በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?

ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማሃል?

“ጥሩ መመሪያ እሰጣችኋለሁ።”—ምሳሌ 4:2

መዝሙሮች፦ 93, 96

1, 2. ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነቶችን እንዲቀበሉ ሌሎችን ማሠልጠን ያለብን ለምንድን ነው?

ኢየሱስ ዋነኛ ሥራው የመንግሥቱን ምሥራች ማወጅ ነበር። ይሁንና እረኞችና አስተማሪዎች እንዲሆኑ ሌሎችን ለማሠልጠን ጊዜ መድቧል። (ማቴ. 10:5-7) ፊልጶስ በወንጌላዊነቱ ሥራ ተጠምዶ የነበረ ቢሆንም አራት ሴቶች ልጆቹን፣ ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ለሌሎች በማካፈሉ ሥራ ውጤታማ እንዲሆኑ እንደረዳቸው አያጠራጥርም። (ሥራ 21:8, 9) በዛሬው ጊዜስ እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና መስጠት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?

2 በዓለም ዙሪያ ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ የሚሰጡ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። አዲሶች ገና ከመጠመቃቸውም በፊት መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው የማጥናትን አስፈላጊነት እንዲገነዘቡ ማድረግ ያስፈልጋል። ለሌሎች ምሥራቹን መስበክና እውነትን ማስተማር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ መማርም ይኖርባቸዋል። በጉባኤዎቻችን ውስጥ ያሉ ወንድሞች፣ የጉባኤ አገልጋዮችና ሽማግሌዎች ለመሆን የሚያስፈልጓቸውን ብቃቶች ለማሟላት እንዲጣጣሩ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል። የጎለመሱ ክርስቲያኖች ለአዲሶች “ጥሩ መመሪያ” በመስጠት መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።—ምሳሌ 4:2

አዲሶች ከአምላክ ቃል ብርታትና ጥበብ እንዲያገኙ እርዷቸው

3, 4. (ሀ) ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ማጥናት በአገልግሎት ውጤታማ ከመሆን ጋር ያለውን ተያያዥነት የገለጸው እንዴት ነው? (ለ) ጥናቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው የማጥናት አስፈላጊነት እንዲገባቸው ለመርዳት እኛ ራሳችን ምን ማድረግ ይኖርብናል?

3 ቅዱሳን መጻሕፍትን በግላችን ማጥናት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ በቆላስይስ ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ የጻፈው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል። እንዲህ ብሏል፦ “ከጥበብና ከመንፈሳዊ ግንዛቤ ሁሉ ጋር [በአምላክ ፈቃድ] ትክክለኛ እውቀት ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም፤ ይህም በመልካም ሥራ ሁሉ ፍሬ እያፈራችሁና ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በመቅሰም እያደጋችሁ ስትሄዱ ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንድታስደስቱ ነው።” (ቆላ. 1:9, 10) የቆላስይስ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለውን ትክክለኛ እውቀት መቅሰማቸው ‘ለይሖዋ በሚገባ ሁኔታ እንዲመላለሱና እሱን ሙሉ በሙሉ እንዲያስደስቱ’ ያስችላቸዋል። ይህም “በመልካም ሥራ ሁሉ” በተለይም ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ‘ፍሬ ማፍራታቸውን’ እንዲቀጥሉ ያስችላቸዋል። አንድ የይሖዋ አገልጋይ በአገልግሎቱ ውጤታማ መሆን ከፈለገ በግሉ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ረገድ ጥሩ ልማድ ሊኖረው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ይህን እውነታ እንዲገነዘቡ መርዳታችን አስፈላጊ ነው።

4 ሌሎች መጽሐፍ ቅዱስን በግላቸው የማጥናት አስፈላጊነት እንዲገባቸው ለመርዳት፣ በቅድሚያ እኛ ራሳችን እንዲህ ዓይነቱን ልማድ ማዳበር ያለውን ጥቅም መገንዘብ ይኖርብናል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን የማጥናት ጥሩ ልማድ ሊኖረን ይገባል። ስለሆነም እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘በአገልግሎት የማገኛቸው ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችን ቢጠቅሱ ወይም ከባድ ጥያቄዎችን ቢጠይቁኝ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መልስ መስጠት እችላለሁ? ኢየሱስና ጳውሎስ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች በአገልግሎት እንዴት እንደጸኑ በማነብበት ጊዜ፣ እነሱ ያሳዩት ጽናት እኔም ለይሖዋ በማቀርበው አገልግሎት ረገድ ምን እንዳደርግ ሊያነሳሳኝ እንደሚገባ ቆም ብዬ አሰላስላለሁ?’ ሁላችንም ከአምላክ ቃል የሚገኘው እውቀትና ምክር ያስፈልገናል። መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን በማጥናታችን ምን ያህል እንደተጠቀምን ለሌሎች ከነገርናቸው፣ እነሱም ተመሳሳይ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት ለማጥናት ሊነሳሱ ይችላሉ።

5. አዲሶች በግላቸው መጽሐፍ ቅዱስን የማጥናት ልማድ እንዲያዳብሩ መርዳት የሚቻልባቸውን አንዳንድ መንገዶች ጥቀስ።

5 ‘ጥናቴ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግሉ የማጥናት ልማድ እንዲያዳብር ላሠለጥነው የምችለው እንዴት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። መጀመሪያ፣ ለጥናታችሁ እንዴት መዘጋጀት እንደሚችል አሳየው። ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ ከምታጠኑት ምዕራፍ ጋር ተያያዥነት ያለውን በተጨማሪ ክፍሉ ላይ የሚገኘውን ርዕስ እንዲሁም አንቀጾቹ ውስጥ ያሉትን ጥቅሶች አውጥቶ እንዲያነብ ሐሳብ ልታቀርብለት ትችላለህ። በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ የመስጠት ግብ ይዞ እንዲዘጋጅ እርዳው። በመጠበቂያ ግንብና በንቁ! ላይ የሚወጡትን ርዕሶች በሙሉ እንዲያነብ አበረታታው። ዎችታወር ላይብረሪ፣ የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት ወይም የምርምር መርጃ መሣሪያ ለይሖዋ ምሥክሮች የተባለው ጽሑፍ በቋንቋው የሚገኝ ከሆነ ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎች መልስ ለማግኘት በእነዚህ ዝግጅቶች እንዴት መጠቀም እንደሚችል አሳየው። ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትህ የምታደርግለት እንዲህ ያለው እርዳታ፣ የአምላክን ቃል በግሉ ማጥናት አስደሳች እንዲሆንለት እንደሚረዳው አያጠራጥርም።

6. (ሀ) ጥናትህ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር እንዲያዳብር ልትረዳው የምትችለው እንዴት ነው? (ለ) ጥናታችን ለቅዱሳን መጻሕፍት ልባዊ ፍቅር ካለው ምን ለማድረግ ይነሳሳል?

6 እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያነብና እንዲያጠና ማንንም ማስገደድ የለብንም። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ድርጅት ያዘጋጀልንን መሣሪያዎች በመጠቀም ጥናታችን ለአምላክ ቃል ያለውን ፍቅር እንዲያሳድግ መርዳት እንችላለን። በጊዜ ሂደት፣ ይህ ቅን ልብ ያለው ሰው “ወደ አምላክ መቅረብ ይበጀኛል። . . . ሉዓላዊውን ጌታ ይሖዋን መጠጊያዬ አድርጌዋለሁ” በማለት እንደዘመረው መዝሙራዊ ዓይነት ስሜት ማዳበሩ አይቀርም። (መዝ. 73:28) ጥናታችን ትጋት የተሞላበት ጥረት የሚያደርግ ከሆነና ለአምላክ ቃል አድናቆት ካለው ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ይረዳዋል።

አዲሶች እንዲሰብኩና እንዲያስተምሩ አሠልጥኗቸው

7. ኢየሱስ የምሥራቹ አዋጅ ነጋሪ የሚሆኑ ሰዎችን ያሠለጠነው እንዴት ነው? (በመግቢያው ላይ ያለውን ፎቶግራፍ ተመልከት።)

7 ማቴዎስ ምዕራፍ 10 ላይ ኢየሱስ ለ12 ሐዋርያቱ የሰጠውን መመሪያ እናገኛለን። ኢየሱስ መመሪያ ሲሰጥ እንዲያው በደፈናው ከመናገር ይልቅ ዝርዝር ነጥቦችን ጠቅሷል። [1] ሐዋርያቱም ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዴት መስበክ እንደሚችሉ ኢየሱስ ሲያስተምራቸው በትኩረት ካዳመጡ በኋላ ወደ አገልግሎት ተሰማሩ። ኢየሱስ ሲሰብክ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች መመልከታቸው፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብቃት ያላቸው የቅዱሳን መጻሕፍት አስተማሪዎች እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። (ማቴ. 11:1) እኛም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ምሥራቹን በመስበክ ረገድ ውጤታማ እንዲሆኑ ልናሠለጥናቸው እንችላለን። ይህን ማድረግ የምንችልባቸውን ሁለት መንገዶች እንመልከት።

8, 9. (ሀ) ኢየሱስ በአገልግሎት ላይ ሰዎችን ያነጋግር የነበረው እንዴት ነው? (ለ) አዳዲስ አስፋፊዎች ከሰዎች ጋር በመወያየት ረገድ የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ ማሠልጠን የምንችለው እንዴት ነው?

8 ከሰዎች ጋር መወያየት። ኢየሱስ ብዙ ጊዜ ከሰዎች ጋር ስለ አምላክ መንግሥት ይወያይ ነበር። ለምሳሌ ሲካር ከተማ አቅራቢያ በሚገኘው የያዕቆብ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ካገኛት ሴት ጋር ደስ የሚልና ፍሬያማ የሆነ ውይይት አድርጓል። (ዮሐ. 4:5-30) በሌላ ጊዜ ደግሞ ሌዊ ተብሎ የሚጠራውንና ቀረጥ ሰብሳቢ የነበረውን ማቴዎስን አነጋግሮታል። ኢየሱስ ከማቴዎስ ጋር ስላደረገው ውይይት የወንጌል ዘገባዎች ብዙም ባይነግሩንም ማቴዎስ የኢየሱስ ተከታይ እንዲሆን የቀረበለትን ግብዣ እንደተቀበለ እናውቃለን። በማቴዎስ ቤት ውስጥ በተደረገው ግብዣ ላይ ኢየሱስ ሲናገር ማቴዎስና በቦታው የነበሩ ሌሎች ሰዎች አዳምጠዋል።—ማቴ. 9:9፤ ሉቃስ 5:27-39

9 በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ኢየሱስ፣ ከናዝሬት ለመጡ ሰዎች አሉታዊ አመለካከት የነበረውን ናትናኤልን ወዳጃዊ በሆነ መንገድ አነጋግሮታል። በመሆኑም ናትናኤል አመለካከቱን የቀየረ ሲሆን የናዝሬት ሰው የሆነው ኢየሱስ ስለሚያስተምረው ትምህርት የበለጠ ለማወቅ ወስኗል። (ዮሐ. 1:46-51) ከዚህ ማየት እንደሚቻለው፣ እኛም አዳዲስ አስፋፊዎች ሰዎችን ወዳጃዊ መንፈስ በሚንጸባረቅበትና ዘና ባለ መንገድ እንዲያነጋግሩ ልናሠለጥናቸው ይገባል። [2] በዚህ መንገድ የምናሠለጥናቸው አስፋፊዎች፣ ለሰዎች ልባዊ አሳቢነትና ደግነት ማሳየታቸው ቅን ልብ ያላቸውን ሰዎች እንደሚማርክ ሲመለከቱ መደሰታቸው አይቀርም።

10-12. (ሀ) ኢየሱስ ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግ ምን አድርጓል? (ለ) አዳዲስ አስፋፊዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ረገድ ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?

10 ፍላጎታቸውን ማሳደግ። ኢየሱስ አገልግሎቱን ለማከናወን ያለው ጊዜ ውስን ነበር። ሆኖም ለምሥራቹ ጥሩ ምላሽ የሰጡ ሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግ ጊዜ መድቧል። ኢየሱስ አንድ ጀልባ ላይ ሆኖ ተሰብስበው የነበሩ ሰዎችን ያስተማረበትን ወቅት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በዚያ ወቅት ጴጥሮስን በተአምራዊ መንገድ ብዙ ዓሣ እንዲያጠምድ ከረዳው በኋላ “ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ” ብሎታል። ኢየሱስ የተናገረው ነገርና ድርጊቱ ምን ውጤት አስገኘ? ጴጥሮስና አብረውት የነበሩት ሰዎች “ጀልባዎቹን መልሰው ወደ የብስ ካስጠጉ በኋላ ሁሉን ነገር ትተው [ኢየሱስን] ተከተሉት።”—ሉቃስ 5:1-11

11 የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል የነበረው ኒቆዲሞስ ኢየሱስ የሚያስተምረው ትምህርት ትኩረቱን ስቦት ነበር። ተጨማሪ እውቀት ማግኘት ቢፈልግም በአደባባይ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገር ቢታይ ሰዎች ምን እንደሚሉት በማሰብ ፈርቶ ነበር። ኢየሱስ፣ ሰዎችን በሚመቻቸው ጊዜ ለማነጋገርና ጊዜውን ሳይሰስት ለመስጠት ፈቃደኛ ስለነበር ማታ ላይ ሰው በሌለበት ኒቆዲሞስን አነጋገረው። (ዮሐ. 3:1, 2) ከእነዚህ ዘገባዎች ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን? የአምላክ ልጅ የሰዎችን እምነት ለመገንባት ጊዜ መድቧል። እኛስ ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ ትጉዎች መሆን አይኖርብንም?

12 ከአዳዲስ አስፋፊዎች ጋር በአገልግሎት አብረናቸው ከተካፈልን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በማስተማር ረገድ ክህሎታቸውን እንዲያሻሽሉ መርዳት እንችላለን። መጠነኛ ፍላጎት ላሳዩ ሰዎችም ጭምር ትኩረት እንዲሰጡ መርዳት ይኖርብናል። ተመላልሶ መጠየቅ ስናደርግና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስንመራ አዳዲስ አስፋፊዎች አብረውን እንዲሄዱ መጋበዝም ጠቃሚ ነው። እንዲህ ያለው ሥልጠናና ማበረታቻ፣ ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው አስፋፊዎች የሰዎችን ፍላጎት ለማሳደግና የራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ለመምራት እንዲነሳሱ ያደርጋል። በተጨማሪም ቶሎ ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ ታጋሾች መሆንና በአገልግሎታቸው መጽናት እንዳለባቸው ይማራሉ።—ገላ. 5:22፤ “ ተስፋ አልቆረጠም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

አዲሶች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዲያገለግሉ አሠልጥኗቸው

13, 14. (ሀ) ለሌሎች ሲሉ ብዙ መሥዋዕትነት ስለከፈሉ ሰዎች የሚገልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን ስታነብ ምን ይሰማሃል? (ለ) ወጣቶችና አዳዲስ አስፋፊዎች ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ፍቅር እንዲያሳዩ ማሠልጠን የምትችለው እንዴት ነው?

13 የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች “የወንድማማች መዋደድ” ሊኖረን እንደሚገባና አንዳችን ሌላውን ማገልገል እንዳለብን ጎላ አድርገው ይገልጻሉ። (1 ጴጥሮስ 1:22ን እና ሉቃስ 22:24-27ን አንብብ።) የአምላክ ልጅ፣ ሌሎችን ለማገልገል ሲል ሕይወቱን ጨምሮ ሁሉ ነገሩን ሰጥቷል። (ማቴ. 20:28) ዶርቃ “መልካም በማድረግና ምጽዋት በመስጠት የምትታወቅ” ሴት ነበረች። (ሥራ 9:36, 39) በሮም ትገኝ የነበረችው ማርያም የተባለች እህትም ለጉባኤው ‘ብዙ ደክማለች።’ (ሮም 16:6) ታዲያ አዲሶች፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን መርዳት አስፈላጊ መሆኑን እንዲገነዘቡ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

አዲሶች ለእምነት ባልንጀሮቻቸው ፍቅር እንዲያሳዩ አሠልጥኗቸው (አንቀጽ 13, 14⁠ን ተመልከት)

14 የጎለመሱ ክርስቲያኖች፣ የታመሙና በዕድሜ የገፉ ሰዎችን በሚጠይቁበት ወቅት አብረዋቸው እንዲሄዱ አዲሶችን ሊጋብዟቸው ይችላሉ። ወላጆችም እንዲህ ያሉትን ወንድሞች ለመጠየቅ ሲሄዱ፣ ተገቢ እንደሆነ ከተሰማቸው ልጆቻቸውን ይዘው መሄድ ይችላሉ። ሽማግሌዎች፣ በዕድሜ የገፉ ውድ ወንድሞቻችን ተስማሚ ምግብ እንዲያገኙና ቤታቸው በሚገባ እንዲያዝ ዝግጅት በሚያደርጉበት ጊዜ ሌሎች እንዲያግዟቸው መጠየቅ ይችላሉ። በዚህ መልኩ ወጣቶችና አዲሶች ለሌሎች ደግነት ማሳየት ስለሚቻልባቸው መንገዶች ይማራሉ። አንድ ሽማግሌ ገጠራማ በሆነ ክልል ውስጥ ሲያገለግል በዚያ አካባቢ የሚኖሩ ወንድሞችን ጎራ ብሎ የመጠየቅ ልማድ ነበረው። በዚህም ምክንያት፣ ብዙ ጊዜ አብሮት ያገለግል የነበረ አንድ ወጣት ወንድም ለሁሉም የጉባኤ አባላት ፍቅር ማሳየት እንደሚያስፈልግ ተምሯል።—ሮም 12:10

15. ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ያሉት ወንዶች እድገት እንዲያደርጉ መርዳታቸው አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

15 ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ አስተማሪዎች አድርጎ የሚጠቀመው ወንዶችን እንደመሆኑ መጠን ወንድሞች ንግግር የማቅረብ ችሎታ ማዳበራቸው አስፈላጊ ነው። ሽማግሌ ከሆንክ አንድ የጉባኤ አገልጋይ ንግግር ለማቅረብ ሲለማመድ ልታዳምጠው ትችል ይሆን? የምታደርግለት እርዳታ፣ የአምላክን ቃል የማስተማር ክህሎቱን ለማዳበር ሊረዳው ይችላል።—ነህ. 8:8 [3]

16, 17. (ሀ) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለማሠልጠን ምን አድርጓል? (ለ) ሽማግሌዎች ወደፊት የጉባኤው እረኞች የሚሆኑ ወንድሞችን በሚገባ ማሠልጠን የሚችሉት እንዴት ነው?

16 በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እረኛ ሆነው የሚያገለግሉ ብዙ ወንዶች ያስፈልጋሉ፤ በመሆኑም ወደፊት ይህን ኃላፊነት የሚቀበሉት ወንድሞች ቀጣይ የሆነ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በተናገረው በሚከተለው ሐሳብ ላይ ሥልጠና መስጠት የሚቻልበትን መንገድ ጠቅለል አድርጎ ገልጿል፦ “ልጄ ሆይ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ በሚገኘው ጸጋ አማካኝነት በርታ፤ ከእኔ የሰማኸውንና ብዙዎች የመሠከሩለትን ነገር፣ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች አደራ ስጥ፤ እነሱም በበኩላቸው ሌሎችን ለማስተማር ብቃቱን ያሟላሉ።” (2 ጢሞ. 2:1, 2) ጢሞቴዎስ ሥልጠና ያገኘው በዕድሜ ከሚበልጠው ሐዋርያ ጋር አብሮ በማገልገል ነው። ከዚያም ጢሞቴዎስ ከጳውሎስ የተማረውን ነገር በስብከቱና በሌሎች የቅዱስ አገልግሎት ዘርፎች ተግባራዊ አድርጓል።—2 ጢሞ. 3:10-12

17 ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን በራሱ ይሠልጥን ብሎ አልተወውም። ከዚህ ይልቅ ይህ ወጣት አብሮት እንዲሠራ አድርጓል። (ሥራ 16:1-5) ሽማግሌዎችም እረኝነት ሲያደርጉ፣ ጥሩ ችሎታ ያላቸውን የጉባኤ አገልጋዮች ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ ይዘዋቸው በመሄድ የጳውሎስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ማድረጋቸው፣ የጉባኤ አገልጋዮች ከክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የሚጠበቁትን ባሕርያት ይኸውም የማስተማር ችሎታን፣ እምነትን፣ ትዕግሥትንና ፍቅርን እንዴት ማንጸባረቅ እንደሚቻል ለማየት አጋጣሚ ይሰጣቸዋል። ይህም ወደፊት ‘የአምላክ መንጋ’ እረኞች የሚሆኑት ወንድሞች ተገቢውን ሥልጠና ማግኘት እንዲችሉ አስተዋጽኦ ያበረክታል።—1 ጴጥ. 5:2

ሌሎችን ማሠልጠን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

18. ከይሖዋ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ሌሎችን ለማሠልጠን ትኩረት መስጠት ያለብን ለምንድን ነው?

18 በዚህ የፍጻሜ ዘመን ብዙ አዳዲስ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ ችሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ከዚህም ሌላ ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ ኃላፊነት መሸከም እንዲችሉ መሠልጠን አለባቸው። ኢየሱስና ጳውሎስ ሥልጠና በመስጠት ረገድ የተዉትን ምሳሌ መከተላችን ዛሬም ቢሆን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ፣ በዚህ ዘመን የሚኖሩ አገልጋዮቹ ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት በሚገባ የሠለጠኑ እንዲሆኑ ይፈልጋል። አምላክ፣ ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው ወንድሞች በጉባኤ ውስጥ የሚያስፈልጉትን ሥራዎች መሥራት እንዲችሉ የማሠልጠን መብት ሰጥቶናል። የዓለም ሁኔታ እያሽቆለቆለና መስበክ የምንችልባቸው ተጨማሪ አጋጣሚዎች እየተከፈቱ በሄዱ መጠን ለሌሎች እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና መስጠት ይበልጥ አስፈላጊና አጣዳፊ እንደሚሆን ግልጽ ነው።

19. ሌሎችን ለማሠልጠን የምታደርገው ጥረት ስኬታማ እንደሚሆን እርግጠኛ መሆን የምትችለው ለምንድን ነው?

19 እርግጥ ነው፣ ሰዎችን ማሠልጠን ጊዜና ጥረት ይጠይቃል። ይሁንና እንዲህ ዓይነቱን ሥልጠና ስንሰጥ ይሖዋና ልጁ ይደግፉናል እንዲሁም ጥበብ ይሰጡናል። ሥልጠና የሰጠናቸው ሰዎች ‘ጠንክረው ሲሠሩና ብርቱ ጥረት ሲያደርጉ’ ስናይ ደስታ እናገኛለን። (1 ጢሞ. 4:10) እኛም ለይሖዋ በምናቀርበው ቅዱስ አገልግሎት መንፈሳዊ እድገት ማድረጋችንን እንቀጥል።

^ [1] (አንቀጽ 7) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ (1) የሚሰብኩት መልእክት ምን እንደሆነ፣ (2) አምላክ በሚሰጣቸው ነገሮች መርካት እንዳለባቸው፣ (3) ከቤት ወደ ቤት ሲሄዱ ከሚያገኟቸው ሰዎች ጋር ክርክር ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው፣ (4) ተቃዋሚዎች ሲያጋጥሟቸው በአምላክ መታመን እንደሚያስፈልጋቸውና (5) በፍርሃት መሸነፍ እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል።

^ [2] (አንቀጽ 9) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለው መጽሐፍ ከገጽ 62-64 ላይ በአገልግሎታችን ከሰዎች ጋር መወያየትን በተመለከተ ግሩም ሐሳቦችን ይዟል።

^ [3] (አንቀጽ 15) በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ከሚሰጠው ሥልጠና ተጠቀም የተባለው መጽሐፍ ከገጽ 52-61 ጥሩ ንግግር ለማቅረብ የሚያስፈልጉትን የንግግር ባሕርያት ያብራራል።