በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የአንባቢያን ጥያቄዎች

የኢየሱስ ተቃዋሚዎች ለእጅ መታጠብ ትልቅ ቦታ ይሰጡ የነበረው ለምንድን ነው?

የኢየሱስ ጠላቶች በእሱና በደቀ መዛሙርቱ ላይ ጥፋት ከሚፈላልጉባቸው በርካታ ጉዳዮች መካከል አንዱ ይህ ነበር። የሙሴ ሕግ አንድን ሰው የሚያረክሱት ነገሮች ምን እንደሆኑ ይዘረዝራል፤ ከእነዚህ መካከል ከሰውነት የሚወጡ ፈሳሾች፣ የሥጋ ደዌ በሽታ እንዲሁም የሰዎችን ወይም የእንስሳት አስከሬኖችን መንካት ይገኙበታል። በተጨማሪም ሕጉ ከርኩሰት መንጻት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ መመሪያዎችን ይዟል። ይህ የመንጻት ሥርዓት መሥዋዕት በማቅረብ፣ በመታጠብ ወይም ውኃ በመርጨት ሊፈጸም ይችላል።—ዘሌ. ከምዕ. 11 እስከ 15፤ ዘኁ. ምዕ. 19

አይሁዳውያን ረቢዎች በእነዚህ ሕጎች ላይ ብዙ ዝርዝር ማብራሪያ ይሰጡ ነበር። አንድ ጽሑፍ እንደገለጸው፣ አንድን ሰው ሊያረክሰው የሚችለው ነገር ምን እንደሆነ እንዲሁም ግለሰቡ ሌሎች ሰዎችን ሊያረክስ የሚችለው እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ተጨማሪ ሕግ አውጥተው ነበር። ከዚህም ሌላ ሊረክሱ የሚችሉና የማይችሉ ዕቃዎች የትኞቹ እንደሆኑ እንዲሁም የመንጻት ሥርዓት የሚካሄድበት መንገድና ለመንጻት የሚያስፈልጉት ነገሮች ምን እንደሆኑ የሚገልጹ ደንቦች ነበሯቸው።

የኢየሱስ ተቃዋሚዎች “ደቀ መዛሙርትህ የአባቶችን ወግ ከመከተል ይልቅ በረከሰ እጅ የሚበሉት ለምንድን ነው?” ብለው ጠይቀውት ነበር። (ማር. 7:5) እነዚህ ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ያሳሰባቸው አንድ ሰው ንጽሕናውን ለመጠበቅ ሲል እጁን የመታጠቡ ጉዳይ አልነበረም። ረቢዎች ምግብ ከመብላታቸው በፊት ሌላ ሰው ውኃ እያፈሰሰላቸው እጃቸውን የመታጠብ ልማድ ነበራቸው። ከላይ የተጠቀሰው ጽሑፍ አክሎ እንዲህ ብሏል፦ “ውኃውን ለማፍሰስ ስለሚያገለግለው ዕቃ፣ ስለ ውኃው ዓይነት፣ ስለሚያስታጥባቸው ሰው እንዲሁም እጃቸውን እስከ የት ድረስ መታጠብ እንዳለባቸው የተለያየ አመለካከት አላቸው።”

ኢየሱስ ሰዎች ያወጧቸውን እንዲህ ያሉትን ሕጎች አስመልክቶ ያለው አቋም ግልጽ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩት የሃይማኖት መሪዎች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ኢሳይያስ፣ ግብዞች ስለሆናችሁት ስለ እናንተ በትክክል ተንብዮአል፤ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፦ ‘ይህ ሕዝብ በከንፈሩ ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ [ከይሖዋ] እጅግ የራቀ ነው። የሚያስተምሩት የሰውን ሥርዓት ስለሆነ እኔን የሚያመልኩት በከንቱ ነው።’ የአምላክን ትእዛዝ ትታችሁ የሰውን ወግ አጥብቃችሁ ትከተላላችሁ።”—ማር. 7:6-8