በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ ሕዝቡን በሕይወት መንገድ ላይ ይመራል

ይሖዋ ሕዝቡን በሕይወት መንገድ ላይ ይመራል

“መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ።”—ኢሳ. 30:21

መዝሙሮች፦ 65, 48

1, 2. (ሀ) የብዙ ሰዎች ሕይወት እንዲተርፍ ያስቻለው የትኛው ማስጠንቀቂያ ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) የአምላክ ሕዝቦች ሕይወታቸውን ከአደጋ የሚጠብቅ ምን መመሪያ ያገኛሉ?

“ቁም፣ ተመልከት፣ ስማ።” እነዚህ ቃላት ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ሰዎች ሕይወት ከአደጋ አትርፈዋል። ከ100 ዓመታት በፊት በሰሜን አሜሪካ ውስጥ የባቡር ሐዲድ ማቋረጫ ላይ እነዚህ ቃላት በትልቁ ተጽፈው ይለጠፉ ነበር። ለምን? ባቡሩ በፍጥነት በሚመጣበት ሰዓት ተሽከርካሪዎች ሃዲዱ ላይ ተገኝተው እንዳይገጩ ነው። በእርግጥም፣ ለዚህ ማስጠንቀቂያ ትኩረት መስጠት የሰዎች ሕይወት እንዲተርፍ አስችሏል።

2 ይሖዋ ከአደጋ የሚጠብቁንን ምልክቶች ከመለጠፍ እጅግ የተሻለ ነገር ያደርጋል። ሕዝቦቹን እየመራ ወደ ዘላለም ሕይወት የሚወስዳቸውንና አደጋ የሌለበትን መንገድ ይጠቁማቸዋል። ከዚህ በተጨማሪ አፍቃሪ እረኛ እንደመሆኑ መጠን በጎቹ አደገኛ የሆነ ጎዳና ከመከተል እንዲርቁ አስፈላጊውን መመሪያና ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል።​—ኢሳይያስ 30:20, 21ን አንብብ።

ይሖዋ ከጥንት ጀምሮ ሕዝቡን ሲመራ ቆይቷል

3. የሰው ልጆች ወደ ሞት በሚመራ ጎዳና ላይ መጓዝ የጀመሩት እንዴት ነው?

3 በታሪክ ዘመናት ሁሉ ይሖዋ ዝርዝር መመሪያዎች ወይም ትእዛዛት ሲሰጥ ቆይቷል። ለምሳሌ በኤደን ገነት የዘላለም ሕይወትና ዘላቂ ደስታ ሊያስገኝ የሚችል ግልጽ መመሪያ ለአዳምና ለሔዋን ሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍ. 2:15-17) እነዚህ ባልና ሚስት መመሪያውን ቢታዘዙ ኖሮ ችግር ላይ አይወድቁም ነበር፤ ባለመታዘዛቸው ምክንያት ግን በመከራ የተሞላ እንዲሁም ያለምንም ተስፋ በሞት የሚደመደም ሕይወት ለመምራት ተገደዋል። ሔዋን መመሪያውን በመታዘዝ ፋንታ ከአንድ ተራ እንስሳ የመጣ የሚመስለውን ምክር ተቀብላለች። አዳምም ቢሆን ሟች የሆነችው ሔዋን የነገረችውን ነገር ሰማ። ሁለቱም አፍቃሪ የሆነው አባታቸው የሰጣቸውን መመሪያ አልተቀበሉም። በዚህም የተነሳ የሰው ልጆች ወደ ሞት በሚመራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀመሩ።

4. (ሀ) ከጥፋት ውኃው በኋላ ተጨማሪ መመሪያዎች ያስፈለጉት ለምንድን ነው? (ለ) የተፈጠሩት አዳዲስ ሁኔታዎች የአምላክ አስተሳሰብ ግልጽ እንዲሆን ያደረጉት እንዴት ነው?

4 በኖኅ ዘመን አምላክ ሕይወት አድን የሆነ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። ከጥፋት ውኃው በኋላ አምላክ ደም መብላትን የሚከለክል ግልጽ መመሪያ ሰጠ። ይህ ያስፈለገው ለምንድን ነው? አዳዲስ ሁኔታዎች ስለተፈጠሩ ነው። ይሖዋ የሰው ልጆች የእንስሳት ሥጋ እንዲበሉ ፈቀደላቸው። በመሆኑም ከዚህ ጋር በተያያዘ አዳዲስ መመሪያዎች ያስፈልጉ ነበር፤ ለምሳሌ “ሕይወቱ ማለትም ደሙ በውስጡ ያለበትን ሥጋ ብቻ አትብሉ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸዋል። (ዘፍ. 9:1-4) በወቅቱ የተፈጠሩት አዳዲስ ሁኔታዎች አምላክ የእሱ ስለሆነው ነገር ማለትም ስለ ሕይወት ያለው አመለካከት ግልጽ እንዲሆን አድርጓል። ይሖዋ ፈጣሪና ሕይወት ሰጪ በመሆኑ ሕይወትን የሚመለከቱ መመሪያዎችን የማውጣት መብት ያለው እሱ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ሰው ሰውን መግደል እንደሌለበት ደንግጓል። አምላክ ሕይወትንና ደምን የሚመለከተው ቅዱስ አድርጎ ስለሆነ እነዚህን ነገሮች አላግባብ የሚጠቀሙ ሰዎች በእሱ ዘንድ ተጠያቂ ይሆናሉ።—ዘፍ. 9:5, 6

5. በዚህ ጥናት ውስጥ ምን እንመረምራለን? ለምንስ?

5 አምላክ ከዚያ በኋላ በነበሩት ዘመናት መመሪያ መስጠቱን እንዴት እንደቀጠለ የሚያሳዩ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመለከታለን። እነዚህን ምሳሌዎች መመልከታችን ይሖዋ ወደ አዲሱ ዓለም ሲመራን እሱን ለመከተል ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል።

አዲስ ብሔር፣ አዲስ መመሪያ

6. የአምላክ ሕዝቦች በሙሴ በኩል የተሰጣቸውን ሕግ መታዘዝ የነበረባቸው ለምንድን ነው? እስራኤላውያን ምን ዓይነት አመለካከት እንዲኖራቸው ይጠበቅባቸው ነበር?

6 በሙሴ ዘመን፣ ተገቢ ሥነ ምግባርንና ተቀባይነት ያለውን አምልኮ የሚመለከት ግልጽ መመሪያ ያስፈልግ ነበር። ለምን? በዚህ ጊዜም ቢሆን አንዳንድ ሁኔታዎች በመለወጣቸው ነው። የያዕቆብ ዘሮች ከ200 ለሚበልጡ ዓመታት የኖሩት ሙታንና ጣዖታት በሚመለኩበት እንዲሁም ለአምላክ ክብር የማያመጡ ሌሎች እምነቶችና ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በሞሉበት አገር ይኸውም በግብፅ ነበር። የአምላክ ሕዝቦች ከግብፅ ባርነት ነፃ ሲወጡ አዳዲስ መመሪያዎች አስፈለጉ። ከዚህ በኋላ በግዞት ያለ ብሔር መሆናቸው አብቅቶ በይሖዋ ሕግ የሚመራ ነፃ ብሔር ይሆናሉ። አንዳንድ የማመሳከሪያ ጽሑፎች እንደሚገልጹት “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “መጠቆም፣ መምራት፣ ማስተማር” የሚል ትርጉም ካለው ቃል ጋር ይዛመዳል። የሙሴ ሕግ እስራኤላውያንን፣ ሌሎች ብሔራት ይከተሉት ከነበረው ያዘቀጠ የሥነ ምግባርና የሃይማኖት ልማድ እንደሚጠብቅ ግድግዳ ሆኖ አገልግሏል። እስራኤላውያን የአምላክን መመሪያ ሲታዘዙ ብሔሩ የእሱን በረከት ያገኝ ነበር። መመሪያውን ችላ ሲሉ ደግሞ አስከፊ መዘዝ ደርሶባቸዋል።—ዘዳግም 28:1, 2, 15ን አንብብ።

7. (ሀ) ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያ የሰጠው ለምን እንደሆነ አብራራ። (ለ) ሕጉ ለእስራኤላውያን ሞግዚት የነበረው እንዴት ነው?

7 በወቅቱ መመሪያዎች አስፈላጊ የነበሩበት ሌላም ምክንያት አለ። ሕጉ ከይሖዋ ፈቃድ ጋር በተያያዘ አንድ ትልቅ ክንውን እንደሚኖር ይጠቁም ነበር። ይህም የመሲሑ የኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት ነው። ሕጉ እስራኤላውያን ፍጹማን እንዳልሆኑ ምንም በማያሻማ መንገድ አሳይቷል። በተጨማሪም ቤዛ ማለትም ኃጢአታቸውን ሙሉ በሙሉ የሚሸፍን ፍጹም የሆነ መሥዋዕት እንደሚያስፈልጋቸው አስገንዝቧቸዋል። (ገላ. 3:19፤ ዕብ. 10:1-10) ከዚህም ሌላ የመሲሑ የዘር ሐረግ እንዲጠበቅ አድርጓል፤ እንዲሁም መሲሑ ሲመጣ በቀላሉ ተለይቶ እንዲታወቅ አስችሏል። በእርግጥም ሕጉ ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ጊዜያዊ አስተማሪ ወይም ‘ሞግዚት’ ሆኖ አገልግሏል።—ገላ. 3:23, 24

8. ከሙሴ ሕግ በስተጀርባ ባሉት መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ያለብን ለምንድን ነው?

8 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን እኛም ለእስራኤል ብሔር የተሰጠው ሕግ በውስጡ ካካተታቸው መመሪያዎች ጥቅም ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ከሕጉ በስተጀርባ ያሉትን መሠረታዊ ሥርዓቶች ቆም ብለን በመመርመር ነው። በእነዚህ ሕጎች ሥር ባንሆንም እንኳ አብዛኞቹ ከዕለት ተዕለት ሕይወታችንና ለቅዱሱ አምላካችን ለይሖዋ ከምናቀርበው አምልኮ ጋር በተያያዘ አስተማማኝ መመሪያ ይሰጡናል። አምላክ እነዚህ ሕጎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲጻፉ ያደረገው ትምህርት እንድንቀስምባቸውና ከክርስቲያኖች የሚጠበቀውን የላቀ የሥነ ምግባር ደረጃ መገንዘብ እንድንችል ነው። ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ በል፦ “‘አታመንዝር’ እንደተባለ ሰምታችኋል። እኔ ግን እላችኋለሁ፣ አንዲትን ሴት በፍትወት ስሜት የሚመለከት ሁሉ በዚያን ጊዜ በልቡ ከእሷ ጋር አመንዝሯል።” በመሆኑም ምንዝር ከመፈጸም መራቅ ብቻ ሳይሆን የፆታ ብልግና የመፈጸም ምኞትንም ማስወገድ ይኖርብናል።—ማቴ. 5:27, 28

9. አምላክ አዲስ መመሪያ እንዲሰጥ ያደረገው አዲስ ሁኔታ ምንድን ነው?

9 ኢየሱስ መሲሕ ሆኖ በመጣ ጊዜ አዲስ መለኮታዊ መመሪያ እንዲሁም የይሖዋን ዓላማ በተመለከተ ተጨማሪ ዝርዝር ሐሳብ አስፈለገ። ለምን? በዚህ ጊዜም ቢሆን አዳዲስ ሁኔታዎች ተከስተው ስለነበር ነው። በ33 ዓ.ም. ይሖዋ ሞገሱን ከሥጋዊ እስራኤል ጉባኤ ላይ አንስቶ ለክርስቲያን ጉባኤ ሰጠ።

ለአዲሱ መንፈሳዊ ብሔር የተሰጠ መመሪያ

10. የክርስቲያን ጉባኤ አዳዲስ ሕጎች ያስፈለጉት ለምንድን ነው? እነዚህ ሕጎች ለእስራኤላውያን ከተሰጡት ሕጎች የሚለዩትስ እንዴት ነው?

10 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ወደ ክርስትና የመጡት የአምላክ ሕዝቦች ከአምልኮና ከአኗኗር ጋር የተያያዘ አዲስ ወይም ዝርዝር መመሪያ ተሰጣቸው። እነዚህ ለአምላክ ያደሩ ሰዎች በአዲስ ቃል ኪዳን ታቀፉ። የሙሴ ሕግ የተሰጠው ለአንድ ብሔር ይኸውም ለሥጋዊ እስራኤላውያን ነበር። በአንጻሩ ግን መንፈሳዊ እስራኤል የተለያየ ብሔርና አኗኗር ከነበራቸው ሰዎች የተውጣጣ ነው። በእርግጥም “አምላክ [አያዳላም]፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (ሥራ 10:34, 35) ሥጋዊ እስራኤላውያን ተስፋይቱ ምድር በነበሩበት ጊዜ ይጠቀሙበት የነበረው የሙሴ ሕግ የተቀረጸው በድንጋይ ላይ ነበር። በሌላ በኩል መንፈሳዊ እስራኤላውያን የሚመሩበት ‘የክርስቶስ ሕግ’ በዋነኝነት የተመሠረተው በልብ ላይ በተቀረጹ መሠረታዊ ሥርዓቶች ነው። ክርስቲያኖች የሚኖሩት የትም ይሁን የት ‘በክርስቶስ ሕግ’ ሥር ናቸው፤ ከሕጉም ጥቅም አግኝተዋል።—ገላ. 6:2

11. ‘ከክርስቶስ ሕግ’ ጋር የተያያዙት የክርስቲያናዊ ሕይወት ሁለት ገጽታዎች የትኞቹ ናቸው?

11 መንፈሳዊ እስራኤላውያን አምላክ በልጁ በኩል ከሚሰጠው አመራር በእጅጉ ይጠቀማሉ። አዲሱ ቃል ኪዳን ከመቋቋሙ በፊት ኢየሱስ ከፍተኛ ትርጉም ያላቸው ሁለት ትእዛዛት ሰጠ። አንዱ ከስብከቱ ሥራ ጋር የተያያዘ ነው። ሌላኛው ደግሞ የኢየሱስ ተከታዮች ከሚያሳዩት ምግባርና የእምነት ባልንጀሮቻቸውን ከሚይዙበት መንገድ ጋር የሚያያዝ ነው። እነዚህ መመሪያዎች የተሰጡት ለሁሉም ክርስቲያኖች ስለሆነ ተስፋቸው በሰማይ መኖርም ይሁን በምድር በዛሬው ጊዜ ያሉ የአምላክ አገልጋዮችን በሙሉ ይመለከታሉ።

12. ከስብከቱ ሥራ ጋር በተያያዘ የተከሰተው አዲስ ነገር ምንድን ነው?

12 ኢየሱስ ለተከታዮቹ ስለሰጣቸው የስብከት ሥራ አስብ። ምሥራቹን የሚሰብኩበት ዘዴም ሆነ ሥራውን የሚያከናውኑበት ስፋት በዓይነቱ የተለየ ነው። ከዚያ በፊት በነበሩት ዘመናት፣ እስራኤላውያን የሌላ ብሔር ሰዎች ይሖዋን ለማምለክ ወደ እስራኤል ሲመጡ በደስታ ይቀበሏቸው ነበር። (1 ነገ. 8:41-43) እንዲህ ያደርጉ የነበረው ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ ያለውን ትእዛዝ ከመስጠቱ በፊት ነው። (ጥቅሱን አንብብ።) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ግን ወደ ብሔራት ሁሉ “ሂዱ” የሚል መመሪያ ተሰጣቸው። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ይሖዋ አዲስ ዓይነት አሠራር መጠቀም እንደጀመረ የሚጠቁም ማስረጃ ታየ፤ ይህም ዓለም አቀፍ የወንጌላዊነት ሥራ ነው። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ የአዲሱ ጉባኤ አባል ለሆኑት 120 ደቀ መዛሙርት ኃይል ስለሰጣቸው በተአምር ባገኙት ችሎታ ለአይሁዳውያንና ወደ ይሁዲነት ለተቀየሩ ሰዎች በየቋንቋቸው መስበክ ጀመሩ። (ሥራ 2:4-11) ከዚያም ክልላቸው ሰፍቶ ሳምራውያንን አካተተ። በኋላም በ36 ዓ.ም. ክልላቸው ይበልጥ በመስፋቱ ላልተገረዙ አሕዛብ መስበክ ጀመሩ። የስብከቱ መስክ አይሁዳውያንን ካቀፈ “ኩሬ” ተነስቶ የሰውን ዘር ወዳቀፈ “ውቅያኖስ” አደገ ሊባል ይችላል።

13, 14. (ሀ) ኢየሱስ የሰጠው “አዲስ ትእዛዝ” ምን ያካትታል? (ለ) ኢየሱስ ከተወው ምሳሌ ምን እንማራለን?

13 አሁን ደግሞ የእምነት ባልንጀሮቻችንን በምንይዝበት መንገድ ላይ እናተኩር። ኢየሱስ “አዲስ ትእዛዝ” ሰጥቷል። (ዮሐንስ 13:34, 35ን አንብብ።) ይህ ትእዛዝ በዕለት ተዕለት ሕይወት ፍቅር ከማሳየት ባለፈ ለእምነት ባልንጀራችን ሕይወታችንንም ጭምር ለመስጠት ፈቃደኛ መሆንን የሚጠይቅ ነው። በሙሴ ሕግ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ሐሳብ አናገኝም።—ማቴ. 22:39፤ 1 ዮሐ. 3:16

14 በዚህ ረገድ ኢየሱስ ተወዳዳሪ የሌለው ምሳሌ ትቷል። ለደቀ መዛሙርቱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ነበረው። እንዲህ ያለው ፍቅር ለደቀ መዛሙርቱ ሲል ሕይወቱን እስከመስጠት የሚያደርስ ነው፤ ኢየሱስ ደግሞ ይህን ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። በመሆኑም ከእኛም ሆነ ከደቀ መዛሙርቱ በሙሉ እንዲህ ያለ መንፈስ ይጠብቃል። ለእምነት ባልንጀሮቻችን ስንል ለመከራ አልፎ ተርፎም ለሞት በሚዳርግ ጎዳና ላይ መሄድ ሊያስፈልገን ይችላል።—1 ተሰ. 2:8

ለዘመናችንም ሆነ ለወደፊቱ ጊዜ የተሰጡ መመሪያዎች

15, 16. አሁን ያለንበት አዲስ ሁኔታ ምን ይመስላል? አምላክ እየመራን ያለውስ እንዴት ነው?

15 በተለይ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ከተሾመበት ጊዜ አንስቶ ኢየሱስ ሕዝቡ በተገቢው ጊዜ መንፈሳዊ ምግብ እንዲያገኝ ዝግጅት አድርጓል። (ማቴ. 24:45-47) ይህ ምግብ የተፈጠሩትን አዳዲስ ሁኔታዎች ለማስተናገድ የሚረዱ ጠቃሚ መመሪያዎችን ያካተተ ነው።

16 የምንኖረው መጽሐፍ ቅዱስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ብሎ በሚጠራው ዘመን ውስጥ ነው፤ በቅርቡ ደግሞ ፈጽሞ ተከስቶ የማያውቅ መከራ ይጀምራል። (2 ጢሞ. 3:1፤ ማር. 13:19) በተጨማሪም ሰይጣንና አጋንንቱ ከሰማይ ተባረው በምድር አካባቢ እንዲወሰኑ ተደርገዋል፤ ይህም በምድር ነዋሪዎች ላይ ከባድ ወዮታ አስከትሏል። (ራእይ 12:9, 12) እኛ ደግሞ ከዚህ በፊት ታይቶ በማያውቅ ስፋት ለብሔራትና የተለያየ ቋንቋ ለሚናገሩ ሕዝቦች ምሥራቹን የማዳረስ ታሪካዊና ተወዳዳሪ የሌለው ተልእኮ ተሰጥቶናል!

17, 18. ለሚሰጡን መመሪያዎች ምን ምላሽ ልንሰጥ ይገባል?

17 የአምላክ ድርጅት ለስብከቱ ሥራ ያዘጋጃቸውን መሣሪያዎች መጠቀም አለብን። እንዲህ የማድረግ ፍላጎት አለህ? በስብሰባዎቻችን ላይ፣ እነዚህን መሣሪያዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ የሚሰጡትን መመሪያዎች በንቃት ትከታተላለህ? ደግሞስ እነዚህ መመሪያዎች ከአምላክ እንደመጡ ይሰማሃል?

18 በእርግጥም የአምላክ በረከት እንዳይቋረጥብን ከፈለግን በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ለሚሰጡን መመሪያዎች ትኩረት መስጠት አለብን። በአሁኑ ጊዜ የታዛዥነት መንፈስ ካለን የሰይጣንን ክፉ ሥርዓት የሚያስወግደው ‘ታላቁ መከራ’ በሚጀምርበት ወቅት መመሪያዎችን መከተል ቀላል ይሆንልናል። (ማቴ. 24:21) ከዚያ በኋላ ከሰይጣን ተጽዕኖ ሙሉ በሙሉ በጸዳ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ምድር ውስጥ እንኖራለን፤ በዚህ ጊዜም አዳዲስ መመሪያዎች ያስፈልጉናል።

ምድር ገነት ስትሆን በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚገልጹ መመሪያዎችን የያዙ ጥቅልሎች ይከፈታሉ (አንቀጽ 19, 20⁠ን ተመልከት)

19, 20. የትኞቹ ጥቅልሎች ይከፈታሉ? ይህስ ምን ያስገኛል?

19 በሙሴ አመራር ሥር የነበረው የእስራኤል ብሔርም ሆነ ከጊዜ በኋላ የተቋቋመውና “በክርስቶስ ሕግ” ሥር ያለው የክርስቲያን ጉባኤ አዳዲስ መመሪያዎች አስፈልገውት ነበር። በተመሳሳይም በአዲሱ ዓለም ውስጥ እንዴት መኖር እንዳለብን የሚገልጹ መመሪያዎችን የያዙ ጥቅልሎች እንደሚከፈቱ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ራእይ 20:12ን አንብብ።) እነዚህ ጥቅልሎች በዚያ ጊዜ ይሖዋ ከሕዝቡ የሚጠብቃቸውን ነገሮች እንደሚገልጹ እንጠብቃለን። ከሞት የሚነሱትን ጨምሮ ሁሉም ሰዎች እነዚህን ጥቅልሎች በማጥናት አምላክ ለእነሱ ያለውን ዓላማ ማወቅ ይችላሉ። ጥቅልሎቹ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ እንድንረዳ እንደሚያስችሉን ጥርጥር የለውም። ምድር ገነት ስትሆን በዚያ የሚኖሩት ሰዎች በመንፈስ መሪነት ስለተጻፈው የአምላክ ቃል ያላቸው እውቀት እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም ከአዳዲሶቹ ጥቅልሎች አዲስ መረጃ ያገኛሉ። በእነዚህ ነገሮች መመራታቸው ሰዎችን በፍቅር፣ በአሳቢነትና በአክብሮት እንዲይዙ ያስችላቸዋል። (ኢሳ. 26:9) በንጉሡ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር የሚኖረው የትምህርት መርሐ ግብር ምን ሊመስል እንደሚችል አስብ!

20 “በጥቅልሎቹ ውስጥ [ለተጻፉት] ነገሮች” ጥሩ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። በመጨረሻው ፈተና ወቅት ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው የሚኖሩ ሰዎችን ስም ይሖዋ ‘በሕይወት መጽሐፍ’ ላይ በማይፋቅ መንገድ ይጽፈዋል። እኛም ይህን በረከት ማግኘት እንችላለን! ቆም ብለን የአምላክን ቃል ከመረመርን፣ ለእኛ ምን ትርጉም እንዳለው ለመረዳት በትኩረት ከተመለከትን እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ አምላክ የሚሰጠንን መመሪያ በመታዘዝ እሱን ከሰማን ወደፊት ታላቁን መከራ በሕይወት ለማለፍ መጠባበቅ እንችላለን፤ እንዲሁም ፍጹም ጥበብ ስላለውና አፍቃሪ ስለሆነው አምላካችን ይሖዋ ለዘላለም የመማር አጋጣሚ እናገኛለን።—መክ. 3:11፤ ሮም 11:33