በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 34

በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ቦታ አለህ!

በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ቦታ አለህ!

“አካል አንድ ቢሆንም ብዙ የአካል ክፍሎች እንዳሉትና የዚህ አካል ክፍሎች በሙሉ ብዙ ቢሆኑም አንድ አካል እንደሆኑ ሁሉ ክርስቶስም እንደዚሁ ነው።”—1 ቆሮ. 12:12

መዝሙር 101 በአንድነት አብሮ መሥራት

ማስተዋወቂያ *

1. ምን አስደሳች መብት አግኝተናል?

በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ መታቀፍ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የምንኖረው ሰላማዊና ደስተኛ ሰዎች በሞሉበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። ታዲያ አንተ በጉባኤው ውስጥ ያለህ ቦታ ምንድን ነው?

2. ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች ላይ ምን ምሳሌ ተጠቅሟል?

2 ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው የተለያዩ ደብዳቤዎች ላይ የጠቀሰው አንድ ምሳሌ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ስላለን ቦታ ብዙ ያስተምረናል። ጳውሎስ በእነዚህ ደብዳቤዎች ላይ ጉባኤውን ከሰው አካል ጋር አነጻጽሮታል። በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ደግሞ ከሰው አካል ክፍሎች ጋር አመሳስሏቸዋል።—ሮም 12:4-8፤ 1 ቆሮ. 12:12-27፤ ኤፌ. 4:16

3. በዚህ ርዕስ ላይ የትኞቹን ሦስት ትምህርቶች እንመለከታለን?

3 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ጳውሎስ ከጠቀሰው ምሳሌ የምናገኛቸውን ሦስት አስፈላጊ ትምህርቶች እንመለከታለን። በመጀመሪያ፣ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ እያንዳንዳችን ቦታ * እንዳለን እንማራለን። ሁለተኛ፣ በጉባኤ ውስጥ ያለን ቦታ ምን እንደሆነ ማስተዋል ከከበደን ምን ማድረግ እንደምንችል እናያለን። ሦስተኛ፣ እያንዳንዳችን በአምላክ ጉባኤ ውስጥ ያለንን ድርሻ በትጋት መወጣት ያለብን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

እያንዳንዳችን በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ የምናበረክተው ድርሻ አለ

4. ሮም 12:4, 5 ምን ያስተምረናል?

4 ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው የመጀመሪያው ትምህርት፣ እያንዳንዳችን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ አስፈላጊ ድርሻ ያለን መሆኑን ነው። ጳውሎስ ምሳሌውን የጀመረው እንዲህ በማለት ነው፦ “በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤ ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።” (ሮም 12:4, 5) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር? እያንዳንዳችን በጉባኤው ውስጥ የተለያየ ድርሻ ቢኖረንም ሁላችንም ጠቃሚ ቦታ እንዳለን መግለጹ ነበር።

እያንዳንዳችን በጉባኤው ውስጥ የምናበረክተው ድርሻ የተለያየ ነው፤ ሆኖም ሁላችንም ጠቃሚ ቦታ አለን (ከአንቀጽ 5-12⁠ን ተመልከት) *

5. ይሖዋ ለጉባኤው ምን “ስጦታ” ሰጥቷል?

5 በጉባኤው ውስጥ ቦታ ስላላቸው ክርስቲያኖች ስታስብ ወዲያውኑ ወደ አእምሮህ የሚመጡት አመራር የሚሰጡ ወንድሞች ሊሆኑ ይችላሉ። (1 ተሰ. 5:12፤ ዕብ. 13:17) እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በክርስቶስ አማካኝነት ወንዶችን “ስጦታ” አድርጎ ለጉባኤው ሰጥቷል። (ኤፌ. 4:8) “ስጦታ” የሆኑ ወንዶች ከተባሉት መካከል የበላይ አካል አባላት፣ የበላይ አካሉ ረዳቶች፣ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት፣ የወረዳ የበላይ ተመልካቾች፣ የመስክ አስተማሪዎች፣ የጉባኤ ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ይገኙበታል። እነዚህ ወንድሞች በሙሉ የይሖዋን ውድ በጎች እንዲንከባከቡና ጉባኤውን እንዲያገለግሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ናቸው።—1 ጴጥ. 5:2, 3

6. በ1 ተሰሎንቄ 2:6-8 ላይ እንደተገለጸው በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ወንድሞች ምን ለማድረግ ተግተው ይሠራሉ?

6 ወንድሞች በመንፈስ ቅዱስ የሚሾሙት የተለያዩ ኃላፊነቶችን እንዲወጡ ነው። የተለያዩ የአካል ክፍሎች ለምሳሌ እጅና እግር፣ መላውን አካል የሚጠቅም ሥራ እንደሚያከናውኑ ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ የተሾሙ ወንድሞችም መላውን ጉባኤ የሚጠቅም ሥራ በትጋት ያከናውናሉ። እነዚህ ወንድሞች ለራሳቸው ክብር ለማግኘት አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን ለማነጽና ለማጠናከር ተግተው ይሠራሉ። (1 ተሰሎንቄ 2:6-8ን አንብብ።) ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር የሚያሳዩና መንፈሳዊ የሆኑ እንዲህ ያሉ ወንድሞች ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን!

7. በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ብዙ ክርስቲያኖች ምን በረከት ያገኛሉ?

7 በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሚስዮናውያን፣ ልዩ አቅኚዎች ወይም የዘወትር አቅኚዎች ሆነው እንዲያገለግሉ ይሾማሉ። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ብዙ ወንድሞችና እህቶች የስብከቱንና ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ የሙሉ ጊዜ ሥራቸው ለማድረግ ወስነዋል። እንዲህ በማድረጋቸውም ብዙዎች የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ መርዳት ችለዋል። አብዛኞቹ የሙሉ ጊዜ ወንጌላውያን ከቁሳዊ ነገር አንጻር ብዙ ባይኖራቸውም ይሖዋ በሕይወታቸው ውስጥ አትረፍርፎ ባርኳቸዋል። (ማር. 10:29, 30) እነዚህን ውድ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ የጉባኤው ክፍል በመሆናቸውም አመስጋኞች ነን!

8. ምሥራቹን የሚሰብክ እያንዳንዱ አስፋፊ በይሖዋ ፊት ውድ የሆነው ለምንድን ነው?

8 የተሾሙ ወንድሞችና በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የሚካፈሉ ክርስቲያኖች በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ እንደሚያበረክቱ ተመልክተናል፤ ይሁንና በጉባኤው ውስጥ ቦታ ያላቸው እነሱ ብቻ ናቸው? በፍጹም! ምሥራቹን የሚሰብክ እያንዳንዱ አስፋፊ በአምላክ ዘንድም ሆነ በጉባኤው ውስጥ አስፈላጊ ሚና አለው። (ሮም 10:15፤ 1 ቆሮ. 3:6-9) እንዲያውም ጉባኤው ከተቋቋመባቸው ዋነኛ ዓላማዎች አንዱ ሰዎችን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ማድረግ ነው። (ማቴ. 28:19, 20፤ 1 ጢሞ. 2:4) በጉባኤው ውስጥ ያሉ የተጠመቁም ሆኑ ያልተጠመቁ አስፋፊዎች በሙሉ ለዚህ ሥራ ቅድሚያ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ።—ማቴ. 24:14

9. ክርስቲያን ሴቶችን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው?

9 ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ለክርስቲያን ሴቶች የተከበረ ቦታ ሰጥቷቸዋል። እሱን በታማኝነት የሚያገለግሉትን ሚስቶች፣ እናቶች፣ መበለቶችና ያላገቡ እህቶች ከፍ አድርጎ ይመለከታቸዋል። በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ አምላክን ያስደሰቱ በርካታ ሴቶች ተጠቅሰዋል። እነዚህ ሴቶች ጥበብ፣ እምነት፣ ቅንዓት፣ ድፍረትና ልግስና በማሳየት እንዲሁም መልካም ሥራዎችን በማከናወን ግሩም ምሳሌ በመሆናቸው ተመስግነዋል። (ሉቃስ 8:2, 3፤ ሥራ 16:14, 15፤ ሮም 16:3, 6፤ ፊልጵ. 4:3፤ ዕብ. 11:11, 31, 35) በዛሬው ጊዜም እንዲህ ያሉ ግሩም ባሕርያት ያሏቸው ክርስቲያን ሴቶች በየጉባኤዎቻችን በመኖራቸው ይሖዋን በእጅጉ እናመሰግነዋለን!

10. በዕድሜ የገፉ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከፍ አድርገን የምንመለከታቸው ለምንድን ነው?

10 በተጨማሪም በየጉባኤዎቻችን በዕድሜ የገፉ በርካታ ክርስቲያኖች በመኖራቸው ደስተኞች ነን። በአንዳንድ ጉባኤዎች ውስጥ፣ ዕድሜያቸውን ሙሉ ይሖዋን በታማኝነት ሲያገለግሉ የኖሩ በዕድሜ የገፉ ወንድሞችና እህቶች አሉ። ሌሎች አረጋውያን ክርስቲያኖች ደግሞ ወደ እውነት ከመጡ ብዙ አልቆዩ ይሆናል። አረጋውያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እውነት ውስጥ የቆዩበት ጊዜ ምንም ያህል ቢሆን በዕድሜ ምክንያት ከሚመጡ የተለያዩ የጤና እክሎች ጋር ይታገሉ ይሆናል። በእነዚህ ችግሮች የተነሳ፣ በጉባኤ ውስጥም ሆነ በስብከቱ ሥራ የሚያደርጉት ተሳትፎ ውስን ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን እነዚህ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በመስክ አገልግሎት የቻሉትን ያህል ይካፈላሉ፤ እንዲሁም አቅማቸው በፈቀደው መጠን ሌሎችን ለማበረታታትና ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም ካካበቱት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። በእርግጥም እነዚህ ክርስቲያኖች በይሖዋም ሆነ በእኛ ዘንድ ውብ ናቸው።—ምሳሌ 16:31

11-12. በጉባኤህ ውስጥ ያሉ ወጣቶች ያበረታቱህ እንዴት ነው?

11 ስለ ወጣቶቻችንም እናስብ። ሰይጣን ዲያብሎስ በሚቆጣጠረውና የእሱ የክፋት ፍልስፍናዎች በነገሡበት ዓለም ውስጥ ስለሚያድጉ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። (1 ዮሐ. 5:19) ሆኖም እነዚህ ወጣት ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ፣ በአገልግሎት ሲካፈሉና ለሚያምኑባቸው ነገሮች በድፍረት ጥብቅና ሲቆሙ ስናይ ሁላችንም እንበረታታለን። በእርግጥም እናንተ ወጣቶች በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ አስፈላጊ ቦታ አላችሁ!—መዝ. 8:2

12 ይሁን እንጂ አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ እያበረከቱ መሆኑን ማመን ይከብዳቸዋል። ታዲያ እያንዳንዳችን በግለሰብ ደረጃ በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዳለን እንዲሰማን ምን ሊረዳን ይችላል? ይህን ቀጥለን እንመለከታለን።

በጉባኤው ውስጥ ያለህን ቦታ አስተውል

13-14. አንዳንዶች በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ እንደሌላቸው የሚሰማቸው ለምንድን ነው?

13 ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘውን ሁለተኛ ትምህርት ደግሞ እንመልከት። ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የሚቸገሩበትን ጉዳይ ጠቅሷል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች በጉባኤው ውስጥ ጠቃሚ ድርሻ የሚያበረክቱ መሆኑን ይጠራጠራሉ። ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እግር ‘እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም’ ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም። እንዲሁም ጆሮ ‘እኔ ዓይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም’ ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም።” (1 ቆሮ. 12:15, 16) ጳውሎስ ሊያስተላልፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው?

14 በጉባኤው ውስጥ ካሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ራስህን የምታወዳድር ከሆነ አንተ የምታበረክተውን ድርሻ ዝቅ አድርገህ ልትመለከት ትችላለህ። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በማስተማር፣ በማደራጀት ወይም እረኝነት በማድረግ ረገድ የተዋጣላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አንተ ግን በዚህ ረገድ የእነሱን ያህል ችሎታ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ማሰብህ ትሑትና ልክህን የምታውቅ እንደሆንክ ያሳያል። (ፊልጵ. 2:3) ሆኖም ልትጠነቀቅ ይገባል። የላቀ ተሰጥኦ ካላቸው ሰዎች ጋር ሁልጊዜ ራስህን የምታወዳድር ከሆነ በራስህ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። እንዲያውም ጳውሎስ እንደገለጸው በጉባኤው ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። ታዲያ እንዲህ ያሉ ስሜቶችን ለማሸነፍ ምን ሊረዳህ ይችላል?

15. በ1 ቆሮንቶስ 12:4-11 ላይ በተገለጸው መሠረት ስጦታዎቻችንን በተመለከተ ምን ልንገነዘብ ይገባል?

15 እስቲ አንድ እውነታ እንመልከት፦ ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎችን ሰጥቷቸው ነበር፤ ሆኖም ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ስጦታዎች አልተቀበሉም። (1 ቆሮንቶስ 12:4-11ን አንብብ።) ይሖዋ ለእነዚያ ክርስቲያኖች የተለያዩ ስጦታዎችን እና ችሎታዎችን ቢሰጣቸውም እያንዳንዱ ክርስቲያን ጠቃሚ ድርሻ ነበረው። በዛሬው ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎች የሉንም። መሠረታዊ ሥርዓቱ ግን ዛሬም ይሠራል። ሁላችንም ተመሳሳይ ተሰጥኦዎች አይኖሩን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ሁላችንም በይሖዋ ፊት ዋጋ አለን።

16. ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የትኛውን ምክር መከተል ይኖርብናል?

16 ራሳችንን ከሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ከማወዳደር ይልቅ ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን የሚከተለውን ምክር መከተል ይኖርብናል፦ “እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም ራሱን ከሌላ ሰው ጋር ሳያወዳድር ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።”—ገላ. 6:4

17. የጳውሎስን ምክር መከተላችን ምን ጥቅም ያስገኝልናል?

17 ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር በመከተል የራሳችንን ተግባር ከመረመርን፣ ሌሎች የሌሏቸው ተሰጥኦዎችና ችሎታዎች እንዳሉን እናስተውላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ከመድረክ የማስተማር ችሎታው ያን ያህል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በጣም ውጤታማ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በጉባኤው ያሉ ሌሎች ሽማግሌዎችን ያህል በሚገባ የተደራጀ ላይሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ አስፋፊዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሲፈልጉ በነፃነት የሚቀርቡት አፍቃሪ እረኛ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ይታወቅ ይሆናል። (ዕብ. 13:2, 16) ጠንካራ ጎናችን እና ያሉን ስጦታዎች ግልጽ ሆነው ሲታዩን ለጉባኤው በምናበረክተው አስተዋጽኦ ረክተን እንኖራለን። ከእኛ የተለየ ስጦታ ባላቸው ወንድሞችም አንቀናም።

18. ችሎታዎቻችንን ማሻሻል የምንችለው እንዴት ነው?

18 በጉባኤው ውስጥ ያለን ድርሻ ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም አገልግሎታችንን ለማሻሻልና ችሎታዎቻችንን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ማሻሻያ ማድረግ እንድንችል ይሖዋ በድርጅቱ አማካኝነት ግሩም ሥልጠና ይሰጠናል። ለምሳሌ በሳምንቱ መሃል በምናደርገው ስብሰባ ላይ፣ በአገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን የሚረዳን ሥልጠና እናገኛለን። ታዲያ ከዚህ ሥልጠና ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ጥረት እያደረግህ ነው?

19. በመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ለመካፈል የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ምን ይረዳሃል?

19 ግሩም ሥልጠና የምናገኝበት ሌላው ፕሮግራም የመንግሥቱ ወንጌላውያን ትምህርት ቤት ነው። በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉና ከ23 እስከ 65 ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ትምህርት ቤት መካፈል ይችላሉ። መቼም ቢሆን በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ብቃቱን እንደማታሟላ ይሰማህ ይሆናል። ይሁንና በትምህርት ቤቱ መካፈል የማትችልባቸውን ምክንያቶች ከመደርደር ይልቅ የመካፈል ፍላጎት እንዲያድርብህ የሚያደርጉ ምክንያቶችን ለማሰብ ሞክር። ከዚያም ብቃቶቹን ለማሟላት የሚረዳህን ዕቅድ አውጣ። በይሖዋ እርዳታ እንዲሁም አንተ በምታደርገው ትጋት የተሞላበት ጥረት፣ የማይቻል የሚመስልህ ነገር እውን ሊሆን ይችላል።

ስጦታዎችህን ጉባኤውን ለማነጽ ተጠቀምባቸው

20. ከሮም 12:6-8 ምን እንማራለን?

20 ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው ሦስተኛው ትምህርት በሮም 12:6-8 ላይ ተጠቅሷል። (ጥቅሱን አንብብ።) ጳውሎስ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁሉ የተለያዩ ስጦታዎች እንዳሏቸው በድጋሚ ገልጿል። በዚህኛው ጥቅስ ላይ ግን፣ ያለንን ማንኛውም ስጦታ ጉባኤውን ለማነጽና ለማጠናከር ልንጠቀምበት እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ተናግሯል።

21-22. ከሮበርት እና ከፍሊቼ ምን ትምህርት እናገኛለን?

21 ሮበርት * የተባለ ወንድም ያጋጠመውን ሁኔታ እንመልከት። በሌላ አገር ሲያገለግል ከቆየ በኋላ በትውልድ አገሩ በሚገኝ ቤቴል ውስጥ እንዲያገለግል ተመደበ። የአገልግሎት ምድቡ የተቀየረው ድክመት ስላለበት እንዳልሆነ ቢነገረውም ምን ስሜት እንደተፈጠረበት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “የተሰጠኝን ኃላፊነት በአግባቡ እንዳልተወጣሁ አስብ ስለነበር ለበርካታ ወራት አሉታዊ ስሜት ተቆጣጥሮኝ ነበር። የቤቴል አገልግሎቴን ለማቆም ያሰብኩባቸው ጊዜያት ነበሩ።” ታዲያ ደስታው እንዲመለስለት የረዳው ምንድን ነው? አብሮት የሚያገለግል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ ይሖዋ ቀደም ሲል በነበረን በእያንዳንዱ የአገልግሎት ምድብ ላይ ያሠለጠነን አሁን በተሰጠን የአገልግሎት ምድብ ላይ ይበልጥ ጠቃሚ ድርሻ ማበርከት እንድንችል መሆኑን አስታወሰው። ሮበርት ስላለፈው ነገር ማሰቡን ትቶ አሁን ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ማተኮር እንዳለበት ተገነዘበ።

22 ፍሊቼ ኤፒስኮፖ የተባለው ወንድምም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። እሱና ባለቤቱ በ1956 ከጊልያድ ከተመረቁ በኋላ በቦሊቪያ በወረዳ ሥራ ተካፍለዋል። በ1964 ልጅ ወለዱ። ወንድም ፍሊቼ እንዲህ ብሏል፦ “የምንወደውን የአገልግሎት ምድባችንን ትተን መሄድ በጣም ከብዶን ነበር። አንድ ዓመት ሙሉ ስቆዝም አሳለፍኩ። ሆኖም በይሖዋ እርዳታ አመለካከቴን ማስተካከል የቻልኩ ሲሆን በወላጅነት ኃላፊነቴ ላይ ማተኮር ጀመርኩ።” አንተስ እንደ ሮበርት ወይም ፍሊቼ ተሰምቶህ ያውቃል? ቀደም ሲል የነበሩህ የአገልግሎት መብቶች አሁን ስለሌሉህ ተስፋ ቆርጠሃል? ከሆነ የትኩረት አቅጣጫህን በመቀየር፣ ይሖዋን እና ወንድሞችህን ለማገልገል በአሁኑ ወቅት ማድረግ በምትችለው ነገር ላይ ማተኮርህ ደስተኛ ለመሆን ይረዳሃል። ያሉህን ስጦታዎችና ችሎታዎች ተጠቅመህ ሌሎችን በመርዳት ተጠመድ፤ በዚህ መንገድ ጉባኤውን ማነጽህ ደስታ ያስገኝልሃል።

23. ምን ማድረጋችን ጠቃሚ ነው? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

23 እያንዳንዳችን በይሖዋ ፊት ውድ ነን። ይሖዋ የቤተሰቡ አባል እንድንሆን ይፈልጋል። ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለማነጽ ምን ማድረግ እንደምንችል ጊዜ ወስደን ካሰላሰልን እንዲሁም ይህን ድርሻችንን ለመወጣት በትጋት ከሠራን በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንደሌለን አይሰማንም። ይሁንና በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች ክርስቲያኖችን እንዴት ልንመለከታቸው ይገባል? እነዚህን ክርስቲያኖች እንደምንወዳቸውና እንደምናከብራቸው እንዴት ማሳየት እንችላለን? በቀጣዩ ርዕስ ላይ እነዚህን አስፈላጊ ነጥቦች እንመረምራለን።

መዝሙር 24 ኑ! ወደ ይሖዋ ተራራ

^ አን.5 ሁላችንም በይሖዋ ፊት ዋጋ እንዳለን ሲሰማን ደስ ይለናል። አንዳንድ ጊዜ ግን በጉባኤ ውስጥ ጠቃሚ ቦታ ያለን መሆኑን እንጠራጠር ይሆናል። ይህ ርዕስ፣ ሁላችንም በጉባኤው ውስጥ በጣም ጠቃሚ ቦታ እንዳለን እንድንገነዘብ ይረዳናል።

^ አን.3 ተጨማሪ ማብራሪያ፦ በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ስላለን ቦታ ስንናገር፣ ጉባኤውን በማነጽና በማጠናከር ረገድ የምናበረክተውን ድርሻ ማመልከታችን ነው። ዘራችን፣ ጎሣችን፣ የኑሮ ደረጃችን፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለን ቦታ፣ ባሕላችን ወይም የትምህርት ደረጃችን በጉባኤ ውስጥ ባለን ቦታ ላይ ለውጥ አያመጣም።

^ አን.21 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።

^ አን.63 የሥዕሉ መግለጫ፦ ሦስቱ ፎቶግራፎች ከጉባኤ ስብሰባ በፊት፣ በስብሰባው ወቅትና ከስብሰባ በኋላ የሚከናወኑ ነገሮችን ያሳያሉ። ሥዕል 1፦ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ፣ አንድን እንግዳ ሞቅ አድርጎ ሲቀበል፤ አንድ ወጣት ወንድም የድምፅ መሣሪያዎቹን ሲያስተካክል፤ አንዲት እህት በዕድሜ ከገፉ እህት ጋር ስትጨዋወት። ሥዕል 2፦ ወጣትም ሆኑ አረጋውያን ወንድሞችና እህቶች በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ሐሳብ ለመስጠት እጃቸውን ሲያወጡ። ሥዕል 3፦ አንድ ባልና ሚስት የስብሰባ አዳራሹን ሲያጸዱ። አንዲት እናት፣ በመዋጮ ሣጥኑ ውስጥ ገንዘብ እንድታስገባ ልጇን ስታግዛት። አንድ ወጣት ወንድም ጽሑፍ ክፍል ውስጥ ሲያገለግል፤ አንድ ወንድም በዕድሜ የገፉትን እህት ሲያበረታታ።