በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 18

በኢየሱስ ምክንያት ትሰናከላለህ?

በኢየሱስ ምክንያት ትሰናከላለህ?

“በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።”—ማቴ. 11:6

መዝሙር 54 “መንገዱ ይህ ነው”

ማስተዋወቂያ *

1. አንዳንዶች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለሌሎች መናገር ሲጀምሩ ምን የሚያስገርም ነገር አጋጥሟቸዋል?

እውነትን እንዳገኘህ የተገነዘብክበትን ጊዜ ታስታውሳለህ? የተማርካቸው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ግልጽና አሳማኝ እንደሆኑ ተሰምቶህ ነበር። ይህን እውነት ሁሉም ሰው እንደሚቀበለው አስበህ ነበር። የነገርካቸው ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ቢቀበሉ በአሁኑ ጊዜ ሕይወታቸው ትርጉም ያለው እንደሚሆን፣ ለወደፊቱም አስደናቂ ተስፋ እንደሚኖራቸው እርግጠኛ ሆነህ ነበር። (መዝ. 119:105) በመሆኑም ያገኘኸውን እውነት ለጓደኞችህና ለቤተሰቦችህ ሁሉ በጉጉት ነገርካቸው። ሆኖም ለመልእክቱ ምን ምላሽ ሰጡ? ብዙዎቹ መልእክቱን ለመቀበል ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ይህን ስታይ በጣም ተገርመህ መሆን አለበት።

2-3. በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አብዛኞቹ ሰዎች ለእሱ ምን አመለካከት ነበራቸው?

2 ማናችንም ብንሆን ሰዎች የምንሰብከውን መልእክት ለመቀበል ፈቃደኛ ባይሆኑ ልንገረም አይገባም። ኢየሱስ፣ ከአምላክ የተላከ መሆኑን የሚያሳዩ በርካታ ተአምራትን ቢፈጽምም እንኳ በዘመኑ የነበሩ አብዛኞቹ ሰዎች አልተቀበሉትም። ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል፤ ይህ ተቃዋሚዎቹ እንኳ ሊክዱ የማይችሉት ተአምር ነው። ያም ቢሆን የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን አልተቀበሉም። እንዲያውም ኢየሱስንም ሆነ አልዓዛርን ለመግደል ተነሱ!—ዮሐ. 11:47, 48, 53፤ 12:9-11

3 ኢየሱስ አብዛኞቹ ሰዎች የእሱን መሲሕነት እንደማይቀበሉ ያውቅ ነበር። (ዮሐ. 5:39-44) ለመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት “በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው” ብሏቸዋል። (ማቴ. 11:2, 3, 6) ይሁንና ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ያልተቀበሉት ለምንድን ነው?

4. በዚህ ርዕስ ላይ ምን እንመረምራለን?

4 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ በርካታ ሰዎች በኢየሱስ እንዳያምኑ ያደረጓቸውን አንዳንድ ምክንያቶች በዚህና በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመረምራለን። በተጨማሪም በዘመናችን ያሉ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ ተከታዮች የሚሰናከሉት ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ፣ እኛ ራሳችን በኢየሱስ እንዳንሰናከል ጠንካራ እምነት ለማዳበር የሚረዱንን ነጥቦች እንመረምራለን።

(1) የኢየሱስ የኋላ ታሪክ

ብዙዎች በኢየሱስ የኋላ ታሪክ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 5ን ተመልከት) *

5. አንዳንዶች ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ ሊሆን እንደማይችል የተሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል?

5 ብዙዎች በኢየሱስ እንዲሰናከሉ ያደረጋቸው የኋላ ታሪኩ ነው። ኢየሱስ ግሩም አስተማሪ እንደሆነና ብዙ ተአምራትን እንደሠራ ተቀብለው ነበር። ሆኖም በእነሱ ዓይን ኢየሱስ የአንድ ድሃ አናጺ ልጅ ብቻ ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ኢየሱስ ያደገው በናዝሬት ነው፤ ናዝሬት ያን ያህል ትኩረት የሚሰጣት ከተማ አልነበረችም። ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር የሆነው ናትናኤል እንኳ “ደግሞ ከናዝሬት ጥሩ ነገር ሊገኝ ይችላል?” ብሏል። (ዮሐ. 1:46) ናትናኤል፣ ኢየሱስ በወቅቱ የሚኖርባትን ከተማ አይወዳት ይሆናል። አሊያም ደግሞ በሚክያስ 5:2 ላይ የሚገኘውን ትንቢት አስታውሶ ሊሆን ይችላል፤ ትንቢቱ እንደሚገልጸው መሲሑ የሚወለደው በናዝሬት ሳይሆን በቤተልሔም ነው።

6. በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ሰዎች እሱ መሲሕ መሆኑን ሊያውቁ ይገባ ነበር የምንለው ለምንድን ነው?

6 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ነቢዩ ኢሳይያስ፣ የኢየሱስ ጠላቶች ‘ትኩረት ሰጥተው የመሲሑን ትውልድ በዝርዝር ለማወቅ እንደማይሞክሩ’ ትንቢት ተናግሮ ነበር። (ኢሳ. 53:8) በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ መሲሑ በዝርዝር የሚናገሩ በርካታ ትንቢቶች ይገኛሉ። በኢየሱስ ዘመን የነበሩት ሰዎች ጊዜ ወስደው መረጃዎቹን በሙሉ ቢመረምሩ ኖሮ ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም እንደሆነና የንጉሥ ዳዊት ዘር መሆኑን ይገነዘቡ ነበር። (ሉቃስ 2:4-7) በእርግጥም በሚክያስ 5:2 ላይ ከሚገኘው ትንቢት ጋር በሚስማማ መልኩ ኢየሱስ የተወለደው በቤተልሔም ነው። ታዲያ ችግሩ ምን ነበር? ሰዎቹ ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቸኮላቸው ነው። የተሟላ መረጃ አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት ተሰናከሉ።

7. በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች የይሖዋን ሕዝቦች የማይቀበሉት ለምንድን ነው?

7 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። አብዛኞቹ የይሖዋ ሕዝቦች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያን ያህል ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሰዎች አይደሉም፤ እንዲያውም ብዙዎች “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” እንደሆኑ አድርገው ይመለከቷቸዋል። (ሥራ 4:13) አንዳንዶች፣ የአምላክ ሕዝቦች ስመ ጥር ከሆኑ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ስላልተመረቁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች እምነት “የአሜሪካ ሃይማኖት” እንደሆነ ይናገራሉ፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ከይሖዋ ምሥክሮች መካከል በአሜሪካ የሚኖሩት 14 በመቶ ገደማ የሚሆኑት ብቻ ናቸው። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ እንደማያምኑ ሲወራ ሰምተዋል። የይሖዋ ሕዝቦች “ኮሚኒስት፣” “የአሜሪካ ሰላይ” ወይም “ጽንፈኛ” ተብለው የተወነጀሉባቸው ጊዜያትም አሉ። እነዚህን ወሬዎች የሰሙት ሰዎች እውነታውን ስለማያውቁ ወይም ስለማይቀበሉ ይሰናከላሉ።

8. በሐዋርያት ሥራ 17:11 መሠረት በዛሬው ጊዜ የአምላክ አገልጋዮች እነማን እንደሆኑ ለማወቅ ምን ማድረግ ያስፈልጋል?

8 አንድ ሰው እንዳይሰናከል የሚረዳው ምንድን ነው? መረጃዎቹን መመርመር አስፈላጊ ነው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ይህን ለማድረግ ጥረት አድርጎ ነበር። “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ” መርምሯል። ወንጌሉን የሚያነቡ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሰሟቸው ነገሮች “እርግጠኛ መሆናቸውን በሚገባ” እንዲያውቁ ፈልጎ ነበር። (ሉቃስ 1:1-4) በጥንቷ ቤርያ የነበሩት አይሁዳውያንም እንደ ሉቃስ አድርገዋል። ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች መጀመሪያ በሰሙበት ወቅት፣ የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መርምረዋል። (የሐዋርያት ሥራ 17:11ን አንብብ።) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችም በተመሳሳይ መረጃዎቹን መመርመር ያስፈልጋቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ያስተማሯቸውን ነገር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው ነገር ጋር ማወዳደር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ያስመዘገቡትን ታሪክ ማጥናት ያስፈልጋቸዋል። መረጃዎቹን በጥንቃቄ ከመረመሩ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ወይም አሉባልታ እንዲያሳውራቸው አይፈቅዱም።

(2) ኢየሱስ ለታይታ ብሎ ምልክት አላሳየም

ብዙዎች ኢየሱስ ለታይታ ብሎ ምልክት ባለማሳየቱ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 9-10ን ተመልከት) *

9. ኢየሱስ ከሰማይ ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆኑ ምን አስከትሏል?

9 በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ግሩም የሆኑ ትምህርቶቹን መስማታቸው ብቻ አላረካቸውም። ተጨማሪ ነገር ፈልገው ነበር። መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ “ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።” (ማቴ. 16:1) ምናልባትም ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ዳንኤል 7:13, 14⁠ን በተሳሳተ መንገድ ስለተረዱት ሊሆን ይችላል። ሆኖም በይሖዋ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ይህ ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ ገና አልደረሰም ነበር። ኢየሱስ የሚያስተምረው ነገር እሱ መሲሕ መሆኑን የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ሊሆናቸው ይገባ ነበር። ኢየሱስ የጠየቁትን ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆኑ እንዲሰናከሉ አደረጋቸው።—ማቴ. 16:4

10. ኢየሱስ፣ ኢሳይያስ ስለ መሲሑ የጻፈውን ትንቢት የፈጸመው እንዴት ነው?

10 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ መሲሑ ሲጽፍ “አይጮኽም ወይም ድምፁን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁንም በጎዳና ላይ አያሰማም” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 42:1, 2) ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነው ወደ ራሱ ትኩረት በሚስብ መንገድ አልነበረም። ኢየሱስ ግዙፍ የሆኑ ቤተ መቅደሶችን አልገነባም፤ ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ልብስ አልለበሰም፤ ወይም ሰዎች በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች እንዲጠሩት አልጠየቀም። ሞት ሊፈረድበት በነበረ ጊዜ እንኳ ኢየሱስ ንጉሥ ሄሮድስን የሚያስደምም ተአምር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ሉቃስ 23:8-11) እርግጥ ኢየሱስ ተአምራት የፈጸመባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው ምሥራቹን በመስበኩ ላይ ነበር። ደቀ መዛሙርቱን “የመጣሁት ለዚሁ ነው” ብሏቸዋል።—ማር. 1:38

11. በዛሬው ጊዜ ያሉ አንዳንዶች ምን የተሳሳተ አመለካከት አላቸው?

11 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በዛሬው ጊዜም ብዙዎች ውድ የሆኑ ቅርሶችን በያዙ አብያተ ክርስቲያናት፣ በረጃጅም የማዕረግ ስሞች በሚጠሩ ቀሳውስት እንዲሁም አረማዊ አመጣጥና ትርጉም እንዳላቸው በተረሱ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይማረካሉ። ይሁንና በእነዚህ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ላይ የሚታደሙት ሰዎች ስለ አምላክና ስለ ዓላማዎቹ የሚማሩት ነገር አለ? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ የሚገኙ ሰዎች ግን ይሖዋ ከእኛ ምን እንደሚፈልግ እንዲሁም ከፈቃዱ ጋር በሚስማማ መንገድ መመላለስ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይማራሉ። የስብሰባ አዳራሾቻችን ንጹሕና ምቹ ቢሆኑም የተንቆጠቆጡ አይደሉም። አመራር የሚሰጡት ወንድሞችም ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ልብስ አይለብሱም፤ ሃይማኖታዊ በሆኑ የማዕረግ ስሞችም አይጠሩም። ትምህርታችንና እምነታችን የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነው። ያም ቢሆን ብዙዎች አምልኳችን የሚያስደምም ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሌለው መሆኑ ያሰናክላቸዋል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ትምህርታችን እነሱ መስማት ከሚፈልጉት ነገር ጋር አይስማማም።

12. ዕብራውያን 11:1, 6 እንደሚያሳየው እምነታችን በምን ላይ መመሥረት ይኖርበታል?

12 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የሚገኙትን ክርስቲያኖች “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው። ቃሉን መስማት የሚቻለው ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር ሰው ሲኖር ነው” ብሏቸው ነበር። (ሮም 10:17) ስለሆነም እምነታችንን የምንገነባው ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት እንጂ ለዓይን በሚስቡ ሆኖም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በመካፈል አይደለም። በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት ማዳበር ይኖርብናል፤ ምክንያቱም “ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም።” (ዕብራውያን 11:1, 6ን አንብብ።) እንግዲያው እውነትን ማግኘታችንን ለማረጋገጥ ከሰማይ አስደናቂ ምልክት ማየት አያስፈልገንም። እውነትን እንዳገኘን እርግጠኞች ለመሆን እንዲሁም ማንኛውንም ጥርጣሬ ለማስወገድ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እምነት የሚያጠናክር ትምህርት በጥንቃቄ መመርመራችን ብቻ በቂ ነው።

(3) ኢየሱስ ብዙ የአይሁዳውያን ልማዶችን አልተከተለም

ብዙዎች ኢየሱስ አንዳንድ የአይሁዳውያን ልማዶችን ባለመከተሉ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 13ን ተመልከት) *

13. ብዙዎች ኢየሱስን እንዳይቀበሉት ያደረጋቸው ምንድን ነው?

13 የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት አለመጾማቸው የመጥምቁ ዮሐንስን ደቀ መዛሙርት አስገርሟቸው ነበር። ኢየሱስም እሱ በሕይወት እስካለ ድረስ ደቀ መዛሙርቱ የሚጾሙበት ምክንያት እንደሌለ ገልጿል። (ማቴ. 9:14-17) ያም ቢሆን ፈሪሳውያንና ሌሎች ተቃዋሚዎቹ ኢየሱስ የእነሱን ልማዶችና ወጎች ባለመከተሉ አውግዘውታል። የታመሙ ሰዎችን በሰንበት በመፈወሱ በጣም ተቆጥተው ነበር። (ማር. 3:1-6፤ ዮሐ. 9:16) እነዚህ ሰዎች በአንድ በኩል ሰንበትን እንደሚያከብሩ በኩራት ይናገራሉ፤ በሌላ በኩል ግን ያለአንዳች እፍረት በቤተ መቅደሱ ውስጥ የንግድ እንቅስቃሴ ያካሂዳሉ። ይህን በማድረጋቸው ኢየሱስ ስላወገዛቸው በጣም ተቆጥተው ነበር። (ማቴ. 21:12, 13, 15) ኢየሱስ በናዝሬት በሚገኘው ምኩራብ የሰበከላቸው ሰዎችም፣ ኢየሱስ በእስራኤል ታሪክ ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን በመጥቀስ ራስ ወዳድነታቸውንና እምነት የለሽነታቸውን ስላጋለጠባቸው በጣም ተበሳጭተው ነበር። (ሉቃስ 4:16, 25-30) በርካታ አይሁዳውያን ኢየሱስ የጠበቁትን ነገር ባለማድረጉ ተሰናክለውበታል።—ማቴ. 11:16-19

14. ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጩ የሰው ወጎችን ያወገዘው ለምንድን ነው?

14 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ይሖዋ በነቢዩ ኢሳይያስ አማካኝነት እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ሕዝብ ወደ እኔ የሚቀርበው በአፉ ብቻ ነው፤ በከንፈሩም ያከብረኛል፤ ልቡ ግን ከእኔ እጅግ የራቀ ነው፤ እኔንም የሚፈራው፣ ሰዎች ያስተማሩትን ትእዛዛት በማክበር ነው።” (ኢሳ. 29:13) ኢየሱስ ከቅዱሳን መጻሕፍት ጋር የሚጋጩ የሰው ወጎችን ማውገዙ ትክክል ነበር። ሰው ሠራሽ ሕጎችንና ወጎችን ከቅዱሳን መጻሕፍት ያስበለጡት ሰዎች ይሖዋንና እሱ የላከውን መሲሕ እንደማይቀበሉ አሳይተዋል።

15. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር በተያያዘ የማያስደስታቸው ነገር ምንድን ነው?

15 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። የይሖዋ ምሥክሮች እንደ ልደት እና ገና ያሉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ በዓላት አብረዋቸው አለማክበራቸው ብዙዎችን ያበሳጫቸዋል። ሌሎች ደግሞ የይሖዋ ምሥክሮች በብሔራዊ ክብረ በዓላት ላይ አለመገኘታቸው ወይም ከአምላክ ቃል ጋር በሚጋጩ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች አለመካፈላቸው ያስቆጣቸዋል። በእነዚህ ምክንያቶች የሚሰናከሉ ሰዎች አምላክን በትክክለኛ መንገድ እያመለኩ እንዳለ ከልባቸው ያምኑ ይሆናል። ይሁን እንጂ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኘው ግልጽ ትምህርት ይልቅ የዓለምን ወጎች ከመረጡ አምላክን ማስደሰት አይችሉም።—ማር. 7:7-9

16. ምን ማድረግ አለብን? ከየትኞቹ ነገሮችስ መራቅ ይኖርብናል? (መዝሙር 119:97, 113, 163-165)

16 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? ለይሖዋ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ጥልቅ ፍቅር ማዳበር ይኖርብናል። (መዝሙር 119:97, 113, 163-165ን አንብብ።) ይሖዋን የምንወደው ከሆነ እሱን ከሚያሳዝኑ ልማዶች በሙሉ እንርቃለን። ከይሖዋ አስበልጠን የምንወደው ምንም ነገር አይኖርም።

(4) ኢየሱስ በዘመኑ የነበረውን ፖለቲካዊ ሥርዓት አልለወጠውም

ብዙዎች ኢየሱስ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ጣልቃ ለመግባት ፈቃደኛ ባለመሆኑ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 17ን ተመልከት) *

17. በኢየሱስ ዘመን የኖሩ ብዙ ሰዎች የተሰናከሉት መሲሑ ምን እንደሚያደርግ ይጠብቁ ስለነበር ነው?

17 በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ያኔውኑ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ይፈልጉ ነበር። መሲሑ ከሮማውያን ጭቆና ነፃ እንደሚያወጣቸው ጠብቀው ነበር። ኢየሱስ ግን ሊያነግሡት ሲሞክሩ ፈቃደኛ አልሆነም። (ዮሐ. 6:14, 15) ካህናቱን ጨምሮ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ኢየሱስ ሮማውያንን የሚያስቆጣ ፖለቲካዊ ለውጥ ያመጣል የሚል ስጋት አድሮባቸው ነበር፤ ስጋት ያደረባቸው እንዲህ ያለው ለውጥ ሮማውያን ለካህናቱ የሰጧቸውን ሥልጣን እንዲቀሟቸው ሊያደርግ ስለሚችል ነው። ብዙ አይሁዳውያን በኢየሱስ እንዲሰናከሉ ያደረጓቸው እንዲህ ያሉ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ነበሩ።

18. ብዙዎች ስለ መሲሑ የሚገልጹትን የትኞቹን ትንቢቶች ችላ ብለዋቸው ነበር?

18 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? መሲሑ ከጊዜ በኋላ ድል አድራጊ ንጉሥ እንደሚሆን የሚጠቁሙ በርካታ ትንቢቶች ቢኖሩም ሌሎች ትንቢቶች ደግሞ መሲሑ መጀመሪያ ለኃጢአታችን እንደሚሞት ይገልጻሉ። (ኢሳ. 53:9, 12) ታዲያ አይሁዳውያን ስለ መሲሑ የተሳሳተ አመለካከት የነበራቸው ለምንድን ነው? በኢየሱስ ዘመን የኖሩ በርካታ ሰዎች ችግሮቻቸው ወዲያውኑ እንደሚፈቱ የማይገልጹ ትንቢቶችን ችላ ብለዋቸው ስለነበር ነው።—ዮሐ. 6:26, 27

19. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች የሚሰናከሉት ምን የተሳሳተ አመለካከት ስላላቸው ነው?

19 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። ብዙዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ረገድ ገለልተኛ በመሆናችን ይሰናከሉብናል። ምርጫ ሲካሄድ ድምፅ እንድንሰጥ ይጠብቁብናል። ይሁንና ሰብዓዊ መሪ እንዲገዛን መምረጥ የይሖዋን አገዛዝ አንቀበልም ማለት ይሆንብናል። (1 ሳሙ. 8:4-7) አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ትምህርት ቤቶችንና ሆስፒታሎችን መገንባት እንዲሁም ሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራትን መፈጸም እንዳለብን ይሰማቸዋል። በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ከማድረግ ይልቅ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት በማድረጋችን ይሰናከሉብናል።

20. በማቴዎስ 7:21-23 ላይ ኢየሱስ እንደተናገረው በዋነኝነት ትኩረት ማድረግ የሚገባን በምን ላይ ነው?

20 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? (ማቴዎስ 7:21-23ን አንብብ።) በዋነኝነት ትኩረት ልናደርግ የሚገባው ኢየሱስ የሰጠንን ሥራ በማከናወን ላይ ነው። (ማቴ. 28:19, 20) በዚህ ዓለም ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ትኩረታችን እንዲከፋፈል ፈጽሞ መፍቀድ አይኖርብንም። ሰዎችን እንወዳለን፤ ችግሮቻቸውም ያሳስቡናል። ያም ቢሆን ሰዎችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እነሱን ስለ አምላክ መንግሥት ማስተማርና ከይሖዋ ጋር ወዳጅነት እንዲመሠርቱ መርዳት እንደሆነ እናውቃለን።

21. ቁርጥ ውሳኔያችን ምን ሊሆን ይገባል?

21 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖሩ ብዙ ሰዎች በኢየሱስ እንዲሰናከሉ ያደረጓቸውን አራት ምክንያቶች በዚህ ርዕስ ውስጥ ተመልክተናል፤ እነዚህ ምክንያቶች በዛሬው ጊዜም ብዙዎች የኢየሱስን ተከታዮች እንዳይቀበሉ አድርገዋቸዋል። ይሁንና ሊያሰናክሉ የሚችሉት እነዚህ ነገሮች ብቻ ናቸው? አይደሉም። ሊያሰናክሉ የሚችሉ ሌሎች አራት ነገሮችን በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንመለከታለን። እንግዲያው ላለመሰናከልና ምንጊዜም ጠንካራ እምነት ለመያዝ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

መዝሙር 56 እውነትን የራስህ አድርግ

^ አን.5 ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩት ሰዎች ሁሉ ይልቅ ታላቅ አስተማሪ ቢሆንም በዘመኑ ከነበሩት ሰዎች አብዛኞቹ በእሱ ተሰናክለው ነበር። ለምን? በዚህ ርዕስ ላይ አራት ምክንያቶችን እንመለከታለን። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች በሚናገሩትና በሚያደርጉት ነገር የሚሰናከሉት ለምን እንደሆነ እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ እኛ ራሳችን በኢየሱስ እንዳንሰናከል ጠንካራ እምነት ለማዳበር የሚረዱንን ነጥቦች እንመረምራለን።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ ናትናኤል ኢየሱስን እንዲተዋወቀው ፊልጶስ ሲያበረታታው።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ምሥራቹን ሲሰብክ።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ እጁ የሰለለበትን ሰው ተቃዋሚዎቹ እያዩት ሲፈውስ።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ብቻውን ወደ ተራራ ሲወጣ።