በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል!

የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል!

“ሕዝቡም ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ይሖዋን አወድሱ!”—መሳ. 5:2

መዝሙሮች፦ 84, 75

1, 2. (ሀ) ኤሊፋዝና በልዳዶስ፣ አምላክ ስለምናቀርበው አገልግሎት ምን እንደሚሰማው ተናግረዋል? (ለ) ይሖዋ አመለካከቱን ግልጽ ያደረገው እንዴት ነው?

“ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል? ማስተዋል ያለውስ ሰው ምን ይፈይድለታል? ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ አንተ ጻድቅ መሆንህ ግድ ይሰጠዋል? ወይስ በንጹሕ አቋም መመላለስህ እሱን ይጠቅመዋል?” (ኢዮብ 22:1-3) እንደ እነዚህ ያሉ ጥያቄዎች ወደ አእምሮህ መጥተው ያውቃሉ? ቴማናዊው ኤሊፋዝ፣ ኢዮብን እንዲህ ብሎ ሲጠይቀው መልሱ ‘በጭራሽ’ የሚል እንደሚሆን ተማምኖ ነበር። ወዳጁ የሆነው ሹሃዊው በልዳዶስ ደግሞ ሰው በአምላክ ፊት ጻድቅ መሆን እንደማይችል ተናግሯል።ኢዮብ 25:4ን አንብብ።

2 እነዚህ የሐሰት አጽናኞች ይሖዋን በታማኝነት ለማገልገል የምናደርገው ጥረት እሱን ምንም እንደማይጠቅመው እንዲሁም አምላክ ከብል፣ ከእጭ ወይም ከትል አስበልጦ እንደማይመለከተን ለማሳመን እየሞከሩ ነበር። (ኢዮብ 4:19፤ 25:6) የኤሊፋዝና የበልዳዶስ ሐሳብ ላይ ላዩን ሲታይ ትሕትናን የሚያንጸባርቅ ሊመስል ይችላል። (ኢዮብ 22:29) ለነገሩ ከተራራ ጫፍ ወይም ከአውሮፕላን ላይ ሆኖ ወደ ታች ለሚመለከታቸው የሰው ልጆች ዓይን ውስጥ እንኳ አይገቡም። ይሁንና ይሖዋ ከፍ ካለው መኖሪያው ሆኖ የሰው ልጆች የመንግሥቱን ሥራ ለመደገፍ ምድር ላይ ሆነው የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ ሲመለከት ሥራችን ከቁጥር የማይገባ እንደሆነ ይሰማዋል? በፍጹም! ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተሳሳተ ነገር ስለተናገሩ ይሖዋ እርማት የሰጣቸው መሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለውን አመለካከት ግልጽ ያደርገዋል፤ ኢዮብን ግን “አገልጋዬ” ብሎ በመጥራት በእሱ እንደሚደሰት አሳይቷል። (ኢዮብ 42:7, 8) በእርግጥም “ሰው አምላክን ሊጠቅመው ይችላል።”

“ለእሱ ምን ትጨምርለታለህ?”

3. ኤሊሁ ይሖዋን ለማገልገል ስለምናደርገው ጥረት ምን ብሏል? ይህን ሲል ምን ማለቱ ነበር?

3 ኤሊሁ “ጻድቅ ብትሆን ለእሱ [ለአምላክ] ምን ትጨምርለታለህ? ከአንተ እጅ ምን ይቀበላል?” ብሏል፤ በእርግጥ ይህን በማለቱ ይሖዋ አልገሠጸውም። (ኢዮብ 35:7) ኤሊሁ ይህን ሲል አምላክን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት ዋጋ የለውም ማለቱ ነበር? በፍጹም። ኤሊሁ፣ ይሖዋ እኛ ባናመልከውም ምንም የሚጎድልበት ነገር እንደሌለ መግለጹ ነው። ይሖዋ በራሱ ምሉዕ ነው። እኛ የምናደርገው ማንኛውም ነገር ለይሖዋ ብልጽግና ወይም ኃይል ሊጨምርለት አይችልም። እንዲያውም ያለንን ማንኛውም መልካም ባሕርይ፣ ተሰጥኦ ወይም ችሎታ ያገኘነው ከይሖዋ ነው፤ እሱም ይህን እንዴት እንደምንጠቀምበት በትኩረት ይመለከታል።

4. ይሖዋ ለሌሎች የምናሳየውን ደግነት እንዴት ይመለከተዋል?

4 ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ታማኝ ፍቅር ስናሳይ ይህን ለእሱ እንዳደረግንለት ይቆጥረዋል። ምሳሌ 19:17 “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል” ይላል። ይህ ጥቅስ ይሖዋ ለችግረኛ ሰው የሚደረግን ማንኛውንም የደግነት ተግባር እንደሚመለከት የሚያሳይ ነው? የአጽናፈ ዓለም ፈጣሪ ደግነት ለሚያሳዩ ሰዎች ባለዕዳ እንደሆነ ይሰማዋል ማለት ነው? ደግሞስ እንዲህ ያለውን ልግስና የሚያደርጉ ሰዎችን ለእሱ እንዳበደሩት በመቁጠር ሞገሱንና በረከቱን ይሰጣቸዋል ብለን መደምደም እንችላለን? አዎ፣ የአምላክ ልጅ ራሱ ይህንን አረጋግጦልናል።ሉቃስ 14:13, 14ን አንብብ።

5. ቀጥሎ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመረምራለን?

5 ይሖዋ፣ እሱን ወክሎ እንዲናገር ነቢዩ ኢሳይያስን ጋብዞት ነበር፤ ይህም ታማኝ የሆኑ የሰው ልጆች ዓላማውን ዳር በማድረስ ረገድ የራሳቸውን ሚና እንዲጫወቱ እንደሚፈልግ ያሳያል። (ኢሳ. 6:8-10) ኢሳይያስ የቀረበለትን ግብዣ በደስታ ተቀብሏል። በዛሬው ጊዜም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ ተፈታታኝ የሆኑ ምድቦችን በመቀበል ልክ እንደ ኢሳይያስ “እነሆኝ! እኔን ላከኝ!” ብለዋል። ያም ሆኖ አንዳንዶች የሚከተሉት ጥያቄዎች ይፈጠሩባቸው ይሆናል፦ ‘እኔ በግለሰብ ደረጃ የማደርገው ጥረት ያን ያህል ዋጋ አለው? ይሖዋ በዚህ ሥራ በፈቃደኝነት እንድካፈል ግብዣ ማቅረቡ ታላቅ ደግነት እንደሆነ ግልጽ ነው፤ ይሁን እንጂ እኔ በአገልግሎቱ የማደርገው ተሳትፎ ምንም ያህል ቢሆን እሱ ዓላማውን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ነገር ማድረጉ ይቀራል?’ በዲቦራና በባርቅ ዘመን የተፈጸመው ሁኔታ ለእነዚህ ጥያቄዎች እንዴት መልስ እንደሚሰጠን እስቲ እንመልከት።

በፍርሃት ቢርድም አምላክ አበርትቶታል

6. በእስራኤል መንደሮች በሚኖሩት ሰዎችና በያቢን ሠራዊት መካከል የነበረውን ልዩነት ግለጽ።

6 የከነአን ንጉሥ ያቢን እስራኤላውያንን ለ20 ዓመት ‘ክፉኛ ጨቁኗቸው’ ነበር። በእስራኤል መንደሮች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በአደባባይ መታየት እንኳ ይፈሩ ነበር። ከወታደራዊ ስልት አንጻር ሲታይ፣ እስራኤላውያን በጠላቶቻቸው ላይ ጥቃት ለመሰንዘርም ሆነ ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችል የጦር መሣሪያ አልነበራቸውም፤ በሌላ በኩል ግን ጠላቶቻቸው የብረት ማጭድ የተገጠመላቸው 900 የጦር ሠረገሎች ነበሯቸው።—መሳ. 4:1-3, 13፤ 5:6-8 *

7, 8. (ሀ) ይሖዋ ለባርቅ የሰጠው የመጀመሪያው ትእዛዝ ምንድን ነው? (ለ) እስራኤላውያን የያቢንን ሠራዊት ድል ያደረጉት እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

7 ያም ቢሆን ይሖዋ በነቢዪቱ ዲቦራ በኩል ለባርቅ የሚከተለውን ግልጽ መመሪያ ሰጠው፦ “ሂድና ወደ ታቦር ተራራ ዝመት፤ ከአንተም ጋር ከንፍታሌምና ከዛብሎን 10,000 ወንዶችን ውሰድ። እኔም የያቢን ሠራዊት አለቃ የሆነውን ሲሳራን ከጦር ሠረገሎቹና ከሠራዊቱ ጋር ወደ ቂሾን ጅረት ወደ አንተ አመጣዋለሁ፤ እሱንም በእጅህ አሳልፌ እሰጥሃለሁ።”—መሳ. 4:4-7

8 በፈቃደኝነት የሚዘምቱ ተዋጊዎች እንደሚያስፈልጉ በአካባቢው ሁሉ ተሰማ። በመሆኑም ፈቃደኛ የሆኑ ተዋጊዎች በታቦር ተራራ ላይ ተሰበሰቡ። ባርቅ ምንም ጊዜ ሳያጠፋ የይሖዋን መመሪያ በሥራ ላይ አዋለ። (መሳፍንት 4:14-16ን አንብብ።) በታአናክ በተካሄደው በዋናው ውጊያ ላይ ድንገት የጣለው ዶፍ ዝናብ አካባቢውን አጨቅይቶት ነበር። በውጊያው ላይ ባርቅ የሲሳራን ሠራዊት 24 ኪሎ ሜትር ርቃ እስከምትገኘው እስከ ሃሮሼትጎይም ድረስ አሳደደ። በዚህ መሃል የሲሳራ ሠረገላ በጭቃ ተያዘ፤ በመሆኑም ሲሳራ፣ በአንድ ወቅት አስፈሪ ከነበረው አሁን ግን ምንም ጥቅም ከሌለው ሠረገላው ላይ ወርዶ ወደ ጻናኒም በእግሩ ሸሸ። ከዚያም ከአሳዳጆቹ ለመደበቅ ሲል የቄናዊው የሄቤር ሚስት ወደሆነችው ወደ ኢያዔል ድንኳን ሄደ፤ ኢያዔልም ሲሳራን ተቀበለችው። ሲሳራ ውጊያው ስላደከመው ድብን ያለ እንቅልፍ ወሰደው። በመሆኑም ኢያዔል እሱን ለመግደል ከወሰደችው ድፍረት የተሞላበት ወሳኝ እርምጃ ራሱን ማዳን አልቻለም። (መሳ. 4:17-21) በዚህ መንገድ እስራኤላውያን ጠላቶቻቸውን ድል አደረጉ! *

የፈቃደኝነት መንፈስ—ሁለት ተቃራኒ አመለካከቶች

9. መሳፍንት 5:20, 21 ከሲሳራ ጋር ስለተደረገው ውጊያ ምን ዝርዝር ሐሳቦች ይዟል?

9 መሳፍንት ምዕራፍ 4 እና 5⁠ን አንድ ላይ መመርመሩ ጠቃሚ ነው፤ ምክንያቱም በአንዱ ምዕራፍ ውስጥ የማይገኘው ዝርዝር ሐሳብ በሌላው ምዕራፍ ውስጥ ይገኛል። ለምሳሌ መሳፍንት 5:20, 21 እንዲህ ይላል፦ “ከዋክብት ከሰማይ ተዋጉ፤ በምሕዋራቸው ላይ ሆነው ከሲሳራ ጋር ተዋጉ። . . . የቂሾን ወንዝ ጠራርጎ ወሰዳቸው።” ይህ ጥቅስ የሚናገረው መላእክት ለእስራኤላውያን ስላደረጉት እርዳታ ነው? ወይስ ከጠፈር ስለመጡ ተወርዋሪ ኮከቦች? ዘገባው በግልጽ አይናገርም። ይሁንና እንዲህ ያለ ከባድ ዝናብ ውጊያው በተካሄደበት ጊዜና ቦታ ላይ እንዲጥል ብሎም 900 የጦር ሠረገሎች በጭቃ ማጥ እንዲያዙ ያደረገው ከመለኮታዊ ኃይል ውጪ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? በመሳፍንት 4:14, 15 ላይ ያለው ሐሳብ ለድሉ ሊመሰገን የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ ሦስት ጊዜ ይጠቅሳል። ፈቃደኛ ሆነው በውጊያው ከተካፈሉት 10,000 እስራኤላውያን መካከል ማናቸውም ቢሆን ድሉን እንዳስገኙ መናገር አይችሉም።

10, 11. “መሮዝ” ምንድን ናት? የተረገመችውስ ለምንድን ነው?

10 ዲቦራና ባርቅ፣ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ድል እንዲቀዳጁ ስለረዳቸው ይሖዋን ለማወደስ በዘመሩት የድል መዝሙር ላይ የሚከተለውን ሐሳብ መጥቀሳቸው ትኩረት የሚስብ ነው፦ “የይሖዋ መልአክ እንዲህ አለ፦ ‘መሮዝን እርገሙ፤ ነዋሪዎቿንም እርገሙ፣ ይሖዋን ለመርዳት አልመጡምና፣ ይሖዋን ለመርዳት ከኃያላኑ ጋር አልመጡም።’”—መሳ. 5:23

11 እዚህ ላይ የተጠቀሰችው መሮዝ ምንድን ናት? በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። ምክንያቱም በመሮዝ ላይ የተነገረው እርግማን በመፈጸሙ ሙሉ በሙሉ ሳትጠፋ አልቀረችም። መሮዝ፣ ፈቃደኛ የሆኑ ተዋጊዎች እንዲሰባሰቡ መጀመሪያ ላይ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ያልሰጡ ነዋሪዎች ያሉባት ከተማ ትሆን? ሲሳራ በሸሸበት መንገድ ላይ ያለች ከተማ ከሆነች ደግሞ ነዋሪዎቿ እሱን ለመያዝ አጋጣሚ ቢያገኙም ይህን ሳያደርጉ ቀርተው ይሆን? ይሖዋ ፈቃደኛ ተዋጊዎች እንዲሰባሰቡ ያቀረበውን ጥሪ እንዴት ላይሰሙ ይችላሉ? በአካባቢያቸው የነበሩ አሥር ሺህ ሰዎች ለዚህ ውጊያ ተሰባስበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የመሮዝ ነዋሪዎች በጭንቀት ተውጦ ብቻውን የሚሸሸው ይህ ክፉ የጦር መሪ በመሮዝ ጎዳናዎች ላይ በሚሮጥበት ጊዜ በዝምታ ሲመለከቱት ይታይህ። የመሮዝ ሰዎች የይሖዋን ዓላማ ለመደገፍና የእሱን በረከት ለማግኘት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ተከፍቶላቸው ነበር። ይሁን እንጂ እርምጃ የመውሰድ አሊያም ምንም ሳያደርጉ እጃቸውን አጣጥፎ የመቀመጥ ምርጫ በተደቀነባቸው በዚያ ወሳኝ ወቅት ቸልተኛ በመሆን ምንም ሳያደርጉ ቀርተው ይሆን? የመሮዝ ነዋሪዎች ያደረጉት ነገር በቀጣዮቹ ቁጥሮች ላይ ከተገለጸውና ኢያዔል ከወሰደችው የድፍረት እርምጃ ምንኛ የተለየ ነው!—መሳ. 5:24-27

12. መሳፍንት 5:9, 10 ሕዝቡ ስለነበረው የተለያየ አመለካከት የሚገልጸው እንዴት ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

12 በመሳፍንት 5:9, 10 ላይ ከባርቅ ጋር በዘመቱትና ይህን ባላደረጉት መካከል የነበረውን የአመለካከት ልዩነት የሚያሳይ ተጨማሪ ሐሳብ እናገኛለን። ዲቦራና ባርቅ ‘ከሕዝቡ ጋር በፈቃደኝነት የወጡትን የእስራኤል አዛዦች’ አመስግነዋል። እነዚህ አዛዦች የነበራቸው አመለካከት፣ ኩሩ ከመሆናቸው የተነሳ በውጊያው ሳይሳተፉ ከቀሩት “ነጣ ባሉ ቡናማ አህዮች [የሚጋልቡ]” ሰዎች እንዲሁም ‘ባማሩ ምንጣፎች ላይ ከሚቀመጡት’ ማለትም የቅንጦት ኑሮ ከሚወዱት ሰዎች ምንኛ የተለየ ነው! አስቸጋሪ ያልሆነውን አማራጭ በመውሰድ ‘በመንገድ ላይ ከሚሄዱት’ ሰዎች በተቃራኒ፣ ከባርቅ ጋር የዘመቱት ተዋጊዎች ድንጋያማ በሆነው የታቦር ተራራና በረግረግ በተሞላው የቂሾን ሸለቆ ውስጥ በተካሄደው ውጊያ ላይ ለመካፈል ፈቃደኞች ነበሩ! የተደላደለ ሕይወት ለሚወዱት ሁሉ “ልብ በሉ!” የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። እነዚህ ሰዎች በይሖዋ ሥራ የመካፈል አጋጣሚ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት አልፏቸዋል፤ ይህን ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል። በዛሬው ጊዜም አምላክን በሙሉ ልባቸው ከማገልገል ወደኋላ የሚሉ ሁሉ ይህን ማስጠንቀቂያ ልብ ሊሉት ይገባል።

13. የሮቤል፣ የዳንና የአሴር ነገዶች የነበራቸው አመለካከት ከዛብሎንና ከንፍታሌም የሚለየው እንዴት ነው?

13 ራሳቸውን በፈቃደኝነት ያቀረቡት ሰዎች ይሖዋ ሉዓላዊ ገዢ መሆኑን እንዴት እንዳሳየ በገዛ ዓይናቸው መመልከት ችለዋል። በመሆኑም “የይሖዋን የጽድቅ ሥራዎች” በሚተርኩበት ወቅት የሚጠቅሱት ነገር አላቸው። (መሳ. 5:11) በሌላ በኩል ግን በመሳፍንት 5:15-17 ላይ እንደተገለጸው የሮቤል፣ የዳንና የአሴር ነገዶች በይሖዋ ሥራ ከመካፈል ይልቅ ለቁሳዊ ነገሮች ይኸውም ለመንጎቻቸው፣ ለመርከቦቻቸውና ለወደቦቻቸው ቅድሚያ ሰጥተው ነበር። ከዚህ በተቃራኒ የዛብሎንና የንፍታሌም ነገዶች ‘እስከ ሞት ድረስ ሕይወታቸውን ለአደጋ በማጋለጥ’ ዲቦራና ባርቅን ረድተዋል። (መሳ. 5:18) በፈቃደኝነት ከሚቀርብ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሕዝቡ ከነበረው የተለያየ አመለካከት ትልቅ ትምህርት ማግኘት እንችላለን።

“ይሖዋን አወድሱ!”

14. በዛሬው ጊዜ የይሖዋን ሉዓላዊነት እንደምንደግፍ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 በዛሬው ጊዜ በጦርነት እንድንካፈል ጥሪ አልቀረበልንም፤ ይሁንና በስብከቱ ሥራ በቅንዓት በመካፈል ድፍረት የማሳየት አጋጣሚ ተሰጥቶናል። በአሁኑ ወቅት በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ራሳቸውን በፈቃደኝነት የሚያቀርቡ ሰዎች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ይፈለጋሉ። በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንድሞችና እህቶች በተለያዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መስኮች ለመካፈል ለምሳሌ አቅኚ፣ ቤቴላዊ ወይም የመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ለማገልገል ራሳቸውን እያቀረቡ ነው፤ በተጨማሪም ወጣት አዋቂ ሳይል በርካታ ክርስቲያኖች በትላልቅ ስብሰባዎች ላይ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ያገለግላሉ። በሌላ በኩል ደግሞ ከሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች እና ትላልቅ ስብሰባዎችን ከማደራጀት ጋር የተያያዙ ከባድ ኃላፊነቶችን የሚወጡ ሽማግሌዎችም አሉ። ሁላችንም ይሖዋ የምናሳየውን የፈቃደኝነት መንፈስ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተውና ፈጽሞ እንደማይረሳው እርግጠኛ መሆን እንችላለን።—ዕብ. 6:10

አንድ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ውሳኔህ በቤተሰብህና በጉባኤህ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ አስብ (አንቀጽ 15⁠ን ተመልከት)

15. ለይሖዋ ሥራ ቸልተኛ የመሆን ዝንባሌ ይኖረን እንደሆነ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?

15 እያንዳንዳችን ራሳችንን እንደሚከተለው ብለን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከባድ የሆነውን ሥራ ሌሎች እንዲሠሩት ለእነሱ እተወዋለሁ? ለቁሳዊ ነገሮች ከሚገባው በላይ ትኩረት መስጠቴ የፈቃደኝነት መንፈስ እንዳላሳይ እንቅፋት እየሆነብኝ ነው? ያለኝን ነገር ሁሉ የይሖዋን ግልጽ ትእዛዝ ለመፈጸም በማዋል እንደ ባርቅ፣ ዲቦራ፣ ኢያዔልና ራሳቸውን በፈቃደኝነት እንዳቀረቡት 10,000 ሰዎች እምነትና ድፍረት እንዳለኝ አሳያለሁ? የተሻለ ኑሮ ለማግኘት ስል ወደ ሌላ ከተማ ወይም አገር ለመዛወር እያቀድኩ ከሆነ፣ ይህ በቤተሰቤና በጉባኤዬ ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ በጸሎት አስቤበታለሁ?’ *

16. ይሖዋ ሁሉ ነገር ያለው ቢሆንም እኛ ልንሰጠው የምንችለው ምን ነገር አለ?

16 ይሖዋ ሉዓላዊነቱን በመደገፍ ረገድ የራሳችንን አስተዋጽኦ እንድናበረክት በመፍቀድ እንደሚያከብረን አሳይቷል። ዲያብሎስ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት በማታለል የይሖዋን ሉዓላዊነት እንዲቃወሙና እሱን እንዲደግፉ አድርጓል፤ እኛ ግን የይሖዋን አገዛዝ ስንደግፍ ከማን ጎን እንደቆምን ሰይጣን በግልጽ እንዲያይ እናደርጋለን። እምነትና ታማኝነት ለይሖዋ አገልግሎት ራስህን በፈቃደኝነት እንድታቀርብ ያነሳሳሃል፤ ይህን ማድረግህ ደግሞ ይሖዋን ያስደስተዋል። (ምሳሌ 23:15, 16) ከይሖዋ ጎን ከቆምክ አምላክ እሱን ለሚነቅፈው ለሰይጣን መልስ መስጠት ይችላል። (ምሳሌ 27:11) በመሆኑም ይሖዋን በታማኝነት ስትታዘዘው እሱ ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር እየሰጠኸው ነው ሊባል ይችላል፤ እሱም በዚህ በጣም ይደሰታል።

17. መሳፍንት 5:31 ስለ ወደፊቱ ጊዜ ምን ይጠቁመናል?

17 በቅርቡ ምድር ከማንኛውም አገዛዝ በላይ የይሖዋን ሉዓላዊነት በሚደግፉ ሰዎች ትሞላለች። ያን ቀን በጉጉት እንጠባበቃለን! ልክ እንደ ዲቦራና ባርቅ እኛም “ይሖዋ ሆይ፣ ጠላቶችህ ሁሉ ይጥፉ፣ አንተን የሚወዱ ግን ደምቃ እንደምትወጣ ፀሐይ ይሁኑ” ብለን እንዘምራለን። (መሳ. 5:31) ይሖዋ የሰይጣንን ክፉ ዓለም ሲያጠፋ ይህ ልመናችን ምላሽ ያገኛል! የአርማጌዶን ጦርነት በሚጀምርበት ወቅት ከሰው ልጆች መካከል ጠላትን ድል የሚያደርጉ ፈቃደኛ ተዋጊዎች አያስፈልጉም። በዚያ ወቅት “ዝም ብላችሁ ቁሙ፤ ይሖዋ . . . የሚወስደውን የማዳን እርምጃ ተመልከቱ” የሚለውን መመሪያ ከመታዘዝ ሌላ የሚጠበቅብን ነገር አይኖርም። (2 ዜና 20:17) እስከዚያው ድረስ ግን የይሖዋን ዓላማ በድፍረትና በቅንዓት ለመደገፍ የሚያስችሉን ብዙ አጋጣሚዎች አሉ።

18. የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ሌሎችን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

18 ዲቦራና ባርቅ የድል መዝሙራቸውን የጀመሩት ለሰው ሳይሆን ለይሖዋ ውዳሴ በማቅረብ ነበር። “ሕዝቡም ፈቃደኛ ስለሆነ፣ ይሖዋን አወድሱ!” በማለት ዘምረዋል። (መሳ. 5:1, 2) ዛሬም የምታሳዩት የፈቃደኝነት መንፈስ ሌሎችም ‘ይሖዋን እንዲያወድሱ’ የሚያነሳሳ ይሁን!

^ አን.6 እዚህ ላይ የተጠቀሰው ማጭድ፣ ረጅምና ስለታማ ሲሆን ማጭዱ የተገጠመው የሠረገላዎቹ መንኮራኩር ላይ ነው። እንዲህ ወዳለው አስፈሪ የሆነ የጦር መሣሪያ ለመጠጋት ማንም እንደማይደፍር ግልጽ ነው።

^ አን.8 ቀልብ ስለሚስበው ስለዚህ ዘገባ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት “እኔ በእስራኤል እናት ሆኜ እስክነሳየነሐሴ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 12-15 ተመልከት።

^ አን.15 በሐምሌ 1, 2015 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ስለ ገንዘብ መጨነቅ” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።