በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ወዳጅነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ እውነተኛ ወዳጅ መሆን

ወዳጅነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ እውነተኛ ወዳጅ መሆን

ጃኒ እና ማውሪትስዮ የተባሉት ጓደኛሞች ወደ 50 ለሚጠጉ ዓመታት የዘለቀ ወዳጅነት አላቸው። ይሁን እንጂ በአንድ ወቅት ወዳጅነታቸው አደጋ ላይ ወድቆ ነበር። ማውሪትስዮ “በአንድ አስቸጋሪ ወቅት ከባድ ስህተት ሠራሁ፤ ይህም እንድንራራቅ አደረገን” ሲል ተናግሯል። ጃኒ ደግሞ እንዲህ ብሏል፦ “መጽሐፍ ቅዱስን ያስጠናኝ ማውሪትስዮ ነበር። በመንፈሳዊ ብዙ ረድቶኛል። በመሆኑም ያደረገውን ነገር መቀበል አቃተኝ። ከዚያ በኋላ ወዳጅነታችን እንደማይቀጥል ሳስበው ሰማይ ምድሩ ዞረብኝ። እንደከዳኝ ሆኖ ተሰማኝ።”

ጥሩ ወዳጆች በቀላሉ አይገኙም፤ ዘላቂ ወዳጅነትም እንዲሁ በአጋጣሚ የሚገኝ ነገር አይደለም። ከሌሎች ጋር ያለን ወዳጅነት እንዲበላሽ ሊያደርግ የሚችል ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ይህ እንዳይሆን ምን ማድረግ ይቻላል? በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱ ጥሩ ወዳጅነት የነበራቸው ሰዎች ትምህርት መውሰድ እንችላለን፤ እነዚህ ሰዎች ወዳጅነታቸውን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን አድርገዋል?

ወዳጃችን ስህተት በሚሠራበት ጊዜ

እረኛና ንጉሥ የነበረው ዳዊት ጥሩ ወዳጆች ነበሩት። ከወዳጆቹ መካከል ቶሎ ትዝ የሚለን ዮናታን ነው። (1 ሳሙ. 18:1) ይሁንና ዳዊት እንደ ነቢዩ ናታን ያሉ ሌሎች ወዳጆችም ነበሩት። የዳዊትና የናታን ወዳጅነት የጀመረው መቼ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ይሁንና በአንድ ወቅት ዳዊት የልብ ወዳጅ ለሆነ ሰው የሚነገርን ጉዳይ ለነቢዩ ናታን እንዳካፈለው መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ዳዊት ለይሖዋ ቤት መሥራት ፈልጎ ነበር። ንጉሥ ዳዊት ናታንን ያማከረው የልብ ወዳጁና የአምላክ መንፈስ ያለበት ሰው እንደሆነ አድርጎ ስለተመለከተው መሆን አለበት።—2 ሳሙ. 7:2, 3

ይሁንና ወዳጅነታቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል አንድ ነገር ተከሰተ። ንጉሥ ዳዊት ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር የፈጸመ ሲሆን ከዚያም ባሏን ኦርዮን አስገደለው። (2 ሳሙ. 11:2-21) ዳዊት ለብዙ ዓመታት ይሖዋን በታማኝ ያገለገለ ከመሆኑም ሌላ ለፍትሕ የሚቆረቆር ሰው ነበር። ሆኖም ይህን ከባድ ኃጢአት ፈጸመ! ይህ ጥሩ ንጉሥ እንዴት እንዲህ ያለ ድርጊት ሊፈጽም ቻለ? ያደረገው ነገር ምን ያህል ከባድ እንደሆነ አልተገነዘበም? ድርጊቱን ከአምላክ መደበቅ እንደሚችል አስቦ ይሆን?

ናታን ምን ያደርግ ይሆን? ሌላ ሰው ንጉሡን እንዲያናግረው ያደርግ ይሆን? ሌሎች ሰዎችም ዳዊት ኦርዮን እንዴት እንዳስገደለው ያውቁ ነበር። ታዲያ ናታን እዚህ ጉዳይ ውስጥ በመግባት ከንጉሡ ጋር የነበረውን ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ወዳጅነት ለምን አደጋ ላይ ይጥላል? ናታን ስለዚህ ጉዳይ መናገሩ ሕይወቱንም ጭምር ሊያሳጣው ይችላል። ዳዊት ንጹሕ ሰው የነበረውን ኦርዮን እንኳ ከማስገደል ወደኋላ እንዳላለ ያውቃል።

ይሁንና ናታን የአምላክ ቃል አቀባይ ነበር። በመሆኑም ዝም ካለ ሕሊናው እንደሚወቅሰው እንዲሁም ከዳዊት ጋር የነበረው ዝምድና እንደሚበላሽ ያውቅ ነበር። ወዳጁ ዳዊት በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ድርጊት ፈጽሟል። ንጉሡ ከይሖዋ ጋር የነበረውን ግንኙነት ለማስተካከል የግድ እርዳታ ማግኘት ያስፈልገው ነበር። አዎ፣ ዳዊት እውነተኛ ወዳጅ ያስፈልገው ነበር። ናታን ደግሞ እንዲህ ዓይነት ወዳጅ ነበር። ዳዊት ቀደም ሲል እረኛ ስለነበር ናታን የእሱን ልብ ሊነካ የሚችል ምሳሌ በመጠቀም አነጋገረው። ናታን የአምላክን መልእክት ያደረሰው፣ ዳዊት ስህተቱ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲገነዘብና እርምጃ እንዲወስድ በሚያበረታታ መንገድ ነበር።—2 ሳሙ. 12:1-14

አንተስ ወዳጅህ ትልቅ ስህተት ቢሠራ ወይም ከባድ ኃጢአት ቢፈጽም ምን ታደርጋለህ? ስህተቱን ብትነግረው ከእሱ ጋር ያለህ ወዳጅነት እንደሚበላሽ በማሰብ እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ ትል ይሆናል። አሊያም ደግሞ የሠራውን ኃጢአት በመንፈሳዊ ሊረዱት ለሚችሉት ሽማግሌዎች መናገር እሱን እንደመክዳት ሆኖ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ ምን ታደርጋለህ?

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጃኒ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “አንድ የተፈጠረ ነገር እንዳለ ተገነዘብኩ። ማውሪትስዮ እንደ በፊቱ በግልጽ አያነጋግረኝም ነበር። በጣም ከባድ የነበረ ቢሆንም ቀርቤ ላነጋግረው ወሰንኩ። ‘ምን አዲስ ነገር ልነግረው እችላለሁ? እሱ ሁሉንም ነገር ያውቀዋል። ይህን ጉዳይ ማንሳቱ ሊያስቆጣው ይችላል!’ ብዬ አሰብኩ። ይሁንና ከእሱ ጋር ያጠናናቸውን ነገሮች ማስታወሴ እሱን ለማነጋገር የሚያስችል ጥንካሬ ሰጠኝ። ማውሪትስዮ እርዳታ ባስፈለገኝ ጊዜ እንዲህ አድርጎልኛል። ከእሱ ጋር ያለኝን ወዳጅነት ማጣት ባልፈልግም እሱን ለመርዳት አንድ ነገር ማድረግ እንዳለብኝ ወሰንኩ።”

ማውሪትስዮ እንዲህ ብሏል፦ “ጃኒ ከልቡ ሊረዳኝ ሞክሯል፤ ደግሞም ያደረገው ነገር ትክክል ነበር። ያደረግኩት የተሳሳተ ምርጫ ላስከተለብኝ መጥፎ ውጤት እሱም ሆነ ይሖዋ ተጠያቂ እንዳልሆኑ አውቃለሁ። በመሆኑም ሽማግሌዎች የሰጡኝን ተግሣጽ የተቀበልኩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በመንፈሳዊ አገገምኩ።”

ወዳጃችን ችግር በሚያጋጥመው ጊዜ

ዳዊት በአስቸጋሪ ጊዜያት በታማኝነት ከጎኑ የቆሙ ሌሎች ወዳጆችም ነበሩት። ከእነዚህ ሰዎች መካከል ኩሲ ይገኝበታል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ኩሲን “የዳዊት ወዳጅ” በማለት ይጠራዋል። (2 ሳሙ. 16:16፤ 1 ዜና 27:33) ኩሲ የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን ሳይሆን አይቀርም፤ የንጉሡ የቅርብ ወዳጅ የነበረው ይህ ሰው አንዳንድ ጊዜ ሚስጥራዊ ተልእኮዎችንም ይወጣ ነበር።

የዳዊት ልጅ አቢሴሎም የመንግሥት ግልበጣ ባደረገበት ጊዜ በርካታ እስራኤላውያን ከአቢሴሎም ጎን ቆመው የነበረ ቢሆንም ኩሲ እንዲህ አላደረገም። ዳዊት እየሸሸ በነበረበት ወቅት ኩሲ ወደ እሱ ሄደ። ዳዊት የገዛ ልጁ እንዲሁም ያምናቸው የነበሩ ሌሎች ሰዎች ስለከዱት ስሜቱ በጣም ተጎድቶ ነበር። ኩሲ ግን ሴራውን እንዲያከሽፍ የተሰጠውን ተልእኮ ለመወጣት ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ በመጣል በታማኝነት ከዳዊት ጎን ቆሟል። ኩሲ ይህን ያደረገው የቤተ መንግሥት ባለሥልጣን መሆኑ የሚያስከትልበትን ኃላፊነት ለመወጣት ያህል ብቻ ሳይሆን የዳዊት ታማኝ ወዳጅ ስለነበር ነው።—2 ሳሙ. 15:13-17, 32-37፤ 16:15 እስከ 17:16

በዛሬው ጊዜም ወንድሞችና እህቶች እርስ በርስ የሚደጋገፉት በጉባኤ ውስጥ ያላቸው ቦታ የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ያህል ብቻ ሳይሆን በመካከላቸው እውነተኛ ወዳጅነት ስላለ ነው። እነዚህ ሰዎች ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ወዳጅ የሆኑት ግዴታቸው ስለሆነ ሳይሆን ለእነሱ ትልቅ ቦታ ስለሚሰጡ እንደሆነ ከሚያደርጉት ነገር በግልጽ ማየት ይቻላል።

ፌዴሪኮ የተባለ ወንድም ይህን በራሱ ሕይወት ተመልክቷል። ወዳጁ አንቶንዮ ያደረገለት እርዳታ፣ ያጋጠመውን አስቸጋሪ ሁኔታ እንዲቋቋም አስችሎታል። ፌዴሪኮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንቶንዮ ወደ ጉባኤያችን እንደተዛወረ ወዲያውኑ ወዳጆች ሆንን። ሁለታችንም የጉባኤ አገልጋዮች የነበርን ሲሆን አብረን መሥራት ያስደስተን ነበር። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እሱ ሽማግሌ ሆኖ ተሾመ። አንቶንዮ ጓደኛዬ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊ እንደ አርዓያ አድርጌ የምመለከተው ሰው ነበር።” ከጊዜ በኋላ ፌዴሪኮ የኃጢአት ድርጊት ፈጸመ። ወዲያውኑ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ጥረት ያደረገ ቢሆንም የጉባኤ አገልጋይነትና የአቅኚነት መብቱን አጣ። በዚህ ወቅት አንቶንዮ ምን አደረገ?

ፌዴሪኮ ችግር ውስጥ በገባበት ወቅት ወዳጁ አንቶንዮ አዳምጦታል እንዲሁም አበረታቶታል

ፌዴሪኮ እንዲህ ሲል ያስታውሳል፦ “አንቶንዮ ስሜቴን ተረድቶልኝ ነበር። እኔን ለማጽናናት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። መንፈሳዊነቴ ያሳስበው የነበረ ከመሆኑም ሌላ ከጎኔ አልተለየም። እንደ ቀድሞው በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድሆንና ተስፋ እንዳልቆርጥ አበረታቶኛል።” አንቶንዮ እንዲህ ብሏል፦ “ከፌዴሪኮ ጋር ብዙ ጊዜ አሳልፍ ነበር። የተሰማውን ነገር ሁሉ ለእኔ ለመንገር ነፃነት እንዲሰማው እፈልግ ነበር።” ደስ የሚለው ፌዴሪኮ ከጊዜ በኋላ ወደ ቀድሞ መንፈሳዊ ሁኔታው መመለስ የቻለ ሲሆን በድጋሚ አቅኚና የጉባኤ አገልጋይ ሆኖ ተሾመ። አንቶንዮ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አሁን የምናገለግለው በተለያዩ ጉባኤዎች ውስጥ ቢሆንም ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንቀራረባለን።”

እንደተከዳህ ይሰማሃል?

የቅርብ ወዳጅህ፣ የእሱ እርዳታ በጣም በሚያስፈልግህ ወቅት ጀርባውን ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? ይህ ስሜትህን በጥልቅ ሊጎዳው ይችላል። ታዲያ በዚህ ወቅት ወዳጅህን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ትሆናለህ? ወዳጅነታችሁ እንደ በፊቱ ጠንካራ ሊሆን ይችላል?

ኢየሱስ በምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ቀናት ምን እንዳጋጠመው እስቲ አስብ። ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ብዙ ጊዜ ያሳለፈ ሲሆን በመካከላቸው የጠበቀ ትስስር ነበር። ኢየሱስ ሐዋርያቱን “ወዳጆች” ብሎ ጠርቷቸዋል። (ዮሐ. 15:15) ይሁንና ኢየሱስ በተያዘ ጊዜ ምን ተከሰተ? ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሹ። ጴጥሮስ ጌታውን ፈጽሞ እንደማይተወው በግልጽ የተናገረ ቢሆንም በዚያው ምሽት ኢየሱስን “አላውቀውም” ብሎ ካደ!—ማቴ. 26:31-33, 56, 69-75

ኢየሱስ የመጨረሻ ፈተናውን ብቻውን እንደሚጋፈጥ ቢያውቅም ቅር ሊሰኝና ስሜቱ ሊጎዳ ይችል ነበር። ነገር ግን ከሞት ከተነሳ ከጥቂት ቀናት በኋላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ያደረገው ውይይት ፈጽሞ ቅር እንዳልተሰኘ፣ እንዳልተከፋ ወይም እንዳላዘነ ያሳያል። ደቀ መዛሙርቱ በተያዘበት ምሽት ያደረጉትን ነገርም ሆነ ከዚያ በፊት የሠሯቸውን ስህተቶች በመጥቀስ አልወቀሳቸውም።

በተቃራኒው ኢየሱስ ጴጥሮስንና ሌሎቹን ሐዋርያት አበረታቷቸዋል። በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ በጣም አስፈላጊ ስለሆነ የማስተማር ሥራ መመሪያ በመስጠት በእነሱ ላይ እምነት እንዳለው አረጋግጦላቸዋል። በዚህ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ሐዋርያቱን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ይመለከታቸው ነበር። ኢየሱስ ያሳያቸው ፍቅር የሐዋርያቱን ልብ በጥልቅ ነክቶታል። ጌታቸውን ዳግም ላለማሳዘን የሚችሉትን ሁሉ እንዲያደርጉ አነሳስቷቸዋል። ደግሞም ኢየሱስ የሰጣቸውን ሥራ በተሳካ ሁኔታ ተወጥተዋል።—ሥራ 1:8፤ ቆላ. 1:23

ኤልቪራ የተባለች እህት የቅርብ ወዳጇ ከሆነችው ከጁልያና ጋር አለመግባባት በተፈጠረ ጊዜ የነበረውን ሁኔታ በደንብ ታስታውሳለች። ኤልቪራ እንዲህ ብላለች፦ “ጁልያና ባደረግኩት ነገር እንደተጎዳች ስትነግረኝ በጣም አዘንኩ። ደግሞም መበሳጨቷ አያስገርምም። ይሁንና በጣም የተጨነቀችው ስለ እኔ መሆኑ አስገረመኝ፤ ያሳየሁት ጠባይ የሚያስከትለው ውጤት አሳስቧት ነበር። ባደረስኩባት በደል ላይ ከማተኮር ይልቅ ድርጊቱ በራሴ ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት ማሰቧ ምንጊዜም ያስደንቀኛል። ከራሷ ስሜት በላይ ለእኔ ደህንነት የምትጨነቅ ጓደኛ ስለሰጠኝ ይሖዋን አመሰገንኩት።”

ታዲያ ወዳጅነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ጥሩ ወዳጅ ምን እርምጃ ይወስዳል? አስፈላጊ ሲሆን ወዳጁን በደግነት ሆኖም በግልጽ ከማነጋገር ወደኋላ አይልም። እንዲህ ያለ ወዳጅ ልክ እንደ ናታን እና ኩሲ በአስቸጋሪ ጊዜያትም ታማኝ ነው፤ በተጨማሪም ልክ እንደ ኢየሱስ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ይሆናል። አንተስ እንዲህ ዓይነት ወዳጅ ነህ?