በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከአልማዝ ይበልጥ ውድ የሆነ ግሩም ባሕርይ

ከአልማዝ ይበልጥ ውድ የሆነ ግሩም ባሕርይ

አልማዝ፣ ከጥንትም ጀምሮ ውድ ዋጋ ካላቸው የከበሩ ድንጋዮች ተርታ ይመደብ ነበር። በሚሊዮኖች የሚቆጠር የአሜሪካ ዶላር የሚያወጡ አልማዞች አሉ። ይሁን እንጂ በአምላክ ዓይን ከአልማዝ ወይም ከከበሩ ድንጋዮች የበለጠ ውድ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ይኖሩ ይሆን?

ሃይጋኑሽ የምትባል በአርሜኒያ የምትኖር አንዲት ያልተጠመቀች አስፋፊ በቤቷ አቅራቢያ አንድ ፓስፖርት አገኘች። በፓስፖርቱ ውስጥ ዴቢት ካርዶችና ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ ነበረ። ሃይጋኑሽ እንደ እሷ ያልተጠመቀ አስፋፊ ለነበረው ለባለቤቷ ሁኔታውን ነገረችው።

ባልና ሚስቱ ከባድ የገንዘብ ችግር ያለባቸው ከመሆኑም ሌላ ዕዳ ነበረባቸው፤ ሆኖም በፓስፖርቱ ላይ ወደተመዘገበው አድራሻ ሄደው ገንዘቡን ለመመለስ ወሰኑ። የፓስፖርቱ ባለቤትም ሆነ ቤተሰቡ ይህን ሲያዩ በጣም ተገረሙ። ሃይጋኑሽና ባለቤቷ፣ ሐቀኛ እንዲሆኑ የረዳቸው ከመጽሐፍ ቅዱስ እየተማሩ ያሉት ነገር እንደሆነ ገለጹላቸው። ከዚያም በዚህ አጋጣሚ ተጠቅመው ለዚህ ቤተሰብ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የተናገሩ ሲሆን አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችንም ሰጧቸው።

ይህ ቤተሰብ ለሃይጋኑሽ ወሮታ ለመክፈል ሲል የተወሰነ ገንዘብ ሊሰጣት ፈልጎ ነበር፤ እሷ ግን አልተቀበለችም። በማግስቱ ሚስትየዋ ወደ ሃይጋኑሽ ቤት የሄደች ሲሆን ቤተሰቧ የተሰማውን አድናቆት ለመግለጽ ስትል ሃይጋኑሽን የግድ ብላ አንድ የአልማዝ ቀለበት ሰጠቻት።

ሃይጋኑሽና ባለቤቷ ሐቀኛ መሆናቸው ያንን ቤተሰብ እንዳስገረመ ሁሉ ሌሎች ሰዎችንም ያስገርም ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ምግባር ይሖዋን ያስገርመዋል? የባልና ሚስቱን ሐቀኝነት እንዴት ይመለከተዋል? ደግሞስ ሐቀኝነት የሚያስገኘው ብድራት አለ?

ከቁሳዊ ነገሮች ይበልጥ ውድ የሆኑ ባሕርያት

የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ከባድ አይደለም። የአምላክ አገልጋዮች የይሖዋን ባሕርያት ማንጸባረቅ በእሱ ዘንድ ትልቅ ቦታ እንዳለው ይገነዘባሉ፤ እነዚህ ባሕርያት ከአልማዝ፣ ከወርቅ ወይም ከሌሎች ቁሳዊ ነገሮች የበለጠ እጅግ ውድ ናቸው። በእርግጥም ይሖዋ ውድ ስለሆነው ነገር ያለው አመለካከት አብዛኞቹ ሰዎች ካላቸው አመለካከት የተለየ ነው። (ኢሳ. 55:8, 9) የይሖዋ አገልጋዮችም ቢሆኑ የእሱን ባሕርያት በተሟላ መልኩ ማንጸባረቅን ትልቅ ቦታ ይሰጡታል።

መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጥበብና ጥልቅ ግንዛቤ የሚናገረው ነገር ይህን ያሳያል። ምሳሌ 3:13-15 እንዲህ ይላል፦ “ጥበብን የሚያገኝ፣ ጥልቅ ግንዛቤንም የራሱ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ ጥበብን ማግኘት ብርን ከማግኘት የተሻለ ነው፤ እሷንም ማትረፍ ወርቅ ከማግኘት የተሻለ ነው። ከዛጎል ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም።” በግልጽ ማየት እንደሚቻለው፣ ይሖዋ እነዚህን ባሕርያት ከማንኛውም ቁሳዊ ሀብት ይበልጥ ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል።

ታዲያ ስለ ሐቀኝነት ምን ማለት ይቻላል?

ይሖዋ ሐቀኛ አምላክ ነው፤ ‘ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ይሖዋ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት ዕብራውያን ክርስቲያኖች እንደሚከተለው በማለት እንዲጽፍ በመንፈሱ መርቶታል፦ “ለእኛ መጸለያችሁን ቀጥሉ፤ ምክንያቱም ሐቀኛ ሕሊና እንዳለን እናምናለን፤ ደግሞም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር እንፈልጋለን።”—ዕብ. 13:18

ኢየሱስ ክርስቶስም በሐቀኝነት ረገድ ግሩም አርዓያ ትቷል። ለምሳሌ ያህል፣ ሊቀ ካህናቱ ቀያፋ “አንተ የአምላክ ልጅ ክርስቶስ መሆን አለመሆንህን እንድትነግረን በሕያው አምላክ አስምልሃለሁ!” ብሎት ነበር። በዚህ ጊዜ ኢየሱስ፣ መሲሕ መሆኑን በሐቀኝነት ተናግሯል፤ ይህን ያደረገው እውነቱን ቢናገር የሳንሄድሪን ሸንጎ ‘አምላክን ሰድቧል’ ብሎ ሊከሰውና ሞት ሊፈርድበት እንደሚችል እያወቀ ነው።—ማቴ. 26:63-67

እኛስ በዚህ ረገድ እንዴት ነን? አንዳንድ ነገሮችን ሳንናገር መቅረታችን ወይም መረጃን በትንሹ ማዛባታችን ቁሳዊ ጥቅም የሚያስገኝልን ቢሆንም እንኳ ሐቀኞች እንሆናለን?

ሐቀኝነት ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው?

ብዙዎች “ራሳቸውን የሚወዱ” እንዲሁም “ገንዘብ የሚወዱ” በሆኑባቸው በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ሐቀኛ መሆን ከባድ እንደሆነ አይካድም። (2 ጢሞ. 3:2) ሰዎች ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ችግር ሲያጋጥማቸው ወይም ሥራ ማግኘት አስቸጋሪ በሚሆንባቸው ጊዜ ሐቀኛ መሆን ፈታኝ ሊሆንባቸው ይችላል። በዚህ ጊዜ ለመስረቅ፣ ለማጭበርበር ወይም ሐቀኝነት በጎደላቸው ሌሎች ድርጊቶች ለመካፈል በቂ ምክንያት እንዳላቸው ያስባሉ። ይህ አስተሳሰብ በጣም የተስፋፋ ከመሆኑ የተነሳ ብዙዎች ቁሳዊ ጥቅም ከማግኘት ጋር በተያያዘ ሐቀኛ መሆን ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ይሰማቸዋል። አንዳንድ ክርስቲያኖችም እንኳ በዚህ ረገድ የተሳሳተ ውሳኔ ያደረጉ ሲሆን “አግባብ ያልሆነ ጥቅም ለማግኘት” ሲሉ በጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ጥሩ አቋም አጥተዋል።—1 ጢሞ. 3:8፤ ቲቶ 1:7

ይሁን እንጂ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ኢየሱስን ይመስላሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች፣ አምላክን የሚያስደስቱ ባሕርያት ከየትኛውም ሀብት ወይም ጥቅማ ጥቅም እጅግ የላቀ ዋጋ እንዳላቸው ይገነዘባሉ። በመሆኑም ክርስቲያን ወጣቶች በትምህርት ቤት ጥሩ ውጤት ለማግኘት ብለው አይኮርጁም። (ምሳሌ 20:23) እውነት ነው፣ ሐቀኛ መሆን እንደ ሃይጋኑሽ ሁልጊዜ ሽልማት ላያስገኝ ይችላል። ይሁን እንጂ በአምላክ ዘንድ ትክክለኛ የሆነው አካሄድ ሐቀኝነት ነው፤ ሐቀኛ መሆን ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን የሚያደርግ ሲሆን ይህም ውድ ሀብት ነው።

ጋጊክ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። እንዲህ ብሏል፦ “ክርስቲያን ከመሆኔ በፊት አንድ ትልቅ ኩባንያ ውስጥ እሠራ ነበር፤ የኩባንያው ባለቤት የሚጠበቅበትን ግብር ላለመክፈል ሲል ድርጅቱ ከሚያገኘው ትርፍ የሚያሳውቀው ጥቂቱን ብቻ ነበር። እኔም የኩባንያው ሥራ አስኪያጅ እንደመሆኔ መጠን የግብር ኦዲተሩ ሲመጣ፣ ሐቀኝነት የጎደለውን የድርጅቱን አሠራር እንዲያልፈው ለማድረግ ስል ጉቦ በመስጠት ‘እንዳግባባው’ ይጠበቅብኝ ነበር። እንዲህ ያለ የማጭበርበር ድርጊት በመፈጸሜ መጥፎ ስም አተረፍኩ። እውነትን ሳውቅ ግን ሥራው በጣም ጥሩ ደሞዝ የሚያስገኝ ቢሆንም እንኳ ሐቀኝነት በጎደለው በዚህ ድርጊት መካፈሌን መቀጠል አልፈለግኩም። በመሆኑም የራሴን ሥራ መሥራት ጀመርኩ። ሥራ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ ኩባንያዬን ሕጋዊ በሆነ መንገድ አስመዘገብኩ፤ እንዲሁም የሚጠበቅብኝን ግብር በሙሉ እከፍላለሁ።”—2 ቆሮ. 8:21

ጋጊክ በመቀጠል እንዲህ ይላል፦ “ገቢዬ በግማሽ ያህል ቀነሰ፤ በዚህም የተነሳ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገውን ማቅረብ ተፈታታኝ ነበር። ይሁን እንጂ አሁን ከቀድሞው የበለጠ ደስተኛ ነኝ። በይሖዋ ፊት ንጹሕ ሕሊና አለኝ። ለሁለቱ ወንዶች ልጆቼ ጥሩ ምሳሌ ነኝ፤ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ የማገልገል መብት ለማግኘት የሚያስፈልገውን ብቃት አሟልቻለሁ። አሁን ከሥራዬ ጋር በተያያዘ የማገኛቸው ኦዲተሮችና ሌሎች ሰዎች የሚያውቁኝ ሐቀኛ ሰው በመሆኔ ነው።”

ይሖዋ ይረዳናል

ይሖዋ ሐቀኝነትን ጨምሮ ወደር የሌላቸውን ባሕርያቱን በማንጸባረቅ መለኮታዊው ትምህርት ውበት እንዲጎናጸፍ የሚያደርጉ ሰዎችን ይወዳቸዋል። (ቲቶ 2:10) ንጉሥ ዳዊት “በአንድ ወቅት ወጣት ነበርኩ፤ አሁን ግን አርጅቻለሁ፤ ይሁንና ጻድቅ ሰው ሲጣል፣ ልጆቹም ምግብ ሲለምኑ አላየሁም” የሚል ማረጋገጫ በቃሉ ላይ እንዲያሰፍር ይሖዋ በመንፈሱ መርቶታል።—መዝ. 37:25

ታማኝ የሆነችው የሩት ታሪክ ይህን ያረጋግጣል። አማቷን ናኦሚን በስተ እርጅናዋ ጥላት ከመሄድ ይልቅ ከእሷ ላለመለየት ቆርጣለች። ሩት እውነተኛውን አምላክ ማምለክ ወደምትችልበት ወደ እስራኤል ሄደች። (ሩት 1:16, 17) እዚያ ከሄደችም በኋላ በሕጉ ውስጥ በተደረገው ዝግጅት መሠረት በትጋት በመቃረም ሐቀኛና ታታሪ መሆኗን አሳይታለች። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ከተሞክሮ በመነሳት ከተናገረው ጋር በሚስማማ መልኩ ይሖዋ፣ ሩትና ናኦሚን አልተዋቸውም። (ሩት 2:2-18) ይሖዋ ለሩት በቁሳዊ የሚያስፈልጋትን ከማቅረብም ባለፈ ብዙ ነገር ያደረገላት መሆኑ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል። የንጉሥ ዳዊት ቅድመ አያት እንድትሆን መርጧታል፤ ሌላው ቀርቶ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ በእሷ የዘር ሐረግ በኩል እንዲመጣ አድርጓል!—ሩት 4:13-17፤ ማቴ. 1:5, 16

አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች መሠረታዊ ነገሮችን ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች ካሉበት ሁኔታ በቀላሉ ለመገላገል ሲሉ ሐቀኝነት የጎደለው ነገር ከማድረግ ይልቅ ታታሪዎች በመሆን ጠንክረው ይሠራሉ። በዚህም መንገድ፣ ከማንኛውም ቁሳዊ ነገር ይልቅ ለሐቀኝነትና ለሌሎች ተወዳዳሪ የሌላቸው የአምላክ ባሕርያት ትልቅ ቦታ እንደሚሰጡ በተግባር ያሳያሉ።—ምሳሌ 12:24፤ ኤፌ. 4:28

በጥንት ዘመን እንደኖረችው እንደ ሩት ሁሉ በምድር ዙሪያ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም ይሖዋ እነሱን ለመርዳት ባለው ኃይል እንደሚተማመኑ አሳይተዋል። “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” በማለት ቃል በገባልን አምላክ ላይ ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ። (ዕብ. 13:5) ይሖዋ ምንጊዜም ሐቀኛ ለመሆን የሚጥሩ የተቸገሩ ሰዎችን መርዳት እንደሚችል ብሎም እንደሚረዳቸው በተደጋጋሚ አሳይቷል። ለሕይወት የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያቀርብ የገባውን ቃል ጠብቋል።—ማቴ. 6:33

ሰዎች ለአልማዝና ከፍተኛ ዋጋ ለሚያወጡ ሌሎች ነገሮች ትልቅ ግምት ይሰጡ ይሆናል። የሰማዩ አባታችን ግን ከማንኛውም ነገር፣ ሌላው ቀርቶ ውድ ከሆኑ ዕንቁዎች እንኳ በላይ ከፍ አድርጎ የሚመለከተው ሐቀኝነትንና ሌሎች የእሱን ባሕርያት ማንጸባረቃችንን ነው!

ሐቀኛ መሆን ሕሊናችን ንጹሕ እንዲሆንና በአገልግሎት ላይ የመናገር ነፃነት እንዲኖረን ያደርጋል