በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በታላቁ ሸክላ ሠሪ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ?

በታላቁ ሸክላ ሠሪ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ?

“እነሆ፣ በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ ጭቃ፣ እናንተም በእኔ እጅ እንዲሁ ናችሁ።”—ኤር. 18:6

መዝሙሮች፦ 60, 22

1, 2. አምላክ ዳንኤልን “እጅግ የተወደድክ ሰው” በማለት የጠራው ለምንድን ነው? እኛስ እንደ ዳንኤል ታዛዦች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

በጥንት ዘመን አይሁዳውያን በግዞት ወደ ባቢሎን ተወስደው ነበር፤ ባቢሎን በጣዖታት የተሞላች ስትሆን ሕዝቧም በመናፍስታዊ ድርጊቶች ተተብትበው ነበር። ያም ቢሆን ዳንኤልና ሦስቱ ጓደኞቹ እንዲሁም ሌሎች ታማኝ አይሁዳውያን ባቢሎናውያን እንዲቀርጿቸው አልፈቀዱም። (ዳን. 1:6, 8, 12፤ 3:16-18) ዳንኤልና ጓደኞቹ፣ ታላቅ ሸክላ ሠሪ የሆነውን ይሖዋን ብቻ ለማምለክ ቆርጠው ነበር። ደግሞም ይህን ማድረግ ችለዋል! ዳንኤል መላ ሕይወቱን ያሳለፈው በባቢሎን ነበር ማለት ይቻላል፤ ያም ቢሆን የአምላክ መልአክ “እጅግ የተወደድክ ሰው” በማለት ጠርቶታል።—ዳን. 10:11, 19

2 በጥንት ዘመን አንድ ሸክላ ሠሪ፣ ጭቃው እሱ የፈለገውን ቅርጽ እንዲይዝ ለማድረግ ቅርጽ ማውጫ ይጠቀም ነበር። በዛሬው ጊዜ የሚገኙ እውነተኛ የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ እንደሆነ እንዲሁም ሰዎችንና ብሔራትን የመቅረጽ ሥልጣን እንዳለው ይገነዘባሉ። (ኤርምያስ 18:6ን አንብብ።) በተጨማሪም አምላክ እኛን በግለሰብ ደረጃ የመቅረጽ ሥልጣን አለው። ይሁንና የመምረጥ ነፃነታችንን የሚያከብርልን ሲሆን በእሱ ለመቀረጽ ፈቃደኞች እንድንሆን ይፈልጋል። እንደ ለስላሳ የሸክላ ጭቃ፣ ምንጊዜም በአምላክ እጅ ለመቀረጽ ፈቃደኞች መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመረምራለን፤ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች እንመለከታለን፦ (1) የአምላክን ምክር እንዳንቀበል ልባችንን ሊያደነድኑ የሚችሉ ባሕርያትን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? (2) ምንጊዜም በቀላሉ የምንቀረጽና ታዛዦች እንድንሆን የሚረዱንን ባሕርያት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (3) ክርስቲያን ወላጆች፣ ልጆቻቸውን በሚቀርጹበት ጊዜ ለአምላክ ታዛዥ መሆናቸውን ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

ልባችሁን ሊያደነድኑ የሚችሉ ባሕርያትን አስወግዱ

3. ልባችንን ሊያደነድኑ የሚችሉት የትኞቹ ባሕርያት ናቸው? ምሳሌ ስጥ።

3 ምሳሌ 4:23 “ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ከእሱ ዘንድ ነውና” ይላል። ልባችንን ሊያደነድኑ የሚችሉትን የትኞቹን ባሕርያት ማስወገድ ይኖርብናል? ከእነዚህ መካከል ተገቢ ያልሆነ ኩራት፣ ኃጢአትን ልማድ ማድረግ እንዲሁም እምነት ማጣት ይገኙበታል። እንደነዚህ ያሉት ዝንባሌዎች ያለመታዘዝና የዓመፀኝነት መንፈስ እንዲኖረን ሊያደርጉ ይችላሉ። (ዳን. 5:1, 20፤ ዕብ. 3:13, 18, 19) የይሁዳ ንጉሥ የነበረው ዖዝያ ታብዮ ነበር። (2 ዜና መዋዕል 26:3-5, 16-21ን አንብብ።) ዖዝያ በንግሥናው መጀመሪያ ላይ “በይሖዋ ፊት ትክክል የሆነውን ነገር” ያደረገ ከመሆኑም ሌላ “አምላክን ይፈልግ ነበር።” አምላክም ዖዝያን አበረታው፤ የሚያሳዝነው ግን “በበረታ ጊዜ ልቡ ታበየ።” እንዲያውም ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ በመግባት ዕጣን ለማጠን ሞከረ፤ ይህ የአሮን ዘሮች ለሆኑት ካህናት ብቻ የተሰጠ መብት ነበር። ካህናቱ ድርጊቱ ትክክል አለመሆኑን ሲነግሩት ደግሞ ትዕቢተኛው ዖዝያ እጅግ ተቆጣ! ይህ ምን አስከተለ? አምላክ ውርደት ያከናነበው ሲሆን እስከ ዕለተ ሞቱ ድረስ የሥጋ ደዌ በሽተኛ ሆኖ ኖረ።—ምሳሌ 16:18

4, 5. የኩራት ዝንባሌ ካደረብን ምን ሊያጋጥመን ይችላል? ምሳሌ ስጥ።

4 እኛም የኩራት ዝንባሌ ካደረብን ‘ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን በማሰብ ራሳችንን ከፍ አድርገን’ ልንመለከት አልፎ ተርፎም ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክርን ለመቀበል ፈቃደኞች ላንሆን እንችላለን። (ሮም 12:3፤ ምሳሌ 29:1) ጂም የተባለ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት፤ ጂም አብረውት ከሚያገለግሉት ሽማግሌዎች ጋር በአንድ የጉባኤ ጉዳይ ላይ አልተግባባም። ጂም እንዲህ ብሏል፦ “ፍቅር እንደሚጎድላቸው ከነገርኳቸው በኋላ ስብሰባውን ትቼ ወጣሁ።” ከስድስት ወር ገደማ በኋላ በአቅራቢያው ወደሚገኝ ጉባኤ ተዛወረ፤ ሆኖም ሽማግሌ ሆኖ አልተሾመም። ጂም “ቅስሜ ተሰበረ። ‘እኔ ትክክል ነኝ’ የሚል ግትር አቋም ስለነበረኝ እውነትን ተውኩ” ብሏል። ከይሖዋ ቤት ርቆ አሥር ዓመት ቆየ። እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “ክብሬ እንደተነካ ስለተሰማኝ ለተፈጠረው ነገር ይሖዋን ማማረር ጀመርኩ። በእነዚህ ዓመታት ወንድሞች መጥተው ይጠይቁኝ ነበር፤ እኔን ለመርዳት ብዙ ጥረት ያደርጉ የነበረ ቢሆንም እርዳታቸውን ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆንኩም።”

5 የጂም ተሞክሮ እንደሚያሳየው፣ ኩራት ለድርጊታችን ሰበብ እንድንፈጥርና ለመቀረጽ ፈጽሞ የማንመች እንድንሆን ሊያደርገን ይችላል። (ኤር. 17:9) ጂም “ሌሎቹ እንደተሳሳቱ ስለተሰማኝ ነገሩ ሁልጊዜ ይከነክነኝ ነበር” ብሏል። በአንድ የእምነት ባልንጀራህ ቅር ተሰኝተህ ታውቃለህ? አሊያም አንድን መብት በማጣትህ ስሜትህ ተጎድቶ ያውቃል? ከሆነ ምን አደረግክ? ክብርህ እንደተነካ ተሰማህ? ወይስ በዋነኝነት ያሳሰበህ ከወንድምህ ጋር ሰላም በመፍጠር ለይሖዋ ታማኝ መሆንህ ነው?—መዝሙር 119:165ን እና ቆላስይስ 3:13ን አንብብ።

6. ኃጢአት የመፈጸም ልማድ ካዳበርን ምን ሊያጋጥመን ይችላል?

6 አንድ ሰው ኃጢአትን ልማድ ካደረገ ምናልባትም በድብቅ ኃጢአት የሚፈጽም ከሆነ መለኮታዊ ምክር ሲሰጠው ለመቀበል ፈቃደኛ ላይሆን ይችላል። ይህ ደግሞ ኃጢአትን እንደ ቀላል ነገር እንዲመለከት ሊያደርገው ይችላል። አንድ ወንድም፣ ኃጢአት ሲፈጽም የሚሰማው የጥፋተኝነት ስሜት እያደር እየጠፋ እንደሄደ ገልጿል። (መክ. 8:11) የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች የመመልከት ልማድ የነበረው ሌላ ወንድም ደግሞ “ሽማግሌዎችን መንቀፍ ጀመርኩ” በማለት ተናግሯል። መጥፎ ልማዱ መንፈሳዊነቱ ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ ነበር። ውሎ አድሮ ይህ ልማዱ ስለታወቀ ሽማግሌዎች እርዳታ ሰጡት። ሁላችንም ፍጽምና እንደሚጎድለን የታወቀ ነው። ሆኖም የአምላክን ምሕረትና እርዳታ ከመሻት ይልቅ ሌሎችን መንቀፍ ወይም ለፈጸምነው ኃጢአት ሰበብ መደርደር ከጀመርን ልባችን ደንድኗል ማለት ነው።

7, 8. (ሀ) የጥንቶቹ እስራኤላውያን ታሪክ፣ እምነት ማጣት ልብን ሊያደነድን እንደሚችል የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) ከእነሱ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

7 እስራኤላውያን ይሖዋ ከግብፅ ነፃ ካወጣቸው በኋላ የፈጸሙት ድርጊት፣ እምነት ማጣት ልብን ሊያደነድን እንደሚችል የሚያሳይ ምሳሌ ይሆናል። እነዚህ እስራኤላውያን አምላክ ለእነሱ ሲል የፈጸማቸውን በርካታ ተአምራት ተመልክተዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ተአምራት በጣም አስደናቂ ነበሩ! ይሁንና ሕዝቡ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲቃረቡ እምነት እንደጎደላቸው የሚያሳይ ድርጊት ፈጸሙ። በይሖዋ አልታመኑም፤ ይልቁንም ፍርሃት ስላደረባቸው በሙሴ ላይ አጉረመረሙ። ይባስ ብለውም፣ በባርነት ይማቅቁ ወደነበሩበት ወደ ግብፅ መመለስ ፈለጉ! ይሖዋ በጣም ስላዘነ “ይህ ሕዝብ የሚንቀኝ እስከ መቼ ነው?” ብሎ ነበር። (ዘኁ. 14:1-4, 11፤ መዝ. 78:40, 41) ያ ትውልድ ልበ ደንዳና እና እምነት የለሽ በመሆኑ በምድረ በዳ አለቀ።

8 ወደ አዲሱ ዓለም የምንገባበት ጊዜ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት የእኛም እምነት እየተፈተነ ነው። በመሆኑም የእምነታችንን ጥንካሬ መመርመራችን የተገባ ነው። ለምሳሌ ኢየሱስ በማቴዎስ 6:33 ላይ የተናገረውን ሐሳብ በተመለከተ ያለንን አመለካከት መመርመራችን ጠቃሚ ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ቅድሚያ የምሰጣቸው ነገሮችና የማደርጋቸው ውሳኔዎች ኢየሱስ በተናገረው ሐሳብ ከልቤ እንደማምን ያሳያሉ? ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ስል ከስብሰባ ወይም ከአገልግሎት እቀራለሁ? ሥራዬ ጊዜዬን በጣም የሚሻማና ኃይሌን የሚያሟጥጥ ቢሆን ምን አደርጋለሁ? ዓለም እንዲቀርጸኝ እፈቅዳለሁ? ምናልባትም በዚህ ዓለም ተጽዕኖ ተሸንፌ እውነትን እስከመተው እደርስ ይሆን?’

9. በእምነት ውስጥ መሆናችንን ‘ዘወትር መፈተሽ’ ያለብን ለምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለውስ እንዴት ነው?

9 በሌላ በኩል ደግሞ ‘ከጓደኛ ምርጫ፣ ከውገዳ ወይም ከመዝናኛ ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች ለመታዘዝ አመነታለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን የተገባ ነው። ልባችንን ሊያደነድን የሚችል እንዲህ ያለ ዝንባሌ እንዳለን ካስተዋልን ዛሬ ነገ ሳንል እምነታችንን መመርመራችን አስፈላጊ ነው! መጽሐፍ ቅዱስ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” የሚል ምክር ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 13:5) በአምላክ ቃል በመጠቀም አዘውትረን ራሳችንን በሐቀኝነት መመርመርና አስተሳሰባችንን ማስተካከል ያስፈልገናል።

ምንጊዜም ለመቀረጽ ፈቃደኛ ሁኑ

10. በይሖዋ እጅ በቀላሉ እንደሚቀረጽ የሸክላ ጭቃ እንድንሆን ምን ይረዳናል?

10 አምላክ፣ ምንጊዜም በቀላሉ እንደሚቀረጽ የሸክላ ጭቃ እንድንሆን እኛን ለመርዳት ካደረጋቸው ዝግጅቶች መካከል ቃሉ፣ የክርስቲያን ጉባኤና አገልግሎት ይገኙበታል። የሸክላ ጭቃ እንዲለሰልስ ውኃ እንደሚያስፈልገው ሁሉ እኛም በይሖዋ እጅ በቀላሉ መቀረጽ እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። የእስራኤል ነገሥታት የአምላክን ሕግ ቅጂ ለራሳቸው እንዲጽፉና በየዕለቱ እንዲያነቡት ይሖዋ ይጠብቅባቸው ነበር። (ዘዳ. 17:18, 19) ሐዋርያትም ቅዱሳን መጻሕፍትን ማንበባቸውና ባነበቡት ላይ ማሰላሰላቸው ለአገልግሎታቸው እንደሚጠቅማቸው ተገንዝበው ነበር። በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ከዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት በተደጋጋሚ ጊዜያት የጠቀሱ ከመሆኑም ሌላ የሚሰብኩላቸውን ሰዎችም ቅዱሳን መጻሕፍትን እንዲያነቡ ያበረታቷቸው ነበር። (ሥራ 17:11) እኛም የአምላክን ቃል በየዕለቱ የማንበብንና የማሰላሰልን አስፈላጊነት እንገነዘባለን። (1 ጢሞ. 4:15) ይህን ማድረጋችን በይሖዋ ፊት ምንጊዜም ትሑትና በቀላሉ የምንቀረጽ እንድንሆን ይረዳናል።

ምንጊዜም በአምላክ እጅ በቀላሉ መቀረጽ እንድትችል በአምላክ ዝግጅቶች ተጠቀም (ከአንቀጽ 10-13 ተመልከት)

11, 12. ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት እያንዳንዳችንን በሚያስፈልገን መንገድ የሚቀርጸን እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

11 ይሖዋ በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት እያንዳንዳችንን በሚያስፈልገን መንገድ ይቀርጸናል። ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ጂም፣ አንድ ሽማግሌ ያሳየው አሳቢነት አመለካከቱን እንዲለውጥ ረድቶታል። ጂም እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሽማግሌ፣ አንድም ጊዜ ሊወቅሰኝ ወይም ሊነቅፈኝ አልሞከረም። አዎንታዊ ነገሮች ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሲሆን ከልቡ ሊረዳኝ እንደሚፈልግ ገለጸልኝ።” ከሦስት ወር ገደማ በኋላ ሽማግሌው በስብሰባ ላይ እንዲገኝ ጋበዘው። ጂም እንዲህ በማለት ተናግሯል፦ “የጉባኤው አባላት ሞቅ ባለ ስሜት ተቀበሉኝ፤ ያሳዩኝ ፍቅር ለውጥ እንዳደርግ አነሳሳኝ። ዋናው ነገር የእኔ ስሜት እንዳልሆነ አስተዋልኩ። ወንድሞችና በመንፈሳዊ ንቁ ሆና የኖረችው ውዷ ባለቤቴ ያደረጉልኝ ድጋፍ ቀስ በቀስ በመንፈሳዊ እንድጠነክር ረዳኝ። በተጨማሪም በኅዳር 15, 1992 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጡት ‘ተወቃሹ ይሖዋ አይደለም’ እና ‘ለይሖዋ በታማኝነት እየቆማችሁ አገልግሉት’ የሚሉት ርዕሶች በጣም አበረታተውኛል።”

12 ከጊዜ በኋላ ጂም፣ ሽማግሌ ሆኖ ተሾመ። ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሌሎች ወንድሞችም ተመሳሳይ ፈተናዎችን መወጣት እንዲችሉና በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ መርዳት ችሏል። እንዲህ ብሏል፦ “ከይሖዋ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዳለኝ ይሰማኝ የነበረ ቢሆንም እውነታው ግን ከዚህ ፈጽሞ የተለየ ነበር። ኩራት ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች እንዳላስተውል ከዚህ ይልቅ በሌሎች ሰዎች ድክመቶች ላይ እንዳተኩር ተጽዕኖ አሳድሮብኝ እንደነበር ሳስበው ይቆጨኛል።”—1 ቆሮ. 10:12

13. የመስክ አገልግሎት የትኞቹን ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል? ይህስ ምን ጥቅም አለው?

13 የመስክ አገልግሎት የተሻልን ሰዎች እንድንሆን የሚረዳንና የሚቀርጸን እንዴት ነው? ምሥራቹን ለሰዎች መስበክ ትሕትናን እንዲሁም የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎችን ማዳበር እንድንችል ይረዳናል። (ገላ. 5:22, 23) በአገልግሎት ላይ ያዳበራችኋቸውን መልካም ባሕርያት እስቲ መለስ ብላችሁ አስቡ። ከዚህም ሌላ የክርስቶስ ዓይነት ባሕርያት ስናንጸባርቅ መልእክታችንን እናስውባለን፤ ይህ ደግሞ የአንዳንድ ሰዎች አመለካከት እንዲለወጥ ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በአውስትራሊያ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች፣ ለአንዲት ሴት ሊመሠክሩላት ሲሉ ሥርዓት የጎደለው ምላሽ ሰጠቻቸው፤ እነሱ ግን ስትናገር በአክብሮት አዳመጧት። ይሁንና በኋላ ላይ ሴትየዋ በድርጊቷ ስለተጸጸተች ለቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ጻፈች። ደብዳቤው በከፊል እንዲህ ይላል፦ “እነዚያን በጣም ታጋሽና ትሑት ሰዎች፣ ራሴን በማመጻደቅና እነሱን ዝቅ በማድረግ ስላናገርኳቸው ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። የአምላክን ቃል የሚናገሩ ሰዎችን በዚያ መንገድ ማባረሬ ሞኝነት እንደሆነ ተሰምቶኛል።” አስፋፊዎቹ በትንሹም እንኳ እንደተናደዱ የሚያሳይ ነገር አድርገው ቢሆን ኖሮ ሴትየዋ እንዲህ ዓይነት ደብዳቤ ትጽፍ ነበር? ላትጽፍ ትችላለች። በእርግጥም አገልግሎታችን ለእኛም ሆነ ለምንሰብክላቸው ሰዎች ጠቃሚ ነው!

ልጆቻችሁን ስትቀርጹ ለአምላክ እንደምትገዙ አሳዩ

14. ወላጆች ልጆቻቸውን በመቅረጽ ረገድ ውጤታማ ለመሆን ምን ማድረግ አለባቸው?

14 አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የማወቅ ጉጉት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ትሑቶች ናቸው። (ማቴ. 18:1-4) በመሆኑም ጥበበኛ ወላጆች የእውነትን እውቀት በልጆቻቸው ልብና አእምሮ ውስጥ ለመቅረጽ እንዲሁም ልጆቻቸው ለእውነት ፍቅር እንዲያድርባቸው ለመርዳት ይጥራሉ። (2 ጢሞ. 3:14, 15) እርግጥ ነው፣ ወላጆች በዚህ ረገድ እንዲሳካላቸው በቅድሚያ እውነትን በራሳቸው ልብ ውስጥ መቅረጽና በአኗኗራቸው ማሳየት ይኖርባቸዋል። ወላጆች እውነትን በቃል ከመናገር አልፈው በሕይወታቸው ተግባራዊ የሚያደርጉት ከሆነ ልጆቻቸው እውነትን መውደድ ቀላል ይሆንላቸዋል። በተጨማሪም ወላጆቻቸው ተግሣጽ የሚሰጧቸው ስለሚወዷቸው እንደሆነና እንዲህ ያለው ተግሣጽ ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር እንደሚያሳይ ይገነዘባሉ።

15, 16. ወላጆች ልጃቸው ቢወገድ በአምላክ እንደሚታመኑ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

15 አንዳንድ ልጆች፣ ክርስቲያን ወላጆች ቢያሳድጓቸውም እንኳ ከጊዜ በኋላ እውነትን ይተዋሉ አሊያም ይወገዳሉ፤ ይህ ደግሞ ቤተሰቡን በእጅጉ ያሳዝናል። በደቡብ አፍሪካ የምትኖር አንዲት እህት “ወንድሜ ሲወገድ የሞተ ያህል ነበር የተሰማኝ። ልቤ ተሰበረ!” ብላለች። ታዲያ እሷና ወላጆቿ ምን አድርገው ይሆን? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን መመሪያ ተግባራዊ አደረጉ። (1 ቆሮንቶስ 5:11, 13ን አንብብ።) ወላጆቿ እንዲህ ብለዋል፦ “የአምላክን መንገድ መከተል የተሻለ ውጤት እንደሚያስገኝ ስለተገነዘብን የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር ሥራ ላይ ለማዋል ቆርጠን ነበር። ውገዳን ከአምላክ የመጣ ተግሣጽ እንደሆነ አድርገን የተመለከትነው ሲሆን ይሖዋ ተግሣጽ የሚሰጠው በፍቅር ተነሳስቶና በመጠኑ እንደሆነ እምነት ነበረን። በመሆኑም ከልጃችን ጋር የምንነጋገረው የግድ አስፈላጊ የሆነ የቤተሰብ ጉዳይ ሲያጋጥመን ብቻ ነበር።”

16 የተወገደው ልጅ ምን ተሰምቶት ይሆን? “ቤተሰቦቼ እንደማይጠሉኝ ከዚህ ይልቅ ይህን ያደረጉት ይሖዋንና ድርጅቱን ለመታዘዝ ብለው እንደሆነ አውቅ ነበር” በማለት ከጊዜ በኋላ ተናግሯል። አክሎም “የይሖዋን እርዳታና ምሕረት እንድትለምን የሚያስገድድ ሁኔታ ሲያጋጥምህ እሱ ምን ያህል እንደሚያስፈልግህ ትገነዘባለህ” ብሏል። ይህ ወጣት ወደ ክርስቲያን ጉባኤ ሲመለስ ቤተሰቦቹ ምን ያህል ተደስተው እንደሚሆን መገመት ይቻላል! በእርግጥም በመንገዳችን ሁሉ ለአምላክ መመሪያዎች ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ የተሻለ ውጤት እናገኛለን።—ምሳሌ 3:5, 6፤ 28:26

17. ይሖዋን ምንጊዜም መታዘዝ ያለብን ለምንድን ነው? ይህስ የሚጠቅመን እንዴት ነው?

17 ነቢዩ ኢሳይያስ በባቢሎን ምርኮ የነበሩት አይሁዳውያን ንስሐ እንደሚገቡና እንደሚከተለው እንደሚሉ ተንብዮ ነበር፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ። እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።” ከዚያም “በደላችንንም ለዘላለም አታስታውስ። እባክህ ተመልከተን፤ እኛ ሁላችን ሕዝብህ ነንና” ብለው ይሖዋን ይለምኑታል። (ኢሳ. 64:8, 9) እኛም ትሑቶችና ምንጊዜም ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆንን ልክ እንደ ነቢዩ ዳንኤል በይሖዋ ፊት የተወደድን እንሆናለን። ከዚህም በላይ ይሖዋ በቃሉ፣ በመንፈሱና በድርጅቱ አማካኝነት ሁልጊዜ ይቀርጸናል፤ ይህም ወደፊት ፍጹም “የአምላክ ልጆች” ለመሆን ያስችለናል።—ሮም 8:21