በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ መሟገት

በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ መሟገት

“ይህ ሰው በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታት . . . ፊት ስሜን እንዲሸከም ለእኔ የተመረጠ ዕቃ [ነው]።” (ሥራ 9:15) ጌታ ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው፣ በቅርቡ የክርስትናን እምነት የተቀበለን አንድ አይሁዳዊ አስመልክቶ ነው፤ ይህ ሰው ከጊዜ በኋላ ሐዋርያው ጳውሎስ ተብሎ ተጠርቷል።

ኢየሱስ ከጠቀሳቸው “ነገሥታት” አንዱ ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ ነበር። እንዲህ ባለው መሪ ፊት ለእምነትህ መሟገት ቢኖርብህ ምን ይሰማህ ነበር? ክርስቲያኖች የጳውሎስን አርዓያ እንዲከተሉ ተበረታተዋል። (1 ቆሮ. 11:1) የጳውሎስን ምሳሌ ከምንከተልባቸው መንገዶች አንዱ፣ ሐዋርያው በወቅቱ ከነበረው የሕግ ሥርዓት ጋር በተያያዘ የወሰደውን እርምጃ መኮረጅ ነው።

በእስራኤል ምድር ይሠራበት የነበረው ሕግ፣ የሙሴ ሕግ ሲሆን በየትኛውም ቦታ ለሚኖሩ ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን የሥነ ምግባር መሥፈርት ሆኖ የሚያገለግለውም ይኸው ሕግ ነበር። በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል በኋላ ግን እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች በሙሴ ሕግ ሥር መሆናቸው አበቃ። (ሥራ 15:28, 29፤ ገላ. 4:9-11) ይሁንና ጳውሎስም ሆነ ሌሎች ክርስቲያኖች ሕጉን የሚያቃልል ነገር አይናገሩም ነበር፤ እንዲያውም በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ የአይሁዳውያን ማኅበረሰቦች ያለምንም እንቅፋት መስበክ ችለዋል። (1 ቆሮ. 9:20) ጳውሎስ፣ ስለ አብርሃም አምላክ የሚያውቁና በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርቶ ሊያስረዳቸው የሚችል ሰዎች ለማግኘት ሲል ብዙ ጊዜ ወደ ምኩራቦች ይሄድ ነበር።—ሥራ 9:19, 20፤ 13:5, 14-16፤ 14:1፤ 17:1, 2

ሐዋርያት፣ መጀመሪያ ላይ ለስብከቱ ሥራ አመራር ለመስጠት ማዕከል እንዲሆን የመረጡት ቦታ ኢየሩሳሌም ነበር። ሐዋርያት አዘውትረው በቤተ መቅደሱ ያስተምሩ ነበር። (ሥራ 1:4፤ 2:46፤ 5:20) ጳውሎስ አልፎ አልፎ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ የነበረ ሲሆን ከጊዜ በኋላም በቁጥጥር ሥር እንዲውል የተደረገው በዚያ እያለ ነው። በዚህ መንገድ የተጀመረው የፍርድ ሂደት፣ ውሎ አድሮ ጳውሎስ ወደ ሮም እንዲሄድ ምክንያት ሆኗል።

ጳውሎስና የሮም ሕግ

የሮም ባለሥልጣናት ጳውሎስ ለሚሰብከው መልእክት ምን አመለካከት ነበራቸው? ይህን ጥያቄ መመለስ እንድንችል ሮማውያን ስለ ሃይማኖቶች በአጠቃላይ የነበራቸውን አመለካከት ማወቃችን ጠቃሚ ነው። ሮማውያን በግዛታቸው ውስጥ የሚኖሩት የተለያዩ ሕዝቦች ሃይማኖታቸውን እንዲተዉ አያስገድዱም ነበር፤ በእርግጥ እንዲህ ዓይነት ነፃነት የሚሰጧቸው ሃይማኖታቸው ለመንግሥት ችግር የሚፈጥር ወይም የሕዝቡን ሥነ ምግባር አደጋ ላይ የሚጥል እስካልሆነ ድረስ ነው።

ሮም በግዛቷ ለነበሩት አይሁዳውያን ሰፋ ያለ ነፃነት ሰጥታ ነበር። ባክግራውንድስ ኦቭ ኧርሊ ክርስቺያኒቲ የተባለው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “የአይሁድ እምነት በሮም ግዛት ውስጥ የተከበረ ቦታ ተሰጥቶት ነበር። . . . አይሁዳውያን ሃይማኖታቸውን በነፃነት ማራመድ ይችሉ የነበረ ከመሆኑም በላይ የሮምን አማልክት ማምለክ አይጠበቅባቸውም። እንዲሁም በራሳቸው ማኅበረሰብ ውስጥ በሕጋቸው መመራት ይፈቀድላቸው ነበር።” በተጨማሪም የውትድርና አገልግሎት የመስጠት ግዴታ አልነበረባቸውም። * ጳውሎስ በሮም ባለሥልጣናት ፊት ለክርስትና ሲሟገት፣ የሮም ሕግ ለአይሁድ እምነት የሰጠውን ይህን ከለላ ጠቅሷል።

የጳውሎስ ተቃዋሚዎች፣ ተራው ሕዝብም ሆነ ባለሥልጣናቱ በሐዋርያው ላይ እንዲነሱ ለማድረግ የተለያዩ ሙከራዎችን አድርገው ነበር። (ሥራ 13:50፤ 14:2, 19፤ 18:12, 13) በአንድ ወቅት ያደረጉትን ነገር እንመልከት። በኢየሩሳሌም ጉባኤ የሚገኙ ክርስቲያን ሽማግሌዎች፣ ጳውሎስ “የሙሴን ሕግ እንዲተዉ” እያስተማረ እንዳለ የሚገልጽ ወሬ በአይሁዳውያን መካከል እየተሰራጨ እንዳለ ሰሙ። እንዲህ ዓይነቱ ወሬ፣ በቅርቡ ክርስትናን የተቀበሉ አንዳንድ አይሁዳውያን ጳውሎስ የአምላክን ዝግጅቶች እንደማያከብር እንዲያስቡ ሊያደርግ ይችላል። እንዲሁም የሳንሄድሪን ሸንጎ፣ ክርስትናን በአይሁድ እምነት ላይ እንደተነሳ ክህደት አድርጎ እንዲመለከተው ሊያደርግ ይችላል። ይህ ከሆነ ደግሞ ከክርስቲያኖች ጋር የሚተባበሩ አይሁዳውያን ቅጣት ሊበየንባቸው ይችላል። እነዚህ ሰዎች፣ ከማኅበረሰቡ እንዲገለሉ እንዲሁም በቤተ መቅደስም ሆነ በምኩራቦች እንዳይሰብኩ ሊከለከሉ ይችላሉ። ስለሆነም የጉባኤው ሽማግሌዎች፣ ጳውሎስ እየተሰራጨ ያለው ወሬ ውሸት መሆኑን ለማሳየት ሲል ወደ ቤተ መቅደሱ እንዲሄድና ስህተት ባይሆንም እንኳ አምላክ የማይጠብቅበትን የአምልኮ ሥርዓት እንዲያከናውን መከሩት።—ሥራ 21:18-27

ጳውሎስ ይህን ማድረጉ “ለምሥራቹ [ለመሟገትና] በሕግ የጸና እንዲሆን ለማድረግ” የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ከፍቶለታል። (ፊልጵ. 1:7) አይሁዳውያኑ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ብጥብጥ ያስነሱ ሲሆን ጳውሎስን ለመግደል ፈልገው ነበር። በመሆኑም የሮም ሠራዊት ሻለቃ ጳውሎስን በቁጥጥር ሥር አዋለው። ወታደሮቹ ሊገርፉት እየተዘጋጁ ሳለ ጳውሎስ የሮም ዜግነት እንዳለው ተናገረ። በዚህም ምክንያት ወደ ቂሳርያ ተወሰደ፤ ሮማውያን ይሁዳን የሚያስተዳድሩት በቂሳርያ ሆነው ነበር። በዚያም ጳውሎስ በባለሥልጣናቱ ፊት በድፍረት መስበክ የሚችልበት አጋጣሚ ተከፈተለት። ይህም ስለ ክርስትና እምብዛም ለማያውቁ ሰዎች ክርስትናን ይበልጥ ለማሳወቅ ሳያስችል አልቀረም።

የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 24፣ ጳውሎስ የይሁዳ አገረ ገዢ በነበረው በሮማዊው ፊሊክስ ፊት ለፍርድ ስለቀረበበት ጊዜ ይናገራል፤ ፊሊክስ ከዚያ በፊት ስለ ክርስቲያኖች እምነት የተወሰነ ነገር ሰምቶ ነበር። አይሁዳውያኑ፣ ቢያንስ በሦስት መንገዶች የሮምን ሕግ እንደጣሰ በመግለጽ ጳውሎስን ከሰሱት። በሮም ግዛት ውስጥ በሚገኙት አይሁዳውያን ሁሉ መካከል ዓመፅ እንዳነሳሳ፣ የአደገኛ ኑፋቄ ቀንደኛ መሪ እንደሆነ እንዲሁም በወቅቱ በሮም ጥበቃ ሥር የነበረውን ቤተ መቅደስ ለማርከስ እንደሞከረ ገለጹ። (ሥራ 24:5, 6) እነዚህ ክሶች ሞት እንዲፈረድበት ሊያደርጉ ይችሉ ነበር።

ጳውሎስ ክስ ሲሰነዘርበት ያደረገው ነገር፣ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስብ ነው። ጳውሎስ በተረጋጋና አክብሮት በተሞላበት መንገድ መልስ ሰጥቷል። ስለ ሕጉና ስለ ነቢያት መጻሕፍት የተናገረ ሲሆን ‘የአባቶቹን አምላክ’ የማምለክ መብት እንዳለውም ገልጿል። የሮም ሕግ ለሁሉም አይሁዳውያን ይህን መብት ሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 24:14) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በቀጣዩ አገረ ገዢ በጶርቅዮስ ፊስጦስ እንዲሁም በንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ፊት ስለ እምነቱ የመናገርና የመሟገት አጋጣሚ አግኝቷል።

በመጨረሻም ጳውሎስ ፍትሐዊ ፍርድ ለማግኘት ሲል “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አለ፤ ቄሳር በወቅቱ የነበረው ከፍተኛ ባለሥልጣን ነው።—ሥራ 25:11

ጳውሎስ በቄሳር ሸንጎ ፊት ለፍርድ ቀረበ

ከጊዜ በኋላ አንድ መልአክ ለጳውሎስ “ቄሳር ፊት መቅረብ ይገባሃል” ብሎታል። (ሥራ 27:24) ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ፣ እሱ ብይን የሚሰጠው ለሁሉም የፍርድ ጉዳዮች እንደማይሆን በግዛቱ መጀመሪያ ላይ ተናግሮ ነበር። በግዛት ዘመኑ መጀመሪያ ላይ በነበሩት ስምንት ዓመታት የዳኝነቱን ሥራ በአብዛኛው ለሌሎች አስተላልፎ ነበር። ዘ ላይፍ ኤንድ ኤፒስልስ ኦቭ ሴንት ፖል የተባለው መጽሐፍ እንደዘገበው ኔሮ አንድን የፍርድ ጉዳይ ለመዳኘት ከተስማማ፣ ችሎቱ የሚሰየመው በራሱ ቤተ መንግሥት ውስጥ ሲሆን ብዙ ተሞክሮና ተደማጭነት ያላቸው አማካሪዎቹ ያግዙት ነበር።

የጳውሎስን ጉዳይ የሰማውና ፍርድ የሰጠው ራሱ ኔሮ ይሁን ወይም የጳውሎስን ይግባኝ ሰምቶ ጉዳዩን እንዲነግረው ሌላ ሰው ይመድብ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም። ሁኔታው ምንም ሆነ ምን ጳውሎስ፣ የአይሁዳውያንን አምላክ እንደሚያመልክ እንዲሁም ሁሉም ሰዎች ለመንግሥት ተገቢውን ክብር እንዲሰጡ እንደሚያበረታታ ገልጾ መሆን አለበት። (ሮም 13:1-7፤ ቲቶ 3:1, 2) ጳውሎስ በከፍተኛ ባለሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ በመሟገት ረገድ የተሳካለት ይመስላል፤ ምክንያቱም የቄሳር ሸንጎ ጳውሎስን ነፃ ለቆታል።—ፊልጵ. 2:24፤ ፊልሞና 22

ለምሥራቹ እንድንሟገት የተሰጠን ተልእኮ

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “በእኔ ምክንያት በገዢዎችና በነገሥታት ፊት ያቀርቧችኋል፤ በዚያ ጊዜ ለእነሱም ሆነ ለአሕዛብ መመሥከር ትችላላችሁ።” (ማቴ. 10:18) በዚህ መልኩ ኢየሱስን ወክለን መቆማችን ትልቅ መብት ነው። ለምሥራቹ ለመሟገት የምናደርገው ጥረት በፍርድ ቤት ድል ሊያስገኝልን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች የሚያደርጉት ውሳኔ ምሥራቹ ሙሉ በሙሉ “በሕግ የጸና እንዲሆን” አያደርግም። ለጭቆናና ለፍትሕ መጓደል ዘላቂ መፍትሔ የሚያስገኘው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው።—መክ. 8:9፤ ኤር. 10:23

ሆኖም በአሁኑ ጊዜም እንኳ ክርስቲያኖች ለእምነታቸው መሟገታቸው የይሖዋ ስም እንዲከበር ያደርጋል። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በእርጋታና በቅንነት አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ መሞከር ይኖርብናል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ፣ ‘የሚሰጡትን መልስ አስቀድመው መዘጋጀት እንደማያስፈልጋቸው’ ነግሯቸዋል፤ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲገልጽ “ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ” ብሏል።—ሉቃስ 21:14, 15፤ 2 ጢሞ. 3:12፤ 1 ጴጥ. 3:15

ክርስቲያኖች በነገሥታት፣ በገዢዎች ወይም በሌሎች ባለሥልጣናት ፊት ቀርበው ለእምነታቸው መሟገታቸው፣ በሌላ መንገድ መልእክታችን ለማይደርሳቸው ሰዎች ምሥክርነት ለመስጠት ያስችላል። በፍርድ ቤት ያገኘናቸው አንዳንድ ድሎች፣ ሕጎች እንዲሻሻሉ ያደረጉ ሲሆን ይህም የመናገርና የአምልኮ ነፃነት እንድናገኝ አስችሎናል። እንዲህ ላሉት የፍርድ ጉዳዮች የሚሰጠው ብያኔ ምንም ይሁን ምን፣ የአምላክ ሕዝቦች በፈተና ውስጥ የሚያሳዩት ድፍረት ይሖዋን ያስደስተዋል።

ለእምነታችን ስንሟገት የይሖዋ ስም ይከበራል

^ አን.8 ጄምስ ፓርክስ የተባሉ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “አይሁዳውያኑ . . . የራሳቸውን ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የመከተል መብት ነበራቸው። ሮማውያን ይህን መብት መስጠታቸው ለአይሁዳውያን የተለየ አስተያየት እንዳደረጉ የሚያሳይ አይደለም፤ ምክንያቱም ሮማውያን ቀድሞውንም ቢሆን በግዛታቸው ሥር የነበሩ የተለያዩ ክፍሎች በተቻለ መጠን ራስ አገዝ መስተዳደር እንዲኖራቸው የማድረግ ልማድ ነበራቸው።”