በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገርነት—ምን ጥቅሞች አሉት?

ገርነት—ምን ጥቅሞች አሉት?

“በተፈጥሮዬ ዓይናፋር ነኝ፤ በራስ መተማመን ይጎድለኛል” በማለት ሣራ * የተባለች እህት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “ስለዚህ ኃይለኛ ከሆኑ ወይም ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ከሚሉ ሰዎች ጋር መሆን ይጨንቀኛል። ገር እና ትሑት ከሆኑ ሰዎች ጋር ስሆን ግን ደስ ይለኛል። እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ላለው ሰው ስሜቴን አውጥቼ መናገርና ስላጋጠሙኝ ችግሮች ማውራት አይከብደኝም። በጣም የምቀርባቸው ወዳጆቼ እንዲህ ዓይነት ባሕርይ ያላቸው ናቸው።”

ሣራ የተናገረችው ሐሳብ እንደሚጠቁመው ገርነት በሌሎች ዘንድ እንድንወደድ ያደርገናል። ገርነት ይሖዋም የሚወደው ባሕርይ ነው። የአምላክ ቃል “ገርነትን . . . ልበሱ” በማለት ያሳስበናል። (ቆላ. 3:12) ገርነት ምንድን ነው? ኢየሱስ ገርነትን ያሳየው እንዴት ነው? ይህ ባሕርይ ይበልጥ ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርገንስ እንዴት ነው?

ገርነት ምንድን ነው?

ገር የሚባለው ረጋ ያለና ሰላማዊ የሆነ ሰው ነው። ገር የሆነ ሰው ሌሎችን የሚይዘው ደግነት በሚንጸባረቅበትና ለስለስ ባለ መንገድ ነው፤ የሚያበሳጩ ሁኔታዎች በሚያጋጥሙት ጊዜም በተረጋጋ መንፈስ ነገሮችን ይይዛል።

ገርነት የድክመት ምልክት አይደለም። “ገርነት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል፣ የተገራ ፈረስን ለመግለጽ ይሠራበት ነበር። ፈረሱ ቢገራም ጥንካሬውን አያጣም፤ ሆኖም በትዕግሥት የተሰጠው ሥልጠና ጉልበቱን እንዲቆጣጠር አድርጎታል። እኛም በተመሳሳይ ገርነትን ስናዳብር ያልተገራ ባሕርያችንን መቆጣጠርና ከሌሎች ጋር ሰላማዊ ግንኙነት መፍጠር እንችላለን።

‘በተፈጥሮዬ ገር ሰው አይደለሁም’ ብለን እናስብ ይሆናል። ደግሞም የምንኖረው ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ የሚሉና ትዕግሥት የሌላቸው ሰዎች በበዙበት ዓለም ውስጥ ነው፤ በመሆኑም የገርነት መንፈስ ማሳየት ተፈታታኝ ሊሆንብን ይችላል። (ሮም 7:19) ገርነትን ማዳበር ጥረት እንደሚጠይቅ ጥያቄ የለውም፤ ይሁን እንጂ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ይህን ባሕርይ ለማዳበር ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል። (ገላ. 5:22, 23) ታዲያ ገርነትን ለማዳበር ጥረት ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

ገርነት ተወዳጅ ባሕርይ ነው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሣራ እንደገለጸችው፣ ገር ከሆነ ሰው ጋር መሆን ያስደስተናል። ገርና ደግ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቷል። (2 ቆሮ. 10:1) በደንብ የማያውቁት ትናንሽ ልጆችም እንኳ ከእሱ ጋር መሆን ይፈልጉ ነበር።—ማር. 10:13-16

ገርነት እኛንም ሆነ የምንቀርባቸውን ሰዎች ከጉዳት ይጠብቀናል። ገር ከሆንን ቶሎ አንበሳጭም ወይም ተቆጥተን እርምጃ አንወስድም። (ምሳሌ 16:32) ይህም ሌሎችን በተለይም የምንወደውን ሰው የሚጎዳ ነገር አድርገን በኋላ ላይ በጥፋተኝነት ስሜት ከመሠቃየት ይጠብቀናል። ገርነት የምንቀርባቸውን ሰዎችም ከጉዳት ይጠብቃል፤ ምክንያቱም ቁጣችንን ባለመቆጣጠራችን የተነሳ ጉዳት አይደርስባቸውም።

ለገርነት ፍጹም ምሳሌ የሚሆነው ማን ነው?

ኢየሱስ ከባድ ኃላፊነቶች የነበሩትና በሥራ የተጠመደ ቢሆንም ሁሉንም ሰው በገርነት ይይዝ ነበር። በዘመኑ ብዙ ሰዎች ሕይወታቸው አስቸጋሪ ከመሆኑም ሌላ ሸክማቸው ከብዷቸው ነበር፤ በመሆኑም እረፍት ያስፈልጋቸው ነበር። ኢየሱስ “ወደ እኔ ኑ፤ . . . እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” ሲላቸው ምንኛ ተጽናንተው ይሆን!—ማቴ. 11:28, 29

እንደ ኢየሱስ ገርነትን ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን ቃል በማጥናት፣ ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት እንደያዘና አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙት ምን እንዳደረገ ለማወቅ ጥረት እናድርግ። እንዲህ ካደረግን ገርነታችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል እንጥራለን። (1 ጴጥ. 2:21) ኢየሱስን ገር እንዲሆን የረዱትን ሦስት ነገሮች እስቲ እንመልከት።

ኢየሱስ በልቡ ትሑት ነበር። ኢየሱስ “እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” ብሏል። (ማቴ. 11:29) ገርነት እና ትሕትና ጥብቅ ትስስር ያላቸው ባሕርያት ስለሆኑ መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን ሁለት ባሕርያት አንድ ላይ ይጠቅሳቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3) ለመሆኑ ሁለቱን ባሕርያት የሚያስተሳስራቸው ነገር ምንድን ነው?

ትሑት የሆነ ሰው አትንኩኝ ባይ አይሆንም። ኢየሱስ “ሆዳምና ለወይን ጠጅ ያደረ” ብለው በሐሰት ለነቀፉት ሰዎች ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? መልስ የሰጠው በአኗኗሩ ነው፤ በተጨማሪም “ጥበብ ጻድቅ መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” በማለት በገርነት ተናግሯል።—ማቴ. 11:19

አንድ ሰው ዘርህን፣ ፆታህን ወይም ባሕልህን በተመለከተ ጎጂ ነገር ቢናገር ገርነት የተንጸባረቀበት ምላሽ ለመስጠት ጥረት ማድረግህ ጠቃሚ ነው። በደቡብ አፍሪካ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ፒተር እንዲህ ብሏል፦ “አንድ ሰው የተናገረው ነገር ሲያበሳጨኝ ‘ኢየሱስ ቢሆን ኖሮ ምን ምላሽ ይሰጥ ነበር?’ ብዬ አስባለሁ። ሆደ ባሻ ላለመሆን ጥረት አደርጋለሁ።”

ኢየሱስ የሰው ልጆች ፍጹማን እንዳልሆኑ ይረዳ ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ትክክለኛውን ነገር የማድረግ ፍላጎት ቢኖራቸውም ፍጹማን ስላልሆኑ ይህን ማድረግ የሚከብዳቸው ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ እሱ እንደጠየቃቸው ከጎኑ መሆኑ ሳይችሉ ቀርተዋል። ሆኖም ኢየሱስ “መንፈስ ዝግጁ” ቢሆንም ‘ሥጋ ደካማ’ እንደሆነ ተረድቶ ነበር። (ማቴ. 26:40, 41) ኢየሱስ ይህን መረዳቱ በሐዋርያቱ እንዳይበሳጭ አድርጎታል።

ማንዲ ከሰዎች ብዙ የምትጠብቅ ሴት ነበረች፤ አሁን ግን ኢየሱስ በገርነት ረገድ የተወውን ምሳሌ ለመከተል ከፍተኛ ጥረት ታደርጋለች። ይህች እህት “ፍጹም ስላልሆንን ሁሉም ሰው የራሱ ድክመት እንዳለው ለማስታወስ እንዲሁም ልክ እንደ ይሖዋ የሌሎችን መልካም ጎን ለማየት እጥራለሁ” ብላለች። አንተም ኢየሱስ ለሰዎች ድክመት ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበርህ ሌሎችን በገርነት እንድትይዝ ሊረዳህ ይችላል።

ኢየሱስ በአምላክ በመተማመን ነገሮችን ለእሱ ትቷል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ግፍ ደርሶበታል። ያለስሙ ስም ተሰጥቶታል፣ ተንቋል እንዲሁም በሰዎች እጅ ሥቃይ ደርሶበታል። ያም ቢሆን “በጽድቅ ለሚፈርደው ራሱን በአደራ [ስለሰጠ]” ምንጊዜም የገርነት መንፈስ ማሳየት ችሏል። (1 ጴጥ. 2:23) ኢየሱስ በሰማይ ያለው አባቱ እንደሚያስብለትና ግፍ ባደረሱበት ላይ በትክክለኛው ጊዜ ተገቢውን እርምጃ እንደሚወስድ ያውቅ ነበር።

ግፍ ሲደርስብን ተቆጥተን የራሳችንን እርምጃ ለመውሰድ የምንጥር ከሆነ ሁኔታውን ልናባብሰው እንችላለን። ቅዱሳን መጻሕፍት “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” የሚሉት ለዚህ ነው። (ያዕ. 1:20) ለመቆጣት በቂ ምክንያት ቢኖረንም እንኳ አለፍጽምና የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ ሊያደርገን ይችላል።

በጀርመን የምትኖር ካቲ የተባለች እህት ‘ለራሴ መቆም ያለብኝ እኔው ራሴ ነኝ’ ብላ ታስብ ነበር። በይሖዋ መታመንን ስትማር ግን አመለካከቷ ተቀየረ። እንዲህ ብላለች፦ “አሁን በእያንዳንዱ ነገር ለራሴ ጥብቅና መቆም እንዳለብኝ አይሰማኝም። ይሖዋ ሁሉንም ነገር እንደሚያስተካክለው ስለምተማመን ገርነትን ማሳየት ቀላል ሆኖልኛል።” አንተም ግፍ ደርሶብህ የሚያውቅ ከሆነ እንደ ኢየሱስ በአምላክ መታመንህ ምንጊዜም የገርነት መንፈስ እንድታሳይ ይረዳሃል።

“ገሮች ደስተኞች ናቸው”

አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ገርነት የሚረዳን እንዴት ነው?

ኢየሱስ ገርነት ለደስታችን ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ጠቁሟል። “ገሮች ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:5) ገርነት ከሚከተሉት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ እንዴት እንደሚጠቅመን እስቲ እንመልከት።

ገርነት በትዳር ውስጥ የሚፈጠረውን ውጥረት ያረግባል። በአውስትራሊያ የሚኖር ሮበርት የተባለ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ባለቤቴን የሚጎዱ ብዙ ነገሮች ሳላስበው የተናገርኩባቸው ጊዜያት አሉ። የሚያሳዝነው ተቆጥተን የተናገርናቸውን ጎጂ ነገሮች መመለስ አንችልም። ባለቤቴን ምን ያህል እንደጎዳኋት ስገነዘብ በኋላ ላይ በጣም እጸጸታለሁ።”

“ሁላችንም [በንግግራችን] ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን”፤ በመሆኑም በግዴለሽነት የምንናገራቸው ቃላት በትዳራችን ውስጥ ውጥረት እንዲፈጠር ሊያደርጉ ይችላሉ። (ያዕ. 3:2) እንዲህ ባሉት ጊዜያት፣ ገርነት እንድንረጋጋና አንደበታችንን እንድንቆጣጠር ይረዳናል።—ምሳሌ 17:27

ሮበርት ነገሮችን በእርጋታ ለመያዝና ራሱን ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ጀመረ። እንዲህ ብሏል፦ “በአሁኑ ወቅት አለመግባባት ሲፈጠር በጥሞና ለማዳመጥ፣ በገርነት መልስ ለመስጠት እንዲሁም ላለመበሳጨት የታሰበበት ጥረት አደርጋለሁ። አሁን ከባለቤቴ ጋር ያለኝ ግንኙነት በጣም ተሻሽሏል።”

ገርነት ከሌሎች ጋር ተስማምተን ለመኖር ይረዳናል። ቶሎ ቅር የሚሰኙ ሰዎች ብዙ ጓደኞች አይኖሯቸውም። ገርነት ግን ‘አንድ ላይ የሚያስተሳስረውን ሰላምን ለመጠበቅ’ ይረዳናል። (ኤፌ. 4:2, 3) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ካቲ “ገርነትን ማዳበሬ ከሁሉም ሰው ጋር ሌላው ቀርቶ አስቸጋሪ ከሚባሉ ሰዎች ጋር እንኳ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ እንድችል ረድቶኛል” ብላለች።

ገርነት ውስጣዊ ሰላም እንዲኖረን ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ከገርነትና ከሰላም ጋር አያይዞ ይጠቅሰዋል። (ያዕ. 3:13, 17) ገር የሆነ ሰው “የሰከነ ልብ” አለው። (ምሳሌ 14:30) ገርነትን ለማዳበር ብዙ ጥረት ያደረገ ማርቲን የተባለ ወንድም “አሁን እንደ ቀድሞው ግትር እና ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ የምል ሰው አይደለሁም፤ በመሆኑም ውስጣዊ ሰላምና ደስታ አግኝቻለሁ” ብሏል።

የገርነት መንፈስን ማዳበር ትግል ሊጠይቅብን እንደሚችል አይካድም። አንድ ወንድም “እውነቱን ለመናገር፣ አሁንም እንኳ በንዴት የምበግንባቸው ጊዜያት አሉ” በማለት ተናግሯል። ያም ቢሆን ገርነትን እንድናዳብር የሚያበረታታን ይሖዋ፣ በዚህ ረገድ በምናደርገው ትግል ይረዳናል። (ኢሳ. 41:10፤ 1 ጢሞ. 6:11) ይሖዋ ‘ሥልጠናችን እንዲጠናቀቅ ያደርጋል’ እንዲሁም ‘ያጠነክረናል።’ (1 ጴጥ. 5:10) ውሎ አድሮ እኛም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘የክርስቶስን ገርነትና ደግነት’ ማንጸባረቅ እንችላለን።—2 ቆሮ. 10:1

^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።