በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 7

በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት

በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት ትክክለኛ ግንዛቤ ማግኘት

“ክርስቶስ አካሉ ለሆነውና አዳኙ ለሆነለት ጉባኤ ራስ . . . ነው።”—ኤፌ. 5:23

መዝሙር 137 ታማኝ ሴቶች፣ ክርስቲያን እህቶች

ማስተዋወቂያ *

1. የይሖዋ ቤተሰብ አንድነት እንዲኖረው አስተዋጽኦ ያደረገው አንዱ ነገር ምንድን ነው?

የይሖዋ ቤተሰብ ክፍል በመሆናችን ደስተኛ ነን። ቤተሰባችን እንዲህ ሰላማዊ የሆነውና አንድነት ሊኖረው የቻለው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ሁላችንም ይሖዋ ያቋቋመውን የራስነት ሥርዓት ለማክበር የምንችለውን ሁሉ ማድረጋችን ነው። ስለ ራስነት ሥርዓት የተሻለ ግንዛቤ እያገኘን ስንሄድ አንድነታችን ይበልጥ ይጠናከራል።

2. በዚህ ርዕስ ላይ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

2 በዚህ ርዕስ ላይ በጉባኤው ውስጥ ስላለው የራስነት ሥርዓት እንመረምራለን። በተጨማሪም የሚከተሉትን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን፦ የእህቶች ድርሻ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ወንድም የእያንዳንዷ እህት ራስ ነው ልንል እንችላለን? ሽማግሌዎች፣ በወንድሞችና በእህቶች ላይ የተሰጣቸው ሥልጣን አንድ ባል በሚስቱና በልጆቹ ላይ ካለው የራስነት ሥልጣን ጋር ተመሳሳይ ነው? በመጀመሪያ ግን ለእህቶች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን እንደሚገባ እንመልከት።

ለእህቶች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?

3. እህቶቻችን ለሚያከናውኑት ሥራ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3 ቤተሰባቸውን ለመንከባከብ፣ ምሥራቹን ለመስበክና ጉባኤውን ለመደገፍ በትጋት እየሠሩ ያሉትን እህቶቻችንን እናደንቃቸዋለን። ይሖዋና ኢየሱስ ለእነሱ ያላቸውን አመለካከት መመርመራችን ለእህቶቻችን ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ሴቶችን ስለያዘበት መንገድ መመልከታችንም ይጠቅመናል።

4. ይሖዋ፣ ወንዶችንም ሴቶችንም እኩል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ የሚጠቁመው እንዴት ነው?

4 ይሖዋ ወንዶችንም ሴቶችንም እኩል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ለወንዶች ብቻ ሳይሆን ለሴቶችም እንደሰጠ እናነባለን፤ ይህ መንፈስ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገርን ጨምሮ ተአምራት እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል። (ሥራ 2:1-4, 15-18) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። (ገላ. 3:26-29) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሽልማት የሚሰጣቸው ወንዶችም ሴቶችም ናቸው። (ራእይ 7:9, 10, 13-15) ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ተልእኮ የተሰጠውም ለወንዶችም ለሴቶችም ነው። (ማቴ. 28:19, 20) እንዲያውም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጵርስቅላ የተባለችው እህት ስላከናወነችው ሥራ ይገልጻል፤ ከባሏ ከአቂላ ጋር ሆና አጵሎስ የተባለን አንድ የተማረ ሰው ስለ እውነት ይበልጥ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ መርዳት ችላለች።—ሥራ 18:24-26

5. ሉቃስ 10:38, 39, 42 ኢየሱስ ለሴቶች ስለነበረው አመለካከት ምን ይጠቁማል?

5 ኢየሱስ ለሴቶች አክብሮት ነበረው። ሴቶችን ይንቁ የነበሩትን የፈሪሳውያንን ልማድ አልተከተለም፤ ፈሪሳውያን ከሴቶች ጋር ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት መወያየት ቀርቶ በአደባባይ ከሴቶች ጋር ሲነጋገሩ መታየት እንኳ አይፈልጉም ነበር። ኢየሱስ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን ባብራራበት ወቅት ወንዶችም ሴቶችም ይገኙ ነበር። * (ሉቃስ 10:38, 39, 42ን አንብብ።) በተጨማሪም ኢየሱስ ለስብከት በሚሄድበት ወቅት ሴቶችም አብረውት እንዲጓዙ ፈቅዷል። (ሉቃስ 8:1-3) እንዲሁም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለሐዋርያቱ የማብሰር መብት የሰጠው ለሴቶች ነው።—ዮሐ. 20:16-18

6. ሐዋርያው ጳውሎስ ለሴቶች አክብሮት እንዳለው ያሳየው እንዴት ነው?

6 ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሴቶችን እንዲያከብር በቀጥታ ምክር ሰጥቶታል። “አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች” አድርጎ እንዲይዛቸው ነግሮታል። (1 ጢሞ. 5:1, 2) ጳውሎስ ጢሞቴዎስን መንፈሳዊ ጉልምስና ላይ እንዲደርስ ብዙ እንደረዳው የታወቀ ነው፤ ሆኖም ጳውሎስ መጀመሪያ ለጢሞቴዎስ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ ያስተማሩት እናቱና አያቱ እንደሆኑ በመጥቀስ ለእነሱ እውቅና ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እህቶችን በስም ጠቅሶ ሰላምታ ልኮላቸዋል። የእህቶችን ሥራ እንዲሁ ማስተዋል ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላከናወኑት ነገር ያለውን አድናቆት ገልጿል።—ሮም 16:1-4, 6, 12፤ ፊልጵ. 4:3

7. ከዚህ ቀጥሎ የየትኞቹን ጥያቄዎች መልስ እንመለከታለን?

7 ቀደም ባሉት አንቀጾች ላይ እንደተመለከትነው እህቶች ከወንድሞች ያንሳሉ ብለን እንድናስብ የሚያደርግ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያት የለም። አፍቃሪና ደግ የሆኑት እህቶቻችን ትልቅ በረከት ናቸው፤ ሽማግሌዎች በጉባኤ ውስጥ ሰላምና አንድነት ለማስፈን በሚያደርጉት ጥረት እህቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። ሆኖም መልስ የሚያሻቸው አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ እህቶች በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ራሳቸውን እንዲሸፍኑ የሚጠብቅባቸው ለምንድን ነው? ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው የሚሾሙት ወንድሞች ብቻ መሆናቸው በጉባኤው ውስጥ ያለው እያንዳንዱ ወንድም የእያንዳንዷ እህት ራስ እንደሆነ ይጠቁማል?

እያንዳንዱ ወንድም የእያንዳንዷ እህት ራስ ነው?

8. በኤፌሶን 5:23 መሠረት እያንዳንዱ ወንድም የእያንዳንዷ እህት ራስ ነው? አብራራ።

8 በአጭሩ አይደለም! አንድ ወንድም በጉባኤው ውስጥ ላሉት እህቶች ሁሉ ራስ ሊሆን አይችልም፤ ራሳቸው ክርስቶስ ነው። (ኤፌሶን 5:23ን አንብብ።) በቤተሰብ ውስጥ ባል በሚስቱ ላይ ሥልጣን ተሰጥቶታል። አንድ የተጠመቀ ልጅ የእናቱ ራስ አይደለም። (ኤፌ. 6:1, 2) በጉባኤው ውስጥም ቢሆን ሽማግሌዎች በእህቶችም ሆነ በወንድሞች ላይ ያላቸው ሥልጣን የተገደበ ነው። (1 ተሰ. 5:12፤ ዕብ. 13:17) ከአባትና ከእናታቸው ቤት የወጡ ያላገቡ እህቶች ወላጆቻቸውንም ሆነ ሽማግሌዎችን ማክበር ይጠበቅባቸዋል። ሆኖም በጉባኤው ውስጥ እንዳሉት ወንዶች ሁሉ ራሳቸው ኢየሱስ ብቻ ነው።

አድገው ከወላጆቻቸው ቤት የወጡ ነጠላ ክርስቲያኖች በኢየሱስ የራስነት ሥልጣን ሥር ናቸው (አንቀጽ 8⁠ን ተመልከት)

9. በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር እህቶች ራሳቸውን መሸፈን ያለባቸው ለምንድን ነው?

9 እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በጉባኤ ውስጥ በማስተማርም ሆነ ከአምልኮ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በማከናወን ረገድ ግንባር ቀደም ሆነው እንዲመሩ የሾመው ወንዶችን ነው፤ ለሴቶች እንዲህ ያለ ሥልጣን አልተሰጣቸውም። (1 ጢሞ. 2:12) ለምን? ምክንያቱ ይሖዋ ኢየሱስን የወንዶች ራስ አድርጎ ከሾመበት ምክንያት ጋር ተመሳሳይ ነው፤ ይሖዋ ይህን ያደረገው በቤተሰቡ ውስጥ ሥርዓት እንዲሰፍን ሲል ነው። አንዲት እህት አንድ ወንድም ሊያከናውነው የሚገባውን ነገር እንድታከናውን የሚያስገድድ ሁኔታ ቢፈጠር ይሖዋ ራሷን እንድትሸፍን ይጠብቅባታል። * (1 ቆሮ. 11:4-7) ይሖዋ እህቶችን እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዘው እነሱን ዝቅ ለማድረግ ሳይሆን እሱ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት አክብሮት እንዲያሳዩ ስለሚፈልግ ነው። እነዚህን ሐሳቦች በአእምሯችን ይዘን የሚከተለውን ጥያቄ መልስ እንመልከት፦ የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ምን ያህል ሥልጣን አላቸው?

የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ያላቸው ሥልጣን

10. አንድ ሽማግሌ ለጉባኤው ደንቦች ለማውጣት እንዲነሳሳ የሚያደርገው ምን ሊሆን ይችላል?

10 ሽማግሌዎች ክርስቶስን ይወዱታል፤ ይሖዋና ኢየሱስ በአደራ ለሰጧቸው በጎችም ፍቅር አላቸው። (ዮሐ. 21:15-17) አንድ ሽማግሌ ለጉባኤው እንደ አባት እንደሆነ በቅንነት ሊያስብ ይችላል። ይህ ሽማግሌ፣ ‘አንድ የቤተሰብ ራስ ቤተሰቡን ለመጠበቅ መመሪያዎች የማውጣት መብት ካለው እኔም የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ ደንቦች ማውጣት እችላለሁ’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። አንዳንድ ወንድሞችና እህቶችም ሽማግሌዎችን ውሳኔ እንዲወስኑላቸው ይጠይቋቸዋል፤ ይህ ደግሞ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ላሉት መንፈሳዊ ራስ እንደሆኑ እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል። ይሁንና ሽማግሌዎች በጉባኤው ላይ ያላቸው ሥልጣን የቤተሰብ ራሶች ካላቸው ሥልጣን ጋር ተመሳሳይ ነው?

ሽማግሌዎች ለጉባኤው መንፈሳዊም ሆነ ስሜታዊ እንክብካቤ ያደርጋሉ። ይሖዋ የጉባኤውን ሥነ ምግባራዊ ንጽሕና የመጠበቅ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል (ከአንቀጽ 11-12⁠ን ተመልከት)

11. የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ያላቸው ሥልጣን የሚመሳሰሉባቸው አንዳንድ አቅጣጫዎች ምንድን ናቸው?

11 የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ባላቸው ሥልጣን መካከል የተወሰነ ተመሳሳይነት እንዳለ ሐዋርያው ጳውሎስ ጠቁሟል። (1 ጢሞ. 3:4, 5) ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ የቤተሰብ አባላት ለቤተሰቡ ራስ እንዲታዘዙ ይጠብቅባቸዋል። (ቆላ. 3:20) በጉባኤው ውስጥ ያሉትም ለሽማግሌዎች እንዲታዘዙ ይጠብቅባቸዋል። ይሖዋ የቤተሰብ ራሶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በእነሱ ኃላፊነት ሥር ያሉትን ሰዎች መንፈሳዊነት እንዲንከባከቡ ይፈልጋል። የቤተሰብ ራሶችም ሆኑ ሽማግሌዎች በእነሱ ኃላፊነት ሥር ያሉት ሁሉ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ማድረግ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም ጥሩ የቤተሰብ ራሶች እንደሚያደርጉት ሁሉ ሽማግሌዎችም በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ችግር ሲያጋጥማቸው እርዳታ እንዲያገኙ ያደርጋሉ። (ያዕ. 2:15-17) በተጨማሪም ይሖዋ ከሽማግሌዎችም ሆነ ከቤተሰብ ራሶች የሚጠብቅባቸው ነገር አለ፤ ይህም በእነሱ ኃላፊነት ሥር ያሉ ሰዎች የእሱን መሥፈርቶች እንዲጠብቁ መርዳት ነው፤ ከዚህም ሌላ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ‘ከተጻፈው እንዳያልፉ’ ይጠብቅባቸዋል።—1 ቆሮ. 4:6

የቤተሰብ ራሶች ለቤተሰባቸው አመራር እንዲሰጡ ይሖዋ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። አፍቃሪ የሆነ የቤተሰብ ራስ ውሳኔዎች ከማድረጉ በፊት ሚስቱን ያማክራል (አንቀጽ 13⁠ን ተመልከት)

12-13. ከሮም 7:2 አንጻር የቤተሰብ ራሶችና ሽማግሌዎች ባላቸው ሥልጣን መካከል ምን ልዩነት አለ?

12 ይሁንና ሽማግሌዎችና የቤተሰብ ራሶች ባላቸው ሥልጣን መካከል ጉልህ ልዩነቶችም አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለሽማግሌዎች የመፍረድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፤ በመሆኑም ንስሐ የማይገባን ኃጢአተኛ ከጉባኤው የማስወገድ ሥልጣን አላቸው።—1 ቆሮ. 5:11-13

13 በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች ለሽማግሌዎች ያልሰጠው ዓይነት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ መመሪያ የማውጣትና ያንን የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ሮም 7:2ን አንብብ።) ለአብነት ያህል፣ አንድ የቤተሰብ ራስ ልጆቹ ማታ ቤት የሚገቡበትን ሰዓት የመወሰን መብት አለው። ልጆቹ መመሪያውን ሳይታዘዙ ቢቀሩ ለእነሱ ተግሣጽ የመስጠት ሥልጣንም አለው። (ኤፌ. 6:1) እርግጥ ነው፣ አንድ አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ መመሪያ ከማውጣቱ በፊት ሚስቱን ያማክራል፤ ምክንያቱም ሁለቱ “አንድ ሥጋ ናቸው።” *ማቴ. 19:6

የጉባኤው ራስ የሆነውን ክርስቶስን አክብሩ

ኢየሱስ በይሖዋ የራስነት ሥልጣን ሥር ሆኖ ለክርስቲያን ጉባኤ መመሪያ ይሰጣል (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት)

14. (ሀ) በማርቆስ 10:45 ላይ ከተገለጸው አንጻር ይሖዋ ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ መሾሙ ተገቢ የሆነው ለምንድን ነው? (ለ) የበላይ አካሉ ሚና ምንድን ነው? (“ የበላይ አካሉ ሚና” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

14 ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ያለውን የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሕይወት የዋጀው በቤዛው አማካኝነት ነው። (ማርቆስ 10:45ን አንብብሥራ 20:28፤ 1 ቆሮ. 15:21, 22) ከዚህ አንጻር ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠውን ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ መሾሙ የተገባ ነው። ኢየሱስ ራሳችን እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና መላው ጉባኤ የሚመሩባቸውን ደንቦች የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ገላ. 6:2) ሆኖም ኢየሱስ ደንብ በማውጣት ብቻ አይወሰንም። እያንዳንዳችንን ይመግበናል እንዲሁም በፍቅር ይንከባከበናል።—ኤፌ. 5:29

15-16. ማርሊ የተባለች እህትና ቤንጃሚን የተባለ ወንድም ከሰጡት ሐሳብ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

15 እህቶች እነሱን እንዲንከባከቡ የተሾሙ ወንዶች የሚሰጡትን መመሪያ በመከተል ክርስቶስን እንደሚያከብሩ ያሳያሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ማርሊ የተባለች እህት የሰጠችው ሐሳብ የብዙ እህቶችን ስሜት የሚያንጸባርቅ ነው። እንዲህ ብላለች፦ “የሚስትነት ኃላፊነቴንና እንደ አንዲት እህት መጠን በጉባኤው ውስጥ ያለኝን ቦታ ከፍ አድርጌ እመለከተዋለሁ። ይሖዋ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት ትክክለኛውን አመለካከት ለመያዝ ሁልጊዜ ጥረት ማድረግ ያስፈልገኛል። ሆኖም ባለቤቴና በጉባኤው ውስጥ ያሉት ወንድሞች ይህ ቀላል እንዲሆንልኝ አድርገዋል፤ ምክንያቱም ያከብሩኛል እንዲሁም ለማከናውነው ሥራ አድናቆታቸውን ይገልጹልኛል።”

16 ወንድሞች፣ እህቶችን በማክበር ስለ ራስነት ሥርዓት ትክክለኛው ግንዛቤ እንዳላቸው ያሳያሉ። በእንግሊዝ የሚኖር ቤንጃሚን የተባለ አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “እህቶች ስብሰባ ላይ ከሚሰጧቸው ሐሳቦች እንዲሁም የጥናት አመራርንና በአገልግሎት ውጤታማ መሆንን በተመለከተ ከሚሰጧቸው አስተያየቶች ብዙ ተምሬያለሁ። የሚያከናውኑት ሥራ በጣም ጠቃሚ እንደሆነ ይሰማኛል።”

17. ለራስነት ሥርዓት አክብሮት ሊኖረን የሚገባው ለምንድን ነው?

17 ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ የቤተሰብ ራሶችንና ሽማግሌዎችን ጨምሮ በጉባኤው ውስጥ ያለን ሁላችን ስለ ራስነት ሥርዓት ትክክለኛው ግንዛቤ ካለንና ለዚህ ዝግጅት አክብሮት የምናሳይ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰማይ ላለው አፍቃሪ አባታችን ለይሖዋ ውዳሴ እናመጣለን።—መዝ. 150:6

መዝሙር 123 ለቲኦክራሲያዊ ሥርዓት በታማኝነት መገዛት

^ አን.5 ሴቶች በጉባኤ ውስጥ ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው? እያንዳንዱ ወንድም ለእያንዳንዷ እህት ራስ ነው? የሽማግሌዎች ሥልጣንና የቤተሰብ ራሶች ሥልጣን አንድ ዓይነት ነው? በዚህ ርዕስ ውስጥ የሚገኙት ከአምላክ ቃል የተወሰዱ ምሳሌዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጡናል።

^ አን.5 መስከረም 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ክርስቲያን ሴቶችን ደግፏቸው” በሚለው ርዕስ ሥር አንቀጽ 6⁠ን ተመልከት።

^ አን.13 አንድ ቤተሰብ በየትኛው ጉባኤ ቢያገለግል የተሻለ እንደሆነ የመወሰን መብት ያለው ማን እንደሆነ መረጃ ለማግኘት ነሐሴ 2020 መጠበቂያ ግንብ ላይ “ሌሎች በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ ያላቸውን ቦታ አክብሩ” የሚለውን ርዕስ ከአንቀጽ 17-19 ተመልከት።

^ አን.59 ስለዚህ ጉዳይ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’ የተባለውን መጽሐፍ ከገጽ 209-211 ተመልከት።

^ አን.64 ስለ በላይ አካሉ ሚና የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት የሐምሌ 15, 2013 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 20-25⁠ን ተመልከት።