ የይሖዋ አገልጋይ፣ እንዲህ ያለ ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት የክፋት አካሄድ እንደማይከተል የታወቀ ነው። ሆኖም አንድ ክርስቲያን በዚህ ዓለም ውስጥ ሀብት ወይም ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሥራ ለማግኘት ፍላጎት ካለውም ይህ በመንፈሳዊነቱ ላይ ጎጂ ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል። የነቢዩ ኤርምያስ ጸሐፊ የሆነው ባሮክ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ትኩረቱ ተሰርቆ ነበር፤ መጽሐፍ ቅዱስ የባሮክን ሐሳብ የከፋፈለው ምን እንደሆነ በግልጽ ባይናገርም ይሖዋ የሚከተለውን መልእክት እንደላከለት ይገልጻል፦ “እነሆ፣ የገነባሁትን አፈርሳለሁ፤ የተከልኩትንም እነቅላለሁ፤ ምድሪቱን በሙሉ አወድማለሁ። አንተ ግን ለራስህ ታላላቅ ነገሮችን ትፈልጋለህ። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ፈጽሞ አትፈልግ።” (ኤር. 45:4, 5) ባሮክ የተሰጠውን እርማት ተቀብሏል። እኛም የዚህን ክፉ ዓለም ጥፋት በምንጠባበቅበት ጊዜ፣ አምላክ ለባሮክ የተናገረውን ሐሳብ ማስታወሳችን የጥበብ እርምጃ ነው!

12. ራስ ወዳድ ከሆንን ለአምላክ ታማኝ መሆን የማንችለው ለምን እንደሆነ አብራራ።

12 በሜክሲኮ የሚኖር ዳንኤል የተባለ ወንድም፣ ለአምላክ ታማኝ ከመሆን አሊያም ራስ ወዳድነት የሚንጸባረቅበት ፍላጎቱን ከማሟላት አንዱን መምረጥ ነበረበት። ዳንኤል፣ የይሖዋ ምሥክር ያልሆነች ሴት ማግባት ፈልጎ ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “አቅኚ ከሆንኩ በኋላም ከእሷ ጋር መጻጻፌን አላቆምኩም። መጨረሻ ላይ ግን ራሴን ዝቅ በማድረግ ተሞክሮ ያለውን አንድ ሽማግሌ አነጋገርኩ፤ ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብኝ ግራ መጋባቴን ነገርኩት። እሱም ለአምላክ ታማኝ መሆን ከፈለግኩ ከእሷ ጋር መጻጻፌን ማቆም እንዳለብኝ እንድገነዘብ ረዳኝ። ከብዙ ጸሎት በኋላ እንዲህ ማድረግ ችያለሁ፤ በእርግጥ ይህን ውሳኔ ሳደርግ ብዙ አልቅሻለሁ። ብዙም ሳይቆይ ግን በአገልግሎቴ የማገኘው ደስታ ጨመረ።” ከጊዜ በኋላ ዳንኤል አንዲት ጥሩ ክርስቲያን ያገባ ሲሆን አሁን በወረዳ የበላይ ተመልካችነት እያገለገለ ነው።

ለአምላክ ታማኝ መሆን ደግ እንድንሆን ይረዳናል

አንድ የእምነት ባልንጀራህ ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅ መንፈሳዊ እርዳታ እንዲያገኝ በማድረግ ታማኝነት ታሳያለህ? (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

13. ዳዊት ኃጢአት በሠራበት ወቅት ናታን ለዳዊትም ሆነ ለአምላክ ታማኝ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

13 ለይሖዋ ታማኝ መሆናችን፣ ለሰዎችም ታማኝ እንድንሆንና እነሱን በተሻለ መንገድ መርዳት እንድንችል ያደርገናል። ነቢዩ ናታን ለይሖዋ ያለውን ታማኝነት ሳያጓድል ለዳዊትም ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ዳዊት ምንዝር እንደፈጸመና የሴትየዋ ባል በጦርነት እንዲገደል ሁኔታዎችን እንዳመቻቸ ናታን አወቀ። ዳዊትን እንዲገሥጸው ይሖዋ ናታንን በላከው ጊዜ ይህ ነቢይ ለዳዊት ታማኝ ቢሆንም ይሖዋን በመታዘዝ በድፍረት የተባለውን አድርጓል። ናታን ተግሣጹን የሰጠው በጥበብና በደግነት ነው። ናታን፣ ዳዊት የፈጸመው ስህተት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብ ለመርዳት ሲል፣ የድሃውን ሰው በግ በግፍ ስለወሰደበት ሀብታም ሰው የሚገልጽ ምሳሌ ነገረው። ሀብታሙ ሰው በፈጸመው ድርጊት ዳዊት በተቆጣ ጊዜ ናታን “ያ ሰው አንተ ነህ!” አለው። ዳዊትም ናታን ምን ማለት እንደፈለገ ገባው!—2 ሳሙ. 12:1-7, 13

14. ለይሖዋ እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶችህ ታማኝ መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

14 ለማን ታማኝ መሆን እንዳለብህ ግራ ስትጋባ ደግነት ሊረዳህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የእምነት ባልንጀራህ ከባድ ኃጢአት እንደሠራ በእርግጠኝነት ታውቃለህ እንበል። ይህ ሰው በተለይ የቅርብ ወዳጅህ ወይም ዘመድህ ከሆነ ለእሱ ታማኝ መሆን እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና ኃጢአቱን የምትደብቅለት ከሆነ ለአምላክ ያለህን ታማኝነት እያጓደልክ ነው። ከማንም በላይ ታማኝ መሆን ያለብህ ለይሖዋ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። በመሆኑም እንደ ናታን ደግ ሆኖም ደፋር ልትሆን ይገባል። ጓደኛህ ወይም ዘመድህ የሽማግሌዎችን እርዳታ እንዲጠይቅ አበረታታው። በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ይህን ካላደረገ ግን ለአምላክ ያለህ ታማኝነት፣ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች እንድታሳውቅ ሊያነሳሳህ ይገባል። እንዲህ ስታደርግ ለይሖዋ ታማኝነት፣ ለወዳጅህ ወይም ለዘመድህ ደግሞ ደግነት ታሳያለህ፤ ምክንያቱም ክርስቲያን ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን ሰው በገርነት ለማስተካከል ይጥራሉ።—ዘሌዋውያን 5:1ን እና ገላትያ 6:1ን አንብብ።

ለአምላክ ታማኝ መሆን ድፍረት ይጠይቃል

15, 16. ኩሲ ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ድፍረት ያስፈለገው ለምንድን ነው?

15 ኩሲ የተባለ ሰው ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ድፍረት ማሳየት አስፈልጎታል። ኩሲ፣ የንጉሥ ዳዊት ታማኝ ወዳጅ ነበር። ሆኖም የዳዊት ልጅ አቢሴሎም የብዙዎችን ልብ በማሸፈት ኢየሩሳሌምን ለመያዝና ዙፋን ላይ ለመውጣት በሞከረበት ወቅት የኩሲ ታማኝነት ተፈተነ። (2 ሳሙ. 15:13፤ 16:15) ዳዊት ከተማዋን ለቆ ሸሸ፤ ታዲያ ኩሲ ምን ያደርግ ይሆን? ታማኝነቱን በማላላት ከአቢሴሎም ጎን ይቆም ይሆን? ወይስ ሕይወቱን ለማትረፍ እየሸሸ ያለውን በዕድሜ የገፋውን ንጉሥ ይከተላል? ኩሲ፣ አምላክ ለሾመው ንጉሥ ታማኝ ለመሆን ስለቆረጠ ዳዊትን ለማግኘት ወደ ደብረ ዘይት ተራራ ወጣ።—2 ሳሙ. 15:30, 32

16 ዳዊት፣ ኩሲ ወደ ኢየሩሳሌም እንዲመለስና የአቢሴሎም ወዳጅ በመምሰል የአኪጦፌልን ምክር እንዲያከሽፍለት ጠየቀው። ኩሲ፣ ሕይወቱን አደጋ ላይ ጥሎ ዳዊት የጠየቀውን በመፈጸም ለይሖዋ ታማኝ መሆኑን አሳይቷል። ልክ ዳዊት እንደጸለየው፣ ደፋር የሆነው ኩሲ የሰጠው ምክር የአኪጦፌል ምክር ከንቱ እንዲሆን አድርጓል።—2 ሳሙ. 15:31፤ 17:14

17. ታማኝ ለመሆን ድፍረት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

17 ለይሖዋ ታማኝ ለመሆን ድፍረት ያስፈልገናል። ብዙዎቻችን ለአምላክ ታማኝ ለመሆን ስንል ከቤተሰባችን አባላት፣ አብረውን ከሚሠሩ ሰዎች ወይም ከዓለማዊ ባለሥልጣናት የሚደርስብንን ጫና በድፍረት ተቋቁመናል። በጃፓን የሚኖረውን ታሮን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ለወላጆቹ ታማኝ መሆንና እነሱን መታዘዝ ከልጅነቱ ጀምሮ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነበር። ይህን የሚያደርገው ግዴታው እንደሆነ ስለተሰማው ሳይሆን ወላጆቹን ለማስደሰት ከልቡ ስለሚፈልግ ነው። በመሆኑም ወላጆቹ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መገናኘቱን እንዲያቆም ከነገሩት በኋላ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት እንደወሰነ ለእነሱ መንገር በጣም ከበደው። ታሮ እንዲህ ብሏል፦ “ወላጆቼ በጣም ስለተናደዱ ቤት ሄጄ እንዳልጠይቃቸው ለብዙ ዓመታት ከልክለውኝ ነበር። በመሆኑም በውሳኔዬ ለመጽናት የሚያስፈልገኝን ድፍረት ለማግኘት ጸለይኩ። አሁን አመለካከታቸው የተቀየረ ሲሆን በየጊዜው እየሄድኩ እንድጠይቃቸው ፈቅደውልኛል።”ምሳሌ 29:25ን አንብብ።

18. ከዚህ የጥናት ርዕስ ምን ትምህርት አግኝተሃል?

18 እንደ ዳዊት፣ ዮናታን፣ ናታንና ኩሲ ሁሉ እኛም ለይሖዋ ታማኝ መሆን የሚያስገኘውን ከፍተኛ እርካታ እናጣጥም። በሌላ በኩል ደግሞ ታማኝነታቸውን ካጓደሉት ከአበኔርና ከአቢሴሎም ትምህርት እንውሰድ። እኛም እንደ ዳዊት ከይሖዋ ጋር መጣበቅ እንደምንፈልግ ጥርጥር የለውም። በእርግጥ ፍጹማን ባለመሆናችን ስህተት መሥራታችን አይቀርም። ያም ቢሆን ከማንም በላይ ታማኝ መሆን የምንፈልገው ለይሖዋ መሆኑን ማሳየት እንችላለን።

^ [1] (አንቀጽ 7) አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።