ይህን ያውቁ ኖሯል?
ድንጋይ ላይ የተቀረጸ አንድ ጥንታዊ ጽሑፍ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት ነው?
ኢየሩሳሌም ባለው ባይብል ላንድስ ሙዚየም ውስጥ፣ ጽሑፍ የተቀረጸበት አንድ ድንጋይ አለ፤ ጽሑፉ የተቀረጸው ከ700-600 ዓ.ዓ. ባለው ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ይገመታል። ድንጋዩ የተገኘው እስራኤል ውስጥ በኬብሮን አቅራቢያ ባለ አንድ የመቃብር ዋሻ ውስጥ ነው። የተቀረጸው ጽሑፍ “የሃጋቭ ልጅ ሃጋፍ በያህዌህ ጸባኦት የተረገመ ይሁን” ይላል። ይህ የተቀረጸ ጽሑፍ የመጽሐፍ ቅዱስን ሐሳብ የሚደግፈው እንዴት ነው? የሐወሐ በተባሉት ጥንታዊ የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈው የአምላክ ስም፣ በጥንት ዘመን በደንብ የሚታወቅና ሰዎች በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው የሚጠቀሙበት ስም እንደነበረ ይጠቁማል። እንዲያውም ይህን የሚደግፉ በመቃብር ዋሻዎች ውስጥ ተቀርጸው የተገኙ ሌሎች ጽሑፎች አሉ፤ እነዚህ ጽሑፎች እንደሚያሳዩት፣ ወደ ዋሻዎቹ ይመጡና በዚያ ይሸሸጉ የነበሩ ሰዎች የአምላክን ስምና ስሙን የያዙ የግለሰብ ስሞችን በግድግዳ ላይ የመጻፍ ልማድ ነበራቸው።
በጆርጂያ ዩኒቨርሲቲ የሚሠሩት ዶክተር ሬቸል ናቡልሲ፣ እነዚህን የተቀረጹ ጽሑፎች በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “የሐወሐ የተባለው ስም በተደጋጋሚ መገኘቱ ትኩረት የሚስብ ነው። . . . [ቅዱሳን] መጻሕፍትም ሆኑ የተቀረጹ ጽሑፎች፣ የሐወሐ በእስራኤልና በይሁዳ ትልቅ ቦታ ይሰጠው እንደነበር ይጠቁማሉ።” ይህ እውነታ መጽሐፍ ቅዱስን ይደግፋል፤ ምክንያቱም የሐወሐ በተባሉት የዕብራይስጥ ፊደላት የተጻፈው የአምላክ ስም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ጊዜያት ይገኛል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሰው የሚገኙ የግለሰብ ስሞችም ብዙውን ጊዜ የአምላክን ስም የያዙ ናቸው።
በድንጋዩ ላይ የተቀረጸው “ያህዌህ ጸባኦት” የሚለው ጽሑፍ፣ “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚል ትርጉም አለው። ይህም በጥንት ዘመን፣ የአምላክ ስም ብቻ ሳይሆን “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽም የተለመደ እንደነበር ይጠቁማል። ከዚህ አንጻር “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ” የሚለው አገላለጽ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከ250 ጊዜ በላይ የተጠቀሰ መሆኑ አያስገርምም፤ ይህ አገላለጽ በአብዛኛው የሚገኘው ኢሳይያስ፣ ኤርምያስ እና ዘካርያስ በጻፏቸው መጻሕፍት ላይ ነው።