የጥናት ርዕስ 10
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ በጉባኤ ደረጃ መርዳት
“እያንዳንዱ የአካል ክፍል [አካሉ] እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል።”—ኤፌ. 4:16
መዝሙር 85 አንዳችን ሌላውን መቀበል
ማስተዋወቂያ *
1-2. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ እነማን ሊረዱት ይችላሉ?
“በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቴ ላይ የምማረውን ነገር በጣም ወድጄው ነበር” በማለት በፊጂ የምትኖረው ኤሚ ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “የምማረው ነገር እውነት መሆኑን አውቄ ነበር። ግን አስፈላጊውን ለውጥ ያደረግኩትና እድገት አድርጌ የተጠመቅኩት ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር መቀራረብ ከጀመርኩ በኋላ ነው።” የኤሚ ተሞክሮ አንድን ወሳኝ እውነታ ያስገነዝበናል፦ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የጉባኤውን ወንድሞችና እህቶች እርዳታ ማግኘቱ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ይረዳዋል።
2 እያንዳንዱ አስፋፊ ጉባኤው እንዲያድግ የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል። (ኤፌ. 4:16) ሌላኒ የተባለች በቫኑዋቱ የምትኖር አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “‘ልጅን የሚያሳድገው መንደሩ በሙሉ ነው’ የሚል አባባል አለ። ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ይመስለኛል፤ ብዙውን ጊዜ አንድን ሰው ወደ እውነት ለማምጣት የመላው ጉባኤ እርዳታ ያስፈልጋል።” አንድ ልጅ አድጎ አዋቂ እስኪሆን ድረስ የቤተሰቡ አባላት፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም አስተማሪዎቹ በሙሉ ይረዱታል። ይህን የሚያደርጉት ልጁን በማበረታታትና አንዳንድ አስፈላጊ ነገሮችን በማስተማር ነው። በተመሳሳይም አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መምከር፣ ማበረታታትና ለእነሱ ጥሩ ምሳሌ መሆን ይችላሉ። በዚህ መልኩ ጥናቶቹ እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ይረዷቸዋል።—ምሳሌ 15:22
3. አና፣ ዶሪን እና ሌላኒ ከተናገሩት ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን የሚመራው አስፋፊ፣ ሌሎች አስፋፊዎች ጥናቱን እንዲረዱት ፈቃደኛ መሆን ያለበት ለምንድን ነው? በሞልዶቫ የምትኖር አና የተባለች ልዩ አቅኚ ምን እንዳለች ልብ እንበል፦ “አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት እንዲያደርግ ብዙ እርዳታ ያስፈልገዋል። ስለዚህ አስጠኚው፣ ዮሐ. 13:35
ጥናቱ የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ ብቻውን ማሟላት ከባድ ይሆንበታል።” በዚያው አገር በልዩ አቅኚነት የሚያገለግለው ዶሪንም እንዲህ ብሏል፦ “ሌሎች አስፋፊዎች የጥናቴን ልብ የሚነካ ነገር ሲናገሩ ብዙ ጊዜ አጋጥሞኛል፤ እነሱ የጠቀሱትን ነገር እኔ ብሆን ጨርሶ አላስበውም ነበር።” ሌላኒ ደግሞ ተጨማሪ ነጥብ ገልጻለች፦ “ወንድሞችና እህቶች ለጥናቱ የሚያሳዩት ፍቅርና ወዳጃዊ ስሜት የይሖዋ ሕዝቦች መሆናችንን እርግጠኛ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል።”—4. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?
4 ይሁንና ‘የእኔ ጥናት ያልሆነ ሰው እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ መርዳት የምችለው እንዴት ነው?’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ እንድንገኝ ስንጋበዝ እንዲሁም ጥናቱ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር ምን ማድረግ እንደምንችል እስቲ እንመልከት። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ በመርዳት ረገድ ሽማግሌዎች ምን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክቱ እንመለከታለን።
ጥናት ስትጋበዝ
5. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስትጋበዝ የአንተ ሚና ምንድን ነው?
5 በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ተማሪው የአምላክን ቃል እንዲረዳ ማድረግ በዋነኝነት የአስጠኚው ኃላፊነት ነው። አስጠኚው ጥናት ሲመራ እንድትገኝ ከጋበዘህ የእሱ ረዳት መሆንህን ማስታወስ ይኖርብሃል። የአንተ ሚና እሱን ማገዝ ነው። (መክ. 4:9, 10) ታዲያ በጥናቱ ወቅት ጥሩ ረዳት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
6. ጥናት ስትጋበዝ በምሳሌ 20:18 ላይ ያለውን መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው?
6 ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ተዘጋጅ። በመጀመሪያ አስጠኚው ስለ ተማሪው አንዳንድ ነገሮችን እንዲነግርህ ጠይቀው። (ምሳሌ 20:18ን አንብብ።) እንዲህ ብለህ ልትጠይቀው ትችላለህ፦ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ ምን ልትነግረኝ ትችላለህ? የምታጠኑት ስለ ምንድን ነው? በዛሬው ጥናት ማስጨበጥ የምትፈልገው የትኛውን ነጥብ ነው? በጥናቱ ወቅት እንዳደርግ ወይም እንድናገር የምትፈልገው አሊያም የማትፈልገው ነገር አለ? ጥናቱ እድገት እንዲያደርግ ለማበረታታት ምን ማድረግ እችላለሁ?” እርግጥ አስጠኚው የጥናቱን ሚስጥር አይነግርህም። ሆኖም ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን ሊነግርህ ይችላል። ጆይ የተባለች ሚስዮናዊት፣ ጥናት ከምትጋብዛቸው ሰዎች ጋር እንዲህ ዓይነት ውይይት ታደርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረጌ ጥናት የምጋብዘው ሰው ጥናቴን ለመርዳት እንዲነሳሳና በጥናቱ ወቅት ምን ማለት እንዳለበት እንዲያውቅ ይረዳዋል።”
7. ጥናት ስትጋበዝ ለጥናቱ መዘጋጀት ያለብህ ለምንድን ነው?
7 ጥናት ከተጋበዝክ የምታጠኑትን ትምህርት አስቀድመህ መዘጋጀትህ ጥሩ ይሆናል። (ዕዝራ 7:10) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ዶሪን እንዲህ ብሏል፦ “ጥናት የጋበዝኩት ሰው ለጥናቱ ተዘጋጅቶ ሲመጣ ደስ ይለኛል። እንዲህ ማድረጉ በጥናቱ ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለመስጠት ይረዳዋል።” በተጨማሪም ጥናቱ ሁለታችሁም በደንብ እንደተዘጋጃችሁ ማስተዋሉ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ለእሱም ጥሩ ምሳሌ ይሆነዋል። ትምህርቱን በጥልቀት መዘጋጀት ባትችልም እንኳ ጥቂት ጊዜ ወስደህ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማግኘት መሞከርህ ጠቃሚ ነው።
8. በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ወቅት ትርጉም ያለው ጸሎት ማቅረብ የምትችለው እንዴት ነው?
8 ጸሎት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ወሳኝ ክፍል ነው። ስለዚህ አስጠኚው እንድትጸልይ ቢጠይቅህ ምን ብለህ እንደምትጸልይ አስቀድመህ አስብ። እንዲህ ካደረግክ ጸሎትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆናል። (መዝ. 141:2) በጃፓን የምትኖረው ሃናኤ ከአስጠኚዋ ጋር አብራ ትመጣ የነበረች እህት ታቀርበው የነበረውን ጸሎት እስካሁን ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላት ስላስተዋልኩ እኔም እንደ እሷ ለመሆን ፈለግኩ። ስሜን እየጠቀሰች መጸለይዋም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።”
9. በያዕቆብ 1:19 መሠረት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ጥሩ ረዳት መሆን የምትችለው እንዴት ነው?
9 በጥናቱ ወቅት አስጠኚውን አግዘው። በናይጄርያ የምትኖር ኦማሙዮቪ የተባለች ልዩ አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ ረዳት ጥናቱ ሲመራ በሚገባ ይከታተላል። በጥናቱ ወቅት ጥሩ ሐሳቦችን ይሰጣል። ሆኖም ጥናቱን በዋነኝነት የሚመራው አስጠኚው እንደሆነ ስለሚገነዘብ ብዙ ላለመናገር ይጠነቀቃል።” ይሁንና ሐሳብ መስጠት ያለብህ መቼ እንደሆነ እና ምን ማለት እንዳለብህ ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? (ምሳሌ 25:11) አስጠኚውና ጥናቱ ሲነጋገሩ በትኩረት አዳምጥ። (ያዕቆብ 1:19ን አንብብ።) አስፈላጊ ሲሆን ሐሳብ መስጠት የምትችለው እንዲህ ካደረግክ ብቻ ነው። እርግጥ አስተዋይ መሆን አለብህ። ለምሳሌ ብዙ ማውራት፣ አስጠኚው ሲያስረዳ ጣልቃ መግባት ወይም ሌላ ርዕሰ ጉዳይ ማንሳት አይኖርብህም። ሆኖም አጠር ያለ ሐሳብ፣ ምሳሌ ወይም ጥያቄ በማንሳት ነጥቡ ይበልጥ ግልጽ እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ በርዕሰ ጉዳዩ ላይ ብዙም የምትጨምረው ሐሳብ እንደሌለ ይሰማህ ይሆናል። ያም ቢሆን ጥናቱን ማመስገንህና አሳቢነት ማሳየትህ እድገት እንዲያደርግ በእጅጉ ሊረዳው ይችላል።
10. ተሞክሮህን መናገርህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱን ሊረዳው የሚችለው እንዴት ነው?
10 ለጥናቱ ተሞክሮህን ንገረው። ጥናቱን እንደሚጠቅመው ከተሰማህ፣ እንዴት እውነትን እንደሰማህ ወይም አንድን ተፈታታኝ ሁኔታ እንዴት እንደተወጣህ አሊያም በሕይወትህ ውስጥ የይሖዋን እጅ ያየኸው እንዴት እንደሆነ በአጭሩ ልትነግረው ትችላለህ። (መዝ. 78:4, 7) ተሞክሮህ ጥናቱን በእጅጉ ሊረዳው ይችላል። እምነቱን ሊያጠናክርለት እንዲሁም እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ሊያነሳሳው ይችላል። በተጨማሪም ያጋጠመውን ፈተና እንዴት መወጣት እንደሚችል እንዲገነዘብ ሊረዳው ይችላል። (1 ጴጥ. 5:9) በብራዚል የሚኖር ጋብርኤል የተባለ የዘወትር አቅኚ መጽሐፍ ቅዱስን እያጠና በነበረበት ወቅት ምን እንደረዳው ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “የወንድሞችን ተሞክሮ ስሰማ ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚያይ ተገነዘብኩ። እንዲሁም እነሱ እነዚህን ፈተናዎች መወጣት ከቻሉ እኔም እንደምችል ተረዳሁ።”
ጥናቱ በስብሰባዎች ላይ መገኘት ሲጀምር
11-12. አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በስብሰባ ላይ ሲገኝ ሞቅ ያለ አቀባበል ልናደርግለት የሚገባው ለምንድን ነው?
11 አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ አዘውትሮ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘትና ከስብሰባዎች ጥቅም ማግኘት አለበት። (ዕብ. 10:24, 25) አስጠኚው፣ ጥናቱ በስብሰባዎች ላይ እንዲገኝ መጋበዙ አይቀርም። ጥናቱ በስብሰባ ላይ ሲገኝ ወደ ስብሰባ መምጣቱን እንዲቀጥል ሁላችንም ልናበረታታው እንችላለን። እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
12 ጥናቱን ሞቅ አድርገህ ተቀበለው። (ሮም 15:7) ጥናቱ ጥሩ አቀባበል ከተደረገለት ወደ ስብሰባ መምጣቱን ለመቀጠል ሊነሳሳ ይችላል። ጥናቱን ሞቅ ባለ መንገድ ሰላም በለው እንዲሁም ከሌሎች ጋር አስተዋውቀው፤ ሆኖም ይህን የምታደርገው ጥናቱን በሚያስጨንቅ መንገድ መሆን የለበትም። አስጠኚው ስላለ ብቻውን አይሆንም ብለህ አታስብ፤ አስጠኚው ዘግይቶ ሊመጣ ወይም በስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ሌላ ሥራ ሊኖረው ይችላል። ደግሞም ጥናቱ ሲናገር ትኩረት ሰጥተህ አዳምጠው፤ በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት አሳየው። ለጥናቱ ሞቅ ያለ አቀባበል ማድረግህ ምን ውጤት ሊኖረው ይችላል? ከጥቂት ዓመታት በፊት የተጠመቀውንና አሁን በጉባኤ አገልጋይነት እያገለገለ ያለውን የዲሚትሪን ምሳሌ እንመልከት። ለመጀመሪያ ጊዜ በስብሰባ ላይ ስለተገኘበት ወቅት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ፈራ ተባ እያልኩ ከስብሰባ አዳራሹ ውጭ ቆሜ እየጠበቅኩ ሳለ አንድ ወንድም መጣና በደግነት ወደ አዳራሹ ይዞኝ ገባ። ብዙ ሰዎች መጥተው ሰላም አሉኝ። ሁኔታው በጣም አስገረመኝ። በጣም ስለተደሰትኩ በየቀኑ ስብሰባ ቢኖረን ብዬ ተመኘሁ። ከዚህ በፊት የትም ቦታ እንደዚህ ተሰምቶኝ አያውቅም።”
13. ምግባራችን በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይችላል?
13 ጥሩ ምሳሌ ሁን። የምታሳየው ምግባር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል። (ማቴ. 5:16) አሁን በሞልዶቫ በአቅኚነት የሚያገለግለው ቪታሊ እንዲህ ብሏል፦ “በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን አኗኗር፣ አስተሳሰብና ምግባር አስተውል ነበር። ይህም የይሖዋ ምሥክሮች እውነተኛውን ሃይማኖት እንደያዙ እርግጠኛ እንድሆን አደረገኝ።”
14. የእኛ መልካም ምሳሌነት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ሊረዳቸው የሚችለው እንዴት ነው?
14 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ለመጠመቅ ብቃቱን እንዲያሟላ፣ የተማረውን ነገር በሥራ ላይ ማዋል አለበት። እንዲህ ማድረግ ግን ቀላል የማይሆንበት ጊዜ አለ። ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች ተግባራዊ ማድረጋችን እንዴት እንደጠቀመን ጥናቱ ሲመለከት የእኛን ምሳሌ ለመከተል ሊነሳሳ ይችላል። (1 ቆሮ. 11:1) ቀደም ሲል የተጠቀሰችውን የሃናኤን ተሞክሮ እንመልከት። እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞችና እህቶች እኔ የምማረውን ነገር ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ተመልክቼ ነበር። ሌሎችን የማበረታታ፣ ይቅር ባይና አፍቃሪ ሰው መሆን የምችለው እንዴት እንደሆነ ከእነሱ ተማርኩ። ምንጊዜም ስለ ሌሎች የሚናገሩት መልካም ነገር ነበር። ስለዚህ እኔም እንደ እነሱ ለመሆን ተነሳሳሁ።”
15. በምሳሌ 27:17 መሠረት አንድ ጥናት በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ሲቀጥል ጓደኛ ልናደርገው የሚገባው ለምንድን ነው?
15 ጥናቱን ጓደኛ አድርገው። ጥናቱ በስብሰባዎች ላይ መገኘቱን ሲቀጥል አንተም ለእሱ ትኩረት መስጠትህን ቀጥል። (ፊልጵ. 2:4) ለምን ቀረብ ብለህ አታጫውተውም? እስካሁን ላደረጋቸው ለውጦች አመስግነው፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እንዴት እየሄደ እንዳለ፣ ስለ ቤተሰቡና ስለ ሥራው ጠይቀው፤ እርግጥ እንዲህ ስታደርግ በግል ጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለብህም። ከጥናቱ ጋር የምታደርገው ጭውውት ይበልጥ እንድትቀራረቡ ሊረዳችሁ ይችላል። ጥናቱን ጓደኛ ማድረግህ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ሊረዳው ይችላል። (ምሳሌ 27:17ን አንብብ።) ሃናኤ አሁን በዘወትር አቅኚነት እያገለገለች ነው። በስብሰባዎች ላይ መገኘት ስለጀመረችበት ጊዜ ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤ ውስጥ ጓደኞች ሳፈራ ስብሰባዎችን በጉጉት መጠበቅ ጀመርኩ። ቢደክመኝም እንኳ ከስብሰባ አልቀርም ነበር። ከአዲሶቹ ጓደኞቼ ጋር ጊዜ ማሳለፍ ያስደስተኝ ነበር፤ ይህም እምነቴን ከማይጋሩ ሰዎች ጋር የነበረኝን ጓደኝነት ለማቆም ረድቶኛል። ከይሖዋ እንዲሁም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ይበልጥ ለመቀራረብ ተነሳሳሁ። በመሆኑም ለመጠመቅ ወሰንኩ።”
16. ጥናቱ የጉባኤው ክፍል እንደሆነ እንዲሰማው ለመርዳት ሌላስ ምን ማድረግ እንችላለን?
16 ተማሪው እድገትና ለውጥ ማድረጉን ሲቀጥል የጉባኤው ክፍል እንደሆነ እንዲሰማው ልንረዳው ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ እንግዳ ተቀባይ መሆን ነው። (ዕብ. 13:2) በሞልዶቫ የሚያገለግለው ዴኒስ መጽሐፍ ቅዱስን ያጠና ስለነበረበት ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ወንድሞች እኔንና ባለቤቴን አብረናቸው ጊዜ እንድናሳልፍ ይጋብዙን ነበር። በሕይወታቸው የይሖዋን እጅ ስላዩበት መንገድ ያጫውቱን ነበር። ይህም በጣም አበረታቶናል። ከእነሱ ጋር በመጨዋወት ያሳለፍነው ጊዜ፣ ይሖዋን ለማገልገል እንድንወስንና እንዲህ ማድረጋችን ሕይወታችንን አስደሳች እንደሚያደርገው እርግጠኛ እንድንሆን ረድቶናል።” ጥናቱ አስፋፊ ከሆነ በኋላ ደግሞ አብሮን እንዲያገለግል ልንጋብዘው እንችላለን። በብራዚል የሚኖር ዲዬጎ የተባለ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወንድሞች አብሬያቸው እንዳገለግል ጋብዘውኛል። ይህም ከእነሱ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። ይበልጥ በተዋወቅኳቸው መጠን ከእነሱ ብዙ ትምህርት አገኘሁ። ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋርም ይበልጥ እንደተቀራረብኩ ተሰማኝ።”
ሽማግሌዎች ምን እርዳታ ማበርከት ይችላሉ?
17. ሽማግሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
17 ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ጊዜ ስጧቸው። ሽማግሌዎች ለጥናቶች ፍቅርና አሳቢነት ማሳየታችሁ እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ሊረዳቸው ይችላል። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ጋር ለመጨዋወት ጊዜ መመደብ ትችሉ ይሆን? ስማቸውን ማስታወሳችሁ ትኩረት እንደሰጣችኋቸው እንዲሰማቸው ያደርጋል፤
በተለይ በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ሲጀምሩ ስማቸውን ማስታወሳችሁ አስፈላጊ ነው። ፕሮግራማችሁን አስተካክላችሁ አስፋፊዎች ጥናት ሲመሩ አልፎ አልፎ አብራችኋቸው መሆን ትችላላችሁ? እንዲህ ስታደርጉ ከምታስቡት በላይ ጥናቱን መርዳት ትችሉ ይሆናል። በናይጄርያ የምትኖር ጃኪ የተባለች አቅኚ እንዲህ ብላለች፦ “ብዙ ጥናቶች አብሮኝ የመጣው ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ መሆኑን ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ። እንዲያውም አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲህ ብሎ ነበር፦ ‘የእኛ ፓስተር በፍጹም እንዲህ ሊያደርግ አይችልም። እሱ የሚጠይቀው ሀብታሞችን ብቻ ያውም ገንዘብ ከከፈሉት ነው!’” ይህ ጥናት አሁን በስብሰባዎች ላይ ይገኛል።18. ሽማግሌዎች በሐዋርያት ሥራ 20:28 ላይ የተሰጣቸውን ኃላፊነት መወጣት የሚችሉት እንዴት ነው?
18 አስጠኚዎችን አሠልጥኗቸው እንዲሁም አበረታቷቸው። ሽማግሌዎች፣ አስፋፊዎች በአገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት አለባችሁ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራትን ሥራ ይጨምራል። (የሐዋርያት ሥራ 20:28ን አንብብ።) አንድ አስፋፊ አንተ በተገኘህበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ካስፈራው ጥናቱን አንተ ልትመራ እንደምትችል ግለጽለት። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ጃኪ እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቼ አዘውትረው ይጠይቁኛል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከመምራት ጋር በተያያዘ የከበደኝ ነገር ካለ ጠቃሚ ምክር ይሰጡኛል።” ሽማግሌዎች አስጠኚዎችን ለማበረታታትና ተስፋ እንዳይቆርጡ ለመርዳት ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ። (1 ተሰ. 5:11) ጃኪ አክላ እንዲህ ብላለች፦ “ሽማግሌዎች ሲያበረታቱኝና የማደርገውን ጥረት እንደሚያደንቁ ሲገልጹልኝ በጣም ደስ ይለኛል። በሞቃታማ ቀን ቀዝቃዛ ውኃ መጠጣት እንደሚያረካ ሁሉ ሽማግሌዎች የሚሰጡኝ ማበረታቻም መንፈሴን ያድሰዋል። ሥራዬን የሚያደንቁ መሆኑ በራስ የመተማመን ስሜቴን ያሳድገዋል፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራቱ ሥራ ይበልጥ ደስታ እንዳገኝ ይረዳኛል።”—ምሳሌ 25:25
19. ሁላችንም በየትኛው አስደሳች ሥራ መካፈል እንችላለን?
19 በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይኖረንም እንኳ ጥናቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን። በጥናቱ ወቅት፣ በደንብ የታሰበባቸው ሐሳቦች በመስጠት አስጠኚውን ማገዝ እንችላለን፤ እርግጥ ብዙ እንዳናወራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጥናቶች ወደ ስብሰባ ሲመጡ ጓደኛ ልናደርጋቸው እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ ልንሆንላቸው እንችላለን። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ለጥናቶች ጊዜ በመስጠት ሊያበረታቷቸው ይችላሉ፤ ለአስጠኚዎች ደግሞ ሥልጠናና ማበረታቻ መስጠት ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው አባታችንን ይሖዋን እንዲወድና እንዲያገለግል አነስተኛም ቢሆን አስተዋጽኦ ከማበርከት ይበልጥ የሚያስደስት ምን ነገር ይኖራል!
መዝሙር 79 ጸንተው እንዲቆሙ አስተምሯቸው
^ አን.5 አንዳንዶቻችን በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የለንም። ሆኖም ሁላችንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ መርዳት እንችላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት እያንዳንዳችን ምን አስተዋጽኦ ማበርከት እንደምንችል በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን።