በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎች የሚሠሩት ስህተት እንቅፋት አይሁንብህ

ሌሎች የሚሠሩት ስህተት እንቅፋት አይሁንብህ

“እርስ በርስ . . . በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።” —ቆላ. 3:13

መዝሙሮች፦ 121, 75

1, 2. መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር እንደሚጨምር የሚገልጽ ምን ትንቢት ይዟል?

በምድር ላይ ያሉ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮችን ወይም ምሥክሮቹን ያቀፈ አንድ ልዩ ድርጅት አለ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ሰዎች ፍጽምና የጎደላቸው በመሆናቸው ስህተት ይሠራሉ። ያም ሆኖ አምላክ፣ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ዓለም አቀፉን ጉባኤ በመባረክ እያደገና እየተጠናከረ እንዲሄድ አድርጓል። ይሖዋ፣ ፍጹማን ባልሆኑ ፈቃደኛ ሕዝቦቹ በመጠቀም እያከናወናቸው ያሉትን አንዳንድ አስደናቂ ነገሮች እስቲ እንመልከት።

2 የዚህ ሥርዓት የመጨረሻ ቀናት በ1914 ሲጀምሩ በምድር ላይ የነበሩት የአምላክ አገልጋዮች በአንጻራዊ ሁኔታ ትንሽ ነበሩ። ይሁንና ይሖዋ የስብከቱን ሥራቸውን ባርኮታል። በቀጣዮቹ አሥርተ ዓመታት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ተምረው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል። ይሖዋ ይህን አስደናቂ እድገት በተመለከተ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሮ ነበር፦ “ጥቂት የሆነው ሺህ፣ ትንሽ የሆነውም ኃያል ብሔር ይሆናል። እኔ ይሖዋ፣ ይህን በራሱ ጊዜ አፋጥነዋለሁ።” (ኢሳ. 60:22) ይህ ትንቢት በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ፍጻሜውን እንዳገኘ በግልጽ ማየት ይቻላል። የይሖዋ ሕዝቦች እንደ አንድ ታላቅ ብሔር ሆነዋል፤ እንዲያውም በአሁኑ ወቅት፣ በምድር ላይ ካሉት የአምላክ ሕዝቦች አጠቃላይ ቁጥር ያነሰ የሕዝብ ብዛት ያላቸው በርካታ አገራት አሉ።

3. የአምላክ አገልጋዮች ፍቅር ያሳዩት እንዴት ነው?

3 በተጨማሪም ይሖዋ፣ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ሕዝቡ የእሱ ዋነኛ ባሕርይ የሆነውን ፍቅርን ይበልጥ እንዲያንጸባርቁ ረድቷቸዋል። (1 ዮሐ. 4:8) የአባቱን ፍቅር በማንጸባረቅ ረገድ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ . . . እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐ. 13:34, 35) ብሔራት ዘግናኝ ጦርነቶችን ባካሄዱበት በዚህ ዘመን፣ የይሖዋ አገልጋዮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅር ማሳየታቸው በጣም አስፈላጊ ነበር። ለምሳሌ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ብቻ 55 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች አልቀዋል። የይሖዋ ምሥክሮች ግን በዚህ ዓለም አቀፋዊ ጦርነት አልተካፈሉም። (ሚክያስ 4:1, 3ን አንብብ።) በመሆኑም “ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ” መሆን ችለዋል።—ሥራ 20:26

4. የይሖዋ ሕዝቦች እድገት አስገራሚ የሆነው ለምንድን ነው?

4 የአምላክ ሕዝቦች እንዲህ ያለ እድገት እያደረጉ ያሉት በጥላቻ በተሞላ ዓለም ውስጥ ነው፤ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይህ ዓለም “የዚህ ሥርዓት አምላክ” በሆነው በሰይጣን ቁጥጥር ሥር እንደሆነ ይናገራል። (2 ቆሮ. 4:4) ሰይጣን የዚህን ዓለም የፖለቲካ ድርጅቶችና የመገናኛ ብዙኃን ይቆጣጠራል። ምሥራቹ እንዳይሰበክ ማገድ ግን አይችልም። ይሁንና ሰይጣን የቀረው ጊዜ በጣም አጭር እንደሆነ ስለሚያውቅ ሰዎችን ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቁ ለማድረግ የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም።—ራእይ 12:12

ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜም እንኳ ታማኝ እንሆናለን?

5. አንዳንዶች አልፎ አልፎ ስሜታችንን ሊጎዱ የሚችሉት ለምንድን ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

5 የአምላክ አገልጋዮች፣ አምላክንና ሰዎችን መውደድ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ይማራሉ። ኢየሱስ የዚህን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ በማለት መልስ ሰጥቷል፦ “‘አምላክህን ይሖዋን በሙሉ ልብህ፣ በሙሉ ነፍስህና በሙሉ አእምሮህ ውደድ።’ ይህ ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ነው። ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል።” (ማቴ. 22:35-39) ይሁንና መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እንደሚያሳየው ሁላችንም ከአዳም ኃጢአት ስለወረስን ፍጽምና ይጎድለናል። (ሮም 5:12, 19ን አንብብ።) ስለሆነም አልፎ አልፎ አንዳንድ ወንድሞች ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ይናገሩ ወይም ያደርጉ ይሆናል። በዚህ ጊዜ ለይሖዋና ለሕዝቡ ያለን ፍቅር ሊፈተን ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ምን እናደርጋለን? በጥንት ዘመን የነበሩ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮችም እንኳ ሌሎችን የሚጎዳ ነገር የተናገሩበት ወይም ያደረጉበት ጊዜ ነበር፤ ስለ እነዚህ የአምላክ አገልጋዮች ከሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንደምንችል እስቲ እንመልከት።

በኤሊ ዘመን ብትኖር ኖሮ ኤሊ የልጆቹን ኃጢአት በቸልታ ሲያልፍ ምን ይሰማህ ነበር? (አንቀጽ 6ን ተመልከት)

6. ኤሊ ለልጆቹ ተግሣጽ አልሰጠም የተባለው ለምንድን ነው?

6 ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ ካህናቱ ኤሊ የይሖዋን ሕግ የማያከብሩ ሁለት ልጆች ነበሩት። መጽሐፍ ቅዱስ “የኤሊ ወንዶች ልጆች ምግባረ ብልሹ ነበሩ፤ ለይሖዋ አክብሮት አልነበራቸውም” ይላል። (1 ሳሙ. 2:12) ኤሊ እውነተኛውን አምልኮ በማራመድ ረገድ ትልቅ ቦታ የነበረው ቢሆንም ሁለቱ ልጆቹ ከባድ ኃጢአት ይፈጽሙ ነበር። ኤሊ ይህን ጉዳይ ስለሚያውቅ ተግሣጽ ሊሰጣቸው ይገባ ነበር፤ እሱ ግን ልል ነበር። በመሆኑም አምላክ ኤሊንም ሆነ ልጆቹን ቀጥቷቸዋል። (1 ሳሙ. 3:10-14) ውሎ አድሮ ዘሮቹም እንኳ ሊቀ ካህናት ሆነው የማገልገል መብት አጥተዋል። በኤሊ ዘመን ብትኖር ኖሮ ኤሊ የልጆቹን ኃጢአት በቸልታ ሲያልፍ ምን ይሰማህ ነበር? በዚህ ተሰናክለህ አምላክን ማገልገልህን ታቆም ነበር?

7. ዳዊት ምን ከባድ ኃጢአት ፈጽሟል? አምላክስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ምን አደረገ?

7 ይሖዋ ዳዊትን ይወደው የነበረ ሲሆን “እንደ ልቤ የሆነ” ሲል ጠርቶታል። (1 ሳሙ. 13:13, 14፤ ሥራ 13:22) ሆኖም ዳዊት ከጊዜ በኋላ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር በመፈጸሙ ቤርሳቤህ አረገዘች። በዚህ ጊዜ ባለቤቷ ኦርዮ ከሠራዊቱ ጎን ተሰልፎ በውጊያ ላይ ነበር። ዳዊት፣ ኦርዮ ለተወሰነ ጊዜ ወደ ቤት በተመለሰበት ወቅት ከቤርሳቤህ ጋር እንዲተኛ ለማድረግ ሞከረ፤ ይህን ያደረገው ቤርሳቤህ የፀነሰችው ከኦርዮ እንደሆነ ተደርጎ እንዲታሰብ ብሎ ነው። ኦርዮ ግን ከቤርሳቤህ ጋር አላደረም፤ በመሆኑም ዳዊት፣ ኦርዮ በጦርነቱ እንዲገደል መመሪያ አስተላለፈ። ዳዊት በፈጸመው ወንጀል ምክንያት ከባድ ቅጣት ደርሶበታል፤ በራሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ መከራ አምጥቷል። (2 ሳሙ. 12:9-12) ይሁን እንጂ በጥቅሉ ሲታይ ዳዊት በአምላክ ፊት “በንጹሕ ልብና በቅንነት” ስለተመላለሰ ይሖዋ ምሕረት አድርጎለታል። (1 ነገ. 9:4) በዚያ ዘመን የምትኖር የአምላክ አገልጋይ ብትሆን ኖሮ ይህን ሁኔታ ስታይ ምን ይሰማህ ነበር? ዳዊት በፈጸመው ኃጢአት የተነሳ ትሰናከል ነበር?

8. (ሀ) ሐዋርያው ጴጥሮስ ቃሉን ሳይጠብቅ እንደቀረ የሚያሳየው ምንድን ነው? (ለ) ጴጥሮስ ስህተት ከሠራም በኋላ ይሖዋ የተጠቀመበት ለምንድን ነው?

8 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮ የምናገኘው ሌላው ምሳሌ የሐዋርያው ጴጥሮስ ታሪክ ነው። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስን ሐዋርያ እንዲሆን የመረጠው ቢሆንም ጴጥሮስ በኋላ ላይ የተቆጨባቸውን ነገሮች የተናገረባቸው ወይም ያደረገባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ሐዋርያቱ ወሳኝ በሆነ ጊዜ ላይ ኢየሱስን ጥለውት ሸሽተዋል። ቀደም ሲል ጴጥሮስ፣ ሌሎቹ ኢየሱስን ቢተዉት እንኳ እሱ እንደማይተወው ተናግሮ ነበር። (ማር. 14:27-31, 50) የሚያሳዝነው ግን ኢየሱስ ሲያዝ፣ ጴጥሮስን ጨምሮ ሐዋርያቱ ሁሉ ጥለውት ሸሹ። ጴጥሮስ ኢየሱስን ጨርሶ እንደማያውቀው በመግለጽ በተደጋጋሚ ጊዜ ካደው። (ማር. 14:53, 54, 66-72) ያም ሆኖ ጴጥሮስ በመጸጸቱ ይሖዋ ከዚያም በኋላ ተጠቅሞበታል። በዚያን ጊዜ የምትኖር የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ብትሆን ኖሮ የጴጥሮስ ድርጊት ይሖዋን በታማኝነት እንዳታገለግል እንቅፋት ይሆንብህ ነበር?

9. አምላክ ምንጊዜም ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ የምትተማመነው ለምንድን ነው?

9 እነዚህ ጥቂት ምሳሌዎች አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች የሌሎችን ስሜት የሚጎዳ ነገር ያደረጉባቸው ጊዜያት እንደነበሩ ያሳያሉ። ቀደም ባሉት ዘመናትም ሆነ በቅርብ ጊዜያት፣ ይሖዋን ያገለግሉ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ከባድ ስህተት በመፈጸም ሌሎችን የጎዱባቸው ሁኔታዎች እንዳሉ የሚያሳዩ ብዙ ምሳሌዎችን መጥቀስ ይቻላል። ዋናው ነገር ‘አንተ እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥምህ ምን ታደርጋለህ?’ የሚለው ነው። በእነዚህ ሰዎች ተሰናክለህ ከስብሰባ ትቀራለህ? ወይም ከይሖዋና ከሕዝቡ ትርቃለህ? ወይስ ይሖዋ ስህተት የሠሩት ሰዎች ንስሐ እንዲገቡ ጊዜ እንደሚሰጣቸው እንዲሁም የተፈጸመውን ስህተት ውሎ አድሮ እንደሚያስተካክለውና ትክክለኛውን እርምጃ እንደሚወስድ ትተማመናለህ? በሌላ በኩል ደግሞ ከባድ ኃጢአት የፈጸሙ አንዳንድ ሰዎች ንስሐ ገብተው የይሖዋን ምሕረት ለማግኘት ጥረት ላያደርጉ ይችላሉ። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲፈጠር ይሖዋ በተገቢው ጊዜ እነዚህን ኃጢአተኞች እንደሚፈርድባቸው ምናልባትም ከጉባኤው እንደሚያስወግዳቸው እምነት አለህ?

ምንጊዜም ታማኝ ሁን

10. የአስቆሮቱ ይሁዳና ጴጥሮስ ከፈጸሙት ስህተት ጋር በተያያዘ ኢየሱስ ምን አላደረገም?

10 መጽሐፍ ቅዱስ ሌሎች በፈጸሙት ከባድ ስህተት ሳይሰናከሉ፣ ምንጊዜም ከይሖዋም ሆነ ከሕዝቡ ጎን በታማኝነት ስለቆሙ የአምላክ አገልጋዮች የሚገልጹ ዘገባዎችን ይዟል። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል፤ ኢየሱስ 12ቱን ሐዋርያት የመረጠው ሌሊቱን በሙሉ ወደ አባቱ ከጸለየ በኋላ ነው። ከሐዋርያቱ አንዱ የአስቆሮቱ ይሁዳ ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ይሁዳ ክርስቶስን አሳልፎ ሰጥቶታል፤ ጴጥሮስም ቢሆን ክዶታል። ሆኖም ክርስቶስ ይህ ሁኔታ ከአባቱ ከይሖዋ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያበላሽበት አልፈቀደም። (ሉቃስ 6:12-16፤ 22:2-6, 31, 32) እነዚህ ሐዋርያት የፈጸሙት ስህተት፣ ኢየሱስ በይሖዋ ወይም በአምላክ ሕዝቦች ላይ እንዲቆጣ አላደረገውም። ኢየሱስ አንዳንድ ተከታዮቹ ቢያሳዝኑትም አባቱን በታማኝነት ማገልገሉን ቀጥሏል። ይሖዋም ኢየሱስን ከሞት በማስነሳት ወሮታ የከፈለው ሲሆን በሰማይ የተቋቋመው መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን አድርጎታል።—ማቴ. 28:7, 18-20

11. መጽሐፍ ቅዱስ በዘመናችን ያሉ የይሖዋ አገልጋዮችን በተመለከተ ምን ትንቢት ይዟል?

11 ኢየሱስ በይሖዋና በሕዝቡ መተማመኑ ተገቢ ነበር፤ አሁንም ቢሆን ሁኔታው አልተለወጠም። በእርግጥም ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት በአገልጋዮቹ አማካኝነት እያከናወነ ያለው ነገር እጅግ አስደናቂ ነው። ይሖዋ አንድነት ያለውን የክርስቲያን ጉባኤ እየመራው በመሆኑ አገልጋዮቹ እውነትን በዓለም ዙሪያ መስበክ ችለዋል፤ እንዲህ እያደረገ ያለ ሌላ ሕዝብ የለም። ኢሳይያስ 65:14 የአምላክ ሕዝቦች ስላሉበት መንፈሳዊ ሁኔታ ሲገልጽ “እነሆ፣ አገልጋዮቼ ከልባቸው ደስታ የተነሳ እልል ይላሉ” በማለት ይናገራል።

12. ሌሎች ከሚፈጽሟቸው ስህተቶች ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

12 ይሖዋ እየመራንና ብዙ መልካም ነገሮችን እንድናከናውን እየረዳን በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን! ከዚህ በተቃራኒ በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም በሐዘን ተውጧል፤ ምክንያቱም ሁኔታዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ ነው። ከዚህ አንጻር ሲታይ፣ አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች ለፈጸሙት ስህተት ይሖዋንና ሕዝቡን ተወቃሽ ማድረግ ምንኛ ሞኝነት ነው! ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ለይሖዋና ለዝግጅቶቹ ታማኝ መሆን አለብን፤ በተጨማሪም ሌሎች ከሚፈጽሟቸው ስህተቶች ጋር በተያያዘ ምን ብናደርግ የተሻለ እንደሚሆን መማር ይኖርብናል።

ሌሎች ስህተት ሲሠሩ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

13, 14. (ሀ) እርስ በርስ ባለን ግንኙነት ረገድ ትዕግሥተኞች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? (ለ) ይሖዋ የገባውን የትኛውን ቃል ማስታወስ ይኖርብናል?

13 አንድ የአምላክ አገልጋይ ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ቢናገር ወይም ቢፈጽም ምን ማድረግ ይኖርብናል? መጽሐፍ ቅዱስ “የሞኞች ቁጣ በጉያቸው ውስጥ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል” የሚል ግሩም ምክር ይሰጠናል። (መክ. 7:9) የሰው ልጅ ከፍጽምና ከራቀ 6,000 ያህል ዓመታት እንዳለፉ ማስታወስ ይኖርብናል። ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች ስህተት መሥራታቸው አይቀርም። በመሆኑም ከእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ መጠበቅ የለብንም፤ በተጨማሪም እነሱ የሚፈጽሙት ስህተት፣ በዚህ የመጨረሻ ዘመን ካሉት የአምላክ ሕዝቦች መካከል መሆናችን የሚያስገኝልንን ደስታ እንዲያሳጣን መፍቀድ አይኖርብንም። ሌሎች በፈጸሙት ስህተት ተሰናክለን የይሖዋን ድርጅት ብንተው ደግሞ ከዚህ የከፋ ይሆናል። እንዲህ ብናደርግ ይሖዋን የማገልገል መብታችንን ብቻ ሳይሆን አምላክ በሚያመጣው አዲስ ዓለም ውስጥ የመኖር ተስፋችንንም እናጣለን።

14 ደስታችንንና ተስፋችንን ጠብቀን ለመኖር ከፈለግን ይሖዋ የገባውን የሚከተለውን የሚያጽናና ቃል ምንጊዜም ማስታወስ ይኖርብናል፦ “እነሆ፣ አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እየፈጠርኩ ነውና፤ የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።” (ኢሳ. 65:17፤ 2 ጴጥ. 3:13) ሌሎች የሚፈጽሙት ስህተት ይህን በረከት እንዳታገኝ እንቅፋት እንዲሆንብህ አትፍቀድ!

15. ኢየሱስ ሌሎች ሲበድሉን ምን ማድረግ እንዳለብን ተናግሯል?

15 እርግጥ፣ አሁን ወደ አዲሱ ዓለም አልገባንም፤ ስለዚህ ሌሎች ስሜታችንን የሚጎዳ ነገር ሲናገሩ ወይም ሲፈጽሙ ምን ማድረግ እንዳለብን ለማወቅ የአምላክን አስተሳሰብ ከግምት ማስገባት ይኖርብናል። ለምሳሌ ኢየሱስ የሰጠውን የሚከተለውን መሠረታዊ ሥርዓት ማስታወሱ ጠቃሚ ነው፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።” በተጨማሪም ጴጥሮስ ወደ ኢየሱስ ቀርቦ “እስከ ሰባት ጊዜ ይቅር [ማለት]” ይኖርበት እንደሆነ ሲጠይቀው ኢየሱስ “እስከ 77 ጊዜ እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ ብቻ አልልህም” ብሎ እንደመለሰለት መዘንጋት አይኖርብንም። ኢየሱስ ይህን የተናገረው ምንጊዜም ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ለማጉላት ነው፤ ሌሎችን ይቅር ማለት የሚቀናን ዓይነት ሰዎች መሆን አለብን።—ማቴ. 6:14, 15፤ 18:21, 22

16. ዮሴፍ ምን ግሩም ምሳሌ ትቷል?

16 ራሔል ለያዕቆብ ከወለደቻቸው ሁለት ልጆች መካከል የመጀመሪያው የሆነው ዮሴፍ፣ ሌሎች ሲበድሉን ምን ማድረግ እንዳለብን ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። ያዕቆብ ለዮሴፍ ልዩ ፍቅር ስለነበረው አሥሩ ወንድሞቹ ቅናት አደረባቸው። በዚህም የተነሳ ዮሴፍን ለባርነት ሸጡት። ከብዙ ዓመታት በኋላ፣ ዮሴፍ በግብፅ ባከናወነው መልካም ሥራ የተነሳ በአገሪቱ ውስጥ ከንጉሡ ቀጥሎ ያለውን ቦታ መያዝ ቻለ። ረሃብ ሲከሰት የዮሴፍ ወንድሞች ምግብ ለመግዛት ወደ ግብፅ መጡ፤ በዚህ ጊዜ ዮሴፍን አላወቁትም ነበር። ዮሴፍ ወንድሞቹ ለፈጸሙበት ከባድ በደል ሥልጣኑን ተጠቅሞ ሊበቀላቸው ይችል ነበር። እሱ ግን የወንድሞቹ ባሕርይ ተለውጦ እንደሆነ ለማወቅ ሲል ፈተናቸው። ወንድሞቹ እውነተኛ ለውጥ እንዳደረጉ ሲረዳ ማንነቱን ነገራቸው። ከተወሰነ ጊዜ በኋላም “አትፍሩ። ለእናንተም ሆነ ለትናንሽ ልጆቻችሁ የሚያስፈልገውን እህል እሰጣችኋለሁ” አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ “እሱም በዚህ መንገድ አጽናናቸው፤ እንዲሁም አረጋጋቸው” በማለት ይናገራል።—ዘፍ. 50:21

17. ሌሎች ስህተት ሲሠሩ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?

17 ሁላችንም ስህተት ስለምንሠራ እኛም ሌሎችን ልንበድል እንደምንችል ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። የበደልነው ሰው እንዳለ ከተገነዘብን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያ በመከተል ወደ ግለሰቡ ሄደን እርቅ ለማውረድ ጥረት ማድረግ አለብን። (ማቴዎስ 5:23, 24ን አንብብ።) ሌሎች የፈጸምነውን በደል ይቅር ሲሉን ደስ ይለናል፤ እኛም እነሱ ሲበድሉን እንዲሁ ማድረግ ይኖርብናል። ቆላስይስ 3:13 እንዲህ ሲል ያሳስበናል፦ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ። ይሖዋ በነፃ ይቅር እንዳላችሁ ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ።” በተጨማሪም 1 ቆሮንቶስ 13:5 ክርስቲያናዊ “ፍቅር የበደል መዝገብ” እንደሌለው ይናገራል። ሌሎችን ይቅር የምንል ከሆነ ይሖዋም ይቅር ይለናል። በእርግጥም እኛ ስህተት ስንሠራ በሰማይ ያለው አባታችን ይቅር እንደሚለን ሁሉ እኛም ሌሎች ስህተት በሚሠሩበት ጊዜ ይቅር ባዮች ልንሆን ይገባል።—መዝሙር 103:12-14ን አንብብ።