ይሖዋን በደስታ ማገልገላችሁን ቀጥሉ
በሕይወትህ ውስጥ በጣም የተደሰትክበትን ቀን አስብ። ወደ አእምሮህ የመጣው ያገባህበት ወይም የመጀመሪያ ልጅህ የተወለደበት ቀን ነው? ወይስ ሕይወትህን ለይሖዋ መወሰንህን በውኃ ጥምቀት ያሳየህበት ቀን? ይህ ቀን ለአንተ ትልቅ ትርጉም ያለውና ከምንም በላይ የተደሰትክበት ዕለት እንደሆነ ይሰማህ ይሆናል። አምላክን በሙሉ ልብህ፣ ነፍስህ፣ አእምሮህና ኃይልህ እንደምትወድ የሚያሳይ እርምጃ በሕዝብ ፊት ስትወስድ የእምነት አጋሮችህም በጣም ተደስተው መሆን አለበት!—ማር. 12:30
ከተጠመቅህ በኋላም ይሖዋን በማገልገል ከፍተኛ ደስታ እንዳገኘህ አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ አንዳንድ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች በአንድ ወቅት የነበራቸው ደስታ ቀንሷል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን ለመቀጠል የሚያነሳሱን ምን ምክንያቶች አሉ?
አንዳንዶች ደስታቸውን ያጡት ለምንድን ነው?
ይሖዋ፣ አሁን ያለውን ክፉ ሥርዓት በቅርቡ አጥፍቶ በምትኩ አዲስ ዓለም እንደሚያመጣ የሚገልጸውን ተስፋ የያዘው የመንግሥቱ መልእክት ደስተኛ እንደሚያደርገን ጥርጥር የለውም። ከዚህም በተጨማሪ ሶፎንያስ 1:14 “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ ነው! ቅርብ ነው፤ ደግሞም በፍጥነት እየቀረበ ነው!” በማለት ያረጋግጥልናል። ሆኖም ይህን ቀን ካሰብነው በላይ ለረጅም ጊዜ መጠበቃችን፣ በአንድ ወቅት የነበረን ደስታ እንዲቀንስና ለአምላክ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት እንደቀድሞው በቅንዓት እንዳናከናውን ሊያደርግ ይችላል።—ምሳሌ 13:12
ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ያለን ቅርርብ ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን እንድንቀጥል ሊያበረታታን ይችላል። መጀመሪያውኑም ቢሆን ወደ እውነተኛው አምልኮ የሳበንና አምላክን በደስታ ማገልገል እንድንጀምር የረዳን የይሖዋ አገልጋዮች መልካም ምግባር ሊሆን ይችላል። (1 ጴጥ. 2:12) ይሁን እንጂ የእምነት አጋራችን የሆነ አንድ ክርስቲያን በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች መሠረት ባለመመላለሱ ምክንያት ተግሣጽ ቢሰጠውስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ፣ በይሖዋ ሕዝቦች አምላካዊ ባሕርያት ተማርከው ወደ እውነት የመጡ አንዳንዶች ግራ ሊጋቡና ደስታቸውን ሊያጡ ይችላሉ።
በሰይጣን ክፉ ሥርዓት ውስጥ ያለው የንግዱ ዓለም የሚያስፋፋቸው ፕሮፓጋንዳዎችም ደስታችንን ሊነጥቁን ይችላሉ። ዲያብሎስ በቁጥጥሩ ሥር ያለውን ዓለም በመጠቀም፣ እምብዛም የማያስፈልጉን ነገሮች የግድ እንደሚያስፈልጉን እንዲሰማን ያደርጋል። ይሁንና የሚከተሉትን የኢየሱስ ቃላት ብናስታውስ እንጠቀማለን፦ “ለሁለት ጌቶች ባሪያ ሆኖ መገዛት የሚችል ማንም የለም፤ አንዱን ጠልቶ ሌላውን ይወዳል ማቴ. 6:24) ከዚህ ዓለም የምንችለውን ሁሉ ለማግኘት እየጣርን ይሖዋን በደስታ ማገልገል አንችልም።
ወይም አንዱን ደግፎ ሌላውን ይንቃል። ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።” (‘አዳኛችን በሆነው አምላክ መደሰት’
ይሖዋን ለሚወዱ ሰዎች፣ እሱን ማገልገል ከባድ አይደለም። (1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ እንደሚከተለው ብሎ መናገሩን እናስታውስ፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። ቀንበሬን ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ፤ ለራሳችሁም እረፍት ታገኛላችሁ። ቀንበሬ ልዝብ፣ ሸክሜም ቀላል ነውና።” (ማቴ. 11:28-30) የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ስንሆን የምንሸከመው ቀንበር፣ እረፍት የሚሰጥ ከመሆኑም ሌላ ደስታ ያስገኛል። ደግሞም በይሖዋ አገልግሎት በጣም እንድንደሰት የሚያደርግ ምክንያት እንዳለን ጥርጥር የለውም። ‘አዳኛችን በሆነው አምላክ እንድንደሰት’ ከሚያደርጉን ምክንያቶች መካከል ሦስቱን እስቲ እንመልከት።—ዕን. 3:18
የምናገለግለው ሕይወት የሰጠንን ደስተኛ አምላክ ነው። (ሥራ 17:28፤ 1 ጢሞ. 1:11) ሕልውና ያገኘነው ከፈጣሪያችን ነው። በመሆኑም ከተጠመቅን ምንም ያህል ጊዜ ቢያልፍ እሱን በደስታ ማገልገላችንን እንቀጥላለን።
በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ይሖዋን ለ40 ዓመታት ያገለገለውን ኤክቶርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ወንድም ‘ባረጀ ጊዜም እንኳ ማበቡን ቀጥሏል።’ (መዝ. 92:12-14) ኤክቶር፣ የባለቤቱ መታመም በይሖዋ አገልግሎት የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ቢገድብበትም ደስታውን አላሳጣውም። እንዲህ ይላል፦ “የባለቤቴ ጤንነት እያደር ሲያሽቆለቁል ማየት የሚያሳዝን ከመሆኑም ሌላ እሷን መንከባከብ ተፈታታኝ ነው፤ ያም ቢሆን፣ ይህ ሁኔታ እውነተኛውን አምላክ በማገልገል የማገኘውን ደስታ እንዲነጥቀኝ አልፈቀድኩም። ሕይወቴን ያገኘሁት ሰውን በዓላማ ከፈጠረው ከይሖዋ መሆኑን ማወቄ እሱን በጥልቅ እንድወደውና በሙሉ ልብ እንዳገለግለው የሚነሳሳ በቂ ምክንያት ነው። በስብከቱ ሥራ ንቁ ተሳትፎ ለማድረግ እሞክራለሁ፤ እንዲሁም ደስታዬን እንዳላጣ የመንግሥቱን ተስፋ ሁሌም ለማስታወስ እጥራለሁ።”
ይሖዋ የቤዛውን ዝግጅት በማድረግ አስደሳች ሕይወት መምራት እንድንችል መንገድ ከፍቶልናል። በእርግጥም “አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።” (ዮሐ. 3:16) በእርግጥም፣ ኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት እንዲሆን አምላክ ባደረገው ፍቅራዊ ዝግጅት ላይ እምነት ካለን ኃጢአታችን ይቅር ሊባልልን እና የዘላለም ሕይወት ልናገኝ እንችላለን። ይህ አመስጋኝ እንድንሆን የሚገፋፋ ትልቅ ምክንያት አይደለም? ደግሞስ ለቤዛው ያለን አመስጋኝነት ይሖዋን በደስታ ለማገልገል ሊያነሳሳን አይገባም?
በሜክሲኮ የሚኖር ኼሱስ የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ለሥራዬ ያደርኩ ሰው ነበርኩ፤ ግዴታ ባይኖርብኝም እንኳ አንዳንድ ጊዜ ያለምንም እረፍት አምስት ፈረቃ እሠራ
ነበር። ይህን የማደርገው ተጨማሪ ገንዘብ ለማግኘት ስል ብቻ ነበር። ከዚያም ስለ ይሖዋ ተማርኩ፤ ውድ ልጁን ለሰው ዘር እንደሰጠም አወቅኩ። ይህም እሱን የማገልገል ከፍተኛ ምኞት እንዲያድርብኝ አደረገ። በመሆኑም ሕይወቴን ለይሖዋ ወሰንኩ፤ በዚያ ኩባንያ ውስጥ ለ28 ዓመታት የሠራሁ ቢሆንም ሥራዬን ለቅቄ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመርኩ።” ከዚያ ጊዜ ጀምሮ አምላክን ለዓመታት በደስታ ሲያገለግል ቆይቷል።የምናፈራው ፍሬ፣ ሐዘን ሳይሆን ታላቅ ደስታ ያስገኛል። ይሖዋን ከማወቅህ በፊት ምን ዓይነት ሕይወት እንደነበረህ ታስታውሳለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የነበሩትን ክርስቲያኖች “በአንድ ወቅት የኃጢአት ባሪያዎች” እንደነበሩ ካስታወሳቸው በኋላ አሁን ያሉበትን ሁኔታ ሲገልጽ “የጽድቅ ባሪያዎች ሆናችኋል” ብሏል። ክርስቲያኖች ከሆኑ በኋላ “በቅድስና ጎዳና” ፍሬ ያፈሩ ሲሆን ይህም በመጨረሻ የዘላለም ሕይወት ያስገኛል። (ሮም 6:17-22) እኛም፣ በሥነ ምግባር የረከሰ ወይም ዓመፅ የሚንጸባረቅበት አኗኗር ለሚያስከትለው ሐዘን ሳንጋለጥ ቅዱስ የሆነ የሕይወት ጎዳና እየተከተልን ነው። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ነው!
የኻይሜን ሁኔታ እንመልከት፤ በአምላክ መኖር የማያምንና የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ የሚደግፍ ሰው ነበር፤ ከዚህም ሌላ ኻይሜ በቡጢ ስፖርት ይካፈል ነበር። ይህ ሰው በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር እዚያ በሚታየው ፍቅር ተደነቀ። ኻይሜ የቀድሞ አኗኗሩን ለመተው ስለፈለገ ይሖዋን በእሱ ለማመን እንዲረዳው በጸሎት ለመነው። ኻይሜ እንዲህ ብሏል፦ “አፍቃሪ አባትና መሐሪ የሆነ አምላክ መኖሩን እያደር ተገነዘብኩ። ከይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር ተስማምቼ መኖሬ ጥበቃ ሆኖልኛል። አኗኗሬን ባልለውጥ ኖሮ እኔም በቡጢ ስፖርት ይካፈሉ እንደነበሩ አንዳንድ የቀድሞ ጓደኞቼ እሞት ነበር። በሕይወቴ ውስጥ በጣም የተደሰትኩባቸው ዓመታት ይሖዋን በማገልገል ያሳለፍኳቸው ናቸው።”
ተስፋ አትቁረጡ!
የዚህን ክፉ ሥርዓት ፍጻሜ በምንጠባበቅበት ጊዜ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን የሚገባ ይመስልሃል? ‘ለመንፈስ ብለን እየዘራን’ እንደሆነና ይህን በማድረጋችንም “የዘላለም ሕይወት” እንደምናጭድ አስታውስ። እንግዲያው “ጊዜው ሲደርስ ስለምናጭድ ተስፋ ቆርጠን መልካም ሥራ መሥራታችንን አንተው።” (ገላ. 6:8, 9) በይሖዋ እርዳታ እየታገዝን እስከ መጨረሻው እንጽና፤ “ታላቁን መከራ” በሕይወት ለማለፍ የሚያስፈልጉንን ባሕርያት ለማዳበር ጠንክረን እንሥራ፤ እንዲሁም መከራ ቢደርስብንም ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን እንቀጥል።—ራእይ 7:9, 13, 14፤ ያዕ. 1:2-4
አምላክ የምናከናውነውን ሥራም ሆነ ለእሱና ለስሙ ያለንን ፍቅር በሚገባ ስለሚያውቅ ጽናታችን ሽልማት እንደሚያስገኝ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋን በደስታ ማገልገላችንን ከቀጠልን እንደሚከተለው በማለት እንደተናገረው እንደ መዝሙራዊው ዳዊት ዓይነት ስሜት ይኖረናል፦ “ይሖዋን ሁልጊዜ በፊቴ አደርገዋለሁ። እሱ በቀኜ ስላለ ፈጽሞ አልናወጥም። ስለዚህ ልቤ ሐሴት ያደርጋል፤ ሁለንተናዬ ደስ ይለዋል። ያለ ስጋትም እኖራለሁ።”—መዝ. 16:8, 9