በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 19

‘የሰሜኑ ንጉሥ’ በፍጻሜው ዘመን

‘የሰሜኑ ንጉሥ’ በፍጻሜው ዘመን

“በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ [ከሰሜኑ ንጉሥ] ጋር ይጋፋል።”—ዳን. 11:40

መዝሙር 150 ትድኑ ዘንድ አምላክን ፈልጉ

ማስተዋወቂያ *

1. የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ይገልጽልናል?

በቅርቡ የይሖዋ ሕዝቦች ምን ያጋጥማቸዋል? የዚህን ጥያቄ መልስ መገመት አያስፈልገንም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ሁላችንንም ስለሚነኩ ወሳኝ ክንውኖች ፍንጭ ይሰጠናል። በተለይ አንድ ትንቢት፣ በምድር ላይ የሚነሱ አንዳንድ ኃያላን መንግሥታት ምን እንደሚያደርጉ ይገልጽልናል። በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ይህ ትንቢት፣ ተቀናቃኝ ስለሆኑ ሁለት የፖለቲካ ኃይሎች ማለትም ስለ ሰሜኑ ንጉሥና ስለ ደቡቡ ንጉሥ ይናገራል። የዚህ ትንቢት አብዛኛው ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል፤ በመሆኑም የቀረው የትንቢቱ ክፍልም እንደሚፈጸም መተማመን እንችላለን።

2. በዘፍጥረት 3:15 እንዲሁም በራእይ 11:7 እና 12:17 ላይ በተገለጸው መሠረት የዳንኤልን ትንቢት ስንመረምር ግምት ውስጥ ማስገባት ያሉብን ነገሮች የትኞቹ ናቸው?

2 በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ለመረዳት፣ ትንቢቱ የሚገልጸው ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸው ገዢዎችና መንግሥታት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ደግሞም የአምላክ አገልጋዮች ከዓለም ሕዝብ አንጻር ሲታዩ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ወሳኝ ክንውኖች በእጅጉ ይነኳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ፣ የይሖዋንና የኢየሱስን አገልጋዮች ድል መንሳት ነው። (ዘፍጥረት 3:15ን፣ ራእይ 11:7⁠ን እና 12:17ን አንብብ።) ይህን የዳንኤል ትንቢት ስንመረምር ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ሌላው ነገር፣ ትንቢቱ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር መስማማት ያለበት መሆኑን ነው። ደግሞም የዳንኤልን ትንቢት በትክክል መረዳት የምንችለው ከሌሎች የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ጋር አያይዘን ካየነው ብቻ ነው።

3. በዚህና በቀጣዩ ርዕስ ላይ ምን እንመለከታለን?

3 እነዚህን ነጥቦች በአእምሯችን ይዘን በዳንኤል 11:25-39 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እንመረምራለን። ከ1870 እስከ 1991 ባሉት ዓመታት የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ የነበሩት እነማን እንደሆኑ እናያለን፤ በተጨማሪም የዚህን ትንቢት የተወሰነ ክፍል በምንረዳበት መንገድ ላይ ማስተካከያ ማድረግ የሚያስፈልገን ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። በቀጣዩ ርዕስ ላይ ደግሞ ከዳንኤል 11:40 እስከ 12:1⁠ን እንመረምራለን፤ እንዲሁም ይህ የትንቢቱ ክፍል ከ1990ዎቹ ዓመታት አንስቶ እስከ አርማጌዶን ጦርነት ድረስ ስላለው ጊዜ ምን እንደሚገልጽ የጠራ ግንዛቤ እናገኛለን። እነዚህን ሁለት ርዕሶች ስታጠና “በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት” የሚለውን ሰንጠረዥ መመልከትህ ጠቃሚ ነው። በመጀመሪያ ግን በዚህ ትንቢት ላይ የተጠቀሱትን ሁለት ነገሥታት ማንነት ማወቅ ስለሚቻልበት መንገድ እንመልከት።

የሰሜኑን ንጉሥ እና የደቡቡን ንጉሥ ማንነት ማወቅ የሚቻልበት መንገድ

4. የሰሜኑን ንጉሥ እና የደቡቡን ንጉሥ ማንነት ለማወቅ ጥረት ስናደርግ የትኞቹን ሦስት ነገሮች ግምት ውስጥ ማስገባት አለብን?

4 ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” የሚሉት መጠሪያዎች መጀመሪያ ላይ የሚያመለክቱት ከእስራኤል ምድር በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችን ነበር። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? መልእክቱን ለዳንኤል ያደረሰው መልአክ ምን እንዳለ ልብ በል፤ መልአኩ “በሕዝብህ ላይ የሚደርሰውን ነገር አስረዳህ ዘንድ መጥቻለሁ” ብሎት ነበር። (ዳን. 10:14) በ33 ዓ.ም. እስከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ የአምላክ ሕዝብ የነበረው የእስራኤል ብሔር ነው። ከዚያ ወዲህ ግን ይሖዋ፣ ሕዝቡ አድርጎ የመረጠው የኢየሱስን ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንደሆነ ግልጽ አደረገ። በመሆኑም በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ትንቢት አብዛኛው ክፍል የሚገልጸው ስለ እስራኤል ብሔር ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ተከታዮች ነው። (ሥራ 2:1-4፤ ሮም 9:6-8፤ ገላ. 6:15, 16) በተጨማሪም የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ ማንነት ሲለዋወጥ ቆይቷል። ያም ቢሆን ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ነገሥታቱ ከአምላክ ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው። ሁለተኛ፣ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ያደረሱት ነገር እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንደሚጠሉ ያሳያል። ሦስተኛ፣ በሁለቱ ነገሥታት መካከል የበላይ ለመሆን የሚደረግ ሽኩቻ ነበር።

5. ከ2ኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ባለው ጊዜ ውስጥ የተነሱ የሰሜንና የደቡብ ነገሥታት ነበሩ? አብራራ።

5 በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የሆነ ጊዜ ላይ እውነተኛው የክርስቲያን ጉባኤ በሐሰተኛ ክርስቲያኖች እየተዋጠ መጣ፤ እነዚህ ሐሰተኛ ክርስቲያኖች አረማዊ ትምህርቶችን ማስተማርና በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች መሸሸግ ጀመሩ። ከዚያ ጊዜ አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ በቡድን ሆነው ይሖዋን የሚያመልኩ ሰዎች በምድር ላይ አልነበሩም። በእንክርዳድ የተመሰለው የሐሰት ክርስትና የተስፋፋ ሲሆን እውነተኛ ክርስቲያኖችን ለይቶ ማወቅ አይቻልም ነበር። (ማቴ. 13:36-43) ይህን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? ስለ ሰሜኑና ስለ ደቡቡ ንጉሥ የሚገልጸው ትንቢት ከ2ኛው መቶ ዘመን አንስቶ እስከ 19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ድረስ የተነሱትን ገዢዎች ወይም መንግሥታት ሊያመለክት እንደማይችል ይጠቁመናል። ምክንያቱም በዚህ ወቅት እነዚህ ነገሥታት ሊያጠቁት የሚችሉት የአምላክ አገልጋዮች ቡድን አልነበረም። * ሆኖም የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በድጋሚ ብቅ እንደሚሉ መጠበቅ እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?

6. የአምላክ ሕዝቦች ማንነት እንደገና የታወቀው መቼ ነበር? አብራራ።

6 ከ1870 አንስቶ የአምላክ ሕዝቦች በቡድን ሆነው መደራጀት ጀመሩ። ቻርልስ ቴዝ ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ያቋቋሙት በዚህ ዓመት ነው። ወንድም ራስል እና የቅርብ አጋሮቹ፣ መሲሐዊው መንግሥት ከመቋቋሙ በፊት ‘መንገድ እንደሚጠርግ’ በትንቢት የተነገረለት መልእክተኛ ሆነዋል። (ሚል. 3:1) የአምላክ ሕዝቦች ማንነት እንደገና ታወቀ! ታዲያ በዚህ ጊዜ በአምላክ አገልጋዮች ላይ ተጽዕኖ ያደረጉ የዓለም የፖለቲካ ኃይሎች ነበሩ? እስቲ ቀጥሎ የቀረቡትን ማስረጃዎች እንመልከት።

የደቡቡ ንጉሥ ማን ነው?

7. ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በኋላ እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የደቡቡ ንጉሥ የነበረው ማን ነው?

7 በ1870 ብሪታንያ በግዛቷ ስፋትና በወታደራዊ ኃይሏ ብርታት ተወዳዳሪ የሌላት ሆና ነበር። በወቅቱ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ሦስት ቀንዶችን ባሸነፈ አንድ ትንሽ ቀንድ ተመስሏል፤ ሦስቱ ቀንዶች ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ኔዘርላንድስ ናቸው። (ዳን. 7:7, 8) አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የደቡቡ ንጉሥ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ነው። በዚሁ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በኢኮኖሚ አንደኛውን ቦታ ይዛ የነበረ ሲሆን ከብሪታንያ ጋር የጠበቀ አጋርነት መመሥረት ጀምራ ነበር።

8. በመጨረሻዎቹ ቀናት የደቡቡ ንጉሥ የሆነው ማን ነው?

8 በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ከፍተኛ ኃይል ያለው ወታደራዊ ጥምረት መሠረቱ። በዚህ ጊዜ ብሪታንያና የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኑ። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው ይህ ንጉሥ “እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት” ሰብስቦ ነበር። (ዳን. 11:25) በመጨረሻዎቹ ቀናት የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል የደቡቡ ንጉሥ ሆኖ ቀጥሏል። * ይሁንና የሰሜኑ ንጉሥ የሆነውስ ማን ነው?

የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ አለ

9. የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ ያለው መቼ ነው? ዳንኤል 11:25 ፍጻሜውን ያገኘውስ እንዴት ነው?

9 በ1871 ማለትም ራስል እና አጋሮቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቡድን ካቋቋሙ ከአንድ ዓመት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ በድጋሚ ብቅ አለ። በዚህ ዓመት ኦቶ ቮን ቢስማርክ፣ የተለያዩ ክልሎችን አንድ በማድረግ ኃያል የሆነ የጀርመን ግዛት እንዲቋቋም አደረገ። የጀርመኑ ንጉሥ ቀዳማዊ ቪልሄልም የዚህ ግዛት የመጀመሪያ ንጉሠ ነገሥት ሆነ፤ ንጉሠ ነገሥቱ፣ ቢስማርክን የመጀመሪያው መራሄ መንግሥት አድርጎ ሾመው። * በቀጣዮቹ ጥቂት አሥርተ ዓመታት የጀርመን መንግሥት፣ በአፍሪካ እና በፓስፊክ ውቅያኖስ ላይ የሚገኙ አገሮችን በቅኝ ግዛት የተቆጣጠረ ሲሆን ብሪታንያን መቀናቀን ጀምሮ ነበር። (ዳንኤል 11:25ን አንብብ።) የጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ጠንካራ ሠራዊት የገነባ ከመሆኑም ሌላ የባሕር ኃይሉ በዓለም ላይ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን መንግሥት ይህን ሠራዊት ጠላቶቹን ለማጥቃት ተጠቅሞበታል።

10. ዳንኤል 11:25ለ, 26 ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?

10 በመቀጠል ዳንኤል የጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ ግዛትና የገነባው ወታደራዊ ኃይል ምን እንደሚደርስበት ገልጿል። ትንቢቱ፣ የሰሜኑን ንጉሥ በተመለከተ “መቋቋም አይችልም” በማለት ይናገራል። ለምን? ምክንያቱም ‘ሴራ ይጠነስሱበታል’፤ “የእሱን ምርጥ ምግብ የሚበሉም ለውድቀት ይዳርጉታል።” (ዳን. 11:25ለ, 26ሀ) በዳንኤል ዘመን “[ለንጉሡ] ከሚቀርበው ምርጥ ምግብ” ከሚበሉት መካከል “ንጉሡን ለማገልገል” የተሰማሩ ሰዎች ይገኙበታል። (ዳን. 1:5) ታዲያ ይህ ትንቢት የሚናገረው ስለ እነማን ነው? ትንቢቱ የሚናገረው የንጉሠ ነገሥቱን ጄኔራሎች እና የጦር አማካሪዎች ጨምሮ በጀርመን ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዝ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ስለነበራቸው ሰዎች ነው፤ እነዚህ ሰዎች ውሎ አድሮ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙ እንዲወድቅ አድርገዋል። * ትንቢቱ፣ ንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙ እንደሚወድቅ ከመግለጽ ባለፈ የሰሜኑ ንጉሥ ከደቡቡ ንጉሥ ጋር የሚያደርገው ጦርነት ውጤት ምን እንደሚሆን ይናገራል። ስለ ሰሜኑ ንጉሥ ሲናገር “ሠራዊቱ ተጠራርጎ ይወሰዳል፤ ብዙዎችም ተገድለው ይወድቃሉ” ይላል። (ዳን. 11:26ለ) ልክ በትንቢት በተነገረው መሠረት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ሠራዊት ‘ተጠራርጎ የተወሰደ’ ሲሆን ብዙ ሰዎች ‘ተገድለው ወድቀዋል።’ ይህ ጦርነት እስከዚያ ጊዜ ድረስ ከተካሄዱ ጦርነቶች ሁሉ በርካታ ሰው ያለቀበት ነው።

11. የሰሜኑ ንጉሥ እና የደቡቡ ንጉሥ ምን አድርገዋል?

11 ዳንኤል 11:27, 28 እስከ አንደኛው የዓለም ጦርነት ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ስለሚፈጸመው ክንውን ሲናገር የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ “በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ውሸት ይነጋገራሉ” ይላል። በተጨማሪም የሰሜኑ ንጉሥ ‘ብዙ ንብረት እንደሚሰበስብ’ ይናገራል። እነዚህ የትንቢቱ ክፍሎችም በትክክል ተፈጽመዋል። ጀርመን እና ብሪታንያ ሰላም እንደሚፈልጉ እርስ በርሳቸው ቢነጋገሩም በ1914 ጦርነቱ ሲፈነዳ ይህ ውሸት መሆኑ ተረጋግጧል። በተጨማሪም ከ1914 በፊት በነበሩት አሥርተ ዓመታት የጀርመን አገዛዝ ሀብት ያካበተ ሲሆን በዓለም ላይ በኢኮኖሚ ረገድ ሁለተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር። በኋላ ግን በዳንኤል 11:29 እና በቁጥር 30 የመጀመሪያው ሐሳብ ላይ በትንቢት እንደተገለጸው የጀርመን መንግሥት ከደቡቡ ንጉሥ ጋር ባደረገው ውጊያ ተሸንፏል።

ነገሥታቱ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራሉ

12. በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑም ሆነ የደቡቡ ንጉሥ ምን አድርገዋል?

12 ከ1914 ወዲህ ሁለቱ ነገሥታት እርስ በርስ የሚያደርጉትን ሽኩቻም ሆነ በአምላክ ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝሩትን ጥቃት አፋፍመው ቀጥለዋል። ለምሳሌ ያህል በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን መንግሥትም ሆነ የብሪታንያ መንግሥት፣ በጦርነቱ ሰው ለመግደል ፈቃደኛ ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን አሳድደዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም ቢሆን የስብከቱን ሥራ የሚመሩት ወንድሞች እስር ቤት እንዲጣሉ አድርጓል። ይህም በራእይ 11:7-10 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ ነው።

13. በ1930ዎቹ ዓመታትና በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ ምን አድርጓል?

13 ከዚያም በ1930ዎቹ ዓመታት፣ በተለይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ያለምንም ርኅራኄ አሳድዷል። የናዚ ፓርቲ ጀርመንን ከተቆጣጠረ በኋላ ሂትለርና ተከታዮቹ በአምላክ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል። ተቃዋሚዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ልከዋል። ዳንኤል ይህ እንደሚሆን አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። የሰሜኑ ንጉሥ፣ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን በሕዝብ ፊት ለማወደስ በሚያከናውኑት ሥራ ላይ ከፍተኛ ገደብ በመጣሉ ‘መቅደሱን አርክሷል’ እንዲሁም ‘የዘወትሩን መሥዋዕት አስቀርቷል።’ (ዳን. 11:30ለ, 31ሀ) እንዲያውም የጀርመን መሪ የነበረው ሂትለር የአምላክ ሕዝቦችን ከአገሪቱ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ዝቶ ነበር።

አዲስ የሰሜን ንጉሥ ተነሳ

14. ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ሆኖ የተነሳው ማን ነው? አብራራ።

14 ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሶቪየት ኅብረት የኮሚኒስት መንግሥት በጀርመን አገዛዝ ሥር የነበረውን ሰፊ ግዛት በመቆጣጠር የሰሜኑ ንጉሥ ሆነ። የሶቪየት ኅብረት መንግሥት የአምባገነኑን የናዚ አገዛዝ አካሄድ ተከትሏል፤ ይኸውም ከመንግሥት ይልቅ ለእውነተኛው አምላክ ቅድሚያ የሚሰጡ ሰዎችን አሳድዷል።

15. ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የሰሜኑ ንጉሥ ምን አድርጓል?

15 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ ብዙም ሳይቆይ፣ ሶቪየት ኅብረትንና አጋሮቹን የሚያመለክተው አዲሱ የሰሜን ንጉሥ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ። በራእይ 12:15-17 ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይህ ንጉሥ በስብከቱ ሥራችን ላይ እገዳ የጣለ ሲሆን በሺዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮች በግዞት እንዲወሰዱ አድርጓል። በመጨረሻዎቹ ቀናት በሙሉ የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክ ሕዝቦችን ሥራ ለማስቆም የስደት “ወንዝ” ሲለቅ ቆይቷል፤ ሆኖም ጥረቱ አልተሳካለትም። *

16. በዳንኤል 11:37-39 ላይ በትንቢት በተገለጸው መሠረት የሶቪየት ኅብረት መንግሥት ምን አድርጓል?

16 ዳንኤል 11:37-39ን አንብብ። ልክ በዚህ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው የሰሜኑ ንጉሥ “ለአባቶቹ አምላክ” ምንም ቦታ አልሰጠም። ይህን ያሳየው እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ረጅም ዘመን ያስቆጠሩ ሃይማኖታዊ ተቋማት የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ ለማዳከም ጥረት አድርጓል፤ ዓላማውም ሃይማኖትን ማጥፋት ነበር። የሶቪየት መንግሥት ይህን ግቡን ለማሳካት ሲል ገና በ1918 ትምህርት ቤቶችንና ሃይማኖትን የሚመለከት ትእዛዝ አስተላልፎ ነበር፤ ይህም ‘አምላክ የለም’ የሚለው ትምህርት ከጊዜ በኋላ በትምህርት ቤቶች ውስጥ እንዲሰጥ መንገድ ከፍቷል። ታዲያ ይህ የሰሜን ንጉሥ ‘ለምሽጎች አምላክ ክብር የሰጠው’ እንዴት ነው? የሶቪየት ኅብረት መንግሥት፣ ሠራዊቱን ለመገንባትና ግዛቱን ለማጠናከር የሚያስችሉ በሺዎች የሚቆጠሩ የኑክሌር መሣሪያዎችን ለማምረት ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል። የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ የደቡቡ ንጉሥ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚጨርሱ የጦር መሣሪያዎችን ቀስ በቀስ አከማችተዋል።

ያልተለመደ ትብብር

17. ‘ጥፋት የሚያመጣው ርኩስ ነገር’ ምንድን ነው?

17 የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ የተባበሩበት አንድ ቁልፍ ጉዳይ አለ፤ ይህም ‘ጥፋት የሚያመጣውን ርኩስ ነገር’ ማቋቋም ነው። (ዳን. 11:31) “ርኩስ ነገር” የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ነው።

18. የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ርኩስ ነገር” ተብሎ የተገለጸው ለምንድን ነው?

18 የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት “ርኩስ ነገር” ተብሎ የተገለጸው የአምላክ መንግሥት ብቻ ሊያከናውን የሚችለውን ነገር እንደሚያደርግ ይኸውም ዓለም አቀፍ ሰላም እንደሚያመጣ ስለሚናገር ነው። ይህ ርኩስ ነገር ‘ጥፋት እንደሚያመጣ’ ትንቢቱ አክሎ ተናግሯል፤ እንዲህ የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ሁሉንም የሐሰት ሃይማኖቶች በማጥፋት ረገድ ቁልፍ ሚና ስለሚጫወት ነው።—“በፍጻሜው ዘመን የተነሱ ተቀናቃኝ ነገሥታት” የሚለውን ሰንጠረዥ ተመልከት።

ይህን ታሪክ ማወቃችን ምን ይጠቅመናል?

19-20. (ሀ) ይህን ታሪክ ማወቃችን ምን ይጠቅመናል? (ለ) በቀጣዩ ርዕስ ላይ የየትኛውን ጥያቄ መልስ እንመረምራለን?

19 ይህን ታሪክ ማወቃችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ዳንኤል የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ከ1870ዎቹ አንስቶ እስከ 1990ዎቹ መጀመሪያ ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ ፍጻሜውን እንዳገኘ ያረጋግጥልናል። በመሆኑም የቀረው የትንቢቱ ክፍልም እንደሚፈጸም መተማመን እንችላለን።

20 ሶቪየት ኅብረት በ1991 ፈርሷል። ታዲያ በዛሬው ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥ ማን ነው? ቀጣዩ ርዕስ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።

መዝሙር 128 እስከ መጨረሻው መጽናት

^ አን.5 ዳንኤል ‘የደቡቡን ንጉሥ’ እና ‘የሰሜኑን ንጉሥ’ አስመልክቶ የተናገረው ትንቢት ፍጻሜውን እያገኘ እንደሆነ የሚጠቁሙ ማስረጃዎችን እያየን ነው። ትንቢቱ እየተፈጸመ መሆኑን እርግጠኛ እንድንሆን የሚያደርገን ምንድን ነው? እንዲሁም የዚህን ትንቢት ዝርዝር ጉዳዮች መረዳት የሚያስፈልገን ለምንድን ነው?

^ አን.5 እዚህ ላይ ከተጠቀሰው ምክንያት አንጻር የሮም ንጉሠ ነገሥት ኦሬሊየን (270-275 ዓ.ም.) ‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እንደሆነ፣ ንግሥት ዘኖቢያ (267-272 ዓ.ም.) ደግሞ “የደቡቡ ንጉሥ” እንደሆነች መናገራችን ትክክል አይመስልም። ይህ ሐሳብ የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል! በተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 13 እና 14 ላይ በወጣው ትምህርት ላይ የተደረገ ማስተካከያ ነው።

^ አን.9 በ1890 ዳግማዊ ቄሳር ቪልሄልም፣ ቢስማርክን ሥልጣኑን እንዲለቅ አስገድዶታል።

^ አን.10 እነዚህ ሰዎች፣ የንጉሠ ነገሥታዊ አገዛዙን ውድቀት ለማፋጠን የተለያዩ ነገሮችን አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ለንጉሡ የሚሰጡትን ድጋፍ አቁመዋል፤ ስለ ጦርነቱ በሚስጥር ሊያዙ የሚገቡ መረጃዎችን አውጥተዋል፤ እንዲሁም ንጉሡ ሥልጣኑን እንዲለቅ ጫና አሳድረዋል።

^ አን.15 በዳንኤል 11:34 ላይ እንደተገለጸው በሰሜኑ ንጉሥ ሥር ያሉ ክርስቲያኖች ከስደት የተወሰነ እፎይታ ያገኙበት ወቅት ነበር። ለምሳሌ፣ ሶቪየት ኅብረት በ1991 ሲፈርስ ስደቱ ጋብ ብሎላቸዋል።