በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የማረካቸው ፈገግታ ነው!

የማረካቸው ፈገግታ ነው!

የፊሊፒንስ ከተማ በሆነችው በባጊዮ ሲቲ ባለ የንግድ አካባቢ፣ ሁለት ወጣት ሴቶች በእግራቸው እየሄዱ ነው። እየሄዱ ሳለ የምሥክርነት መስጫ ጋሪ ተመለከቱ፤ ሆኖም ወደዚያ ለመቅረብ አላሰቡም። ከጋሪው አጠገብ የቆመችው ሄለን የተባለችው እህት ሞቅ ያለ ፈገግታ አሳየቻቸው። ሴቶቹ መንገዳቸውን ቀጠሉ፤ ሆኖም ሄለን ያሳየቻቸው ሞቅ ያለ ፈገግታ ትኩረታቸውን ስቦት ነበር።

በኋላ ላይ ሴቶቹ አውቶብስ ተሳፍረው ወደ ቤታቸው ሲሄዱ በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ላይ ትልቅ የjw.org ምልክት ተለጥፎ አዩ። ይህን ምልክት ቀደም ሲል በምሥክርነት መስጫ ጋሪው ላይ እንዳዩት አስታወሱ። ሁለቱም ከአውቶብሱ ወርደው ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሄዱ፤ እዚያም መግቢያው ላይ የተለያዩ ጉባኤዎች ስብሰባ የሚያደርጉበትን ፕሮግራም ተመለከቱ።

ሁለቱ ሴቶች በአንደኛው የጉባኤ ስብሰባ ላይ ተገኙ። ስብሰባ አዳራሹ ውስጥ ማንን ቢያገኙ ጥሩ ነው? ሄለንን! ያኔ ሞቅ ያለ ፈገግታ ያሳየቻቸው ሴት እንደሆነች ለመለየት ጊዜ አልፈጀባቸውም። ሄለን እንዲህ ብላለች፦ “ወደ እኔ ሲመጡ ሳያቸው ትንሽ ግራ ተጋብቼ ነበር። ምን አድርጌያቸው ይሆን ብዬ አስቤ ነበር።” ሴቶቹ ግን የተፈጠረውን ነገር ለሄለን ነገሯት።

ወጣቶቹ በስብሰባው እንዲሁም ከወንድሞችና ከእህቶች ጋር ባሳለፉት ጊዜ በጣም ተደሰቱ፤ እንግድነት አልተሰማቸውም። ሌሎች አዳራሹን ሲያጸዱ ሲያዩ እነሱም ማገዝ ይችሉ እንደሆነ ጠየቁ። ከዚያ ወዲህ አንደኛዋ ወጣት ከአገር ብትወጣም ሌላኛዋ ወጣት በስብሰባዎች ላይ መገኘትና መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምራለች። እንግዲህ ይህ ውጤት የተገኘው እህት ባሳየችው ፈገግታ የተነሳ ነው!