የሕይወት ታሪክ
በመስጠት ያገኘሁት ደስታ
ለሌሎች ላካፍለው የምችለው ውድ ነገር እንዳለኝ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገነዘብኩት የ12 ዓመት ልጅ እያለሁ ነው። በአንድ የወረዳ ስብሰባ ላይ አንድ ወንድም መስበክ እፈልግ እንደሆነ ጠየቀኝ። እኔም ከዚያ በፊት ሰብኬ ባላውቅም “አዎ” ብዬ መለስኩለት። ወደ አገልግሎት ክልላችን ከሄድን በኋላ ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጹ ቡክሌቶች ሰጠኝ። ከዚያም “አንተ በመንገዱ ማዶ ያሉትን ቤቶች አንኳኳ፤ እኔ ደግሞ በወዲህ በኩል ያሉትን ሰዎችን አነጋግራለሁ” አለኝ። በፍርሃት ብዋጥም ከቤት ወደ ቤት መሄድ ጀመርኩ፤ የሚገርመው ግን የያዝኳቸውን ቡክሌቶች ብዙም ሳይቆይ አበርክቼ ጨረስኩ። በዚያ ወቅት፣ የምሰብከው መልእክት በጣም ተፈላጊ እንደሆነ ተገነዘብኩ።
በ1923 በቻተም፣ ኬንት፣ እንግሊዝ ውስጥ ተወለድኩ፤ በወቅቱ ብዙ ሰዎች የጠበቁት ሳይፈጸም በመቅረቱ ተስፋ ቆርጠው ነበር። ከታላቁ ጦርነት (አንደኛው የዓለም ጦርነት) በኋላ ዓለም የተሻለች ቦታ እንደምትሆን የተሰጠው ተስፋ እውን ሊሆን አልቻለም። ወላጆቼ፣ የራሳቸውን ጥቅም በማራመድ ላይ ብቻ ባተኮሩት የባፕቲስት ቤተ ክርስቲያን ቀሳውስትም ቅር ተሰኝተው ነበር። ዘጠኝ ዓመት ገደማ ሲሆነኝ እናቴ፣ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ማኅበር (የይሖዋ ምሥክሮች) ወደሚያደርጉት ስብሰባ መሄድ ጀመረች። በዚያ ከነበሩት እህቶች አንዷ፣ ልጆች የሆንነውን ሰብስባ በመጽሐፍ ቅዱስና ዘ ሃርፕ ኦፍ ጎድ በተሰኘው መጽሐፍ ላይ የተመሠረተ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ትሰጠን ነበር። እኔም የተማርኩትን ነገር ወደድኩት።
በዕድሜ ከሚበልጡኝ ወንድሞች መማር
በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ እያለሁ በአምላክ ቃል ላይ የሚገኘውን ተስፋ ለሰዎች መናገር ያስደስተኝ ነበር። ብዙውን ጊዜ ከቤት ወደ ቤት የማገለግለው ብቻዬን ቢሆንም ከሌሎች ጋርም እሰብክ ነበር፤ በዚህ መንገድ ከእነሱ ትምህርት ቀስሜአለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ቀን በዕድሜ ከሚበልጠኝ ወንድም ጋር ወደ ክልላችን በብስክሌት እየሄድን ሳለ በመንገድ ላይ አንድ ቄስ አየን፤ እኔም “ፍየሉን አየኸው?” አልኩት። ወንድም ብስክሌቱን አቆመና አንድ ግንድ ላይ አረፍ እንድንል ጠየቀኝ። ከዚያም “ሰዎችን ፍየል ብለህ ለመፈረጅ ማን ሥልጣን ሰጠህ? ፍርዱን ለይሖዋ እንተወውና ለሰዎች ምሥራቹን በመናገር ደስ ይበለን” አለኝ። በእነዚያ ዓመታት፣ መስጠት ምን ያህል ደስታ እንደሚያስገኝ ተምሬያለሁ።—ማቴ. 25:31-33፤ ሥራ 20:35
በዕድሜ የሚበልጠኝ ሌላ ወንድም ደግሞ በመስጠት ደስታ ለማግኘት አንዳንድ ጊዜ በትዕግሥት መጽናት እንዳለብን አስተምሮኛል። ባለቤቱ የይሖዋ ምሥክሮችን አትወድም ነበር። በአንድ ወቅት ሻይ ሊጋብዘኝ ወደ ቤቱ ይዞኝ ሄደ። ምሥራቹን ለመስበክ በመውጣቱ ባለቤቱ በጣም ስለተናደደች የሻይ ቅጠል ፓኮዎችን ትወረውርብን ጀመር። እሱ ግን ባለቤቱን ከመቆጣት ይልቅ ፈገግ ብሎ የሻይ ቅጠል ፓኮዎቹን ወደ ቦታቸው መለሳቸው። ከዓመታት በኋላ ባለቤቱ ተጠምቃ የይሖዋ ምሥክር በመሆኗ፣ ያሳየው ትዕግሥት ወሮታ አስገኝቶለታል።
ወደፊት ስለተዘረጋልን ተስፋ ለሌሎች የመናገር ፍላጎቴ እየጨመረ በመሄዱ እኔና እናቴ መጋቢት 1940 ዶቨር ውስጥ ተጠመቅን። መስከረም 1939 የ16 ዓመት ልጅ ሳለሁ ብሪታንያ በጀርመን ላይ ጦርነት አወጀች። ሰኔ 1940 በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ቅስማቸው የተሰበረ ወታደሮች በጭነት መኪና ሲያልፉ ደጃፋችን ላይ ሆኜ ተመለከትኳቸው። እነዚህ ወታደሮች ከደንከርክ ጦርነት የተረፉ ነበሩ። ተስፋ እንደቆረጡ ፊታቸው ላይ ይነበብ ስለነበር ‘ስለ አምላክ መንግሥት ብነግራቸው’ ብዬ ተመኘሁ። በዚያው ዓመት መገባደጃ አካባቢ፣ በብሪታንያ ላይ በተደጋጋሚ የቦምብ ጥቃት ይሰነዘር ጀመር። በየምሽቱ የጀርመን ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች በአካባቢያችን እየበረሩ ሲያልፉ እመለከት ነበር። አውሮፕላኖቹ ቦምቡን ሲጥሉ የሚሰማው የፉጨት ድምፅ እንዲሁም ቦምቡ ሲወድቅ የሚሰማው ፍንዳታ በፍርሃት የሚያርድ ነበር። በማግስቱ ከቤት ስንወጣ አንዳንድ አካባቢዎች ሙሉ በሙሉ በቦምብ ወድመው እናያለን። እነዚህን ነገሮች መመልከቴ፣ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ ማድረግ የምችለው በአምላክ መንግሥት ላይ ብቻ እንደሆነ ይበልጥ አስገንዝቦኛል።
በመስጠት ላይ ያተኮረ ሕይወት
ከፍተኛ ደስታ ያገኘሁበትን ሕይወት የጀመርኩት በ1941 ነው። ቻተም ውስጥ በሚገኘው ሮያል ዶክያርድ የተባለ መርከብ የሚሠራና የሚጠግን ድርጅት ውስጥ ተለማማጅ ሆኜ እሠራ ነበር፤ ይህም ብዙ ጥቅማ ጥቅሞች የሚያስገኝ ተፈላጊ ሥራ ነበር። የይሖዋ አገልጋዮች፣ አገራት በሚያደርጉት ጦርነት ላይ መካፈል እንደሌለባቸው ካወቁ ቆይተዋል። በ1941 አካባቢ ደግሞ የጦር መሣሪያ ማምረቻዎች ውስጥ መሥራት እንደሌለብን ተገነዘብን። (ዮሐ. 18:36) የምሠራበት ድርጅት፣ ባሕር ሰርጓጅ መርከቦችን ይሠራ ስለነበረ ሥራዬን ለመልቀቅና የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ። መጀመሪያ የተመደብኩት ካትስዎልድዝ ውስጥ በምትገኝ ሳይረንሴስተር የምትባል ውብ ከተማ ነበር።
አሥራ ስምንት ዓመት ሲሞላኝ በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኔ ለዘጠኝ ወር ታሰርኩ። እስር ቤት እንደገባሁ በሩ ከኋላዬ ሲዘጋና ብቻዬን እንደሆንኩ ሳውቅ በጣም ከፍቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ ዘበኞቹና እስረኞቹ የታሰርኩት ለምን እንደሆነ ይጠይቁኝ ጀመር፤ እኔም በደስታ ስለ እምነቴ እነግራቸው ነበር።
ከእስር ከተፈታሁ በኋላ፣ ከሌነርድ ስሚዝ * ጋር ሆኜ ኬንት በምትባለው ባደግንባት ክልል ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ከተሞች እንድሰብክ ተጠየቅኩ። ከ1944 ወዲህ፣ ፈንጂዎች የጫኑ ከአንድ ሺህ በላይ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በኬንት ወድቀዋል። እኛ የምንኖረው ደግሞ በናዚዎች ቁጥጥር ሥር ባለው የአውሮፓ ክፍል እና በለንደን መካከል ሲሆን አውሮፕላኖቹ የሚያልፉት በዚህ ቀጠና ላይ ነበር። ቦምብ የተሸከሙት እነዚያ አውሮፕላኖች ዱድልበግ ተብለው ይጠሩ ነበር። የእነዚህ አውሮፕላኖች መምጣት በሕዝቡ ላይ ሽብር የሚለቅ ነበር፤ ምክንያቱም የአውሮፕላኑ ሞተር ሲጠፋ ከተሰማ ከጥቂት ሴኮንዶች በኋላ አውሮፕላኑ እንደሚከሰከስና እንደሚፈነዳ ይታወቃል። በዚያ ወቅት አምስት አባላት ያሉትን አንድ ቤተሰብ መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠና ነበር። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ሰዎች ቤት እያለን፣ አውሮፕላኑ ሲወድቅ ቤቱ በላያችን ላይ ቢደረመስ ከሚያደርሰው ጉዳት ለመትረፍ ስንል ከብረት በተሠራ ጠረጴዛ ሥር እንቀመጥ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሁሉም የዚህ ቤተሰብ አባላት ተጠምቀዋል።
ምሥራቹን በሌሎች አገሮች መስበክ
ከጦርነቱ በኋላ ለሁለት ዓመታት በደቡብ አየርላንድ በአቅኚነት አገልግያለሁ። በአየርላንድ ያለው ሁኔታ ከእንግሊዝ የተለየ እንደሆነ አላወቅንም ነበር። ከቤት ወደ ቤት እየሄድን ሚስዮናውያን መሆናችንን በመግለጽ ማረፊያ ቦታ እንዲሰጡን እንጠይቅ ነበር፤ እንዲሁም መጽሔቶቻችንን መንገድ ላይ ለማበርከት እንሞክር ነበር። የካቶሊኮች አገር በሆነችው በአየርላንድ እንዲህ ማድረግ “ሞኝነት” እንደሆነ አልገባንም! አንድ ሰው እንደሚደበድበን ሲዝትብን ለአንድ ፖሊስ አቤቱታ አቀረብኩ፤ እሱ ግን “እና ምን ጠብቀህ ነበር?” አለኝ። ቀሳውስቱ ምን ያህል ተሰሚነት እንዳላቸው አልተገነዘብንም ነበር። ቀሳውስቱ፣ ሰዎች የእኛን መጽሐፍ ከተቀበሉ ከሥራቸው እንዲባረሩ ያደርጋሉ፤ እኛንም ከተከራየነው ቤት እንድንወጣ ያደርጉ ነበር።
ወደ አንድ አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ ስንሄድ፣ ከተከራየነው ቤት ርቆ ወደሚገኝና ቄሱ ወደማያውቀን ቦታ በብስክሌት ሄደን መስበካችን የተሻለ እንደሆነ ብዙም ሳይቆይ ተገነዘብን። በተከራየነው ቤት አቅራቢያ ላሉት ሰዎች የምንሰብክላቸው በመጨረሻ ነበር። ኪልኬኒ ውስጥ ሕዝቡ ጥቃት እንደሚያደርስብን ቢያስፈራራንም አንድን ወጣት በሳምንት ሦስት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ እናስጠና ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር በጣም ስለሚያስደስተኝ፣ በጊልያድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የሚስዮናዊነት ሥልጠና ለማግኘት አመለከትኩ።
ኒው ዮርክ ውስጥ ለአምስት ወራት ሥልጠናውን ወሰድኩ፤ ከዚያም ከጊልያድ ከተመረቅነው መካከል አራታችን በካሪቢያን ባሕር ላይ በሚገኙት ትናንሽ ደሴቶች ላይ እንድናገለግል ተመደብን። ኅዳር 1948 ኒው ዮርክ ሲቲን ለቀን ሲቢያ በምትባል 18 ሜትር ርዝመት ባላት ጀልባ ላይ ተሳፈርን። ከዚያ በፊት በጀልባ ተጉዤ ስለማላውቅ በጣም ጓጉቼ ነበር። ከአራታችን መካከል አንዱ የሆነው ገስት ማኪ፣ ልምድ ያለው የመርከብ ካፒቴን ነበረ። በመሆኑም መርከብ ከመንዳት ጋር በተያያዘ አንዳንድ መሠረታዊ ነገሮችን አስተማረን፤ ለምሳሌ የመርከብ ሸራዎችን መወጠርና ዝቅ ማድረግ፣ በኮምፓስ ተጠቅሞ አቅጣጫችንን ማወቅ እንዲሁም ከነፋሱ አቅጣጫ በተቃራኒ መጓዝ የሚቻልበትን መንገድ አሠልጥኖናል። በጉዟችን ላይ አደገኛ የሆነ ማዕበል ቢያጋጥመንም ጥሩ ልምድ ያለው ገስት ከ30 ቀናት በኋላ ባሃማስ አደረሰን።
‘በደሴቶች ቃሉን አውጁ’
በባሃማስ ትናንሽ ደሴቶች ላይ ለጥቂት ወራት ከሰበክን በኋላ ወደ ሊዋርድ ደሴቶችና ወደ ዊንድዋርድ ደሴቶች ተጓዝን፤ እነዚህ ደሴቶች በፖርቶ ሪኮ አቅራቢያ ከሚገኙት ከቨርጅን ደሴቶች አንስቶ እስከ ትሪኒዳድ ድረስ ባለው 800 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ቦታ ላይ ይገኛሉ። ለአምስት ዓመታት ያህል በዋነኝነት የሰበክነው አንድም የይሖዋ ምሥክር በሌለባቸው ገለልተኛ ደሴቶች ላይ ነው። አንዳንድ ጊዜ ደብዳቤ መላክም ሆነ መቀበል ሳንችል ሳምንታት ያልፉ ነበር። ይሁን እንጂ የይሖዋን ቃል በደሴቶች ላይ ማወጅ በመቻላችን በጣም ደስተኞች ነበርን!—ኤር. 31:10
በአንድ የባሕር ዳርቻ ላይ መልሕቃችንን ስንጥል የመንደሩ ነዋሪዎች ማን እንደሆንን ለማወቅ ስለሚፈልጉ ወደቡ ላይ ይኮለኮላሉ። አንዳንዶቹ ከዚያ በፊት የዚህ ዓይነት ጀልባም ሆነ ነጮችን አይተው አያውቁም። የደሴቶቹ ነዋሪዎች መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ የሚያውቁና ወዳጃዊ የሆኑ ሃይማኖተኛ ሰዎች ነበሩ። ብዙውን ጊዜም አቮካዶና ኦቾሎኒ እንዲሁም ወዲያው ያጠመዱትን ዓሣ ይሰጡን ነበር። ትንሿ ጀልባችን ጠባብ ብትሆንም የምንተኛው፣ ምግባችንን የምናበስለውና ልብሳችንን የምናጥበው እዚያው ነበር።
በጀልባችን ወደ ባሕሩ ዳርቻ ከሄድን በኋላ ቀኑን ሙሉ ለሰዎች ስንሰብክ እንውላለን። የመጽሐፍ ቅዱስ ንግግር እንደሚቀርብ እንነግራቸው ነበር። ከዚያም ደንገዝገዝ ሲል የጀልባዋን ደወል እንደውላለን። ነዋሪዎቹ ሲመጡ ማየት በጣም
የሚያስደስት ነበር። ወደ እኛ ለመምጣት ከኮረብታው ሲወርዱ የፋኖስ መብራቶቻቸው ጭል ጭል የሚሉ ከዋክብት ይመስላሉ። አንዳንድ ጊዜ መቶ ያህል ሰዎች የሚመጡ ሲሆን ጥያቄዎች እየጠየቁን በጣም ያመሹ ነበር። መዘመር ይወዱ ስለነበረ ከመዝሙሮቻችን አንዳንዶቹን በታይፕ ጽፈን እንሰጣቸዋለን። አራታችንም ዜማውን በተቻለን መጠን ጥሩ አድርገን ለመዘመር ስንጥር ሰዎቹም እየተከተሉ ይዘምሩ ነበር፤ ደግሞም ድምፃቸው በጣም ደስ ይላል። ያ ጊዜ በጣም አስደሳች ነበር!አንዳንዶቹ ጥናቶቻችን መጽሐፍ ቅዱስ ካስጠናናቸው በኋላ ሌሎችን ለማስጠናት ስንሄድ እነሱም አብረውን በመጓዝ በጥናቱ ላይ ይገኙ ነበር። በአንድ ቦታ ጥቂት ሳምንታት ካሳለፍን በኋላ ወደ ሌላ ቦታ መሄድ ነበረብን፤ ሆኖም ከምናስጠናቸው መካከል ለእውነት ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች፣ እኛ እስክንመለስ ድረስ ሌሎችን እንዲያስጠኑልን ብዙ ጊዜ እንጠይቃቸዋለን። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ የሰጠናቸውን ኃላፊነት ምን ያህል በቁም ነገር እንደሚመለከቱት ማየት በጣም የሚያስደስት ነበር።
በዛሬው ጊዜ ከእነዚያ ደሴቶች መካከል ብዙዎቹ የቱሪስት መዝናኛዎች ሆነዋል፤ በዚያን ጊዜ ግን ደሴቶቹ ወደ አረንጓዴ የሚወስደው ሰማያዊ መልክ ያላቸው ኩሬዎች፣ አሸዋማ የባሕር ዳርቻዎችና የዘንባባ ዛፎች ያሏቸው ጭር ያሉ ቦታዎች ነበሩ። አብዛኛውን ጊዜ ከአንዱ ደሴት ወደ ሌላው ደሴት በጀልባችን የምንሄደው ማታ ላይ ነበር። ዶልፊኖች እየተጫወቱ በጀልባዋ ግራና ቀኝ የሚዋኙ ሲሆን በዚያ ወቅት የሚሰማው፣ ጀልባችን ውኃውን እየሰነጠቀች ስትጓዝ የሚፈጠረው ድምፅ ብቻ ነበር። የጨረቃዋ ብርሃን ፀጥ ባለው ባሕር ላይ ተንጸባርቆ ሲታይ እስከ አድማስ የተዘረጋ ጎዳና ይመስል ነበር።
በደሴቶቹ ላይ ለአምስት ዓመታት ከሰበክን በኋላ በነፋስ የምትንቀሳቀሰውን ጀልባችንን በሞተር ጀልባ ለመቀየር ወደ ፖርቶ ሪኮ ሄድን። እዚያ ስንደርስ ማክሲን ቦይድ ከምትባል አንዲት ቆንጆ ሚስዮናዊት ጋር ተዋወቅሁና ወደድኳት። ማክሲን ከልጅነቷ ጀምሮ ምሥራቹን በቅንዓት ስትሰብክ ቆይታለች። በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ውስጥ በሚስዮናዊነት ያገለገለች ሲሆን የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆነው መንግሥት በ1950 ከአገር እስኪያስወጣት ድረስ እዚያ ቆይታለች። ከመርከበኞቹ አንዱ እንደመሆኔ መጠን ፖርቶ ሪኮ ውስጥ መቆየት የሚፈቀድልኝ ለአንድ ወር ብቻ ነበር። ብዙም ሳይቆይ በጀልባችን ወደ ደሴቶቹ የምንሄድ ሲሆን በዚያም ለተወሰኑ ዓመታት ልቆይ እችላለሁ። ስለዚህ ‘ይህችን ልጅ የምፈልጋት ከሆነ ቶሎ እርምጃ መውሰድ አለብኝ’ ብዬ አሰብኩ። ከሦስት ሳምንታት በኋላ ለጋብቻ ጥያቄ አቀረብኩላት፤ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ተጋባን። እኔና ማክሲን እዚያው ፖርቶ ሪኮ ውስጥ በሚስዮናዊነት እንድናገለግል ስለተመደብን በአዲሷ ጀልባ ለመጓዝ አጋጣሚ አላገኘሁም።
በ1956 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኜ ጉባኤዎችን መጎብኘት ጀመርን፤ ወንድሞችን መጎብኘት በጣም ያስደስተን ነበር። ብዙዎቹ ወንድሞች ድሆች ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ ፖታላ ፓስቲልዮ በምትባል አንዲት መንደር ውስጥ ብዙ ልጆች ያሏቸው ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰቦች ነበሩ፤ እኔም ዋሽንት የሚመስል የትንፋሽ መሣሪያ እጫወትላቸው ነበር። ከልጆቹ መካከል ኢልዳ የምትባለዋን አብራን መስበክ ትፈልግ እንደሆነ ጠየቅኳት። እሷም “እፈልጋለሁ፤ ግን አልችልም። ምክንያቱም ጫማ የለኝም” አለችኝ። ጫማ ገዛንላትና ከእኛ ጋር መስበክ ጀመረች። ዓመታት ካለፉ በኋላ እኔና ማክሲን በ1972 ብሩክሊን ቤቴልን እየጎበኘን ሳለን በቅርቡ ከጊልያድ ትምህርት ቤት የተመረቀች አንዲት እህት መጥታ አነጋገረችን። በኢኳዶር እንድታገለግል ስለተመደበች ወደዚያ ለመሄድ እየተዘጋጀች ነበር፤ ይህች እህት “አላስታወሳችሁኝም አይደል? በፓስቲልዮ ያገኛችሁኝ ጫማ ያልነበረኝ ልጅ ነኝ” አለችን። ለካስ ኢልዳ ነበረች! እኛም በጣም ከመደሰታችን የተነሳ አለቀስን!
በ1960 በሳንቱርሴ፣ ሳን ሁዋን በሚገኘው የፖርቶ ሪኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ እንድናገለግል ተጠየቅን፤ ቅርንጫፍ ቢሮው የሚገኘው በአንድ አነስተኛ ባለ ሁለት ፎቅ ቤት ላይ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ አብዛኛውን ሥራ የምንሠራው እኔና ሌናርት ጆንሰን ነበርን። ሌናርትና ባለቤቱ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ያገለገሉት የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች ሲሆኑ ወደ ፖርቶ ሪኮ የመጡት በ1957 ነበር። ከጊዜ በኋላ ማክሲን የመጽሔት ኮንትራት ለገቡ ሰዎች መጽሔቶችን በመላኩ ሥራ መካፈል ጀመረች፤ በየሳምንቱ ከአንድ ሺህ በላይ መጽሔቶችን ትልክ ነበር። ማክሲን እነዚያ ሁሉ ሰዎች መንፈሳዊ ምግብ ሲደርሳቸው የሚያገኙትን ጥቅም ስለምታስብ ይህን ሥራ ትወደው ነበር።
የቤቴል ሥራ፣ መስጠትን የሚጠይቅ በመሆኑ እወደዋለሁ። ይሁን እንጂ ተፈታታኝ ሁኔታ የለውም ማለት አይደለም። ለምሳሌ ያህል፣ በ1967 በፖርቶ ሪኮ ባደረግነው የመጀመሪያው ብሔራት አቀፍ ስብሰባ ወቅት ኃላፊነቱ ከብዶኝ ነበር። በዚያን ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ በበላይነት ይከታተል የነበረው ወንድም ናታን ኖር ወደ ፖርቶ ሪኮ መጥቶ ነበር። ወደ ስብሰባው ለሚመጡት ሚስዮናውያን የመጓጓዣ ዝግጅት አድርጌ የነበረ ቢሆንም ወንድም ኖር ይህን ሳላደርግ የቀረሁ መስሎት ነበር። በኋላ ላይ፣ ነገሮችን በተደራጀ መልክ ስለማከናወን ጠንከር ያለ ምክር የሰጠኝ ሲሆን እንዳዘነብኝ ነገረኝ። ከእሱ ጋር
መከራከር አልፈለግኩም፤ ይሁን እንጂ በተሳሳተ መንገድ እንደተረዳኝ ስለተሰማኝ ለተወሰነ ጊዜ ቅር ተሰኝቼ ነበር። እኔና ማክሲን ከወንድም ኖር ጋር በሌላ ጊዜ ስንገናኝ ግን ክፍሉ ጋብዞን ምግብ ሠራልን።ፖርቶ ሪኮ እያለን እንግሊዝ የሚኖሩትን ቤተሰቦቼን በተለያየ ጊዜ እየሄድን ጠይቀናቸዋል። እኔና እናቴ እውነትን በተቀበልንበት ጊዜ አባቴ እውነትን አልተቀበለም ነበር። ይሁን እንጂ ከቤቴል የመጡ ተናጋሪዎች በሚጎበኟቸው ጊዜ እናቴ በአብዛኛው እኛ ቤት እንዲያርፉ ታደርግ ነበር። አባቴ ከቤቴል የመጡት እነዚህ የበላይ ተመልካቾች፣ ከብዙ ዓመታት በፊት ቅር ካሰኙት ቀሳውስት ጋር ሲነጻጸሩ ምን ያህል ትሑቶች እንደሆኑ አስተዋለ። በመጨረሻም በ1962 ተጠምቆ የይሖዋ ምሥክር ሆነ።
ውዷ ባለቤቴ ማክሲን በ2011 በሞት አንቀላፋች። በትንሣኤ ከእሷ ጋር እንደገና የምገናኝበትን ጊዜ የምጠብቀው በናፍቆት ነው። ያንን ጊዜ ሳስበው ደስ ይለኛል! ከማክሲን ጋር ባሳለፍናቸው 58 ዓመታት ውስጥ በፖርቶ ሪኮ ያሉት የይሖዋ ሕዝቦች ቁጥር ከ650 ተነስቶ 26,000 ሲደርስ ተመልክተናል! በ2013 የፖርቶ ሪኮ ቅርንጫፍ ቢሮ ከዩናይትድ ስቴትስ ቅርንጫፍ ቢሮ ጋር ስለተዋሃደ በዎልኪል፣ ኒው ዮርክ እንዳገለግል ተጠየቅኩ። በደሴቷ ላይ 60 ዓመታት ስለኖርኩ፣ ኮኪ እንደተባለውና ምሽት ላይ ኮኪ ኮኪ እያለ እንደሚዘምረው የፖርቶ ሪኮ እንቁራሪት ሁሉ እኔም የዚያ አገር ተወላጅ የሆንኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ያም ሆኖ ወደ ሌላ ምድብ መሄድ ነበረብኝ።
‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ይወዳል’
አሁንም ቢሆን በቤቴል አምላክን ማገልገል ደስ ይለኛል። አሁን ከ90 ዓመት በላይ ሆኖኛል፤ ሥራዬ በቤቴል ውስጥ የቤተሰቡን አባላት በመንፈሳዊ ማበረታታት ነው። ወደ ዎልኪል ከመጣሁ ወዲህ ከ600 የሚበልጡ ቤቴላውያንን እንደጎበኘሁ ተነግሮኛል። እኔ ጋ ከሚመጡት ቤቴላውያን አንዳንዶቹ በግላቸው ወይም በቤተሰባቸው ውስጥ ስላጋጠማቸው ችግር መወያየት ይፈልጋሉ። በቤቴል አገልግሎታቸው እንዲሳካላቸው ምክር የሚጠይቁኝም አሉ። በቅርብ የተጋቡ ሌሎች ደግሞ ስለ ትዳር ምክር እንድሰጣቸው ይፈልጋሉ። አንዳንዶች በመስክ ላይ እንዲያገለግሉ ተመድበዋል። ሊያነጋግሩኝ የሚመጡትን ሁሉ አዳምጣቸዋለሁ፤ ተገቢ በሚሆንበት ጊዜም እንዲህ እላቸዋለሁ፦ “‘አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ይወዳል።’ ስለዚህ በሥራችሁ ደስ ይበላችሁ። ምክንያቱም የምትሠሩት ለይሖዋ ነው።”—2 ቆሮ. 9:7
በቤቴልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ደስተኛ ሆናችሁ መኖር ከፈለጋችሁ፣ እየሠራችሁ ያላችሁት ሥራ አስፈላጊ የሆነው ለምን እንደሆነ ማስታወስ ይኖርባችኋል። በቤቴል የምንሠራው ማንኛውም ሥራ ቅዱስ አገልግሎት ነው። “ታማኝና ልባም ባሪያ” ለዓለም አቀፉ የወንድማማች ማኅበር መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት እናንተም የበኩላችሁን አስተዋጽኦ ታደርጋላችሁ። (ማቴ. 24:45) ይሖዋን የምናገለግለው የትም ይሁን የት፣ እሱን ለማወደስ የሚያስችሉን አጋጣሚዎች አሉን። “አምላክ በደስታ የሚሰጠውን ሰው ስለሚወድ” ይሖዋ የሚጠይቀንን ነገር በደስታ እናከናውን።
^ አን.13 የሌነርድ ስሚዝ የሕይወት ታሪክ በሚያዝያ 15, 2012 መጠበቂያ ግንብ ላይ ወጥቷል።