በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እናንት ወጣቶች፣ እምነታችሁን አጠናክሩ

እናንት ወጣቶች፣ እምነታችሁን አጠናክሩ

“እምነት . . . የምናምንበት ነገር በዓይን የሚታይ ባይሆንም እውን መሆኑን የሚያሳይ ተጨባጭ ማስረጃ ነው።”—ዕብ. 11:1

መዝሙሮች፦ 41, 69

1, 2. በዛሬው ጊዜ ያሉ ወጣቶች ምን ጫና ይደርስባቸዋል? ይህን ለመቋቋም ምን ማድረግ ይችላሉ?

በብሪታንያ የምትኖር አንዲት ወጣት፣ አብራት ለምትማር እህት “እንደ አንቺ ያለ አስተዋይ ሰው በአምላክ ያምናል ብዬ ማሰብ ይከብደኛል” ብላት ነበር። በጀርመን የሚኖር አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አስተማሪዎቼ ስለ ፍጥረት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ የሚመለከቱት እንደ አፈ ታሪክ ነው። በዝግመተ ለውጥ የማያምን ተማሪ አለ ብለው አያስቡም።” በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት ወጣት እህት ደግሞ “በትምህርት ቤታችን ያሉ አስተማሪዎች በዛሬው ጊዜም እንኳ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑ ተማሪዎች እንዳሉ ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ” ብላለች።

2 አንተም ይሖዋን የምታገለግል አሊያም ስለ እሱ እየተማርክ ያለህ ወጣት ልትሆን ትችላለህ፤ ታዲያ የብዙኃኑን አመለካከት እንድትቀበል፣ ለምሳሌ በፈጣሪ ሳይሆን በዝግመተ ለውጥ እንድታምን ጫና እየተደረገብህ እንዳለ ይሰማሃል? ከሆነ እምነትህን ለማጠናከርና ምንጊዜም ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግ ልትወስዳቸው የምትችላቸው እርምጃዎች አሉ። ከእነዚህ መካከል አንዱ አምላክ የሰጠህን የማመዛዘን ችሎታ መጠቀም ነው፤ የማመዛዘን ችሎታህ “ምንጊዜም ይጠብቅሃል።” ይህ ችሎታ እምነትህን ሊያጠፉ የሚችሉ ዓለማዊ ፍልስፍናዎች ተጽዕኖ እንዳያሳድሩብህ ይከላከልልሃል።—ምሳሌ 2:10-12ን አንብብ።

3. በዚህ ርዕስ ላይ የትኛውን ጉዳይ እንመለከታለን?

3 እውነተኛ እምነት ለመገንባት ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት ማዳበር ያስፈልጋል። (1 ጢሞ. 2:4) እንግዲያው የአምላክን ቃል ወይም ክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችንን በምታጠናበት ጊዜ ሐሳቡን ገረፍ ገረፍ አድርገህ አትለፈው። ያነበብከውን ነገር ‘ማስተዋል’ እንድትችል የማመዛዘን ችሎታህን ተጠቀም። (ማቴ. 13:23) እንዲህ ማድረግህ አምላክ ፈጣሪ ስለመሆኑ እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለመሆኑ ያለህን እምነት ለማጠናከር የሚረዳህ እንዴት እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፤ ደግሞም እነዚህን ርዕሰ ጉዳዮች በተመለከተ ብዙ “ተጨባጭ ማስረጃ” ማግኘት ይቻላል።—ዕብ. 11:1

እምነታችሁን ማጠናከር የምትችሉበት መንገድ

4. ዝግመተ ለውጥንም ሆነ ፍጥረትን መቀበል እምነት ይጠይቃል የምንለው ለምንድን ነው? የትኛውን አካሄድ መከተሉ ምክንያታዊ ይሆናል?

4 ሰዎች፣ ‘አምላክ አለ’ የሚለው ሐሳብ በእምነት ላይ የተመሠረተ፣ ዝግመተ ለውጥ ግን በሳይንስ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ሲናገሩ ሰምተህ ታውቃለህ? ብዙዎች እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው። ይሁንና ልንዘነጋው የማይገባ አንድ ሐቅ አለ፦ አምላክ እንዳለ ለመቀበልም ሆነ ዝግመተ ለውጥን ለማመን እምነት ያስፈልጋል። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ማንኛችንም ብንሆን አምላክን አይተን አሊያም አንድ ነገር ሲፈጠር ተመልክተን አናውቅም። (ዮሐ. 1:18) በሌላ በኩል ደግሞ ሕይወት ያለው አንድ ነገር በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ወደ ሌላ ሕያው ነገር ሲቀየር ተመልክቶ የሚያውቅ የሳይንስ ሊቅም ሆነ ሌላ ሰው የለም። ለምሳሌ፣ በደረቱ የሚሳብ እንስሳ ወደ አጥቢ እንስሳ ሲቀየር ተመልክቶ የሚያውቅ ሰው የለም። (ኢዮብ 38:1, 4) በመሆኑም ሁላችንም ብንሆን ያሉትን ማስረጃዎች መመርመርና በማመዛዘን ችሎታችን ተጠቅመን ምክንያታዊ የሆነ መደምደሚያ ላይ መድረስ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ አምላክ የፍጥረት ሥራዎች ሲናገር እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የማይታዩት ባሕርያቱ ይኸውም ዘላለማዊ ኃይሉና አምላክነቱ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይታያሉ፤ ምክንያቱም ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል፤ ስለሆነም የሚያመካኙበት ነገር የላቸውም።”—ሮም 1:20

ከሌሎች ጋር ስትወያዩ የይሖዋ ድርጅት ያዘጋጃቸውን የተለያዩ መሣሪያዎች በሚገባ ተጠቀሙ (አንቀጽ 5ን ተመልከት)

5. የአምላክ ሕዝቦች የማስተዋል ችሎታችንን እንድንጠቀም የሚረዱን ምን ዝግጅቶች ተደርገውልናል?

5 “ማስተዋል” ሲባል በቀላሉ የማይታይን ወይም ግልጽ ያልሆነን ነገር መረዳት ወይም መገንዘብ ማለት ነው። (ዕብ. 11:3) በመሆኑም አስተዋይ የሆኑ ሰዎች በሚያዩትና በሚሰሙት ነገር ብቻ ከመወሰን ይልቅ አእምሯቸውን ወይም የማመዛዘን ችሎታቸውን ይጠቀማሉ። የይሖዋ ድርጅት በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ሲል ጥሩ ምርምር የተደረገባቸው ብዙ መርጃ መሣሪያዎች አቅርቦልናል። በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀማችን ፈጣሪያችንን በእምነት ዓይናችን ‘ለማየት’ ያስችለናል። (ዕብ. 11:27) ከእነዚህ መሣሪያዎች መካከል አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎች የአምላክን ክብር ይገልጣሉ የተባለው ቪዲዮ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም ሕይወት የተገኘው በፍጥረት ነው? እና የሕይወት አመጣጥ—መልስ የሚያሻቸው አምስት ጥያቄዎች የተባሉት ብሮሹሮች እና ስለ አንተ የሚያስብ ፈጣሪ ይኖር ይሆን? (እንግሊዝኛ) የተባለው መጽሐፍ ይገኙበታል። በተጨማሪም በመጽሔቶቻችን ላይ ትኩረት የሚስቡ ትምህርቶች ይወጣሉ። ብዙውን ጊዜ ንቁ! መጽሔት፣ በአምላክ እንዲያምኑ ያደረጋቸው ምን እንደሆነ ከገለጹ የሳይንስ ሊቃውንትና ሌሎች ሰዎች ጋር የተደረጉ ቃለ ምልልሶችን ይዞ ይወጣል። “ንድፍ አውጪ አለው?” በሚል ዓምድ ሥር የሚወጡት የተለያዩ ርዕሶች ደግሞ በፍጥረት ላይ የሚታየውን አስደናቂ ንድፍ ያጎላሉ። የሳይንስ ሊቃውንት እነዚህን አስደናቂ ንድፎች ለመኮረጅ ብዙ ጊዜ ጥረት ያደርጋሉ።

6. የይሖዋ ድርጅት ያደረገልን ዝግጅቶች ምን ጥቅም ያስገኙልናል? አንተ በግልህ ከእነዚህ ዝግጅቶች ጥቅም ያገኘኸው እንዴት ነው?

6 በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የ19 ዓመት ወጣት ወንድም፣ ቀደም ባለው አንቀጽ ላይ ስለተጠቀሱት ሁለት ብሮሹሮች ሲናገር “በጣም ጠቅመውኛል። ብሮሹሮቹን ደግሜ ደጋግሜ አጥንቻቸዋለሁ” ብሏል። በፈረንሳይ የምትኖር አንዲት እህት ደግሞ እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “‘ንድፍ አውጪ አለው?’ በሚለው ዓምድ ሥር የሚወጡት ርዕሶች በጣም ያስደንቁኛል! የላቀ ችሎታ ያላቸው የምህንድስና ባለሙያዎች በተፈጥሮ ላይ የሚታዩትን ውስብስብ ንድፎች መኮረጅ ይችሉ ይሆናል እንጂ ከዚያ ጋር የሚመጣጠን ነገር መሥራት በፍጹም እንደማይችሉ ከእነዚህ ርዕሶች መገንዘብ ችያለሁ።” የ15 ዓመት ልጅ ያላቸው በደቡብ አፍሪካ የሚኖሩ ባልና ሚስት “ልጃችን ንቁ! ሲደርሳት ብዙውን ጊዜ መጀመሪያ የምታነበው ‘ቃለ ምልልስ’ የሚለውን ዓምድ ነው” ብለዋል። እናንተስ በእነዚህ ዝግጅቶች ሙሉ በሙሉ ትጠቀማላችሁ? እንዲህ ካደረጋችሁ ጠንካራ እምነት ስለሚኖራችሁ ሥሮቹን በጥልቀት እንደሰደደ ዛፍ ትሆናላችሁ። ዛፉ ኃይለኛ ነፋስ ቢመጣበትም ጸንቶ እንደሚቆም ሁሉ እናንተም እንደ አውሎ ነፋስ የሆኑ የሐሰት ትምህርቶችን መቋቋም ትችላላችሁ።—ኤር. 17:5-8

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያላችሁ እምነት

7. አምላክ የማሰብ ችሎታችሁን እንድትጠቀሙ የሚፈልገው ለምንድን ነው?

7 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል ስለመሆኑ በቅንነት ጥያቄ ማንሳት ስህተት ነው? በፍጹም! ይሖዋ “የማሰብ ችሎታችሁን ተጠቅማችሁ” መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንድታረጋግጡ ይፈልጋል። ሌሎች ስላመኑበት ብቻ እንድታምኑበት አይፈልግም። ስለሆነም ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት የማመዛዘን ችሎታችሁን ተጠቀሙ። ይህ እውቀት ጠንካራ እምነት ለማዳበር መሠረት ይሆናችኋል። (ሮም 12:1, 2ን እና 1 ጢሞቴዎስ 2:4ን አንብብ።) እንደዚህ ዓይነት እውቀት ለመቅሰም የሚረዳችሁ አንዱ ነገር፣ ይበልጥ ልታውቋቸው የምትፈልጓቸውን ርዕሰ ጉዳዮች መርጣችሁ ምርምር ማድረግ ነው።

8, 9. (ሀ) አንዳንዶች ስለ የትኞቹ ርዕሰ ጉዳዮች ለማጥናት ግብ አውጥተዋል? (ለ) አንዳንዶች በሚያጠኑት ነገር ላይ ማሰላሰላቸው የጠቀማቸው እንዴት ነው?

8 አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሰፈሩት ትንቢቶች ወይም መጽሐፍ ቅዱስ ከታሪክ፣ ከአርኪኦሎጂና ከሳይንስ አንጻር ትክክል ስለመሆኑ ለማጥናት ግብ አውጥተዋል። ምርምር ልታደርጉባቸው ከምትችሏቸው ትኩረት የሚስቡ ትንቢቶች አንዱ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ይገኛል። ይህ ጥቅስ የመጽሐፍ ቅዱስ ዋና ጭብጥ ምን እንደሆነ ይኸውም በአምላክ መንግሥት አማካኝነት የይሖዋ አገዛዝ ትክክለኛነት እንደሚረጋገጥና ስሙ እንደሚቀደስ ይጠቁመናል። በምሳሌያዊ አነጋገር የተቀመጠው ይህ ጥቅስ፣ ከኤደን ጀምሮ በሰው ልጆች ላይ የደረሱትን መከራዎች በሙሉ ይሖዋ እንዴት እንደሚያስወግድ ይገልጻል። ታዲያ በዘፍጥረት 3:15 ላይ ምርምር ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ ክንውኖቹን በዘመን ቅደም ተከተል ማስፈር ሊሆን ይችላል። አምላክ፣ በዚህ ጥቅስ ላይ ከተገለጸው ዝግጅትና ከተጠቀሱት ግለሰቦች ጋር የተያያዙ እውነታዎችን ቀስ በቀስ እንዴት እንደገለጠ የሚጠቁሙ እንዲሁም ትንቢቱ እንዴት እንደሚፈጸም የሚያሳዩ ቁልፍ ጥቅሶችን በቅደም ተከተል ማስፈር ትችላላችሁ። ከዚያም ጥቅሶቹን አንድ ላይ ስትመለከቷቸው እርስ በርሱ የሚስማማ መልእክት እንደሚያስተላልፉ ታስተውላላችሁ፤ ይህን ስታዩ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያትና ጸሐፊዎች ሐሳቡን ያሰፈሩት “በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው” እንደሆነ መገንዘባችሁ አይቀርም።—2 ጴጥ. 1:21

9 በጀርመን የሚኖር አንድ ወንድም፣ በእያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጽ ሐሳብ እንደሚገኝ ተናግሯል፤ ከዚያም “የሚያስገርመው መጽሐፍ ቅዱስን የጻፉት 40 የሚያህሉ ሰዎች ናቸው። አብዛኞቹ የኖሩት በተለያየ ዘመን ሲሆን እርስ በርስም አይተዋወቁም” ብሏል። አንዲት አውስትራሊያዊት እህት ደግሞ በታኅሣሥ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ የጥናት ርዕስ ላይ የወጣው ስለ ፋሲካ ትርጉም የሚያብራራው ትምህርት ልቧን ነክቶታል። ይህ ልዩ በዓል ከዘፍጥረት 3:15 እና ከመሲሑ መምጣት ጋር ይያያዛል። እህት “ይህ የጥናት ርዕስ፣ ይሖዋ ምን ያህል አስደናቂ አምላክ እንደሆነ እንድገነዘብ ረድቶኛል” ስትል ጽፋለች። ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ይህን በዓል እንዲያከብሩ አስቀድሞ ዝግጅት ማድረጉና ይህ ዝግጅት ለኢየሱስ መሥዋዕት ጥላ መሆኑ በጣም እንዳስገረማት ገልጻለች። አክላም “ትንቢታዊ ትርጉም ያለው ይህ የፋሲካ በዓል፣ ምን ያህል አስደናቂ ዝግጅት እንደሆነ ቆም ብዬ ማሰብ አስፈልጎኝ ነበር!” ብላለች። ይህች እህት እንዲህ የተሰማት ለምንድን ነው? ያነበበችውን ነገር በጥልቀት ስላሰላሰለችበት እና ትርጉሙን ‘ስላስተዋለች’ ነው። ይህም እምነቷን እንድታጠናክርና ወደ ይሖዋ ይበልጥ እንድትቀርብ አስችሏታል።—ማቴ. 13:23

10. የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሐቀኝነት፣ በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያጠናክረው እንዴት ነው?

10 እምነታችሁን ለማጠናከር ምርምር ልታደርጉበት የምትችሉት ሌላው ነገር ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የነበራቸው ድፍረትና ሐቀኝነት ነው። ብዙዎቹ የጥንት ጸሐፊዎች ያሰፈሯቸው ዘገባዎች መሪዎቻቸውን የሚክቡና አገራቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው። የይሖዋ ነቢያት ግን ምንጊዜም እውነተኛውን ዘገባ ያሰፍሩ ነበር። የሕዝባቸውን ሌላው ቀርቶ የንጉሦቻቸውንም ጭምር ድክመት አስፍረዋል። (2 ዜና 16:9, 10፤ 24:18-22) ከዚህም ሌላ ጸሐፊዎቹ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች የአምላክ አገልጋዮች የፈጸሟቸውን ስህተቶች ሳይሸሽጉ ዘግበዋል። (2 ሳሙ. 12:1-14፤ ማር. 14:50) በብሪታንያ የሚኖር አንድ ወጣት ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እንደዚህ ያለ ሐቀኝነት ብዙ ጊዜ የሚታይ አይደለም። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ በእርግጥም የይሖዋ ቃል መሆኑን ይበልጥ እንድንተማመን ያደርገናል።”

11. በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ መመሪያዎች መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንድናምን የሚረዱን እንዴት ነው?

11 የአምላክ ቃል ለሕይወት ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን የያዘ መሆኑ፣ ብዙዎች ይህ መጽሐፍ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መሆኑን እንዲያምኑ አድርጓቸዋል። (መዝሙር 19:7-11ን አንብብ።) በጃፓን የምትኖር አንዲት ወጣት እህት እንዲህ በማለት ጽፋለች፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርቶች ተግባራዊ በማድረጋችን ቤተሰባችን ደስተኛ መሆን ችሏል። እንዲሁም በመካከላችን ሰላም፣ አንድነትና ፍቅር አለ።” የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች ተግባራዊ ማድረጋችን በሐሰት አምልኮ እንዳንካፈል የጠበቀን ከመሆኑም ሌላ ብዙዎችን ባሪያ ካደረጉት አጉል እምነቶች ነፃ አውጥቶናል። (መዝ. 115:3-8) አምላክ የለም የሚሉ ፍልስፍናዎች በሰዎች ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድረዋል? እንደ ዝግመተ ለውጥ ያሉ ትምህርቶች ለይሖዋ ብቻ የሚገባውን የአምላክነት ቦታ ለፍጥረት እንዲሰጥ አድርገዋል። አምላክ የለም የሚሉ ሰዎች የወደፊት ሕልውናችን ሙሉ በሙሉ በሰው ልጆች እጅ እንደሆነ ይሰማቸዋል። ይሁንና የተሻለ የወደፊት ሕይወት እንደሚኖረን እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ሊሰጡን አይችሉም።—መዝ. 146:3, 4

ሌሎችን ማስረዳት

12, 13. አብረዋችሁ ከሚማሩት ልጆች፣ ከአስተማሪዎቻችሁ ወይም ከሌሎች ሰዎች ጋር ስለ ፍጥረትና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ለመወያየት ውጤታማ የሆነው መንገድ ምንድን ነው?

12 ስለ ፍጥረትና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ውጤታማ በሆነ መንገድ ሌሎችን ማስረዳት የምትችሉት እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ የምታነጋግሩት ሰው ምን ብሎ እንደሚያምን እንደምታውቁ አድርጋችሁ አታስቡ። አንዳንዶች በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አምላክ እንዳለም ያስባሉ። አምላክ፣ ሕይወት ያላቸውን የተለያዩ ነገሮች ለመፍጠር ዝግመተ ለውጥን እንደተጠቀመ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምኑ የሚናገሩት ‘ይህ ጽንሰ ሐሳብ እውነት ባይሆን ኖሮ በትምህርት ቤት አንማረውም ነበር’ ብለው ስለሚያስቡ ነው። አንዳንዶች በአምላክ ማመን ያቆሙት በሃይማኖት ውስጥ የሚፈጸመው ነገር ቅር ስላሰኛቸው ነው። በመሆኑም ስለ ሕይወት አመጣጥ ከአንድ ሰው ጋር ስትወያዩ በቅድሚያ ጥያቄ መጠየቁ የተሻለ ነው። ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምን ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ምክንያታዊ ብሎም ለማዳመጥ ፈቃደኛ ከሆናችሁ ግለሰቡም እናንተ የምትናገሩትን ለማዳመጥ ሊነሳሳ ይችላል።—ቲቶ 3:2

13 አንድ ሰው በፍጥረት በማመናችሁ እየተቻችሁ እንዳለ ከተሰማችሁ፣ እሱን ለማስረዳት ከመሞከር ይልቅ ግለሰቡ የራሱን አመለካከት እንዲገልጽላችሁ ጠይቁት። ለምሳሌ፣ ፈጣሪ ሳይኖር ሕይወት እንዴት ሊገኝ እንደቻለ እንዲያስረዳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። የመጀመሪያው ሕይወት ያለው ነገር በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት ወደ ሌላ ሕያው ነገር መለወጥ እንዲችል መራባት ማለትም ራሱን ማባዛት መቻል አለበት። አንድ የኬሚስትሪ ፕሮፌሰር ይህን ለማድረግ ከሚያስፈልጉት ነገሮች መካከል የሚከተሉት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፦ (1) መከላከያ ሽፋን፣ (2) ኃይል የማግኘትና ጥቅም ላይ የማዋል ችሎታ፣ (3) በጂኖቹ ላይ የሰፈረ መረጃ እንዲሁም (4) ይህን መረጃ የመገልበጥ ችሎታ። ፕሮፌሰሩ አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው፣ ሕይወት ካላቸው ነገሮች መካከል ውስብስብ የማይባለው እንኳ ምን ያህል ውስብስብ እንደሆነ ሲመለከት በጣም መገረሙ አይቀርም።”

14. ስለ ፍጥረት ለማስረዳት ዝግጁ እንዳልሆናችሁ ከተሰማችሁ ምን ማድረግ ትችላላችሁ?

14 ስለ ፍጥረት ለማስረዳት ዝግጁ እንዳልሆናችሁ ከተሰማችሁ ጳውሎስ የተጠቀመበትን ቀላል ማስረጃ መጠቀም ትችላላችሁ። እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ ቤት ሠሪ እንዳለው የታወቀ ነው፤ ሁሉን ነገር የሠራው ግን አምላክ ነው።” (ዕብ. 3:4) ይህ ማብራሪያ ምክንያታዊነት የሚንጸባረቅበት ከመሆኑም ሌላ ውጤታማ ነው! በእርግጥም ውስብስብ የሆነ ንድፍ ሊያወጣ የሚችለው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ነው። ሌላው አማራጭ ደግሞ ተስማሚ የሆነ ጽሑፍ መጠቀም ነው። አንዲት እህት፣ አምላክ መኖሩን እንደማይቀበልና በዝግመተ ለውጥ እንደሚያምን ለነገራት አንድ ወጣት ከላይ የተጠቀሱትን ሁለት ብሮሹሮች ሰጠችው። ከአንድ ሳምንት ገደማ በኋላ ወጣቱ “አሁን አምላክ መኖሩን አምኛለሁ” አላት። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ወንድማችን ሆኗል።

15, 16. ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄ ከሚያነሱ ሰዎች ጋር ስትወያዩ ምን ማድረግ ትችላላችሁ? ግባችሁስ ምን ሊሆን ይገባል?

15 መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን ከሚጠራጠር ሰው ጋር ስትወያዩም ይህን ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ። ግለሰቡ ምን ብሎ እንደሚያምንና ትኩረቱን የሚስቡት ርዕሰ ጉዳዮች የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ ጥረት አድርጉ። (ምሳሌ 18:13) ሳይንሳዊ ነገሮች ትኩረቱን የሚስቡት ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ከሳይንስ አንጻር ትክክል መሆኑን የሚያሳዩ ነጥቦችን ብትጠቅሱለት ጥሩ ምላሽ ይሰጥ ይሆናል። ሌሎች ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፍጻሜያቸውን ያገኙ ትንቢቶችንና ትክክለኛ ታሪኮችን እንደያዘ የሚያሳዩ ምሳሌዎችን መመልከታቸው ልባቸውን ይነካው ይሆናል። አሊያም በተራራው ስብከት ላይ እንደሚገኙት ያሉ ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን መጥቀስ ትችላላችሁ።

16 ግባችሁ የሰውየውን ልብ መንካት እንጂ ተከራክሮ መርታት አለመሆኑን አስታውሱ። ስለዚህ ግለሰቡ ሲናገር በጥሞና አዳምጡት። በቅንነት ጥያቄዎችን አቅርቡለት፤ በተለይ በዕድሜ የሚበልጧችሁን ሰዎች ገርነትና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ ለማነጋገር ጥረት አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ አመለካከታችሁን ይበልጥ ሊያከብሩላችሁ ይችላሉ። በተጨማሪም የምታምኑበትን ነገር በሚገባ እንዳሰባችሁበት ይገነዘባሉ። ብዙዎቹ ወጣቶች የሚያምኑበትን ነገር በቁም ነገር አያስቡበትም። እርግጥ ነው፣ ምክንያታዊ ያልሆኑ ወይም በእምነታችሁ የሚያሾፉ ሰዎች ለሚያነሱት ጥያቄ መልስ የመስጠት ግዴታ የለባችሁም።—ምሳሌ 26:4

እውነትን የራሳችሁ አድርጉ

17, 18. (ሀ) እውነትን የራሳችሁ ለማድረግ ምን ሊረዳችሁ ይችላል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የትኛውን ጥያቄ እንመለከታለን?

17 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውቀት በመቅሰም ብቻ ጠንካራ እምነት ማዳበር አይቻልም። በመሆኑም የተቀበረ ሀብት የሚፈልግ ሰው በጥልቀት እንደሚቆፍር ሁሉ እናንተም በአምላክ ቃል ላይ ጥልቀት ያለው ምርምር አድርጉ። (ምሳሌ 2:3-6) የይሖዋ ድርጅት ያዘጋጃቸውን ሌሎች መሣሪያዎች ለምሳሌ፣ የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት እና በዲቪዲ የሚገኘውን ዎችታወር ላይብረሪ (እንግሊዝኛ) እንዲሁም የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች ማውጫ (እንግሊዝኛ) ወይም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባሉትን ጽሑፎች በሚገባ ተጠቀሙባቸው። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን ከዳር እስከ ዳር የማንበብ ግብ አውጡ። መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ ዓመት ውስጥ አንብባችሁ ለመጨረስ ልትሞክሩ ትችላላችሁ። የአምላክን ቃል የማንበብን ያህል ጠንካራ እምነት እንድናዳብር የሚረዳን ነገር የለም። አንድ የወረዳ የበላይ ተመልካች ስለ ወጣትነቱ ጊዜ አስታውሶ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን እንድገነዘብ የረዳኝ አንዱ ነገር ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ማንበቤ ነው። ትንሽ ልጅ እያለሁ የተማርኳቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ይበልጥ ትርጉም የሚሰጡ ሆነው አገኘኋቸው። ይህም መንፈሳዊ እድገት እንዳደርግ ትልቅ ሚና ተጫውቷል።”

18 እናንት ወላጆች፣ ልጆቻችሁ መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በመርዳት ረገድ ትልቅ ድርሻ አላችሁ። ታዲያ ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ ልትረዷቸው የምትችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጣል።