በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“የአምላክ ቃል ሕያው” ነው

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

በዕብራውያን 4:12 ላይ “ሕያውና ኃይለኛ ነው” የተባለው “የአምላክ ቃል” ምንድን ነው?

በጥቅሱ ዙሪያ ካለው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው፣ ሐዋርያው ጳውሎስ “የአምላክ ቃል” ሲል ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸውን መልእክት ማመልከቱ ነው፤ ይህ መልእክት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍረው የሚገኙትን ሐሳቦችም ይጨምራል።

ዕብራውያን 4:12 ብዙውን ጊዜ ጽሑፎቻችን ላይ የሚጠቀሰው፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይል እንዳለው ለመግለጽ ነው፤ ጥቅሱ በዚህ መንገድ መብራራቱም ተገቢ ነው። ነገር ግን ዕብራውያን 4:12 በዙሪያው ካለው ሐሳብ አንጻር ሰፋ ያለ ትርጉም እንዳለው መገንዘባችን አስፈላጊ ነው። ጳውሎስ፣ ዕብራውያን ክርስቲያኖችን ከአምላክ ዓላማዎች ጋር በሚስማማ መንገድ እንዲመላለሱ ማሳሰቡ ነበር። ከአምላክ ዓላማዎች መካከል ብዙዎቹ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፍረው ይገኛሉ። ጳውሎስ ከግብፅ ባርነት ነፃ የወጡትን እስራኤላውያን እንደ ምሳሌ ጠቅሷል። እነዚህ እስራኤላውያን “ወተትና ማር ወደምታፈሰው” እና እውነተኛ እረፍት ወደሚያገኙባት ተስፋይቱ ምድር እንደሚገቡ ቃል ተገብቶላቸው ነበር።—ዘፀ. 3:8፤ ዘዳ. 12:9, 10

አምላክ ለሕዝቡ የገለጸው ዓላማ ይህ ነበር። እስራኤላውያን ግን ከጊዜ በኋላ ልባቸውን ያደነደኑ ከመሆኑም በላይ እምነት አላሳዩም፤ ስለሆነም ብዙዎቹ እስራኤላውያን ወደ አምላክ እረፍት አልገቡም። (ዘኁ. 14:30፤ ኢያሱ 14:6-10) ይሁንና ጳውሎስ ‘ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋ አሁንም እንዳለ’ ተናግሯል። (ዕብ. 3:16-19፤ 4:1) ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸው መልእክት ይህን “ተስፋ” እንደሚጨምር ግልጽ ነው። እንደ ዕብራውያን ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ስለ አምላክ ዓላማ መማርና ከዚህ ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር እንችላለን። ጳውሎስ፣ ይህ ተስፋ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ መሆኑን ለማጉላት ዘፍጥረት 2:2⁠ን እና መዝሙር 95:11⁠ን በከፊል ጠቅሷል።

‘ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋ አሁንም’ ያለ መሆኑ ትኩረታችንን የሚስብ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው ወደ አምላክ እረፍት የመግባት ተስፋችን እውን እንደሚሆን እናምናለን፤ እንዲሁም ወደዚያ እረፍት ለመግባት የሚያስችሉንን እርምጃዎች ወስደናል። ይህን ያደረግነው የሙሴን ሕግ በመጠበቅ ወይም የይሖዋን ሞገስ ያስገኛሉ የሚባሉ ሌሎች ተግባራትን በመፈጸም አይደለም። ከዚህ ይልቅ እምነታችን፣ አምላክ ከገለጸው ዓላማ ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር በፈቃዳችን ጥረት እንድናደርግ አነሳስቶናል፤ ወደፊትም ይህን ማድረጋችንን እንቀጥላለን። ይሁን እንጂ ከላይ እንደተገለጸው በዕብራውያን 4:12 ላይ የሚገኘው “የአምላክ ቃል” የሚለው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱስንም ሊያመለክት ይችላል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጸውን መልእክት ማወቅ ችለዋል። በመሆኑም ከእነዚህ ሰዎች መካከል ብዙዎቹ አኗኗራቸውን ለመቀየር፣ እምነት ለማሳየትና ተጠምቀው ክርስቲያኖች ለመሆን ተነሳስተዋል። እነዚህ ሰዎች እየወሰዱ ያሉት እርምጃ “የአምላክ ቃል ሕያውና ኃይለኛ” መሆኑን በግልጽ ያሳያል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈረው ስለ አምላክ ዓላማ የሚገልጽ መልእክት በሕይወታችን ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ወደፊትም በሕይወታችን ላይ ለውጥ ማምጣቱን ይቀጥላል።