በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ‘ጎዳናዬን ቀና አድርጎልኛል’

ይሖዋ ‘ጎዳናዬን ቀና አድርጎልኛል’

በአንድ ወቅት፣ አንድ ወጣት ወንድም “የምትወደው ጥቅስ የትኛው ነው?” ብሎ ጠይቆኝ ነበር። ምንም ሳላመነታ “ምሳሌ 3 ቁጥር 5 እና 6 ብዬ መለስኩለት፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ ‘በሙሉ ልብህ በይሖዋ ታመን፤ ደግሞም በገዛ ራስህ ማስተዋል አትመካ። በመንገድህ ሁሉ እሱን ግምት ውስጥ አስገባ፤ እሱም ጎዳናህን ቀና ያደርገዋል።’” በእርግጥም ይሖዋ ጎዳናዬን ቀና አድርጎልኛል። እንዴት?

ወላጆቼ በትክክለኛው ጎዳና ላይ መጓዝ እንድጀምር ረድተውኛል

ወላጆቼ እውነትን የሰሙት በ1920ዎቹ ዓመታት ገና ከመጋባታቸው በፊት ነው። እኔ የተወለድኩት በ1939 መጀመሪያ አካባቢ ነው። የምንኖረው እንግሊዝ ውስጥ ነበር፤ ትንሽ ልጅ ሳለሁ ከወላጆቼ ጋር ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች እሄድ ነበር፤ ቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤትን እወደው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ክፍል ያቀረብኩበትን ዕለት አልረሳውም፤ ቁመቴ አትራኖሱ ላይ ስለማይደርስ ክፍሌን ያቀረብኩት ሳጥን ላይ ቆሜ ነው። በወቅቱ ገና ስድስት ዓመቴ ነበር፤ ቁጭ ብለው በሚመለከቱኝ ትላልቅ ሰዎች ፊት ክፍል ማቅረብ በጣም አስፈርቶኝ ነበር።

ከወላጆቼ ጋር መንገድ ላይ ሳገለግል

አባቴ፣ ለአገልግሎት እንድጠቀምበት ቀለል ያለ አቀራረብ ካርድ ላይ ጽፎ ሰጠኝ። አገልግሎት ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ብቻዬን ሄጄ የሰው በር ያንኳኳሁት ገና በስምንት ዓመቴ ነው። የቤቱ ባለቤት ካርዱን ካነበበ በኋላ “እግዚአብሔር እውነተኛ ይሁን” የተባለውን መጽሐፍ ሲቀበለኝ በጣም ተደሰትኩ! መንገድ ላይ ቆሞ ወደሚጠብቀኝ አባቴ እየሮጥኩ ሄጄ ነገርኩት። አገልግሎትና ስብሰባዎች በጣም ያስደስቱኝ ነበር፤ ይሖዋን በሙሉ ጊዜ የማገልገል ፍላጎት እንዲያድርብኝም ረድተውኛል።

የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይበልጥ ልቤን የነካው አባቴ የመጠበቂያ ግንብ ኮንትራት ከገባልኝ በኋላ ነው። እያንዳንዱ ቅጂ በፖስታ ሲደርሰኝ በጉጉት አነብበው ነበር። በይሖዋ ላይ ያለኝ እምነት እየተጠናከረ ሲሄድ ራሴን ለእሱ ለመወሰን ተነሳሳሁ።

በ1950 ኒው ዮርክ ውስጥ በተካሄደው የቲኦክራሲው እድገት በተባለው ስብሰባ ላይ ቤተሰባችን ልዑክ ሆኖ ተገኝቶ ነበር። ሐሙስ ማለትም ነሐሴ 3 ለዕለቱ የተሰጠው ጭብጥ “የሚስዮናውያን ቀን” የሚል ነበር። ያን ዕለት የጥምቀት ንግግሩን የሰጠው በኋላ ላይ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ኬሪ ባርበር ነው። በንግግሩ መጨረሻ ላይ ለዕጩ ተጠማቂዎች ሁለት ጥያቄዎች ሲያቀርብ ተነስቼ “አዎ!” የሚል መልስ ሰጠሁ። በወቅቱ ገና 11 ዓመቴ ቢሆንም ወሳኝ እርምጃ እንደወሰድኩ ገብቶኝ ነበር። ሆኖም ዋና ስላልተማርኩ ውኃ ውስጥ መግባት አስፈርቶኝ ነበር። ስለዚህ አጎቴ ወደ ጥምቀት ገንዳው ወሰደኝና ምንም እንደማልሆን ነገረኝ። ደግሞም ሁኔታዎች በፍጥነት ከመከናወናቸው የተነሳ እግሬ የመጠመቂያ ገንዳውን ወለል እንኳ አልነካም። ገና ከመግባቴ ወንድሞች ተቀባበሉኝ፤ አንደኛው አጠመቀኝ፣ ሌላኛው ደግሞ ተቀብሎ ከገንዳው አወጣኝ። ይህን ወሳኝ እርምጃ ከወሰድኩበት ከዚያን ዕለት አንስቶ ይሖዋ ጎዳናዬን ቀና አድርጎልኛል።

በይሖዋ ለመታመን መረጥኩ

ትምህርት ስጨርስ አቅኚ መሆን ፈልጌ ነበር፤ አስተማሪዎቼ ግን ከፍተኛ ትምህርት እንድከታተል ገፋፉኝ። በእነሱ ግፊት ስለተሸነፍኩ ዩኒቨርሲቲ ገባሁ፤ ብዙም ሳይቆይ ግን የዩኒቨርሲቲ ትምህርቴን እየተከታተልኩ በእውነት ውስጥ ጠንካራ ሆኜ መቀጠል እንደማልችል ገባኝ፤ ስለዚህ ትምህርቴን ለማቆም ወሰንኩ። ስለ ጉዳዩ ይሖዋን በጸሎት ነገርኩት፤ ከዚያም አክብሮት የሚንጸባረቅበት የመልቀቂያ ደብዳቤ ጽፌ አስገባሁና በመጀመሪያው ዓመት መጨረሻ ላይ ለቅቄ ወጣሁ። ይሖዋ እንደሚረዳኝ በመተማመን ወዲያውኑ የአቅኚነት አገልግሎት ጀመርኩ።

ሐምሌ 1957 ዌሊንግቦሮ በተባለች ከተማ ውስጥ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጀመርኩ። የአገልግሎት ጓደኛዬ ሊሆን የሚችል ተሞክሮ ያለው አቅኚ ወንድም እንዲጠቁሙኝ በለንደን ቤቴል ያሉ ወንድሞችን ጠየቅኩ። ወንድም በርት ቬዚ ጥሩ አሠልጣኝ ሆኖልኛል፤ የእሱ ትጋት ጥሩ የአገልግሎት ልማድ እንዲኖረኝ ረድቶኛል። ጉባኤያችን ውስጥ ያለነው ስድስት አረጋውያን እህቶች፣ ወንድም ቬዚና እኔ ብቻ ነበርን። ለሁሉም ስብሰባዎች መዘጋጀቴና በስብሰባዎቹ ላይ ተሳትፎ ማድረጌ በይሖዋ ላይ ያለኝን እምነት ለማጠናከርና እምነቴን ለሌሎች ለመግለጽ ብዙ አጋጣሚ ሰጥቶኛል።

በወታደራዊ አገልግሎት ለመካፈል ፈቃደኛ ባለመሆኔ ለአጭር ጊዜ ከታሰርኩ በኋላ ባርባራ ከተባለች ልዩ አቅኚ እህት ጋር ተዋወቅኩ። በ1959 ተጋባን፤ የትኛውንም የአገልግሎት ምድብ ለመቀበል ዝግጁዎች ነበርን። መጀመሪያ የተመደብነው ሰሜን ምዕራብ እንግሊዝ ውስጥ በሚገኘው በላንከሸር ክልል ነው። ከዚያም ጥር 1961 ለንደን ቤቴል ውስጥ በሚካሄደውና አንድ ወር በሚፈጀው የመንግሥት አገልግሎት ትምህርት ቤት ላይ እንድካፈል ተጋበዝኩ። ትምህርት ቤቱ ሲያልቅ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅኩት ነበር። በርሚንግሃም ከተማ ውስጥ አንድ ተሞክሮ ያለው የወረዳ የበላይ ተመልካች ለሁለት ሳምንት ሥልጠና ሰጠኝ፤ በሥልጠናው ወቅት ባርባራም አብራኝ እንድትሆን ተፈቀደላት። ከዚያም በላንከሸርና በቸሸር ክልሎች ወደሚገኘው የአገልግሎት ምድባችን ሄድን።

ይሖዋ በእሱ በመታመናችን ፈጽሞ አላሳፈረንም

ነሐሴ 1962 እረፍት ላይ ሳለን ከቅርንጫፍ ቢሮው ደብዳቤ ደረሰን። ከደብዳቤው ጋር የጊልያድ ትምህርት ቤት ማመልከቻ ቅጽ ነበር! ጉዳዩን ከጸለይንበት በኋላ እኔና ባርባራ ደብዳቤው ላይ በተጠየቅነው መሠረት ፎርሙን ሞልተን ወዲያውኑ ወደ ቅርንጫፍ ቢሮው ላክነው። ከአምስት ወራት በኋላ በ38ኛው የጊልያድ ትምህርት ቤት ላይ አሥር ወር የሚፈጀውን ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ለመከታተል ወደ ብሩክሊን፣ ኒው ዮርክ አመራን።

በጊልያድ ያገኘነው ትምህርት ስለ አምላክ ቃልና ስለ ድርጅቱ ብቻ ሳይሆን ስለ ወንድማማች ማኅበራችንም ብዙ አሳውቆናል። በወቅቱ ዕድሜያችን ገና በ20ዎቹ አጋማሽ ላይ ስለነበር አብረውን ከተማሩት ሌሎች ተማሪዎች ብዙ የምንማረው ነገር ነበር። በየቀኑ ከጊልያድ አስተማሪያችን ከወንድም ፍሬድ ረስክ ጋር የመሥራት መብት አግኝቼ ነበር። እሱ ካስተማረው ነገር አንድ የማልረሳው ነጥብ ትክክለኛ ምክር የመስጠትን አስፈላጊነት ነው፤ ሁልጊዜም ቢሆን በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ምክር የመስጠትን አስፈላጊነት አጽንኦት ሰጥቶ ይናገር ነበር። በትምህርት ቤቱ ላይ ንግግር ከሰጡን ተሞክሮ ያላቸው ወንድሞች መካከል ናታን ኖር፣ ፍሬድሪክ ፍራንዝና ካርል ክላይን ይገኙበታል። በትሕትና ረገድ ግሩም ምሳሌ ከሚሆነው ከወንድም ማክሚላን ያገኘነውን ትምህርትም አንረሳውም፤ የሰጠን ንግግር ከ1914 እስከ 1919 መጀመሪያ ባለው የፈተና ጊዜ ውስጥ ይሖዋ ሕዝቡን እንዴት እንደመራ ጥልቅ ግንዛቤ እንድናገኝ ረድቶናል!

የአገልግሎት ምድብ ለውጥ

ትምህርታችንን ልናጠናቅቅ አካባቢ ወንድም ኖር፣ በአፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በቡሩንዲ መመደባችንን ለእኔና ለባርባራ ነገረን። በወቅቱ ቡሩንዲ ውስጥ ምን ያህል አስፋፊዎች እንዳሉ የዓመት መጽሐፍ ላይ ለማየት እየሮጥን ወደ ቤቴል ቤተ መጻሕፍት ሄድን። ስለዚህች አገር የሚገልጽ ምንም አኃዛዊ መረጃ እንደሌለ ስናይ በጣም ተገረምን! የተመደብነው ምንም ተሠርቶበት በማያውቅ ክልል ላይ ነበር፤ ይህች አገር ስለምትገኝበት አህጉርም ቢሆን የምናውቀው ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። በመሆኑም በጣም ተጨንቀን ነበር! አጥብቀን መጸለያችን ልባችን እንዲረጋጋ ረድቶናል።

አዲሱ የአገልግሎት ምድባችን እኛ ከምናውቀው ፈጽሞ የተለየ ነው፤ አየሩ፣ ባሕሉና ቋንቋው አዲስ ሆነብን። የፈረንሳይኛ ቋንቋ መማር አስፈልጎን ነበር። መኖሪያ ቤት ማግኘትም ተቸግረን ነበር። እዚያ ከደረስን ከሁለት ቀን በኋላ ጊልያድ አብሮን የተማረው ሃሪ አርኖት እኛ ወዳለንበት መጣ፤ በዛምቢያ ወደሚገኘው የአገልግሎት ምድቡ እየተመለሰ ነበር። ቤት አፈላልገን እንድናገኝ ረዳን፤ ይህ ቤት የመጀመሪያው የሚስዮናውያን ቤት ሆነ። ብዙም ሳይቆይ ግን የአካባቢው ባለሥልጣናት ይቃወሙን ጀመር፤ እነዚህ ሰዎች ስለ ይሖዋ ምሥክሮች የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ልክ የአገልግሎት ምድቡን መውደድ ስንጀምር ባለ ሥልጣናቱ አስፈላጊው የሥራ ፈቃድ ከሌለን እዚያ መቆየት እንደማንችል ነገሩን። የሚያሳዝነው አገሪቱን ለቀን ለመውጣት ተገደድን፤ ኡጋንዳ ሄደን እንድናገለግል ተመደብን።

ቪዛ ሳይኖረን ኡጋንዳ መግባት አስፈርቶን የነበረ ቢሆንም በይሖዋ መታመናችን እንድንረጋጋ ረድቶናል። ለአገልግሎት ወደ ኡጋንዳ የመጣ አንድ ካናዳዊ ወንድም ሁኔታችንን ለአንድ የኢሚግሬሽን ባለሥልጣን አስረዳልን፤ በመሆኑም ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ እስክናገኝ ድረስ ለተወሰኑ ወራት እንድንኖር ተፈቀደልን። ይህ ሁኔታ ይሖዋ እየረዳን እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ሆኖልናል።

አዲሱ የአገልግሎት ምድባችን በቡሩንዲ ከነበረው በጣም ይለይ ነበር። ምንም እንኳ በመላ አገሪቱ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች 28 ብቻ ቢሆኑም የስብከቱ ሥራ ተጀምሮ ነበር። ክልላችን ውስጥ እንግሊዝኛ የሚናገሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ ግን ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እድገት እንዲያደርጉ ለመርዳት ከአገሪቱ ቋንቋዎች ቢያንስ አንዱን መማር እንደሚያስፈልገን ተገነዘብን። አገልግሎት የጀመርነው የሉጋንዳ ቋንቋ በስፋት ይነገርበት በነበረው በካምፓላ አካባቢ ነው፤ ስለዚህ ይህን ቋንቋ ለመማር ወሰንን። ቋንቋውን አቀላጥፈን ለመናገር የተወሰኑ ዓመታት ወስዶብናል፤ ሥራችን ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ግን ትልቅ ለውጥ አምጥቷል! የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን መንፈሳዊ ፍላጎት በተሻለ መንገድ ለመረዳት አስችሎናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንም እነሱን ለመርዳት የምናደርገውን ጥረት ማየታቸው ስለሚማሩት ነገር የልባቸውን አውጥተው እንዲነግሩን አነሳስቷቸዋል።

ወደተለያዩ ቦታዎች መጓዝ

ኡጋንዳ ውስጥ ወደተለያየ ቦታ በምንጓዝበት ወቅት

ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን እንዲማሩ መርዳት በራሱ አስደሳች ሥራ ነበር፤ በአገሪቱ ወደተለያዩ ቦታዎች እየተጓዝን እንድናገለግል ስንጠየቅ ደግሞ ይበልጥ ተደሰትን። የኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ በሰጠን መመሪያ መሠረት ልዩ አቅኚዎች የሚያስፈልጉባቸውን ቦታዎች ለይተን ለማወቅ አገሪቱን ማካለል ጀመርን። በጉዟችን ላይ የይሖዋ ምሥክሮችን አግኝተው የማያውቁ ሰዎች እንኳ ለየት ያለ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይተውናል። ሞቅ ያለ አቀባበል የሚያደርጉልን ከመሆኑም ሌላ ምግብ የተጋበዝንበት ጊዜም ነበር።

በኋላ ላይ ደግሞ ራቅ ብዬም መጓዝ ጀመርኩ። ከካምፓላ ተነስቼ ለሁለት ቀናት በባቡር ከተጓዝኩ በኋላ የኬንያ የወደብ ከተማ የሆነችው ሞምባሳ እደርሳለሁ፤ ከዚያም መርከብ ተሳፍሬ ወደ ሲሸልስ እሄዳለሁ፤ ሲሸልስ በሕንድ ውቅያኖስ ላይ ያሉ የተወሰኑ ደሴቶችን ያቀፈች አገር ናት። በኋላ ላይ ከ1965 እስከ 1972 ባሉት ዓመታት ወደ ሲሸልስ በማደርገው ጉዞ ባርባራም አብራኝ ትሄድ ጀመር። በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ሁለት አስፋፊዎች ብቻ በነበሩበት በዚህ ቦታ ቡድን ተቋቋመ፤ በኋላም ቡድኑ አድጎ ሞቅ ያለ ጉባኤ ሆነ። በሱዳን፣ በኢትዮጵያና በኤርትራ ያሉ ወንድሞችን ለመጎብኘትም የተለያዩ ጉዞዎች አድርጌአለሁ።

ኡጋንዳ ውስጥ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከተካሄደ በኋላ የፖለቲካው ሁኔታ በድንገት ተቀየረ። ከዚያ በኋላ ባሉት ሽብር የነገሠባቸው ዓመታት “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር [ስጡ]” የሚለውን መመሪያ መታዘዝ ያለውን ጥቅም ተመልክቻለሁ። (ማር. 12:17) በአንድ ወቅት፣ ሁሉም የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ነዋሪዎች በአቅራቢያቸው ወዳለ ፖሊስ ጣቢያ ሄደው እንዲመዘገቡ መመሪያ ወጥቶ ነበር። እኛም ወዲያውኑ እንደተባልነው አደረግን። ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአንድ ሚስዮናዊ ጋር ካምፓላ ውስጥ በመኪና እየሄድን ሳለ የደህንነት ፖሊሶች አስቁመው አነጋገሩን። በጣም ፈርተን ነበር! ሰላዮች ናችሁ ብለው ወደ ዋናው ፖሊስ ጣቢያ ይዘውን ሄዱ፤ እዚያም ሰላማዊ ሚስዮናውያን መሆናችንን ለማስረዳት ሞከርን። ፖሊስ ጣቢያ ሄደን እንደተመዘገብን ለመግለጽ ብንሞክርም ሊሰሙን ፈቃደኞች አልሆኑም። በኋላም አንድ የታጠቀ ወታደር የሚስዮናውያኑ ቤት አቅራቢያ ወደሚገኝ ፖሊስ ጣቢያ ይዞን እንዲሄድ ተደረገ። ደስ የሚለው ግን ፖሊስ ጣቢያው ውስጥ ቀደም ሲል እንደተመዘገብን የሚያውቅ አንድ ፖሊስ አገኘን፤ እሱም ገና ሲያየን ስላወቀን አጅቦን የመጣውን ጠባቂ እንዲለቀን ነገረው!

በዚያን ጊዜ በወታደሮች የሚጠበቁ ኬላዎችን አልፈን መሄድ በጣም ያስፈራን ነበር፤ ወታደሮቹ ሲጠጡ ከነበረ ደግሞ ሁኔታው የባሰ ነበር። በመሆኑም እነዚህን ኬላዎች በምናልፍበት ወቅት ሁልጊዜ እንጸልያለን፤ ይህም ልባችን እንዲረጋጋ ረድቶናል። የሚያሳዝነው በ1973 የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ሚስዮናውያን በሙሉ ኡጋንዳን ለቀው እንዲወጡ ትእዛዝ ተላለፈ።

የመንግሥት አገልግሎታችን ቅጂዎችን ሳባዛ፣ አቢጃን ውስጥ የሚገኘው የኮት ዲቩዋር ቅርንጫፍ ቢሮ

አሁንም ሌላ የአገልግሎት ምድብ ተሰጠን፤ በምዕራብ አፍሪካ ወደምትገኘው ወደ ኮት ዲቩዋር እንድንሄድ ተነገረን። ይህም ትልቅ ለውጥ ማድረግ ጠይቆብናል፤ ከምናውቀው የተለየ ባሕልን መልመድ፣ እንደገና ፈረንሳይኛ መናገር እንዲሁም የተለያየ ዘር ካላቸው ሚስዮናውያን ጋር መኖርን መልመድ አስፈልጎናል! በዚህ ጊዜም ይሖዋ እየረዳን እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ በግልጽ ተመልክተናል፤ በክልሉ ላይ የነበሩ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ለምሥራቹ ፈጣን ምላሽ ሲሰጡ ማየት ችለናል። ሁለታችንም በይሖዋ መታመናችን ጎዳናችንን እንዴት ቀና እንዳደረገልን ከራሳችን ተሞክሮ ተምረናል።

ከዚያም ባርባራ ካንሰር እንዳለባት በምርመራ ታወቀ። ይህ ፈጽሞ ያልጠበቅነው ነገር ነበር፤ ለየት ያለ ሕክምና እንድታገኝ ወደተለያዩ ቦታዎች ብንጓዝም በ1983 በአፍሪካ ማገልገላችንን መቀጠል እንደማንችል ተገነዘብን። ይህ ሁለታችንንም በጣም አሳዝኖን ነበር!

የሁኔታዎች መለወጥ

በለንደን ቤቴል እያገለገልን ሳለ የባርባራ ካንሰር እየተስፋፋ ሄደ፤ በኋላም ሕይወቷ አለፈ። በዚህ ጊዜ የቤቴል ቤተሰብ የብርታት ምንጭ ሆኖልኛል። በተለይ አንድ ባልና ሚስት ራሴን ከሁኔታው ጋር እንዳላምድና በይሖዋ መታመኔን እንድቀጥል ረድተውኛል። በኋላ ላይ ቤቴል እየተመላለሰች ከምታገለግል አንዲት እህት ጋር ተዋወቅኩ፤ ይህች እህት ልዩ አቅኚ የነበረች ሲሆን ይሖዋን እንደምትወድና መንፈሳዊ ሰው እንደሆነች በግልጽ ይታይ ነበር። በ1989 እኔና አን ተጋባን፤ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በለንደን ቤቴል እያገለገልን እንገኛለን።

እንግሊዝ ውስጥ በተገነባው አዲሱ ቤቴል ፊት ለፊት ከአን ጋር

ከ1995 እስከ 2018 ባሉት ዓመታት የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ (ቀደም ሲል የዞን የበላይ ተመልካች ይባል ነበር) በመሆን ወደ 60 የሚጠጉ አገሮችን የመጎብኘት መብት አግኝቻለሁ። በእያንዳንዱ ጉብኝት ላይ ይሖዋ አገልጋዮቹ ያሉበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን እነሱን እንዴት እንደሚባርካቸው የማየት አጋጣሚ አግኝቻለሁ።

የዋናው መሥሪያ ቤት ተወካይ ሆኜ ባደረግኳቸው ጉብኝቶች በ2017 ተመልሼ ወደ አፍሪካ ሄድኩ። አን ቡሩንዲን ስለማታውቀው ለመጀመሪያ ጊዜ አብረን ወደዚያ ስንሄድ በጣም ደስ አለኝ፤ ሁለታችንም በክልሉ ላይ በተገኘው እድገት በጣም ተገረምን! በ1964 ከቤት ወደ ቤት በሰበክሁበት መንገድ ላይ አሁን የሚያምር የቤቴል ሕንፃ ተሠርቷል፤ እንዲሁም በአገሪቱ ውስጥ ከ15,500 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ።

በ2018 የምጎበኛቸው አገሮች ዝርዝር ሲደርሰኝ በጣም ተደሰትኩ። ምክንያቱም በዝርዝሩ ውስጥ ኮት ዲቩዋር ትገኝበት ነበር። ዋና ከተማዋ አቢጃን ስንደርስ አገሬ የተመለስኩ ያህል ተሰምቶኝ ነበር። ቤቴል ባረፍንበት ክፍል ውስጥ የስልክ ቁጥር ማውጫውን ስመለከት ከእኛ ቀጥሎ ባለው ክፍል ውስጥ ሶሱ የሚባል ወንድም እንዳለ አየሁ። ይህን ስም ከዚህ በፊት አውቀዋለሁ፤ ያኔ አቢጃን በነበርኩበት ወቅት ይህ ወንድም የከተማ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለግል እንደነበር አስታወስኩ። ግን ተሳስቼ ነበር። ይሄኛው ሶሱ እኔ ያሰብኩት ሶሱ አይደለም፤ ለካስ የእሱ ልጅ ነው።

ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን ይጠብቃል። ብዙ ፈተናዎች ቢደርሱብንም በይሖዋ የምንታመን ከሆነ ጎዳናችንን ቀና እንደሚያደርግልን ከራሴ ተሞክሮ ተምሬያለሁ። ደግሞም በአዲሱ ዓለም ውስጥ ከአሁኑም የበለጠ እየደመቀ በሚሄደው ዘላለማዊ ጎዳና ላይ ጉዞ የምንቀጥልበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን።—ምሳሌ 4:18