በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 32

በትሕትና እና ልክህን በማወቅ ከአምላክህ ጋር ሂድ

በትሕትና እና ልክህን በማወቅ ከአምላክህ ጋር ሂድ

“ልክህን አውቀህ ከአምላክህ ጋር [ሂድ]!”—ሚክ. 6:8

መዝሙር 31 ከአምላክ ጋር ሂድ!

ማስተዋወቂያ *

1. ዳዊት የይሖዋን ትሕትና በተመለከተ ምን ብሏል?

ይሖዋ ትሑት እንደሆነ መናገር እንችላለን? አዎን። በአንድ ወቅት ዳዊት “የመዳን ጋሻህን ትሰጠኛለህ፤ ትሕትናህም ታላቅ ያደርገኛል” ብሎ ነበር። (2 ሳሙ. 22:36፤ መዝ. 18:35) ዳዊት ይህን ሲጽፍ፣ ነቢዩ ሳሙኤል የእስራኤል ንጉሥ የሚሆነውን ሰው ለመቀባት ወደ ቤታቸው የመጣበትን ቀን አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ከስምንት ወንዶች ልጆች የመጨረሻው ነበር፤ ሆኖም በንጉሥ ሳኦል ቦታ እንዲነግሥ ይሖዋ የቀባው እሱን ነበር።—1 ሳሙ. 16:1, 10-13

2. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

2 አንድ መዝሙራዊ ስለ ይሖዋ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ሰማይንና ምድርን ለማየት ወደ ታች ያጎነብሳል፤ ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል። ድሃውን . . . ብድግ ያደርገዋል፤ ይህም ከታላላቅ ሰዎች . . . ጋር ያስቀምጠው ዘንድ ነው።” ዳዊት ከዚህ መዝሙራዊ ጋር እንደሚስማማ ጥርጥር የለውም። (መዝ. 113:6-8) በዚህ ርዕስ ላይ፣ ይሖዋ ትሕትና ያሳየባቸውን ሁኔታዎች በመመርመር ስለዚህ ባሕርይ የምናገኛቸውን አንዳንድ ጠቃሚ ትምህርቶች እንመለከታለን። ከዚያም ልክን ማወቅን በተመለከተ ከንጉሥ ሳኦል፣ ከነቢዩ ዳንኤልና ከኢየሱስ የምናገኘውን ትምህርት እንመረምራለን።

ይሖዋ ከተወው ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን?

3. ይሖዋ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን የሚይዘው እንዴት ነው? ይህስ ምን ያረጋግጣል?

3 ይሖዋ ፍጹማን ያልሆኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን የያዘበት መንገድ ትሑት መሆኑን ያረጋግጣል። እሱን እንድናመልከው መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቹ አድርጎም ይመለከተናል። (መዝ. 25:14) ይሖዋ ቅድሚያውን ወስዶ፣ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለንን መንገድ ከፍቷል፤ ይህን ያደረገው ለኃጢአታችን መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን በመስጠት ነው። ይሖዋ ያሳየን ምሕረትና ርኅራኄ እንዴት ታላቅ ነው!

4. ይሖዋ ምን ሰጥቶናል? ይህን ስጦታ የሰጠንስ ለምንድን ነው?

4 የይሖዋ ትሕትና የተገለጸበትን ሌላም መንገድ እንመልከት። ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ የመምረጥ ችሎታ እንዳይኖረን አድርጎ ሊፈጥረን ይችል ነበር። ሆኖም እንዲህ አላደረገም። በራሱ አምሳል የፈጠረን ከመሆኑም ሌላ የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል። እኛ የሰው ልጆች ከቁጥር የማንገባ ብንሆንም እንኳ የምናደርገው ምርጫ ለእሱ ለውጥ ያመጣል፤ ለእሱ ባለን ፍቅር ተነሳስተንና እሱን መታዘዛችን የሚያስገኛቸውን ጥቅሞች ተገንዝበን በምርጫችን እንድናገለግለው ይፈልጋል። (ዘዳ. 10:12፤ ኢሳ. 48:17, 18) ይሖዋ በትሕትና እንዲህ ያለ አጋጣሚ ስለሰጠን ምንኛ አመስጋኞች ነን!

ኢየሱስና አብረውት ከሚገዙት መካከል አንዳንዶቹ፣ እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸውን መላእክት እየተመለከቱ ነው። አንዳንድ መላእክት የተሰጣቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ወደ ምድር ሲወርዱ ይታያል። ይሖዋ በሥዕሉ ላይ ለሚታዩት ሁሉ ሥልጣን ሰጥቷል (አንቀጽ 5⁠ን ተመልከት)

5. ከይሖዋ ስለ ትሕትና መማር የምንችለው እንዴት ነው? (ሽፋኑን ተመልከት።)

5 ይሖዋ እኛን የሚይዝበትን መንገድ በመመልከት ስለ ትሕትና መማር እንችላለን። በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ይሖዋን በጥበቡ የሚወዳደረው የለም። ያም ቢሆን የሌሎችን ሐሳብ ለመቀበል ፈቃደኛ ነው። ለምሳሌ፣ ይሖዋ ሁሉን ነገር በፈጠረበት ወቅት ልጁ አብሮት እንዲሠራ አድርጓል። (ምሳሌ 8:27-30፤ ቆላ. 1:15, 16) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ቢሆንም ለሌሎች ኃላፊነት ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን ኢየሱስን ሾሞታል፤ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች ለሚሆኑት 144,000 የሰው ልጆችም በተወሰነ መጠን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 12:32) በእርግጥ ይሖዋ፣ ኢየሱስን ንጉሥና ሊቀ ካህናት መሆን እንዲችል አሠልጥኖታል። (ዕብ. 5:8, 9) ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑትን ሰዎችም ያሠለጥናቸዋል፤ አንድ ጊዜ ይህን ኃላፊነት ከሰጣቸው በኋላ ግን ጣልቃ ገብቶ እያንዳንዱን ሥራቸውን አይቆጣጠርም። ከዚህ ይልቅ ፈቃዱን እንደሚያደርጉ ይተማመንባቸዋል።—ራእይ 5:10

ሌሎችን በማሠልጠንና ለእነሱ ኃላፊነት በመስጠት ይሖዋን መምሰል እንችላለን (ከአንቀጽ 6-7⁠ን ተመልከት) *

6-7. ለሌሎች ኃላፊነት መስጠትን በተመለከተ ከሰማዩ አባታችን ምን ትምህርት እናገኛለን?

6 የማንም እገዛ የማያስፈልገው የሰማዩ አባታችን ለሌሎች ኃላፊነት የሚሰጥ ከሆነ እኛማ እንዲህ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! የቤተሰብ ራስ ወይም የጉባኤ ሽማግሌ ነህ? ለሌሎች ሥራ በመስጠት እንዲሁም ሥራውን ሲያከናውኑ እያንዳንዱን እርምጃቸውን ባለመቆጣጠር የይሖዋን ምሳሌ ተከተል። የይሖዋን ምሳሌ መከተልህ ሥራው እንዲከናወን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ሌሎችን ለማሠልጠንና በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንዲጨምር ለመርዳት አጋጣሚ ይሰጥሃል። (ኢሳ. 41:10) ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ከይሖዋ መማር የሚችሉት ሌላስ ምን ነገር አለ?

7 ይሖዋ፣ ልጆቹ የሆኑት መላእክት የሚሰጡትን ሐሳብ መስማት እንደሚያስደስተው መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። (1 ነገ. 22:19-22) ወላጆች የይሖዋን ምሳሌ መከተል የምትችሉት እንዴት ነው? ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ አንድ ሥራ የሚከናወንበትን መንገድ በተመለከተ ሐሳብ እንዲሰጡ ልጆቻችሁን ጠይቋቸው። የሚቻል ከሆነም፣ የሚሰጡትን ሐሳብ ተግባራዊ አድርጉት።

8. ይሖዋ አብርሃምንና ሣራን በትዕግሥት የያዛቸው እንዴት ነው?

8 ይሖዋ ትሕትና የሚያሳይበት ሌላው መንገድ ታጋሽ መሆኑ ነው። ለምሳሌ ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ውሳኔውን በተመለከተ በአክብሮት ጥያቄ ሲያነሱ በትዕግሥት ይይዛቸዋል። ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት አብርሃም ይህን በተመለከተ ያሳሰበውን ነገር ሲገልጽ አምላክ አዳምጦታል። (ዘፍ. 18:22-33) ይሖዋ የአብርሃም ሚስት የሆነችውን ሣራን የያዘበትን መንገድም እናስታውስ። ሣራ በስተርጅናዋ እንደምትፀንስ ይሖዋ በገባው ቃል ስቃ ነበር፤ ይሖዋ ግን በዚህ ቅር አልተሰኘም ወይም አልተቆጣም። (ዘፍ. 18:10-14) እንዲያውም ሣራን በአክብሮት ይዟታል።

9. ወላጆች እና ሽማግሌዎች ከይሖዋ ምሳሌ ምን መማር ይችላሉ?

9 ወላጆች እና ሽማግሌዎች፣ ከይሖዋ ምሳሌ ምን መማር ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ ወይም በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች፣ በውሳኔያችሁ ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ምን ምላሽ እንደምትሰጡ ለማሰብ ሞክሩ። ወዲያውኑ እነሱን ለማረም ትሞክራላችሁ? ወይስ አመለካከታቸውን ለመረዳት ትጥራላችሁ? ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ይሖዋን የሚመስሉ ከሆነ ቤተሰቦችም ሆኑ ጉባኤዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ። ይሖዋ ከተወው ምሳሌ ስለ ትሕትና ምን ትምህርት እንደምናገኝ እስካሁን ተመልክተናል። ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ በአምላክ ቃል ውስጥ ከተጠቀሱ አንዳንድ ሰዎች፣ ልክን ማወቅን በተመለከተ ምን ትምህርት እንደምናገኝ እናያለን።

ከሌሎች ሰዎች ምን ትምህርት እናገኛለን?

10. ይሖዋ የሌሎች ሰዎችን ታሪክ ተጠቅሞ የሚያስተምረን እንዴት ነው?

10 ‘ታላቁ አስተማሪያችን’ የሆነው ይሖዋ እኛን ለማስተማር ሲል የተለያዩ ሰዎች ታሪክ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍር አድርጓል። (ኢሳ. 30:20, 21) ልክን ማወቅን ጨምሮ ሌሎች አምላክ የሚደሰትባቸው ባሕርያትን ያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች በተዉት ምሳሌ ላይ በማሰላሰል ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ያሉትን ግሩም ባሕርያት ያላሳዩ ሰዎች ምን እንዳጋጠማቸው በመመልከትም የምናገኘው ትምህርት አለ።—መዝ. 37:37፤ 1 ቆሮ. 10:11

11. ከሳኦል ስህተት ምን እንማራለን?

11 ንጉሥ ሳኦል ስላጋጠመው ነገር እናስብ። ሳኦል ወጣት እያለ ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ከቦታው አልፎ የሚሄድ ሰው አልነበረም፤ ተጨማሪ ኃላፊነት ሲሰጠው እንኳ ለመቀበል አመንትቶ ነበር። (1 ሳሙ. 9:21፤ 10:20-22) ከጊዜ በኋላ ግን ሳኦል ከቦታው አልፎ መሄድ ጀመረ። ይህ መጥፎ ባሕርይ መታየት የጀመረው ንጉሥ ከሆነ ብዙም ሳይቆይ ነው። በአንድ ወቅት ሳኦል፣ ነቢዩ ሳሙኤልን በትዕግሥት መጠበቅ አቅቶት ነበር። ሳኦል፣ ልኩን የሚያውቅ ሰው ቢሆን ኖሮ ይሖዋ ለሕዝቡ ሲል እርምጃ እንደሚወስድ ይተማመን ነበር፤ እሱ ግን የሚቃጠል መሥዋዕት በማቅረብ ያልተፈቀደለትን ነገር አደረገ። በዚህም ምክንያት የይሖዋን ሞገስ ከጊዜ በኋላ ደግሞ ንግሥናውን አጣ። (1 ሳሙ. 13:8-14) እኛም ከዚህ የማስጠንቀቂያ ምሳሌ ትምህርት በመውሰድ ከቦታችን አልፈን ላለመሄድ መጠንቀቃችን የጥበብ እርምጃ ነው።

12. ዳንኤል ልኩን የሚያውቅ ሰው መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?

12 ከሳኦል በተቃራኒ ግሩም ምሳሌ ከሚሆነን ከነቢዩ ዳንኤል ምን እንደምንማር እስቲ እንመልከት። ዳንኤል በመላ ሕይወቱ ትሑትና ልኩን የሚያውቅ የአምላክ አገልጋይ መሆኑን አሳይቷል፤ ምንጊዜም የይሖዋን መመሪያ ለማግኘት ይጥር ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዳንኤል በይሖዋ እርዳታ የናቡከደነጾርን ሕልም በፈታበት ወቅት እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ አልተሰማውም። ከዚህ ይልቅ ልኩን የሚያውቅ ሰው ስለነበር ክብርና ምስጋና የሰጠው ለይሖዋ ነው። (ዳን. 2:26-28) ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ጥሩ ንግግር የመስጠት ችሎታ ሊኖረን ወይም በአገልግሎት ላይ ስኬታማ ልንሆን እንችላለን፤ ሆኖም ክብር ሁሉ ሊሰጠው የሚገባው ይሖዋ መሆኑን አንርሳ። ልካችንን በማወቅ፣ በይሖዋ እርዳታ ባይሆን ኖሮ እነዚህን ነገሮች ማከናወን እንደማንችል አምነን ልንቀበል ይገባል። (ፊልጵ. 4:13) እንዲህ ዓይነት አመለካከት ስናዳብር የኢየሱስን ግሩም ምሳሌም እየተከተልን ነው። እንዴት?

13. ኢየሱስ በዮሐንስ 5:19, 30 ላይ ከተናገረው ሐሳብ ልክን ስለ ማወቅ ምን እንማራለን?

13 ኢየሱስ ፍጹም የሆነ የአምላክ ልጅ ቢሆንም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። (ዮሐንስ 5:19, 30ን አንብብ።) የሰማዩ አባቱን ሥልጣን ለመውሰድ ሞክሮ አያውቅም። ፊልጵስዩስ 2:6 እንደሚገልጸው ኢየሱስ “የሥልጣን ቦታን ለመቀማት ማለትም ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን አላሰበም።” ኢየሱስ ቦታውን የሚያውቅና የአባቱን ሥልጣን የሚያከብር ታዛዥ ልጅ ነው።

ኢየሱስ ቦታውን ያውቅ ነበር፤ ከሥልጣኑ አልፎም አልሄደም (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. ኢየሱስ በእሱ ሥልጣን ሥር ያልሆነን ነገር እንዲያደርግ በተጠየቀበት ወቅት ምን ምላሽ ሰጥቷል?

14 ደቀ መዛሙርቱ ያዕቆብና ዮሐንስ ከእናታቸው ጋር ሆነው በእሱ ሥልጣን ሥር ያልሆነን ነገር እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር፤ በዚህ ወቅት ኢየሱስ ምን ብሎ እንደመለሰላቸው እንመልከት። ኢየሱስ በመንግሥቱ በእሱ ቀኝና ግራ የሚቀመጡትን ሰዎች የሚወስነው የሰማዩ አባቱ ብቻ እንደሆነ ወዲያውኑ ነገራቸው። (ማቴ. 20:20-23) ኢየሱስ፣ ከተሰጠው ቦታ አልፎ እንደማይሄድ አሳይቷል። ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ይሖዋ ከሰጠው ሥልጣን አልፎ በመሄድ ምንም ነገር አድርጎ አያውቅም። (ዮሐ. 12:49) እኛስ ኢየሱስ የተወውን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

ልክን በማወቅ ረገድ ኢየሱስን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት) *

15-16. በ1 ቆሮንቶስ 4:6 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

15 በ1 ቆሮንቶስ 4:6 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ ኢየሱስ ልክን በማወቅ ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ጥቅሱ “ከተጻፈው አትለፍ” ይላል። ስለዚህ ምክር ስንጠየቅ፣ የራሳችንን አመለካከት ከመግለጽ ወይም መጀመሪያ ወደ አእምሯችን የመጣውን ሐሳብ ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ምክር የጠየቀን ሰው ትኩረቱን በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ እንዲያደርግ መርዳት አለብን። በዚህ መንገድ ቦታችንን እንደምናውቅ እናሳያለን። ልካችንን በማወቅ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ “የጽድቅ ድንጋጌዎች” እውቅና እንሰጣለን።—ራእይ 15:3, 4

16 ልካችንን ማወቃችን ለይሖዋ ክብር ከማምጣቱ በተጨማሪ ሌሎች ጥቅሞች አሉት። ትሕትና እና ልክን ማወቅ ደስተኛ እንድንሆን ብሎም ከሌሎች ጋር ተስማምተን እንድንኖር የሚረዱን እንዴት እንደሆነ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

ትሑት መሆንና ልክን ማወቅ ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17. ትሑት የሆኑና ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች ደስተኛ የሆኑት ለምንድን ነው?

17 ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ለምን? አቅማችን ውስን መሆኑን የምንገነዘብ ከሆነ ሌሎች የሚሰጡንን ማንኛውም እርዳታ በደስታና በአመስጋኝነት እንቀበላለን። ኢየሱስ አሥር የሥጋ ደዌ ሕመምተኞችን በፈወሰበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከዚህ አስከፊ በሽታ ስለፈወሰው ኢየሱስን ሊያመሰግነው የተመለሰው አንደኛው ብቻ ነው፤ ሰውየው በራሱ ችሎታ ከዚህ በሽታ መንጻት እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። ትሑት የሆነውና ልኩን የሚያውቀው ይህ ሰው ለተደረገለት ነገር አመስጋኝ ነበር፤ ለአምላክም ክብር ሰጥቷል።—ሉቃስ 17:11-19

18. ትሕትና እና ልክን ማወቅ ከሌሎች ጋር ተስማምተን ለመኖር የሚረዱን እንዴት ነው? (ሮም 12:10)

18 ትሑት የሆኑና ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች ከሌሎች ጋር ተስማምተው መኖርና የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ቀላል ይሆንላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ሌሎች ሰዎች ግሩም ባሕርያት እንዳሏቸው መቀበል አይከብዳቸውም፤ እንዲሁም በሌሎች እንደሚተማመኑ ያሳያሉ። ትሑት የሆኑና ልካቸውን የሚያውቁ ግለሰቦች፣ ሌሎች ሰዎች የተሰጣቸውን የትኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ሲሳካላቸው ይደሰታሉ፤ እነሱን ከማመስገንና ከማክበርም ወደኋላ አይሉም።—ሮም 12:10ን አንብብ።

19. ከኩራት እንድንርቅ የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

19 ከዚህ በተቃራኒ፣ ኩሩ የሆኑ ሰዎች እነሱ ራሳቸው እንዲመሰገኑ ስለሚፈልጉ ሌሎችን ማመስገን ይተናነቃቸዋል። ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ስለሚያወዳድሩ የፉክክር መንፈስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ሌሎችን ከማሠልጠንና ለእነሱ ኃላፊነት ከመስጠት ይልቅ ‘አንድ ሥራ በትክክል እንዲሠራ እኔው ራሴ ባከናውነው ይሻላል’ የሚል አመለካከት አላቸው፤ ትክክለኛ መንገድ ብለው የሚያስቡት ደግሞ እነሱ የሚፈልጉትን መንገድ ነው። ኩሩ የሆነ ሰው በአብዛኛው ከሌሎች ልቆ መታየት የሚፈልግ ሲሆን ቅናተኛ ነው። (ገላ. 5:26) እንዲህ ያሉ ሰዎች ከሌሎች ጋር ዘላቂ ወዳጅነት ለመመሥረት ይቸገራሉ። በውስጣችን ኩራት እንዳለ ካስተዋልን ‘አእምሯችንን በማደስ ለመለወጥ’ እንዲረዳን አጥብቀን ይሖዋን እንለምነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ይህን ጎጂ ባሕርይ በውስጣችን ሥር ሳይሰድድ ለማስወገድ ያስችለናል።—ሮም 12:2

20. ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ መሆን ያለብን ለምንድን ነው?

20 ይሖዋ ለተወልን ግሩም ምሳሌ ምንኛ አመስጋኞች ነን! አገልጋዮቹን የሚይዝበት መንገድ ትሑት እንደሆነ ያሳያል፤ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። በተጨማሪም ልካቸውን አውቀው ከአምላክ ጋር የሄዱ ሰዎች ግሩም ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮልናል፤ የእነሱን ምሳሌም መከተል እንፈልጋለን። እንግዲያው ለይሖዋ የሚገባውን ግርማና ክብር ምንጊዜም እንስጠው። (ራእይ 4:11) እንዲህ ካደረግን እኛም፣ ትሑትና ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎችን ከሚወደው የሰማዩ አባታችን ጋር የመሄድ መብት እናገኛለን።

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

^ አን.5 ትሕትና ለሌሎች ምሕረት በማድረግና ርኅራኄ በማሳየት ይገለጻል። ከዚህ አንጻር ይሖዋ ትሑት እንደሆነ መናገራችን ተገቢ ነው። ይህ ርዕስ እንደሚያሳየው ይሖዋ ከተወው ምሳሌ ስለ ትሕትና መማር እንችላለን። በተጨማሪም ልክን ስለ ማወቅ ከንጉሥ ሳኦል፣ ከነቢዩ ዳንኤልና ከኢየሱስ የምናገኘውን ትምህርት እንመለከታለን።

^ አን.58 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ ከጉባኤው ክልል ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ስለሚያከናውንበት መንገድ አንድን ወጣት ወንድም ጊዜ ወስዶ ሲያሠለጥነው። ከዚያ በኋላ ሽማግሌው፣ ወጣቱ ወንድም ሥራውን የሚያከናውንበትን መንገድ ከመቆጣጠር ይልቅ ራሱን ችሎ እንዲሠራ ይተወዋል።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሚካሄድ የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ መገኘቷ ተገቢ ስለ መሆኑ አንድን የጉባኤ ሽማግሌ ትጠይቀዋለች። ሽማግሌው የራሱን አመለካከት ከመንገር ይልቅ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን እያሳያት ነው።