በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ዛሬም የሚሠራ ጥንታዊ ጥበብ

አትጨነቁ

አትጨነቁ

የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያ፦ “ስለ ሕይወታችሁ . . . አትጨነቁ።”—ማቴዎስ 6:25

ይህ ምን ማለት ነው? ኢየሱስ ይህን ሐሳብ የተናገረው በተራራው ስብከት ላይ ነው። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት እንደገለጸው ከሆነ በዚህ ጥቅስ ላይ ‘ጭንቀት’ ተብሎ የተተረጎመው ግሪከኛ ቃል “አንድ ሰው ድህነት፣ ረሃብ ወይም ሌሎች ችግሮች በሕይወቱ ውስጥ ሲያጋጥሙት የሚኖረውን የተለመደ ስሜት” ሊያመለክት ይችላል። ብዙውን ጊዜ የሚያስጨንቁን ወደፊት ይሆናሉ ብለን የምናስባቸው ነገሮች ናቸው። ስለሚያስፈልጉን ቁሳዊ ነገሮችም ሆነ ስለ ቤተሰባችን ደኅንነት ማሰባችን ተገቢና ተፈጥሯዊ ነው። (ፊልጵስዩስ 2:20) ሆኖም ኢየሱስ “ፈጽሞ አትጨነቁ” ብሎ ለተከታዮቹ ምክር ሲሰጣቸው አላስፈላጊ ጭንቀትን እንዲያስወግዱ እየነገራቸው ነበር፤ እንዲህ ዓይነቱ ጭንቀት ደግሞ ነገ ስለሚሆነው ነገር በመስጋት የዛሬውን ደስታችንን እንድናጣ ሊያደርገን ይችላል።—ማቴዎስ 6:31, 34

ይህ ምክር ዛሬም ይሠራል? የኢየሱስን ምክር መከተል ብልህነት ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንዳንድ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች በጣም ሲጨነቁ ሲምፐታቲክ የተባለው የነርቭ ሥርዓት ያለማቋረጥ ሥራ ላይ ይሆናል፤ ይህም “በውስጥ አካል ላይ ለሚፈጠር ቁስለት፣ ለልብ በሽታ፣ ለአስም እና ለሌሎች የጤና ችግሮች” ሊያጋልጥ ይችላል።

ኢየሱስ ከመጠን በላይ መጨነቅ የሌለብን ለምን እንደሆነ ተናግሯል፦ እንዲህ ማድረግ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። ኢየሱስ “ከእናንተ መካከል ተጨንቆ በዕድሜው ርዝማኔ ላይ አንድ ክንድ መጨመር የሚችል ይኖራል?” በማለት ጠይቋል። (ማቴዎስ 6:27) ጭንቀት በሕይወታችን ላይ ለውጥ ሊያመጣ ቀርቶ በዕድሜያችን ላይ አንድ ሴኮንድ እንኳ ሊጨምር አይችልም። በዚያ ላይ ደግሞ ነገሮች እኛ እንደፈራነው ላይሆኑ ይችላሉ። አንድ ምሁር ሁኔታውን እንዲህ በማለት ገልጸውታል፦ “ስለ ወደፊቱ ጊዜ እያሰቡ መጨነቅ ከንቱ ልፋት ነው፤ ምክንያቱም ወደፊት የሚያጋጥመን ነገር ብዙውን ጊዜ የፈራነውን ያህል የከፋ ላይሆን ይችላል።”

ታዲያ ጭንቀትን ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ በአምላክ እንታመን። አምላክ ወፎችን የሚመግባቸው፣ አበቦችን ደግሞ የሚያለብሳቸው ከሆነ በሕይወታቸው ውስጥ እሱን ለማገልገል ቅድሚያ ለሚሰጡ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን ነገር አይሰጣቸውም? (ማቴዎስ 6:25, 26, 28-30) ሁለተኛ፣ ስለ ወደፊቱ አንጨነቅ። ኢየሱስ “ስለ ነገ ፈጽሞ አትጨነቁ፤ ምክንያቱም ነገ የራሱ የሆኑ የሚያስጨንቁ ነገሮች አሉት” በማለት ተናግሯል። “እያንዳንዱ ቀን የራሱ የሆነ በቂ ችግር አለው” ቢባል አትስማማም?—ማቴዎስ 6:34

ኢየሱስ የሰጠውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጤንነታችንን መጠበቅ እንችላለን። ከሁሉም በላይ መጽሐፍ ቅዱስ “የአምላክ ሰላም” ብሎ የሚጠራው ዓይነት ውስጣዊ መረጋጋት ይኖረናል።—ፊልጵስዩስ 4:6, 7