በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዮሐንስ ራውተ በመስክ አገልግሎት ላይ (በ1920ዎቹ ውስጥ ሳይሆን አይቀርም)

ከታሪክ ማኅደራችን

‘ለይሖዋ ውዳሴ ማቅረብ’

‘ለይሖዋ ውዳሴ ማቅረብ’

“በአሁኑ ወቅት በአውሮፓ እየተካሄደ ካለው ታላቅ ውጊያ አንጻር ከዚህ በፊት የተከናወኑት ጦርነቶች በሙሉ ከቁጥር የሚገቡ አይደሉም።” የመስከረም 1, 1915 መጠበቂያ ግንብ አንደኛው የዓለም ጦርነትን የገለጸው በዚህ መንገድ ነበር፤ ውሎ አድሮ 30 የሚያህሉ አገሮች በዚህ ጦርነት ተካፍለዋል። በወቅቱ በነበረው ጦርነት የተነሳ “[የመንግሥቱ] አገልግሎት፣ በተለይም በጀርመንና በፈረንሳይ በተወሰነ ደረጃ ተስተጓጉሏል” በማለት የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ሪፖርት አድርጎ ነበር።

መላውን ዓለም ባናወጠው በዚህ ጦርነት ወቅት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ክርስቲያናዊ የገለልተኝነት አቋም ምን እንደሚያካትት ሙሉ በሙሉ ግልጽ አልሆነላቸውም ነበር። ይሁን እንጂ ምሥራቹን ለማወጅ ቆርጠው ነበር። ቪልሄልም ሂልደብራንት፣ በአምላክ መንግሥት አገልግሎት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማበርከት ስለፈለገ ዘ ባይብል ስቱደንትስ መንዝሊ የተባለው ትራክት በፈረንሳይኛ እንዲላክለት ጠየቀ። ቪልሄልም ወደ ፈረንሳይ የሄደው ኮልፖርተር (የሙሉ ጊዜ ሰባኪ) ሆኖ ለማገልገል ሳይሆን የጀርመን ወታደር ሆኖ ነበር። ፈረንሳይ ውስጥ እንደ ጠላት የሚቆጠረው ቪልሄልም፣ የወታደር የደንብ ልብሱን ለብሶ መንገድ ላይ ለሚያገኛቸው ፈረንሳውያን የሰላም መልእክት የያዘ ጽሑፍ ይሰጥ ነበር፤ እነሱም በአግራሞት ይመለከቱት ነበር።

በመጠበቂያ ግንብ ላይ የታተሙ ደብዳቤዎች እንደሚያሳዩት ጀርመናዊ የሆኑ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጦር ሠራዊቱ ውስጥ እያገለገሉ የመንግሥቱን ምሥራች መስበክ ይፈልጉ ነበር። በባሕር ኃይል ውስጥ ያገለግል የነበረው ወንድም ሌምኪ፣ አብረውት ከሚሠሩት ሰዎች መካከል አምስቱ ምሥራቹን እንደተቀበሉ ሪፖርት አድርጓል። በጦር መርከብ ላይ እየሠራም እንኳ ‘ለይሖዋ ውዳሴ ማቅረብ’ እንደቻለ ጽፏል።

ጌኦርግ ካይዘር ወደ ጦር ግንባር ሲሄድ ወታደር የነበረ ቢሆንም ሲመለስ የእውነተኛው አምላክ አገልጋይ ሆኖ ነበር። እንዴት? የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ጽሑፍ አግኝቶ የመንግሥቱን እውነት በሙሉ ልቡ ስለተቀበለ መዋጋቱን አቆመ። ከዚያም በጦርነቱ በቀጥታ መካፈል የማይጠይቅ ሥራ መሥራት ጀመረ። ከጦርነቱ በኋላ ለብዙ ዓመታት ቀናተኛ አቅኚ ሆኖ አገልግሏል።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ የገለልተኝነት ጉዳይ በደንብ ባይገባቸውም አመለካከታቸውና ምግባራቸው ጦርነቱን በደስታ ከተቀበሉት ሰዎች በጣም የተለየ ነበር። በወቅቱ ፖለቲከኞችና የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ጦርነቱን ቢደግፉም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የሚደግፉት ‘የሰላሙን መስፍን’ ነበር። (ኢሳ. 9:6) አንዳንድ ወንድሞች የገለልተኝነት አቋማቸውን ሙሉ በሙሉ ባይጠብቁም እንኳ ኮንራት መርተ የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የያዘው ዓይነት አቋም ነበራቸው፤ ኮንራት “አንድ ክርስቲያን መግደል እንደሌለበት የአምላክ ቃል በግልጽ አስገንዝቦኛል” ብሎ ነበር።—ዘፀ. 20:13 *

ሀንስ ህልተሆፍ ዘ ጎልደን ኤጅ የተባለውን መጽሔት ለማስተዋወቅ በዚህ ጋሪ ተጠቅሟል

በወቅቱ በጀርመን፣ ወታደራዊ አገልግሎት ለመስጠት ሕሊናው የማይፈቅድለት ሰው ከውትድርና አገልግሎት ነፃ መሆን የሚችልበት ዝግጅት አልነበረም፤ በዚያ የሚኖሩ ከ20 የሚበልጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በማንኛውም ወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገለጹ። በመሆኑም አንዳንዶቹ የአእምሮ ሕሙማን እንደሆኑ ተቆጥረው ነበር። ጉስታፍ ኩያትን እንደ ምሳሌ መውሰድ ይቻላል፤ ጉስታፍ ወደ አእምሮ ሕክምና ተቋም እንዲገባ ከተደረገ በኋላ ለአእምሮ ሕሙማን የሚሆን መድኃኒት ተሰጥቶታል። እንዲሁም ሀንስ ህልተሆፍ በውትድርና ለማገልገል ፈቃደኛ አለመሆኑን በመግለጹ እስር ቤት ገባ፤ በዚያም ቢሆን ከጦርነቱ ጋር የሚያያዝ ማንኛውንም ነገር ለመሥራት ፈቃደኛ አልሆነም። በዚህ ምክንያት ጠባቂዎቹ እንዳይንቀሳቀስ ጥፍር አድርገው አስረው ስላቆዩት እጅና እግሩ ደንዝዞ ነበር። ጠባቂዎቹ ይህን ሁሉ አድርገውበትም በአቋሙ መጽናቱን ሲያዩ የሚገድሉት በማስመሰል ሊያስፈራሩት ሞከሩ። ይሁን እንጂ ሀንስ እስከ ጦርነቱ ማብቂያ ድረስ በታማኝነት ጸንቷል።

ለውትድርና የተመለመሉ ሌሎች ወንድሞችም የጦር መሣሪያ ለመታጠቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን የገለጹ ሲሆን በሠራዊቱ ውስጥ በቀጥታ መዋጋትን የማይጠይቅ ሥራ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ነበር። * ዮሐንስ ራውተ እንዲህ ዓይነት አቋም በመውሰዱ በባቡር ጣቢያ ውስጥ እንዲሠራ ተላከ። ኮንራት መርተ ሆስፒታል ውስጥ ተላላኪ እንዲሆን፣ ራይንሆልት ቬበር ደግሞ ነርስ ሆኖ እንዲሠራ ተመደቡ። ኦገስት ክራፍቺክ፣ ወደ ጦር ግንባር ከመሄድ ይልቅ ሻንጣዎችን ከመሸከም ጋር የተያያዘ ሥራ እንዲያከናውን ስለተመደበ ደስ ብሎት ነበር። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችም ሆኑ እንደ እነሱ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖች፣ ይሖዋን ስለመውደድና ለእሱ ታማኝ ስለመሆን በተረዱት መጠን አምላክን ለማገልገል ቆርጠው ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጦርነቱ ወቅት በነበራቸው አቋም የተነሳ ባለሥልጣናቱ በጥብቅ ይከታተሏቸው ጀመር። በቀጣዮቹ ዓመታት በጀርመን የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች፣ በስብከት ሥራቸው ምክንያት በፍርድ ቤት በሺዎች የሚቆጠሩ ክሶች ተመሥርተውባቸው ነበር። በጀርመን የነበረው ቅርንጫፍ ቢሮ እነዚህን ክርስቲያኖች ለመርዳት፣ በማግደቡርግ በነበረው ቤቴል አንድ የሕግ ክፍል አቋቁሞ ነበር።

የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ክርስቲያናዊ ገለልተኝነት ያላቸው ግንዛቤ ቀስ በቀስ ተስተካክሏል። ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፈነዳበት ወቅት ከጦር ሠራዊቱ ጋር የተያያዘ ምንም ዓይነት ሥራ ባለመሥራት የገለልተኝነት አቋማቸውን ጠብቀዋል። በዚህ የተነሳ የጀርመን መንግሥት ጠላቶች እንደሆኑ ተደርገው የታዩ ሲሆን ከባድ ስደት ደርሶባቸዋል። “ከታሪክ ማኅደራችን” የተባለው ይህ አምድ ወደፊት ይህን የተመለከተ ዘገባ ይዞ ይወጣል።—በመካከለኛ አውሮፓ ካለው የታሪክ ማኅደራችን

^ አን.7 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በብሪታንያ ስለነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ለማወቅ፣ በግንቦት 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ላይ የወጣውን “ከታሪክ ማኅደራችን—‘በፈተና ሰዓት’ በአቋማቸው ጸንተዋል” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 ሚሌኒያል ዶውን ጥራዝ 6 (1904) እና የነሐሴ 1906 የጽዮን መጠበቂያ ግንብ የጀርመንኛ እትም ላይ ክርስቲያኖች እንዲህ ማድረግ እንደሚችሉ የሚገልጽ ሐሳብ ወጥቶ ነበር። የመስከረም 1915 መጠበቂያ ግንብ ላይ ግን ይህ ትምህርት ማስተካከያ የተደረገበት ሲሆን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በጦር ሠራዊት ውስጥ ከመግባት እንዲቆጠቡ ሐሳብ ቀርቦላቸው ነበር። ይሁን እንጂ ይህ ርዕስ በጀርመንኛው እትም ላይ አልወጣም።