በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታስታውሳለህ?

ታስታውሳለህ?

በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በደንብ አንብበሃቸዋል? እስቲ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞክር፦

ይሖዋ የጥንቶቹ እስራኤላውያን ጦርነት እንዲያካሂዱ የፈቀደላቸው ለምን ነበር?

ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ ነው። ሆኖም የክፋትና የጭቆና ድርጊቶች የሕዝቡን ሕልውና ስጋት ላይ ሲጥሉ እስራኤላውያን እንዲዋጉ የፈቀደባቸው ጊዜያት አሉ። በጦርነቱ ላይ ማን መሰለፍ እንዳለበት እንዲሁም ጦርነቱ መቼ መካሄድ እንዳለበት የሚወስነው ግን አምላክ ራሱ ነበር።—w15 11/1 ከገጽ 4-5

ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያገለግሉ ለማሠልጠን ሊወስዷቸው የሚገቡ አስፈላጊ እርምጃዎች የትኞቹ ናቸው?

ወላጆች በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ልጆቻቸውን ሊወዷቸውና ትሕትና በማሳየት ረገድ ምሳሌ ሊሆኗቸው ይገባል። በተጨማሪም ወላጆች አስተዋዮች መሆንና ልጆቻቸውን ለመረዳት መጣር አለባቸው።—w15 11/15 ከገጽ 9-11

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የጴጥሮስ ተተኪ እንደሆኑ ተደርገው መታየት የሌለባቸው ለምንድን ነው?

ማቴዎስ 16:17, 18 ሐዋርያው ጴጥሮስ የክርስቲያን ጉባኤ ራስ እንደሚሆን አይናገርም። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ጴጥሮስ ከሁሉ የላቀ ቦታ እንደሚኖረው አይገልጽም፤ ከዚህ ይልቅ የጉባኤው የማዕዘን ራስ ድንጋይ ኢየሱስ ነው። (1 ጴጥ. 2:4-8)—w15 12/1 ከገጽ 12-14

ከመናገራችን በፊት የትኞቹን ነገሮች ከግምት ማስገባት ይኖርብናል?

አንደበታችንን ለመልካም ነገር ለማዋል የሚከተሉትን ነገሮች ልናስብባቸው ይገባል፦ (1) መቼ እንናገር? (መክ. 3:7)፣ (2) ምን እንናገር? (ምሳሌ 12:18) እንዲሁም (3) እንዴት እንናገር? (ምሳሌ 25:15)—w15 12/15 ከገጽ 19-22

ክርስቲያኖች ሊርቋቸው የሚገቡ ሐቀኝነት የጎደላቸው አንዳንድ ድርጊቶች የትኞቹ ናቸው?

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከመዋሸትም ሆነ የሌሎችን ስም ከማጥፋት ይርቃሉ። ሌሎችን የሚጎዳ የሐሰትና የተንኮል ወሬ አያስተላልፉም፤ በማጭበርበርና በስርቆትም አይካፈሉም።—wp16.1 ገጽ 5

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት “የካህናት አለቆች” እነማን ናቸው?

“የካህናት አለቆች” የሚለው መጠሪያ የሚያገለግለው በክህነት ሥርዓቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያላቸውን ሰዎች ለማመልከት ሳይሆን አይቀርም፤ ከኃላፊነታቸው የወረዱ የቀድሞ ሊቀ ካህናትም በዚህ ስያሜ ይጠሩ ነበር።—wp16.1 ገጽ 10

በመታሰቢያው በዓል ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስድ ሰው ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

ክርስቲያኖች ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስዱ ሰዎች ልዩ አክብሮት አይሰጡም። በትክክል ቅቡዕ የሆነ ክርስቲያን ሌሎች ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት አይፈልግም አሊያም በአምላክ ፊት ያለውን ቦታ ሌሎች እንዲያውቁለት ለማድረግም አይጥርም። (ማቴ. 23:8-12)—w16.01 ከገጽ 23-24

አብርሃም የአምላክ ወዳጅ ለመሆን የበቃው እንዴት እንደሆነ ማወቃችን ምን ያስተምረናል?

አብርሃም ስለ አምላክ እውቀት ነበረው፤ እንዲህ ያለ እውቀት እንዲያካብት የረዳው ሴም ሳይሆን አይቀርም። በተጨማሪም አብርሃም፣ አምላክ ከእሱና ከቤተሰቡ ጋር ከነበረው ግንኙነት በመነሳት ተሞክሮ አካብቶ ነበር። እኛም እውቀትና ተሞክሮ ለማግኘት ጥረት ማድረግ እንችላለን።—w16.02 ከገጽ 9-10

መጽሐፍ ቅዱስ በምዕራፍና በቁጥር የተከፋፈለው እንዴት ነው?

መጽሐፍ ቅዱስን በምዕራፍ የከፋፈለው በ13ኛው መቶ ዘመን የኖረ ስቲቨን ላንግተን የተባለ ቄስ ነው። አይሁዳውያን ገልባጮች የዕብራይስጡን መጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ በቁጥር ከፋፍለውት ነበር፤ በ16ኛው መቶ ዘመን ደግሞ ሮበርት ኤትዬን የተባለ ምሁር የክርስቲያን ቅዱሳን መጻሕፍትን በቁጥር ከፋፈላቸው።—wp16.2 ከገጽ 14-15

ሰይጣን ኢየሱስን ሲፈትነው ወደ ቤተ መቅደሱ የወሰደው ቃል በቃል በአካል ነበር?

በእርግጠኝነት መናገር አንችልም። በማቴዎስ 4:5 እና በሉቃስ 4:9 ላይ የሚገኘው ዘገባ ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደሱ የተወሰደው በራእይ እንደሆነ አሊያም ደግሞ በቤተ መቅደሱ አቅራቢያ ከፍ ያለ ቦታ ላይ ቆሞ እንደነበር የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።—w16.03 ከገጽ 31-32

ክርስቲያናዊው አገልግሎት እንደ ጤዛ የሚሆነው እንዴት ነው?

ጤዛ የሚፈጠረው ቀስ በቀስ ነው፤ መንፈስን ያድሳል እንዲሁም ሕይወትን ያለመልማል። ጤዛ ከአምላክ የተገኘ በረከት ነው። (ዘዳ. 33:13) የአምላክ ሕዝቦች በኅብረት ሆነን የምናከናውነው አገልግሎትም እንዲሁ በረከት ያስገኛል።—w16.04 ገጽ 4