በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እምነት እንዲያዳብሩ እርዷቸው

እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እምነት እንዲያዳብሩ እርዷቸው

“ወጣት ወንዶችና ወጣት ሴቶች . . . የይሖዋን ስም ያወድሱ።”—መዝ. 148:12, 13

መዝሙሮች፦ 88, 115

1, 2. (ሀ) ወላጆች ምን ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል? ይህን ተፈታታኝ ሁኔታ መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው? (ለ) የትኞቹን አራት ነጥቦች እንመለከታለን?

“እኛ በይሖዋ እናምናለን ማለት ልጆቻችንም በይሖዋ ያምናሉ ማለት አይደለም። እምነት የሚወረስ ነገር አይደለም። ልጆቻችን ቀስ በቀስ የሚያዳብሩት ነገር ነው።” ይህን የተናገሩት በፈረንሳይ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ናቸው። አንድ አውስትራሊያዊ ወንድም ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ለወላጆች ከምንም በላይ ፈታኝ የሆነው ነገር በልጃቸው ልብ ውስጥ እምነት መገንባት ሳይሆን አይቀርም። ያሉትን መሣሪያዎች ሁሉ መጠቀም ያስፈልጋችኋል። ልጃችሁ ላነሳው ጥያቄ አጥጋቢ መልስ እንደሰጣችሁት ይሰማችሁ ይሆናል። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ግን ልጃችሁ ያንኑ ጥያቄ መልሶ ይጠይቃችኋል! ልጃችሁ፣ የሰጣችሁትን መልስ ዛሬ አጥጋቢ ሆኖ ቢያገኘውም ነገ ተጨማሪ ማብራሪያ ሊፈልግ ይችላል። በመሆኑም በአንዳንድ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በተደጋጋሚ መወያየት ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።”

2 ወላጅ ከሆናችሁ ልጆቻችሁ በይሖዋ ላይ ጠንካራ እምነት እንዲኖራቸው እነሱን የማስተማሩና የመቅረጹ ኃላፊነት ከአቅማችሁ በላይ እንደሆነ ተሰምቷችሁ ያውቃል? ማናችንም ብንሆን ይህን ኃላፊነት በራሳችን ጥበብ መወጣት እንደማንችል ግልጽ ነው! (ኤር. 10:23) አምላክ መመሪያ እንዲሰጠን የምንጠይቀው ከሆነ ግን ሊሳካልን ይችላል። ልጆቻችሁ እምነት እንዲያዳብሩ በመርዳት ረገድ ስኬታማ ለመሆን የሚያግዟችሁን አራት ነጥቦች እስቲ እንመልከት፦ (1) ልጆቻችሁን በሚገባ እወቁ። (2) ከልባችሁ አስተምሯቸው። (3) ጥሩ ምሳሌዎችን ተጠቀሙ። (4) ታጋሽ ሁኑ፤ እንዲሁም የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ።

ልጆቻችሁን በሚገባ እወቁ

3. ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያስተምሩ የኢየሱስን ምሳሌ መከተል የሚችሉት እንዴት ነው?

3 ኢየሱስ ተከታዮቹ ምን ብለው እንደሚያምኑ ከመጠየቅ ወደኋላ አላለም። (ማቴ. 16:13-15) እናንተም የእሱን ምሳሌ ተከተሉ። ከልጆቻችሁ ጋር ስትጨዋወቱ ስሜታቸውን እንዲገልጹ አበረታቷቸው። ይህም በአእምሯቸው ውስጥ የሚፈጠሩባቸውን ጥርጣሬዎች ወይም ጥያቄዎች አውጥተው እንዲናገሩ ማበረታታትን ይጨምራል። በአውስትራሊያ የሚኖር የ15 ዓመት ወጣት ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አባባ ስለማምንበት ነገር ብዙ ጊዜ የሚያወያየኝ ሲሆን የማሰብ ችሎታዬን እንድጠቀም ይረዳኛል። ‘ስለዚህ ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?’ ‘አንተስ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳብ ታምንበታለህ?’ ‘እንድታምንበት ያደረገህ ምንድን ነው?’ የሚሉትን ጥያቄዎች ይጠይቀኛል። እሱ ወይም እማማ የነገሩኝን ደግሜ እንድናገር ሳይሆን በራሴ አባባል እንድመልስ ይፈልጋል። እያደግኩ ስሄድ ደግሞ የምሰጠው መልስ የዚያኑ ያህል ጥልቀት ያለው እንዲሆን ይጠብቅብኝ ነበር።”

4. ልጃችሁ የሚያነሳውን ጥያቄ በቁም ነገር መመልከት ያለባችሁ ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ልጃችሁ አንድን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በተመለከተ ጥርጣሬ ካደረበት፣ ከመቆጣት ወይም እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ እንዳልሆነ እንዲሰማው ከማድረግ ተቆጠቡ። ከዚህ ይልቅ ጉዳዩን በጥሞና እንዲያመዛዝን በትዕግሥት እርዱት። አንድ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጃችሁ የሚያነሳውን ጥያቄ በቁም ነገር ተመልከቱት። የማይረባ ጥያቄ አድርጋችሁ በማሰብ ችላ ብላችሁ አትለፉት፤ እንዲሁም አንድን ትምህርት ማስረዳት ስለሚከብዳችሁ ብቻ ከርዕሰ ጉዳዩ ለመሸሽ አትሞክሩ።” እንደ እውነቱ ከሆነ ልጃችሁ በቅንነት የሚያነሳቸው ጥያቄዎች፣ ለጉዳዩ ትኩረት እንደሰጠውና የማወቅ ፍላጎት እንዳለው ይጠቁማሉ። ኢየሱስ ገና በ12 ዓመቱ ቁም ነገር ያዘሉ ጥያቄዎችን ጠይቋል። (ሉቃስ 2:46ን አንብብ።) በዴንማርክ የሚኖር አንድ የ15 ዓመት ወጣት እንዲህ ብሏል፦ “የያዝነው ሃይማኖት እውነተኛ ስለመሆኑ እርግጠኛ እንዳልሆንኩ ለወላጆቼ ስነግራቸው ጉዳዩ ቢያስጨንቃቸውም በረጋ መንፈስ አናገሩኝ። መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም ለጥያቄዎቼ በሙሉ መልስ ሰጡኝ።”

5. ልጆች በይሖዋ ላይ እምነት ያላቸው ቢመስሉም እንኳ ወላጆች ምን ማድረግ ይኖርባቸዋል?

5 ልጆቻችሁን በሚገባ እወቋቸው፤ ይኸውም አስተሳሰባቸውን፣ ስሜታቸውንና የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ለመረዳት ጥረት አድርጉ። አብረዋችሁ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ስለሚገኙና በአገልግሎት ስለሚካፈሉ ብቻ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳላቸው አድርጋችሁ አታስቡ። ከልጆቻችሁ ጋር አብራችሁ በምታሳልፉት በማንኛውም ጊዜ በውይይታችሁ ውስጥ መንፈሳዊ ነገሮችን ለማካተት ጥረት አድርጉ። ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም እነሱን በተመለከተ ጸልዩ። ከእምነታቸው ጋር በተያያዘ የሚያጋጥማቸውን ማንኛውንም ፈተና ለማስተዋል ጥረት አድርጉ፤ ፈተናውን እንዲወጡትም እርዷቸው።

ከልባችሁ አስተምሯቸው

6. ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በልባቸው እንዲቀረጽ ማድረጋቸው ጥሩ አስተማሪዎች እንዲሆኑ የሚረዳቸው እንዴት ነው?

6 ኢየሱስ ይሖዋን፣ የአምላክን ቃልና ሰዎችን ይወድ ስለነበር የሌሎችን ልብ በሚነካ መንገድ ማስተማር ችሏል። (ሉቃስ 24:32፤ ዮሐ. 7:46) ወላጆችም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ካላቸው የልጆቻቸውን ልብ መንካት ይችላሉ። (ዘዳግም 6:5-8ን እና ሉቃስ 6:45ን አንብብ።) ስለሆነም ወላጆች መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን በትጋት አጥኑ። ለፍጥረት ሥራዎች እንዲሁም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ በጽሑፎቻችን ላይ ለሚወጡ ርዕሶች ትኩረት ስጡ። (ማቴ. 6:26, 28) እንዲህ ማድረጋችሁ ግንዛቤያችሁን የሚያሰፋና ለይሖዋ ያላችሁን አድናቆት የሚያሳድግ ከመሆኑም ሌላ ልጆቻችሁን ለማስተማር ይበልጥ ዝግጁ እንድትሆኑ ይረዳችኋል።—ሉቃስ 6:40

7, 8. ወላጆች ልባቸው በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሲሞላ ምን ለማድረግ ይነሳሳሉ? ምሳሌ ስጥ።

7 የእናንተ ልብ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከተሞላ ያወቃችሁትን ነገር ከቤተሰባችሁ ጋር ለመወያየት ትነሳሳላችሁ። ይህን የምታደርጉት ለጉባኤ ስብሰባዎች ስትዘጋጁ ወይም የቤተሰብ አምልኮ ስታከናውኑ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ጊዜ ሊሆን ይገባል። በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት የምታደርጉት ይህን የማድረግ ኃላፊነት እንዳለባችሁ ስለሚሰማችሁ ብቻ መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ በዕለታዊ ጭውውታችሁ ውስጥ ልታካትቱት የሚገባ ነገር ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት፣ የተፈጥሮን ውበት እንዲያደንቁ የሚያደርግ ነገር ሲያጋጥማቸው ወይም አንዳንድ ምግቦችን ሲመገቡ ከልጆቻቸው ጋር ስለ ይሖዋ አንስተው እንደሚወያዩ ገልጸዋል። እነዚህ ወላጆች “ይሖዋ የሰጠን ነገሮች በሙሉ ለእኛ ፍቅርና አሳቢነት እንዳለው የሚያሳዩ መሆናቸውን ለልጆቻችን እንነግራቸዋለን” ብለዋል። በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት ደግሞ ከሁለት ሴቶች ልጆቻቸው ጋር አትክልት በሚንከባከቡበት ጊዜ አስደናቂ የሆኑ ነገሮችን ለምሳሌ፣ ዘር እንዴት እንደሚበቅልና ከዚያም ተክሉ እንዴት እንደሚያድግ ይገልጹላቸዋል። እነዚህ ወላጆች “ልጆቻችን፣ ሕይወት ምን ያህል አስደናቂና ውስብስብ እንደሆነ እንዲገነዘቡ ለመርዳት ጥረት እናደርጋለን” በማለት ተናግረዋል።

8 በአውስትራሊያ የሚኖር አንድ አባት፣ ልጁ አሥር ዓመት ገደማ ሲሆነው አንድ ሙዚየም እንዲጎበኙ ይዞት ሄደ፤ ይህ አባት፣ በዚያ የተመለከቱትን ነገር መሠረት በማድረግ አምላክ ፈጣሪ ስለመሆኑ ልጁ እምነቱን እንዲያጠናክር ረዳው። አባትየው እንዲህ ብሏል፦ “አመኖይድ እና ትራይሎባይት የተባሉትን ጥንታዊ የባሕር ፍጥረታት ቅሪተ አካል ተመለከትን። ከምድር ገጽ የጠፉት እነዚህ እንስሳት ምን ያህል ውብ፣ ውስብስብ በሆነ መንገድ የተፈጠሩ ብሎም ሁሉ ነገራቸው የተሟላ እንደሆነ ስንመለከት በጣም ተደነቅን፤ ዛሬ ከምናያቸው ፍጥረታት ጋር ሲወዳደሩ ምንም የሚጎድላቸው ነገር የለም። ውስብስብ ያልሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እየተሻሻሉ መጥተው ይበልጥ ውስብስብ የሆኑ ሕያዋን ፍጥረታት አስገኙ ከተባለ እነዚህ ጥንታዊ ፍጥረታት በዚያን ጊዜም እንኳ ይህን ያህል ውስብስብ ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ይህ በጣም ስላስገረመኝ ያገኘሁትን ትምህርት ከልጄ ጋር ተወያየንበት።”

ውጤታማ ምሳሌዎችን ተጠቀሙ

9. በምሳሌ ማስተማር ውጤታማ የሆነው ለምንድን ነው? አንዲት እናት ያደረገችው ነገር ይህን የሚያሳየው እንዴት ነው?

9 ኢየሱስ፣ ሰዎች ቆም ብለው እንዲያስቡ የሚያደርጉ፣ ልብ የሚነኩና በቀላሉ የማይረሱ ምሳሌዎችን ብዙ ጊዜ ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 13:34, 35) ልጆች፣ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናቸው የመሳል ልዩ ችሎታ አላቸው። ስለሆነም ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ስታስተምሩ ብዙ ጊዜ ምሳሌዎችን ተጠቀሙ። በጃፓን የምትኖር አንዲት እናት ያደረገችውም ይህንኑ ነው። ሁለት ወንዶች ልጆቿ ስምንትና አሥር ዓመት ሲሆናቸው ስለ ምድር ከባቢ አየር ካስረዳቻቸው በኋላ ይሖዋ ከባቢ አየርን የሠራበት መንገድ ለሰው ልጆች ምን ያህል እንደሚያስብ የሚያሳይ መሆኑን ገለጸችላቸው። ይህን ነጥብ ለማስረዳት ስትል ለልጆቿ ወተት፣ ስኳርና ቡና ሰጠቻቸው። ከዚያም ሁለቱንም ልጆች ቡና እንዲያዘጋጁላት ጠየቀቻቸው። እንዲህ ብላለች፦ “ቡናውን ያዘጋጁት በጥንቃቄ ነበር። ይህን ያህል የተጨነቁት ለምን እንደሆነ ስጠይቃቸው ልክ እኔ የምወደው ዓይነት እንዲሆን ስለፈለጉ እንደሆነ ነገሩኝ። በተመሳሳይም አምላክ በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙትን ጋዞች መጠን ሲወስን ለእኛ በሚስማማ መልክ በጥንቃቄ እንዳዘጋጀው አስረዳኋቸው።” ይህች እናት ልጆቿን ለማስረዳት የተጠቀመችበት ይህ ምሳሌ ለዕድሜያቸው ተስማሚ ከመሆኑም ሌላ ትምህርቱ በዚህ መንገድ መቅረቡ አስደሳች ሆኖላቸዋል። ይህን ትምህርት መቼም ቢሆን እንደማይረሱት ጥርጥር የለውም!

አምላክ ፈጣሪ መሆኑን በተመለከተ በልጆቻችሁ ልብ ውስጥ እምነት ለመገንባት በቀላሉ የሚገኙ ነገሮችን መጠቀም ትችላላችሁ (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10, 11. (ሀ) ልጃችሁ በአምላክ ላይ እምነት እንዲያዳብር ለመርዳት ምን ዓይነት ምሳሌ መጠቀም ትችላላችሁ? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።) (ለ) እናንተ ውጤታማ ሆነው ያገኛችኋቸውን ምሳሌዎች ተናገሩ።

10 ልጃችሁ በአምላክ ላይ እምነት እንዲያዳብር ለመርዳት የምግብ አዘገጃጀት መመሪያንም እንደ ምሳሌ ልትጠቀሙ ትችላላችሁ። እንዴት? ዳቦ ወይም ኬክ ስትጋግሩ የአዘገጃጀት መመሪያውን ተከትላችሁ መሥራታችሁ ምን ጥቅም እንዳለው ንገሩት። ከዚያም ልጃችሁን ከፍራፍሬዎች አንዱን ለምሳሌ ፖም ወይም ብርቱካን ስጡትና “ይህ ብርቱካን ‘የአዘገጃጀት መመሪያ’ እንዳለው ታውቃለህ?” ብላችሁ ጠይቁት። ቀጥሎ ደግሞ ብርቱካኑን ሁለት ቦታ ቁረጡትና ፍሬውን ወይም ዘሩን አውጥታችሁ ስጡት። የብርቱካኑ የአዘገጃጀት መመሪያ በዘሩ ላይ “እንደተጻፈ” አስረዱት፤ በእርግጥ ዘሩ ላይ የተጻፈው መመሪያ፣ ከምግብ አዘገጃጀት መመሪያ ይበልጥ ውስብስብ ነው። “የምግብ አዘገጃጀት መመሪያውን የጻፈው ሰው እንዳለ የታወቀ ነው፤ ታዲያ ከዚያ በላይ ውስብስብ የሆነውን የብርቱካኑን የአዘገጃጀት መመሪያ የጻፈው ማን ነው?” ብላችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። በዕድሜ ከፍ ላለ ልጅ ደግሞ የብርቱካኑ እንዲያውም የዛፉ “የአዘገጃጀት መመሪያ” በዲ ኤን ኤው ውስጥ እንደሚገኝ ልታብራሩለት ትችላላችሁ። በተጨማሪም የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች በተባለው ብሮሹር ከገጽ 10 እስከ 20 ላይ የሚገኙትን ሥዕሎች ከልጃችሁ ጋር መመልከት ትችላላችሁ።

11 ብዙ ወላጆች፣ ንቁ! ላይ የሚወጣውን “ንድፍ አውጪ አለው?” የሚለውን ዓምድ ከልጆቻቸው ጋር መወያየት ያስደስታቸዋል። አንዳንድ ወላጆች፣ በዚህ ዓምድ በመጠቀም ለትናንሽ ልጆቻቸው ቀለል ያሉ ትምህርቶችን ያስተምሯቸዋል። ለምሳሌ፣ በዴንማርክ የሚኖሩ ባልና ሚስት አውሮፕላኖችን ከወፎች ጋር በማነጻጸር ልጆቻቸውን ያስተምራሉ። እንዲህ ይሏቸዋል፦ “አውሮፕላኖችና ወፎች ይመሳሰላሉ። ይሁንና አውሮፕላኖች እንቁላል መጣልና ትናንሽ አውሮፕላኖችን መፈልፈል ይችላሉ? አውሮፕላኖች ለየት ባለ መንገድ የተሠራ ማረፊያ ያስፈልጋቸዋል፤ ወፎችስ? እስቲ የአውሮፕላንን ድምፅ ከወፎች ዝማሬ ጋር ለማወዳደር ሞክሩ። ታዲያ የበለጠ ችሎታ ያለው ማን ነው? የአውሮፕላኑ ሠሪ ነው ወይስ የወፎቹ ፈጣሪ?” ወላጆች እንዲህ ያሉ ነጥቦችን ማንሳታቸውና ተስማሚ ጥያቄዎችን መጠየቃቸው ልጃቸው “የማመዛዘን ችሎታ” እንዲያዳብርና በአምላክ ላይ ያለው እምነት እንዲያድግ ሊረዳው ይችላል።—ምሳሌ 2:10-12

12. ልጃችሁ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ያለውን እምነት ለማጠናከር በምሳሌዎች መጠቀም የምትችሉት እንዴት ነው?

12 ልጃችሁ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛነት ያለውን እምነት ለማጠናከርም ውጤታማ ምሳሌዎችን መጠቀም ትችላላችሁ። ኢዮብ 26:7ን (ጥቅሱን አንብብ) እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህ ጥቅስ በመንፈስ መሪነት እንደተጻፈ ለልጃችሁ ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው? እውነታውን እንዲሁ ልትነግሩት ትችሉ ይሆናል። ይህን ከማድረግ ይልቅ ልጃችሁ ነገሮችን በዓይነ ሕሊናው ለመሳል እንዲሞክር ለምን አትረዱትም? ኢዮብ የኖረው ቴሌስኮፕና መንኮራኩር ባልተሠራበት ዘመን እንደሆነ ግለጹ። የልጃችሁ ድርሻ፣ በዚያ ዘመን የነበሩ ሰዎች እንደ ምድር ያለ ትልቅ ነገር ያለምንም ድጋፍ ይንጠለጠላል ብሎ ማመን ምን ያህል ሊከብዳቸው እንደሚችል ማስረዳት ሊሆን ይችላል። ክብደት ያላቸው ነገሮች የሚደግፋቸው ነገር ሳይኖር በባዶ መንጠልጠል እንደማይችሉ በምሳሌ ለማሳየት አንድ ኳስ ወይም ድንጋይ መጠቀም ይችላል። ልጆችን በዚህ መንገድ ማስተማር የሚከተለውን ሐቅ እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል፦ ሰዎች አንዳንድ ሳይንሳዊ እውነታዎችን ለማረጋገጥ ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል፤ ይሖዋ ግን ይህ እውነታ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲሰፍር ያደረገው ጥንት ነው።—ነህ. 9:6

የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ጥቅም በምሳሌ አስረዷቸው

13, 14. ወላጆች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ለልጆቻቸው ማስረዳት የሚችሉት እንዴት ነው?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆኑ ልጆቻችሁ እንዲገነዘቡ መርዳታችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። (መዝሙር 1:1-3ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የሚቻልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ፣ ልጆቻችሁ ራቅ ብሎ በሚገኝ ደሴት ላይ ሊኖሩ እንዳሰቡ አድርገው በዓይነ ሕሊናቸው እንዲስሉ ጠይቋቸው፤ በደሴቱ ላይ አብረዋቸው የሚኖሩትን ሰዎች መምረጥ እንዳለባቸው ንገሯቸው። “የደሴቷ ነዋሪዎች በሙሉ እርስ በርስ ተስማምተው በሰላም እንዲኖሩ፣ እያንዳንዱ ሰው ምን ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው የሚገባ ይመስላችኋል?” ብላችሁ ጠይቋቸው። ከዚያም ይሖዋ በአዲስ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ሰዎች ምን ዓይነት እንደሆኑ ለማሳየት ገላትያ 5:19-23⁠ን ልታነቡ ትችላላችሁ።

14 ይህን ምሳሌ መጠቀማችሁ ሁለት አስፈላጊ ትምህርቶችን ለማስተማር ይረዳችኋል። አንደኛ፣ አምላክ ያወጣቸው መመሪያዎች እውነተኛ ሰላምና አንድነት እንዲኖር ያደርጋሉ። ሁለተኛ፣ ይሖዋ አሁን የሚሰጠን ትምህርት በአዲሱ ዓለም ለሚኖረው ሕይወት ያዘጋጀናል። (ኢሳ. 54:13፤ ዮሐ. 17:3) በጽሑፎቻችን ላይ የሚገኙ ተሞክሮዎችን በመጥቀስ ነጥቡን ይበልጥ ማጉላት ትችላላችሁ። “መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል” በሚለው የመጠበቂያ ግንብ ዓምድ ሥር የሚወጡ ተሞክሮዎችን መጠቀም ትችሉ ይሆናል። አሊያም ይሖዋን ለማስደሰት ሲል በሕይወቱ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ ያደረገ ሰው በጉባኤያችሁ ካለ ቤታችሁ ልትጋብዙትና ተሞክሮውን እንዲናገር ልትጠይቁት ትችላላችሁ። እንዲህ ያሉ ተሞክሮዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያላቸውን ጥቅም ያጎላሉ!—ዕብ. 4:12

15. ልጆቻችሁን የምታስተምሩበትን መንገድ በተመለከተ ግባችሁ ምን ሊሆን ይገባል?

15 ዋናው ነጥብ ይህ ነው፦ ልጆቻችሁን የምታስተምሩበት መንገድ አሰልቺ አይሁንባቸው። አዳዲስ ዘዴዎችን ለመፍጠር ሞክሩ። የልጆቻችሁን ዕድሜ ግምት ውስጥ በማስገባት፣ የማሰብ ችሎታቸውን እንዲጠቀሙ አበረታቷቸው። የምታስተምሩበት መንገድ አስደሳችና እምነት የሚገነባ እንዲሆን አድርጉ። “የተለመዱትን ትምህርቶች ለማስተማር ምንጊዜም አዳዲስ መንገዶችን ሞክሩ” በማለት አንድ አባት ተናግሯል።

እምነትና ትዕግሥት አሳዩ፤ የይሖዋን እርዳታ ለማግኘት ጸልዩ

16. ልጆችን ለማስተማር ትዕግሥት ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? ምሳሌ ስጥ።

16 ጠንካራ እምነት ለማዳበር የአምላክ መንፈስ አስፈላጊ ነው። (ገላ. 5:22, 23) አንድ ፍሬ ለማደግ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እምነትም የሚያድገው በጊዜ ሂደት ነው። በመሆኑም ልጆቻችሁን ሳትሰለቹ በትዕግሥት ማስተማር ይኖርባችኋል። በጃፓን የሚኖር የሁለት ልጆች አባት እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ከልጆቻችን ጋር ብዙ ጊዜ እናሳልፋለን። ገና ከጨቅላነታቸው አንስቶ በየቀኑ ለ15 ደቂቃ ያህል አስጠናቸው ነበር፤ የማናጠናው የጉባኤ ስብሰባ ባለን ቀን ብቻ ነው። አሥራ አምስት ደቂቃ ለእኛም ሆነ ለእነሱ ያን ያህል ብዙ አይደለም።” አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካችም እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ሳለሁ በጣም ብዙ ጥያቄዎችና ጥርጣሬዎች በአእምሮዬ ይጉላሉ የነበረ ሲሆን አንዳንዶቹን ለሰው እንኳ ተናግሬ አላውቅም። በጊዜ ሂደት ግን በጉባኤ ስብሰባ ላይ አሊያም በቤተሰብ ወይም በግል ጥናት ወቅት ለብዙዎቹ ጥያቄዎቼ መልስ አግኝቻለሁ። ወላጆች ልጆቻቸውን በቀጣይነት ማስተማር ያለባቸው ለዚህ ነው።”

ውጤታማ አስተማሪዎች መሆን ከፈለጋችሁ በቅድሚያ የአምላክ ቃል በእናንተ ልብ ውስጥ መተከል አለበት (አንቀጽ 17ን ተመልከት)

17. ወላጆች ጥሩ ምሳሌ መሆናቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ባልና ሚስት በዚህ ረገድ ለልጆቻቸው ጥሩ ምሳሌ የሆኑት እንዴት ነው?

17 እርግጥ ነው፣ በጣም አስፈላጊው ነገር በይሖዋ ላይ እምነት በማሳደር ረገድ እናንተ ራሳችሁ ምሳሌ ሆናችሁ መገኘት ነው። ልጆቻችሁ የምታደርጉትን ነገር ያስተውላሉ፤ ይህም በእነሱ ላይ በጎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥርጥር የለውም። ስለዚህ ወላጆች የራሳችሁን እምነት መገንባታችሁን ቀጥሉ። ልጆቻችሁ ይሖዋ ለእናንተ ምን ያህል እውን እንደሆነ እንዲመለከቱ አድርጉ። በቤርሙዳ የሚኖሩ አንድ ባልና ሚስት፣ የሚያስጨንቅ ሁኔታ በሚያጋጥማቸው ወቅት ይሖዋ መመሪያ እንዲሰጣቸው ከልጆቻቸው ጋር ሆነው የሚጸልዩ ሲሆን ልጆቻቸውንም እንዲጸልዩ ያበረታቷቸዋል። “በተጨማሪም ትልቋ ልጃችንን ‘ሙሉ በሙሉ በይሖዋ ታመኚ፤ ራስሽን በአገልግሎት አስጠምጂ እንዲሁም ከልክ በላይ አትጨነቂ’ እንላታለን። እንዲህ ማድረግ የሚያስገኘውን ውጤት ስትመለከት ይሖዋ እየረዳን እንዳለ ትገነዘባለች። ይህም በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላት እምነት እንዲጠናከር ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል” በማለት ተናግረዋል።

18. ወላጆች የትኛውን እውነታ ማስታወስ ይኖርባቸዋል?

18 እርግጥ ነው፣ እናንተ ምንም ያህል ጥረት ብታደርጉም እምነት ማዳበር ያለባቸው ልጆቹ ራሳቸው ናቸው። የእናንተ ድርሻ መትከልና ውኃ ማጠጣት ነው። ሊያሳድገው የሚችለው አምላክ ብቻ ነው። (1 ቆሮ. 3:6) እንግዲያው ይሖዋ መንፈሱን እንዲሰጣችሁ ጸልዩ፤ እንዲሁም ውድ የሆኑ ልጆቻችሁን ለማስተማር ከፍተኛ ጥረት አድርጉ፤ ይህን ካደረጋችሁ ይሖዋ ይባርካችኋል።—ኤፌ. 6:4