በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 4

ከልብ ለመዋደድ ጥረት አድርጉ

ከልብ ለመዋደድ ጥረት አድርጉ

“በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ።”—ሮም 12:10

መዝሙር 109 አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ

ማስተዋወቂያ *

1. ተፈጥሯዊ ፍቅር እየጠፋ እንደሆነ የሚጠቁሙ ምን ነገሮች እያየን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ፣ በመጨረሻው ዘመን ሰዎች “ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው” እንደሚሆኑ አስቀድሞ ተናግሯል። (2 ጢሞ. 3:1, 3) ይህ ትንቢት በዘመናችን ሲፈጸም እየተመለከትን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በፍቺ ምክንያት ሲፈርሱ እየተመለከትን ነው። ፍቺ በፈጸሙት ወላጆች መካከል ጥላቻ ይኖር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው እንደማይወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋል። የቤተሰብ አባላት፣ በአንድ ጣሪያ ሥር ቢኖሩም እንኳ የሚኖሩት እንደ ደባል ሊሆን ይችላል። አንድ የቤተሰብ አማካሪ እንዲህ ብለዋል፦ “አባት፣ እናትና ልጆች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ተቋርጧል፤ አሁን ግንኙነታቸው ከኮምፒውተራቸው፣ ከታብሌታቸው፣ ከስልካቸው ወይም ከቪዲዮ ጌማቸው ጋር ነው። እነዚህ ቤተሰቦች፣ በአንድ ጣሪያ ሥር እየኖሩም ጭራሽ አይተዋወቁም ሊባል ይችላል።”

2-3. (ሀ) በሮም 12:10 መሠረት ለእነማን ልባዊ ፍቅር ማሳየት አለብን? (ለ) በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

2 ፍቅር የሌለው ይህ ዓለም እንዲቀርጸን አንፈልግም። (ሮም 12:2) ከዚህ ይልቅ ለቤተሰባችን አባላት ብቻ ሳይሆን በእምነት ለሚዛመዱን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ልባዊ ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። (ሮም 12:10ን አንብብ።) ታዲያ ከልብ መዋደድ ሲባል ምን ማለት ነው? ከልብ መዋደድ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በቅርብ የቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን የጠበቀ ፍቅር ያመለክታል። ለመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት ማለትም ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማዳበር ይኖርብናል። ልባዊ ፍቅር ስናሳይ በመካከላችን ያለው አንድነት እንዲጠበቅ እናደርጋለን፤ አንድነት ደግሞ ለእውነተኛው አምልኮ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።—ሚክ. 2:12

3 ልባዊ ፍቅር በማዳበርና በማሳየት ረገድ የሚጠቅሙን አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን እስቲ እንመልከት።

“እጅግ አፍቃሪ” የሆነው ይሖዋ

4. ያዕቆብ 5:11 ስለ ይሖዋ ፍቅር ምን ይላል?

4 መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ ማራኪ ባሕርያት ይናገራል። ለምሳሌ “አምላክ ፍቅር ነው” ይላል። (1 ዮሐ. 4:8) ይህ አባባል በራሱ ወደ ይሖዋ እንድንቀርብ ያነሳሳናል። ይህ ብቻ ሳይሆን “ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ” እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ያዕቆብ 5:11ን አንብብ።) ይሖዋ ለእኛ ያለውን ጥልቅ ስሜት የሚያሳይ እንዴት ያለ ግሩም አገላለጽ ነው!

5. ይሖዋ ምሕረት የሚያሳየው እንዴት ነው? እኛስ እሱን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው?

5 ያዕቆብ 5:11 ይሖዋ አፍቃሪ ስለመሆኑ ከተናገረ በኋላ ስለ መሐሪነቱ ይገልጻል፤ ምሕረት ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሳን ሌላው ባሕርይ ነው። (ዘፀ. 34:6) ይሖዋ ለእኛ ምሕረት የሚያሳይበት አንዱ መንገድ ስህተቶቻችንን ይቅር ማለት ነው። (መዝ. 51:1) ምሕረት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ አገባቡ ከይቅር ባይነት ያለፈ ሰፊ ትርጉም አለው። ምሕረት፣ አንድ የተቸገረ ሰው ስናይ እንድናዝንለትና እሱን ለመርዳት እርምጃ እንድንወስድ የሚያነሳሳ ጥልቅ ስሜት ነው። ይሖዋ፣ እሱ እኛን ለመርዳት እንዲነሳሳ የሚያደርገው ጥልቅ ስሜት፣ እናት ለልጇ ካላት ስሜትም እንኳ እንደሚበልጥ ገልጿል። (ኢሳ. 49:15) ችግር ላይ ስንወድቅ፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳት የሚያነሳሳው ምሕረቱ ነው። (መዝ. 37:39፤ 1 ቆሮ. 10:13) እኛም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቅር ሲያሰኙን ይቅር በማለትና ቂም ባለመያዝ ምሕረት ማሳየት እንችላለን። (ኤፌ. 4:32) ምሕረት የምናሳይበት ሌላው ዋነኛ መንገድ ግን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግር ላይ ሲወድቁ መርዳት ነው። በፍቅር ተነሳስተን ለሌሎች ምሕረት ስናሳይ ልባዊ ፍቅር በማሳየት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለውን ይሖዋን እንመስለዋለን።—ኤፌ. 5:1

“የጠበቀ ወዳጅነት” የነበራቸው ዮናታንና ዳዊት

6. ዮናታንና ዳዊት ከልብ እንደሚዋደዱ ያሳዩት እንዴት ነው?

6 መጽሐፍ ቅዱስ ልባዊ ፍቅር ስላሳዩ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። ዮናታንንና ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ፤ ዮናታንም እንደ ራሱ ወደደው” ይላል። (1 ሳሙ. 18:1) ዳዊት በሳኦል ምትክ እንዲነግሥ ተቀብቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሳኦል በዳዊት ስለቀና ሊገድለው ፈለገ። የሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን ግን አባቱ ዳዊትን ለመግደል በከፈተው ዘመቻ ተባባሪ መሆን አልፈለገም። ዮናታንና ዳዊት ወዳጅነታቸውን ጠብቀው ለመኖርና ምንጊዜም እርስ በርስ ለመደጋገፍ ቃል ተጋብተው ነበር።—1 ሳሙ. 20:42

የዕድሜ ልዩነት ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት እንዳይመሠርቱ እንቅፋት አልሆነባቸውም (ከአንቀጽ 6-9⁠ን ተመልከት)

7. ዮናታንና ዳዊት ጓደኛሞች እንዳይሆኑ እንቅፋት ሊሆንባቸው የሚችለው አንዱ ነገር ምን ነበር?

7 ዮናታንና ዳዊት ጓደኛሞች እንዳይሆኑ እንቅፋት ሊሆኑባቸው የሚችሉ ነገሮችን ስናስብ እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረታቸው ይበልጥ ያስገርመናል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው ነበር። ዮናታን በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ በጣም ከሚያንሰው ከዚህ ወጣት ጋር ምንም የጋራ ነገር እንደሌላቸው ሊያስብ ይችል ነበር። ያም ቢሆን ዮናታን ዳዊትን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተውም።

8. ዮናታን ለዳዊት እንዲህ ያለ ጥሩ ወዳጅ እንዲሆን ያስቻለው ምን ይመስልሃል?

8 ዮናታን በዳዊት ላይ ቅናት ሊያድርበት ይችል ነበር። የንጉሥ ሳኦል ልጅ እንደመሆኑ መጠን ዮናታን ‘ዙፋኑ የሚገባው ለእኔ ነው’ የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችል ነበር። (1 ሳሙ. 20:31) ዮናታን ግን ትሑት ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ ታማኝ ነበር። በመሆኑም ዳዊት ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ ያደረገውን ውሳኔ በሙሉ ልቡ ደግፏል። ዮናታን ለዳዊትም ታማኝ ነበር፤ ይህ ሳኦልን ቢያስቆጣውም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላለም።—1 ሳሙ. 20:32-34

9. ዮናታን ዳዊትን እንደ ተቀናቃኙ አድርጎ ተመልክቶታል? አብራራ።

9 ዮናታን ዳዊትን ከልቡ ይወደው ስለነበር ተቀናቃኙ አድርጎ አልተመለከተውም። ዮናታን የተዋጣለት ቀስተኛና ጀግና ተዋጊ ነበር። እሱና አባቱ ሳኦል “ከንስር ይልቅ ፈጣኖች፣ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች” የሚል ስም አትርፈው ነበር። (2 ሳሙ. 1:22, 23) በመሆኑም ዮናታን በጦርነት ስላከናወናቸው ጀብዱዎች ጉራውን ሊነዛ ይችል ነበር። ዮናታን ግን የፉክክር ወይም የቅናት መንፈስ አልነበረበትም። ከዚህ ይልቅ ዳዊትን በድፍረቱና በይሖዋ ላይ ባለው እምነት አድንቆታል። እንዲያውም ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ የወደደው፣ ዳዊት ጎልያድን ከገደለው በኋላ ነው። እኛስ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን እንዲህ ያለ ልባዊ ፍቅር ማሳየት የምችለው እንዴት ነው?

በዛሬው ጊዜ ልባዊ ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10. ‘አጥብቆ ከልብ መዋደድ’ ሲባል ምን ማለት ነው?

10 መጽሐፍ ቅዱስ “እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ” በማለት ይመክረናል። (1 ጴጥ. 1:22) ይሖዋ በዚህ ረገድ ምሳሌ ትቶልናል። እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር በጣም ጥልቅ ነው፤ እኛ ታማኝነታችንን እስከጠበቅን ድረስ እሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ሊበጥሰው የሚችል ነገር የለም። (ሮም 8:38, 39) “አጥብቃችሁ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “በኃይል መንጠራራት” የሚል ሐሳብ በውስጡ ይዟል። የእምነት ባልንጀራችንን ከልብ ለመውደድ በኃይል መንጠራራት የሚያስፈልገን ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ‘እርስ በርሳችን በፍቅር መቻቻልና’ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” ማድረግ ያስፈልገናል። (ኤፌ. 4:1-3) ‘የሰላምን ማሰሪያ’ ለመጠበቅ ጥረት የምናደርግ ከሆነ በወንድሞቻችን ድክመቶች ላይ ትኩረት አናደርግም። ወንድሞቻችንን በይሖዋ ዓይን ለማየት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን።—1 ሳሙ. 16:7፤ መዝ. 130:3

ኤዎድያንና ሲንጤኪ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው ምክር ተሰጥቷቸዋል፤ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ባለን ግንኙነት አንድ ዓይነት አስተሳሰብ መያዝ ሁልጊዜ ቀላል ላይሆን ይችላል (አንቀጽ 11⁠ን ተመልከት)

11. ልባዊ ፍቅር ማሳየት አንዳንድ ጊዜ ከባድ የሚሆንብን ለምን ሊሆን ይችላል?

11 ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ነው ማለት አይደለም፤ በተለይ ድክመቶቻቸውን የምናውቅ ከሆነ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ ተፈታታኝ ሳይሆንባቸው አልቀረም። ለምሳሌ ያህል፣ ኤዎድያንና ሲንጤኪ “ለምሥራቹ ሲሉ [ከጳውሎስ ጎን] ተሰልፈው” መሥራት የከበዳቸው አይመስልም። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባናውቅም እርስ በርስ ግን መስማማት ተቸግረው ነበር። ስለዚህ “በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” ጳውሎስ መክሯቸዋል።—ፊልጵ. 4:2, 3

ወጣትና በዕድሜ የገፉ የጉባኤ ሽማግሌዎች የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ (አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት)

12. ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ለማዳበር ምን ማድረግ እንችላለን?

12 ታዲያ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻችንን እያወቅናቸው ስንሄድ እነሱን መረዳትና ከልብ መውደድ ቀላል ይሆንልናል። ዕድሜ ወይም ያለንበት የተለያየ ሁኔታ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው እንደነበረ አስታውሱ፤ ሆኖም ይህ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳይመሠርት አላገደውም። እናንተስ በዕድሜ ከሚበልጧችሁ ወይም ከሚያንሷችሁ የእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ትችሉ ይሆን? እንዲህ በማድረግ “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር” እንዳላችሁ ታሳያላችሁ።—1 ጴጥ. 2:17

አንቀጽ 12⁠ን ተመልከት *

13. በጉባኤ ውስጥ ካሉት ሁሉ ጋር እኩል ቅርበት ሊኖረን የማይችለው ለምንድን ነው?

13 ለእምነት ባልንጀሮቻችን ልባዊ ፍቅር እናሳያለን ሲባል በጉባኤ ውስጥ ካሉ ሁሉም ክርስቲያኖች ጋር እኩል ቀረቤታ ይኖረናል ማለት ነው? እንዲህ ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ ነው። በጋራ በሚያመሳስሉን ነገሮች የተነሳ አንዳንዶችን ከሌሎች አስበልጠን መቅረባችን ስህተት አይደለም። ኢየሱስ ሁሉንም ሐዋርያቱን ‘ወዳጆቼ’ ብሎ የጠራቸው ቢሆንም ዮሐንስን አብልጦ ይወደው ነበር። (ዮሐ. 13:23፤ 15:15፤ 20:2) ሆኖም ኢየሱስ ለዮሐንስ አላዳላም። ለምሳሌ ያህል፣ ዮሐንስና ወንድሙ ያዕቆብ በአምላክ መንግሥት ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት ወቅት ኢየሱስ “በቀኜ ወይም በግራዬ መቀመጥ . . . በእኔ ፈቃድ የሚሆን አይደለም” ብሎ መልሶላቸዋል። (ማር. 10:35-40) የኢየሱስን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ ለምንቀርባቸው ወዳጆቻችን አናዳላም። (ያዕ. 2:3, 4) እንዲህ ማድረግ ክፍፍል እንዲፈጠር ሊያደርግ ይችላል፤ ክፍፍል ደግሞ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ቦታ የለውም።—ይሁዳ 17-19

14. በፊልጵስዩስ 2:3 ላይ በተገለጸው መሠረት የፉክክር መንፈስ እንዳይፈጠር የሚረዳን ምንድን ነው?

14 አንዳችን ለሌላው ልባዊ ፍቅር የምናሳይ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ የፉክክር መንፈስ እንዳይፈጠር አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንደምናስታውሰው፣ ዮናታን የፉክክር መንፈስ አልነበረውም፤ ዳዊትን ዙፋኑን እንደሚነጥቅ ተቀናቃኝ አድርጎ አልተመለከተውም። ዮናታን ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ባሏቸው ችሎታዎች የተነሳ እንደ ተቀናቃኝ አድርጋችሁ አትመልከቷቸው፤ ከዚህ ይልቅ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።” (ፊልጵስዩስ 2:3ን አንብብ።) እያንዳንዱ ክርስቲያን በጉባኤው ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አትርሱ። በትሕትና ለራሳችን ትክክለኛውን አመለካከት ከያዝን የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን መልካም ጎን ማየት እንዲሁም ከእነሱ ግሩም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ቀላል ይሆንልናል።—1 ቆሮ. 12:21-25

15. ታኒያና ቤተሰቧ ካጋጠማቸው ነገር ምን ትምህርት አግኝተሃል?

15 ያልተጠበቁ ችግሮች ሲያጋጥሙን ይሖዋ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በሚያሳዩን ልባዊ ፍቅርና በሚሰጡን ተግባራዊ እርዳታ አማካኝነት ያጽናናናል። አንድ ቤተሰብ ያጋጠመውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ይህ ቤተሰብ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በ2019 “ፍቅር ለዘላለም ይኖራል” በሚል ርዕስ ከተካሄዱት ብሔራት አቀፍ ስብሰባዎች በአንዱ ላይ ተገኝቶ ነበር። የቅዳሜውን ዕለት ፕሮግራም ተካፍለው ሲመለሱ አንድ ነገር አጋጠማቸው። የሦስት ልጆች እናት የሆነችው ታኒያ ስላጋጠማቸው ነገር ስትናገር እንዲህ ብላለች፦ “በመኪና ወደ ሆቴላችን እየተመለስን ሳለ አንድ መኪና ፍሬን በጥሶ እየተንደረደረ ወደ እኛ አቅጣጫ መጣና ገጨን። ማናችንም ጉዳት አልደረሰብንም፤ ግን ከመደናገጣችን የተነሳ ከመኪናችን ወጥተን መሐል መንገድ ላይ ቆመን ቀረን። አንድ ሰው መንገድ ዳር ላይ መኪናውን አቁሞ ወደ እሱ መኪና እንድንገባ በእጁ ምልክት ይሰጠን ጀመር፤ መሐል መንገድ ላይ ቆመን ሌላ መኪና እንዳይገጨን ፈርቶ ነበር። ይህ ሰው ወንድማችን ነው፤ እሱም ከስብሰባ እየተመለሰ ነበር። የቆመው ግን እሱ ብቻ አልነበረም። ከስዊድን የመጡ አምስት ልዑካንም እኛን ለመርዳት ቆመው ነበር። እህቶች እኔንና ልጄን እቅፍ አደረጉን፤ ይህ በጣም አረጋጋን! ‘ከዚህ በኋላ ምንም አንሆንም’ ብላቸውም ትተውን ሊሄዱ አልፈለጉም። የሕክምና እርዳታ የሚሰጡት ሰዎች ከመጡ በኋላም እንኳ ከእኛ አልተለዩም፤ የሚያስፈልገን ነገር ሁሉ መሟላቱን ማረጋገጥ ፈልገው ነበር። በዚያ አስቸጋሪ ወቅት የይሖዋን ፍቅር በብዙ መንገድ አይተናል። ይህ ገጠመኝ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር እንዲጨምር አድርጓል፤ ለይሖዋ ያለንን ፍቅርና አድናቆትም አሳድጎታል።” እናንተስ እንዲህ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ አጋጥሟችሁ የእምነት ባልንጀራችሁ ልባዊ ፍቅር ያሳያችሁን አጋጣሚ ታስታውሳላችሁ?

16. እርስ በርስ ከልብ እንድንዋደድ የሚያነሳሱን ምክንያቶች የትኞቹ ናቸው?

16 እርስ በርስ ከልብ መዋደዳችን ምን ጥቅሞች እንዳሉት እስቲ ለማሰብ ሞክር። ችግር ላይ የወደቁ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን ለማጽናናት ያስችለናል። በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እናደርጋለን። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን እናሳያለን፤ ይህ ደግሞ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳቡ ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ግን “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን እናስደስተዋለን። (2 ቆሮ. 1:3) እንግዲያው ሁላችንም ልባዊ ፍቅር ለማዳበርና ለማሳየት ጥረት ማድረጋችንን እንቀጥል!

መዝሙር 130 ይቅር ባይ ሁኑ

^ አን.5 ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። ሁላችንም እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ለማሳየት ጥረት እናደርጋለን። ወንድሞቻችንን ከልባችን ለመውደድ ጥረት በማድረግ ለእነሱ ያለንን ፍቅር ማሳደግ ይኖርብናል፤ ይህም ሲባል የቅርብ የቤተሰባችንን አባላት የምንወዳቸውን ያህል ወንድሞቻችንንም ልንወዳቸው ይገባል ማለት ነው። ይህ ርዕስ በእምነት ለሚዛመዱን ሰዎች ያለንን ልባዊ ፍቅር ለማሳደግ ይረዳናል።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንድ ወጣት የጉባኤ ሽማግሌ በዕድሜ ከገፋ ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ ሥልጠና እያገኘ ነው፤ ወጣቱ ሽማግሌ በዕድሜ የገፋው ሽማግሌ ቤት ተጋብዟል። ሁለቱ የጉባኤ ሽማግሌዎችም ሆኑ ሚስቶቻቸው አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና ልግስና እያሳዩ ነው።