በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት

በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት

በዚህ ሰንጠረዥ ላይ የተጠቀሱ አንዳንድ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በተመሳሳይ ጊዜ ላይ ነው። ትንቢቶቹ በሙሉ፣ የምንኖረው ‘በፍጻሜው ዘመን’ እንደሆነ በተለያየ መንገድ ያረጋግጣሉ።—ዳን. 12:4

  • ጥቅስ፦ ራእይ 11:7፤ 12:13, 17፤ 13:1-8, 12

    ትንቢት፦ “አውሬው” የምድርን ነዋሪዎች ለበርካታ መቶ ዘመናት ይገዛል። በፍጻሜው ዘመን የአውሬው ሰባተኛ ራስ ይቆስላል። በኋላ ላይ ይህ ራስ ቁስሉ ይድንለታል፤ “ምድርም ሁሉ” አውሬውን ይከተለዋል። ሰይጣን ይህን አውሬ በመጠቀም ‘ቀሪዎቹን ይዋጋል።’

    ፍጻሜ፦ ከጥፋት ውኃ በኋላ ይሖዋን የሚቃወሙ ሰብዓዊ መንግሥታት ተነስተዋል። ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ፣ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የብሪታንያ መንግሥት በእጅጉ ተዳክሞ ነበር። ሆኖም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ጥምረት ሲፈጥር ማንሰራራት ቻለ። በተለይ በፍጻሜው ዘመን ሰይጣን በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለውን የፖለቲካ ሥርዓት ተጠቅሞ የአምላክን ሕዝቦች ያሳድዳል።

  • ጥቅስ፦ ዳን. 11:25-45

    ትንቢት፦ በፍጻሜው ዘመን በሰሜኑ ንጉሥና በደቡቡ ንጉሥ መካከል የሚኖረው ሽኩቻ።

    ፍጻሜ፦ የጀርመን መንግሥትና የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ተቀናቃኝ ሆኑ። በ1945 ሶቪየት ኅብረት እና አጋሮቹ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኑ። በ1991 ሶቪየት ኅብረት ፈራረሰ፤ ከጊዜ በኋላ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኑ።

  • ጥቅስ፦ ኢሳ. 61:1፤ ሚል. 3:1፤ ሉቃስ 4:18

    ትንቢት፦ ይሖዋ፣ መሲሐዊው መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ‘መንገድ የሚጠርግ መልእክተኛ’ ይልካል። “መልእክተኛ” የሚሆነው ቡድን “የዋህ ለሆኑ ሰዎች ምሥራች” ይናገራል።

    ፍጻሜ፦ ከ1870ዎቹ ዓመታት አንስቶ ቻርልስ ቴዝ ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችን ለማብራራት ትጋት የተሞላበት ጥረት አድርገዋል። በ1880ዎቹ ዓመታት ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች መስበክ እንዳለባቸው ጎላ አድርገው መግለጽ ጀመሩ። ካወጧቸው ርዕሶች መካከል “1,000 ሰባኪዎች ያስፈልጋሉ” እና “ለስብከት መቀባት” የሚሉት ይገኙበታል።

  • ጥቅስ፦ ማቴ. 13:24-30, 36-43

    ትንቢት፦ አንድ ጠላት በስንዴ ማሳ ላይ እንክርዳድ ይዘራል፤ እስከ መከር ወቅት ድረስ እንክርዳዱ ከስንዴው ጋር እንዲያድግ ይተዋል፤ ስንዴውም በእንክርዳዱ ይዋጣል፤ ከዚያም እንክርዳዱን ከስንዴው የመለየቱ ሥራ ይከናወናል።

    ፍጻሜ፦ ከ1800ዎቹ ዓመታት መገባደጃ አንስቶ በእውነተኛ ክርስቲያኖችና በሐሰተኛ ክርስቲያኖች መካከል ያለው ልዩነት ይበልጥ ግልጽ እየሆነ መጣ። በፍጻሜው ዘመን እውነተኛ ክርስቲያኖች ይሰበሰባሉ፤ እንዲሁም ከሐሰተኛ ክርስቲያኖች ይለያሉ።

  • ጥቅስ፦ ዳን. 2:31-33, 41-43

    ትንቢት፦ የብረትና የሸክላ እግር፤ ይህ እግር ከተለያዩ የብረት ዓይነቶች የተሠራው ምስል ክፍል ነው።

    ፍጻሜ፦ ሸክላው፣ በአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ግዛት ውስጥ የሚደረጉ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ያመለክታል። እነዚህ ንቅናቄዎች ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት እንደ ብረት ያለ ጥንካሬውን እንዳይጠቀምበት ያዳክሙታል።

  • ጥቅስ፦ ማቴ. 13:30፤ 24:14, 45፤ 28:19, 20

    ትንቢት፦ “ስንዴው” ወደ “ጎተራ” ይሰበሰባል፤ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” “በቤተሰቦቹ” ላይ ይሾማል። “የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር” መሰበክ ይጀምራል።

    ፍጻሜ፦ በ1919 ታማኙ ባሪያ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ተሾመ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች የስብከቱን ሥራ አጧጧፉት። በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ከ200 በሚበልጡ አገሮች ውስጥ እየሰበኩ ነው፤ እንዲሁም ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያዘጋጃሉ።

  • ጥቅስ፦ ዳን. 12:11፤ ራእይ 13:11, 14, 15

    ትንቢት፦ ባለ ሁለት ቀንዱ አውሬ፣ ‘ለአውሬው ምስል እንዲሠራ’ ትእዛዝ ያስተላልፋል፤ ‘ለምስሉም እስትንፋስ ይሰጠዋል።’

    ፍጻሜ፦ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት፣ ቅድሚያውን ወስዶ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር የተባለ ድርጅት እንዲቋቋም አድርጓል። ሌሎች አገራትም ይህን ድርጅት ተቀላቅለዋል። ከጊዜ በኋላ የሰሜኑ ንጉሥም ይህን ማኅበር ተቀላቅሏል፤ ሆኖም ኅብረት ፈጥሮ የቆየው ከ1926 እስከ 1933 ብቻ ነበር። በኋላ ላይ እንደተቋቋመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሁሉ ይህ ማኅበርም ለአምላክ መንግሥት ብቻ የሚገባው እውቅና ተሰጥቶታል።

  • ጥቅስ፦ ዳን. 8:23, 24

    ትንቢት፦ አስፈሪ መልክ ያለው ንጉሥ “ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት ያደርሳል።”

    ፍጻሜ፦ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ብዙ ጥፋት አድርሷል። ለምሳሌ ያህል፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል ጠላት በሆነ አገር ላይ ሁለት አቶሚክ ቦምቦች ጥሏል፤ ይህም ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ጥፋት አስከትሏል።

  • ጥቅስ፦ ዳን. 11:31፤ ራእይ 17:3, 7-11

    ትንቢት፦ አሥር ቀንዶች ያሉት “ደማቅ ቀይ” አውሬ ከጥልቁ ይወጣል፤ ስምንተኛ ንጉሥም ይሆናል። ይህ ንጉሥ፣ በዳንኤል መጽሐፍ ላይ ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር’ ተብሎ ተጠርቷል።

    ፍጻሜ፦ የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር፣ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከእንቅስቃሴ ውጭ ሆኖ ነበር። ከጦርነቱ በኋላ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋቋመ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከእሱ በፊት እንደነበረው የቃል ኪዳኑ ማኅበር ሁሉ ለአምላክ መንግሥት የሚገባው ክብር ተሰጥቶታል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ በሃይማኖት ላይ ጥቃት ይሰነዝራል።

  • ጥቅስ፦ 1 ተሰ. 5:3፤ ራእይ 17:16

    ትንቢት፦ ብሔራት “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” ብለው ያውጃሉ፤ “አሥሩ ቀንዶች” እና “አውሬው” “አመንዝራዋን” ያጠቋታል እንዲሁም ያጠፏታል። ከዚያም በብሔራት ላይ ጥፋት ይመጣል።

    ፍጻሜ፦ ብሔራት፣ ሰላም እና ደህንነት ማስፈን እንደቻሉ ይናገራሉ። ከዚያም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑ ብሔራት፣ የሐሰት ሃይማኖት ተቋማትን ያጠፋሉ። ይህም ታላቁ መከራ እንደጀመረ የሚያሳይ ምልክት ይሆናል። ይህ መከራ የሚያበቃው መላው የሰይጣን ሥርዓት በአርማጌዶን ሲደመሰስ ነው።

  • ጥቅስ፦ ሕዝ. 38:11, 14-17፤ ማቴ. 24:31

    ትንቢት፦ ጎግ የአምላክን ሕዝቦች ምድር ይወርራል። ከዚያም መላእክት “የተመረጡትን” ይሰበስባሉ።

    ፍጻሜ፦ የሰሜኑ ንጉሥ ከሌሎቹ የዓለም መንግሥታት ጋር በመሆን በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ይህ ጥቃት ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ፣ የቀሩት ቅቡዓን ወደ ሰማይ ይሰበሰባሉ።

  • ጥቅስ፦ ሕዝ. 38:18-23፤ ዳን. 2:34, 35, 44, 45፤ ራእይ 6:2፤ 16:14, 16፤ 17:14፤ 19:20

    ትንቢት፦ ‘በነጭ ፈረስ’ ላይ “የተቀመጠው” ጋላቢ፣ ጎግንና ሠራዊቱን በማጥፋት ‘ድሉን ያጠናቅቃል።’ “አውሬው” ‘ወደ እሳት ሐይቅ ይወረወራል’፤ ትልቁ ምስልም ይደቅቃል።

    ፍጻሜ፦ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሆነው ኢየሱስ የአምላክ ሕዝቦችን ይታደጋል። ከ144,000 ተባባሪ ገዢዎችና ከመላእክት ሠራዊት ጋር በመሆን ኢየሱስ፣ ጥምረት የፈጠሩ ብሔራትን ያጠፋል፤ መላው የሰይጣን ሥርዓት በዚህ መንገድ ይጠፋል።