በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

ክርስቲያኖች መልእክት መላላኪያ አፕሊኬሽኖችን ሲጠቀሙ ጥንቃቄ ማድረግ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?

አንዳንድ ክርስቲያኖች ከቤተሰቦቻቸውና ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር ለመገናኘት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ይጠቀማሉ። እርግጥ ነው፣ ጎልማሳ የሆኑ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ተግባራዊ ያደርጋሉ፦ “ብልህ ሰው አደጋ አይቶ ይሸሸጋል፤ ተሞክሮ የሌለው ሰው ግን ዝም ብሎ ይሄዳል፤ መዘዙንም ይቀበላል።”—ምሳሌ 27:12

ይሖዋ ከአደጋ ሊጠብቀን እንደሚፈልግ እንገነዘባለን። በመሆኑም ክፍፍል ከሚፈጥሩ፣ ከጉባኤ ከተወገዱ ወይም ጠማማ ትምህርት ከሚያስፋፉ ሰዎች ጋር አንቀራረብም። (ሮም 16:17፤ 1 ቆሮ. 5:11፤ 2 ዮሐ. 10, 11) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንዶች ጥሩ ምግባር ላይኖራቸው ይችላል። (2 ጢሞ. 2:20, 21) ጓደኝነት ስንመሠርት ይህን በአእምሯችን እንይዛለን። መልእክት መለዋወጫ አፕሊኬሽኖችን ስንጠቀም ግን ጥሩ ጓደኞች መምረጥ ቀላል ላይሆን ይችላል።

በተለይ ብዙ አባላት ባሉት የቻት ቡድን ውስጥ ለመግባት እያሰብን ከሆነ ጓደኛ የምንሆነው ከማን ጋር እንደሆነ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል። ትላልቅ የቻት ቡድኖች ውስጥ የገቡ አንዳንድ ክርስቲያኖች ጉዳት ደርሶባቸዋል። አንድ ክርስቲያን በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ያሉት ቡድን ውስጥ ከገባ በጓደኛ ምርጫ ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ እንዴት ይችላል? የእያንዳንዱን አባል እውነተኛ ማንነትና መንፈሳዊ አቋም ማወቅ አይቻልም። መዝሙር 26:4 ምን እንደሚል ልብ በል፦ “አታላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር አልቀራረብም፤ ማንነታቸውን ከሚደብቁም እርቃለሁ።” ታዲያ ከዚህ ጥቅስ አንጻር መልእክት መለዋወጫ አፕሊኬሽኖችን ከምናውቃቸው ሰዎች ጋር ብቻ ለመገናኘት መጠቀማችን ጥበብ አይሆንም?

ቡድኑ ትልቅ ባይሆንም እንኳ አንድ ክርስቲያን ጊዜውና የውይይቱ ርዕሰ ጉዳይ ሊያሳስበው ይገባል። የወሬውን ይዘትና የሚፈጀውን ጊዜ ግምት ውስጥ ሳያስገባ በሁሉም ውይይቶች መሳተፍ እንዳለበት ሊሰማው አይገባም። ጳውሎስ አንዳንዶች “ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ” እንደሆኑ ለጢሞቴዎስ ነግሮታል። (1 ጢሞ. 5:13) ዛሬም ቢሆን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች ተጠቅመው እንዲህ የሚያደርጉ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ።

አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ስለ እምነት ባልንጀሮቹ ነቀፋ ያዘለ ነገር አይናገርም ወይም ሚስጥራቸውን አያወጣም፤ እንዲህ ያለውን ወሬ ለማዳመጥም ቢሆን ፈቃደኛ አይሆንም። (መዝ. 15:3፤ ምሳሌ 20:19) በተጨማሪም የተጋነኑ ወይም ያልተረጋገጡ ወሬዎችን ከመስማትም ሆነ ከማሰራጨት ይቆጠባል። (ኤፌ. 4:25) በ⁠jw.org እንዲሁም JW ብሮድካስቲንግ ላይ በሚወጡት ወርሃዊ ፕሮግራሞች አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ብሎም አስተማማኝ የሆነ ወቅታዊ መረጃ እናገኛለን።

አንዳንድ ክርስቲያኖች ምርቶችን ለመሸጥ፣ ለመግዛት ወይም ለማስተዋወቅ አሊያም የሥራ ማስታወቂያዎችን ለማውጣት በመልእክት መለዋወጫ አፕሊኬሽኖች ይጠቀማሉ። እነዚህ ከመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው የንግድ ጉዳዮች ናቸው። “ከገንዘብ ፍቅር ነፃ” መሆን የሚፈልጉ ክርስቲያኖች የወንድማማች ማኅበራችንን የንግድ ጥቅማቸውን ለማራመድ ሊጠቀሙበት አይገባም።—ዕብ. 13:5

ለተቸገሩ ወይም በአደጋ ለተጎዱ ወንድሞቻችን እርዳታ ለማሰባሰብ በመልእክት መለዋወጫ አፕሊኬሽኖች መጠቀምስ ተገቢ ነው? ወንድሞቻችንን ስለምንወዳቸውና ስለምናስብላቸው እነሱን መደገፍና ማበረታታት እንፈልጋለን። (ያዕ. 2:15, 16) ይሁንና በትላልቅ የቻት ቡድኖች አማካኝነት እንዲህ ለማድረግ መሞከር ቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ጉባኤው የሚያደርገውን የተሻለ ዝግጅት ሊያስተጓጉል ይችላል። (1 ጢሞ. 5:3, 4, 9, 10, 16) ደግሞም ማናችንም ብንሆን የአምላክን በጎች የመንከባከብ ልዩ ኃላፊነት እንደተሰጠን አድርገን እንደምናስብ የሚያስመስል ነገር ማድረግ አንፈልግም።

የምናደርገው ነገር ሁሉ ለአምላክ ክብር የሚያመጣ እንዲሆን እንፈልጋለን። (1 ቆሮ. 10:31) በመሆኑም አንድን የመልእክት መለዋወጫ አፕሊኬሽን በምንጠቀምበት ጊዜ አደጋዎቹን ከግምት ማስገባትና ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል።