በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የጥናት ርዕስ 19

ጻድቃንን ሊያሰናክላቸው የሚችል ምንም ነገር የለም

ጻድቃንን ሊያሰናክላቸው የሚችል ምንም ነገር የለም

“ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ሊያደናቅፋቸው የሚችል ምንም ነገር የለም።”—መዝ. 119:165

መዝሙር 122 ጸንታችሁ ቁሙ፣ አትነቃነቁ!

ማስተዋወቂያ *

1-2. አንድ ጸሐፊ ምን ብለዋል? በዚህ ርዕስ ውስጥ ምን እንመለከታለን?

በዛሬው ጊዜ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ እንደሚያምኑ ይናገራሉ፤ ሆኖም እሱ ያስተማራቸውን ነገሮች አይቀበሉም። (2 ጢሞ. 4:3, 4) እንዲያውም አንድ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል፦ “በዛሬው ጊዜ ሌላ ኢየሱስ ቢነሳና ጥንት የነበረው ኢየሱስ ባስተማረበት መንገድ ቢያስተምር . . . ከሁለት ሺህ ዓመት በፊት የነበሩ ሰዎች እንዳልተቀበሉት እኛም ሳንቀበለው እንቀር ይሆን? . . . መልሱ ግልጽ ነው፦ አዎ፣ አንቀበለውም።”

2 በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ሰዎች ኢየሱስ ሲያስተምር ያዳመጡና ተአምራት ሲፈጽም የተመለከቱ ቢሆንም በእሱ ለማመን ፈቃደኞች አልሆኑም። ለምን? ባለፈው ርዕስ ላይ ሰዎች ኢየሱስ በተናገረውና ባደረገው ነገር የተሰናከሉባቸውን አራት ምክንያቶች ተመልክተናል። አሁን ደግሞ አራት ተጨማሪ ምክንያቶችን እንመለከታለን። ከዚህም ሌላ በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች የማይቀበሉባቸውን ምክንያቶች እንዲሁም እኛ ራሳችን እንዳንሰናከል ምን ማድረግ እንደምንችል እንመለከታለን።

(1) ኢየሱስ አያዳላም ነበር

ብዙዎች ኢየሱስ እንደ ኃጢአተኛ ከሚቆጠሩ ሰዎች ጋር ጊዜ በማሳለፉ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 3ን ተመልከት) *

3. አንዳንዶችን ያሰናከላቸው ኢየሱስ ምን ማድረጉ ነው?

3 ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ከሁሉም ዓይነት ሰዎች ጋር ጊዜ ያሳልፍ ነበር። ኢየሱስ ሀብትና ሥልጣን ካላቸው ሰዎች ጋር ተመግቧል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከድሆችና ከተጨቆኑ ሰዎች ጋርም ብዙ ጊዜ አሳልፏል። በተጨማሪም ብዙዎች እንደ ኃጢአተኛ አድርገው ለሚቆጥሯቸው ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። ተመጻዳቂ የሆኑ አንዳንድ ሰዎች ኢየሱስ ባደረገው ነገር ተሰናክለዋል። ደቀ መዛሙርቱን “ከቀረጥ ሰብሳቢዎችና ከኃጢአተኞች ጋር የምትበሉትና የምትጠጡት ለምንድን ነው?” በማለት ጠይቀዋቸው ነበር። ኢየሱስም እንዲህ በማለት መለሰ፦ “ሐኪም የሚያስፈልጋቸው ሕመምተኞች እንጂ ጤነኞች አይደሉም። እኔ የመጣሁት ኃጢአተኞች ንስሐ እንዲገቡ ለመጥራት እንጂ ጻድቃንን ለመጥራት አይደለም።”—ሉቃስ 5:29-32

4. በነቢዩ ኢሳይያስ ትንቢት መሠረት አይሁዳውያን ስለ መሲሑ ምን ነገር መጠበቅ ነበረባቸው?

4 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ኢየሱስ ከመምጣቱ ከረጅም ጊዜ በፊት ነቢዩ ኢሳይያስ፣ መሲሑ በዓለም ዘንድ ሰፊ ተቀባይነት እንደማያገኝ ተናግሮ ነበር። ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ሰዎች የናቁትና ያገለሉት . . . ሰው ነበር። ፊቱ የተሰወረብን ያህል ነበር። ሰዎች ናቁት፤ እኛም ከቁብ አልቆጠርነውም።” (ኢሳ. 53:3) መሲሑን “ሰዎች” እንደሚንቁት ተነግሯል፤ ስለዚህ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን ኢየሱስ ተቀባይነት እንደማያገኝ መጠበቅ ነበረባቸው።

5. በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ለኢየሱስ ተከታዮች ምን አመለካከት አላቸው?

5 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በርካታ ቀሳውስት ታዋቂ፣ ሀብታም ወይም በዓለም ዘንድ እንደ ጥበበኛ የሚታዩ ሰዎችን እጃቸውን ዘርግተው ይቀበላሉ። እነዚህ ሰዎች ሥነ ምግባራቸውና አኗኗራቸው ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የማይስማማ ቢሆንም እንኳ ቀሳውስቱ በደስታ ይቀበሏቸዋል። ሆኖም እነዚሁ ቀሳውስት፣ ቀናተኛ እና በሥነ ምግባር ንጹሕ የሆኑትን የይሖዋን ታማኝ አገልጋዮች በንቀት ይመለከታሉ፤ እንዲህ የሚያደርጉት የአምላክ አገልጋዮች በዓለም መሥፈርት ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ባለመሆናቸው ነው። ጳውሎስ እንደገለጸው አምላክ የመረጣቸው ሰዎች ‘የተናቁ’ ናቸው። (1 ቆሮ. 1:26-29) በይሖዋ ዓይን ግን ሁሉም ታማኝ አገልጋዮቹ ውድ ናቸው።

6. በማቴዎስ 11:25, 26 ላይ የተገለጸውን የኢየሱስን አመለካከት ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው?

6 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? (ማቴዎስ 11:25, 26ን አንብብ።) ዓለም ለይሖዋ ሕዝቦች ያለው አመለካከት ተጽዕኖ ሊያደርግብን አይገባም። ይሖዋ ፈቃዱን ለመፈጸም የሚጠቀመው ትሑት ሰዎችን ብቻ እንደሆነ ልንዘነጋ አይገባም። (መዝ. 138:6) ደግሞም ይሖዋ በዓለም ዓይን ጥበበኛ ባልሆኑ ወይም ባልተማሩ ሰዎች ተጠቅሞ ምን ያህል ሥራ እንዳከናወነ ማሰብ ይኖርብናል።

(2) ኢየሱስ የተሳሳቱ ሐሳቦችን አጋልጧል

7. ኢየሱስ ፈሪሳውያንን ግብዞች ያላቸው ለምንድን ነው? እነሱስ ምን ምላሽ ሰጡ?

7 ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን ግብዝነት የሚንጸባረቅባቸው ሃይማኖታዊ ልማዶች በድፍረት አውግዟል። ለምሳሌ ፈሪሳውያን፣ ወላጆቻቸውን ከሚንከባከቡበት መንገድ ይልቅ እጃቸውን የሚታጠቡበት መንገድ ያሳስባቸው ነበር፤ ኢየሱስም የእነሱን ግብዝነት አጋልጧል። (ማቴ. 15:1-11) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እሱ በተናገረው ነገር ተገርመው መሆን አለበት። እንዲያውም “ፈሪሳውያን በተናገርከው ነገር ቅር እንደተሰኙ [እንደተሰናከሉ] አውቀሃል?” ብለው ጠይቀውታል። ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አላቸው፦ “የሰማዩ አባቴ ያልተከለው ተክል ሁሉ ይነቀላል። ተዉአቸው፤ እነሱ ዕውር መሪዎች ናቸው። ስለዚህ ዕውር ዕውርን ቢመራ ሁለቱም ጉድጓድ ውስጥ ይወድቃሉ።” (ማቴ. 15:12-14) ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎች መበሳጨታቸው እውነቱን ከመናገር እንዲያግደው አልፈቀደም።

8. ኢየሱስ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሁሉም ሃይማኖታዊ እምነቶች እንዳልሆኑ ያሳየው እንዴት ነው?

8 ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶችንም አጋልጧል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ሁሉም ሃይማኖታዊ እምነቶች እንደሆኑ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ብዙዎች ወደ ጥፋት በሚወስደው ሰፊ መንገድ እንደሚሄዱና ወደ ሕይወት የሚወስደውን ቀጭን መንገድ የሚያገኙት ጥቂቶች ብቻ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 7:13, 14) በተጨማሪም አንዳንዶች አምላክን የሚያገለግሉ ቢመስሉም እሱን በትክክለኛው መንገድ እያገለገሉ እንዳልሆኑ በግልጽ ተናግሯል። እንዲህ በማለት አስጠንቅቋል፦ “በውስጣቸው ነጣቂ ተኩላዎች ሆነው ሳሉ የበግ ለምድ ለብሰው ወደ እናንተ ከሚመጡ ሐሰተኛ ነቢያት ተጠንቀቁ። ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።”—ማቴ. 7:15-20

ብዙዎች ኢየሱስ የሐሰት እምነቶችንና ልማዶችን በማውገዙ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 9ን ተመልከት) *

9. ኢየሱስ ካጋለጣቸው የሐሰት ሃይማኖታዊ ትምህርቶች መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው?

9 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሲሑ ለይሖዋ ቤት ያለው ቅንዓት እንደሚበላው ይናገራል። (መዝ. 69:9፤ ዮሐ. 2:14-17) ኢየሱስ የሐሰት ሃይማኖታዊ እምነቶችንና ልማዶችን እንዲያጋልጥ ያነሳሳው ይህ ቅንዓት ነው። ለምሳሌ ፈሪሳውያን ነፍስ እንደማትሞት ያምኑ ነበር፤ ኢየሱስ ግን የሞቱ ሰዎች እንቅልፍ ላይ እንደሆኑ አስተምሯል። (ዮሐ. 11:11) ሰዱቃውያን ትንሣኤ የለም ይሉ ነበር፤ ኢየሱስ ግን ወዳጁን አልዓዛርን ከሞት አስነስቶታል። (ዮሐ. 11:43, 44፤ ሥራ 23:8) ፈሪሳውያን የሁሉም ነገር መንስኤ ዕድል እና አምላክ እንደሆነ ይናገሩ ነበር፤ ኢየሱስ ግን የሰው ልጆች አምላክን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል መምረጥ እንደሚችሉ አስተምሯል።—ማቴ. 11:28

10. ብዙዎች በትምህርታችን የሚሰናከሉት ለምንድን ነው?

10 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ትምህርቶቻችን የሐሰት ትምህርቶችን ስለሚያጋልጡ ብዙዎች ይሰናከሉብናል። ቀሳውስት አምላክ ክፉዎችን በገሃነመ እሳት እንደሚያቃጥል ያስተምራሉ። ይህን የሐሰት ትምህርት፣ ሕዝቡ ሁልጊዜም በእነሱ ቁጥጥር ሥር እንዲሆን ለማድረግ ይጠቀሙበታል። የፍቅር አምላክ የሆነውን ይሖዋን የሚያገለግሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይህ ትምህርት ሐሰት መሆኑን ያጋልጣሉ። ቀሳውስት ነፍስ እንደማትሞትም ያስተምራሉ። እኛ ግን ይህ ትምህርት ምንጩ አረማዊ እንደሆነ እናጋልጣለን፤ ደግሞም ነፍስ የማትሞት ከሆነ ትንሣኤ አስፈላጊ አይሆንም። በተጨማሪም ብዙ ሃይማኖቶች የሰው ዕድል አስቀድሞ የተወሰነ እንደሆነ ያስተምራሉ። እኛ ግን የሰው ልጆች የመምረጥ ነፃነት እንዳላቸውና አምላክን ለማገልገል መምረጥ እንደሚችሉ እናስተምራለን። እንዲህ ስናደርግ የሃይማኖት መሪዎች ምን ይሰማቸዋል? አብዛኛውን ጊዜ በጣም ይበሳጫሉ።

11. ኢየሱስ በዮሐንስ 8:45-47 ላይ በተናገረው መሠረት አምላክ ሕዝቦቹን ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል?

11 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? ለእውነት ፍቅር ካለን የአምላክን ቃል መቀበል አለብን። (ዮሐንስ 8:45-47ን አንብብ።) ከሰይጣን ዲያብሎስ በተለየ መልኩ እኛ በእውነት ውስጥ ጸንተን እንቆማለን። መቼም ቢሆን ከእምነታችን ጋር የሚጋጭ ነገር አናደርግም። (ዮሐ. 8:44) የአምላክ ሕዝቦች፣ ኢየሱስ እንዳደረገው ‘ክፉ የሆነውን እንዲጸየፉ ጥሩ የሆነውን ደግሞ አጥብቀው እንዲይዙ’ ይጠበቅባቸዋል።—ሮም 12:9፤ ዕብ. 1:9

(3) ኢየሱስ ስደት ደርሶበታል

ብዙዎች ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በመሞቱ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (አንቀጽ 12ን ተመልከት) *

12. ኢየሱስ የሞተበት መንገድ በርካታ አይሁዳውያንን ያሰናከላቸው ለምንድን ነው?

12 በኢየሱስ ዘመን የኖሩትን አይሁዳውያን ያሰናከላቸው ሌላው ነገር ምን ነበር? ጳውሎስ “እኛ ግን በእንጨት ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን እንሰብካለን፤ ይህም ለአይሁዳውያን መሰናክል . . . ነው” ብሏል። (1 ቆሮ. 1:23) ኢየሱስ የሞተበት መንገድ በርካታ አይሁዳውያንን ያሰናከላቸው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ ስለሞተ ወንጀለኛና ኃጢአተኛ አድርገው ተመልክተውታል፤ ስለዚህ መሲሕ መሆኑን አልተቀበሉም።—ዘዳ. 21:22, 23

13. በኢየሱስ የተሰናከሉ ሰዎች ምን ሳያስተውሉ ቀርተዋል?

13 በኢየሱስ የተሰናከሉት አይሁዳውያን ኢየሱስ ምንም ወንጀል እንዳልሠራ፣ የተከሰሰው በሐሰት እንደሆነ እንዲሁም የፍትሕ መጓደል እንደተፈጸመበት አላስተዋሉም። በኢየሱስ ላይ ለመፍረድ ሸንጎ የተቀመጡት ሰዎች ስለ ፍትሕ ምንም ግድ አልነበራቸውም። የአይሁዳውያን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተሰየመው በጥድፊያ ነበር፤ የፍርድ ሂደቱም ተገቢውን አካሄድ የተከተለ አልነበረም። (ሉቃስ 22:54፤ ዮሐ. 18:24) ዳኞቹ በኢየሱስ ላይ የተሰነዘረውን ክስና የቀረበውን ማስረጃ ከአድልዎ ነፃ ሆነው ከማዳመጥ ይልቅ እነሱ ራሳቸው “ኢየሱስን ለመግደል በእሱ ላይ የሐሰት የምሥክርነት ቃል እየፈለጉ ነበር።” ይህ አልሳካ ሲላቸው ደግሞ ሊቀ ካህናቱ፣ ኢየሱስ ራሱ ወንጀለኛ አድርጎ ሊያስቆጥረው የሚችል ነገር እንዲናገር ለማድረግ ሞከረ። ይህም ተቀባይነት ካለው የሕግ አሠራር ጋር ፈጽሞ የሚጋጭ አካሄድ ነው። (ማቴ. 26:59፤ ማር. 14:55-64) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም እነዚህ ግፈኛ ዳኞች የኢየሱስን መቃብር ይጠብቁ ለነበሩት ሮማውያን ወታደሮች “በርከት ያሉ የብር ሳንቲሞች” በመስጠት መቃብሩ ባዶ ስለሆነበት ምክንያት የሐሰት ወሬ እንዲያናፍሱ አደረጉ።—ማቴ. 28:11-15

14. ቅዱሳን መጻሕፍት የመሲሑን አሟሟት በተመለከተ ምን ትንቢት ይዘዋል?

14 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? በኢየሱስ ዘመን የነበሩ በርካታ አይሁዳውያን መሲሑ መሞት እንደሚኖርበት ባይገነዘቡም ይህ ጉዳይ በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ አስቀድሞ ተነግሮ ነበር፤ ትንቢቱ እንዲህ ይላል፦ “ሕይወቱን እስከ ሞት ድረስ አፍስሷልና፤ ከሕግ ተላላፊዎችም ጋር ተቆጥሯል፤ የብዙ ሰዎችን ኃጢአት ተሸክሟል፤ ስለ ሕግ ተላላፊዎችም ማልዷል።” (ኢሳ. 53:12) ከዚህ አንጻር ኢየሱስ እንደ ኃጢአተኛ ተቆጥሮ መገደሉ አይሁዳውያንን ሊያሰናክላቸው አይገባም ነበር።

15. አንዳንዶች እንዲሰናከሉ ያደረጓቸው በይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተሰነዘሩት የትኞቹ ክሶች ናቸው?

15 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። ኢየሱስ በሐሰት ተከስሶ ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደተፈረደበት ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮችም ተመሳሳይ ግፍ ደርሶባቸዋል። እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት። በዩናይትድ ስቴትስ በ1930ዎቹ እና በ1940ዎቹ በተደጋጋሚ ፍርድ ቤት ቀርበን ለአምልኮ ነፃነታችን መሟገት አስፈልጎናል። አንዳንድ ዳኞች በእኛ ላይ ዓይን ያወጣ አድልዎ ፈጽመዋል። በኩዊቤክ፣ ካናዳ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት ሥራችንን ለመቃወም እጅና ጓንት ሆነው ሠርተዋል። ብዙ አስፋፊዎች፣ ለጎረቤቶቻቸው ስለ አምላክ መንግሥት በመናገራቸው ብቻ ታስረዋል። ፈሪሃ አምላክ የሌለው የጀርመኑ የናዚ አገዛዝ በርካታ ታማኝ ወጣት ወንድሞችን አስገድሏል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በሩሲያ የሚኖሩ በርካታ ወንድሞቻችን ስለ መጽሐፍ ቅዱስ በመወያየታቸው ምክንያት “በጽንፈኝነት እንቅስቃሴ ተካፍለዋል” በሚል ክስ ተፈርዶባቸው ታስረዋል። በሩሲያኛ የተዘጋጀው አዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ እንኳ ይሖዋ የሚለውን ስም በመጠቀሙ ምክንያት “ከጽንፈኛ መጻሕፍት” ተርታ ተፈርጆ ታግዷል።

16. አንደኛ ዮሐንስ 4:1 እንደሚናገረው ስለ ይሖዋ ሕዝቦች የሚነገሩ የሐሰት ወሬዎች ሊያታልሉን የማይገባው ለምንድን ነው?

16 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? እውነታውን አጣሩ። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ ለአድማጮቹ አንዳንዶች “ክፉውን ሁሉ በውሸት [እንደሚያስወሩባቸው]” ነግሯቸው ነበር። (ማቴ. 5:11) የእነዚህ ውሸቶች ምንጭ ሰይጣን ነው። ሰይጣን፣ ተቃዋሚዎች እውነትን የሚወዱ ሰዎችን ስም እንዲያጠፉ ያነሳሳቸዋል። (ራእይ 12:9, 10) ተቃዋሚዎቻችን የሚናገሩት ውሸት ሊያሳስበን አይገባም። እንዲህ ያሉ ውሸቶች እንዲያሸብሩን ወይም እምነታችንን እንዲያዳክሙት ፈጽሞ ልንፈቅድ አይገባም።—1 ዮሐንስ 4:1ን አንብብ።

(4) ኢየሱስ ክህደት ተፈጽሞበታል፤ ሐዋርያቱም ትተውት ሄደዋል

ብዙዎች ኢየሱስ በይሁዳ በመከዳቱ ተሰናክለዋል። ይኸው ነገር በዛሬው ጊዜ አንዳንዶችን ሊያሰናክል የሚችለው እንዴት ነው? (ከአንቀጽ 17-18ን ተመልከት) *

17. አንዳንዶች ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት የተከናወኑት የትኞቹ ነገሮች ሊያሰናክሏቸው ይችሉ ነበር?

17 ኢየሱስ ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ ከ12 ሐዋርያቱ አንዱ ከድቶታል። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ደግሞ ሌላኛው ሐዋርያ ኢየሱስን ሦስት ጊዜ ክዶታል፤ እንዲሁም ሁሉም ሐዋርያት ጥለውት ሸሽተዋል። (ማቴ. 26:14-16, 47, 56, 75) ኢየሱስ በዚህ አልተገረመም፤ እንዲያውም ይህ እንደሚያጋጥመው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ዮሐ. 6:64፤ 13:21, 26, 38፤ 16:32) አንዳንዶች ግን ይህን ሲመለከቱ ‘የኢየሱስ ሐዋርያት እንዲህ ካደረጉ እኔ ከእነሱ ጋር መቆጠር አልፈልግም’ በማለት ሊሰናከሉ ይችሉ ነበር።

18. ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ጊዜ ላይ የትኞቹ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል?

18 ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ይሖዋ፣ መሲሑ ‘በ30 የብር ሰቅል’ አልፎ እንደሚሰጥ ከዘመናት በፊት በቃሉ ውስጥ አስነግሮ ነበር። (ዘካ. 11:12, 13) ኢየሱስን የሚከዳው ከቅርብ ወዳጆቹ አንዱ እንደሚሆንም ተገልጿል። (መዝ. 41:9) በተጨማሪም ነቢዩ ዘካርያስ “እረኛውን ምታ፤ መንጋውም ይበተን” በማለት ጽፎ ነበር። (ዘካ. 13:7) ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በእነዚህ ክስተቶች ከመሰናከል ይልቅ ትንቢቶቹ በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን በማግኘታቸው እምነታቸው ሊጠናከር ይገባ ነበር።

19. ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ምን ይገነዘባሉ?

19 በዛሬው ጊዜስ ተመሳሳይ ችግር አለ? አዎ። በዘመናችን አንዳንድ የታወቁ የይሖዋ ምሥክሮች እውነትን ትተው በመውጣት ከሃዲዎች ሆነዋል፤ ከዚያም ሌሎችን ከእውነት ለማራቅ ሞክረዋል። እነዚህ ሰዎች በዜና ማሰራጫዎችና በኢንተርኔት አማካኝነት ስለ ይሖዋ ምሥክሮች አሉታዊ ዘገባ፣ ከፊል እውነትነት ያለው ወሬ ይባስ ብሎም ዓይን ያወጣ ውሸት አሰራጭተዋል። ያም ሆኖ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በዚህ አይሰናከሉም። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያሉ ነገሮች እንደሚፈጸሙ አስቀድሞ እንደተናገረ ያውቃሉ።—ማቴ. 24:24፤ 2 ጴጥ. 2:18-22

20. እውነትን በተዉ ሰዎች ላለመሰናከል ምን ይረዳናል? (2 ጢሞቴዎስ 4:4, 5)

20 እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? አዘውትረን በማጥናት፣ ሳናሰልስ በመጸለይና ይሖዋ በሰጠን ሥራ በመጠመድ ጠንካራ እምነት ይዘን መቀጠል ይኖርብናል። (2 ጢሞቴዎስ 4:4, 5ን አንብብ።) ጠንካራ እምነት ካለን አሉታዊ ዘገባዎችን ስንሰማ አንደናገጥም። (ኢሳ. 28:16) ለይሖዋ፣ ለቃሉ እንዲሁም ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅር እውነትን በተዉ ሰዎች እንዳንሰናከል ይረዳናል።

21. በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች መልእክታችንን ባይቀበሉም እንኳ ስለ ምን ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

21 በመጀመሪያው መቶ ዘመን ብዙዎች በኢየሱስ ተሰናክለው እሱን ሳይቀበሉት ቀርተዋል። በሌላ በኩል ግን ሌሎች ብዙ ሰዎች ተቀብለውታል። ከእነዚህ መካከል ቢያንስ አንድ የሳንሄድሪን ሸንጎ አባል እንዲሁም “ብዙ ካህናት” ይገኙበታል። (ሥራ 6:7፤ ማቴ. 27:57-60፤ ማር. 15:43) በዛሬው ጊዜም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች አልተሰናከሉም። ለምን? በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ያሉትን እውነቶች ስለሚያውቁና ስለሚወዷቸው ነው። የአምላክ ቃል “ሕግህን የሚወዱ ብዙ ሰላም አላቸው፤ ሊያደናቅፋቸው የሚችል ምንም ነገር የለም” ይላል።—መዝ. 119:165

መዝሙር 124 ምንጊዜም ታማኝ መሆን

^ አን.5 ባለፈው ርዕስ ላይ በጥንት ዘመን የነበሩ ሰዎች ኢየሱስን እንዳይቀበሉ ያደረጓቸውን እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች የማይቀበሉባቸውን አራት ምክንያቶች ተመልክተናል። በዚህ ርዕስ ላይ ደግሞ አራት ተጨማሪ ምክንያቶችን እንመረምራለን። ከዚህም ሌላ ይሖዋን የሚወዱ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ማንኛውም ነገር እንዲያሰናክላቸው የማይፈቅዱት ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

^ አን.60 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ከማቴዎስ እና ከቀረጥ ሰብሳቢዎች ጋር ሲመገብ።

^ አን.62 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ ነጋዴዎቹን ከቤተ መቅደሱ ሲያባርር።

^ አን.64 የሥዕሉ መግለጫ፦ ኢየሱስ የመከራ እንጨቱን ሲሸከም።

^ አን.66 የሥዕሉ መግለጫ፦ ይሁዳ ኢየሱስን በመሳም አሳልፎ ሲሰጠው።