በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 33

ትንሣኤ የአምላክን ፍቅር፣ ጥበብና ትዕግሥት ያሳያል

ትንሣኤ የአምላክን ፍቅር፣ ጥበብና ትዕግሥት ያሳያል

‘ከሞት ይነሳሉ።’—ሥራ 24:15

መዝሙር 151 አምላክ ይጣራል

ማስተዋወቂያ *

1. ይሖዋ ሕያዋን ፍጥረታትን የፈጠረው ለምንድን ነው?

ይሖዋ ብቻውን የሚኖርበት ወቅት ነበር። ሆኖም ብቸኝነት ይሰማው ነበር ማለት አይደለም። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር የለም። ያም ሆኖ አምላክ፣ በሕይወት መኖር የሚያስገኘውን ደስታ ሌሎችም እንዲቀምሱ ፈለገ። ስለዚህ በፍቅር ተነሳስቶ መፍጠር ጀመረ።—መዝ. 36:9፤ 1 ዮሐ. 4:19

2. ኢየሱስም ሆነ መላእክት ስለ ይሖዋ የፍጥረት ሥራዎች ምን ተሰምቷቸዋል?

2 ይሖዋ መጀመሪያ የፈጠረው ልጁን ኢየሱስን ነው። ከዚያም በበኩር ልጁ አማካኝነት፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጨምሮ ‘ሌሎች ነገሮችን በሙሉ’ ፈጠረ። (ቆላ. 1:16) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር አብሮ የመሥራት መብት በማግኘቱ ደስተኛ ነበር። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጆች የሆኑት መላእክትም ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነገር ነበረ። ይሖዋ እና ዋና ሠራተኛው የሆነው ኢየሱስ፣ ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥሩ መላእክት በቀጥታ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል። ታዲያ ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ምድር ስትፈጠር ‘በደስታ ጮኸዋል’፤ ይሖዋ የፍጥረት ሥራው ቁንጮ የሆነውን የሰው ልጅን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ሲፈጥርም ደስታቸውን ገልጸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 38:7፤ ምሳሌ 8:31) እያንዳንዱ የይሖዋ የፍጥረት ሥራ የእሱን ፍቅርና ጥበብ ያሳያል።—መዝ. 104:24፤ ሮም 1:20

3. በ1 ቆሮንቶስ 15:21, 22 ላይ እንደተገለጸው የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ምን አጋጣሚ አስገኝቷል?

3 የይሖዋ ዓላማ፣ የሰው ልጆች እሱ በፈጠራት ውብ ፕላኔት ላይ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነበር። አዳምና ሔዋን በአፍቃሪ አባታቸው ላይ ሲያምፁ ግን ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ላይ አጠላ። (ሮም 5:12) ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? የሰውን ዘር ለመታደግ የሚያደርገውን ዝግጅት ወዲያውኑ ገለጸ። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ የአዳምንና የሔዋንን ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚያወጣ ቤዛ ለማዘጋጀት አሰበ። ይህን ቤዛ መሠረት በማድረግም፣ እሱን ለማገልገል የሚመርጥ ማንኛውም ግለሰብ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መንገድ ከፈተ።—ዮሐ. 3:16፤ ሮም 6:23፤ 1 ቆሮንቶስ 15:21, 22ን አንብብ።

4. በዚህ ርዕስ ላይ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

4 አምላክ የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት የገባው ቃል አንዳንድ ጥያቄዎች እንዲፈጠሩብን ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ፣ ትንሣኤ የሚከናወነው እንዴት ሊሆን ይችላል? የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት ሲነሱ ለይተን ልናውቃቸው እንችል ይሆን? ትንሣኤ ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን እንዴት ነው? በትንሣኤ ተስፋ ላይ ስናሰላስል ስለ ይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ትዕግሥት ምን እንማራለን? እስቲ የእያንዳንዱን ጥያቄ መልስ እንመልከት።

ትንሣኤ የሚከናወነው እንዴት ሊሆን ይችላል?

5. የሞቱ ሰዎች የሚነሱት ደረጃ በደረጃና ሥርዓት ባለው መንገድ እንደሚሆን የምንጠብቀው ለምንድን ነው?

5 ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን ከሞት በሚያስነሳበት ወቅት ሁሉም በአንድ ጊዜ ትንሣኤ ያገኛሉ ብለን አንጠብቅም። ለምን? ምክንያቱም የምድር ሕዝብ ቁጥር በአንድ ጊዜ ከጨመረ ትርምስ ይፈጠራል። ይሖዋ ደግሞ ባልተደራጀና በተተራመሰ መንገድ ምንም ነገር አያደርግም። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ ያውቃል። (1 ቆሮ. 14:33) ይሖዋ ጥበበኛና ታጋሽ አምላክ ስለሆነ ከኢየሱስ ጋር ሆኖ ምድርን ለሰው ልጅ መኖሪያነት ያዘጋጃት ደረጃ በደረጃ ነው። በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ኢየሱስም እነዚህን የይሖዋ ባሕርያት ያሳያል፤ ከአርማጌዶን በሕይወት ከሚተርፉት ሰዎች ጋር ሆኖ የሞቱ ሰዎችን ለመቀበል ምድርን የሚያዘጋጀው ጥበብና ትዕግሥት በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው።

ከአርማጌዶን የሚተርፉ ሰዎች፣ ከሞት የሚነሱትን ስለ አምላክ መንግሥት እና ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች ያስተምሯቸዋል (አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት) *

6. በሐዋርያት ሥራ 24:15 መሠረት ይሖዋ ከሞት ከሚያስነሳቸው መካከል እነማን ይገኙበታል?

6 ከሁሉ በላይ አስፈላጊ የሆነ ሌላም ሥራ ይኖራል፤ ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉ ሰዎች ከሞት የሚነሱትን ስለ አምላክ መንግሥትና ስለ ይሖዋ መሥፈርቶች ማስተማር ይኖርባቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ከሞት ከሚነሱት አብዛኞቹ፣ መጽሐፍ ቅዱስ “ዓመፀኞች” ብሎ የሚጠራው ቡድን አባላት ናቸው። (የሐዋርያት ሥራ 24:15ን አንብብ።) እነዚህ ሰዎች ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም ማግኘት ከፈለጉ በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ማስተካከያዎች ማድረግ ያስፈልጋቸዋል። ስለ ይሖዋ ጨርሶ ለማያውቁ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች እውነትን ማስተማር ምን ያህል ሥራ እንደሚጠይቅ አስበው። በዛሬው ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከምንመራበት መንገድ ጋር በሚመሳሰል መልኩ እያንዳንዱ ሰው አስጠኚ ይመደብለት ይሆን? እነዚህ ሰዎች እውነትን ከተማሩ በኋላ በጉባኤዎች ውስጥ የሚታቀፉበትና ከእነሱ በኋላ የሚነሱ ሰዎችን እንዲያስተምሩ ሥልጠና የሚያገኙበት ዝግጅት ይደረግ ይሆን? ይህ ጊዜው ሲደርስ የምናየው ነገር ይሆናል። ይሁንና አንድ የምናውቀው ነገር አለ፤ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ “[ምድር] በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።” (ኢሳ. 11:9) በእርግጥም ያ ሺህ ዓመት በሥራ የምንጠመድበት ሆኖም አስደሳች ወቅት ይሆናል!

7. የአምላክ ሕዝቦች ትንሣኤ ያገኙ ሰዎችን ሲያስተምሩ ስሜታቸውን መረዳት ቀላል የሚሆንላቸው ለምንድን ነው?

7 በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የአምላክ ምድራዊ ልጆች በሙሉ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ የአምላክ ሕዝቦች፣ ከሞት የሚነሱ ሰዎችን የኃጢአት ዝንባሌዎቻቸውን እንዲያሸንፉና የይሖዋን መሥፈርቶች እንዲከተሉ በሚረዱበት ወቅት የእነሱን ስሜት መረዳት አይከብዳቸውም። (1 ጴጥ. 3:8) ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች፣ ትሑት በሆኑትና ‘የራሳቸውን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተው’ በሚሠሩት የይሖዋ ሕዝቦች ባሕርይ መማረካቸው አይቀርም።—ፊልጵ. 2:12

ከሞት የሚነሱትን ሰዎች ለይተን ማወቅ እንችል ይሆን?

8. ትንሣኤ የሚያገኙ ቤተሰቦቻችንን እና ወዳጆቻችንን መለየት እንችላለን ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ የሆነው ለምንድን ነው?

8 ከሞት የሚነሱ ቤተሰቦቻችንን እና ወዳጆቻችንን መለየት እንችላለን እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። ከዚህ በፊት ከተከናወኑ ትንሣኤዎች እንደምንመለከተው ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ሲያስነሳ ልክ ከመሞታቸው በፊት የነበራቸውን ገጽታ፣ አነጋገርና አስተሳሰብ ይዘው እንዲነሱ የሚያደርግ ይመስላል። ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ፣ ትንሣኤን ደግሞ ከእንቅልፍ ከመነሳት ጋር እንዳመሳሰለው እናስታውስ። (ማቴ. 9:18, 24፤ ዮሐ. 11:11-13) እንቅልፍ የወሰዳቸው ሰዎች ሲነቁ መልካቸውም ሆነ አነጋገራቸው አይቀየርም፤ ከመተኛታቸው በፊት አእምሯቸው ውስጥ የነበረው መረጃም አይጠፋም። አልዓዛርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ስለሆነው ሰውነቱ መበስበስ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ከሞት ሲያስነሳው እህቶቹ ወዲያውኑ አውቀውታል፤ አልዓዛርም ቢሆን እህቶቹን እንዳወቃቸው ግልጽ ነው።—ዮሐ. 11:38-44፤ 12:1, 2

9. ሰዎች ከሞት የሚነሱት ፍጹም አእምሮና አካል ይዘው አይደለም የምንለው ለምንድን ነው?

9 በክርስቶስ አገዛዝ ሥር የሚኖር ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” እንደማይል ይሖዋ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 33:24፤ ሮም 6:7) በመሆኑም ሙታን የሚነሱት ጤናማ አካል ይዘው ነው። ይሁንና ወዲያውኑ ፍጽምና ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ማለት አይደለም። እንዲህ ቢሆን፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው እነሱን መለየት ሊከብዳቸው ይችላል። ሁሉም የሰው ዘር በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ የሚደርስ ይመስላል። ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ መልሶ የሚያስረክበው በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ነው። በዚያን ጊዜ፣ መንግሥቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ዳር ያደርሳል፤ ከሚያጠናቅቃቸው ሥራዎች መካከል ደግሞ የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና ማድረስ ይገኝበታል።—1 ቆሮ. 15:24-28፤ ራእይ 20:1-3

ትንሣኤ ደስተኞች እንድንሆን የሚያደርገን እንዴት ነው?

10. ትንሣኤ ምን ስሜት የሚፈጥርብህ ይመስልሃል?

10 በሞት የተለዩህን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና ስታገኝ ምን እንደሚሰማህ እስቲ አስበው። በሳቅ ትፍለቀለቅ ወይም የደስታ እንባ ታነባ ይሆን? ወይስ ለይሖዋ ከልብ የመነጨ የውዳሴ መዝሙር ለመዘመር ትነሳሳለህ? እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር አለ፤ አሳቢ የሆነው አባታችን እና አፍቃሪ የሆነው ልጁ አስደናቂ የሆነውን የትንሣኤ ስጦታ እንድናገኝ አጋጣሚ ስለከፈቱልን ለእነሱ ያለን ፍቅር በእጅጉ መጨመሩ አይቀርም።

11. ኢየሱስ በዮሐንስ 5:28, 29 ላይ በተናገረው መሠረት የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያከብሩ ሰዎች ምን ያገኛሉ?

11 ከሞት የተነሱት ሰዎች አሮጌውን ስብዕና አውልቀው በመጣል በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት መኖር ሲጀምሩ ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስበው። እንዲህ ያለ ለውጥ የሚያደርጉ ሁሉ ትንሣኤያቸው የሕይወት ትንሣኤ ይሆናል። በተቃራኒው ግን በአምላክ ላይ የሚያምፁ ሰዎች በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሰላም እንዲያደፈርሱ አይፈቀድላቸውም።—ኢሳ. 65:20፤ ዮሐንስ 5:28, 29ን አንብብ።

12. በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ የይሖዋን በረከት የሚያገኙት እንዴት ነው?

12 በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በምሳሌ 10:22 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እውነተኝነት የማየት አጋጣሚ ያገኛሉ፤ ጥቅሱ “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም” ይላል። የይሖዋ መንፈስ በእነሱ ላይ ስለሚሠራ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ባለጸጋ ይሆናሉ፤ ክርስቶስን ይበልጥ እየመሰሉ የሚሄዱ ከመሆኑም ሌላ ደረጃ በደረጃ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። (ዮሐ. 13:15-17፤ ኤፌ. 4:23, 24) በየዕለቱ አካላዊ ጥንካሬያቸው እየጨመረና የተሻሉ ሰዎች እየሆኑ ይሄዳሉ። በዚያ ወቅት ሕይወት ምንኛ አስደሳች ይሆናል! (ኢዮብ 33:25) ታዲያ በትንሣኤ ተስፋ ላይ ማሰላሰልህ በዛሬው ጊዜ የሚጠቅምህ እንዴት ነው?

ስለ ይሖዋ ፍቅር ምን እንማራለን?

13. ከመዝሙር 139:1-4 ጋር በሚስማማ መልኩ ትንሣኤ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያውቀን የሚያሳየው እንዴት ነው?

13 ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይሖዋ ሰዎችን ከሞት ሲያስነሳ አእምሯቸው ውስጥ ያሉትን መረጃዎች እና የማንነታቸው መለያ የሆኑትን ነገሮች ይዘው እንዲነሱ ያደርጋል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው። ይሖዋ በጣም ስለሚወድህ የምታስበውን፣ የሚሰማህን፣ የምትናገረውንና የምታደርገውን እያንዳንዱን ነገር ያስተውላል እንዲሁም ያስታውሳል። በመሆኑም አንተም በትንሣኤ ከሚነሱት ሰዎች መካከል ብትሆን አእምሮህ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች፣ አመለካከትህንና የማንነትህ መለያ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ይዘህ እንድትነሳ ማድረግ አይከብደውም። ንጉሥ ዳዊት፣ ይሖዋ እያንዳንዳችንን ምን ያህል በጥልቀት እንደሚያውቀን ተገንዝቦ ነበር። (መዝሙር 139:1-4ን አንብብ።) ታዲያ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን መገንዘባችን በአሁኑ ወቅት ምን ስሜት ይፈጥርብናል?

14. ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን ማሰላሰላችን ምን እንዲሰማን ሊያደርግ ይገባል?

14 ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን ማሰላሰላችን ሊያስጨንቀን አይገባም። ለምን? ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን እናስታውስ። እያንዳንዳችንን ልዩ እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። ማንነታችንን የሚቀርጹ የሕይወት ገጠመኞቻችንን በሚገባ ያስተውላል። ይህን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! መቼም ቢሆን ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። በእያንዳንዱ ቀንና ሴኮንድ ይሖዋ አብሮን ነው፤ ምንጊዜም እኛን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልጋል።—2 ዜና 16:9

ስለ ይሖዋ ጥበብ ምን እንማራለን?

15. የትንሣኤ ተስፋ የይሖዋን ጥበብ የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 የግድያ ዛቻ ጠላት ሊጠቀምበት የሚችል ኃይለኛ መሣሪያ ነው። ይህ መሣሪያ፣ ሰዎች ወዳጆቻቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ ወይም የሚያምኑባቸውን ነገሮች እንዲክዱ ለማድረግ ይሠራበታል። ይሁንና በሰይጣን ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎች የሚጠቀሙበት ይህ ማስፈራሪያ በእኛ ላይ ኃይል የለውም። ምክንያቱም ጠላቶቻችን ቢገድሉን ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳን እናውቃለን። (ራእይ 2:10) ጠላቶቻችን ምንም ቢያደርጉ ከይሖዋ ሊለዩን እንደማይችሉ እርግጠኞች ነን። (ሮም 8:35-39) በእርግጥም ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ መስጠቱ ታላቅ ጥበብ እንዳለው የሚያሳይ ነው! ይህ ተስፋ፣ የሰይጣንን ውጤታማ መሣሪያ የሚያከሽፍ ከመሆኑም ሌላ የማይናወጥ ድፍረት እንዲኖረን ስለሚረዳን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ያስችለናል።

የምናደርጋቸው ውሳኔዎች ይሖዋ በቁሳዊ የሚያስፈልጉንን ነገሮች እንደሚያሟላልን በገባው ቃል እንደምንተማመን ያሳያሉ? (አንቀጽ 16⁠ን ተመልከት) *

16. ራስህን ምን ብለህ መጠየቅህ ጠቃሚ ነው? ለጥያቄዎቹ የምትሰጠው መልስ በይሖዋ ምን ያህል እንደምትተማመን ለማወቅ የሚረዳህ እንዴት ነው?

16 የይሖዋ ጠላቶች እንደሚገድሉህ ቢዝቱብህ ይሖዋ እንደሚያስነሳህ በመተማመን ሕይወትህን በአደራ ትሰጠዋለህ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ በይሖዋ እንደምትተማመን አሁን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ‘በየዕለቱ የማደርጋቸው ትናንሽ ውሳኔዎች በይሖዋ እንደምታመን ያሳያሉ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (ሉቃስ 16:10) በተጨማሪም ‘አኗኗሬ፣ መንግሥቱን ካስቀደምኩ ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልኝ በገባው ቃል እንደምተማመን ያሳያል?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ይጠቅምሃል። (ማቴ. 6:31-33) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ በይሖዋ እንደምትተማመንና ወደፊት ለሚያጋጥምህ ማንኛውም ዓይነት ፈተና ዝግጁ እንደሆንክ እያሳየህ ነው።—ምሳሌ 3:5, 6

ስለ ይሖዋ ትዕግሥት ምን እንማራለን?

17. (ሀ) ትንሣኤ ይሖዋ ታጋሽ መሆኑን የሚያሳየው እንዴት ነው? (ለ) የይሖዋን ትዕግሥት እንደምናደንቅ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

17 ይሖዋ ይህንን አሮጌ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት ወስኗል። (ማቴ. 24:36) ይህ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ትዕግሥቱ አልቆ እርምጃ አይወስድም። ሙታንን ለማስነሳት ቢናፍቅም ይታገሣል። (ኢዮብ 14:14, 15) እነሱን ለማስነሳት የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ እየጠበቀ ነው። (ዮሐ. 5:28) ለይሖዋ ትዕግሥት አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሱን ምክንያቶች አሉ። እስቲ አስበው፦ እኛን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ‘ለንስሐ ለመብቃት’ የሚያስችል ጊዜ ያገኙት ይሖዋ ታጋሽ ስለሆነ ነው። (2 ጴጥ. 3:9) ይሖዋ፣ በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ይፈልጋል። እንግዲያው እኛም የእሱን ትዕግሥት እንደምናደንቅ እናሳይ። እንዴት? “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች በትጋት በመፈለግ እንዲሁም ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት በመርዳት ነው። (ሥራ 13:48) በዚህ መንገድ እነሱም እንደ እኛ ከይሖዋ ትዕግሥት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንረዳቸዋለን።

18. ሌሎችን በትዕግሥት መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

18 ይሖዋ በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ፍጹም የምንሆንበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠብቃል። ያ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። ከዚህ አንጻር እኛም የሌሎችን መልካም ጎን ልንመለከትና እነሱን በትዕግሥት ልንይዛቸው ይገባል። አንዲት እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ የዚህች እህት ባል በከባድ ጭንቀት ይሠቃይ ጀመር፤ ከጊዜ በኋላም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት አቆመ። እንዲህ ብላለች፦ “ሁኔታው በጣም ከብዶኝ ነበር። በቤተሰብ እናደርጋቸዋለን ብለን ያሰብናቸው ነገሮች በሙሉ በድንገት መና ቀሩ።” ይህ ሁሉ ሲሆን ይህች አፍቃሪ ሚስት ባሏን በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት ታደርግ ነበር። በይሖዋ ትተማመን የነበረ ሲሆን በባሏ ፈጽሞ ተስፋ አልቆረጠችም። ከችግሩ ባሻገር በመመልከትና በባሏ መልካም ጎኖች ላይ በማተኮር የይሖዋን ምሳሌ ተከትላለች። ይህች እህት “ባለቤቴ ግሩም ባሕርያት አሉት፤ ከገጠመው ችግር ለማገገምም የተቻለውን ያህል እየጣረ ነው” ብላለች። እኛም በቤተሰባችን ወይም በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ ከባድ ችግር የገጠማቸው ሰዎችን በትዕግሥት መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

19. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

19 ምድር በተፈጠረችበት ወቅት ኢየሱስና መላእክት በጣም ተደስተው ነበር። ወደፊት ምድር ይሖዋን በሚወዱና እሱን በሚያገለግሉ ፍጹማን ሰዎች ስትሞላማ ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት ይቻላል። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ከምድር የተዋጁትም፣ የሰው ዘር እነሱ ከሚያከናውኑት ሥራ የሚያገኘውን ጥቅም ሲመለከቱ በጣም እንደሚደሰቱ ጥያቄ የለውም። (ራእይ 4:4, 9-11፤ 5:9, 10) የደስታ እንጂ የሥቃይ እንባ የማናነባበት እንዲሁም ሕመም፣ መከራና ሞት ታሪክ የሚሆኑበት ያ ጊዜ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስበው። (ራእይ 21:4) እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ታጋሽ የሆነውን አባትህን ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይህን ካደረግህ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ደስታህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ። (ያዕ. 1:2-4) በእርግጥም ይሖዋ ሰዎች ‘ከሞት እንደሚነሱ’ ለገባው ቃል ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ሥራ 24:15

መዝሙር 141 ሕይወት ተአምር ነው

^ አን.5 ይሖዋ አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ታጋሽ የሆነ አባት ነው። የፍጥረት ሥራዎቹ እና የሞቱ ሰዎችን ለማስነሳት ያለው ዓላማ እነዚህን ባሕርያቱን በግልጽ ያሳያሉ። በዚህ ርዕስ ላይ፣ ትንሣኤን በተመለከተ የሚነሱብንን አንዳንድ ጥያቄዎች እንመረምራለን፤ በተጨማሪም የትንሣኤ ተስፋ ስለ ይሖዋ ፍቅር፣ ጥበብና ትዕግሥት ምን እንደሚያስተምረን እንዲሁም ይህን ማወቃችን ምን እንዲሰማን ሊያደርግ እንደሚገባ እንመለከታለን።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት የሞተ አንድ የአሜሪካ ሕንድ፣ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከሞት ተነስቶ። አርማጌዶንን በሕይወት ያለፈ አንድ ወንድም፣ ከሞት የተነሳውን ይህን ሰው ከክርስቶስ ቤዛ ለመጠቀም ምን ማድረግ እንዳለበት ሲያስተምረው።

^ አን.61 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወንድም በሳምንቱ ውስጥ ትርፍ ሰዓት መሥራት የማይችልባቸው ቀናት እንዳሉ ለአለቃው ሲያስረዳው። በእነዚያ ቀናት ምሽት ላይ ከአምልኮው ጋር የተያያዙ እንቅስቃሴዎችን እንደሚያከናውን ይገልጽለታል። በሌሎች ቀናት አጣዳፊ ሥራ ከመጣ ግን ተጨማሪ ሥራ ለመሥራት ፈቃደኛ መሆኑን ይነግረዋል።