በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 21

ከአምላክ ላገኘሃቸው ስጦታዎች አድናቆት አለህ?

ከአምላክ ላገኘሃቸው ስጦታዎች አድናቆት አለህ?

“ይሖዋ አምላኬ ሆይ፣ ያደረግካቸው ድንቅ ሥራዎች፣ ለእኛ ያሰብካቸው ነገሮችም ብዙ ናቸው።”—መዝ. 40:5

መዝሙር 5 የአምላክ ድንቅ ሥራዎች

ማስተዋወቂያ *

1-2. በመዝሙር 40:5 ላይ እንደተገለጸው ይሖዋ ምን ስጦታዎች ሰጥቶናል? ስለ እነዚህ ስጦታዎች መመርመራችን ምን ጥቅም አለው?

ይሖዋ ለጋስ አምላክ ነው። ከእሱ ካገኘናቸው ስጦታዎች መካከል ስለ አንዳንዶቹ እስቲ ለማሰብ ሞክር፤ ለምሳሌ ውብና ልዩ የሆነችውን ምድራችንን፣ አስደናቂ ንድፍ ያለውን አንጎላችንን እንዲሁም ውድ የሆነውን የአምላክን ቃል መጽሐፍ ቅዱስን መጥቀስ ይቻላል። ይሖዋ እነዚህን ሦስት ስጦታዎች ስለሰጠን መኖሪያ ማግኘት ችለናል፣ የማሰብና ከሌሎች ጋር የመነጋገር ችሎታ አለን እንዲሁም በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎቻችን መልስ አግኝተናል።መዝሙር 40:5ን አንብብ።

2 በዚህ ርዕስ ውስጥ ስለ እነዚህ ሦስት ስጦታዎች በአጭሩ እንመለከታለን። በእነዚህ ስጦታዎች ላይ ባሰላሰልን መጠን አድናቆታችን እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም አፍቃሪ የሆነውን ፈጣሪያችንን ይሖዋን ለማስደሰት ይበልጥ እንነሳሳለን። (ራእይ 4:11) በተጨማሪም የሐሰት ትምህርት በሆነው በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ የተታለሉ ሰዎችን በተሻለ መንገድ ለመርዳት ዝግጁ እንሆናለን።

ልዩ የሆነችው ፕላኔታችን

3. ምድራችንን ለየት የሚያደርጋት ምንድን ነው?

3 አምላክ መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን የሠራበት መንገድ ጥበበኛ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። (ሮም 1:20፤ ዕብ. 3:4) ከምድር በተጨማሪ ሌሎች ፕላኔቶችም ፀሐይን ይዞራሉ፤ ምድራችንን ለየት የሚያደርጋት ግን ለሰው ልጆች መኖሪያ ምቹ እንድትሆን የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ አሟልታ የያዘች መሆኗ ነው።

4. ምድራችን ከየትኛውም ሰው ሠራሽ ጀልባ የተሻለች ናት የምንለው ለምንድን ነው?

4 ምድር በሕዋ ውስጥ ያለችበት ሁኔታ፣ ሰፊ በሆነ ውቅያኖስ ላይ ከምትንሳፈፍ ጀልባ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሁንና ምድራችን በርካታ ሰዎችን ካሳፈረች ሰው ሠራሽ ጀልባ ጋር ስትነጻጸር ጉልህ ልዩነቶች አሏት። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ጀልባ ላይ የተሳፈሩ ሰዎች የራሳቸውን ኦክስጅን፣ ምግብና ውኃ ማምረት ቢጠበቅባቸው እንዲሁም ቆሻሻን ወደ ውጭ መጣል ባይችሉ ምን ያህል ጊዜ በሕይወት ሊቆዩ ይችላሉ? በዚያ ጀልባ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ይሞታሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ ምድራችን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ታሟላለች። ምድራችን የሚያስፈልገንን ኦክስጅን፣ ምግብና ውኃ ታመርታለች፤ እንዲሁም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ነገሮች ፈጽሞ አያልቁም። ምድር ቆሻሻዎችንም ወደ ጠፈር አትጥልም፤ ያም ቢሆን ምንጊዜም ውብና ለመኖር አመቺ ናት። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምድራችንን የሠራት፣ የሚጣሉ ነገሮችን ወደ ጠቃሚ ነገር ለመቀየር የሚያስችሉ ዑደቶች እንዲኖሯት አድርጎ ነው። ከእነዚህ አስደናቂ ዑደቶች መካከል እስቲ ሁለቱን እንመልከት፤ እነሱም የኦክስጅን ዑደትና የውኃ ዑደት ናቸው።

5. የኦክስጅን ዑደት ምንድን ነው? ይህ ዑደት ምን ያረጋግጣል?

5 ኦክስጅን እኛን ጨምሮ አንዳንድ ሕያዋን ፍጥረታት በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ጋዝ ነው። ሕያዋን ፍጥረታት በየዓመቱ ወደ ሰውነታቸው የሚያስገቡት ኦክስጅን መጠን መቶ ቢሊዮን ቶን እንደሚሆን ይገመታል። እነዚህ ፍጥረታት ካርቦንዳይኦክሳይድ የተባለ ጋዝ ያስወጣሉ። ሆኖም እነዚህ ፍጥረታት በምድር ላይ ያለውን ኦክስጅን አይጨርሱትም፤ እንዲሁም ከባቢ አየሩ እነሱ በሚያስወጡት ካርቦንዳይኦክሳይድ አይሞላም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ከትንሹ አልጌ አንስቶ እስከ ትላልቅ ዛፎች ያሉ ዕፀዋትን ፈጥሯል፤ እነዚህ ዕፀዋት ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ውስጥ አስገብተው ኦክስጅንን ያስወጣሉ። በእርግጥም የኦክስጅን ዑደት በሐዋርያት ሥራ 17:24, 25 ላይ የሚገኘውን ‘አምላክ ሕይወትንና እስትንፋስን ለሰው ሁሉ ይሰጣል’ የሚለውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው።

6. የውኃ ዑደት ምንድን ነው? ይህ ዑደት ምን ያረጋግጣል? (“ የይሖዋ ስጦታ የሆነው የውኃ ዑደት” የሚለውን ሣጥንም ተመልከት።)

6 ውኃ በምድር ላይ በፈሳሽ መልክ ሊገኝ የቻለው ፕላኔታችን ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ ስለተቀመጠች ነው። ፕላኔታችን ወደ ፀሐይ ትንሽ ቀረብ ብትል ኖሮ በምድር ላይ ያለው ውኃ በሙሉ ተንኖ ያልቅ ነበር፤ በመሆኑም ምድራችን ሕይወት የሌለባት ደረቅ ስፍራ ትሆን ነበር። ምድር ከፀሐይ ትንሽ ራቅ ብትል ኖሮ ደግሞ ውኃው በሙሉ ስለሚረጋ ምድራችን በበረዶ ትሸፈን ነበር። ይሖዋ ምድርን ያስቀመጣት ትክክለኛው ቦታ ላይ ነው፤ በመሆኑም የምድር የውኃ ዑደት ሕይወት እንዲቀጥል አስችሏል። ፀሐይ የምታመነጨው ሙቀት በውቅያኖሶችና በምድር ገጽ ላይ ያለው ውኃ እንዲተን ያደርጋል፤ ከዚያም ደመና ይፈጠራል። በየዓመቱ በፀሐይ ሙቀት የተነሳ የሚተንነው ውኃ 500,000 ኪሎ ሜትር ኩብ ገደማ (በምድር ላይ ባሉት በሁሉም ሐይቆች ውስጥ ካለው ውኃ የሚበልጥ) ይሆናል። የተነነው ውኃ ከባቢ አየር ላይ ለአሥር ቀናት ያህል ከቆየ በኋላ በዝናብ መልክ ይወርዳል። ውሎ አድሮም ውኃው ወደ ውቅያኖሶች ወይም ወደ ሌሎች የውኃ አካላት ይገባል፤ ከዚያም ይኸው ዑደት እንደገና ይደገማል። ይህ ውጤታማና የማይቋረጥ ዑደት ይሖዋ ጥበበኛና ኃያል አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።—ኢዮብ 36:27, 28፤ መክ. 1:7

7. በመዝሙር 115:16 ላይ ለተገለጸው ስጦታ አድናቆት ማሳየት የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

7 አስደናቂ ለሆነችው ፕላኔታችን እና ከእሷ ለምናገኛቸው ነገሮች አድናቆት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (መዝሙር 115:16ን አንብብ።) ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል ነው። ይህም ይሖዋ ለሚሰጠን መልካም ነገሮች በየዕለቱ እሱን እንድናመሰግነው ያነሳሳናል። ከዚህም ሌላ የምንኖርበትን አካባቢ በንጽሕና ለመያዝ የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ለምድር ያለንን አድናቆት እናሳያለን።

አስደናቂ የሆነው አንጎላችን

8. አንጎላችን አስደናቂ ንድፍ ተንጸባርቆበታል የምንለው ለምንድን ነው?

8 አንጎላችን አስደናቂ ንድፍ የተንጸባረቀበት የአካላችን ክፍል ነው። በእናትህ ማህፀን ውስጥ በነበርክበት ወቅት፣ አንጎልህ አስቀድሞ የተቀመጠለትን ንድፍ ተከትሎ ተሠርቷል፤ በየደቂቃው በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የአንጎል ሴሎች ይሠሩ ነበር! የአንድ አዋቂ ሰው አንጎል፣ ኒውሮን ተብለው የሚጠሩ 100 ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሴሎች እንዳሉት ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ወደ 1.5 ኪሎ ግራም ገደማ ክብደት ያለው አንጎላችን የተገነባው በእነዚህ ሴሎች ነው። አንጎላችን ካሉት አስደናቂ ችሎታዎች መካከል እስቲ ጥቂቶቹን እንመልከት።

9. የመናገር ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ መሆኑን የሚያሳምንህ ምንድን ነው?

9 የመናገር ችሎታችን በጣም አስደናቂ ነው። በምንናገርበት ወቅት ምን እንደሚከናወን እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። እያንዳንዱን ቃል ስትጠራ አንጎልህ በምላስህ፣ በጉሮሮህ፣ በከንፈሮችህ፣ በመንገጭላህ እና በደረትህ ላይ የሚገኙ ወደ 100 የሚጠጉ ጡንቻዎችን እንቅስቃሴ ማቀናጀት ያስፈልገዋል። የምትናገራቸው ቃላት ጥርት ብለው መሰማት እንዲችሉ እነዚህ ጡንቻዎች ትክክለኛውን ቅደም ተከተል ጠብቀው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። አንድን ቋንቋ የመናገር ችሎታን በተመለከተ በ2019 የወጣ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው አራስ ሕፃናት ቃላትን ነጥለው የማወቅ ችሎታ አላቸው። ይህ ግኝት፣ ስንወለድ ጀምሮ ቋንቋን ለይተን የማወቅና የመማር ችሎታ እንዳለን የሚያሳይ ነው። በእርግጥም የመናገር ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው።—ዘፀ. 4:11

10. ከአምላክ በስጦታ ላገኘነው የመናገር ችሎታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

10 ከአምላክ በስጦታ ላገኘነው የመናገር ችሎታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ በዝግመተ ለውጥ ለምን እንደማናምን ለሚጠይቁን ሰዎች አምላክ መኖሩን የምናምንበትን ምክንያት ማስረዳት ነው። (መዝ. 9:1፤ 1 ጴጥ. 3:15) ይህን ጽንሰ ሐሳብ የሚያስፋፉ ሰዎች፣ ምድርና በላይዋ ያለው ሕይወት በሙሉ በአጋጣሚ የተገኙ እንደሆኑ ሊያሳምኑን ይሞክራሉ። መጽሐፍ ቅዱስን እና በዚህ ርዕስ ላይ የተጠቀሱትን አንዳንድ ነጥቦች በመጠቀም ለሰማዩ አባታችን ጥብቅና መቆም እንችላለን፤ ለማዳመጥ ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ደግሞ ይሖዋ የሰማይና የምድር ፈጣሪ እንደሆነ የምናምንበትን ምክንያት ልናስረዳቸው እንችላለን።—መዝ. 102:25፤ ኢሳ. 40:25, 26

11. አንጎላችንን አስደናቂ የሚያደርገው አንዱ ነገር ምንድን ነው?

11 የማስታወስ ችሎታችን በጣም አስደናቂ ነው። የሰው አንጎል በ20 ሚሊዮን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው ጋር የሚተካከል መረጃ ማስታወስ እንደሚችል አንድ ደራሲ ከዚህ ቀደም ገምተው ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን፣ የማስታወስ ችሎታችን ከዚህ በጣም የላቀ እንደሆነ ይታመናል። ታዲያ ይህ፣ የሰው ልጆች ምን ለየት ያለ ችሎታ እንዲኖራቸው አድርጓል?

12. የሥነ ምግባር ትምህርት የመቅሰም ችሎታችን ከእንስሳት የሚለየን እንዴት ነው?

12 በምድር ላይ ከሚገኙት ፍጥረታት መካከል፣ ቀደም ሲል ያጋጠማቸውን ነገር አስታውሰው ከሁኔታው የሥነ ምግባር ትምህርት የመቅሰም ችሎታ ያላቸው የሰው ልጆች ብቻ ናቸው። የተሻሉ መሥፈርቶችን መከተል ብሎም በአስተሳሰባችንና በአኗኗራችን ላይ ለውጥ ማድረግ የምንችለው ለዚህ ነው። (1 ቆሮ. 6:9-11፤ ቆላ. 3:9, 10) እንዲያውም ሕሊናችንን፣ ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር እንዲለይ ማሠልጠን እንችላለን። (ዕብ. 5:14) ፍቅርን፣ ርኅራኄንና ምሕረትን ማሳየትን መማር እንችላለን። በተጨማሪም ተገቢ የሆነ የፍትሕ ስሜት ማዳበር እንችላለን።

13. በመዝሙር 77:11, 12 መሠረት የማስታወስ ችሎታችንን እንዴት ልንጠቀምበት ይገባል?

13 ስጦታ ለሆነው የማስታወስ ችሎታችን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳትና ለማጽናናት ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ ለማስታወስ ጥረት ማድረግ ነው። ይህን ማድረጋችን ይሖዋ ወደፊትም እንደሚረዳን ያለንን እምነት ያጠናክርልናል። (መዝሙር 77:11, 12⁠ን አንብብ፤ 78:4, 7) አድናቆታችንን የምናሳይበት ሌላው መንገድ ደግሞ ሌሎች ሰዎች ያደረጉልንን መልካም ነገር አስታውሰን አመስጋኝነታችንን መግለጽ ነው። አመስጋኝ የሆኑ ሰዎች በሕይወታቸው ይበልጥ ደስተኛ እንደሚሆኑ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ነገሮችን በመርሳት ይሖዋን መምሰላችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ቢኖረውም ለሠራነው ጥፋት ንስሐ ከገባን ስህተታችንን ይቅር ለማለትና ለመርሳት ፈቃደኛ ነው። (መዝ. 25:7፤ 130:3, 4) እኛም የበደሉን ሰዎች በሠሩት ጥፋት ከተጸጸቱ ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ይሖዋ ይጠብቅብናል።—ማቴ. 6:14፤ ሉቃስ 17:3, 4

አንጎላችንን ይሖዋን ለማክበር በመጠቀም ከእሱ ላገኘነው ለዚህ ስጦታ አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን (አንቀጽ 14⁠ን ተመልከት) *

14. አስደናቂ ስጦታ ለሆነው ለአንጎላችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

14 አስደናቂ ስጦታ ለሆነው አንጎላችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ስጦታውን የሰጠንን አካል በሚያስከብር መንገድ አንጎላችንን መጠቀም ነው። አንዳንዶች አንጎላቸውን የሚጠቀሙበት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት ነው። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን ይሖዋ ስለሆነ፣ የእሱ መሥፈርቶች እኛ ለራሳችን ከምናወጣቸው ከየትኞቹም መሥፈርቶች የላቁ እንደሆኑ ጥያቄ የለውም። (ሮም 12:1, 2) የይሖዋን መሥፈርቶች ስንከተል ሰላማዊ ሕይወት መምራት እንችላለን። (ኢሳ. 48:17, 18) በተጨማሪም ፈጣሪያችንን እና አባታችንን በሚያስከብርና እሱን በሚያስደስት መንገድ ስለምንኖር ሕይወታችን እውነተኛ ዓላማ ያለው ይሆናል።—ምሳሌ 27:11

ውድ ስጦታ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ

15. ስጦታ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር የሚያሳየው እንዴት ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ የሰጠን ስጦታ ነው። ሰማያዊው አባታችን ሰዎችን በመንፈሱ በመምራት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ለምድራዊ ልጆቹ በጥልቅ ስለሚያስብ ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት፣ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎቻችን መልስ ሰጥቶናል። ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ‘ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?’ የሚሉት ይገኙበታል። ይሖዋ ሁሉም ልጆቹ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንዲያውቁ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለፉት በርካታ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የተወሰነው ክፍል ከ3,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል! የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመና በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። በዓለም ላይ የሚኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የማንበብ አጋጣሚ አላቸው።—“ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ አፍሪካ ቋንቋዎች መተርጎም” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

16. በማቴዎስ 28:19, 20 እንዲሁም በአንቀጹ ላይ በተገለጸው ሐሳብ መሠረት ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?

16 መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ፣ በመልእክቱ ላይ በማሰላሰል እንዲሁም የተማርነውን ነገር በተግባር ለማዋል የምንችለውን ያህል በመጣር ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች በመናገር ለአምላክ ምስጋናችንን መግለጽ እንችላለን።—መዝ. 1:1-3፤ ማቴ. 24:14፤ ማቴዎስ 28:19, 20ን አንብብ።

17. በዚህ ርዕስ ላይ ስለ የትኞቹ ስጦታዎች ተመልክተናል? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

17 በዚህ ርዕስ ውስጥ፣ ከአምላክ ካገኘናቸው ስጦታዎች መካከል መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን፣ አስደናቂ ንድፍ ያለውን አንጎላችንን እንዲሁም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን መጽሐፍ ቅዱስን ተመልክተናል። ሆኖም ይሖዋ በዓይን የማይታዩ ሌሎች ስጦታዎችም ሰጥቶናል። በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ስለ እነዚህ ስጦታዎች እንመለከታለን።

መዝሙር 12 ታላቁ አምላክ ይሖዋ

^ አን.5 ይህ ርዕስ ለይሖዋ እና ከእሱ ላገኘናቸው ሦስት ስጦታዎች ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ከዚህም ሌላ አምላክ መኖሩን ለሚጠራጠሩ ሰዎች አሳማኝ ማስረጃ ለማቅረብ ይረዳናል።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ አንዲት እህት በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን እውነት ከሌላ አገር ለመጡ ሰዎች ለማስተማር ስትል የሌላ አገር ቋንቋ ስትማር።