በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይሖዋ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

ይሖዋ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን የሚጠቅመን እንዴት ነው?

“ይሖዋ ሆይ፣ . . . እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።”—ኢሳ. 64:8

መዝሙሮች፦ 89, 26

1. ከሁሉ የላቀው ሸክላ ሠሪ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው?

በ18ኛው መቶ ዘመን በቻይና የተሠራ አንድ የሸክላ የአበባ ማስቀመጫ ኅዳር 2010 በለንደን፣ እንግሊዝ በተካሄደ ጨረታ ላይ 70 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተተምኖለት ነበር። አንድ ሸክላ ሠሪ፣ እንደ ሸክላ አፈር ያለን የትም ቦታ የሚገኝና ርካሽ የሆነ ነገር ውብና ውድ የሆነ ቅርስ አድርጎ ሊሠራው የሚችል መሆኑ አስገራሚ ነው። ይሁንና በችሎታው ከይሖዋ ጋር ሊወዳደር የሚችል ሸክላ ሠሪ የለም። አምላክ በስድስተኛው የፍጥረት ቀን መገባደጃ ላይ “ከምድር አፈር” ፍጹም ሰው ሠራ፤ ከዚያም የእሱን ባሕርያት የማንጸባረቅ ችሎታ ሰጠው። (ዘፍ. 2:7) ከአፈር የተሠራው ይህ ፍጹም ሰው ማለትም አዳም፣ “የአምላክ ልጅ” ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።—ሉቃስ 3:38

2, 3. ንስሐ የገቡት እስራኤላውያን የነበራቸውን ዓይነት አመለካከት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

2 የሚያሳዝነው ግን አዳም በፈጣሪው ላይ በማመፁ የልጅነት መብቱን አጣ። ይሁንና ባለፉት በርካታ ዘመናት የኖሩ እንደ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” የሆኑ የአዳም ዘሮች የአምላክን ሉዓላዊነት መደገፍ መርጠዋል። (ዕብ. 12:1) እነዚህ ሰዎች ለፈጣሪያቸው በትሕትና በመገዛት፣ ከሰይጣን ይልቅ ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ እንዲቀርጻቸው እንዲሁም አባታቸው እንዲሆን እንደሚፈልጉ በተግባር አሳይተዋል። (ዮሐ. 8:44) ለአምላክ ያላቸው ታማኝነት፣ ንስሐ የገቡት እስራኤላውያን የተናገሩትን የሚከተለውን ሐሳብ ያስታውሰናል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ አንተ አባታችን ነህ። እኛ ሸክላ ነን፤ አንተም ሠሪያችን ነህ፤ ሁላችንም የእጅህ ሥራ ነን።”—ኢሳ. 64:8

3 በዛሬው ጊዜ ይሖዋን በመንፈስና በእውነት የሚያመልኩ ሁሉ እንዲህ ዓይነት የትሕትናና የታዛዥነት መንፈስ ለማሳየት ይጥራሉ። ይሖዋን፣ አባታችን ብለው መጥራትና እሱን እንደ ሸክላ ሠሪያቸው ቆጥረው ለእሱ መገዛትን እንደ ታላቅ መብት ይመለከቱታል። አንተስ በአምላክ እጅ ውስጥ እንዳለ ለስላሳ የሸክላ ጭቃ እንደሆንክ ይሰማሃል? በእሱ ፊት ውድ ዕቃ ሆነህ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ? መንፈሳዊ ወንድሞችህንና እህቶችህን አምላክ ገና እየቀረጻቸው እንዳለ ትገነዘባለህ? እንዲህ ዓይነት አመለካከት ማዳበር እንድንችል ይሖዋ ሸክላ ሠሪ በመሆን ከሚያከናውነው ሥራ ጋር በተያያዘ ሦስት ነጥቦችን እንመልከት፦ ይሖዋ የሚቀርጻቸውን ሰዎች የሚመርጠው እንዴት ነው? ይሖዋ ሕዝቡን የሚቀርጸው ለምንድን ነው? እንዲሁም አምላክ ለእሱ የሚገዙትን የሚቀርጸው እንዴት ነው?

ይሖዋ የሚቀርጻቸውን ይመርጣል

4. ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስባቸውን ሰዎች የሚመርጣቸው እንዴት ነው? ምሳሌ ስጥ።

4 ይሖዋ ሰዎችን ሲመለከት ትኩረት የሚሰጠው ለውጫዊ ገጽታቸው አይደለም። ከዚህ ይልቅ ልባቸውን ይኸውም ውስጣዊ ማንነታቸውን ይመረምራል። (1 ሳሙኤል 16:7ለን አንብብ።) አምላክ የክርስቲያን ጉባኤን ሲያቋቁም ያደረገው ነገር ይህን በግልጽ ያሳያል። ከሰብዓዊ አመለካከት አንጻር እምብዛም የማይፈለጉ የሚመስሉ ብዙ ሰዎችን ወደ ራሱና ወደ ልጁ ስቧል። (ዮሐ. 6:44) ‘አምላክን የሚሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ’ የነበረውን ሳኦል የተባለ ፈሪሳዊ እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል። (1 ጢሞ. 1:13) ‘ልብን የሚመረምረው’ አምላክ ሳኦልን ዋጋ እንደሌለው ሸክላ አድርጎ አልቆጠረውም። (ምሳሌ 17:3) ከዚህ ይልቅ ውድ ዕቃ ተደርጎ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ አፈር አድርጎ ተመልክቶታል፤ እንዲያውም “በአሕዛብ እንዲሁም በነገሥታትና በእስራኤል ልጆች ፊት” የሚመሠክር “የተመረጠ ዕቃ” ተብሎ ተጠርቷል። (ሥራ 9:15) በተጨማሪም አምላክ ቀደም ሲል ሰካራሞች፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙና ሌቦች የነበሩ አንዳንድ ሰዎችን “ክቡር ለሆነ አገልግሎት” ሊውሉ እንደሚችሉ ዕቃዎች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ሮም 9:21፤ 1 ቆሮ. 6:9-11) እነዚህ ሰዎች ከአምላክ ቃል ትክክለኛ እውቀት እየቀሰሙና እምነታቸው እያደገ ሲሄድ በይሖዋ ለመቀረጽ ፈቃደኞች ሆነዋል።

5, 6. (ሀ) ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን በክልላችን ውስጥ ለሚገኙት ሰዎች ባለን አመለካከት ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? (ለ) ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ባለን አመለካከት ላይስ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል?

5 እስካሁን የተመለከትናቸው ነጥቦች የሚጠቅሙን እንዴት ነው? ይሖዋ ልብን የማንበብና እሱ የመረጣቸውን ወደ ራሱ የመሳብ ችሎታ እንዳለው ማመናችን፣ በክልላችን ውስጥም ሆነ በጉባኤ ባሉ ሰዎች ላይ ከመፍረድ እንድንቆጠብ ሊያደርገን ይገባል። ማይክል የተባለን ሰው እንደ ምሳሌ እንመልከት። እንዲህ ብሏል፦ “የይሖዋ ምሥክሮች መጥተው ሲያነጋግሩኝ ፊት እነሳቸው ነበር፤ ጨርሶ ከቁብ አልቆጥራቸውም ነበር። ለእነሱ ምንም አክብሮት አልነበረኝም። ከጊዜ በኋላ ግን በሌላ አጋጣሚ ከአንድ ቤተሰብ ጋር ተዋወቅኩ፤ የእነዚህ ሰዎች መልካም ምግባር እጅግ አስደነቀኝ። ውሎ አድሮ እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች መሆናቸውን ሳውቅ በጣም ተገረምኩ! የእነሱ ባሕርይ፣ የይሖዋ ምሥክሮችን የምጠላበትን ምክንያት እንድመረምር አነሳሳኝ። ብዙም ሳይቆይ፣ ለይሖዋ ምሥክሮች ያለኝ ጥላቻ እንዲሁ በአሉባልታ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ተገነዘብኩ፤ ስለ እነሱ በቂ ግንዛቤ አልነበረኝም።” ማይክል እውነቱን ማወቅ ስለፈለገ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተስማማ። ከጊዜ በኋላ የተጠመቀ ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ጀመረ።

6 ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ እንደሚቀርጸን መገንዘባችን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ባለን አመለካከት ላይም ተጽዕኖ ያሳድራል። ለወንድሞችህና ለእህቶችህ የአምላክ ዓይነት አመለካከት አለህ? ገና በመቀረጽ ላይ እንዳሉ አድርገህ ትመለከታቸዋለህ? ይሖዋ የአንድን ሰው ውስጣዊ ማንነት ይመለከታል፤ እንዲሁም በእሱ የተካኑ እጆች ቢቀረጽ ምን ዓይነት ሰው ሊወጣው እንደሚችል ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ሰዎችን ሲመለከት አዎንታዊ ጎናቸው ላይ እንጂ ጉድለታቸው ላይ አያተኩርም፤ ያለባቸው ጉድለት ወደፊት እንደሚወገድ ያውቃል። (መዝ. 130:3) እኛም የወንድሞቻችንን አዎንታዊ ጎን በመመልከት እሱን መምሰል እንችላለን። እንዲያውም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ሲጥሩ አስፈላጊውን ድጋፍ በመስጠት ከታላቁ ሸክላ ሠሪ ጋር መተባበር እንችላለን። (1 ተሰ. 5:14, 15) “ስጦታ” የሆኑት ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ቅድሚያውን መውሰድ ይኖርባቸዋል።—ኤፌ. 4:8, 11-13

ይሖዋ የሚቀርጸን ለምንድን ነው?

7. ይሖዋ የሚሰጠንን ተግሣጽ ከፍ አድርገህ የምትመለከተው ለምንድን ነው?

7 አንዳንዶች ‘ወላጆቼ ለምን ተግሣጽ ይሰጡኝ እንደነበር የገባኝ የራሴን ልጆች ስወልድ ነው’ ሲሉ ሰምተህ ታውቅ ይሆናል። ትልቅ ሰው ስንሆን ለተግሣጽ ያለን አመለካከት ይቀየራል፤ በሌላ አባባል ተግሣጽን ይሖዋ በሚያየው መንገድ ይኸውም የፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገን መመልከት እንጀምራለን። (ዕብራውያን 12:5, 6, 11ን አንብብ።) በእርግጥም ይሖዋ እንደ ልጆቹ አድርጎ ስለሚያየንና ስለሚወደን በትዕግሥት ይቀርጸናል። ጥበበኞችና ደስተኞች እንድንሆን እንዲሁም እሱን እንድንወደው ይፈልጋል። (ምሳሌ 23:15) ይሖዋ እንድንሠቃይም ሆነ ከአዳም በወረስነው ኃጢአት ምክንያት “የቁጣ ልጆች” ሆነን እንድንሞት አይፈልግም።—ኤፌ. 2:2, 3

8, 9. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ምን እያስተማረን ነው? ወደፊትስ ይህ ትምህርት የሚቀጥለው እንዴት ነው?

8 በአንድ ወቅት “የቁጣ ልጆች” ስለነበርን አምላክን የሚያሳዝኑ ብዙ ባሕርያት ነበሩን፤ እንዲያውም አንዳንዶቻችን የአውሬ ዓይነት ባሕርይ ነበረን። ሆኖም ይሖዋ እየቀረጸን በመሆኑ ተለውጠን የበግ ዓይነት ባሕርይ ማሳየት ጀምረናል። (ኢሳ. 11:6-8፤ ቆላ. 3:9, 10) በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ የምንኖረው ይሖዋ እኛን ለመቅረጽ ሲል ባዘጋጀው መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። በዙሪያችን ያለው ዓለም በክፋት የተሞላ ቢሆንም ያለ ስጋት ተረጋግተን እንኖራለን። ፍቅር በሌለበት ቤተሰብ ውስጥ ያደጉ ወንድሞችና እህቶችም በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ እውነተኛ ፍቅር ያገኛሉ። (ዮሐ. 13:35) በተጨማሪም ለሌሎች ፍቅር ማሳየትን ተምረናል። ከሁሉም በላይ፣ ይሖዋን ማወቅና የእሱን አባታዊ ፍቅር ማጣጣም ችለናል።—ያዕ. 4:8

9 በአዲሱ ዓለም ውስጥ ስንኖር ደግሞ መንፈሳዊው ገነት ከሚያስገኛቸው በረከቶች የተሟላ ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ በዚያ ወቅት በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ምድር ወደ ገነትነት ትለወጣለች። ዓለም አቀፍ ተሃድሶ በሚኖርበት በዚያ ጊዜ፣ ይሖዋ የምድርን ነዋሪዎች መቅረጹን የሚቀጥል ሲሆን ከእሱ የሚያገኙት ትምህርት ከምንገምተው በላይ ይሆናል። (ኢሳ. 11:9) በተጨማሪም እሱ የሚሰጠንን ትምህርት መቀበልና ፈቃዱን ሙሉ በሙሉ መፈጸም እንድንችል ይሖዋ አእምሯችንንና አካላችንን ፍጹም ያደርግልናል። እንግዲያው ለይሖዋ መገዛታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ፤ ይህን ስናደርግ ይሖዋ የሚቀርጸን ስለሚወደን መሆኑን እንደተገነዘብን እናሳያለን።—ምሳሌ 3:11, 12

ይሖዋ የሚቀርጸን እንዴት ነው?

10. ኢየሱስ የታላቁን ሸክላ ሠሪ አመለካከት ያንጸባረቀው እንዴት ነው?

10 ጥሩ ችሎታ እንዳለው ሸክላ ሠሪ ሁሉ ይሖዋም ‘የሸክላውን’ ዓይነትና ጥራት ያውቃል፤ በመሆኑም የሚቀርጸው ይህን መሠረት በማድረግ ነው። (መዝሙር 103:10-14ን አንብብ።) በእርግጥም ይሖዋ የእያንዳንዳችንን ድክመት፣ የአቅም ገደብና መንፈሳዊነት ከግምት በማስገባት በግለሰብ ደረጃ ይቀርጸናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ አባቱ ፍጹም ላልሆኑት አገልጋዮቹ ያለውን አመለካከት አንጸባርቋል። የኢየሱስ ሐዋርያት የተለያየ ድክመት ነበራቸው፤ በተለይ ደግሞ ‘ማን ይበልጣል?’ በሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ይከራከሩ ነበር። በሐዋርያቱ መካከል የነበረውን የጦፈ ክርክር ብትመለከት ኖሮ እነዚህን ሰዎች በቀላሉ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ ጭቃ አድርገህ ታያቸው ነበር? ኢየሱስ አሉታዊ አመለካከት አልነበረውም። ታማኝ ሐዋርያቱ እሱ በደግነትና በትዕግሥት የሚሰጣቸውን ምክር ተግባራዊ ቢያደርጉ እንዲሁም በትሕትና ረገድ የተወውን ምሳሌ ቢከተሉ ሊለወጡ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። (ማር. 9:33-37፤ 10:37, 41-45፤ ሉቃስ 22:24-27) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ሐዋርያቱ መንፈስ ቅዱስ የወረደባቸው ሲሆን ስለ ሥልጣን ከማሰብ ይልቅ በሰጣቸው ሥራ ላይ ትኩረት አድርገዋል።—ሥራ 5:42

11. ዳዊት በቀላሉ ሊቀረጽ እንደሚችል የሸክላ ጭቃ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው? እኛስ እሱን ልንመስለው የምንችለው እንዴት ነው?

11 ይሖዋ በዛሬው ጊዜ አገልጋዮቹን በዋነኝነት የሚቀርጻቸው በቃሉ፣ በመንፈስ ቅዱስና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲቀርጸን የምንፈልግ ከሆነ፣ ቃሉን በግብ ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል እንዲሁም ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ እንድንችል ይሖዋ እንዲረዳን መጠየቅ ይኖርብናል። ዳዊት “መኝታዬ ላይ ሆኜ አንተን አስታውሳለሁ፤ ሌሊት ስለ አንተ አሰላስላለሁ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 63:6) በተጨማሪም “ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል” ሲል ጽፏል። (መዝ. 16:7) በእርግጥም ዳዊት አምላክ የሚሰጠው ምክር ከባድ በሚሆንበት ጊዜም እንኳ ምክሩ ወደ ልቡ ዘልቆ እንዲገባ እንዲሁም ውስጣዊ ሐሳቡንና ስሜቱን እንዲቀርጸው ፈቅዷል። (2 ሳሙ. 12:1-13) ዳዊት ትሑትና ታዛዥ በመሆን ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል! አንተስ በአምላክ ቃል ላይ በማሰላሰል ምክሩ ወደ ውስጥህ ዘልቆ እንዲገባ ትፈቅዳለህ? በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚገባህ ይሰማሃል?—መዝ. 1:2, 3

12, 13. ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱና በክርስቲያን ጉባኤ አማካኝነት የሚቀርጸን እንዴት ነው?

12 መንፈስ ቅዱስ በተለያዩ መንገዶች ሊቀርጸን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የክርስቶስን ዓይነት ባሕርያት እንድናዳብር ይረዳናል፤ ከእነዚህ ባሕርያት መካከል የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ይገኙበታል። (ገላ. 5:22, 23) ከመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች አንዱ ፍቅር ነው። አምላክን እንወደዋለን፤ እንዲሁም የአምላክ ትእዛዛት ከባዶች እንዳልሆኑ ስለምንገነዘብ እሱን መታዘዝና በእሱ መቀረጽ እንፈልጋለን። በተጨማሪም ይህ ዓለምም ሆነ የሚያሳድረው መጥፎ መንፈስ እንዳይቀርጸን የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤፌ. 2:2) ሐዋርያው ጳውሎስ ወጣት በነበረበት ጊዜ የሃይማኖት መሪዎቹ የትዕቢት ዝንባሌ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሮበት ነበር፤ ይሁንና መንፈስ ቅዱስ አመለካከቱን እንዲለውጥ ረድቶታል፤ ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ “ኃይልን በሚሰጠኝ በእሱ አማካኝነት ለሁሉም ነገር የሚሆን ብርታት አለኝ” ሲል ጽፏል። (ፊልጵ. 4:13) እኛም እንደ ጳውሎስ፣ ይሖዋ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን አዘውትረን እንጠይቀው። ይሖዋ የዋሆች የሚያቀርቡትን ልባዊ ልመና ይሰማል።—መዝ. 10:17

ይሖዋ እኛን ለመቅረጽ በክርስቲያን ሽማግሌዎች ይጠቀማል፤ ይሁንና እኛም የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ይኖርብናል (አንቀጽ 12, 13ን ተመልከት)

13 ይሖዋ እኛን በግለሰብ ደረጃ ለመቅረጽ በክርስቲያን ጉባኤና በሽማግሌዎች ይጠቀማል። ለምሳሌ ያህል፣ ሽማግሌዎች ከመንፈሳዊነታችን ጋር በተያያዘ የሆነ ችግር እንዳለብን ካስተዋሉ እርዳታ ሊያደርጉልን ይሞክራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን በሰብዓዊ ጥበብ ላይ ተመርኩዘው አይደለም። (ገላ. 6:1) ይልቁንም ትሑት በመሆን አምላክ ማስተዋልና ጥበብ እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ። ከዚያም የእኛን ሁኔታ ግምት ውስጥ አስገብተው በአምላክ ቃልና በክርስቲያናዊ ጽሑፎቻችን ላይ ምርምር በማድረግ ከጸሎታቸው ጋር የሚስማማ እርምጃ ይወስዳሉ። ይህም በግለሰብ ደረጃ የሚያስፈልገንን እርዳታ ለመስጠት ያስችላቸዋል። ሽማግሌዎች ለምሳሌ አለባበስህን በተመለከተ ደግነትና ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር ቢሰጡህ፣ ምክራቸውን የአምላክ ፍቅር መግለጫ እንደሆነ አድርገህ ትመለከተዋለህ? ከሆነ ለስላሳ እንደሆነ የሸክላ ጭቃ በይሖዋ እጅ በቀላሉ ለመቀረጽ ፈቃደኛ ነህ ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ በጣም ይጠቅምሃል።

14. ይሖዋ የሚቀርጸውን ሸክላ እንደፈለገ የማድረግ ሥልጣን ቢኖረውም የመምረጥ ነፃነታችንን እንደሚያከብር የሚያሳየው እንዴት ነው?

14 አምላክ እንዴት እንደሚቀርጸን መገንዘባችን፣ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን ጨምሮ በክልላችን ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። አንድ ሸክላ ሠሪ፣ ያገኘውን የሸክላ አፈር ወስዶ ቅርጽ ለማስያዝ አይሞክርም። ከዚህ ይልቅ በቅድሚያ፣ እንደ ድንጋይ የመሳሰሉ አላስፈላጊ ነገሮችን ከሸክላው አፈር ይለያል። በተመሳሳይም ታላቁ ሸክላ ሠሪ ይሖዋ፣ ለመቀረጽ ፈቃደኛ የሆኑ ግለሰቦችን መቅረጽ እንዲችል ያዘጋጃቸዋል። ለውጥ እንዲያደርጉ አያስገድዳቸውም፤ ይሁንና በፈቃዳቸው ሕይወታቸውን ለመለወጥና ማስተካከያዎችን ለማድረግ እንዲነሳሱ የጽድቅ መሥፈርቶቹን ያሳውቃቸዋል።

15, 16. የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይሖዋ እንዲቀርጻቸው እንደሚፈልጉ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? በምሳሌ አስረዳ።

15 ቴሲ የተባለችን በአውስትራሊያ የምትኖር እህት እንደ ምሳሌ እንመልከት። ቴሲን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናቻት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ቴሲ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት መቀበል ብዙም አልከበዳትም። ይሁንና ይህ ነው የሚባል መንፈሳዊ እድገት አላደረገችም፤ ሌላው ቀርቶ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ እንኳ አትገኝም ነበር! ስለ ጉዳዩ ብዙ ከጸለይኩና ካሰብኩበት በኋላ ጥናቱን ለማቆም ወሰንኩ። በዚህ ጊዜ የሚገርም ነገር ተፈጠረ። ለመጨረሻ ጊዜ ላስጠናት በሄድኩበት ቀን፣ ቴሲ የልቧን አውጥታ አጫወተችኝ። ቁማር መጫወት እንደምትወድና በዚህም ምክንያት ግብዝ እንደሆነች እንደሚሰማት ነገረችኝ። ከዚህ በኋላ ግን ይህን ልማዷን ለመተው እንደወሰነች ገለጸችልኝ።”

16 ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ቴሲ በስብሰባዎች ላይ መገኘትና ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ማዳበር ጀመረች፤ ጓደኞቿ ቢያፌዙባትም እንኳ ወደኋላ አላለችም። ያስጠናቻት እህት እንዲህ ብላለች፦ “ውሎ አድሮ ቴሲ ተጠመቀች፤ ትናንሽ ልጆች ቢኖሯትም እንኳ የዘወትር አቅኚ ሆና ማገልገል ጀመረች።” በእርግጥም አምላክ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እሱን ለማስደሰት አኗኗራቸውን ሲያስተካክሉ ወደ እነሱ የሚቀርብ ከመሆኑም ሌላ እንደ ሸክላ በመቅረጽ ውድ ዕቃ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

17. (ሀ) ይሖዋ እንደ ሸክላ ሠሪ የሚቀርጽህ መሆኑ ምን እንዲሰማህ ያደርግሃል? (ለ) በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 ዛሬም አንዳንድ ሸክላ ሠሪዎች ጭቃውን በእጃቸው በጥንቃቄ በመቅረጽ ውብ የሸክላ ዕቃ ይሠራሉ። በተመሳሳይም ታላቁ ሸክላ ሠሪ፣ በሚሰጠን ምክር አማካኝነት በጥንቃቄና በትዕግሥት ይቀርጸናል፤ እንዲሁም ለምክሩ የምንሰጠውን ምላሽ በትኩረት ይከታተላል። (መዝሙር 32:8ን አንብብ።) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚያስብልህና በጥንቃቄ እየቀረጸህ እንደሆነ ይሰማሃል? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ፣ ምንጊዜም በቀላሉ ሊቀረጽ እንደሚችል ለስላሳ የሸክላ ጭቃ እንድትሆን የሚረዱህ ባሕርያት የትኞቹ ናቸው? ደረቅ እንደሆነና ለመቅረጽ እንደሚያስቸግር የሸክላ ጭቃ እንዳትሆን የትኞቹን ባሕርያት ማስወገድ ይኖርብሃል? ወላጆች ልጆቻቸውን በመቅረጽ ረገድ ከይሖዋ ጋር ተባብረው መሥራት የሚችሉት እንዴት ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።