በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 21

ይሖዋ ብርታት ይሰጣችኋል

ይሖዋ ብርታት ይሰጣችኋል

“ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።”—2 ቆሮ. 12:10

መዝሙር 73 ድፍረት ስጠን

ማስተዋወቂያ *

1-2. በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች ምን ተፈታታኝ ሁኔታ ያጋጥማቸዋል?

ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ እንዲፈጽም ጢሞቴዎስን አበረታቶታል፤ ይህ ምክር ለሁሉም ክርስቲያኖች ይሠራል። (2 ጢሞ. 4:5) ሁላችንም የጳውሎስን ምክር ለመከተል የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ያም ቢሆን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። ብዙዎቹ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን በስብከቱ ሥራ ለመካፈል ትልቅ ድፍረት ይጠይቅባቸዋል። (2 ጢሞ. 4:2) ለምሳሌ፣ በሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አልፎ ተርፎም ሥራችን በታገደባቸው አገሮች ውስጥ የሚኖሩ ወንድሞቻችንን አስቡ። እነዚህ ወንድሞች ሊታሰሩ እንደሚችሉ ቢያውቁም እንኳ መስበካቸውን ይቀጥላሉ!

2 የይሖዋ ሕዝቦች ተስፋ አስቆራጭ ከሆኑ የተለያዩ ችግሮች ጋር ይታገላሉ። ለምሳሌ ብዙዎች ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን መሠረታዊ ነገር ለማቅረብ እንኳ ለረጅም ሰዓት መሥራት ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ክርስቲያኖች በአገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ቢፈልጉም በሳምንቱ መጨረሻ ይህን ለማድረግ የሚያስችል ኃይል አይኖራቸውም። ሌሎች ደግሞ ባደረባቸው ከባድ በሽታ ወይም በዕድሜ መግፋት የተነሳ ብዙ ማገልገል አይችሉም፤ እንዲያውም አንዳንዶች ጨርሶ ከቤት መውጣት አይችሉ ይሆናል። ‘አልረባም’ ከሚል ስሜት ጋር የሚታገሉም አሉ። በመካከለኛው ምሥራቅ የምትኖር ሜሪ * የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “አሉታዊ ስሜቶቼን ማሸነፍ ሁልጊዜ ትግል ይጠይቅብኛል፤ በዚህም ምክንያት ኃይሌ በእጅጉ ይሟጠጣል። ይህ ደግሞ ለአገልግሎት ላውለው የምችለውን ጊዜና ጉልበት ስለሚሻማብኝ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል።”

3. በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመረምራለን?

3 ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ችግሮቻችንን እንድንቋቋምና ሁኔታችን በፈቀደው መጠን እሱን ማገልገላችንን እንድንቀጥል ኃይል ሊሰጠን ይችላል። ይሖዋ እኛን የሚረዳን እንዴት እንደሆነ ከመመልከታችን በፊት ግን ጳውሎስ እና ጢሞቴዎስ ያጋጠሟቸውን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተቋቁመው አገልግሎታቸውን መፈጸማቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታቸው እንዴት እንደሆነ እንመርምር።

የስብከቱን ሥራ ለማከናወን የሚያስችል ብርታት

4. ጳውሎስ የትኞቹ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል?

4 ጳውሎስ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። በተለይ ደግሞ በተደበደበበት፣ በድንጋይ በተወገረበት እንዲሁም በታሰረበት ጊዜ ብርታት አስፈልጎታል። (2 ቆሮ. 11:23-25) ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር መታገል እንዳስፈለገውም ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ሮም 7:18, 19, 24) በተጨማሪም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” በማለት የጠራው የጤና እክል ነበረበት፤ አምላክ ይህን ችግር እንዲያስወግድለት በተደጋጋሚ ለምኖ ነበር።—2 ቆሮ. 12:7, 8

ጳውሎስ አገልግሎቱን እንዲያከናውን የረዳው ምንድን ነው? (ከአንቀጽ 5-6ን ተመልከት) *

5. ጳውሎስ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙትም ምን ማከናወን ችሏል?

5 ጳውሎስ ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም አገልግሎቱን እንዲፈጽም ይሖዋ ብርታት ሰጥቶታል። ጳውሎስ ምን እንዳከናወነ ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ በነበረበት ጊዜ በአይሁድ መሪዎችና በመንግሥት ባለ ሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ በቅንዓት ተሟግቷል። (ሥራ 28:17፤ ፊልጵ. 4:21, 22) ከዚህም በተጨማሪ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ውስጥ ለነበሩ ብዙ ሰዎች እንዲሁም ሊጠይቁት ለመጡ ሰዎች ሁሉ መሥክሯል። (ሥራ 28:30, 31፤ ፊልጵ. 1:13) በዚያው ወቅት ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ደብዳቤዎችን ጽፏል፤ እነዚህ ደብዳቤዎች በዘመናችን ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ናቸው። ከዚህም ሌላ የጳውሎስ ምሳሌ በሮም ጉባኤ ውስጥ የነበሩ ወንድሞችንና እህቶችን አበረታቷል፤ በዚህም የተነሳ እነዚህ ወንድሞች “የአምላክን ቃል ያለፍርሃት ለመናገር ከቀድሞው የበለጠ ድፍረት” ማሳየት ችለዋል። (ፊልጵ. 1:14) ጳውሎስ ማከናወን የሚችለው ነገር በተገደበበት ጊዜም አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አድርጓል፤ ይህም “ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ” አስተዋጽኦ አድርጓል።—ፊልጵ. 1:12

6. በ2 ቆሮንቶስ 12:9, 10 መሠረት ጳውሎስ አገልግሎቱን እንዲፈጽም የረዳው ምንድን ነው?

6 ጳውሎስ በይሖዋ አገልግሎት ብዙ ነገሮችን ሊያከናውን የቻለው በአምላክ ብርታት እንጂ በራሱ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። ጳውሎስ፣ የአምላክ ኃይል “ፍጹም የሚሆነው [በሚደክምበት] ጊዜ” እንደሆነ ተገንዝቧል። (2 ቆሮንቶስ 12:9, 10ን አንብብ።) ስደት፣ እስርና ሌሎች ችግሮች ቢያጋጥሙትም አገልግሎቱን በተሟላ ሁኔታ ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ኃይል ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ሰጥቶታል።

ጢሞቴዎስ አገልግሎቱን እንዲያከናውን የረዳው ምንድን ነው? (አንቀጽ 7ን ተመልከት) *

7. ጢሞቴዎስ አገልግሎቱን ለመፈጸም የትኞቹን ተፈታታኝ ሁኔታዎች መወጣት አስፈልጎታል?

7 የጳውሎስ የአገልግሎት ጓደኛ የሆነው ወጣቱ ጢሞቴዎስም አገልግሎቱን ለመፈጸም በይሖዋ ኃይል መታመን አስፈልጎታል። ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ ባደረጋቸው ረጅም ሚስዮናዊ ጉዞዎች ላይ አብሮት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ ጢሞቴዎስ ወደተለያዩ ቦታዎች ተጉዞ ጉባኤዎችን እንዲያበረታታ ጳውሎስ ልኮት ነበር። (1 ቆሮ. 4:17) ጢሞቴዎስ እነዚህን ተልእኮዎች ለመፈጸም ብቃት እንደሌለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ምናልባትም ጳውሎስ “ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም” የሚል ምክር የሰጠው ለዚህ ሊሆን ይችላል። (1 ጢሞ. 4:12) በዚያ ላይ ደግሞ ጢሞቴዎስም በዚህ ወቅት ሥጋውን የሚወጋ እሾህ ይኸውም ‘በተደጋጋሚ የሚነሳ ሕመም’ ነበረበት። (1 ጢሞ. 5:23) ሆኖም ጢሞቴዎስ፣ ኃያል የሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምሥራቹን ለመስበክና ወንድሞቹን ለማገልገል የሚያስፈልገውን ብርታት እንደሚሰጠው እርግጠኛ ነበር።—2 ጢሞ. 1:7

ፈተናዎች ቢኖሩም ታማኝ ሆኖ ለመቀጠል የሚያስችል ብርታት

8. ይሖዋ በዛሬው ጊዜ ሕዝቦቹን የሚያበረታቸው እንዴት ነው?

8 በዛሬው ጊዜ ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ እሱን በታማኝነት ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ ለመርዳት “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጣቸዋል። (2 ቆሮ. 4:7) ይሖዋ እኛን ለማበርታትና ምንጊዜም ለእሱ ታማኝ እንድንሆን ለመርዳት ያደረጋቸውን አራት ዝግጅቶች እንመልከት፤ እነሱም ጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም አገልግሎታችን ናቸው።

ይሖዋ በጸሎት አማካኝነት ያበረታናል (አንቀጽ 9ን ተመልከት)

9. ጸሎት የሚረዳን እንዴት ነው?

9 ከጸሎት ብርታት ማግኘት። በኤፌሶን 6:18 ላይ ተመዝግቦ እንደምናገኘው ጳውሎስ “በማንኛውም ጊዜ” ወደ አምላክ እንድንጸልይ አበረታቶናል። እንዲህ ካደረግን አምላካችን ያበረታናል። በቦሊቪያ የሚኖረው ጆኒ መከራዎች በተደራረቡበት ጊዜ እንዲህ ያለውን የአምላክ ድጋፍ አግኝቷል። ባለቤቱና ሁለቱም ወላጆቹ በተመሳሳይ ጊዜ በጠና ታመሙ። ጆኒ ሦስቱንም መንከባከብ ከባድ ሆኖበት ነበር። ከጊዜ በኋላ እናቱ አረፉ፤ ባለቤቱና አባቱም ቢሆኑ ከሕመማቸው ለማገገም ረጅም ጊዜ ወስዶባቸዋል። ጆኒ ስለዚያ ጊዜ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ በምሆንበት ጊዜ የረዳኝ ነገር፣ የምፈልገውን ለይቼ በመጥቀስ ወደ ይሖዋ መጸለዬ ነው።” ጆኒ ለመጽናት የሚያስፈልገውን ብርታት ይሖዋ ሰጥቶታል። የሮናልድን ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። ቦሊቪያ ውስጥ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ የሚያገለግለው ሮናልድ እናቱ ካንሰር እንዳለባቸው አወቀ። ከዚያም እናቱ ከአንድ ወር በኋላ አረፉ። ታዲያ ሮናልድ ሁኔታውን ለመቋቋም የረዳው ምንድን ነው? እንዲህ ብሏል፦ “ወደ ይሖዋ መጸለዬ የልቤን ለማፍሰስና ስሜቴን አውጥቼ ለመናገር አስችሎኛል። ከማንም ሰው በተሻለ ስሜቴን እንደሚረዳልኝ አውቃለሁ፤ ራሴን ከማውቀው በላይ እንኳ እሱ ያውቀኛል።” አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ከአቅማችን በላይ ሆኖ አእምሯችንን ስለሚቆጣጠረው ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ ሊገባን ይችላል። ሆኖም ሐሳባችንን እና ስሜታችንን በቃላት ማስቀመጥ በሚከብደን ጊዜም እንኳ ይሖዋ ወደ እሱ እንድንጸልይ ጋብዞናል።—ሮም 8:26, 27

ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያበረታናል (አንቀጽ 10ን ተመልከት)

10. በዕብራውያን 4:12 መሠረት መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

10 ከመጽሐፍ ቅዱስ ብርታት ማግኘት። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ከቅዱሳን መጻሕፍት ብርታትና መጽናኛ ማግኘት እንችላለን። (ሮም 15:4) የአምላክን ቃል ስናነብና ባነበብነው ነገር ላይ ስናሰላስል፣ ይሖዋ በመንፈሱ ተጠቅሞ ከቃሉ ያነበብነው ነገር ለእኛ ሁኔታ የሚሠራው እንዴት እንደሆነ እንድንገነዘብ ሊረዳን ይችላል። (ዕብራውያን 4:12ን አንብብ።) ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሮናልድ እንዲህ ብሏል፦ “በየምሽቱ መጽሐፍ ቅዱስን የማንበብ ልማድ በማዳበሬ ደስተኛ ነኝ። በይሖዋ ባሕርያትና ለአገልጋዮቹ ባሳየው ፍቅር ላይ ጊዜ ወስጄ አሰላስላለሁ። ይህ ደግሞ ኃይሌን ያድሰዋል።”

11. መጽሐፍ ቅዱስ ሐዘን የደረሰባትን አንዲት እህት የረዳት እንዴት ነው?

11 በአምላክ ቃል ላይ ማሰላሰላችን ስላለንበት ሁኔታ ተገቢውን አመለካከት ለማዳበር ይረዳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ባለቤቷን በሞት ያጣችን አንዲት እህት እንዴት እንደረዳት እንመልከት። የኢዮብን መጽሐፍ በማንበብ ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት እንደምትችል አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ነገራት። እህታችን መጽሐፉን ስታነብ መጀመሪያ ላይ፣ ኢዮብ የተሳሳተ አመለካከት በመያዙ እንደፈረደችበት ተናግራለች። ታሪኩን ስታነብ “አይ ኢዮብ! የራስህ ችግር ብቻ ነው እንዴ የሚታይህ?” በማለት እየገሠጸችው ነበር። በኋላ ግን የእሷም አመለካከት ከኢዮብ ጋር በጣም ተመሳሳይ እንደሆነ አስተዋለች። ይህም አመለካከቷን ለማስተካከል የረዳት ከመሆኑም ሌላ ባለቤቷን ማጣቷ ያስከተለባትን ሐዘን ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ሰጥቷታል።

ይሖዋ በወንድሞችና እህቶች አማካኝነት ያበረታናል (አንቀጽ 12ን ተመልከት)

12. ይሖዋ በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት የሚያበረታን እንዴት ነው?

12 ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ብርታት ማግኘት። ይሖዋ ክርስቲያኖችን የሚያበረታበት ሌላው መንገድ የእምነት ባልንጀሮቻቸውን በመጠቀም ነው። ጳውሎስ ከመንፈሳዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ እንደሚጓጓ ጽፏል። (ሮም 1:11, 12) ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሜሪ ከእምነት አጋሮቿ ጋር መሆን በጣም ያስደስታታል። እንዲህ ብላለች፦ “ይሖዋ ስለ ችግሬ የማያውቁ ወንድሞችንና እህቶችን እንኳ ተጠቅሞ ረድቶኛል። በንግግራቸው ያበረታቱኝ ወይም ካርድ የላኩልኝ ወንድሞችና እህቶች አሉ፤ ልክ በዚያ ወቅት ያስፈለገኝን ማበረታቻ አግኝቻለሁ። ከእኔ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ችግር ላጋጠማቸው እህቶች ስሜቴን መናገሬና ከእነሱ ተሞክሮ መማሬም ጠቅሞኛል። በተጨማሪም ሽማግሌዎቹ ምንጊዜም ጠቃሚ የጉባኤው ክፍል እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጉኛል።”

13. በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አንዳችን ሌላውን ማበረታታት የምንችለው እንዴት ነው?

13 አንዳችን ሌላውን ማበረታታት ከምንችልባቸው ግሩም አጋጣሚዎች አንዱ የጉባኤ ስብሰባ ነው። በስብሰባዎች ላይ ስትገኙ ቅድሚያውን ወስዳችሁ፣ ወንድሞቻችሁን እንደምትወዷቸውና እንደምታደንቋቸው በመንገር ለምን አታበረታቷቸውም? ለምሳሌ ያህል፣ ፒተር የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላትን አንዲት እህት ከስብሰባ በፊት እንዲህ ብሏት ነበር፦ “አንቺን እዚህ ማየታችን በጣም ያበረታታናል። ስድስቱን ልጆችሽን ሁልጊዜ አለባብሰሽና ሐሳብ እንዲሰጡ አዘጋጅተሽ ይዘሻቸው ትመጫለሽ።” እህትም ዓይኖቿ እንባ አቅርረው በአመስጋኝነት ስሜት “እንዲህ ያለ ማበረታቻ ዛሬ በጣም ያስፈልገኝ ነበር” በማለት መለሰች።

ይሖዋ በአገልግሎት አማካኝነት ያበረታናል (አንቀጽ 14ን ተመልከት)

14. በአገልግሎት መካፈል የሚረዳን እንዴት ነው?

14 ከአገልግሎት ብርታት ማግኘት። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ለሌሎች ስናካፍል ሰዎቹ ጥሩ ምላሽ ሰጡም አልሰጡ መንፈሳችን ይታደሳል፤ እንዲሁም ብርታት እናገኛለን። (ምሳሌ 11:25) ስቴሲ የተባለች እህት አገልግሎት ምን ያህል እንደሚያበረታታ በራሷ ሕይወት ተመልክታለች። አንድ የቤተሰቧ አባል ከጉባኤ በተወገደ ጊዜ በጣም አዝና ነበር። ‘የተወገደው እኔ በደንብ ስላልረዳሁት ይሆን?’ እያለች ራሷን ትጠይቅ ነበር። ይህ ጉዳይ አእምሮዋን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጠረው። ታዲያ ይህን አስጨናቂ ሁኔታ ለመወጣት የረዳት ምንድን ነው? አገልግሎት ነው! በስብከቱ ሥራ ስትጠመድ በአገልግሎት ክልሏ ውስጥ የእሷ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ሰዎች ላይ ማተኮር ጀመረች። እንዲህ ብላለች፦ “በዚያ ወቅት ይሖዋ፣ ፈጣን እድገት የምታደርግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ሰጠኝ። ይሄ በእጅጉ አበረታታኝ። በሕይወቴ ውስጥ ሚዛኔን እንድጠብቅ የረዳኝ ዋነኛው ነገር አገልግሎት ነው።”

15. ሜሪ ከተናገረችው ሐሳብ ምን ትምህርት እናገኛለን?

15 አንዳንዶች ባሉበት ሁኔታ የተነሳ በአገልግሎት ብዙ ማከናወን እንደማይችሉ ይሰማቸው ይሆናል። አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ይሖዋ ምርጥህን እስከሰጠኸው ድረስ እንደሚደሰት አስታውስ። ቀደም ሲል የተጠቀሰችውን ሜሪን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በሌላ አገር ቋንቋ ወደሚመራ ጉባኤ በተዛወረች ጊዜ አገልግሎቷ በእጅጉ እንደተገደበ ተሰምቷት ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ አካባቢ አጭር ሐሳብ ከመስጠት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ከማንበብ ወይም አገልግሎት ላይ ትራክት ከማበርከት ያለፈ ነገር ማድረግ አልችልም ነበር።” ሜሪ ቋንቋውን አቀላጥፈው መናገር ከሚችሉ ሰዎች አንጻር ጠቃሚ አስተዋጽኦ እያደረገች እንደሆነ አልተሰማትም። ያም ቢሆን አመለካከቷን አስተካከለች። ችሎታዋ ውስን ቢሆንም ይሖዋ ሊጠቀምባት እንደሚችል ተገነዘበች። እንዲህ ብላለች፦ “ሕይወት አድን የሆኑት የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለመረዳት በጣም ቀላል ናቸው፤ ደግሞም የሰዎችን ሕይወት የሚለውጡት እነዚህ እውነቶች ናቸው።”

16. በሕመም ምክንያት ከቤት መውጣት የማይችሉ ክርስቲያኖች ብርታት ለማግኘት ምን ሊረዳቸው ይችላል?

16 በሕመም ምክንያት ከቤት መውጣት ባንችልም እንኳ ይሖዋ በአገልግሎት ለመካፈል ያለንን ጉጉት ይመለከታል፤ ጥረታችንንም ያደንቃል። ይሖዋ፣ ለሚያስታምሙን ሰዎች ወይም ለሕክምና ባለሙያዎች ለመመሥከር አጋጣሚ ሊከፍትልን ይችላል። አሁን የምናከናውነውን አገልግሎት ቀደም ሲል እናከናውን ከነበረው ጋር የምናወዳድር ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ይሁን እንጂ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ እየረዳን ያለው እንዴት እንደሆነ የምንገነዘብ ከሆነ የሚያጋጥመንን ማንኛውንም ፈተና በደስታ ለመቋቋም የሚያስችል ብርታት ይኖረናል።

17. በመክብብ 11:6 መሠረት የሥራችን ውጤት ወዲያውኑ ባይታየንም እንኳ መስበካችንን መቀጠል ያለብን ለምንድን ነው?

17 ከምንዘራቸው የእውነት ዘሮች መካከል የሚጸድቁትና የሚያድጉት የትኞቹ እንደሆኑ አናውቅም። (መክብብ 11:6ን አንብብ።) ለምሳሌ በ80ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙት እህት ባርባራ ያጋጠማቸውን እንመልከት፤ እኚህ እህት በስልክና በደብዳቤ አዘውትረው ይመሠክራሉ። በአንድ ወቅት ከደብዳቤያቸው ጋር “አምላክ ምን አድርጎልሃል?” የሚል ርዕስ ያለውን የመጋቢት 1, 2014 መጠበቂያ ግንብ አብረው ልከው ነበር። እሳቸው ባያውቁትም ይህን ደብዳቤ የላኩት ከጉባኤ ለተወገዱ ባልና ሚስት ነበር። እነዚህ ባልና ሚስት መጽሔቱን ደጋግመው አነበቡት። ባልየው መጽሔቱን ሲያነብ ይሖዋ በቀጥታ እያነጋገረው እንዳለ እንደተሰማው ተናግሯል። እነዚህ ባልና ሚስት በስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመሩ፤ ከጉባኤ ከተወገዱ ከ27 ዓመታት በኋላ ወደ ይሖዋ ጉባኤ ተመለሱ። እህት ባርባራ የላኩት ደብዳቤ ያስገኘውን ግሩም ውጤት ሲመለከቱ ምን ያህል ተበረታተው ሊሆን እንደሚችል አስቡት!

ይሖዋ (1) በጸሎት፣ (2) በመጽሐፍ ቅዱስ፣ (3) በወንድሞችና እህቶች እንዲሁም (4) በአገልግሎት አማካኝነት ያበረታናል (አንቀጽ 9-10, 12, 14⁠ን ተመልከት)

18. ከአምላክ ኃይል ለመጠቀም ምን ማድረግ ይኖርብናል?

18 ይሖዋ ወሰን የሌለውን ኃይሉን ማየት የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ከፍቶልናል። እንደ ጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ ወንድሞችና እህቶች እንዲሁም አገልግሎት ባሉት የይሖዋ ዝግጅቶች ስንጠቀም ይሖዋ እኛን ለመርዳት ችሎታውም ሆነ ፍላጎቱ እንዳለው እንደምንተማመን እናሳያለን። እንግዲያው “በሙሉ ልባቸው ወደ እሱ ላዘነበሉት ሰዎች ብርታቱን [ማሳየት]” በሚያስደስተው በሰማያዊው አባታችን ምንጊዜም እንታመን!—2 ዜና 16:9

መዝሙር 61 እናንተ ምሥክሮች ወደፊት ግፉ!

^ አን.5 የምንኖርበት ዘመን ተፈታታኝ ነው፤ ሆኖም ይሖዋ ለመጽናት የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። ይሖዋ ሐዋርያው ጳውሎስና ጢሞቴዎስ ያጋጠሟቸውን ችግሮች ተቋቁመው እሱን ማገልገላቸውን እንዲቀጥሉ የረዳቸው እንዴት እንደሆነ በዚህ ርዕስ ውስጥ እንመለከታለን። በተጨማሪም በዛሬው ጊዜ መጽናት እንድንችል ይሖዋ ያደረገልንን አራት ዝግጅቶች እንመረምራለን።

^ አን.2 ስሟ ተቀይሯል።

^ አን.53 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጳውሎስ ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ በነበረበት ጊዜ ለተለያዩ ጉባኤዎች ደብዳቤ ሲጽፍ እንዲሁም ሊጠይቁት ለመጡት ሰዎች ምሥራቹን ሲሰብክ።

^ አን.55 የሥዕሉ መግለጫ፦ ጢሞቴዎስ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ወንድሞችን ሲያበረታታ።