በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው”

“አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው”

“እስራኤል ሆይ ስማ፣ አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።”—ዘዳ. 6:4

መዝሙሮች፦ 138, 112

1, 2. (ሀ) በዘዳግም 6:4 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በስፋት ሊታወቅ የቻለው ለምንድን ነው? (ለ) ሙሴ እነዚህን ቃላት የተናገረው ለምንድን ነው?

አይሁዳውያን ለአምላክ በሚያቀርቡት ልዩ ጸሎት ላይ በዘዳግም 6:4 ላይ የሚገኙትን ስድስት የዕብራይስጥ ቃላት ለበርካታ መቶ ዓመታት ሲደግሙ ኖረዋል። ጸሎቱን በየቀኑ ጠዋትና ማታ ይደግሙታል። ይህ ጸሎት ሽማ ተብሎ ይጠራል፤ ሽማ በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው የመጀመሪያው ቃል ነው። አጥባቂ ሃይማኖተኛ የሆኑ አይሁዳውያን ይህን ጸሎት ሲያቀርቡ፣ አምላክን ብቻ እንደሚያመልኩ መናገራቸው ነው።

2 ሙሴ በዚህ ጥቅስ ላይ ያሉትን ቃላት የተናገረው በ1473 ዓ.ዓ. በሞዓብ ሜዳ ላይ ተሰብስቦ ለነበረው የእስራኤል ብሔር የስንብት ንግግር ባቀረበበት ወቅት ነው። ብሔሩ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሮ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገባበት ጊዜ ተቃርቧል። (ዘዳ. 6:1) ላለፉት 40 ዓመታት እስራኤልን ሲመራ የቆየው ሙሴ፣ ሕዝቡ ከፊቱ የሚጠብቀውን ተፈታታኝ ሁኔታ በድፍረት እንዲጋፈጥ እያበረታታ ነው። እስራኤላውያን በይሖዋ መታመንና አምላካቸው እንደመሆኑ መጠን ለእሱ ታማኝ መሆን ያስፈልጋቸዋል። የሙሴ የመሰናበቻ ንግግር በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን እንደሚችል ጥያቄ የለውም። ሙሴ፣ ይሖዋ ለእስራኤላውያን የሰጣቸውን አሥርቱን ትእዛዛትና ሌሎች ሕግጋት ከጠቀሰ በኋላ በዘዳግም 6:4, 5 ላይ የሚገኘውን ማሳሰቢያ ተናገረ። (ጥቅሱን አንብብ።)

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ የትኞቹን ጥያቄዎች እንመለከታለን?

3 በዚያ ወቅት የተሰበሰቡት እስራኤላውያን አምላካቸው ይሖዋ “አንድ ይሖዋ” መሆኑን ያውቁ እንደነበር ጥርጥር የለውም። ታማኝ የሆኑ እስራኤላውያን የሚያውቁትም ሆነ የሚያመልኩት አንድ አምላክ ብቻ ነው፤ እሱም የአባቶቻቸው ማለትም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የያዕቆብ አምላክ የሆነው ይሖዋ ነው። ይህ ከሆነ ታዲያ ሙሴ፣ አምላካቸው ይሖዋ “አንድ ይሖዋ” መሆኑን መናገር ያስፈለገው ለምንድን ነው? ይሖዋ አንድ መሆኑን መገንዘብ በቁጥር 5 ላይ እንደተገለጸው እሱን በሙሉ ልብ፣ በሙሉ ነፍስና በሙሉ ኃይል ከመውደድ ጋር የሚያያዘው እንዴት ነው? ደግሞስ በዘዳግም 6:4, 5 ላይ የሚገኘው ሐሳብ በዛሬው ጊዜ ላለነው ክርስቲያኖች ምን ትርጉም አለው?

አምላካችን “አንድ ይሖዋ ነው”

4, 5. (ሀ) “አንድ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ ምን ትርጉም አለው? (ለ) ይሖዋ ከአሕዛብ አማልክት የተለየ የሆነው እንዴት ነው?

4 ተወዳዳሪ የሌለው። “አንድ” የሚለው ቃል በዕብራይስጥም ሆነ በሌሎች በርካታ ቋንቋዎች ቁጥርን ብቻ ከማመልከት ያለፈ ትርጉም አለው። ተወዳዳሪ ወይም አቻ የሌለው፣ ብቸኛው የሚል ሐሳብም ሊያስተላልፍ ይችላል። ሙሴ ይህን ያለው ‘አምላክ ሦስትም አንድም ነው’ የሚለው የሐሰት ትምህርት ትክክል እንዳልሆነ ለመግለጽ አይመስልም። ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንዲሁም የአጽናፈ ዓለም ሉዓላዊ ገዢ ነው። እውነተኛው አምላክ እሱ ብቻ ነው፤ እንደ እሱ ያለ ሌላ አምላክ የለም። (2 ሳሙ. 7:22) በመሆኑም ሙሴ፣ እስራኤላውያን ሊያመልኩ የሚገባው ይሖዋን ብቻ እንደሆነ ማሳሰቡ ነበር። በዙሪያቸው እንዳሉት አሕዛብ፣ ተባዕትና እንስት የሆኑ በርካታ አማልክትን ሊያመልኩ አይገባም። ከእነዚህ የሐሰት አማልክት የተወሰኑት፣ አንዳንድ የተፈጥሮ ኃይሎችን እንደሚቆጣጠሩ ይታመን ነበር። ሌሎቹ ደግሞ የአንድ የሐሰት አምላክ የተለያዩ መገለጫዎች ናቸው።

5 ለምሳሌ ያህል፣ ግብፃውያን ራ የተባለውን የፀሐይ አምላክ፣ ነት የተባለችውን የሰማይ አምላክ፣ ጌብ የተባለውን የምድር አምላክ፣ ሃፒ የተባለውን የናይል አምላክና እንደ ቅዱስ የሚታዩ ሌሎች በርካታ እንስሳትን ያመልኩ ነበር። ይሖዋ በአሥሩ መቅሰፍቶች አማካኝነት ከእነዚህ የሐሰት አማልክት አብዛኞቹን አዋርዷቸዋል። ዋነኛው የከነአናውያን አምላክ፣ የመራባት አምላክ የሆነው ባአል ሲሆን ይኸው አምላክ የሰማይ፣ የዝናብና የአውሎ ነፋስ አምላክ እንደሆነም ይታመን ነበር። በተለያዩ ቦታዎች የሚኖሩ ሰዎች፣ ባአል ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ይሰማቸው ነበር። (ዘኁ. 25:3) እስራኤላውያን ግን አምላካቸው ይኸውም “እውነተኛው አምላክ” አንድ ይሖዋ መሆኑን ማስታወስ ነበረባቸው።—ዘዳ. 4:35, 39

6, 7. “አንድ” የሚለው ቃል ምን ሌላ ትርጉም አለው? ይሖዋ “አንድ” መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

6 የማይለዋወጥና ታማኝ። “አንድ” የሚለው ቃል፣ አንድነትን እንዲሁም በዓላማና በድርጊት አንድ መሆንንም ያመለክታል። ይሖዋ በየጊዜው የሚለዋወጥ አምላክ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ታማኝ፣ እምነት የሚጣልበትና እውነተኛ አምላክ ነው። ይሖዋ ለአብርሃም፣ ዘሮቹ ተስፋይቱን ምድር እንደሚወርሱ ቃል የገባለት ሲሆን ይህን ቃሉን ለመጠበቅ አስደናቂ ነገሮችን አከናውኗል። በዚህ መሃል 430 ዓመታት ቢያልፉም ይሖዋ ቃሉን አልለወጠም።—ዘፍ. 12:1, 2, 7፤ ዘፀ. 12:40, 41

7 ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ይሖዋ፣ እስራኤላውያን ምሥክሮቹ እንደሆኑ በተናገረበት ወቅት እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እኔ ምንጊዜም ያው [ነኝ] . . . ከእኔ በፊት አምላክ አልተሠራም፤ ከእኔም በኋላ የለም።” ይሖዋ ዓላማው እንደማይለዋወጥ ለማጉላት ሲል “እኔ ምንጊዜም ያው ነኝ” በማለት አስረግጦ ተናግሯል። (ኢሳ. 43:10, 13፤ 44:6፤ 48:12) በእርግጥም እኛም ሆንን እስራኤላውያን፣ ምንጊዜም የማይለዋወጠውና ታማኝ የሆነው አምላክ አገልጋዮች መሆናችን ምንኛ ታላቅ መብት ነው!—ሚል. 3:6፤ ያዕ. 1:17

8, 9. (ሀ) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ ምን ይጠብቃል? (ለ) ኢየሱስ፣ ሙሴ የተናገረውን ሐሳብ ያጎላው እንዴት ነው?

8 ሙሴ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለው ፍቅር የማይለዋወጥ እንደሆነና ምንጊዜም እንክብካቤ እንደሚያደርግላቸው ለእስራኤላውያን ነግሯቸዋል። ሕዝቡም በምላሹ እሱን ብቻ ማምለክ እንዲሁም ያለ ምንም ገደብ በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸውና ኃይላቸው እሱን መውደድ ይኖርባቸዋል። ወላጆች ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ልጆቻቸውን እንዲያስተምሩ መመሪያ ስለተሰጣቸው ልጆችም ይሖዋን ብቻ ማምለክ ይጠበቅባቸው ነበር።—ዘዳ. 6:6-9

9 የይሖዋ ፈቃድና ዓላማ ስለማይለዋወጥ ዛሬም ቢሆን ከእውነተኛ አገልጋዮቹ የሚጠብቀው ነገር ተመሳሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው። እኛም አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ እሱን ብቻ ማምለክ እንዲሁም በሙሉ ልባችን፣ አእምሯችንና ኃይላችን እሱን መውደድ ይኖርብናል። ኢየሱስ ክርስቶስም ከሁሉ የላቀው ትእዛዝ ይህ እንደሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 12:28-31ን አንብብ።) እንግዲያው “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ” መሆኑን እንደምናምን በተግባር ማሳየት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ይሖዋን ብቻ አምልኩ

10, 11. (ሀ) የምናመልከው ይሖዋን ብቻ ነው ሲባል ምን ማለት ነው? (ለ) በባቢሎን የነበሩት ዕብራውያን ወጣቶች ይሖዋን ብቻ እንደሚያመልኩ ያሳዩት እንዴት ነው?

10 አምላካችን፣ ይሖዋ ብቻ ነው፤ በመሆኑም እሱን ብቻ ልናመልክ ይገባል። እሱን እያመለክን ሌሎች አማልክትንም ማምለክ አሊያም ለእሱ በምናቀርበው አምልኮ ውስጥ የሐሰት ትምህርቶችንና ልማዶችን መቀላቀል አንችልም። ይሖዋን በዓለም ላይ ካሉ በርካታ አማልክት አንዱ እንደሆነ አሊያም ከሌሎች አማልክት ሁሉ የበላይና ኃያል እንደሆነ ብቻ አድርገን ልንመለከተው አይገባም። ሊመለክ የሚገባው ይሖዋ ብቻ ነው።—ራእይ 4:11ን አንብብ።

11 የዳንኤል መጽሐፍ ዳንኤል፣ ሃናንያህ፣ ሚሳኤልና አዛርያስ ስለተባሉ ዕብራውያን ወጣቶች ይተርካል። እነዚህ ወጣቶች ርኩስ የሆኑ ምግቦችን አለመመገባቸው ብቻ ሳይሆን ናቡከደነጾር ላሠራው የወርቅ ምስል ለመስገድ ፈቃደኞች አለመሆናቸውም ይሖዋን ብቻ እንደሚያመልኩ የሚያሳይ ነው። ቅድሚያ የሚሰጡት ለማን እንደሆነ ግልጽ ነበር፤ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ከአቋማቸው ፍንክች ላለማለት ቆርጠው ነበር።—ዳን. 1:1 እስከ 3:30

12. ይሖዋን ብቻ ማምለክ ከፈለግን ልንጠነቀቅበት የሚገባው ጉዳይ ምንድን ነው?

12 ይሖዋን ብቻ ማምለክ ከፈለግን በሕይወታችን ውስጥ ለእሱ ብቻ ልንሰጠው የሚገባውን ቦታ ሌላ ነገር እንዲወስደው ሌላው ቀርቶ እንዲጋራው እንኳ ልንፈቅድ አይገባም። የይሖዋን ቦታ ሊይዙብን የሚችሉት ነገሮች ምንድን ናቸው? ይሖዋ ለእስራኤላውያን አሥርቱን ትእዛዛት ሲሰጥ፣ ከእሱ በቀር ሌሎች አማልክትን እንዳያመልኩና ከማንኛውም ዓይነት የጣዖት አምልኮ እንዲርቁ አዟቸው ነበር። (ዘዳ. 5:6-10) በዘመናችን እንደ ጣዖት የሚመለኩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እነዚህን ነገሮች እንደ ጣዖት እያመለኳቸው እንዳሉ እንኳ ላይገነዘቡ ይችላሉ። የይሖዋ መመሪያዎች ግን አልተለወጡም፤ እሱ አሁንም “አንድ ይሖዋ ነው።” በዛሬው ጊዜ ከጣዖት አምልኮ መራቅ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

13. የትኞቹን ነገሮች ከይሖዋ አስበልጠን ለመውደድ ልንፈተን እንችላለን?

13 በቆላስይስ 3:5 ላይ ክርስቲያኖች ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ልዩ ዝምድና የሚያበላሹ ነገሮችን በተመለከተ ጠንከር ያለ ምክር ተሰጥቷቸዋል። (ጥቅሱን አንብብ።) ስግብግብነት፣ የጣዖት አምልኮ እንደሆነ ተደርጎ መገለጹን ልብ እንበል። እንዲህ የተባለው፣ ሀብታም ለመሆንና የቅንጦት ሕይወት ለመኖር ወይም እንደነዚህ የመሳሰሉ ነገሮችን ለማግኘት ያለን ምኞት ሕይወታችንን ሊቆጣጠረውና ኃያል አምላክ ሊሆንብን ስለሚችል ነው። የጥቅሱን ሙሉ ሐሳብ ስንመለከት፣ እዚያ ላይ የተጠቀሱት የኃጢአት ድርጊቶች በሙሉ ከስግብግብነት ጋር የተያያዙ እንደሆኑ እንረዳለን፤ በመሆኑም እነዚህ ነገሮች እንደ ጣዖት አምልኮ ሊቆጠሩ ይችላሉ። ለእነዚህ ነገሮች ከመጠን ያለፈ ጉጉት ወይም ምኞት ካለን ከአምላክ አስበልጠን ልንወዳቸው እንችላለን። እነዚህ ነገሮች ሕይወታችንን በመቆጣጠር ይሖዋን፣ “አንድ ይሖዋ” አድርገን መመልከታችንን እንድንተው ቢያደርጉን የሚያሳዝን አይሆንም? እንዲህ ያለ ነገር እንዲደርስብን በፍጹም አንፈልግም።

14. ሐዋርያው ዮሐንስ ምን ማሳሰቢያ ሰጥቷል?

14 ሐዋርያው ዮሐንስም ይህንኑ ሐሳብ ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ አንድ ሰው በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች የሚወድ ከሆነ ይኸውም ‘የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት’ ካለው እንዲሁም “ኑሮዬ ይታይልኝ” የሚል ከሆነ “የአብ ፍቅር በውስጡ የለም።” (1 ዮሐ. 2:15, 16) በመሆኑም በዓለም ላይ ያለው መዝናኛና አለባበስ እንዲሁም ዓለማዊ ጓደኞች ልባችንን እየማረኩት መሆን አለመሆኑን ለማረጋገጥ አዘውትረን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ ትምህርት በመከታተል “ታላላቅ ነገሮችን” ለማግኘት የምንጥር ከሆነ ዓለምን እንደምንወድ የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። (ኤር. 45:4, 5) አምላክ ቃል በገባልን አዲስ ዓለም ደፍ ላይ ነን። እንግዲያው ሙሴ የሰጠውን ጠንከር ያለ ምክር ማስታወሳችን በጣም አስፈላጊ ነው! “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ” መሆኑን ከተገነዘብንና ከልባችን ካመንን እሱን ብቻ እናመልከዋለን፤ እንዲሁም ተቀባይነት ባለው መንገድ እናገለግለዋለን።—ዕብ. 12:28, 29

ክርስቲያናዊ አንድነታችንን መጠበቅ

15. ጳውሎስ ክርስቲያኖችን አምላካቸው “አንድ ይሖዋ” ብቻ እንደሆነ ማሳሰብ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

15 “ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው” የሚለው አገላለጽ፣ አገልጋዮቹ ኅብረት እንዲሁም የዓላማ አንድነት እንዲኖራቸው የሚፈልግ መሆኑንም ያስገነዝበናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አይሁዳውያንን፣ ግሪካውያንን፣ ሮማውያንንና ሌሎች ዜጎችን ያቀፈ ነበር። እነዚህ ሰዎች የተለያየ ሃይማኖት፣ ባሕልና ምርጫ ነበራቸው። በዚህም የተነሳ አንዳንዶች አዲሱን የአምልኮ ሥርዓት መከተል ወይም የቀድሞ ልማዶቻቸውን ሙሉ በሙሉ መተው ከብዷቸው ነበር። በመሆኑም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ እነዚህ ክርስቲያኖች አንድ አምላክ ብቻ እንዳላቸው ይኸውም ይሖዋን ብቻ ማምለክ እንደሚገባቸው ማሳሰብ አስፈላጊ እንደሆነ ተሰምቶታል።—1 ቆሮንቶስ 8:5, 6ን አንብብ።

16, 17. (ሀ) በዘመናችን እየተፈጸመ ያለው የትኛው ትንቢት ነው? ይህስ ምን ውጤት አስገኝቷል? (ለ) አንድነታችንን ሊያናጋ የሚችለው ምንድን ነው?

16 በዛሬው ጊዜ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ያለው ሁኔታስ ምን ይመስላል? ነቢዩ ኢሳይያስ “በዘመኑ መጨረሻ” ላይ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች በተራራ ወደተመሰለው ወደ እውነተኛው አምልኮ እንደሚጎርፉ ትንቢት ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች “[ይሖዋ] ስለ መንገዶቹ ያስተምረናል፤ በጎዳናዎቹም እንሄዳለን” ይላሉ። (ኢሳ. 2:2, 3) ይህ ትንቢት ሲፈጸም የማየት አጋጣሚ በማግኘታችን እንዴት ታድለናል! ትንቢቱ በመፈጸሙ ጉባኤዎቻችን የተለያየ ዘር፣ ባሕልና ቋንቋ ያላቸውን ወንድሞችና እህቶች ያቀፉ ሆነዋል፤ ይህም ለይሖዋ ውዳሴ ያመጣል። ይሁንና ይህ ልዩነት አንዳንድ ጊዜ ችግሮች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።

በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ላለው አንድነት አስተዋጽኦ እያደረግክ ነው? (ከአንቀጽ 16-19 ተመልከት)

17 ለምሳሌ ያህል፣ ከአንተ የተለየ ባሕል ላላቸው የእምነት ባልንጀሮችህ ምን አመለካከት አለህ? የአፍ መፍቻ ቋንቋቸው፣ አለባበሳቸው፣ ባሕርያቸው ወይም ምግባቸው አንተ ከለመድከው የተለየ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ወንድሞችና እህቶች ትርቃቸዋለህ? አብዛኛውን ጊዜህን የምታሳልፈው የአንተ ዓይነት አስተዳደግና ባሕል ካላቸው ሰዎች ጋር ነው? አሊያም ደግሞ አንተ ባለህበት ጉባኤና ወረዳ ውስጥ ወይም በቅርንጫፍ ቢሮው ሥር ባሉ ጉባኤዎች ውስጥ የሚያገለግሉት ሽማግሌዎች በዕድሜ ከአንተ የሚያንሱ ወይም የተለየ ባሕልና ዘር ያላቸው ቢሆኑስ? እነዚህ ልዩነቶች በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ሊኖር የሚገባውን አንድነት እንዲያናጉት ትፈቅዳለህ?

18, 19. (ሀ) በኤፌሶን 4:1-3 ላይ ጳውሎስ ምን ምክር ሰጥቷል? (ለ) የጉባኤው አንድነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ምን ማድረግ ይኖርብናል?

18 እንዲህ ዓይነት እንቅፋቶችን ለማስወገድ ምን ሊረዳን ይችላል? የበለጸገች ከተማ በሆነችውና የተለያዩ ዜጎች በሚኖሩባት በኤፌሶን ለነበሩት ክርስቲያኖች ጳውሎስ ከዚህ ጋር በተያያዘ ጠቃሚ ምክር ሰጥቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:1-3ን አንብብ።) ጳውሎስ በመጀመሪያ የጠቀሰው እንደ ትሕትና፣ ገርነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር ያሉትን ባሕርያት እንደሆነ ልብ እንበል። እነዚህ ባሕርያት አንድን ቤት ጸንቶ እንዲቆም ከሚያደርጉት ዓምዶች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ይሁንና አንድ ቤት ጠንካራ ዓምዶች ያሉት መሆኑ ብቻ በቂ አይደለም፤ ቤቱ እያረጀ እንዳይሄድ በየጊዜው መታደስ አለበት። ጳውሎስ፣ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን ምንጊዜም “የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” እንዲያደርጉ አሳስቧቸዋል።

19 እያንዳንዳችን የጉባኤውን አንድነት ለመጠበቅ የበኩላችንን አስተዋጽኦ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለብን መገንዘብ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ጳውሎስ የጠቀሳቸውን እንደ ትሕትና፣ ገርነት፣ ትዕግሥትና ፍቅር ያሉ ባሕርያት ማዳበርና በሕይወታችን ውስጥ ማንጸባረቅ ይኖርብናል። ከዚያም ‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረውን የሰላም ማሰሪያ’ ለማጠናከር ልባዊ ጥረት እናድርግ። በመካከላችን የሚፈጠሩት አለመግባባቶች በአንድ ቤት ላይ እንዳለ ስንጥቅ አንድነታችንን ሊያናጉ ይችላሉ። በመሆኑም ውድ የሆነውን ሰላማችንንና አንድነታችንን መጠበቅ እንድንችል እነዚህን አለመግባባቶች ለመፍታት ጠንክረን መሥራት ይኖርብናል።

20. “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ” መሆኑን እንደተገነዘብን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

20 “አምላካችን ይሖዋ አንድ ይሖዋ ነው።” ይህ ትልቅ ትርጉም ያዘለ ጥቅስ ነው! ይህ ሐሳብ እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲገቡና ምድሪቱን ሲቆጣጠሩ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቷቸዋል። እኛም ይህን ጥቅስ ልብ ማለታችን፣ ከፊታችን የሚጠብቀንን ታላቅ መከራ ለማለፍ የሚያስችል ብርታት እንድናገኝና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለሚኖረው ሰላምና አንድነት አስተዋጽኦ እንድናደርግ ይረዳናል። ይሖዋን በሙሉ ነፍሳችን በመውደድና በማገልገል እንዲሁም በወንድማማች ማኅበራችን መካከል ያለው አንድነት ተጠብቆ እንዲኖር ልባዊ ጥረት በማድረግ፣ እሱን ብቻ ማምለካችንን እንቀጥል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ኢየሱስ በግ እንደሆኑ ለሚፈርድላቸው ሰዎች የተናገረው የሚከተለው ሐሳብ የሚፈጸምበትን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን፦ “እናንተ አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ።”—ማቴ. 25:34