በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ይህን ያውቁ ኖሯል?

ይህን ያውቁ ኖሯል?

በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ደንገል ጀልባ ለመሥራት ያገለግል ነበር?

ደንገል

በጥንቷ ግብፅ፣ ደንገል (ፓፒረስ) ወረቀት ለመሥራት ያገለግል እንደነበር በስፋት ይታወቃል። ግሪካውያንና ሮማውያንም ደንገል ላይ ይጽፉ ነበር። * ሆኖም ደንገል ለመጻፊያነት ብቻ ሳይሆን ለጀልባ መሥሪያነትም ጥቅም ላይ ይውል እንደነበር በብዙዎች ዘንድ አይታወቅም።

በግብፃውያን መቃብር ውስጥ የተገኙትን የደንገል ጀልባዎች በማስመሰል የተሠሩ ሁለት ሞዴሎች

ከ2,500 ዓመታት በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ “በኢትዮጵያ ወንዞች አካባቢ” የሚኖሩ ሰዎች “በደንገል ጀልባ ውኃዎችን አቋርጠው የሚሄዱ መልእክተኞችን” እንደላኩ ጽፏል። ከጊዜ በኋላ ደግሞ ነቢዩ ኤርምያስ፣ ሜዶናውያንና ፋርሳውያን የባቢሎንን ከተማ ሲወርሩ ባቢሎናውያኑ እንዳያመልጡ ሲሉ ‘የደንገል ጀልባዎቻቸውን እንደሚያቃጥሉባቸው’ ትንቢት ተናግሯል።—ኢሳ. 18:1, 2፤ ኤር. 51:32

ለመሆኑ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች ምን ያሳያሉ? የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች በግብፅ ከደንገል ጀልባ ይሠራ እንደነበር የሚያረጋግጥ ግልጽ ማስረጃ አግኝተዋል። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው በአምላክ መንፈስ መሪነት ነው፤ ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ደንገል ጀልባ ለመሥራት ያገለግል እንደነበር የሚያረጋግጡ የአርኪኦሎጂ ግኝቶች መኖራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን አያስገርምም።—2 ጢሞ. 3:16

የደንገል ጀልባዎች የሚሠሩት እንዴት ነበር?

በግብፃውያን መቃብሮች ውስጥ የተገኙ ሥዕሎችና የግድግዳ ላይ ቅርጾች፣ ደንገል የሚሰበሰበውና ጀልባ ለመሥራት የሚውለው እንዴት እንደሆነ ያሳያሉ። ሰዎች ደንገሎቹን ቆርጠው በነዶ በነዶ ያስሯቸዋል፤ ከዚያም ነዶዎቹን አንድ ላይ ያስሯቸዋል። የደንገል አገዳ ሦስት ማዕዘን ቅርጽ አለው። ስለዚህ አገዳዎቹን አንድ ላይ ጥብቅ አድርጎ በማሰር የሚሠሩት ነዶዎች ጠንካራና ጥቅጥቅ ያሉ ናቸው። ኤ ኮምፓንየን ቱ ኤንሸንት ኢጂፕት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው የደንገል ጀልባዎች ከ17 ሜትር በላይ ርዝመት ሊኖራቸው ይችላል፤ በመሆኑም ጀልባው በእያንዳንዱ ጎን 10 ወይም 12 መቅዘፊያ ሊኖረው ይችላል።

የደንገል ጀልባን አሠራር የሚያሳይ ግብፅ ውስጥ የተገኘ ግድግዳ ላይ የተቀረጸ ምስል

ጀልባ ሠሪዎች ደንገል ይጠቀሙ የነበረው ለምንድን ነው?

ደንገል በናይል ሸለቆ ውስጥ በቀላሉ የሚገኝ ጥሬ ዕቃ ነበር። ከዚህም ሌላ በአንጻራዊ ሁኔታ የደንገል ጀልባዎችን መሥራት ቀላል ነበር። ሰዎች መርከብ ለመገንባት በዋነኝነት እንጨት መጠቀም ከጀመሩ በኋላም እንኳ ዓሣ አጥማጆችና አዳኞች ከደንገል የተሠሩ ታንኳዎችንና ትናንሽ ጀልባዎችን መጠቀማቸውን ቀጥለው የነበረ ይመስላል።

ከደንገል የተሠሩ ጀልባዎች ለበርካታ ዘመናት ተፈላጊ ሆነው ቆይተዋል። በመጀመሪያውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የኖረው ግሪካዊው ጸሐፊ ፕሉታርክ እንደገለጸው የደንገል ጀልባዎች በእሱ ዘመንም ጥቅም ላይ ይውሉ ነበር።

^ አን.3 ደንገል የሚበቅለው በረግረጋማ አካባቢዎች እና ዝግ ብለው በሚፈሱ ወንዞች ውስጥ ነው። ይህ ተክል እስከ 5 ሜትር ድረስ ሊያድግ ይችላል፤ አገዳው ደግሞ ከታች በኩል እስከ 15 ሴንቲ ሜትር የሚደርስ ስፋት ሊኖረው ይችላል።