በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 2

ኢየሱስ ‘ይወደው ከነበረው ደቀ መዝሙር’ የምናገኛቸው ትምህርቶች

ኢየሱስ ‘ይወደው ከነበረው ደቀ መዝሙር’ የምናገኛቸው ትምህርቶች

“እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው።”—1 ዮሐ. 4:7

መዝሙር 105 “አምላክ ፍቅር ነው”

ማስተዋወቂያ *

1. የአምላክ ፍቅር ምን እንዲሰማን ያደርጋል?

ሐዋርያው ዮሐንስ “አምላክ ፍቅር ነው” ሲል ጽፏል። (1 ዮሐ. 4:8) ይህ አጭር ዓረፍተ ነገር አንድ መሠረታዊ እውነታ ያስገነዝበናል፤ ይኸውም የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላክ የፍቅርም ምንጭ ነው። ይሖዋ ይወደናል! ፍቅሩ ደህንነት እንዲሰማን፣ ደስተኛ እንድንሆንና አርኪ ሕይወት እንዲኖረን ያደርጋል።

2. በማቴዎስ 22:37-40 ላይ የተገለጹት ሁለት ታላላቅ ትእዛዛት የትኞቹ ናቸው? ሁለተኛውን ትእዛዝ መጠበቅ የሚከብደንስ ለምን ሊሆን ይችላል?

2 ፍቅር ማሳየት ለክርስቲያኖች ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። ትእዛዝ ነው። (ማቴዎስ 22:37-40ን አንብብ።) ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ የመጀመሪያውን ትእዛዝ መፈጸም ቀላል ይሆንልናል። ምክንያቱም ይሖዋ ፍጹም ነው፤ እኛን የሚይዘንም በአሳቢነትና በደግነት ነው። ሁለተኛውን ትእዛዝ መፈጸም ግን አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም የቅርብ ባልንጀሮቻችን የሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ አሳቢነትና ደግነት የጎደለው ነገር ሊናገሩን ወይም ሊያደርጉብን ይችላሉ። ይሖዋ ይህ ተፈታታኝ ሁኔታ እንዳለብን ያውቃል፤ ስለዚህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እርስ በርስ መዋደድ ያለብን ለምን እና እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ቀጥተኛ ምክር እንዲጽፉልን አድርጓል። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ዮሐንስ ነው።—1 ዮሐ. 3:11, 12

3. ዮሐንስ ስለ ምን ነገር በአጽንኦት ተናግሯል?

3 ዮሐንስ በጻፋቸው ሐሳቦች ላይ ክርስቲያኖች ፍቅር ማሳየት እንዳለባቸው ጎላ አድርጎ ገልጿል። እንዲያውም ስለ ኢየሱስ ሕይወት በጻፈው ዘገባ ላይ ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች በድምሩ ከጻፉት የበለጠ ስለ ፍቅር በተደጋጋሚ ጠቅሷል። ዮሐንስ የወንጌል ዘገባውንና ሦስት ደብዳቤዎቹን በጻፈበት ወቅት ዕድሜው ወደ መቶ ዓመት እየተጠጋ ነበር። በመንፈስ መሪነት የተጻፉት እነዚህ መጻሕፍት አንድ ክርስቲያን ማንኛውንም ነገር በፍቅር ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ። (1 ዮሐ. 4:10, 11) ዮሐንስ ግን ይህን ለመማር ጊዜ ወስዶበታል።

4. ዮሐንስ ሁልጊዜ ለሌሎች ፍቅር ያሳይ ነበር?

4 ዮሐንስ ወጣት ሳለ ፍቅር ያላሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሰማርያን አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ነበር። የአንዲት የሳምራውያን መንደር ነዋሪዎች ግን በእንግድነት ሊቀበሏቸው ፈቃደኞች አልሆኑም። በዚህ ጊዜ ዮሐንስ ምን አደረገ? እሳት ከሰማይ ወርዶ የመንደሯን ነዋሪዎች እንዲያጠፋቸው ለማዘዝ ጥያቄ አቀረበ! (ሉቃስ 9:52-56) በሌላ ጊዜ ደግሞ ዮሐንስ ለሌሎቹ ሐዋርያት ፍቅር ሳያሳይ ቀርቷል። በዚህ ወቅት የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ትልቅ ቦታ ለልጆቿ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርባ ነበር፤ እናታቸው ይህን ጥያቄ እንድትጠይቅ የገፋፏት እነሱ ራሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ሌሎቹ ሐዋርያት፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ያደረጉትን ሲያውቁ በጣም ተቆጡ! (ማቴ. 20:20, 21, 24) ዮሐንስ እነዚህ ሁሉ ድክመቶች ቢኖሩበትም ኢየሱስ ይወደው ነበር።—ዮሐ. 21:7

5. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

5 በዚህ ርዕስ ላይ፣ ዮሐንስ ስለተወልን ምሳሌ እንዲሁም ስለ ፍቅር የጻፋቸውን አንዳንድ ሐሳቦች እንመረምራለን። ይህን ስናደርግ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ፍቅር ማሳየት ስለምንችልባቸው መንገዶች እንማራለን። በተጨማሪም አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ያለውን ፍቅር ማሳየት የሚችልበትን አንድ አስፈላጊ መንገድ እናያለን።

ፍቅር በተግባር የሚገለጽ ነገር ነው

ይሖዋ ልጁ ወደ ምድር መጥቶ ለእኛ እንዲሞትልን በማድረግ ፍቅሩን አሳይቶናል (ከአንቀጽ 6-7⁠ን ተመልከት)

6. ይሖዋ እንደሚወደን ያሳየው እንዴት ነው?

6 ብዙውን ጊዜ ፍቅር በስሜት ወይም በአንደበት የሚገለጽ ነገር እንደሆነ እናስብ ይሆናል። እውነተኛ ፍቅር ግን በተግባርም የተደገፈ ሊሆን ይገባል። (ከያዕቆብ 2:17, 26 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ይሖዋ ይወደናል። (1 ዮሐ. 4:19) ፍቅሩን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባስጻፋቸው ግሩም ቃላት ገልጾልናል። (መዝ. 25:10፤ ሮም 8:38, 39) እንደሚወደን ያሳመነን ግን የተናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ያደረገልንም ነገር ነው። ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።” (1 ዮሐ. 4:9) ይሖዋ የሚወደው ልጁ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት ፈቅዷል። (ዮሐ. 3:16) ታዲያ ይሖዋ እንደሚወደን የምንጠራጠርበት ምን ምክንያት አለ?

7. ኢየሱስ እንደሚወደን ያሳየን እንዴት ነው?

7 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንደሚወዳቸው ነግሯቸዋል። (ዮሐ. 13:1፤ 15:15) እነሱንም ሆነ እኛን ምን ያህል እንደሚወደን ያረጋገጠልን ግን የተናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ያደረገልንም ነገር ነው። ኢየሱስ “ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም” ብሏል። (ዮሐ. 15:13) ይሖዋና ኢየሱስ ያደረጉልንን ነገር ስናስብ ምን ለማድረግ እንነሳሳለን?

8. በ1 ዮሐንስ 3:18 ላይ ምን እንድናደርግ ታዘናል?

8 ይሖዋን እና ኢየሱስን እንደምንወዳቸው የምናሳየው እነሱን በመታዘዝ ነው። (ዮሐ. 14:15፤ 1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ ደግሞ እርስ በርስ እንድንዋደድ ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 13:34, 35) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው በቃል መግለጽ ብቻ ሳይሆን በተግባር ልናሳይም ይገባል። (1 ዮሐንስ 3:18ን አንብብ።) ታዲያ ለእነሱ ያለንን ፍቅር በየትኞቹ መንገዶች ማሳየት እንችላለን?

ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ውደዱ

9. ዮሐንስ ፍቅር ምን እንዲያደርግ አነሳስቶታል?

9 ዮሐንስ ከአባቱ ጋር ለመቆየት ቢወስን ኖሮ ቤተሰቡ በሚያካሂደው ዓሣ የማጥመድ ንግድ ተሰማርቶ ሀብት ማፍራት ይችል ነበር። እሱ ግን ቀሪ ሕይወቱን በሙሉ ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ እንዲማሩ እየረዳ ለመኖር መርጧል። ዮሐንስ የመረጠው ሕይወት ቀላል አልነበረም። ስደት ደርሶበታል፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን መጨረሻ በዕድሜ ገፍቶ በነበረበት ወቅትም በግዞት ላይ ነበር። (ሥራ 3:1፤ 4:1-3፤ 5:18፤ ራእይ 1:9) ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ በመስበኩ የተነሳ ታስሮ በነበረበት ወቅትም እንኳ ለሌሎች ያለውን ፍቅር በተግባር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ በጳጥሞስ ደሴት ሳለ የተመለከተውን ራእይ በጽሑፍ በማስፈር ለጉባኤዎቹ ልኮላቸዋል፤ ይህን ያደረገው ጉባኤዎቹ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን” ነገሮች እንዲያውቁ ለመርዳት ነበር። (ራእይ 1:1) ከዚያም ከጳጥሞስ ደሴት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚተርከውን የወንጌል ዘገባ በጽሑፍ አስፍሯል። በተጨማሪም ወንድሞቹንና እህቶቹን ለማበረታታትና ለማጠናከር ሦስት ደብዳቤዎችን ጽፏል። ታዲያ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ሕይወት በመምራት ረገድ ዮሐንስ የተወውን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው?

10. ለሰዎች ያላችሁን ፍቅር ማሳየት የምትችሉት እንዴት ነው?

10 የምትመርጡት የሕይወት ጎዳና ለሰዎች ያላችሁን ፍቅር ሊያሳይ ይችላል። የሰይጣን ሥርዓት ስለ ራሳችሁ ጥቅም ብቻ እንድታስቡ ይኸውም ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ሁሉ ገንዘብ ወይም ዝና በማሳደድ ላይ እንድታውሉ ይፈልጋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ግን በተቻለ መጠን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያውሉት ምሥራቹን ለመስበክና ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ ሙሉ ጊዜያቸውን ሰጥተዋል።

ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን እንዲሁም ለቤተሰባችን የምናደርገው ነገር እንደምንወዳቸው ያሳያል (አንቀጽ 11, 17⁠ን ተመልከት) *

11. ብዙ ታማኝ አስፋፊዎች ለይሖዋም ሆነ ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ያላቸውን ፍቅር በተግባር እያሳዩ ያሉት እንዴት ነው?

11 ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሙሉ ጊዜ ሥራ መሥራት ያስፈልጋቸዋል። ያም ቢሆን እነዚህ ታማኝ አስፋፊዎች በቻሉት ሁሉ የአምላክን ድርጅት ለመደገፍ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በእርዳታ ሥራ እንዲሁም በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እገዛ ያበረክታሉ፤ እንዲሁም ሁሉም አስፋፊዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ይችላሉ። እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ለአምላክና ለባልንጀራቸው ያላቸው ፍቅር ነው። ሁላችንም በየሳምንቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር በተግባር እናሳያለን። ድካም ቢሰማንም ከስብሰባ አንቀርም። በስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠት ቢያስፈራንም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አንልም። እንዲሁም ሁላችንም የየራሳችን ችግሮች ያሉብን ቢሆንም ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ሌሎችን ለማበረታታት ጥረት እናደርጋለን። (ዕብ. 10:24, 25) ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሚያከናውኑት ሥራ ምንኛ አመስጋኞች ነን!

12. ዮሐንስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ያለውን ፍቅር ያሳየበት ሌላው መንገድ ምንድን ነው?

12 ዮሐንስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ያለውን ፍቅር ያሳየው እነሱን በማመስገን ብቻ ሳይሆን ምክር በመስጠትም ጭምር ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በደብዳቤዎቹ ላይ ወንድሞቹንና እህቶቹን ስለ እምነታቸው እንዲሁም ስላከናወኗቸው መልካም ሥራዎች አመስግኗቸዋል፤ ሆኖም ኃጢአትን በተመለከተ ቀጥተኛ ምክርም ሰጥቷቸዋል። (1 ዮሐ. 1:8–2:1, 13, 14) እኛም በተመሳሳይ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ስላከናወኗቸው መልካም ነገሮች ልናመሰግናቸው ይገባል። ይሁንና አንድ ሰው የተሳሳተ አካሄድ እየተከተለ እንደሆነ ካስተዋልን በዘዴ ተገቢውን ምክር በመስጠት ፍቅራችንን ልናሳየው ይገባል። ለሌሎች ምክር መስጠት ድፍረት ይጠይቃል፤ ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ፣ እውነተኛ ወዳጅ ጓደኛውን እንደሚስለው ወይም እንደሚያርመው ይገልጻል።—ምሳሌ 27:17

13. ምን ከማድረግ ልንቆጠብ ይገባል?

13 አንዳንድ ጊዜ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር የምናሳየው አንዳንድ ነገሮችን ባለማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሚናገሩት ነገር ቶሎ ቅር አንሰኝም። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተከሰተን አንድ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ሥጋውን ካልበሉና ደሙን ካልጠጡ ሕይወት እንደማያገኙ ለደቀ መዛሙርቱ ተናገረ። (ዮሐ. 6:53-57) ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ስለሰቀጠጣቸው ትተውት ሄዱ፤ ዮሐንስን ጨምሮ እውነተኛ ወዳጆቹ ግን ይህን አላደረጉም። በታማኝነት ከእሱ ጋር ጸንተዋል። እነሱም ቢሆኑ ኢየሱስ የተናገረው ነገር አልገባቸውም፤ ምናልባትም የተናገረው ነገር አስደንግጧቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ታማኝ ወዳጆቹ ኢየሱስ የተሳሳተ ነገር እንደተናገረ አላሰቡም፤ እንዲሁም ቅር አልተሰኙም። ከዚህ ይልቅ እውነቱን እንደሚናገር ስለሚያውቁ አምነውታል። (ዮሐ. 6:60, 66-69) እንግዲያው ወዳጆቻችን በሚናገሩት ነገር ቶሎ ቅር አለመሰኘታችን ምንኛ ተገቢ ነው! የተናገሩት ነገር ካልገባን እስኪያስረዱን ድረስ እንታገሣለን።—ምሳሌ 18:13፤ መክ. 7:9

14. ጥላቻ በልባችን ውስጥ እንዲያቆጠቁጥ መፍቀድ የሌለብን ለምንድን ነው?

14 ዮሐንስ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዳንጠላም ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። ይህን ማሳሰቢያ ችላ ካልን ሰይጣን እንዲጠቀምብን ዕድል እንሰጠዋለን። (1 ዮሐ. 2:11፤ 3:15) በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ጥላቻና ክፍፍል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ዮሐንስ ደብዳቤዎቹን በጻፈበት ወቅት የሰይጣን ዓይነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች ወደ ጉባኤው ሾልከው ገብተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዲዮጥራጢስ በአንድ ጉባኤ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል ፈጥሮ ነበር። (3 ዮሐ. 9, 10) ከበላይ አካሉ ተልከው ለሚመጡ ወንድሞች አክብሮት አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ እሱ የሚጠላቸውን ሰዎች በእንግድነት የተቀበሉ ክርስቲያኖችን ከጉባኤው ለማባረር ጥረት አድርጓል። እንዴት ያለ እብሪተኝነት ነው! ሰይጣን ዛሬም ቢሆን የአምላክን ሕዝቦች ለመከፋፈል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እንግዲያው ጥላቻ በመካከላችን ክፍፍል እንዲፈጥር ፈጽሞ አንፍቀድ።

ቤተሰባችሁን ውደዱ

ኢየሱስ እናቱን በቁሳዊም ሆነ በመንፈሳዊ እንዲንከባከባት ለዮሐንስ አደራ ሰጥቶታል። በዛሬው ጊዜ ያሉ የቤተሰብ ራሶች፣ ቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር የማሟላት ኃላፊነት አለባቸው (ከአንቀጽ 15-16⁠ን ተመልከት)

15. አንድ የቤተሰብ ራስ ምን ማስታወስ ይኖርበታል?

15 አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ ያለውን ፍቅር የሚያሳይበት አንዱ ወሳኝ መንገድ ቁሳዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። (1 ጢሞ. 5:8) ያም ቢሆን ቁሳዊ ነገሮች የቤተሰቡን መንፈሳዊ ፍላጎት ሊያሟሉ እንደማይችሉ ማስታወስ አለበት። (ማቴ. 5:3) ኢየሱስ ለቤተሰብ ራሶች ምን ምሳሌ እንደተወ እስቲ እንመልከት። በዮሐንስ ወንጌል ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሊሞት እያጣጣረ በነበረበት ወቅትም እንኳ የቤተሰቡ ጉዳይ እንደሚያሳስበው አሳይቷል። ኢየሱስ በተሰቀለበት ቦታ ዮሐንስ ከኢየሱስ እናት ከማርያም ጋር ቆሞ ነበር። ኢየሱስ በከፍተኛ ሥቃይ ውስጥ ሆኖ እየቃተተ በነበረበት በዚያ ወቅት ማርያምን እንዲንከባከባት ለዮሐንስ አደራ ሰጠው። (ዮሐ. 19:26, 27) ኢየሱስ ወንድሞችና እህቶች ስለነበሩት ማርያምን በቁሳዊ ነገር ረገድ እንደሚንከባከቧት መገመት እንችላለን፤ ሆኖም በወቅቱ አንዳቸውም ቢሆኑ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆኑ አይመስልም። ስለዚህ ኢየሱስ፣ ማርያም በቁሳዊ ብቻ ሳይሆን በመንፈሳዊም እንክብካቤ እንድታገኝ ፈልጎ ነበር።

16. ዮሐንስ ምን ኃላፊነቶች ነበሩበት?

16 ዮሐንስ ብዙ ኃላፊነቶች ነበሩበት። ሐዋርያ እንደመሆኑ መጠን በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅበታል። ዮሐንስ አግብቶ ሊሆን እንደሚችልም እንገምታለን፤ ይህ ከሆነ የቤተሰቡን ቁሳዊም ሆነ መንፈሳዊ ፍላጎት በማሟላት ረገድ ሚዛኑን መጠበቅ ነበረበት። (1 ቆሮ. 9:5) ታዲያ በዛሬው ጊዜ ያሉ የቤተሰብ ራሶች ከዚህ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

17. አንድ የቤተሰብ ራስ ከቤተሰቡ ጋር በተያያዘ ምን ትልቅ ኃላፊነት አለበት? ኃላፊነቱን መወጣቱስ ቤተሰቡን የሚጠቅመው እንዴት ነው?

17 የቤተሰብ ራስ የሆነ አንድ ወንድም ብዙ ከባድ ኃላፊነቶች ሊኖሩበት ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ሰብዓዊ ሥራውን በትጋት ማከናወን ይኖርበታል፤ ምክንያቱም በሥራ ቦታ የሚያሳየው ምግባር የይሖዋን ስም እንደሚነካ ያውቃል። (ኤፌ. 6:5, 6፤ ቲቶ 2:9, 10) በጉባኤ ውስጥም ኃላፊነቶች ይኖሩት ይሆናል፤ ለምሳሌ እረኝነት ማድረግና በስብከቱ ሥራ ግንባር ቀደም መሆን ይጠበቅበት ይሆናል። በሌላ በኩል ደግሞ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ሆኖ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሮ ማጥናቱ በጣም አስፈላጊ ነው። የቤተሰቡ አባላት የእነሱን ቁሳዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የሚያደርገውን ጥረት ማድነቃቸው አይቀርም።—ኤፌ. 5:28, 29፤ 6:4

‘በፍቅሬ ኑሩ’

18. ዮሐንስ ስለ ምን ነገር እርግጠኛ ነበር?

18 ዮሐንስ ባሳለፈው ረጅም ዕድሜ ብዙ ነገር አይቷል። እምነቱን ሊያዳክሙ የሚችሉ ብዙ ፈተናዎች አጋጥመውታል። ሆኖም የኢየሱስን ትእዛዛት ለመጠበቅ ምንጊዜም የቻለውን ሁሉ ያደርግ ነበር፤ ከእነዚህ ትእዛዛት አንዱ ደግሞ ወንድሞቹንና እህቶቹን እንዲወድ የተሰጠው ትእዛዝ ነው። ዮሐንስ እንዲህ ዓይነት ታዛዥነት ስላሳየ ይሖዋና ኢየሱስ እንደሚወዱት እንዲሁም ማንኛውንም ፈተና ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት እንደሚሰጡት እርግጠኛ ነበር። (ዮሐ. 14:15-17፤ 15:10፤ 1 ዮሐ. 4:16) ሰይጣንም ሆነ እሱ ያዋቀረው ሥርዓት ዮሐንስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ ፍቅር እንዳይኖረው እንዲሁም ፍቅሩን በቃልም ሆነ በተግባር እንዳይገልጽ አላገዱትም።

19. አንደኛ ዮሐንስ 4:7 ምን እንድናደርግ ያበረታታናል? እንዲህ ማድረግ ያለብንስ ለምንድን ነው?

19 እንደ ዮሐንስ ሁሉ እኛም የምንኖረው በጥላቻ የተሞላው ሰይጣን በሚቆጣጠረው ዓለም ውስጥ ነው። (1 ዮሐ. 3:1, 10) ሰይጣን ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እንዲጠፋ ለማድረግ ይጥራል፤ ሆኖም እኛ እስካልፈቀድንለት ድረስ ይህ ሊሳካለት አይችልም። እንግዲያው ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ለመውደድ እንዲሁም ፍቅራችንን በአንደበትም ሆነ በተግባር ለመግለጽ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። እንዲህ ካደረግን የይሖዋ ቤተሰብ ክፍል መሆን የሚያስገኘውን ደስታ እናጣጥማለን፤ ይህ ደግሞ ሕይወታችን እውነተኛ ትርጉም እንዲኖረው ያደርጋል።1 ዮሐንስ 4:7ን አንብብ።

መዝሙር 88 መንገድህን አሳውቀኝ

^ አን.5 “ኢየሱስ ይወደው የነበረው ደቀ መዝሙር” ተብሎ የተጠራው ሐዋርያው ዮሐንስ እንደሆነ ይታመናል። (ዮሐ. 21:7) ስለዚህ ገና ከወጣትነቱ ጀምሮ ብዙ የሚወደዱ ባሕርያት እንደነበሩት መገመት እንችላለን። ከዓመታት በኋላ ይሖዋ፣ ይህ ሐዋርያ ስለ ፍቅር ብዙ እንዲጽፍ አድርጓል። በዚህ ርዕስ ላይ ዮሐንስ የጻፋቸውን አንዳንድ ሐሳቦች መለስ ብለን እንመለከታለን፤ እንዲሁም ከእሱ ምሳሌ ምን እንደምንማር እናያለን።

^ አን.59 የሥዕሉ መግለጫ፦ ብዙ ኃላፊነቶች ያሉበት አንድ የቤተሰብ ራስ በእርዳታ ሥራ እገዛ ሲያበረክት፣ ዓለም አቀፉን ሥራ ለመደገፍ መዋጮ ሲያደርግ እንዲሁም ሌሎች ሰዎችን ጋብዞ ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር የቤተሰብ አምልኮ ሲያደርግ።