በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?

‘ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ’ ያለብን ለምንድን ነው?

“ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ [አታውቁም]።”—ማቴ. 24:42

መዝሙሮች፦ 136, 129

1. ሰዓቱን ወይም በአካባቢያችን እየተከናወነ ያለውን ነገር ማስተዋላችን አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ በምሳሌ አስረዳ። (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

ስብሰባው ሊጀምር የቀሩት ጥቂት ደቂቃዎች ናቸው። ሊቀ መንበሩ ወደ መድረክ ወጥቶ ስብሰባው ሊጀምር መሆኑን ይገልጻል። ከዚያም ሙዚቃው ይጀምራል። በዚህ ጊዜ ተሰብሳቢዎቹ ቁጭ ብለው ሙዚቃውን በጸጥታ ያዳምጣሉ። ይህም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ኦርኬስትራ ያዘጋጀውን ግሩም ሙዚቃ በማዳመጥ አእምሯቸውንና ልባቸውን ቀጥሎ ለሚቀርቡት ንግግሮች ለማዘጋጀት ይረዳቸዋል። ይሁንና አንዳንዶች ትኩረታቸው በመከፋፈሉና ፕሮግራሙ ሊጀምር መሆኑን ልብ ባለማለታቸው ወዲያ ወዲህ ማለታቸውንና ከጓደኞቻቸው ጋር መጫወታቸውን ይቀጥሉ ይሆናል። እነዚህ ግለሰቦች ሰዓቱንና በአካባቢያቸው እየተከናወነ ያለውን ነገር ይኸውም ሊቀ መንበሩ መድረክ ላይ መውጣቱን፣ ሙዚቃው መጀመሩንና ተሰብሳቢዎቹ ቁጭ ብለው እየተከታተሉ መሆናቸውን በማስተዋል ረገድ ንቁዎች አይደሉም። ይህ ሁኔታ ሰዓቱን ወይም በአካባቢያችን እየተከናወነ ያለውን ነገር የማናስተውል ከሆነ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ያሳያል። ከዚህ ትልቅ ትምህርት ማግኘት ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ነቅቶ መጠበቅ የሚያሻው ትልቅ ክንውን ከፊታችን ይጠብቀናል። ይህ ክንውን ምንድን ነው?

2. ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ያላቸው ለምንድን ነው?

2 ኢየሱስ ክርስቶስ ስለዚህ “ሥርዓት መደምደሚያ” በተናገረበት ወቅት ደቀ መዛሙርቱን እንዲህ በማለት አሳስቧቸዋል፦ “የተወሰነው ጊዜ መቼ እንደሆነ ስለማታውቁ ምንጊዜም በንቃት ተከታተሉ፤ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ።” ከዚያም “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” በማለት ደጋግሞ መክሯቸዋል። (ማቴ. 24:3፤ ማርቆስ 13:32-37ን አንብብ።) ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ያደረገውን ይህን ውይይት በተመለከተ ማቴዎስ ያሰፈረው ዘገባም ደቀ መዛሙርቱ ሁልጊዜ ንቁ እንዲሆኑ ኢየሱስ እንዳሳሰባቸው ይገልጻል፤ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ጌታችሁ በየትኛው ቀን እንደሚመጣ ስለማታውቁ ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ። . . . እናንተም የሰው ልጅ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሁኑ።” አክሎም “እንግዲህ ቀኑንም ሆነ ሰዓቱን ስለማታውቁ ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏቸዋል።—ማቴ. 24:42-44፤ 25:13

3. ኢየሱስ የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ልብ ማለት ያለብን ለምንድን ነው?

3 እኛ የይሖዋ ምሥክሮች፣ ኢየሱስ የሰጠውን ይህን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር እንመለከተዋለን። የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ ውስጥ እንደሆነና ‘ታላቁ መከራ’ ሊጀምር የቀረው ጊዜ አጭር መሆኑን እናውቃለን። (ዳን. 12:4፤ ማቴ. 24:21) በተለያዩ የዓለም ክፍሎች አሰቃቂ ጦርነቶች እንደሚካሄዱ እንዲሁም የምግብ እጥረት፣ ቸነፈርና የምድር ነውጥ እንደሚከሰት እናውቃለን፤ ከዚህም በላይ የሥነ ምግባር ብልግና እንዲሁም ሕገ ወጥነት እየተስፋፋ ሲሆን ብዙዎች በሃይማኖት ግራ ተጋብተዋል። በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ የይሖዋ ሕዝቦች ስለ አምላክ መንግሥት በስፋት እየሰበኩ ነው። (ማቴ. 24:7, 11, 12, 14፤ ሉቃስ 21:11) እኛም ኢየሱስ የሚመጣበትንና የአምላክን ዓላማ የሚያስፈጽምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—ማር. 13:26, 27

ቀኑ እየቀረበ ነው!

4. (ሀ) በአሁኑ ጊዜ ኢየሱስ አርማጌዶን የሚጀምርበትን ጊዜ ያውቃል ማለት የምንችለው ለምንድን ነው? (ለ) ታላቁ መከራ መቼ እንደሚጀምር ባናውቅም ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

4 በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ፣ እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ የሚጀምርበትን ሰዓት እናውቃለን። ከታላቁ መከራ ጋር በተያያዘ ግን የቱንም ያህል ጥረት ብናደርግ ይህ ክንውን የሚጀምርበትን ቀንና ሰዓት ቀርቶ ዓመቱን እንኳ ማወቅ አንችልም። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ “ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም” ብሎ ነበር። (ማቴ. 24:36) ይሁንና ክርስቶስ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ በሰይጣን ዓለም ላይ ጦርነት እንዲያውጅ ሥልጣን ተሰጥቶታል። (ራእይ 19:11-16) በመሆኑም በአሁኑ ወቅት ኢየሱስ፣ አርማጌዶን የሚጀምርበትን ጊዜ ያውቃል ብለን ማሰባችን ምክንያታዊ ነው። እኛ ግን ይህ ቀን መቼ እንደሚመጣ አናውቅም። እንግዲያው ታላቁ መከራ የሚመጣበትን ጊዜ በንቃት መጠባበቃችን የግድ ነው። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ይህ ክንውን መቼ እንደሚፈጸም ምንጊዜም ቢሆን ያውቃል። መጨረሻው የሚመጣበትን ትክክለኛ ጊዜ ወስኗል። ታላቁ መከራ የሚጀምርበት ጊዜ ከቀን ወደ ቀን እየቀረበ ሲሆን ይህ ጊዜ ፈጽሞ “አይዘገይም!” (ዕንባቆም 2:1-3ን አንብብ።) ይህን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

5. ይሖዋ ያስነገራቸው ትንቢቶች ምንጊዜም ቢሆን ልክ በተባለው ጊዜ ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ የሚያሳይ ምሳሌ ጥቀስ።

5 ይሖዋ ያስነገራቸው ትንቢቶች ምንጊዜም ቢሆን ልክ በተባለው ጊዜ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል! እስራኤላውያንን ልክ በተናገረው ጊዜ ከግብፅ ነፃ ያወጣቸው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት። ሙሴ ስለ ኒሳን 14, 1513 ዓ.ዓ. ሲናገር “አራት መቶ ሠላሳው ዓመት በተፈጸመበት በዚያው ዕለት መላው የይሖዋ ሠራዊት ከግብፅ ምድር ወጣ” ብሏል። (ዘፀ. 12:40-42) እነዚህ “430 ዓመታት” መቆጠር የጀመሩት ይሖዋ ከአብርሃም ጋር የገባው ቃል ኪዳን ከጸናበት ጊዜ ይኸውም ከ1943 ዓ.ዓ. ጀምሮ ነው። (ገላ. 3:17, 18) ይህ ከሆነ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይሖዋ ለአብርሃም እንዲህ ብሎት ነበር፦ “ዘሮችህ በባዕድ አገር ባዕዳን ሆነው እንደሚኖሩ እንዲሁም በዚያ ያሉት ሰዎች ለ400 ዓመት በባርነት እንደሚገዟቸውና እንደሚያጎሳቁሏቸው በእርግጥ እወቅ።” (ዘፍ. 15:13፤ ሥራ 7:6) ይስሐቅ፣ ጡት በጣለበት ጊዜ እስማኤል አሹፎበት ነበር፤ የአብርሃም ዘሮች የሚጎሳቆሉባቸው “400 ዓመታት” የጀመሩት በዚህ ጊዜ ይኸውም በ1913 ዓ.ዓ. መሆን አለበት፤ እነዚህ 400 ዓመታት ያበቁት ደግሞ እስራኤላውያን በ1513 ዓ.ዓ. ከግብፅ ነፃ በወጡበት ቀን ነው። (ዘፍ. 21:8-10፤ ገላ. 4:22-29) በእርግጥም ይሖዋ ሕዝቡ ነፃ የሚወጡበትን ትክክለኛ ጊዜ የወሰነው ከ400 ዓመታት በፊት ነበር!

6. ይሖዋ ሕዝቡን እንደሚያድን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ለምንድን ነው?

6 ከግብፅ ነፃ ከወጡት እስራኤላውያን አንዱ የሆነው ኢያሱ ለሕዝቡ እንዲህ በማለት ተናግሮ ነበር፦ “አምላካችሁ ይሖዋ ከገባላችሁ መልካም ቃል ሁሉ አንዲቷም እንኳ ሳትፈጸም እንዳልቀረች በሙሉ ልባችሁና በሙሉ ነፍሳችሁ ታውቃላችሁ። ሁሉም ተፈጽሞላችኋል። ከመካከላቸው ሳይፈጸም የቀረ አንድም ቃል የለም።” (ኢያሱ 23:2, 14) እኛም ከታላቁ መከራ በሕይወት እንደምንተርፍ ይሖዋ የገባልን ቃል እንደሚፈጸም እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሁንና ይህ ሥርዓት ሲጠፋ በሕይወት መትረፍ ከፈለግን ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ አለብን።

በሕይወት ለመትረፍ ነቅቶ መጠበቅ ወሳኝ ነው

7, 8. (ሀ) በጥንት ጊዜ አንድ ጠባቂ ምን ኃላፊነት ነበረበት? ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? (ለ) ጠባቂዎች በሥራ ላይ እያሉ እንቅልፍ ቢወስዳቸው ምን ሊፈጠር እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ተናገር።

7 ነቅቶ የመጠበቅን አስፈላጊነት፣ በጥንት ዘመን ከተሞችን ይጠብቁ ከነበሩ ጠባቂዎች መማር እንችላለን። በዚያን ዘመን፣ እንደ ኢየሩሳሌም ያሉ በርካታ ትላልቅ ከተሞች ዙሪያቸው በረጅም ቅጥር ይታጠር ነበር። እንዲህ ያለው ቅጥር ወራሪዎች ከተማዋን እንዳይደፍሯት የሚከላከል ከመሆኑም ሌላ ጠባቂዎቹ ከፍታ ላይ ሆነው አካባቢውን እንዲቃኙ ያስችላቸዋል። በከተማዎቹ ቅጥሮችና በሮች ላይ ሆነው ቀንና ሌሊት የሚጠብቁ ዘቦች ይመደቡ ነበር። እነዚህ ጠባቂዎች ከተማዋ ላይ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሆነ የሚጠቁም ነገር ከርቀት ከተመለከቱ የከተማዋን ነዋሪዎች ያስጠነቅቃሉ። (ኢሳ. 62:6) ጠባቂዎቹ ንቁ ሆነው አካባቢውን በትኩረት መከታተላቸው የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበር።—ሕዝ. 33:6

8 አይሁዳዊው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ፣ የሮም ሠራዊት ከኢየሩሳሌም ቅጥር ጋር ተያይዞ የተሠራውን የአንቶኒያን ግንብ በ70 ዓ.ም. በቁጥጥር ሥር ሊያውል የቻለው በር ላይ ያሉት ጠባቂዎች ተኝተው ስለነበር እንደሆነ ገልጿል! ሮማውያን በአንቶኒያ ግንብ አልፈው በመግባት ቤተ መቅደሱን በእሳት አጋዩት፤ እንዲሁም ከተማዋን አጠፏት። ይህም በአይሁድ ብሔር ላይ የደረሰው ታላቅ መከራ መደምደሚያ ሆነ።

9. በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች የትኛውን ሁኔታ አያስተውሉም?

9 በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ አገሮች በወታደሮችና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሚታገዙ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች አማካኝነት ድንበራቸውን ያስጠብቃሉ። ወታደሮቹ ወደ ክልላቸው ሰርገው የሚገቡ ሰዎችን ወይም ብሔራዊ ደህንነታቸውን ስጋት ላይ የሚጥሉ ጠላቶችን ነቅተው ይጠባበቃሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ ጠባቂዎች ማየት የሚችሉት ከሰብዓዊ መንግሥታት ወይም ከሌሎች ሰዎች የሚሰነዘረውን ጥቃት ብቻ ነው። ጠባቂዎቹ በክርስቶስ የሚመራ የአምላክ ሰማያዊ መንግሥት መኖሩን እንዲሁም ይህ መንግሥት የሚያከናውነውን ሥራም ሆነ በቅርቡ በመንግሥታት ሁሉ ላይ የሚወስደውን የፍርድ እርምጃ ማስተዋል አይችሉም። (ኢሳ. 9:6, 7 ግርጌ፤ 56:10ዳን. 2:44) እኛ ግን ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ ከሆንን ይህ የፍርድ ቀን ሲመጣ ዝግጁ ሆነን እንገኛለን።—መዝ. 130:6

ነቅታችሁ ከመጠበቅ እንዳትዘናጉ ተጠንቀቁ

10, 11. (ሀ) ምን እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን? ለምንስ? (ለ) ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ፍጻሜ እንዳያስተውሉ ዲያብሎስ አሳውሯቸዋል ብለህ እንድታምን ያደረገህ ምንድን ነው?

10 ሌሊቱን ሙሉ በንቃት ሲጠብቅ የቆየን አንድ ጠባቂ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጠባቂው በጣም የሚደክመውና እንቅልፍ የሚጫጫነው የጥበቃ ሰዓቱ ሊያበቃ ሲቃረብ ነው። በተመሳሳይም ወደዚህ ሥርዓት እየተቃረብን ስንመጣ ነቅቶ መጠበቅ ይበልጥ ተፈታታኝ ይሆንብናል። በዚህ ጊዜ እንቅልፍ ቢጥለን እንዴት የሚያሳዝን ይሆናል! ነቅተን ከመጠበቅ ሊያዘናጉን የሚችሉ ሦስት ነገሮችን እስቲ እንመልከት።

11 ዲያብሎስ፣ ሰዎች ቀስ በቀስ ለመንፈሳዊ ነገሮች ግድየለሽ እንዲሆኑ እያደረገ ነው። ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ደቀ መዛሙርቱን “የዚህ ዓለም ገዢ” ስለሆነው ስለ ዲያብሎስ ሦስት ጊዜ አስጠንቅቋቸዋል። (ዮሐ. 12:31፤ 14:30፤ 16:11) ኢየሱስ፣ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች እንዳያስተውሉና መጨረሻው መቅረቡን እንዳይገነዘቡ በማድረግ ዲያብሎስ አእምሯቸውን እንደሚያጨልም ያውቅ ነበር። (ሶፎ. 1:14) ሰይጣን በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን ተጠቅሞ የሰዎችን አእምሮ እያሳወረ ነው። ሰዎችን ስታነጋግሩ ምን ምላሽ እንደሚሰጡ አስተውላችኋል? የዚህ ሥርዓት መጨረሻ መቅረቡንም ሆነ ክርስቶስ በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ማስተዋል እንዳይችሉ ዲያብሎስ ‘የማያምኑትን ሰዎች አእምሮ እንዳሳወረ’ እየተመለከትን አይደለም? (2 ቆሮ. 4:3-6) ልታነጋግሯቸው ስትሞክሩ “አልፈልግም” የሚሉ ሰዎች በተደጋጋሚ ጊዜ ያጋጥሟችኋል? አብዛኞቹ ሰዎች ይህ ዓለም ወዴት እያመራ እንደሆነ ልንነግራቸው ስንሞክር ይህ ጉዳይ ብዙም ግድ እንደማይሰጣቸው እንመለከታለን።

12. ዲያብሎስ እንዳያታልለን መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?

12 የሰዎች ግድየለሽነት ተስፋ እንዲያስቆርጣችሁ ወይም ነቅታችሁ ከመጠበቅ እንዲያዘናጋችሁ አትፍቀዱ። ነቅተን መጠበቅ ያለብን ለምን እንደሆነ እናውቃለን። ጳውሎስ “የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ መሆኑን እናንተ ራሳችሁ በሚገባ ታውቃላችሁ” በማለት ለእምነት ባልንጀሮቹ ጽፏል። (1 ተሰሎንቄ 5:1-6ን አንብብ።) ኢየሱስም “የሰው ልጅ ይመጣል ብላችሁ ባላሰባችሁት ሰዓት ስለሚመጣ ዝግጁ ሆናችሁ ጠብቁ” በማለት አስጠንቅቆናል። (ሉቃስ 12:39, 40) በቅርቡ ሰይጣን፣ አብዛኞቹ ሰዎች “ሰላምና ደህንነት ሆነ” ብለው እንዲያስቡ በማድረግ ያታልላቸዋል። በዓለም ላይ ሁሉም ነገር እንደተስተካከለ እንዲሰማቸው በማድረግ ያሞኛቸዋል። ስለ እኛስ ምን ማለት እንችላለን? ‘ነቅተን የምንኖር እንዲሁም የማስተዋል ስሜታችንን የምንጠብቅ’ ከሆነ “ሌሊቱ ድንገት እንደሚነጋበት ሌባ፣ ያ ቀን ድንገት [አይደርስብንም]።” የአምላክን ቃል በየዕለቱ ማንበብና ይሖዋ በሚነግረን ነገር ላይ ማሰላሰል ያለብን ለዚህ ነው።

13. የዓለም መንፈስ በሰው ዘር ላይ ምን ተጽዕኖ እያሳደረ ነው? እኛስ ይህ አደገኛ መንፈስ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መከላከል የምንችለው እንዴት ነው?

13 የዓለም መንፈስ፣ ሰዎች በመንፈሳዊ እንዲያንቀላፉ እያደረገ ነው። ብዙዎች በዕለት ተዕለት ጉዳዮቻቸው ከመጠን በላይ ስለተጠመዱ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ” አይደሉም። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) እነዚህ ሰዎች፣ ዓለም በሚያቀርባቸው ‘ለሥጋ ምኞትና ለዓይን አምሮት’ እንድንሸነፍ በሚገፋፉ ማራኪ ቁሳዊ ነገሮች ተጠላልፈዋል። (1 ዮሐ. 2:16) በተጨማሪም የመዝናኛው ኢንዱስትሪ፣ ሰዎች “ሥጋዊ ደስታን” እንዲያሳድዱ አድርጓቸዋል፤ ደስታን እንድናሳድድ የሚገፋፉን ፈተናዎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ ነው። (2 ጢሞ. 3:4) ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “የሥጋ ፍላጎታችሁን ለማርካት ዕቅድ አታውጡ” የሚል ምክር የሰጣቸው ለዚህ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ዓይነቱ አካሄድ በመንፈሳዊ ወደማንቀላፋት ይመራል።—ሮም 13:11-14

14. በሉቃስ 21:34, 35 ላይ ምን ማሳሰቢያ ተሰጥቶናል?

14 እኛ ግን የዓለም መንፈስ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን ከመፍቀድ ይልቅ የአምላክ መንፈስ ሕይወታችንን እንዲመራው እንፈልጋለን፤ ይሖዋ ከፊታችን ስለሚጠብቁን ነገሮች በመንፈሱ አማካኝነት ግልጽ ግንዛቤ ሰጥቶናል። [1] (1 ቆሮ. 2:12) አንድ ሰው በመንፈሳዊ የሚያንቀላፋው የተለየ ነገር ስላጋጠመው ብቻ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል፤ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ክፍል የሆኑት የተለመዱ ነገሮችም እንኳ ካልተጠነቀቅን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች የምናውለውን ጊዜ ሊሻሙብን ይችላሉ። (ሉቃስ 21:34, 35ን አንብብ።) ሰዎች ምንጊዜም ነቅተን በመጠበቃችን ያፌዙብን ይሆናል፤ ሆኖም ይህ የጥድፊያ ስሜታችንን ሊያቀዘቅዝብን አይገባም። (2 ጴጥ. 3:3-7) ከዚህ ይልቅ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አዘውትረን በመሰብሰብ የአምላክን መንፈስ ለማግኘት ጥረት ማድረግ አለብን።

ምንጊዜም በመንፈሳዊ ንቁ ለመሆን አቅማችሁ የሚፈቅደውን ሁሉ እያደረጋችሁ ነው? (ከአንቀጽ 11-16 ተመልከት)

15. ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ምን አጋጠማቸው? እኛስ ተመሳሳይ ሁኔታ ሊያጋጥመን የሚችለው እንዴት ነው?

15 ሥጋችን ደካማ መሆኑ ምንጊዜም ነቅተን እንዳንኖር እንቅፋት ሊሆንብን ይችላል። ኢየሱስ፣ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች በሥጋ ድክመት ሊሸነፉ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። ኢየሱስ ከመገደሉ በፊት በነበረው ምሽት የተፈጸመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን ለመጠበቅ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠው በሰማይ ወደሚገኘው አባቱ መጸለይ አስፈልጎት ነበር። እሱ በሚጸልይበት ጊዜ ለጴጥሮስ፣ ለያዕቆብና ለዮሐንስ “ነቅታችሁ ጠብቁ” ብሏቸው ነበር። እነሱ ግን ከፊታቸው የሚጠብቃቸው ነገር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አልተገነዘቡም። የጌታቸውን ደህንነት በንቃት ከመከታተል ይልቅ በሥጋቸው ስለተሸነፉ እንቅልፍ ወሰዳቸው። በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ በጣም ደክሞት እያለም ንቁ በመሆን ወደ አባቱ አጥብቆ ይጸልይ ነበር። ተከታዮቹም እንዲህ ሊያደርጉ ይገባ ነበር።—ማር. 14:32-41

16. በሉቃስ 21:36 ላይ ኢየሱስ ‘ዘወትር ነቅተን እንድንጠብቅ’ ያሳሰበን እንዴት ነው?

16 “ዘወትር ነቅታችሁ ጠብቁ” የሚለውን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ፣ ፍላጎት ብቻ በቂ አይደለም። በጌትሴማኒ የአትክልት ቦታ ደቀ መዛሙርቱ ካጋጠማቸው ሁኔታ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ ኢየሱስ ለይሖዋ ምልጃ እንዲያቀርቡ ነግሯቸው ነበር። (ሉቃስ 21:36ን አንብብ።) እኛም በመንፈሳዊ እንዳናንቀላፋ ከፈለግን በጸሎት ረገድ ምንጊዜም ንቁዎች መሆን አለብን።—1 ጴጥ. 4:7

ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ

17. በቅርቡ የሚፈጸመውን ክንውን ዝግጁ ሆነን ለመጠባበቅ ምን ይረዳናል?

17 ኢየሱስ መጨረሻው የሚመጣው ‘ባላሰብነው ሰዓት’ እንደሆነ ስለተናገረ አሁን በመንፈሳዊ የምናሸልብበት እንዲሁም ሰይጣንም ሆነ እሱ የሚቆጣጠረው ዓለም የሚያቀርባቸውን የማይጨበጡና ሥጋችንን የሚያማልሉ ነገሮች የምናሳድድበት ጊዜ አይደለም። (ማቴ. 24:44) ይሖዋና ኢየሱስ፣ ስላዘጋጁልንና በቅርቡ ስለምናገኛቸው በረከቶች እንዲሁም ምንጊዜም ነቅተን መጠበቅ ስለምንችልበት መንገድ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ነግረውናል። ለመንፈሳዊነታችንና ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ትኩረት መስጠት እንዲሁም የአምላክን መንግሥት ማስቀደም አለብን። በቅርቡ የሚፈጸመውን ክንውን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንድንችል፣ ያለንበትን ጊዜ እንዲሁም በዙሪያችን የሚከናወኑትን ነገሮች ማስተዋል ይኖርብናል። (ራእይ 22:20) በሕይወት መትረፋችን የተመካው ንቁ በመሆናችን ላይ ነው!

^ [1] (አንቀጽ 14) የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው! የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 21 ተመልከት።