በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ከእናንተ ጋር እንሄዳለን”

“ከእናንተ ጋር እንሄዳለን”

“አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን።”—ዘካ. 8:23

መዝሙሮች፦ 65, 122

1, 2. (ሀ) ይሖዋ በዘመናችን ምን እንደሚከናወን ተናግሯል? (ለ) በዚህ ርዕስ ሥር ለየትኞቹ ጥያቄዎች መልስ እናገኛለን? (በመግቢያው ላይ ያለውን ሥዕል ተመልከት።)

ይሖዋ የምንኖርበትን ዘመን አስመልክቶ የሚከተለውን ትንቢት ተናግሯል፦ “በዚያን ጊዜ ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ አሥር ሰዎች የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” (ዘካ. 8:23) በዚህ ምሳሌያዊ አገላለጽ ላይ እንደተጠቀሱት አሥር ሰዎች ሁሉ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም “የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው” ይዘዋል። ይሖዋ ቅቡዓኑን እየባረካቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ በመንፈስ ከተቀቡት ‘የአምላክ እስራኤል’ አባላት ጋር መተባበራቸው ያኮራቸዋል።—ገላ. 6:16

2 እንደ ነቢዩ ዘካርያስ ሁሉ ኢየሱስም በአምላክ ሕዝቦች መካከል የሚኖረውን አስደሳች አንድነት አጉልቷል። ተከታዮቹ “ትንሽ መንጋ” እና “ሌሎች በጎች” ተብለው በሁለት ቡድኖች እንደሚከፈሉ ገልጿል፤ ያም ቢሆን ሁለቱም ‘በአንድ እረኛ’ የሚመሩ “አንድ መንጋ” እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:32፤ ዮሐ. 10:16) ይሁንና እነዚህ ሁለት ቡድኖች ሊኖራቸው ስለሚገባው ግንኙነት አንዳንድ ጥያቄዎች ይነሳሉ፦ (1) የሌሎች በጎች አባላት በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የሁሉንም ቅቡዓን ስም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? (2) ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል? (3) በጉባኤህ ያለ አንድ ሰው በመታሰቢያው በዓል ላይ ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ ቢጀምር ምን ይሰማሃል? (4) ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ቁጥር መጨመሩ ሊያሳስብህ ይገባል? እስቲ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንመልከት።

በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የሁሉንም ቅቡዓን ስም ማወቅ ያስፈልገናል?

3. የ144,000ዎቹ አባል የሚሆኑትን በእርግጠኝነት ማወቅ የማንችለው ለምንድን ነው?

3 የሌሎች በጎች አባላት በዛሬው ጊዜ የሚገኙትን የሁሉንም ቅቡዓን ስም ማወቅ ያስፈልጋቸዋል? አያስፈልጋቸውም። ለምን? ምክንያቱም አንድ ሰው ሰማያዊ ጥሪ ቢያገኝ እንኳ ግለሰቡ የተቀበለው ግብዣ እንጂ ሽልማቱን እንደሚያገኝ የሚያሳይ የመጨረሻ ማረጋገጫ አይደለም። ሰይጣን ‘ቢቻላቸው የተመረጡትን እንኳ እንዲያስቱ ሐሰተኛ ነቢያትን የሚያስነሳው’ ለዚህ ነው። (ማቴ. 24:24) አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ ሰማያዊ ሽልማት ማግኘት ይገባው እንደሆነ ይሖዋ እስኪወስን ድረስ ግለሰቡ ይህን ሽልማት ማግኘቱን ማንም ሰው ማወቅ አይችልም። ይሖዋ ይህን ውሳኔ የሚያስተላልፈውና የመጨረሻውን ማኅተም የሚያደርግበት፣ ግለሰቡ በታማኝነት ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ አሊያም ‘ታላቁ መከራ’ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ነው። (ራእይ 2:10፤ 7:3, 14) እንግዲያው በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያለ ማንኛውም ሰው ከአምላክ አገልጋዮች መካከል የ144,000ዎቹ አባል የሚሆኑትን በእርግጠኝነት ለማወቅ መሞከሩ ምንም ትርጉም የለውም። [1]

4. በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን የሁሉንም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ስም ማወቅ የማይቻል ከሆነ ከእነሱ ጋር ‘መሄድ’ የምንችለው እንዴት ነው?

4 ታዲያ የሌሎች በጎች አባላት በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉትን የሁሉንም የመንፈሳዊ እስራኤል አባላት ስም ማወቅ የማይችሉ ከሆነ ከእነሱ ጋር ‘መሄድ’ የሚችሉት እንዴት ነው? በዘካርያስ ላይ የሚገኘው ትንቢት ምሳሌያዊዎቹን አሥር ሰዎች በተመለከተ ምን እንደሚል ልብ በል። እነዚህ ሰዎች “የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ ‘አምላክ ከእናንተ ጋር መሆኑን ስለሰማን ከእናንተ ጋር እንሄዳለን’ ይላሉ።” እዚህ ላይ የተጠቀሰው አይሁዳዊ አንድ ብቻ ቢሆንም “እናንተ” ከሚለው ተውላጠ ስም ማየት እንደሚቻለው ሐሳቡ የሚያመለክተው ብዙ ሰዎችን ነው። እንግዲያው እዚህ ላይ የተገለጸው አይሁዳዊ አንድን ሰው ሳይሆን አንድን ቡድን የሚያመለክት ነው! በመሆኑም አይሁዳዊ ተብለው የተገለጹትን ቅቡዓን በግለሰብ ደረጃ አውቀን ከእያንዳንዳቸው ጋር መሄድ አያስፈልገንም። ከዚህ ይልቅ እነዚህን ሰዎች ያቀፈውን ቡድን ለይተን ማወቅና መደገፍ ይኖርብናል። ቅዱሳን መጻሕፍት አንድን ግለሰብ እንድንከተል ፈጽሞ አያበረታቱንም። ምክንያቱም መሪያችን ኢየሱስ ነው።—ማቴ. 23:10

ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ምን አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

5. ቅቡዓን ክርስቲያኖች የትኛውን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል? ለምንስ?

5 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሁሉ በ1 ቆሮንቶስ 11:27-29 ላይ የሚገኘውን ማስጠንቀቂያ በቁም ነገር ሊያስቡበት ይገባል። (ጥቅሱን አንብብ።) እዚህ ላይ ሐዋርያው ጳውሎስ ሊያጎላው የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን ከይሖዋ ጋር ያለውን ጥሩ ግንኙነት ጠብቆ ካልተመላለሰ ከቂጣው የሚበላውና ከጽዋው የሚጠጣው ሳይገባው ይሆናል። (ዕብ. 6:4-6፤ 10:26-29) እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሽልማታቸውን ገና እንዳላገኙ እንዲያስታውሱ ያደርጋል። “አምላክ በክርስቶስ ኢየሱስ በኩል የሚሰጠውን የሰማያዊውን ሕይወት ሽልማት” ያገኙ ዘንድ ግባቸው ላይ ለመድረስ ጥረት ማድረጋቸውን መቀጠል አለባቸው።—ፊልጵ. 3:13-16

6. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ስለ ራሳቸው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖራቸው ይገባል?

6 ጳውሎስ ለቅቡዓን ክርስቲያኖች “ከተጠራችሁበት ጥሪ ጋር በሚስማማ ሁኔታ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፎላቸዋል። ይህን የሚያደርጉት እንዴት ነው? ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በፍጹም ትሕትናና ገርነት፣ በትዕግሥት እንዲሁም እርስ በርሳችሁ በፍቅር በመቻቻል ኑሩ፤ አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።” (ኤፌ. 4:1-3) የይሖዋ መንፈስ ኩራትን ሳይሆን ትሕትናን ማዳበርን ያበረታታል። (ቆላ. 3:12) ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ምድራዊ ተስፋ ካላቸው የበለጠ መንፈስ ቅዱስ እንዳልተቀበሉ በመገንዘብ ትሕትና ያሳያሉ። ልዩ እውቀት እንዳላቸው ወይም ራእይ እንደሚገለጥላቸው አይናገሩም፤ አሊያም በሆነ መንገድ ከሌሎች እንደሚበልጡ ለማሳየት አይሞክሩም። ከዚህም በተጨማሪ ለማንም ሰው፣ በመንፈስ እንደተቀባና ከምሳሌያዊው ቂጣና የወይን ጠጅ መውሰድ እንደሚገባው የሚገልጽ ሐሳብ ፈጽሞ አይሰነዝሩም፤ ከዚህ ይልቅ ቅቡዓንን የሚጠራው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና አምነው ይቀበላሉ።

7, 8. ቅቡዓን ክርስቲያኖች ምን እንዲደረግላቸው አይጠብቁም? ለምንስ?

7 ሰማያዊ ጥሪ ማግኘት ታላቅ መብት ቢሆንም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሌሎች የተለየ ክብር እንዲሰጧቸው አይጠብቁም። (ኤፌ. 1:18, 19፤ ፊልጵስዩስ 2:2, 3ን አንብብ።) የይሖዋ መንፈስ የመሠከረላቸው በግለሰብ ደረጃ ነው። ለሌሎች ሰዎች የተነገረ ማስታወቂያ የለም። በመሆኑም አንድ ቅቡዕ ክርስቲያን፣ በእርግጥ በመንፈስ ቅዱስ መቀባቱን አንዳንዶች ቢጠራጠሩ ሊገረም አይገባም። እንዲያውም ቅዱሳን መጻሕፍት፣ ከአምላክ ልዩ ሹመት እንዳገኘ የሚናገርን ሰው ቶሎ ማመንን እንደማያበረታቱ ቅቡዓኑ ይገነዘባሉ። (ራእይ 2:2) በመሆኑም ከሌሎች ጋር ሲተዋወቁ ቅቡዕ መሆናቸውን አይናገሩም። ወደ ራሳቸው ትኩረት መሳብ ስለማይፈልጉ ይህን ጥሪ ማግኘታቸውን አብዛኛውን ጊዜ ለሌሎች አይገልጹም፤ ወደፊት ስለሚያገኙት ሽልማት እያነሱም አይኩራሩም።—1 ቆሮ. 1:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 4:6-8ን አንብብ።

8 ከዚህም በተጨማሪ ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ልዩ ቦታ የሚሰጠው ቡድን አባላት እንደሆኑ አድርገው አያስቡም። ሰማያዊ ጥሪ እንዳላቸው የሚናገሩ ሌሎች ክርስቲያኖችን በመፈለግ ከእነሱ ጋር ለመቀራረብ ወይም የራሳቸውን ቡድኖች አቋቁመው መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ጥረት አያደርጉም። (ገላ. 1:15-17) እንዲህ ማድረግ በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል የሚፈጥር ከመሆኑም ሌላ ሰላምና አንድነት እንዲኖር ከሚያደርገው የመንፈስ ቅዱስ አሠራር ጋር ይጋጫል።—ሮም 16:17, 18ን አንብብ።

ለቅቡዓኑ ምን አመለካከት ሊኖርህ ይገባል?

9. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስድ ሰው ባለህ አመለካከት ረገድ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብህ ለምንድን ነው? (“ ፍቅር ‘ጨዋነት የጎደለው ምግባር አያሳይም’” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።)

9 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስድ ሰው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ “ሁላችሁም ወንድማማቾች ናችሁ” ብሏቸዋል። አክሎም “ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ዝቅ ይደረጋል፤ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ሁሉ ደግሞ ከፍ ይደረጋል” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 23:8-12) በመሆኑም አንድ ሰው የክርስቶስ ቅቡዕ ወንድም ቢሆንም እንኳ ለዚህ ግለሰብ ልዩ አክብሮት መስጠት ስህተት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አመራር የሚሰጡትን ክርስቲያን ሽማግሌዎች በእምነታቸው እንድንመስላቸው ያበረታታናል፤ ይሁንና ማንኛውንም ሰው እንደ መሪያችን በማየት ከፍ ከፍ እንድናደርግ ጨርሶ አያዘንም። (ዕብ. 13:7) እውነት ነው፣ ቅዱሳን መጻሕፍት አንዳንዶች “እጥፍ ክብር ሊሰጣቸው” እንደሚገባ ይናገራሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ክብር ሊሰጣቸው የሚገባው ግን ቅቡዓን ስለሆኑ ሳይሆን “በመልካም ሁኔታ የሚያስተዳድሩ” እንዲሁም “በመናገርና በማስተማር ተግተው የሚሠሩ” በመሆናቸው ነው። (1 ጢሞ. 5:17) ሰማያዊ ጥሪ ያላቸው ክርስቲያኖች፣ ሌሎች አላስፈላጊ አድናቆት ወይም ትኩረት የሚሰጧቸው ከሆነ ይጨንቃቸዋል። ከዚህ የባሰው ደግሞ እንዲህ ያለው ለየት ያለ ትኩረት፣ ትሑት መሆን እንዲከብዳቸው ሊያደርግ ይችላል። (ሮም 12:3) ማናችንም ብንሆን ለክርስቶስ ወንድሞች ማሰናከያ መሆን አንፈልግም!—ሉቃስ 17:2

በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ለሚወስድ ሰው ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖርህ ይገባል? (ከአንቀጽ 9-11 ተመልከት)

10. ለተቀቡ ክርስቲያኖች አክብሮት ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው?

10 ታዲያ ይሖዋ በመንፈስ ለሚቀባቸው ሰዎች ተገቢውን አክብሮት ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከመቀባታቸው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ልንጠይቃቸው አይገባም። በዚህ መንገድ በማይመለከተን ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንቆጠባለን። (1 ተሰ. 4:11፤ 2 ተሰ. 3:11) በመንፈስ የተቀባው ግለሰብ ወላጆች፣ የትዳር ጓደኛ ወይም ሌሎች ዘመዶችም ቅቡዕ እንደሚሆኑ አድርገን ልናስብ አይገባም። በመንፈስ መቀባት በዝምድና ወይም በጋብቻ የሚገኝ ነገር አይደለም። (1 ተሰ. 2:12) ከዚህም ሌላ የቅቡዓን የትዳር ጓደኛ የሆኑ ክርስቲያኖች፣ ወደፊት ምድር ገነት ስትሆን ከትዳር ጓደኛቸው ጋር እንደማይኖሩ ሲያስቡ ምን እንደሚሰማቸው ልንጠይቃቸው አይገባም። ሌሎች እንዲያዝኑ ሊያደርጉ የሚችሉ ጥያቄዎች ከማንሳት ይልቅ ይሖዋ እጁን እንደሚዘረጋና “የሕያዋን ፍጥረታትንም ሁሉ ፍላጎት” እንደሚያሟላ ሁላችንም ሙሉ በሙሉ መተማመን እንችላለን።—መዝ. 145:16

11. ‘ሌሎችን ከመካብ’ መቆጠባችን ጥበቃ የሚሆንልን እንዴት ነው?

11 ለቅቡዓን ተገቢው አመለካከት ያላቸው ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከአደጋ ይጠብቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ሐሰተኛ ወንድሞች” ወደ ጉባኤው ሾልከው ሊገቡ እንደሚችሉ ይናገራል። (ገላ. 2:4, 5፤ 1 ዮሐ. 2:19) እነዚህ አስመሳይ ሰዎች ቅቡዓን እንደሆኑ እስከመናገር እንኳ ይደርሱ ይሆናል። ከዚህም ሌላ አንዳንድ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከእምነት ጎዳና ይወጡ ይሆናል። (ማቴ. 25:10-12፤ 2 ጴጥ. 2:20, 21) ‘ሌሎችን ከመካብ’ የምንቆጠብ ከሆነ እንዲህ ባሉ አታላዮች ተስበን ከእውነት አንወጣም፤ እንዲሁም ኃላፊነት ያለው ወይም ለረጅም ጊዜ ይሖዋን ያገለገለ ክርስቲያን ታማኝነቱን ቢያጓድል እምነታችን አይናወጥም።—ይሁዳ 16

በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ቁጥር ሊያሳስበን ይገባል?

12, 13. በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚካፈሉት ሰዎች ቁጥር ሊያሳስበን የማይገባው ለምንድን ነው?

12 በክርስቶስ ሞት መታሰቢያ በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት እየቀነሰ ሲሄድ ተመልክተናል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ይህ ቁጥር እየጨመረ ነው። ታዲያ ቁጥሩ መጨመሩ ሊያሳስበን ይገባል? አይገባም። በዚህ ረገድ በአእምሯችን ልንይዛቸው የሚገቡ አንዳንድ ነጥቦችን ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን።

13 “ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።” (2 ጢሞ. 2:19) በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎችን የሚቆጥሩት ወንድሞች፣ በእርግጥ ሰማያዊ ተስፋ ያለው ማን እንደሆነ ማወቅ አይችሉም። ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱት ሰዎች ቁጥር፣ ቅቡዓን ነን ብለው በስህተት የሚያስቡ ሰዎችንም ይጨምራል። በአንድ ወቅት ከቂጣውና ከወይን ጠጁ ይወስዱ የነበሩ አንዳንዶች ከጊዜ በኋላ አቁመዋል። ሌሎች ደግሞ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ እንደሚገዙ አድርገው የሚያስቡት ከአእምሮ ወይም ከስሜት ጋር የተያያዘ ችግር ስላለባቸው ሊሆን ይችላል። ስለሆነም በመታሰቢያው በዓል ላይ ከቂጣውና ከወይን ጠጁ የሚወስዱ ሰዎች ቁጥር፣ በምድር ላይ የቀሩትን ቅቡዓን ትክክለኛ ቁጥር አያመለክትም።

14. ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር የሚኖሩትን ቅቡዓን ቁጥር በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይጠቁማል?

14 ኢየሱስ ቅቡዓኑን ወደ ሰማይ ለመሰብሰብ በሚመጣበት ጊዜ በብዙ የዓለም ክፍሎች ቅቡዓን ይኖራሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ያን ጊዜ በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “[ኢየሱስ] መላእክቱን በታላቅ የመለከት ድምፅ ይልካል፤ እነሱም ከአራቱ ነፋሳት፣ ከአንዱ የሰማይ ዳርቻ እስከ ሌላው የሰማይ ዳርቻ ለእሱ የተመረጡትን ይሰበስባሉ።” (ማቴ. 24:31) በመጨረሻዎቹ ቀናት ከቅቡዓን መካከል በምድር ላይ የሚኖሩት ጥቂት ቀሪዎች ብቻ እንደሚሆኑ ቅዱሳን መጻሕፍት ይናገራሉ። (ራእይ 12:17) ይሁንና ታላቁ መከራ ሲጀምር በምድር ላይ ምን ያህል ቅቡዓን እንደሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ነገር የለም።

15, 16. ይሖዋ የመረጣቸውን 144,000ዎች በተመለከተ ምን ነገር ልንገነዘብ ይገባል?

15 ቅቡዓንን የሚመርጥበትን ዘመን የሚወስነው ይሖዋ ነው። (ሮም 8:28-30) ይሖዋ ቅቡዓንን መምረጥ የጀመረው ኢየሱስ ሞቶ ከተነሳ በኋላ ነው፤ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላት በሙሉ ቅቡዓን ሳይሆኑ አይቀሩም። ከመጀመሪያው መቶ ዘመን በኋላ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት መባቻ ባለው ጊዜ ውስጥ፣ የክርስቶስ ተከታዮች ነን ይሉ የነበሩት አብዛኞቹ ሰዎች ሐሰተኛ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ ኢየሱስ እነዚህን ሰዎች ‘ከእንክርዳድ’ ጋር አመሳስሏቸዋል። ያም ሆኖ ይሖዋ በዚያ ጊዜ ውስጥ ታማኝ የሆኑ አንዳንዶችን መቀባቱን የቀጠለ ሲሆን እነዚህ ሰዎች ኢየሱስ እንደጠቀሰው “ስንዴ” ሆነው ተገኝተዋል። (ማቴ. 13:24-30) በመጨረሻዎቹ ቀናትም ይሖዋ የ144,000ዎቹን አባላት መቀባቱን ቀጥሏል። [2] ይሖዋ ለዚህ መብት ብቁ የሚሆኑ አንዳንድ ሰዎችን ለመምረጥ እስከ መጨረሻዎቹ ቀናት መገባደጃ ለመቆየት ከፈለገ በእሱ ጥበብ ላይ ጥያቄ ለማንሳት እኛ ማን ነን? (ኢሳ. 45:9፤ ዳን. 4:35፤ ሮም 9:11, 16ን አንብብ።) [3] በ11ኛው ሰዓት ለተቀጠሩት ሠራተኞች ጌታው ባደረገው ነገር ቅር ተሰኝተው እንዳጉረመረሙት ሰዎች እንዳንሆን መጠንቀቅ አለብን።ማቴዎስ 20:8-15ን አንብብ።

16 ሰማያዊ ጥሪ ካላቸው መካከል ‘የታማኝና ልባም ባሪያ’ ክፍል የሆኑት ሁሉም አይደሉም። (ማቴ. 24:45-47) እንደ መጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉ በዛሬው ጊዜም ይሖዋና ኢየሱስ በጥቂቶች ተጠቅመው ብዙኃኑን እየመገቡ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማስጻፍ የተጠቀመው በጥቂት ቅቡዓን ነው። ዛሬም በተመሳሳይ “በተገቢው ጊዜ” መንፈሳዊ ምግብ እንዲያቀርቡ የተሾሙት ጥቂት ቅቡዓን ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው።

17. በዚህ ርዕስ ላይ ምን ትምህርት አግኝተናል?

17 ከዚህ ጥናት ምን ትምህርት አግኝተናል? ይሖዋ ሁለት ዓይነት ሽልማቶችን ይኸውም ‘በአይሁዳዊ’ ለተመሰሉት አገልጋዮቹ በሰማይ፣ ‘በአሥር ሰዎች’ ለተመሰሉት አገልጋዮቹ ደግሞ በምድር ላይ ሕይወት አዘጋጅቶላቸዋል። ሰማያዊ ጥሪ ያላቸውንም ሆነ ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን አገልጋዮቹን ታማኝ በመሆን ረገድ ተመሳሳይ መሥፈርት እንዲያሟሉ ይጠብቅባቸዋል። ሁለቱም ቡድኖች ምንጊዜም ትሑት መሆን አለባቸው። እንዲሁም አንድነት ሊኖራቸው ይገባል። ሁለቱም ቡድኖች በጉባኤ ውስጥ ሰላም እንዲኖር ጥረት ማድረግ አለባቸው። የመጨረሻዎቹ ቀናት ወደመገባደጃቸው እየተቃረቡ ሲሄዱ ሁላችንም በክርስቶስ ሥር አንድ መንጋ ሆነን ለማገልገል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።

^ [1] (አንቀጽ 3) በሰማይ ከኢየሱስ ጋር የሚገዙት የሁሉም ቅቡዓን ስም ወደፊት ሊገለጥ እንደሚችል መዝሙር 87:5, 6 ይጠቁማል።—ሮም 8:19

^ [2] (አንቀጽ 15) የሐዋርያት ሥራ 2:33 ቅቡዓኑን በመምረጡ ሥራ ኢየሱስ እንደሚካፈል ቢጠቁምም ጥሪውን የሚያቀርበው ይሖዋ ነው።

^ [3] (አንቀጽ 15) ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የግንቦት 1, 2007 መጠበቂያ ግንብ ከገጽ 30-31 ላይ የወጣውን “የአንባቢያን ጥያቄዎች” ተመልከት።